“ሞት ይሻራል”
“የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው።” —1 ቆሮንቶስ 15:26
1, 2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ ሙታን ምን ተስፋ እንዳላቸው ተናግሯል? (ለ) ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ምን ጥያቄ አቅርቧል?
የካቶሊክና የፕሮቴስታንት የእምነት ጸሎት “በሥጋ ትንሣኤና በዘላለም ሕይወት አምናለሁ” ይላል። የዚህ እምነት ተከታዮች ይህን ጸሎት መጸለይ እንዳለባቸው ስለሚሰማቸው በየጊዜው ይደግሙታል። ሆኖም እምነታቸው ከሐዋርያት እምነት ጋር ሳይሆን ከግሪክ ፍልስፍና ጋር ይበልጥ የሚመሳሰል መሆኑን አልተገነዘቡም። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ የግሪክ ፍልስፍናን አልተቀበለም፤ ነፍስ አትሞትም የሚል እምነትም አልነበረውም። ነገር ግን ወደፊት በሚኖረው ሕይወት ላይ ጠንካራ እምነት ስለነበረው “የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” ሲል በመንፈስ ተገፋፍቶ ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 15:26) ሟች ለሆነው የሰው ዘር ይህ ምን ማለት ይሆናል?
2 መልሱን ለማግኘት ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ማብራሪያ ወደሰጠበት ወደ 1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 እንመለስ። ጳውሎስ በምዕራፉ መክፈቻ ቁጥሮች ላይ ትንሣኤ የክርስቲያን መሠረተ ትምህርት ዐቢይ ክፍል መሆኑን እንደገለጸ ታስታውሳላችሁ። አሁን ደግሞ አንድ ቀጥተኛ ጥያቄ ይጠይቃል:- “ነገር ግን ሰው:- ሙታን እንዴት ይነሣሉ? በምንስ ዓይነት አካል ይመጣሉ? የሚል ይኖር ይሆናል።”—1 ቆሮንቶስ 15:35
ምን ዓይነት አካል?
3. አንዳንዶች ትንሣኤን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?
3 ጳውሎስ ይህን ጥያቄ ሲያነሣ የፕላቶ ፍልስፍና ያሳደረውን ተጽእኖ ለመከላከል አቅዶ መሆን አለበት። ፕላቶ፣ አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ከአካሉ ተለይታ የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለችው ሲል አስተምሯል። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ላዳበሩ ሰዎች ክርስትና የሚያስተምረው የትንሣኤ ትምህርት አላስፈላጊ ነው። ነፍስ የማትሞት ከሆነ ትንሣኤ ምን ትርጉም ይኖረዋል? በተጨማሪም ትንሣኤ ተዓማኒነት የሌለው ይመስል ነበር። አካል አንዴ አፈር ከሆነ በኋላ እንዴት ትንሣኤ ሊኖር ይችላል? አንዳንድ የቆሮንቶስ ሰዎች ትንሣኤን የተቃወሙት “አካል የተገነባባቸው ንጥረ ነገሮች ተመልሰው ሊገጣጠሙ አይችሉም የሚለውን ፍልስፍና መሠረት” አድርገው ሊሆን እንደሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ሄንሪክ ሜየር ተናግረዋል።
4, 5. (ሀ) እምነተ ቢስ የሆኑ ሰዎች ያቀረቡት ተቃውሞ መሠረተ ቢስ የነበረው ለምንድን ነው? (ለ) ጳውሎስ ስለ “ቅንጣት” የተናገረውን ምሳሌ አብራራ። (ሐ) አምላክ ከሞት ለሚነሡት ቅቡዓን ምን ዓይነት አካል ይሰጣቸዋል?
4 ጳውሎስ የአስተሳሰባቸውን ባዶነት ሲያጋልጥ እንዲህ ብሏል:- “አንተ ሞኝ፣ አንተ የምትዘራው ካልሞተ ሕያው አይሆንም፤ የምትዘራውም፣ ስንዴ ቢሆን ከሌላም ዓይነት የአንዱ ቢሆን፣ ቅንጣት ብቻ ነው እንጂ የምትዘራው የሚሆነውን አካል አይደለም፤ እግዚአብሔር ግን እንደ ወደደ አካልን ይሰጠዋል ከዘሮችም ለእያንዳንዱ የገዛ አካሉን ይሰጠዋል።” (1 ቆሮንቶስ 15:36-38) አምላክ፣ ሰዎች በምድር ላይ በነበሩበት ጊዜ ተላብሰውት የነበረውን ያንኑ አካል መልሶ አያስነሣም። ከዚህ ይልቅ ለውጥ ይካሄዳል።
5 ጳውሎስ ትንሣኤን ከሚያቆነጉል ዘር ጋር አመሳስሎታል። አንዲት ትንሽ የስንዴ ዘር ከእሷ በመውጣት ከሚያድገው ተክል ጋር በምንም መንገድ አትመሳሰልም። ዘ ዎርልድ ቡክ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ ይላል:- “አንድ ዘር ማጎንቆል ሲጀምር ከፍተኛ መጠን ያለው ውኃ ይወስዳል። ውኃው በዘሩ ውስጥ ብዙ ኬሚካላዊ ለውጦች እንዲካሄዱ ያደርጋል። በተጨማሪም በዘሩ ውስጥ የሚገኙት ሕብረ ሕዋሳት እንዲያብጡና ገለፈቱን ቀድደው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል።” በሌላ አባባል ዘሩ ዘር ሆኖ ይሞትና የሚያድግ ተክል ሆኖ ብቅ ይላል። የዘሩን እድገት የሚቆጣጠሩት ሳይንሳዊ ሕግጋት ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ በማድረግ አምላክ ለእያንዳንዱ ዘር እንደ ዓይነቱ “አካልን ይሰጠዋል።” (ዘፍጥረት 1:11) በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመጀመሪያ እንደ ማንኛውም ሰው ይሞታሉ። ከዚያም አምላክ በቀጠረው ጊዜ ሙሉ በሙሉ አዲስ የሆነ አካል በመስጠት ወደ ሕይወት መልሶ ያመጣቸዋል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች “[ኢየሱስ ክርስቶስ] . . . ክቡር ሥጋውን እንዲመስል የተዋረደውን ሥጋችንን ይለውጣል” በማለት ተናግሯል። (ፊልጵስዩስ 3:20, 21፤ 2 ቆሮንቶስ 5:1, 2) መንፈሳዊ አካል ይዘው በመነሣት በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ይኖራሉ።—1 ዮሐንስ 3:2
6. አምላክ ከሞት ለሚነሡት ተገቢውን መንፈሳዊ አካል ሊሰጣቸው ይችላል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?
6 ይህ ለማመን እጅግ አስቸጋሪ ነውን? አይደለም። ጳውሎስ እንስሳት ብዙ የተለያየ አካል እንዳላቸው ገልጿል። በተጨማሪም ሰማይ በሚኖሩ መላእክትና ሥጋና ደም ባላቸው ሰዎች መካከል ስላለው ልዩነት ሲናገር “ሰማያዊ አካል አለ፣ ምድራዊም አካል አለ” ብሏል። ግዑዝ ፍጥረታትም ዓይነታቸው ብዙ ነው። ሳይንስ ሰማያዊ፣ ቀይና ነጭ ቀለም ያላቸው እጅግ ግዙፍ ከዋክብት መኖራቸውን ከማወቁ ከረጅም ጊዜ በፊት ጳውሎስ “በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያልና” ብሎ ነበር። አምላክ በትንሣኤ ለሚነሡ ቅቡዓን ተስማሚ የሆነ መንፈሳዊ አካል ሊሰጣቸው እንደሚችል ከዚህ መገንዘብ አይቻልም?—1 ቆሮንቶስ 15:39-41
7. የማይበሰብስ ማለት ምን ማለት ነው? የማይሞትስ?
7 ከዚህ በመቀጠል ጳውሎስ “የሙታን ትንሣኤ ደግሞ እንዲሁ ነው። በመበስበስ ይዘራል፣ ባለመበስበስ ይነሣል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:42) ሰብዓዊ አካል፣ ፍጹም ሆኖም እንኳ ሊበሰብስ ይችላል። ፍጹም ሰብዓዊ አካልን መግደል ይቻላል። ለምሳሌ ያህል ጳውሎስ ከሞት የተነሣው ኢየሱስ ‘እንደ ገና ወደ መበስበስ እንደማይመለስ’ ተናግሮ ነበር። (ሥራ 13:34) ኢየሱስ ፍጹም ቢሆንም እንኳ ሊበሰብስ የሚችለውን ሰብዓዊ አካል ለብሶ ወደ ሕይወት በጭራሽ አይመለስም። አምላክ ከሞት ለሚነሱት ቅቡዓን የሚሰጠው አካል የማይጠፋ ማለትም የማይሞትና የማይበሰብስ ነው። ጳውሎስ በመቀጠል “በውርደት ይዘራል፣ በክብር ይነሣል፤ በድካም ይዘራል፣ በኃይል ይነሣል፤ ፍጥረታዊ አካል ይዘራል፣ መንፈሳዊ አካል ይነሣል” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:43, 44) በተጨማሪም ጳውሎስ “ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሊለብስ ይገባዋልና” በማለት ተናግሯል። የማይሞት ማለት ፍጻሜ የሌለው፣ የማይጠፋ ሕይወት ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:53፤ ዕብራውያን 7:16) በዚህ ዓይነት ከሞት የሚነሱት ቅቡዓን “የሰማያዊውን መልክ” ማለትም ትንሣኤ እንዲያገኙ ያስቻላቸውን የኢየሱስን መልክ ይይዛሉ።—1 ቆሮንቶስ 15:45-49
8. (ሀ) በትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች ቀደም ሲል በምድር ላይ በሕይወት ይኖሩ የነበሩት እነዚያው ግለሰቦች መሆናቸውን እንዴት እናውቃለን? (ለ) ትንሣኤ በሚከናወንበት ጊዜ የትኞቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ?
8 እንዲህ ዓይነቱን ሁለንተናዊ ለውጥ ያድርጉ እንጂ በትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች ከመሞታቸው በፊት የነበሩት እነዚያው ግለሰቦች ናቸው። ቀድሞ የነበሯቸውን ትዝታዎችና ውድ የሆኑ ክርስቲያናዊ ባሕርያት ይዘው ይነሣሉ። (ሚልክያስ 3:3፤ ራእይ 21:10, 18) በዚህ ረገድ ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ይመሳሰላሉ። ከመንፈሳዊ አካል ወደ ሰብዓዊ አካል ተለወጠ። ከሞተ በኋላ መንፈስ ሆኖ ተነሣ። ሆኖም “ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ለዘላለምም ያው ነው።” (ዕብራውያን 13:8) ቅቡዓኑ እንዴት ያለ ክብራማ መብት አላቸው! ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ዳሩ ግን ይህ የሚበሰብሰው የማይበሰብሰውን ሲለብስ ይህም የሚሞተው የማይሞተውን ሲለብስ፣ በዚያን ጊዜ:- ሞት ድል በመነሣት ተዋጠ ተብሎ የተጻፈው ቃል ይፈጸማል። ሞት ሆይ፣ መውጊያህ የት አለ? ሲኦል (“ሞት፣” የ1980 ትርጉም) ሆይ፣ ድል መንሣትህ የት አለ?”—1 ቆሮንቶስ 15:54, 55፤ ኢሳይያስ 25:8፤ ሆሴዕ 13:14
ምድራዊ ትንሣኤ ይኖራል?
9, 10. (ሀ) በ1 ቆሮንቶስ 15:24 ላይ የተገለጸው “ፍጻሜ” የሚያመለክተው ምንድን ነው? ከእሱ ጋር በተያያዘስ ምን ሁኔታዎች ይፈጸማሉ? (ለ) ሞት እንዲሻር ምን ነገር መፈጸም አለበት?
9 በሰማይ የማይሞት መንፈሳዊ ሕይወት የማግኘት ተስፋ የሌላቸው በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የወደፊት ተስፋ አላቸውን? በእርግጥ አላቸው! ጳውሎስ ሰማያዊው ትንሣኤ በክርስቶስ መገኘት ጊዜ እንደሚፈጸም ካብራራ በኋላ ቀጥለው ስለሚመጡ ክንውኖች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በኋላም፣ መንግሥቱን ለእግዚአብሔር ለአባቱ አሳልፎ በሰጠ ጊዜ አለቅነትንም ሁሉና ሥልጣንን ሁሉ ኃይልንም በሻረ ጊዜ፣ ፍጻሜ ይሆናል።”—1 ቆሮንቶስ 15:23, 24
10 “ፍጻሜ” የተባለው የክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ፍጻሜ ሲሆን በዚያን ጊዜም ኢየሱስ በትሕትናና በታማኝነት መንግሥቱን ለአምላኩና ለአባቱ ያስረክባል። (ራእይ 20:4) በዚያን ጊዜ አምላክ የነበረው ‘ሁሉን በክርስቶስ የመጠቅለል’ ዓላማ ፍጻሜውን ያገኛል። (ኤፌሶን 1:9, 10) አስቀድሞ ግን ክርስቶስ የአምላክን ሉዓላዊ ፈቃድ የሚቃወመውን ‘አለቅነት ሁሉ፣ ሥልጣን ሁሉና ኃይል’ ያጠፋል። ይህ በአርማጌዶን ከሚመጣው ጥፋት የበለጠ ነገርን ያካትታል። (ራእይ 16:16፤ 19:11-21) ጳውሎስ “[ክርስቶስ] ጠላቶቹን ሁሉ ከእግሩ በታች እስኪያደርግ ድረስ ሊነግሥ ይገባዋልና። የኋለኛው ጠላት የሚሻረው ሞት ነው” ብሏል። (1 ቆሮንቶስ 15:25, 26) አዎን፣ የአዳማዊ ኃጢአትና ሞት ርዝራዥ ተጠራርጎ ይጠፋል። ከዚያም አምላክ ሙታንን ወደ ሕይወት መልሶ በማምጣት ‘የመታሰቢያ መቃብሮችን’ ባዶ ያደርጋል።—ዮሐንስ 5:28 NW
11. (ሀ) አምላክ የሞቱ ነፍሳትን እንደገና ሊፈጥር እንደሚችል እንዴት እናውቃለን? (ለ) በምድር ላይ ለመኖር የሚነሡት ሰዎች ምን ዓይነት አካል ይኖራቸዋል?
11 ይህ ማለት የሰዎችን ነፍስ እንደገና መፍጠር ማለት ነው። የማይቻል ነገር ይሆን? የለም፣ መዝሙር 104:29, 30 አምላክ ሊያደርገው እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጣል:- “ነፍሳቸውን [“መንፈሳቸውን፣” NW] ታወጣለህ ይሞታሉም፣ ወደ አፈራቸውም ይመለሳሉ። መንፈስህን ትልካለህ ይፈጠራሉም።” በትንሣኤ የሚነሡት ሰዎች ከመሞታቸው በፊት የነበሩት እነዚያው ግለሰቦች ቢሆኑም ቀደም ሲል የነበራቸውን አካል ይዘው መነሣት አያስፈልጋቸውም። አምላክ ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት ለሚያገኙት እንደሚያደርገው ሁሉ ለእነዚህም የወደደውን አካል ይሰጣቸዋል። አዲሱ አካላቸው ጤናማ እንደሚሆንና የሚወዷቸው ሰዎች ሊያውቋቸው እንዲችሉ በመጀመሪያ ከነበራቸው አካል ጋር የሚመሳሰል እንደሚሆን አያጠራጥርም።
12. ምድራዊው ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው?
12 ምድራዊው ትንሣኤ የሚከናወነው መቼ ነው? ማርታ ስለ ሞተው ወንድሟ ስለ አልዓዛር ስትናገር “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ” ብላለች። (ዮሐንስ 11:24) ይህን እንዴት ልታውቅ ቻለች? ፈሪሳውያን በትንሣኤ ሲያምኑ ሰዱቃውያን ግን አያምኑም ነበር፤ በመሆኑም ትንሣኤ በወቅቱ የመከራከሪያ ርዕስ ሆኖ ነበር። (ሥራ 23:8) ይሁንና ማርታ በትንሣኤ ተስፋ ያምኑ ስለነበሩ ከክርስትና በፊት የነበሩ ምሥክሮች ሳታውቅ አትቀርም። (ዕብራውያን 11:35) ከዚህም በላይ ትንሣኤ በመጨረሻው ቀን እንደሚፈጸም ከዳንኤል 12:13 ተረድታ ይሆናል። ከራሱ ከኢየሱስም ተምራ ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 6:39) ይህ ‘የመጨረሻ ቀን’ ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ጋር ይገጣጠማል። (ራእይ 20:6) ይህ ታላቅ ክንውን በሚጀምርበት “ቀን” የሚኖረውን የደስታ ስሜት እስቲ አስበው!—ከሉቃስ 24:41 ጋር አወዳድር።
የሚነሱት እነማን ናቸው?
13. ትንሣኤን በተመለከተ በራእይ 20:12-14 ላይ ምን ራእይ ተመዝግቦ ይገኛል?
13 ስለ ምድራዊው ትንሣኤ የሚገልጸው የዮሐንስ ራእይ፣ በራእይ 20:12-14 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል:- “ሙታንንም ታናናሾችንና ታላላቆችን በዙፋኑ ፊት ቆመው አየሁ፣ መጻሕፍትም ተከፈቱ፤ ሌላ መጽሐፍም ተከፈተ እርሱም የሕይወት መጽሐፍ ነው፤ ሙታንም በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ተከፈሉ። ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትን ሙታን ሰጠ፣ ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፣ እያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን ተከፈለ። ሞትና ሲኦልም በእሳት ባሕር ውስጥ ተጣሉ። ይህም የእሳት ባሕር ሁለተኛው ሞት ነው።”
14. በትንሣኤ ከሚነሡት መካከል እነማን ይገኙበታል?
14 ትንሣኤ በሕይወት ኖረው የሞቱ “ታናናሾችንና ታላላቆችን፣” ስመ ጥር የነበሩትንም ሆነ ተራ ሰዎችን የሚያቅፍ ይሆናል። ሕፃናት ሳይቀሩ ይነሣሉ! (ኤርምያስ 31:15, 16) በሥራ 24:15 ላይ አንድ ሌላ አስፈላጊ ነገር ተገልጿል:- “ጻድቃንም ዓመፀኞችም ከሙታን [ይነሣሉ]።” “ጻድቃን” ከተባሉት ውስጥ እንደ አቤል፣ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራና ረዓብ የመሳሰሉ የጥንት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ይገኙበታል። (ዕብራውያን 11:1-40) በጥንት ጊዜ ለተፈጸሙ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ክንውኖች የዓይን ምሥክሮች ከነበሩ ሰዎች ጋር ለመነጋገርና ከእነሱም ዝርዝር ሐሳቦችን ለመስማት መቻሉ ምንኛ የሚያስደስት ይሆናል! “ጻድቃን” የሚለው አነጋገር ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸውን በቅርብ ጊዜ የሞቱ በሺህ የሚቆጠሩ ፈሪሃ አምላክ የነበራቸው ግለሰቦችም ይጨምራል። ከእነዚህ መካከል የቤተሰብህ አባል የሆነ ወይም የምትወደው ወዳጅህ ይኖር ይሆን? እንደገና ልታያቸው እንደምትችል ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ይሁንና ይነሳሉ የተባሉት “ዓመፀኞች” እነማን ናቸው? የመጽሐፍ ቅዱስ እውነትን ለመማርና ተግባራዊ ለማድረግ አጋጣሚውን ያላገኙ በሚልዮን፣ ምናልባትም በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ናቸው።
15. ዳግመኛ ሕያው የሚሆኑት ሰዎች ‘በመጻሕፍት ተጽፎ እንደነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድ ይቀበላሉ’ ሲባል ምን ማለት ነው?
15 እነዚህ ዳግመኛ ሕያው የሚሆኑ ሰዎች ‘በመጻሕፍት ተጽፎ እንደ ነበረ እንደ ሥራቸው መጠን ፍርድ የሚቀበሉት’ እንዴት ነው? እነዚህ መጻሕፍት ቀደም ሲል የሠሯቸውን ሥራዎች ዘግበው የያዙ አይደሉም፤ በሞቱበት ጊዜ በሕይወት ዘመናቸው ከፈጸሟቸው ኃጢአቶች ነፃ ወጥተዋል። (ሮሜ 6:7,23) ይሁን እንጂ ከሞት ከተነሡም በኋላ ቢሆን በአዳማዊ ኃጢአት ሥር ይሆናሉ። እንግዲያው እነዚህ መጻሕፍት ከኢየሱስ ክርስቶስ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚዎች ለመሆን እንዲችሉ ሊከተሏቸው የሚገቡትን መለኮታዊ መመሪያዎች የያዙ መሆን አለባቸው። የአዳማዊ ኃጢአት የመጨረሻ ርዝራዥ ከተወገደ በኋላ ‘ሞት ሙሉ በሙሉ ይሻራል።’ በሺህ ዓመቱ ማብቂያ ላይ አምላክ ‘ሁሉ በሁሉ ይሆናል።’ (1 ቆሮንቶስ 15:28) ከዚያ በኋላ ሰው ሊቀ ካህናት ወይም ቤዛ አያስፈልገውም። ሁሉም የሰው ዘር አዳም በመጀመሪያ ወደ ነበረው የፍጽምና ደረጃ ይደርሳል።
በሥርዓት የሚከናወን ትንሣኤ
16. (ሀ) ትንሣኤ በሥርዓት የሚከናወን ሂደት ይሆናል ብሎ ማመኑ ምክንያታዊ የሚሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በቅድሚያ የሚነሡት እነማን ሳይሆኑ አይቀሩም?
16 ሰማያዊው ትንሣኤ በሥርዓት እንደሚከናወን ማለትም “እያንዳንዱ በራሱ ተራ” እንደሚነሳ ሁሉ ምድራዊውም ትንሣኤ የሕዝብ ቁጥር ፍንዳታ በማስከተል ትርምስ እንደማይፈጥር የተረጋገጠ ነው። (1 ቆሮንቶስ 15:23) በትንሣኤ የሚነሡት አዳዲስ ሰዎች እንክብካቤ እንደሚያስፈልጋቸው እሙን ነው። (ከሉቃስ 8:55 ጋር አወዳድር።) የሚበሉት ምግብ ያስፈልጋቸዋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕይወት የሚያስገኝላቸውን ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውቀት መቅሰም ይችሉ ዘንድ መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት አለባቸው። (ዮሐንስ 17:3) ሁሉም ወደ ሕይወት የሚመለሱት በተመሳሳይ ጊዜ ቢሆን ኖሮ ለእነሱ ተገቢ እንክብካቤ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆን ነበር። ትንሣኤ ደረጃ በደረጃ ይከናወናል ብሎ መገመቱ ምክንያታዊ ነው። የሰይጣን ሥርዓት ከመጥፋቱ ከጥቂት ጊዜ በፊት የሞቱ ታማኝ ክርስቲያኖች በመጀመሪያ ከሚነሡት መካከል የሚሆኑ ይመስላል። በተጨማሪም የጥንት ታማኝ ሰዎች “ገዥዎች” ሆነው ለማገልገል ቀድመው እንደሚነሡ ልንጠብቅ እንችላለን።—መዝሙር 45:16 NW
17. ትንሣኤን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ መግለጫ የማይሰጥባቸው አንዳንድ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ክርስቲያኖችስ ስለ እነዚህ ጉዳዮች ከመጠን በላይ ማሰብ የማይገባቸው ለምንድን ነው?
17 ሆኖም እነዚህን በመሳሰሉ ጉዳዮች ላይ ድርቅ ያለ አቋም ልንይዝ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ጉዳዮች ላይ የሚሰጠው ዝርዝር መግለጫ የለም። የግለሰቦች ትንሣኤ እንዴት፣ መቼ ወይም የት እንደሚከናወን ዝርዝር ማብራሪያ አይሰጥም። ወደ ሕይወት የተመለሱት እነዚህ ሰዎች መኖሪያ ቤት፣ ምግብና ልብስ ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አይነግረንም። በትንሣኤ የሚነሡ ልጆች የሚያድጉትና እንክብካቤ የሚደረግላቸው እንዴት እንደሆነ ወይም ጓደኞቻችንንና የምንወዳቸውን ሰዎች በሚመለከቱ አንዳንድ ሁኔታዎች ይሖዋ ስለሚያደርጋቸው ነገሮች በእርግጠኝነት ለመናገር አንችልም። እርግጥ ስለነዚህ ጉዳዮች ማሰቡ ያለ ነገር ነው፤ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ መልስ ለማይገኝላቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በመሞከር ጊዜ ማጥፋቱ ጥበብ የጎደለው ተግባር ነው። ሙሉ ትኩረታችን ይሖዋን በታማኝነት በማገልገሉና ዘላለማዊ ሕይወት በማግኘቱ ላይ ሊሆን ይገባል። ቅቡዓን ክርስቲያኖች ክብራማ በሆነ ሰማያዊ ትንሣኤ ላይ ተስፋቸውን ይጥላሉ። (2 ጴጥሮስ 1:10, 11) “ሌሎች በጎች” ደግሞ በአምላክ መንግሥት ምድራዊ ግዛት ውስጥ ዘላለማዊ ውርሻ ለማግኘት ተስፋ ያደርጋሉ። (ዮሐንስ 10:16፤ ማቴዎስ 25:33, 34) ስለ ትንሣኤ የማናውቃቸው ብዙ ዝርዝር ጉዳዮች ቢኖሩም በይሖዋ እንታመናለን። ወደፊት የምናገኘው ደስታ ‘ሕይወት ላለው ሁሉ መልካምን በሚያጠግበው’ አምላክ እጅ ውስጥ ያለ በመሆኑ አስተማማኝ ነው።—መዝሙር 145:16፤ ኤርምያስ 17:7
18. (ሀ) ጳውሎስ ጎላ አድርጎ የገለጸው የትኛውን ድል ነው? (ለ) በትንሣኤ ተስፋ ሙሉ በሙሉ ልንተማመን የምንችለው ለምንድን ነው?
18 ጳውሎስ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ድል መንሣትን ለሚሰጠን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በሚሉት ቃላት ያቀረበውን የመከራከሪያ ሐሳብ ይደመድማል። (1 ቆሮንቶስ 15:57) አዎን፣ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት አዳማዊ ሞት ድል ይደረጋል፤ እንዲሁም ቅቡዓኑም ሆኑ “ሌሎች በጎች” የድሉ ተካፋይ ይሆናሉ። በእርግጥ በአሁኑ ጊዜ በሕይወት ያሉ “ሌሎች በጎች” ይህ ትውልድ ብቻ የሚኖረው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ተስፋ አላቸው። ቁጥራቸው ያለማቋረጥ በማደግ ላይ ያሉት የ“እጅግ ብዙ ሰዎች” ክፍል በመሆን ሥጋዊ ሞትን ሳይቀምሱ መጪውን ‘ታላቅ መከራ’ በሕይወት ሊያልፉ ይችላሉ! (ራእይ 7:9, 14) ይሁን እንጂ “ጊዜና ያልታሰበ አጋጣሚ” በሚፈጥሯቸው ሁኔታዎች ወይም በሰይጣን ወኪሎች ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች በትንሣኤ ተስፋ ሊተማመኑ ይችላሉ።—መክብብ 9:11
19. ዛሬ ሁሉም ክርስቲያኖች የትኛውን ማሳሰቢያ ልብ ሊሉት ይገባል?
19 ስለዚህም ሞት የሚሻርበትን ክብራማ ቀን በጉጉት እንጠባበቃለን። በይሖዋ ተስፋ ላይ ያለን የማይናወጥ እምነት ለነገሮች ትክክለኛ አመለካከት እንዲኖረን ያስችለናል። በአሁኑ ሕይወታችን ምንም ነገር ቢያጋጥመን ሌላው ቀርቶ ብንሞት እንኳ ይሖዋ ቃል የገባልንን ሽልማት ሊነጥቀን የሚችል ነገር አይኖርም። በመሆኑም ጳውሎስ ከሁለት ሺህ ዓመታት በፊት ለቆሮንቶስ ሰዎች የሰጠው ጥብቅ ማሳሰቢያ በጊዜያችንም ይሠራል:- “ስለዚህ፣ የተወደዳችሁ ወንድሞቼ ሆይ፣ ድካማችሁ በጌታ ከንቱ እንዳይሆን አውቃችኋልና የምትደላደሉ፣ የማትነቃነቁም፣ የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ።”—1 ቆሮንቶስ 15:58
[ምን ብለህ ትመልሳለህ?]
◻ ጳውሎስ ቅቡዓኑ ከሞት በሚነሡበት ጊዜ ስለሚኖራቸው አካል ለተነሣው ጥያቄ ምን መልስ ሰጥቷል?
◻ ሞት የሚሻረው እንዴትና መቼ ነው?
◻ ምድራዊው ትንሣኤ እነማንን የሚያጠቃልል ይሆናል?
◻ መጽሐፍ ቅዱስ ዝርዝር መግለጫ የማይሰጥባቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አመለካከታችን ምን መሆን አለበት?
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ ዘር አስደናቂ ለውጥ በማድረግ “ይሞታል”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
እንደ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሣራና ረዓብ የመሳሰሉ የጥንት ታማኝ ወንዶችና ሴቶች በትንሣኤ ከሚነሡት መካከል ይሆናሉ
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ትንሣኤ ታላቅ የደስታ ጊዜ ይሆናል!