ለሕይወት የምታደርጉትን ሩጫ አታቋርጡ!
“በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ።”—ዕብራውያን 12:1
1, 2. በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የይሖዋ አገልጋዮችን ያስፈነደቁ ምን አስደሳች ክንውኖች ታይተዋል?
የምንኖረው አስደሳችም ተፈታታኝም በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። ከ80 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ማለትም በ1914 ኢየሱስ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሾሟል። በዚህ ጊዜ ‘የጌታ ቀንና’ የዚህ የነገሮች ሥርዓት ‘የፍጻሜ ዘመን’ ጀምረዋል። (ራእይ 1:10፤ ዳንኤል 12:9) ከዚያ ጊዜ ወዲህ ክርስቲያኖች ለሕይወት የሚያደርጉት ሩጫ ይበልጥ አጣዳፊ ሆኗል። የአምላክ አገልጋዮች ከይሖዋ ሰማያዊ ሠረገላ ማለትም የይሖዋን ዓላማዎች ለማስፈጸም ያላንዳች እንቅፋት ወደፊት ከሚገሰግሰው ሰማያዊ ድርጅቱ ጋር እኩል ለመራመድ ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ ቆይተዋል።—ሕዝቅኤል 1:4-28፤ 1 ቆሮንቶስ 9:24
2 የአምላክ ሕዝቦች ወደ ዘላለም ሕይወት በሚያደርጉት ‘ሩጫ’ ደስታ አግኝተውበታልን? አዎን፣ አግኝተውበታል! ቀሪዎቹ የኢየሱስ ወንድሞች ሲሰበሰቡ በማየታቸውና የ144,000ዎቹ ቀሪዎች የመጨረሻ መታተም እየተጠናቀቀ መምጣቱን በማስተዋላቸው ተደስተዋል። (ራእይ 7:3, 4) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሾመው ንጉሥ “የምድሪቱን መከር” ለማጨድ ማጭዱን መስደዱን በማስተዋላቸው ተደስተዋል። (ራእይ 14:15, 16) መከሩ በጣም ብዙ ነው! (ማቴዎስ 9:37) እስከ አሁን ድረስ ከአምስት ሚልዮን የሚበልጡ ነፍሳት ተሰብስበዋል፤ “አንድ እንኳ ሊቈጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች” ናቸው። (ራእይ 7:9) ማንም ሊቆጥራቸው የማይችል በመሆናቸው የዚህ ብዙ ሕዝብ ቁጥር በመጨረሻ ይህን ያክል ይሆናል ብሎ ሊናገር የሚችል ሰው አይኖርም።
3. ሁልጊዜ ደስተኛ መንፈስ እንዲኖረን መጣር ያለብን ምን ዓይነት ሁኔታዎች እያሉም ነው?
3 እኛ በፍጥነት እየሮጥን ሳለን ሰይጣን ሊያደናቅፈን ወይም ከሩጫችን ሊያዘገየን እንደሚሞክር አይካድም። (ራእይ 12:17) የመጨረሻው ዘመን ምልክት የሆኑት ጦርነት፣ ረሃብ፣ ቸነፈር እና ሌሎች መከራዎች እያሉ በዚህ ሩጫ መቀጠል ቀላል አይደለም። (ማቴዎስ 24:3-9፤ ሉቃስ 21:11፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ሆኖም የሩጫው ማብቂያ እየተቃረበ ሲመጣ ልባችን በደስታ ይፈነድቃል። ጳውሎስ በዘመኑ የነበሩት ክርስቲያን ወንድሞቹ እንዲኖራቸው ያበረታታውን ዓይነት መንፈስ ለማንጸባረቅ እንጥራለን:- “ሁልጊዜ በጌታ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፣ ደስ ይበላችሁ!”—ፊልጵስዩስ 4:4
4. የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈስ አሳይተዋል?
4 ጳውሎስ እነዚህን ቃላት የጻፈላቸው ክርስቲያኖች በእምነታቸው የሚደሰቱ እንደነበሩ ምንም አያጠያይቅም፤ ምክንያቱም “በጌታ መደሰታችሁን ቀጥሉ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵስዩስ 3:1 NW) የፊልጵስዩስ ጉባኤ በቅንዓትና በግለት የሚያገለግል ለጋስና አፍቃሪ ጉባኤ ነበር። (ፊልጵስዩስ 1:3-5፤ 4:10, 14-20) ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነት መንፈስ የነበራቸው ሁሉም የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ የዕብራውያንን መጽሐፍ የጻፈላቸው አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሁኔታ አሳሳቢ ነበር።
‘አብልጠን እንጠንቀቅ’
5. (ሀ) የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ በተቋቋመበት ወቅት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈስ ነበራቸው? (ለ) በ60 እዘአ ገደማ አንዳንድ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ምን ዓይነት መንፈስ እንደነበራቸው ግለጽ።
5 በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው የክርስቲያን ጉባኤ በትውልድ አይሁዳዊ ከሆኑና ወደ ይሁዲነት ከተለወጡ ሰዎች የተውጣጣ ሲሆን የተቋቋመው በ33 እዘአ በኢየሩሳሌም ነበር። ይህ ጉባኤ ምን ዓይነት መንፈስ ነበረው? ምንም እንኳ ጉባኤው ስደት የነበረበት ቢሆንም ምን ዓይነት ግለትና ደስታ እንደነበረው ለመረዳት የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የመክፈቻ ምዕራፎች ማንበቡ ብቻ ይበቃል። (ሥራ 2:44-47፤ 4:32-34፤ 5:41፤ 6:7) ይሁን እንጂ የተወሰኑ አሥርተ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ሁኔታዎቹ ተለውጠው ብዙ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከሩጫው ወዳኋላ ማለት ጀመሩ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ በ60 እዘአ ገደማ እነዚህ ክርስቲያኖች ስለነበራቸው ሁኔታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “የልግመኝነትና የመዛል፣ የመሰላቸት፣ ተስፋቸው እንደዘገየ የማሰብ፣ የአውቆ አጥፊነት እና በዕለታዊ ሕይወታቸው የእምነት የለሽነት ሁኔታ ይታይባቸው ነበር። ክርስቲያኖች ቢሆኑም ለሰማያዊ ጥሪያቸው የነበራቸው አድናቆት ተሟጥጦ ነበር።” ቅቡዓን ክርስቲያኖች ይህን በመሰለ ሁኔታ ውስጥ እንዴት ሊወድቁ ይችላሉ? ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች (በ61 እዘአ) የጻፈውን ደብዳቤ በከፊል መመርመራችን ለዚህ ጥያቄ መልስ እንድናገኝ ይረዳናል። እንዲህ ያለውን ምርመር ማድረጋችን እኛም ዛሬ ተመሳሳይ ወደሆነ መንፈሳዊ አዘቅት እንዳንወድቅ ይጠብቀናል።
6. በሙሴ ሕግ ሥር ይካሄድ በነበረው አምልኮና በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባለን እምነት ላይ በተመሠረተው አምልኮ መካከል ያሉት አንዳንድ ልዩነቶች ምንድን ናቸው?
6 ዕብራውያን ክርስቲያኖች ከአይሁድ እምነት ወጥተው የመጡ ሰዎች ነበሩ። የአይሁድ እምነት ደግሞ ይሖዋ በሙሴ በኩል የሰጠውን ሕግ እጠብቃለሁ የሚል ሥርዓት ነበር። ሕጉ የብዙዎቹን አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ቀልብ መሳቡን ቀጥሎ የነበረ ይመስላል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ወደ ይሖዋ መቅረብ የሚቻልበት ብቸኛ መንገድ ሆኖ ለብዙ መቶ ዘመናት መቆየቱ እንዲሁም የካህናት አገልግሎት፣ ዘወትር የሚቀርቡ መሥዋዕቶችና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዝናን ያተረፈ ቤተ መቅደስ የነበረው ማራኪ የአምልኮ ሥርዓት መሆኑ ሊሆን ይችላል። ክርስትና ግን ከዚህ የተለየ ነው። ‘[ወደፊት የሚያገኘውን] ብድራት ትኩር ብሎ የተመለከተው’ እና ‘የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ የጸናው’ ሙሴ ያሳየውን ዓይነት መንፈሳዊ አመለካከት መያዝን ይጠይቃል። (ዕብራውያን 11:26, 27) ብዙዎቹ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት መንፈሳዊ አመለካከት እንዳልነበራቸው ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ግባቸው ላይ አትኩረው ከመሮጥ ይልቅ በሁለት ሐሳብ ያነክሱ ነበር።
7. ጥለነው የወጣነው ሥርዓት ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ ላይ ተጽዕኖ ሊኖረው የሚችለው እንዴት ነው?
7 ዛሬስ ተመሳሳይ ሁኔታ አለን? ሁኔታዎቹ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት እንዳልሆኑ አይካድም። ይሁንና ዛሬም ቢሆን ክርስቲያኖች የመጡት ባሉት ነገሮች ከሚኩራራ ሥርዓት ነው። ዓለም ብዙ ማራኪ የሆኑ አጋጣሚዎችን ያቀርባል፤ ይሁን እንጂ በሰዎች ላይ የሚጭነው ሸክምም የዚያኑ ያህል ነው። ከዚህም በተጨማሪ ብዙዎቻችን የምንኖረው የጥርጣሬ አመለካከት በሰፈነባቸውና ሰዎች እኔ ልቅደም የሚል የራስ ወዳድነት አመለካከት በሚያንጸባርቁባቸው አገሮች ውስጥ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሥርዓት ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን ከፈቀድንለት ‘የልባችን ዓይኖች’ በቀላሉ ሊፈዝዙ ይችላሉ። (ኤፌሶን 1:18) ወዴት እንደምንሄድ በትክክል ማስተዋል ከተሳነን የሕይወትን ሩጫ በአግባቡ መሮጥ እንዴት እንችላለን?
8. ክርስትና በሕጉ ሥር ይከናወን ከነበረው አምልኮ የሚበልጥባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
8 ጳውሎስ አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን ለማነቃቃት ሲል የክርስትና ሥርዓት ከሙሴ ሕግ ብልጫ እንዳለው አስታውሷቸዋል። የሥጋዊ እስራኤላውያን ብሔር በሕጉ ሥር የታቀፈ የይሖዋ ሕዝብ በነበረበት ጊዜ ይሖዋ በመንፈስ አነሳሽነት በሚናገሩ ነቢያት አማካኝነት ሐሳቡን ይገልጽለት እንደነበር እሙን ነው። ዛሬ ግን የሚናገረው “ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ” በኩል እንደሆነ ጳውሎስ ገልጿል። (ዕብራውያን 1:2) ከዚህም በላይ ኢየሱስ ‘ከጓደኞቹ’ ማለትም በዳዊት መስመር ከተነሡት ነገሥታት ሁሉ ይበልጣል። ከመላእክትም ሁሉ ሳይቀር ይበልጣል።—ዕብራውያን 1:5, 6, 9
9. በጳውሎስ ዘመን እንደነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ይሖዋ ለሚናገረው ነገር ‘አብልጠን ልንጠነቀቅ’ የሚገባን ለምንድን ነው?
9 በመሆኑም ጳውሎስ አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል:- “ስለዚህ ከሰማነው ነገር ምናልባት እንዳንወሰድ፣ ለእርሱ አብልጠን ልንጠነቀቅ ያስፈልገናል።” (ዕብራውያን 2:1) ስለ ክርስቶስ መማር ድንቅ በረከት ቢሆንም ከዚያ የበለጠ ነገር ያስፈልግ ነበር። በዙሪያቸው የነበረው የአይሁዳውያን ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ለመቋቋም እንዲችሉ የአምላክን ቃል በትኩረት መከታተል ያስፈልጋቸው ነበር። እኛም ብንሆን ከዚህ ዓለም ከሚሰነዘርብን የማያቋርጥ የፕሮፓጋንዳ ውርጅብኝ አንጻር ይሖዋ ለሚነግረን ነገር ‘አብልጠን ልንጠነቀቅ’ ይገባናል። ይህም ማለት ጥሩ የጥናት ልማድ ማዳበርና ጥሩ ፕሮግራም አውጥቶ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብ ማለት ነው። ጳውሎስ ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክት ላይ ወደኋላ እንደገለጸው በስብሰባዎች ላይ በመገኘትም ሆነ እምነታችንን ለሌሎች በመግለጽ ረገድ አዘውታሪ መሆን ማለት ነው። (ዕብራውያን 10:23-25) እንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ዓይናችን ክብራማ በሆነው ተስፋችን ላይ እንዳተኮረ ይቀጥል ዘንድ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር ያስችለናል። አእምሮአችንን በይሖዋ ሐሳቦች ከሞላን ይህ ዓለም ሊያደርስብን በሚችለው ማንኛውም ነገር አንዋጥም ወይም ደግሞ ሚዛናችንን አንስትም።—መዝሙር 1:1-3፤ ምሳሌ 3:1-6
“እርስ በርሳችሁ መመካከራችሁን ቀጥሉ”
10. (ሀ) ለይሖዋ ቃል ‘አብልጦ የማይጠነቀቅ’ ሰው ምን ሊደርስበት ይችላል? (ለ) ‘እርስ በርስ መመካከራችንን’ መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?
10 መንፈሳዊ ነገሮችን በትኩረት የማንከታተል ከሆነ አምላክ የሰጠው ተስፋ የማይጨበጥ ነገር መስሎ ሊታየን ይችላል። ጉባኤዎቹ ከቅቡዓን ብቻ የተውጣጡ በነበሩበትና ሐዋርያትም ገና በሕይወት ባሉበት የመጀመሪያው መቶ ዘመን እንኳ ሳይቀር ተመሳሳይ ነገር ተከስቷል። ጳውሎስ የዕብራውያን ሰዎችን እንዲህ ሲል አስጠንቅቋቸዋል:- “ወንድሞች ሆይ፣ ምናልባት ሕያው እግዚአብሔርን የሚያስክዳችሁ ክፉና የማያምን ልብ ከእናንተ በአንዳችሁ እንዳይኖር ተጠንቀቁ፤ ነገር ግን ከእናንተ ማንም በኃጢአት መታለል እልከኛ እንዳይሆን፣ ዛሬ ተብሎ ሲጠራ ሳለ፣ በእያንዳንዱ ቀን እርስ በርሳችሁ ተመካከሩ።” (ዕብራውያን 3:12, 13) “ተጠንቀቁ” የሚለው የጳውሎስ አነጋገር ንቁ የመሆንን አስፈላጊነት የሚያጎላ ነው። አደጋው ምንጊዜም አለ! “ኃጢአት” እንደሆነ ተደርጎ የተገለጸው የእምነት ማጣት በልባችን ውስጥ ሊጸነስና ወደ አምላክ ከመቅረብ ይልቅ ከእርሱ እየራቅን እንሄድ ይሆናል። (ያዕቆብ 4:8) ጳውሎስ ‘እርስ በርስ መመካከራችንን እንድንቀጥል’ አሳስቦናል። ከወንድማማች ኅብረታችን የምናገኘው ሞቅ ያለ ፍቅር ያስፈልገናል። “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1) ዛሬ ክርስቲያኖች በጉባኤ ስብሰባዎች፣ በወረዳና በልዩ እንዲሁም በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረው እንዲገኙ የሚያነሳሳቸው የዚህ ኅብረት አስፈላጊነት ነው።
11, 12. መሠረታዊ የክርስትና ትምህርቶችን በማወቃችን ብቻ መርካት የማይገባን ለምንድን ነው?
11 ጳውሎስ ቀጥሎ በመልእክቱ ውስጥ እንዲህ ሲል ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ምክር ሰጥቷል:- “ከጊዜው የተነሣ አስተማሪዎች ልትሆኑ ሲገባችሁ፣ አንድ ሰው ስለ እግዚአብሔር ቃላት መጀመሪያ ያለውን የሕፃንነትን ትምህርት እንዲያስተምራችሁ እንደ ገና ያስፈልጋችኋልና፤ የሚያስፈልጋችሁም ወተት ነው እንጂ ጠንካራ ምግብ አይደለም። . . . ጠንካራ ምግብ ግን መልካሙንና ክፉውን ለመለየት በሥራቸው የለመደ ልቡና ላላቸው ለፍጹማን ሰዎች ነው።” (ዕብራውያን 5:12-14) ከሁኔታዎቹ ለመረዳት እንደሚቻለው አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ማስተዋላቸውን ማስፋት ተስኗቸው ነበር። ሕጉን እንዲሁም ግርዘትን በሚመለከት የፈነጠቀላቸውን ተጨማሪ ብርሃን ለመቀበል ፈጣኖች አልነበሩም። (ሥራ 15:27-29፤ ገላትያ 2:11-14፤ 6:12, 13) አንዳንዶች እንደ ሳምንታዊው ሰንበትና ዓመታዊው የስርየት ቀን ላሉት ልማዳዊ ሥርዓቶች ከፍ ያለ ግምት ከመስጠት አልተላቀቁም ነበር።—ቆላስይስ 2:16, 17፤ ዕብራውያን 9:1-14
12 በመሆኑም ጳውሎስ “የክርስቶስን ነገር መጀመሪያ የሚናገረውን ቃል ትተን ወደ ፍጻሜ [“ጉልምስና፣” NW] እንሂድ” ሲል ተናግሯል። (ዕብራውያን 6:1) የአመጋገብ ሥርዓቱን በቁም ነገር የሚከታተል አንድ የማራቶን ሯጭ እጅግ አድካሚ የሆነውን ረጅም ሩጫ በጽናት ለመጨረስ የሚያስችል የተሻለ አቋም ይኖረዋል። በተመሳሳይም ለመንፈሳዊ አመጋገቡ የሚጠነቀቅ ማለትም በመሠረታዊ ወይም ‘የመጀመሪያ ትምህርቶች’ ብቻ የማይወሰን አንድ ክርስቲያን በሩጫው ለመጽናት ብሎም እስከ መጨረሻ ድረስ ለመሮጥ የሚያስችል የተሻለ አቋም ይኖረዋል። (ከ2 ጢሞቴዎስ 4:7 ጋር አወዳድር።) ይህም የእውነትን ‘ስፋትና ርዝመት ከፍታና ጥልቀት’ ለማወቅ በመጓጓት ወደ ጉልምስና ማደግ ማለት ነው።—ኤፌሶን 3:18
“መጽናት ያስፈልጋችኋል”
13. በፊተኞቹ ዘመናት ዕብራውያን ክርስቲያኖች እምነታቸውን ያሳዩት እንዴት ነበር?
13 ከ33 እዘአ የጰንጠቆስጤ ዕለት በኋላ በነበረው ጊዜ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ከባድ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም ጸንተው ቆመዋል። (ሥራ 8:1) ጳውሎስ እንደሚከተለው ብሎ ሲጽፍ ይህንን በአእምሮው ይዞ ሊሆን ይችላል:- “ብርሃን ከበራላችሁ በኋላ መከራ በሆነበት በትልቅ ተጋድሎ የጸናችሁበትን የቀደመውን ዘመን አስቡ።” (ዕብራውያን 10:32) በዚህ መንገድ የታመኑ ሆነው መጽናታቸው ለአምላክ ያላቸውን ፍቅር የሚያሳይ ከመሆኑም ሌላ በፊቱ የመናገር ነፃነት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል። (1 ዮሐንስ 4:17 NW) ጳውሎስ፣ እምነት በማጣት ይህን ነፃነታቸውን ገሸሽ እንዳያደርጉ አጥብቆ አሳስቧል። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና። ገና በጣም ጥቂት ጊዜ ነው፣ ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም” ሲል አጥብቆ አሳስቧቸዋል።—ዕብራውያን 10:35-37
14. ለብዙ ዓመታት ይሖዋን ካገለገልን በኋላም እንኳ እንድንጸና የሚረዱን አንዳንድ እውነታዎች የትኞቹ ናቸው?
14 ዛሬ ስላለነውስ ምን ማለት ይቻላል? ብዙዎቻችን መጀመሪያ የክርስትናን እውነት ስንማር በጣም ቀናተኞች ነበርን። አሁንም ያ ቅንዓት አለ? ወይስ ‘የቀድሞውን ፍቅራችንን ትተናል?’ (ራእይ 2:4) ምናልባትም አርማጌዶንን ከመጠበቅ ተሰላችተን ወይም ዝለን እንቅስቃሴያችን ተዳክሞ ይሆን? ግን እስቲ ቆም ብላችሁ አስቡ። እንደቀድሞው ሁሉ ዛሬም እውነት አስደሳች ነው። ኢየሱስ ዛሬም ሰማያዊ ንጉሣችን ነው። አሁንም ቢሆን ተስፋችን ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ነው፤ ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድናም እንደተጠበቀ ነው። ደግሞ አንድ ነገር ፈጽሞ አትዘንጉ:- “ሊመጣ ያለውም ይመጣል አይዘገይምም።”
15. አንዳንድ ክርስቲያኖች እንደ ኢየሱስ መራራ ስደቶችን በጽናት የተቋቋሙት እንዴት ነው?
15 በመሆኑም በዕብራውያን 12:1, 2 ላይ ተመዝግበው የሚገኙት የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ተገቢ ናቸው:- “እንግዲህ እነዚህን የሚያህሉ ምስክሮች እንደ ደመና በዙሪያችን ካሉልን፣ እኛ ደግሞ ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኃጢአት [የእምነት ማጣትን] አስወግደን፣ የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን፣ በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግሥት [“በጽናት፣” NW] እንሩጥ፤ እርሱ ነውርን ንቆ በፊቱም ስላለው ደስታ በመስቀል ታግሦ በእግዚአብሔር ዙፋን ቀኝ ተቀምጦአልና።” በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የአምላክ አገልጋዮች በጽናት የተወጧቸው ብዙ ነገሮች አሉ። የስቃይ ሞት እስከ መሞት ድረስ የታመነ እንደነበረው እንደ ኢየሱስ አንዳንዶቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የደረሰባቸውን ከፍተኛ ስደት የታመኑ ሆነው በጽናት ተወጥተዋል። አንዳንዶቹ ታሥረዋል፣ ተገርፈዋል፣ በፆታ ተነውረዋል አልፎ ተርፎም ተገድለዋል። (1 ጴጥሮስ 2:21) እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ያሳዩትን የአቋም ጽናት ስናስብ ልባችን ለእነርሱ ባለን ፍቅር አይነካምን?
16, 17. (ሀ) አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በእምነታቸው ላይ የሚደርሱትን የትኞቹን ፈታኝ ሁኔታዎች ይቋቋማሉ? (ለ) ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ እንድንቀጥል የሚረዳን ምን ነገር ማስታወሳችን ነው?
16 ይሁን እንጂ የሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ለአብዛኞቹ ክርስቲያኖች ይሠራሉ:- “ከኃጢአት ጋር እየተጋደላችሁ ገና ደምን እስከ ማፍሰስ ድረስ አልተቃወማችሁም።” (ዕብራውያን 12:4) የሆነ ሆኖ በዚህ ሥርዓት ውስጥ የእውነት መንገድ ለማንኛችንም ቢሆን ቀላል አይደለም። አንዳንዶች በሥራ ቦታ ወይም በትምህርት ቤት መዘበቻ በመሆናቸው ወይም ኃጢአት እንዲሠሩ ግፊት ስለሚደረግባቸው ‘በኃጢአተኞች ተቃውሞ’ ተስፋ ቆርጠዋል። (ዕብራውያን 12:3) ከበድ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች አንዳንዶች የአምላክን ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ጠብቀው ለመመላለስ ያደረጉትን ቁርጥ ውሳኔ አላልተውባቸዋል። (ዕብራውያን 13:4, 5) ከሃዲዎች ለሚያሰራጩት መርዘኛ ፕሮፓጋንዳ ጆሮአቸውን የሰጡ ጥቂቶች መንፈሳዊ ሚዛናቸውን ስተዋል። (ዕብራውያን 13:9) ሌሎች ደግሞ የባሕርይ አለመጣጣም ደስታቸውን ነጥቋቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ለመዝናኛና ለእረፍት ጊዜ ማሳለፊያዎች ከልክ ያለፈ ትኩረት በመስጠታቸው ተዳክመዋል። እንዲሁም አብዛኞቹ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ባሉት የኑሮ ችግሮች ይደቆሳሉ።
17 ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል የትኛውም ቢሆን ‘እስከ ደም ድረስ ትግል’ እንደማይጠይቅ አይካድም። አንዳንዶቹም እኛ ራሳችን ከምናደርጋቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች የሚመነጩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁንና ሁሉም እምነታችንን የሚፈታተኑ ነገሮች ናቸው። ዓይናችን ድንቅ በሆነው የኢየሱስ የጽናት ምሳሌ ላይ ማተኮር ያለበትም ለዚህ ነው። ተስፋችን ምን ያክል ውድ እንደሆነ ዘወትር እናስታውስ። ይሖዋ ‘ከልባቸው የሚፈልጉትን ሰዎች መልሶ እንደሚክስ’ ያለን የጸና እምነት እንዳይጠፋ እንጠብቅ። (ዕብራውያን 11:6) ከዚያ በኋላ በሕይወት ሩጫ ወደፊት ለመግፋት የሚያስችለው መንፈሳዊ ጥንካሬ ይኖረናል።
መጽናት እንችላለን
18, 19. በኢየሩሳሌም የነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት የሰጣቸውን ምክር እንደተቀበሉ የሚያሳየው ታሪካዊ ክስተት የትኛው ነው?
18 አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ለጳውሎስ ደብዳቤ ምን ምላሽ ሰጡ? ለዕብራውያን ሰዎች የተላከው ደብዳቤ ከተጻፈ ከስድስት ዓመታት በኋላ ይሁዳ ጦርነት ውስጥ ገባች። ኢየሱስ በተናገራቸው ቃላት ፍጻሜ መሠረት በ66 እዘአ የሮማ ሠራዊት ኢየሩሳሌምን ከበበ። ኢየሱስ “ኢየሩሳሌም ግን በጭፍራ ተከባ ስታዩ በዚያን ጊዜ ጥፋትዋ እንደ ቀረበ እወቁ” ብሎ ነበር። (ሉቃስ 21:20) ይሁን እንጂ ኢየሱስ በወቅቱ በኢየሩሳሌም ውስጥ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች ጥቅም ሲል እንዲህ ብሏል:- “የዚያን ጊዜ በይሁዳ ያሉ ወደ ተራራዎች ይሽሹ፣ በመካከልዋም ያሉ ከእርስዋ ፈቀቅ ይበሉ፣ በገጠር ያሉም ወደ እርስዋ አይግቡ።” (ሉቃስ 21:21) በመሆኑም ከሮማውያን ጋር የተደረገው ጦርነት ፈታኝ ነበር። እነዚያ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የአይሁዳውያን የአምልኮ ማዕከልና የክብራማው ቤተ መቅደስ መቀመጫ የሆነችውን ኢየሩሳሌምን ትተው ይሄዱ ይሆን?
19 ድንገት፣ በውል በማይታወቅ ምክንያት ሮማውያኑ ወደኋላ አፈገፈጉ። ሃይማኖታዊ የሆኑት አይሁዳውያን አምላክ ቅዱሷን ከተማቸውን እንደሚጠብቅ የሚያሳይ ማስረጃ አድርገው ተመልክተውት እንደሚሆን ግልጽ ነው። ክርስቲያኖችስ? ክርስቲያኖቹ ከተማዋን ጥለው እንደሸሹ ታሪክ ያረጋግጥልናል። ከዚያም በ70 እዘአ ሮማውያኑ ተመልሰው መጡና ኢየሩሳሌምን ሙሉ በሙሉ አጠፏት፤ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ እልቂትም ተፈጸመ። ኢዩኤል አስቀድሞ የተናገረለት ‘የይሖዋ ቀን’ በኢየሩሳሌም ላይ መጥቶ ነበር። ይሁን እንጂ የታመኑ ክርስቲያኖች በዚያ አልተገኙም። ከመዓቱ ‘ድነዋል።’—ኢዩኤል 2:30-32፤ ሥራ 2:16-21
20. ታላቁ ‘የይሖዋ ቀን’ ቅርብ እንደሆነ ማወቃችን ምን እንድናደርግ ሊያንቀሳቅሰን ይገባል?
20 ዛሬ ይህን የነገሮች ሥርዓት በጠቅላላ የሚያናጋ ሌላ ታላቅ ‘የይሖዋ ቀን’ በቅርቡ እንደሚመጣ ተገንዝበናል። (ኢዩኤል 3:12-14) ይህ ቀን መቼ እንደሚመጣ ግን አናውቅም። ይሁን እንጂ መምጣቱ አይቀሬ እንደሆነ የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል! ይሖዋም አይዘገይም ሲል ተናግሯል። (ዕንባቆም 2:3፤ 2 ጴጥሮስ 3:9, 10) እንግዲያው ‘ለሰማነው ነገር አብልጠን እንጠንቀቅ።’ “ቶሎ የሚከብበንን ኃጢአት” ማለትም እምነት ማጣትን እናስወግድ። ሥርዓቱ የቱንም ያህል ቢቆይ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። ታላቁ ሰረገላ መሰል የይሖዋ ሰማያዊ ድርጅት በእንቅስቃሴ ላይ እንዳለ አንዘንጋ። ዓላማውን ከግብ ያደርሳል። እንግዲያውስ ሁላችንም መሮጣችንን እንቀጥል፤ ለሕይወት በሚደረገው ሩጫ ተስፋ ቆርጠን አናቁም!
ታስታውሳለህን?
◻ ለሕይወት በምናደርገው ሩጫ እንድንጸና የሚረዳን ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች የሰጠውን የትኛውን ምክር ማስታወሳችን ነው?
◻ ይህ ዓለም ያለውን የማዘናጋት ባሕርይ ለመዋጋት ምን ነገር ይረዳናል?
◻ በሩጫው ለመጽናት አንዳችን ሌላውን ልንረዳ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን በሩጫው ወደ ኋላ እንዲል የሚያደርጉት አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?
◻ የኢየሱስ ምሳሌ እንድንጸና ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 8, 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ልክ እንደ ሯጮች ምንም ነገር እንዲያዘናጋቸው ሊፈቅዱ አይገባም
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላቁን የይሖዋ ሰማያዊ ሰረገላ የአምላክን ዓላማ ከመፈጸም ሊገታው የሚችል ነገር የለም