የይሖዋን ፈቃድ ፈጽመዋል
ጳውሎስ በሹማምንት ፊት በድፍረት መሠከረ
በሁለቱ ሰዎች መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ ምንም አያዳግትም። አንዱ ዘውድ የደፋ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ በሰንሰለት የታሰረ ነበር። አንደኛው ንጉሥ ሲሆን ሌላኛው ግን እስረኛ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሁለት ዓመታት ያህል በእስር ከቆየ በኋላ አሁን የአይሁድ ገዥ በሆነው በሄሮድስ አግሪጳ ዳግማዊ ፊት ቆሟል። ንጉሡና ሚስቱ በርኒቄ “በብዙ ግርማ መጥተው ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ።” (ሥራ 25:23) አንድ መጽሐፍ “በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች በዚያ ሳይገኙ አይቀርም” በማለት ይናገራል።
ስብሰባውን የጠራው አዲስ የተሾመው ገዥ ፊስጦስ ነበር። ከእርሱ በፊት ገዥ የነበረው ፊልክስ፣ ጳውሎስ ከእስር ቤት ሳይፈታ እዚያው እንዲቆይ አድርጎ ነበር። ይሁን እንጂ ፊስጦስ በጳውሎስ ላይ የተመሠረተውን ክስ ለመመርመር ፈለገ። ሆኖም ጳውሎስ ምንም ጥፋት እንዳልሠራ አጥብቆ ያምን ስለነበር ጉዳዩ በቄሳር ፊት እንዲታይለት ጠየቀ! የጳውሎስ ጉዳይ የንጉሥ አግሪጳን የማወቅ ፍላጎት ቀስቅሶ ነበር። “እኔ ዳግም እኮ እሰማው ዘንድ እወድ ነበር” አለ። ንጉሡ ይህን እስረኛ በተመለከተ ምን ሊሰማው እንደሚችል ለማወቅ በመጓጓት ይመስላል ፊስጦስ ወዲያው ዝግጅት አደረገ።—ሥራ 24:27–25:22
በቀጣዩ ቀን ጳውሎስ በርከት ብለው በተሰበሰቡ ሹማምንት ፊት ቆመ። “የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና . . . ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ” በማለት ለንጉሥ አግሪጳ ተናገረ።—ሥራ 26:2, 3
ጳውሎስ በድፍረት ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ
ጳውሎስ ንግግሩን ሲከፍት ቀደም ሲል ክርስቲያኖችን ያሳድድ እንደነበር ለአግሪጳ ተናገረ። “እምነታቸውን እንዲክዱ አድርጌአለሁ፤ . . . ወደ ሌሎች ከተሞች እንኳ ወጥቼ እየሄድሁ አሳድዳቸው ነበር” (የ1980 ትርጉም) በማለት ተናገረ። ከዚያም ጳውሎስ በጣም አስገራሚ የሆነ ራእይ እንደተመለከተና ከሞት የተነሳው ኢየሱስ “ስለ ምን ታሳድደኛለህ? የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ለአንተ ይብስብሃል” እንዳለው በመግለጽ ትረካውን ቀጠለ።a—ሥራ 26:4-14
ከዚያም ኢየሱስ ሳውልን ‘አሁን እኔን ባየህበትና ወደፊትም እኔ ለአንተ በምገልጥልህ ነገር’ ለአሕዛብ ሁሉ መስክር ሲል አዘዘው። ጳውሎስ የተሰጠውን ሥራ ለመፈጸም ትጋት የተሞላበት ጥረት እንዳደረገ ተናገረ። “በዚህ ምክንያት አይሁዳውያን በቤተ መቅደስ እንዳለሁ ያዙኝና ሊገድሉኝ ፈለጉ” በማለት ለአግሪጳ ተናገረ። አግሪጳ ለአይሁድ እምነት ያለውን ጥሩ አመለካከት መሣሪያ አድርጎ በመጠቀም ጳውሎስ ስለ መሲሑ ሲመሰክር “ነቢያትና ሙሴ አስቀድመው እንዲህ ይሆናል ያሉትን ከመናገር በቀር ሌላ ምንም” እንዳልተናገረ ጠበቅ አድርጎ ገለጸ።—ሥራ 26:15-23 የ1980 ትርጉም
ፊስጦስ ጣልቃ በመግባት “ብዙ መማርህ ወደ እብደት አድርሶሃል!” በማለት ጮክ ብሎ ተናገረ። ጳውሎስም “ክቡር ፊስጦስ ሆይ! እውነተኛውንና ትክክለኛውን ነገር እናገራለሁ እንጂ አላበድሁም” በማለት መለሰ። ከዚያም ጳውሎስ ለአግሪጳ:- “በፊቱ በግልጥ የተናገርሁት ንጉሥ ይህን ነገር ያውቃል። ይህም በስውር ያልተደረገ ስለሆነ ንጉሡ እንደሚረዳው እርግጠኛ ነኝ” አለ።—ሥራ 26:24-26 የ1980 ትርጉም
ከዚያም ጳውሎስ በቀጥታ አግሪጳን የሚመለከት ነገር ተናገረ። “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ! ነቢያትን ታምን የለምን?” አለው። አግሪጳ ጥያቄውን ለመመለስ እንደተቸገረ የተረጋገጠ ነው። የሚከተለው እምነት በሰፊው ይታወቅ ስለነበር ጳውሎስ በተናገረው ነገር ከተስማማ ፊስጦስ “እብደት” ካለው ነገር ጋር እንደተስማማ ያስቆጥረው ነበር። ምናልባት የአግሪጳን ማመንታት ተገንዝቦ ሳይሆን አይቀርም ጳውሎስ ራሱ ላነሳው ጥያቄ መልስ ሰጠ። “እንደምታምን ዐውቃለሁ” አለ። በዚህ ጊዜ አግሪጳ “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው!” በማለት ሁኔታውን አድበስብሶ አለፈው።—ሥራ 26:27, 28 የ1980 ትርጉም
ጳውሎስ፣ አግሪጳ ጉዳዩን ለማድበስበስ ብሎ የተናገረውን ዓረፍተ ነገር በመጠቀም አንድ ቁልፍ ነጥብ አስጨበጠ። “በአጭር ጊዜም ይሁን በረዥም ጊዜ አንተ ብቻ ሳትሆን ዛሬ ንግግሬን የሰሙ ሁሉ ከዚህ ከእስራቴ በቀር እንደ እኔ እንዲሆኑ እግዚአብሔርን እለምናለሁ” በማለት ተናገረ።—ሥራ 26:29 የ1980 ትርጉም
ጳውሎስ ለሞት ወይም ለእስር የሚያበቃ ምንም ጥፋት እንዳልሠራ አግሪጳም ሆነ ፊስጦስ ተገንዝበዋል። ሆኖም ጳውሎስ ጉዳዩን በቄሳር ፊት ለማቅረብ ያነሳው ጥያቄ ሊሻር አይችልም። ለዚህ ነው አግሪጳ ለፊስጦስ “ይህ ሰው ወደ ቄሳር ይግባኝ ባይል ኖሮ በነፃ በተለቀቀ ነበር” በማለት የተናገረው።—ሥራ 26:30-32 የ1980 ትርጉም
ለእኛ የሚሆን ትምህርት
ጳውሎስ በሹማምንት ፊት ለመመሥከር የተጠቀመበት ዘዴ ለእኛ ግሩም የሆነ ምሳሌ ይሆነናል። ጳውሎስ ከንጉሥ አግሪጳ ጋር በሚነጋገርበት ጊዜ ከፍተኛ ጥንቃቄ አድርጓል። በሰፊው የሚታወቀውን በአግሪጳና በበርኒቄ መካከል የተፈጸመውን አሳፋሪ ድርጊት ጳውሎስም እንደሚያውቅ ምንም ጥርጥር የለውም። በርኒቄ የአግሪጳ እህት በመሆኗ ጋብቻቸው በሥጋ ዘመዳሞች መካከል የተደረገ ነበር። ሆኖም በዚህ ወቅት ጳውሎስ ሥነ ምግባርን የሚመለከት ንግግር ለመስጠት አልፈለገም። ከዚህ ይልቅ እርሱንና አግሪጳን ሊያስማሙ በሚችሉ ነጥቦች ላይ ትኩረት አደረገ። ከዚህም በላይ ጳውሎስ ሕግ ዐዋቂ ከሆነው ከፈሪሳዊው ገማልያል የተማረ ቢሆንም አግሪጳ የአይሁድን ልማድ ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን አምኖ ተቀብሏል። (ሥራ 22:3) ምንም እንኳ አግሪጳ ብልሹ ሥነ ምግባር የነበረው ቢሆንም ሥልጣን ላይ የነበረ በመሆኑ ጳውሎስ በአክብሮት አነጋግሮታል።—ሮሜ 13:7
ስለ እምነታችን በድፍረት መመሥከር ያለብን ቢሆንም ዓላማችን የምናነጋግራቸው ሰዎች የሚፈጽሙትን የረከሰ ተግባር ማጋለጥ ወይም ማውገዝ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እውነትን ለመቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው ለሁላችንም የተዘረጋውን ተስፋ ጠበቅ አድርገን በመግለጽ በምሥራቹ አዎንታዊ ገጽታ ላይ ማተኮር ይኖርብናል። ከእኛ በእድሜ ከፍ ካሉ ወይም ሥልጣን ከጨበጡ ሰዎች ጋር በምንነጋገርበት ጊዜ የያዙትን ቦታ በሚገባ መጠበቅ ይኖርብናል። (ዘሌዋውያን 19:32) በዚህ መንገድ “በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፣ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ” ብሎ የተናገረውን ጳውሎስን ልንመስል እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 9:22
[የግርጌ ማስታወሻ]
a “የመውጊያውን ብረት ብትቃወም” የሚለው አገላለጽ አንድ በሬ አቅጣጫውን እንዳይስትና ቀጥ ብሎ እንዲሄድ ከሚያደርገው ሹል በትር ጋር በመጋጨት ራሱን የሚጎዳበትን ድርጊት መግለጹ ነው። በተመሳሳይም ሳውል ክርስቲያኖችን ሲያሳድድ የአምላክ ድጋፍ ካላቸው ሕዝቦች ጋር እየተዋጋ ስለነበረ ራሱን እየጎዳ ነበር።