የአምላክ ቃል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል
“የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”—ኢሳይያስ 40:8
1. (ሀ) እዚህ ላይ “የአምላካችን ቃል” የተባለው ምንድን ነው? (ለ) ሰዎች የሚሰጧቸው ተስፋዎችና የአምላክ ቃል እንዴት ይነፃፀራሉ?
የሰው ልጆች ስመ ጥር ወንዶችና ሴቶች በሚሰጡት ተስፋ ላይ መታመን ይቀናቸዋል። ይሁን እንጂ እነዚህን ተስፋዎች ሕይወታቸው ተሻሽሎ ለማየት የሚናፍቁ ሰዎች የቱንም ያህል እንደ ውድ ነገር አድርገው ቢመለከቷቸው ከአምላክ ቃል ጋር ሲነጻጸሩ እንደሚረግፉ አበባዎች ናቸው። (መዝሙር 146:3, 4) ይሖዋ አምላክ ከ2,700 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ እንደሚከተለው ሲል እንዲጽፍ በመንፈሱ አነሳስቶታል:- “ሥጋ ለባሽ ሁሉ ሣር ነው፣ ክብሩም ሁሉ እንደ ምድረ በዳ አበባ ነው። . . . ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።” (ኢሳይያስ 40:6, 8) ይህ ጸንቶ የሚኖረው “ቃል” ምንድን ነው? አምላክ ዓላማውን አስመልክቶ የተናገረው ቃል ነው። ዛሬ ይህ “ቃል” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጽሑፍ ሰፍሮ እናገኘዋለን።—1 ጴጥሮስ 1:24, 25
2. ይሖዋ የጥንቷን እስራኤልና ይሁዳን በተመለከተ የተናገረውን ቃል የፈጸመው ምን ዓይነት ሁኔታዎችና ድርጊቶች እያሉ ነበር?
2 በጥንቷ እስራኤል ዘመን ይኖሩ የነበሩት ሰዎች ኢሳይያስ የተናገራቸውን ቃላት እውነተኛነት ተመልክተዋል። ይሖዋ በእርሱ ላይ በፈጸሙት ዓይን ያወጣ ክህደት ምክንያት በመጀመሪያ የአሥሩ ነገድ የእስራኤል መንግሥት ከዚያም የሁለቱ ነገድ የይሁዳ መንግሥት በምርኮ እንደሚወሰዱ በነቢያቱ አማካኝነት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ኤርምያስ 20:4፤ አሞጽ 5:2, 27) የይሖዋን ነቢያት ቢያሳድዱና ቢገድሉም፣ እንዲሁም የአምላክን የማስጠንቀቂያ መልእክት የያዙትን ጥቅልሎች በእሳት ቢያቃጥሉና ትንቢቱ እንዳይፈጸም ለማድረግ ግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ እንድትሰጣቸው ቢማጸኑም የይሖዋ ትንቢት መፈጸሙ አልቀረም። (ኤርምያስ 36:1, 2, 21-24፤ 37:5-10፤ ሉቃስ 13:34) ከዚህም ሌላ አምላክ ንስሐ የገቡትን አይሁዳውያን ቀሪዎች መልሶ በምድራቸው ላይ ለማቋቋም የገባው ቃል አስገራሚ ፍጻሜውን አግኝቷል።—ኢሳይያስ ምዕራፍ 35
3. (ሀ) ትኩረታችንን የሚስቡት ኢሳይያስ የመዘገባቸው የትኞቹ ተስፋዎች ናቸው? (ለ) እነዚህ ነገሮች በእርግጥ ይፈጸማሉ ብለህ የምታምነው ለምንድን ነው?
3 በተጨማሪም ይሖዋ በመሲሑ አማካኝነት የሰው ዘር ጽድቅ የሰፈነበት አገዛዝ እንደሚያገኝ፣ ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንደሚወጣ እንዲሁም ምድር ገነት እንደምትሆን በኢሳይያስ በኩል ትንቢት አስነግሯል። (ኢሳይያስ 9:6, 7፤ 11:1-9፤ 25:6-8፤ 35:5-7፤ 65:17-25) እነዚህ ነገሮችስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ይሆን? ምንም አያጠራጥርም! ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ ለእኛ ጥቅም ሲል ትንቢታዊ ቃሉ ተመዝግቦ እንዲቀመጥና እስከ አሁን ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል።—ቲቶ 1:2፤ ሮሜ 15:4
4. ምንም እንኳ ዛሬ የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥንታዊ ቅጂዎች ባይኖሩም የአምላክ ቃል “ሕያው” ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
4 ይሖዋ እስከ ዛሬ ተጠብቆ እንዲቆይ ያደረገው የጥንቶቹ ጸሐፊዎች እነዚህን ትንቢቶች ያሠፈሩባቸውን የመጀመሪያዎቹን ጥንታዊ ቅጂዎች አይደለም። ይሁን እንጂ ‘ቃሉ’ ማለትም የተናገረው ዓላማው ሕያው ቃል መሆኑ ታይቷል። ይህ ዓላማው ያለ አንዳች እንቅፋት ወደ ፊት ይገሰግሳል፤ ዓላማው በዚህ ሁኔታ መገስገሱ ደግሞ ቃሉ ሕይወታቸውን የነካው ሰዎች ያላቸው ውስጣዊ ሐሳብና ዝንባሌ ምን ዓይነት እንደሆነ በግልጽ እንዲታይ ያደርጋል። (ዕብራውያን 4:12) ከዚህም በላይ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች እስካሁን ተጠብቀው የቆዩትና ወደ ሌሎች ቋንቋዎች የተተረጎሙት በመለኮታዊ አመራር ነው።
ሥርጭቱን ለመግታት ሙከራዎች በተካሄዱበት ጊዜ
5. (ሀ)የሶርያ ንጉሥ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ለማጥፋት ምን ጥረት አድርጓል? (ለ) ያልተሳካለትስ ለምንድን ነው?
5 ገዥዎች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ጽሑፎች ለማጥፋት ተደጋጋሚ ሙከራ አድርገዋል። በ168 ከዘአበ የሶርያው ንጉሥ አንቲዮከስ ኢፒፋነስ (ሥዕሉ በገጽ 10 ላይ ይገኛል) ለይሖዋ አገልግሎት በተወሰነው ቤተ መቅደስ ውስጥ ለዚየስ መሠዊያ ተክሏል። ከዚህም በተጨማሪ ‘የሕጉን መጻሕፍት’ ፈልጎ ከማቃጠሉም ሌላ እንደነዚህ ዓይነት ቅዱስ ጽሑፎችን ይዞ የተገኘ ሰው እንደሚገደል አዋጅ አስነግሮ ነበር። በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ምንም ያህል ቅጂዎችን ቢያቃጥልም የቅዱሳን ጽሑፎችን ሥርጭት ጨርሶ ማፈን አልቻለም። በወቅቱ የአይሁዳውያኑ ማኅበረሰብ በብዙ አገሮች ውስጥ ተበታትኖ ይገኝ ስለነበር እያንዳንዱ ምኩራብ በርከት ያሉ የራሱ ጥቅልሎች ነበሩት።—ከሥራ 13:14, 15 ጋር አወዳድር።
6. (ሀ) የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ይጠቀሙባቸው የነበሩትን ቅዱሳን ጽሑፎች ለማጥፋት ምን ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል? (ለ) ውጤቱስ ምን ነበር?
6 የሮማው ንጉሠ ነገሥት ዲዮቅላጢያን በ303 እዘአ የክርስቲያኖች መሰብሰቢያ ቦታዎች እንዲፈርሱና ‘ቅዱሳን ጽሑፎቻቸውም በእሳት እንዲቃጠሉ’ ትእዛዝ አውጥቶ ነበር። እንዲህ ያለው የጥፋት ዘመቻ ለአሥር ዓመታት ያህል ቀጥሏል። ስደቱ ምንም ያህል የከፋ ቢሆን ዲዮቅላጢያን ክርስትናን ጨርሶ ለማጥፋት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም፤ አምላክም የንጉሠ ነገሥቱ ወኪሎች በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃሉን አንድም ክፍል ቢሆን ጨርሰው እንዲያጠፉ አልፈቀደላቸውም። ሆኖም ተቃዋሚዎቹ የአምላክ ቃል በመሠራጨቱና ያደረባቸው መጥፎ ስሜት በውስጣቸው ያለውን አሳብ የሚያሳይ ነበር። ሰይጣን ያሳወራቸውና የእርሱን ፈቃድ የሚፈጽሙ ሰዎች መሆናቸውን አረጋግጠዋል።—ዮሐንስ 8:44፤ 1 ዮሐንስ 3:10-12
7. (ሀ) የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት በምዕራብ አውሮፓ እንዳይሰራጭ ለማከላከል ምን ጥረቶች ተደርገዋል? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስን በመተርጎምና በማሳተም ረገድ ምን ነገር ተከናውኗል?
7 የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትን ስርጭት ለማጨናገፍ የተደረጉት ጥረቶች ሌላም መልክ ነበራቸው። ላቲን የዕለት ተዕለት መግባቢያ ቋንቋ መሆኑ እየቀረ ሲሄድ መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋዎች እንዳይተረጎም ክፉኛ ይቃወሙ የነበሩት አረማዊ ገዥዎች ሳይሆኑ እንደ ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ 7ኛና (1073-85) እንደ ሊቀ ጳጳስ ኢኖሰንት ሦስተኛ (1198-1216) ያሉት ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች ነበሩ። በፈረንሳይ ቱሉዝ ከተማ የሚገኘው የሮማ ካቶሊክ ምክር ቤት በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥልጣን ላይ የሚነሣውን ተቃውሞ ለማዳፈን ሲል ማንም ተራ ሰው በብዙሐኑ መግባቢያ ቋንቋ የተዘጋጀውን መጽሐፍ ቅዱስ በእጁ ይዞ እንዳይገኝ የሚል ድንጋጌ በ1229 አወጣ። ይህንንም ድንጋጌ በኃይል ለማስፈጸም ሲባል ጭካኔ የተሞላበት ኢንኩዊዚሽን ተካሄደ። ይሁንና ኢንኩዊዚሽኑ ከተካሄደ ከ400 ዓመታት በኋላ የአምላክን ቃል የሚያፈቅሩ ሰዎች ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ 20 በሚያክሉ ቋንቋዎችና ተጨማሪ ቀበሌኛዎች እንዲሁም አብዛኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሌሎች 16 ቋንቋዎች ተርጉመው ያሠራጩ ነበር።
8. በ19ኛው መቶ ዘመን መጽሐፍ ቅዱስን በሩሲያ ቋንቋ በመተርጎሙና በማሠራጨቱ መስክ ምን ነገር እየተከናወነ ነበር?
8 ተራው ሕዝብ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያገኝ ትከላከል የነበረችው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብቻ አልነበረችም። በ19ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ በሴንት ፒትስበርግ በሚገኘው በአካዳሚ ኦቭ ዲቪኒቲ ይሠሩ የነበሩት ፕሮፌሰር ፓቭስኪ የማቴዎስን ወንጌል ከግሪክኛ ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተርጉመው ነበር። ሌሎች የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል የሆኑ መጻሕፍትም ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተተርጉመው ስለ ነበር ፓቭስኪ እንደ ዋና አዘጋጅ ሆነው አገልግለዋል። የዛር አገዛዝ በ1826 በቀሳውስቱ ቆስቋሽነት የሩሲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “ቅዱስ ሲኖዶስ” አስተዳደር ሥር እንዲሆን እስካደረገበት ጊዜ ድረስ እነዚህ ቅጂዎች በሰፊው ተሠራጭተዋል፤ ከዚህ በኋላ ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ እንቅስቃሴ በቤተ ክርስቲያኒቱ ተገታ። ከጊዜ በኋላ ፓቭስኪ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከዕብራይስጥ ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተርጉመዋል። በተመሳሳይ ወቅት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አበምኔት የሆነው ማካሪዮስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ከዕብራይስጥ ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተርጉሟል። ሁለቱም ሰዎች ይህን በማድረጋቸው የተቀጡ ሲሆን የትርጉም ሥራቸውም ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቤተ መዘክር እንዲገባ ተደርጓል። ቤተ ክርስቲያኒቱ መጽሐፍ ቅዱስ በወቅቱ ተራው ሕዝብ ሊያነበውም ሆነ ሊረዳው በማይችለው በጥንቱ የስላቮን ቋንቋ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ለማድረግ ቆርጣ ተነሥታ ነበር። ሕዝቡ የመጽሐፍ ቅዱስን እውቀት ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት መቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ ሲደረስ በ1856 “ቅዱስ ሲኖዶሱ” የራሱን አንድ ትርጉም አዘጋጀ፤ በትርጉሙ ውስጥ የተሠራባቸው ቃላት ከቤተ ክርስቲያኒቱ አመለካከት ጋር የሚጣጣሙ እንዲሆኑ ሲባል በጥንቃቄ በተነደፈ መመሪያ የተዘጋጀ ትርጉም ነበር። በዚህ መንገድ ሃይማኖታዊ መሪዎቹ የአምላክን ቃል ሥርጭት በሚመለከት መስለው ለመታየት የሚፈልጉት ሌላ፣ ውስጣዊ ዝንባሌያቸው ደግሞ ሌላ እንደሆነ በቃላቸውና በድርጊታቸው በግልጽ አሳይተዋል።—2 ተሰሎንቄ 2:3, 4
ቃሉ እንዳይበረዝ መከላከል
9. አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ለአምላክ ቃል ያላቸውን ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?
9 ቅዱሳን ጽሑፎችን በመተርጎሙና በመገልበጡ ሥራ ከተካፈሉት ሰዎች መካከል ለአምላክ ቃል እውነተኛ ፍቅር የነበራቸውና ቃሉ ለእያንዳንዱ ሰው እንዲደርስ ለማድረግ ልባዊ ጥረት ያደረጉ ሰዎች ይገኙበታል። ዊልያም ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስን በእንግሊዝኛ ቋንቋ ለማዘጋጀት ባደረገው ጥረት ምክንያት (በ1536) ሰማዕት ሆኗል። ፍራንሲስኮ ደ ኤንቲናስ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን በስፔይን ቋንቋ በመተርጎሙና በማዘጋጀቱ በካቶሊክ ኢንኩዊዚሽን (ከ1544 በኋላ) በቁጥጥር ሥር ውሎ ነበር። ሮበርት ሞሪሰንም (ከ1807 እስከ 1818) በሕይወቱ ቆርጦ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ቻይና ቋንቋ ተርጉሟል።
10. ለአምላክ ቃል ፍቅር ኖሯቸው ሳይሆን ሌላ ዓላማ ይዘው የተነሱ ተርጓሚዎች እንደነበሩ የሚያሳዩ ምን ምሳሌዎች አሉ?
10 ይሁን እንጂ ለአምላክ ቃል ፍቅር ኖሯቸው ሳይሆን ሌላ ዓላማ ይዘው የተነሱ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ አዘጋጆችና ተርጓሚዎች ነበሩ። የሚከተሉትን አራት ምሳሌዎች ተመልከት:- (1) የሰማርያ ሰዎች በኢየሩሳሌም የነበረውን ቤተ መቅደስ ለመቀናቀን ሲሉ በገሪዛን ተራራ ቤተ መቅደስ ገንብተው ነበር። ይህንን ለመደገፍ ሲባል በሳምራውያኑ የፔንታቱች ቅጂ ውስጥ በዘጸአት 20:17 ላይ ባዕድ ሐሳብ ተጨምሮበታል። በገሪዛን ተራራ ላይ የድንጋይ መሠዊያ መሥራትንና በዚያ መሥዋዕት ማቅረብን የሚያዝ ቃል የአሥርቱ ትእዛዝ ክፍል እንደሆነ ተድርጎ ተጨምሯል። (2) የግሪክ ሰፕቱጀንትን የዳንኤል መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ የተረጎመው ሰው መልእክቱን እንደፈለገ እያጣመመ አስቀምጦታል። የዕብራይስጡን ጽሑፍ ግልጽ ያደርጋሉ ወይም ያጎለብታሉ ያላቸውን ዓረፍተ ነገሮችና ሐሳቦች አስገብቷል። በአንባቢዎች ዘንድ ተቀባይነት የላቸውም ብሎ ያሰባቸውን አንዳንድ ዝርዝር ሐሳቦች አስቀርቷል። በዳንኤል 9:24-27 ላይ የሚገኘውን መሲሑ ስለሚገኝበት ጊዜ የሚገልጸውን ትንቢት ሲተረጉም የተጠቀሰውን የጊዜ ርዝማኔ ከማዛባቱም ሌላ የሌሉ ቃላት ጨምሯል፣ የነበሩትን በሌላ ለውጧል፣ ቦታቸውንም አቀያይሯል። ምናልባትም ይህንን ያደረገው ትንቢቱ የመቃባውያንን ትግል የሚደግፍ እንዲመስል አድርጎ ለማስቀመጥ አስቦ ሳይሆን አይቀርም። (3) በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ በላቲን ቋንቋ በተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ ላይ ልክ ከ1 ዮሐንስ 5:7 የተጠቀሰ በማስመሰል “በሰማይ አብ፣ ቃልና መንፈስ ቅዱስ አሉ፤ እነዚህም ሦስቱ አንድ ናቸው” የሚሉትን ቃላት የጨመረው ስለ ሥላሴ ትምህርት ሽንጡን ገትሮ ይሟገት የነበረ ሰው እንደሆነ ግልጽ ነው። ከጊዜ በኋላ ይኸው ምንባብ በላቲን ቋንቋ በተዘጋጀ ጥንታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጅ ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። (4) በፈረንሳይ፣ ሉዊ አሥራ ሦስተኛ (1610-43) የፕሮቴስታንቶችን እንቅስቃሴ ለመቋቋም ሲል ዣክ ኮርበ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ፈረንሳይኛ እንዲተረጉም አድርጓል። ይህንን ዓላማ አንግቦ የተነሳው ኮርበ በሥራ 13:2 ላይ ያስገባውን “የቁርባን ቅዱስ መሥዋዕት” የሚለውን ሐሳብ ጨምሮ የጥቅሶቹን ይዘት የሚቀይሩ ለውጦች አድርጓል።
11. (ሀ) አንዳንድ ሐቀኝነት የጎደላቸው ተርጓሚዎች ቢኖሩም የአምላክ ቃል እስከ መጨረሻው የጸናው እንዴት ነው? (ለ) የመጀመሪያዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች የያዙትን ሐሳብ በትክክል ለማወቅ የሚያስችሉ ምን ያህል የጥንት ቅጂዎችን በማስረጃነት ማቅረብ ይቻላል? (ሣጥኑን ተመልከት።)
11 ይሖዋ በቃሉ ላይ እንደፈለጉ ሲፈነጩ የወሰደው እርምጃ ባይኖርም እንኳ እንዲህ ማድረጋቸው ዓላማውን አልለወጠውም። ይህ ነገር ያመጣው ለውጥ ምንድን ነው? የገሪዛንን ተራራ በሚመለከት የተጨመረው ሐሳብ የሳምራውያኑ ሃይማኖት አምላክ የሰው ልጆችን የሚባርክበት መንገድ እንዲሆን አላደረገም። እንዲያውም የሳምራውያን ሃይማኖት በፔንታቱች ጽሑፎች እንደሚያምን ይናገር እንጂ እውነትን ያስተምራል ተብሎ እምነት ሊጣልበት የሚችል እንዳልሆነ አረጋግጧል። (ዮሐንስ 4:20-24) በሰፕቱጀንት ትርጉም ላይ የተፈጸመው ቃላትን የማጣመም ድርጊትም መሲሑ በነቢዩ ዳንኤል አማካኝነት በትንቢት በተነገረለት ትክክለኛ ጊዜ እንዳይመጣ አላገደውም። ከዚህም በተጨማሪ የሰፕቱጀንት ትርጉም በአንደኛው መቶ ዘመን ይሠራበት የነበረ ቢሆንም ለአይሁዳውያኑ በየምኩራቦቻቸው ከቅዱሳን ጽሑፎች ይነበብላቸው የነበረው በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው። በመሆኑም የትንቢቱ ፍጻሜ በተቃረበበት ጊዜ ‘ሕዝቡ ይጠባበቁት ነበር።’ (ሉቃስ 3:15) የሥላሴን ትምህርት ለመደገፍ ሲባል በ1 ዮሐንስ 5:7 ላይ እንዲሁም ሥርዓተ ቁርባን ተገቢ ነው እንዲባል ለማሰኘት በሥራ 13:2 ላይ የተጨመሩትም ሐሳቦች ቢሆኑ ሐቁን አላጠፉትም። ከጊዜ በኋላም እነዚህ ማታለያዎች ሙሉ በሙሉ ተጋልጠዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በመጀመሪያ የተጻፈባቸው ቋንቋዎች ጥንታዊ ቅጂዎች በብዛት መገኘታቸው የማንኛውንም የትርጉም ሥራ ትክክለኛነት ለመመዘን የሚያስችል ሁኔታ ፈጥሯል።
12. (ሀ) አንዳንዶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ምን ከፍተኛ ለውጦችን አድርገዋል? (ለ) እነዚህ ለውጦችስ ምን ያህል ስፋት ነበራቸው?
12 ቅዱሳን ጽሑፎችን ለመለወጥ የተደረጉት ሌሎቹ ጥረቶች ደግሞ ጥቂት ቁጥሮች ላይ ያሉ ቃላትን ከመቀየር የሚበልጥ ነገርንም የሚጨምሩ ናቸው። እነዚህ ለውጦች በእውነተኛው አምላክ ማንነት ላይ የተሰነዘሩ ጥቃቶች ነበሩ። የተደረጉት ለውጦች ዓይነትና ስፋት ሲታይ ከድርጊቱ በስተጀርባ ከማንኛውም ግለሰብ ወይም ሰብዓዊ ድርጅት የበለጠ ኃይል ያለው አንድ አካል እንዳለ የማያሻማ ማረጋገጫ ይሰጣል፤ አዎን፣ ከዚህ ድርጊት በስተጀርባ ያለው ቀንደኛው የይሖዋ ጠላት ሰይጣን ዲያብሎስ ነው። ከተርጓሚዎቹና ከገልባጮቹ መካከል አንዳንዶቹ ሆነ ብለው ሌሎቹ ደግሞ እያቅማሙም ቢሆን ለዚህ ተጽእኖ እጃቸውን በመስጠታቸው ይሖዋ የሚለውን የአምላክ የግል ስም በሺህ የሚቆጠሩ ቦታዎች ላይ ከሚገኝበት በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፈው ቃሉ ውስጥ አውጥተውታል። ቀደም ባሉት ዘመናት ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክኛ፣ ላቲን፣ ጀርመንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ጣልያንኛና ደች ቋንቋዎች የተመለሱትን ትርጉሞች ጨምሮ ሌሎች ትርጉሞችም መለኮታዊውን ስም ሙሉ በሙሉ አውጥተውታል፣ አለዚያም በጥቂት ቦታዎች ላይ ተወስኖ እንዲቀር አድርገዋል። እንዲሁም ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ቅጂዎች ውስጥ እንዲወጣ ተደርጓል።
13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንድ ለውጦችን ለማድረግ የተካሄደው ከፍተኛ ጥረት የአምላክ ስም ከሰው ልጅ አእምሮ ጨርሶ እንዲደመሰስ ሊያደርግ ያልቻለው ለምንድን ነው?
13 ይሁንና ይህ ክብራማ ስም ጨርሶ ከሰው ልጅ አእምሮ አልተደመሰሰም። ወደ ስፓንኛ፣ ፖርቹጋል፣ ጀርመንኛ፣ እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና ሌሎች ብዙ ቋንቋዎች የተተረጎሙት የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የአምላክን የግል መጠሪያ በሐቀኝነት አስገብተዋል። በ16ኛው መቶ ዘመን የአምላክ የግል ስም በዕብራይስጥ ቋንቋ በተሠሩት የተለያዩ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉሞች ውስጥ እንደገና ብቅ ማለት የጀመረ ሲሆን በ18ኛው መቶ ዘመን በጀርመንኛ፣ በ19ኛው መቶ ዘመን በክሮኤሺያና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተሠሩት ትርጉሞች ውስጥ ገብቷል። ሰዎች የአምላክን ስም ለመሰወር ቢሞክሩም “የይሖዋ ቀን” ሲመጣ አምላክ ራሱ እንደተናገረው ‘አሕዛብ ሁሉ እርሱ ይሖዋ እንደሆነ ያውቃሉ።’ ይህ የአምላክ ዓላማ በምንም ዓይነት መንገድ ሳይፈጸም አይቀርም።—2 ጴጥሮስ 3:10፤ ሕዝቅኤል 38:23፤ ኢሳይያስ 11:9፤ 55:11
መልእክቱ በመላዋ ምድር ተዳረሰ
14. (ሀ) በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በምን ያህል የአውሮፓ ቋንቋዎች ታትሞ ነበር? ውጤቱስ ምን ነበር? (ለ) በ1914 ማብቂያ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በምን ያህል የአፍሪካ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ነበር?
14 በ20ኛው መቶ ዘመን መባቻ ላይ መጽሐፍ ቅዱስ በአውሮፓ ውስጥ ባሉ በ94 ቋንቋዎች በመታተም ላይ ነበር። ይህም በዚህ የምድር ክፍል የሚኖሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የአሕዛብ ዘመን ማለቂያ በሆነው ዓመት በ1914 ዓለምን የሚያናውጡ ክስተቶች እንደሚመጡ እንዲያስተውሉ አንቅቷቸዋል፤ ደግሞም እነዚህ ነገሮች ተከናውነዋል! (ሉቃስ 21:24) አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነው ዓመት 1914 ከመጠናቀቁ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል በሰፊው ከሚሠራባቸው የእንግሊዝኛ፣ የፈረንሳይኛና የፖርቹጋል ቋንቋዎች በተጨማሪ በ157 የአፍሪካ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ነበር። በመሆኑም በዚህ አካባቢ በሚኖሩት ብዙ ነገዶችና ብሔረሰቦች ውስጥ ላሉ ትሑት ሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት የሚያጎናጽፈውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለማስተማር የሚያስችለው መሠረት ተጥሎ ነበር።
15. የመጨረሻዎቹ ቀናት ሲጀምሩ መጽሐፍ ቅዱስ በአሜሪካ አገሮች ውስጥ በሚነገሩ ቋንቋዎች ምን ያህል ተሠራጭቶ ነበር?
15 ዓለም በትንቢት ወደ ተነገሩት የመጨረሻዎቹ ቀናት በገባበት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ በአሜሪካ አገሮች ውስጥ በሰፊው ተሠራጭቶ ይገኝ ነበር። ከአውሮፓ የፈለሱት ሰዎች በተለያዩ ቋንቋዎቻቸው የተዘጋጁ ቅጂዎች ይዘው መጥተው ነበር። በወቅቱ ለሕዝብ በሚቀርቡ ንግግሮች አማካኝነት እንዲሁም በጊዜው ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል የሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች የሚያዘጋጁአቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች በስፋት በማሠራጨት መጠነ ሰፊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መርኃ ግብር በመካሄድ ላይ ነበር። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበራት በምዕራቡ ንፍቅ ክበብ ያሉትን ነዋሪዎች ፍላጎት ለማሟላት ሲሉ በሌሎች 57 ቋንቋዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት ሥራ እያካሄዱ ነበር።
16, 17. (ሀ) ምድር አቀፍ የስብከት ሥራ የሚካሄድበት ጊዜ ከመድረሱ አስቀድሞ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ያህል ተሠራጭቶ ነበር? (ለ) መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም እስከ መጨረሻው እንደጸናና ትልቅ ተጽዕኖ የሚያሳድር መጽሐፍ መሆኑ የተረጋገጠው እንዴት ነው?
16 ‘መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት’ የሚከናወነው ምሥራቹን የመስበክ ምድር አቀፍ ሥራ የሚሠራበት ጊዜ ከመድረሱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስ በእስያ አገሮችና በፓስፊክ ውቅያኖስ ወዳሉ ደሴቶችም ተዳርሶ ነበር። (ማቴዎስ 24:14) በወቅቱ በዚህ የምድር ክፍል በሚነገሩ በ232 የቋንቋ ቤተሰቦች ተዘጋጅቶ ነበር። አንዳንዶቹ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ሲሆኑ ብዙዎቹ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ሌሎቹ ደግሞ በተናጠል የተዘጋጁ የቅዱስ ጽሑፉ መጻሕፍት ነበሩ።
17 በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው መጽሐፍ ቅዱስ እስከ ዘመናችን ድረስ ጸንቶ የኖረው በቤተ መዘክር ቅጂነት አይደለም። ካሉት መጻሕፍት ሁሉ በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመና በስፋት የተሠራጨ መጽሐፍ ነበር። መጽሐፉ መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው ከሚያሳየው ከዚህ ማረጋገጫ በተጨማሪ በውስጡ ተመዝግበው የሚገኙት ነገሮችም ፍጻሜያቸውን እያገኙ ነበር። ትምህርቶቹና ከትምህርቱ በስተጀርባ ያለው መንፈስ በብዙ አገሮች በሚኖሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ዘላቂ ውጤት በማምጣት ላይ ነበሩ። (1 ጴጥሮስ 1:24, 25) ይሁን እንጂ ከዚህ የበለጠ ብዙ የሚከናወን ነገር ነበር።
ታስታውሳለህ?
◻ ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው “የአምላካችን ቃል” ምንድን ነው?
◻ የመጽሐፍ ቅዱስን ሥርጭት ለማፈን ምን ሙከራዎች ተደርገዋል? ውጤቱስ ምን ነበር?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለ ተጠብቆ ሊቆይ የቻለው እንዴት ነው?
◻ አምላክ ዓላማውን በሚመለከት የተናገረው ቃል ሕያው መሆኑ የታየው እንዴት ነው?
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ይዘት በትክክል ማወቅ እንችላለንን?
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ይዘት የሚያረጋግጡ 6,000 የሚያክሉ በእጅ የተጻፉ ጥንታዊ የዕብራይስጥ ጽሑፎች አሉ። ከእነዚህ መካከል ጥቂቶቹ በቅድመ ክርስትና ዘመን የተዘጋጁ ናቸው። ዛሬ የሚገኙት ቢያንስ 19 የሚያክሉት ሙሉ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ጥንታዊ ቅጂዎች ተንቀሳቃሽ ማተሚያ ከመፈልሰፉ በፊት ባለው ዘመን የተዘጋጁ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ በዚሁ ዘመን በ28 ሌሎች ቋንቋዎች የተዘጋጁ ትርጉሞች ይገኛሉ።
ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ደግሞ በግሪክኛ የተዘጋጁ 5,000 የሚያክሉ ጥንታዊ ቅጂዎች ተመዝግበዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ፣ የመጀመሪያው ጽሑፍ ከተዘጋጀ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ማለትም ከ125 እዘአ ቀደም ብሎ የተዘጋጀ ነው። ከዚያ ብዙ ቀደም ብለው እንደተዘጋጁ የሚገመቱ አንዳንድ ቁርጥራጮችም አሉ። በመንፈስ አነሳሽነት ከተጻፉት 27 መጻሕፍት መካከል የሃያ ሁለቱ መጻሕፍት ከ10 እስከ 19 የሚደርሱ የእጅ ግልባጭ የሆኑ የተሟሉ ጥንታዊ ቅጂዎች ተገኝተዋል። ከዚህኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ያሉት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው የተሟሉ ጥንታዊ የእጅ ግልባጭ ቅጂዎች ያሉት መጽሐፍ የራእይ መጽሐፍ ሲሆን ቅጂዎቹ ሦስት ብቻ ናቸው። ሙሉ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ካቀፉት ጥንታዊ ቅጂዎች መካከል አንዱ የተዘጋጀው በአራተኛው መቶ ዘመን እዘአ ገደማ ነው።
ይህን ያክል በርካታ የጥንታዊ መዛግብት ማስረጃ የሚቀርብለት አንድም ጥንታዊ ጽሑፍ አይገኝም።