አመለካከትህ ብሩህ ነው ወይስ አፍራሽ?
“አስደሳች ጊዜ ነበር፣ አስከፊ ጊዜ ነበር፣ . . . ልብን በተስፋ የሚሞላ ነበር፣ የጭንቅ ጊዜ ነበር፣ ሁሉ ነገር ነበረን፣ ምንም አልነበረንም።” የቻርለስ ዲከንስ ምርጥ የስነ ጽሑፍ ሥራ የሆነው የሁለት ከተሞች ወግ የተባለው መጽሐፍ የመክፈቻ ቃላት የሁኔታዎች መለዋወጥ በአስተሳሰባችን፣ በስሜቶቻችንና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ባለን አመለካከት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ በሚገባ ገልጸዋል።
በጽሑፉ ላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ከተሞች በፈረንሳይ አብዮት ወቅት በብጥብጥ ይታመሱ የነበሩት ለንደንና ፓሪስ ናቸው። በ18ኛው መቶ ዘመን ለነበሩት የፈረንሳይ ጭቁን ዜጎች አብዮቱ ስለ ሰው መብቶች ይነዛ የነበረው አዋጅ በእርግጥም “ልብን በተስፋ የሚሞላ ነበር።” ይሁን እንጂ ቀደም ሲል ለነበረው መንግሥት ወይም ቦታውን ለሚለቀው የፖለቲካ ሥርዓት ደግሞ የሞትና የሽረት ወይም “የጭንቅ ጊዜ” ነበር።
ብሩህ አመለካከት ወይስ አፍራሽ አመለካከት? ሁሉም ነገር የተመካው አንተ በመረጥከው ጎራ ነበር። አሁንም ቢሆን ተመሳሳይ ነው።
ራስህን የምትመረምርበት ጊዜ
አመለካከትህ ብሩህ ነው? ሁልጊዜ የተሻለ ነገር ይመጣል ብለህ እያሰብክ የሕይወትን አስደሳች ገጽታ ትመለከታለህ? ወይስ የተሻለ ጊዜ እንዲመጣ ብትፈልግም የከፋ ነገር ይመጣል ብለህ በመጠባበቅ ስለ ወደፊት ጊዜህ አፍራሽ አመለካከት ወደ መያዝ ታዘነብላለህ?
ከስልሳ ዓመታት በፊት አሜሪካዊው የልብ ወለድ ደራሲ ጄምስ ብራንች ካቤል እነዚህን ሁለት ተቃራኒ ፍልስፍናዎች እንዲህ በማለት በአጭሩ አስቀምጠዋቸዋል:- “አመለካከቱ ብሩህ የሆነ ሰው የምንኖረው ከሁሉ በተሻለው ዓለም ውስጥ እንደሆነ ይናገራል፤ አፍራሽ አመለካከት ያለው ሰው ደግሞ ይህ እውነት መሆኑን ይጠራጠራል።” ይህ አመለካከት ወደ ጥርጣሬ ያደላ ሆኖ ከተሰማህ አሁን ስላለው ዓለም ቀጥሎ የቀረቡትን አዎንታዊና አሉታዊ ጎን የሚገልጹ ሦስት ዘርፎች ተመልከት። ከዚያም የተሰማህን ስሜት መርምርና አመለካከቴ ብሩህ ነው ወይስ አፍራሽ? ብለህ ራስህን ጠይቅ።
ዘላቂ ሰላም:- በዓለም ውስጥ ግጭቶች ካሉባቸው ቦታዎች ስንቶቹን መጥቀስ ትችላለህ? እንደ አየርላንድ፣ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ቡሩንዲና ሩዋንዳ የመሳሰሉት ቦታዎች ቶሎ ወደ አእምሮህ እንደሚመጡ ግልጽ ነው። ዘላቂና ዓለም አቀፋዊ ሰላምን ለማምጣት እነዚህና ሌሎችም ትግሎች መፍትሔ ያገኙ ይሆን? ዓለም ወደ ሰላም እያመራች ነውን?
የኢኮኖሚ መረጋጋት:- በ1999 በአንድ ገንዘብ ለመገልገል የሚያስቡት የአውሮፓ ኅብረት አገሮች የዋጋ ግሽበትና ከሕዝብ መበደር ያስከተሏቸው አሳሳቢ ችግሮች ተጋርጠውባቸዋል። በሌሎች ቦታዎች ደግሞ የዋጋ ግሽበት የማይወጡት ሸክም በሆነባቸውና የጎሣ ግጭቶች አሁንም ሰዎችን በሚከፋፍሉባቸው በርካታ የአሜሪካና የአፍሪካ አገሮች ሙስና ኢኮኖሚያዊ ተቋማቸውን በማፈራረስ ላይ ይገኛል። የዓለም ኢኮኖሚ የሚረጋጋበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣልን?
ሥራ አጥነት:- በ1997 በተካሄደው ብሔራዊ ምርጫ የብሪታንያ አብያተ ክርስቲያናት ምክር ቤት ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሰፊ የሥራ መስኮች መክፈትን በአጀንዳቸው ላይ ቅድሚያ ሰጥተው እንዲወያዩበት አሳስበው ነበር። ይሁን እንጂ በሥራው ዓለም ተሰማርተው የመሥራት ብቃት ካላቸው ሰዎች መካከል 30 በመቶ የሚሆኑት ሥራ አጥ ከሆኑ ወይም አጥጋቢ ሥራ ከሌላቸው በተለይ ለወጣቶች ቋሚ የሆነ የሙሉ ጊዜ ሥራ ሊኖር ይችላልን?
ስለ ወደፊቱ ጊዜ አፍራሽ አመለካከት መያዝ እንዴት ቀላል ነው! ሆኖም ብሩህ አመለካከት ለመያዝ የሚያስችል መሠረት አለ። ብሩህ አመለካከት ማዳበር የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንድትመረምር እንጋብዝሃለን።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የፈረንሳይ አብዮት
[ምንጭ]
ፒክቶሪያል ሂስትሪ ኦቭ ዘ ዎርልድ ከተባለው መጽሐፍ