ዋናው ዓላማዬ ይሖዋን ማስደሰት ነው
ቲኦዶሮስ ኔሮስ እንደተናገረው
የታሰርኩበት ክፍል በር ተበርግዶ ተከፈተና አንድ መኮንን “ኔሮስ የሚባለው ማን ነው?” ሲል ጠየቀ። እኔ መሆኔን ስነግረው “ተነስ። አሁን ትገደላለህ” በማለት እንድወጣ አዘዘኝ። ይህ የሆነው በ1952 ሲሆን የግሪክ ከተማ በሆነችው በቆሮንቶስ በሚገኝ አንድ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ነበር። ሕይወቴ እንዲህ በቋፍ ላይ የነበረችው ለምንድን ነው? ስለዚህ ጉዳይ ከመግለጼ በፊት ወደኋላ መለስ ብዬ የሕይወት ታሪኬን ልንገራችሁ።
አባቴ ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች (በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁበት ስም ነው) ጋር የተገናኘው በ1925 አካባቢ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የይሖዋ ምሥክር ሆነና ስምንት ለሚሆኑት ወንድሞቹና እህቶቹ ስለ እምነቱ ነገራቸው። ከዚያም ወላጆቹን ጨምሮ ሁሉም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበሉ። ከጊዜ በኋላ አገባና በ1929 በግሪክ፣ አግሪንዮ ተወለድኩ።
ግሪክ ያሳለፈቻቸው እነዚያ ዓመታት እንዴት አስከፊ ነበሩ! በመጀመሪያ ጭከና የተሞላበት የጄኔራል ሜታክሳስ አምባገነናዊ አገዛዝ ነበር። ከዚያም በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳና ብዙም ሳይቆይ አገሪቷ በናዚዎች እጅ ወደቀች። በሽታና ረሃብ ተስፋፍቶ ነበር። የተነፋፉ አስከሬኖች በእጅ በሚገፉ ጋሪዎች ተጭነው ይወሰዱ ነበር። በዓለም ላይ ክፋት በእጅጉ ተስፋፍቶ ስለነበረ የአምላክ መንግሥት እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነበር።
አምላክን ለማገልገል የተወሰነ ሕይወት
ነሐሴ 20, 1942 ከተሰሎንቄ ከተማ ውጭ በቡድን ተሰብስበን ሳለ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቻችን ከተማይቱ ላይ ቦምብ እየጣሉ ወዳሉት የእንግሊዝ የጦር አውሮፕላኖች እያመለከተ ‘መሰብሰባችንን እንዳንተው’ የተሰጠንን ምክር በመከተላችን ምንኛ እንደተጠበቅን ጎላ አድርጎ ገለጸልን። (ዕብራውያን 10:25) በዚያን ወቅት ስብሰባ ያደረግነው በባሕር ዳርቻ ላይ ሲሆን የጥምቀት ዕጩዎች ከነበሩት መካከል አንዱ ነበርኩ። ከውኃው ከወጣን በኋላ በሰልፍ ቆምንና ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶቻችን ላደረግነው ውሳኔ መዝሙር በመዘመር አመሰገኑን። ያ ቀን ፈጽሞ የማይረሳ ነው!
ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ከአንድ ልጅ ጋር ሆኜ ከቤት ወደ ቤት እያገለገልን ሰዎችን በምናነጋግርበት ጊዜ ፖሊሶች ያዙንና ወደ ጣቢያ ወሰዱን። ኮሚኒስቶች አድርገው እንደሚያዩንና የስብከት ሥራችን የተከለከለ መሆኑን በጥብቅ ለመግለጽ ከደበደቡን በኋላ “እናንተ ደደቦች፣ ይሖዋ ከስታሊን በምንም አይለይም!” አሉን።
በዚያን ወቅት ግሪክ ውስጥ የተጧጧፈ የእርስ በርስ ጦርነት ከመካሄዱም በላይ ከፍተኛ ፀረ ኮሚኒስት እንቅስቃሴም ነበር። በሚቀጥለው ቀን ልክ እንደ ወንጀለኛ እጃችን በካቴና ተጠፍሮ በቤታችን በኩል አድርገው ሕዝብ እያየን አዞሩን። ሆኖም የደረሱብኝ ፈተናዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም።
በትምህርት ቤት የደረሰብኝ የእምነት ፈተና
በ1944 መጀመሪያ ላይ ገና ተማሪ የነበርኩ ሲሆን የተሰሎንቄ ከተማ አሁንም በናዚዎች ቁጥጥር ስር ነበረች። አንድ ቀን ትምህርት ቤት ሳለሁ የግሪክ ኦርቶዶክስ ቄስ የሆኑት የግብረገብ መምህራችን በዕለቱ ከተማርነው ትምህርት ውስጥ ጥያቄ እንደሚያቀርቡልኝ ነገሩኝ። ሌሎቹ ተማሪዎች “እሱ ዕኮ ኦርቶዶክስ ክርስቲያን አይደለም” አሉ።
መምህሩ “ታዲያ ምንድን ነው?” በማለት ጠየቁ።
“የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ብዬ መለስኩ።
“ይሄ፣ በበጎች መካከል ያለ ተኩላ” ብለው በመጮኽ አፈፍ አድርገው በጥፊ መቱኝ።
በልቤ ‘እንዴት ተኩላ በበግ ሊመታ ይችላል?’ ብዬ አሰብኩ።
ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደ 350 የምንጠጋ ተማሪዎች ምሳ ለመመገብ በየጠረጴዛችን ተቀምጠን እያለን ተቆጣጣሪው “ኔሮስ ምግቡን ይባርክልናል” አሉ። እኔም ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያስተማረውን በማቴዎስ 6:9-13 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ‘አባታችን ሆይ’ የሚባለውን ጸሎት ደግሜ ጸለይኩ። ጸሎቴ ተቆጣጣሪውን አላረካቸውም፤ በመሆኑም እዚያው እንደተቀመጡ በንዴት “ለምን እንዲህ ብለህ ጸለይክ?” ሲሉ ጠየቁኝ።
“ምክንያቱም እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ብዬ መለስኩላቸው። በዚህ ጊዜ እሳቸውም አፈፍ አደረጉና በጥፊ መቱኝ። በዚያኑ ዕለት ኋላ ላይ አንድ ሌላ አስተማሪ ወደ ቢሮው ጠርቶ “ጎበዝ ኔሮስ ያመንክበትን ነገር አጥብቀህ ያዝ፣ እጅ አትስጥ” አለኝ። ያን ዕለት ምሽት አባቴ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” በሚሉት የሐዋርያው ጳውሎስ ቃላት አማካኝነት አበረታታኝ።—2 ጢሞቴዎስ 3:12
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ምን ዓይነት ሙያ እንደምይዝ መምረጥ ነበረብኝ። በተጨማሪም ግሪክ ውስጥ እየተካሄደ በነበረው የእርስ በርስ ግጭት የተነሳ ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት ጥያቄም ተደቅኖብኝ ነበር። (ኢሳይያስ 2:4፤ ማቴዎስ 26:52) ውሎ አድሮ በ1952 መጀመሪያ ላይ በግሪክ ታሪክ አስቸጋሪ በነበረው ወቅት በውትድርና ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኔ የ20 ዓመት እስራት ተፈረደብኝ።
ክርስቲያናዊ ገለልተኝነቴ ተፈተነ
በሚሶሎኚዮንና በቆሮንቶስ በሚገኙ ወታደራዊ ካምፖች ውስጥ ታስሬ በነበረበት ወቅት በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነው ሕሊናዬ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችን በመደገፍ ወታደር እንድሆን እንደማይፈቅድልኝ ለወታደራዊ አዛዦቹ የማስረዳት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። በ2 ጢሞቴዎስ 2:3 ላይ የሚገኘውን ጥቅስ በመጥቀስ “አስቀድሜ የኢየሱስ ወታደር ሆኜአለሁ” ስል ገለጽኩላቸው። ጉዳዩን በድጋሚ እንዳስብበት ሲገፋፉኝ፣ ውሳኔዬ በግብታዊነት የተደረገ ሳይሆን በጥሞና ካሰብኩበት በኋላና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ቃል መግባቴን ግምት ውስጥ በማስገባት ያደረኩት መሆኑን ነገርኳቸው።
በዚህ ምክንያት የጉልበት ሥራ እንድሠራ፣ ለ20 ቀናት ያክል በሁለት ቀን አንዴ ብቻ እንድመገብና አንድ ሜትር በሁለት ሜትር በማትሞላ ክፍል ውስጥ ሲሚንቶ ወለል ላይ እንድተኛ ተደረግኩ። በዚህች ክፍል ውስጥ የምኖረው ደግሞ ከሌሎች ሁለት ምሥክሮች ጋር ነበር! እንድገደል የተጠራሁት ቆሮንቶስ በሚገኘው ካምፕ ባለሁበት በዚህ ጊዜ ነበር።
ወደምገደልበት ቦታ እየሄድን ሳለ መኮንኑ “ለመጨረሻ ጊዜ መናገር የምትፈልገው ነገር የለህም?” ሲል ጠየቀኝ።
“የለኝም” አልኩት።
“ለቤተሰቦችህስ የምትጽፈው መልእክት የለም?”
“አስቀድሞም እዚህ ልገደል እንደምችል ስለሚያስቡ ምንም የምጽፍላቸው ነገር የለም” ብዬ መለስኩ።
በቦታው ስንደርስ ፊቴን ወደ ግንቡ አዙሬ እንድቆም ታዘዝኩ። ከዚያም መኮንኑ ወታደሮቹን እንዲተኩሱ ከማዘዝ ይልቅ “ወደ ክፍሉ መልሱት” ሲል ነገራቸው። በአቋሜ እጸና እንደሆነና እንዳልሆነ ለመፈተን የታቀደ የውሸት ማስፈራሪያ ነበር።
ከጊዜ በኋላ ወደ ማክሮኒሶስ ደሴት ተላክሁ፤ እዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ምንም ጽሑፍ እንድይዝ አይፈቀድልኝም ነበር። አሥራ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 500 ከሚጠጉ ወንጀለኛ እስረኞች ተገልለው በአንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ ለብቻቸው ታስረው ነበር። ይሁን እንጂ እንደምንም ጽሑፎች በድብቅ ይደርሱን ነበር። ለምሳሌ ያህል አንድ ቀን የታሸገ ሉኩሚያ (ተወዳጅ ከረሜላ ነው) ተላከልኝ። ፈታሾቹ ሉኩሚያውን ለመቅመስ በጣም ጓጉተው ስለነበር ከሥር ተደብቆ የነበረውን መጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሳያዩት ቀሩ። አንድ ምሥክር “ወታደሮቹ ሉኩሚያውን በሉ እኛ ደግሞ መጠበቂያ ግንቡን ‘በላን’!” ሲል ተናግሯል።
በዚያን ወቅት ሃይማኖት ለሰው ልጆች ምን አድርጎላቸዋል? (የእንግሊዝኛ) የተባለ አዲስ የወጣ መጽሐፍ አንድ ቅጂ ደረሰንና እንግሊዝኛ የሚችል አንድ እስረኛ ወንድም መጽሐፉን ተረጎመልን። በድብቅ አንድ ላይ እየተሰበሰብን የመጠበቂያ ግንብ ጥናትም እናደርግ ነበር። በእኛ አመለካከት እስር ቤቱ መንፈሳዊነታችንን ለማጠናከር አጋጣሚ ያገኘንበት ትምህርት ቤት ነበር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ንጹህ አቋም መጠበቃችን ይሖዋን እንደሚያስደስተው ስላወቅን ደስተኞች ነበርን።
ለመጨረሻ ጊዜ የታሰርኩት ከፔሎፖኒሶስ በስተ ምሥራቅ በታየርኢንታ በሚገኝ እስር ቤት ነው። በእዚያ አብሮኝ ለታሰረ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በምመራበት ጊዜ በጥሞና የሚከታተል አንድ ዘብ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከዚያ ዘብ ጋር ተሰሎንቄ ተገናኘን፤ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነገር ነበር! በተገናኘንበት ወቅት የይሖዋ ምሥክር ሆኗል። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ከልጆቹ አንዱ ወደ እስር ቤት ተላከ። ሆኖም ወደ እስር ቤት የተላከው ዘብ ሆኖ ለማገልገል ሳይሆን እስረኛ ሆኖ ነው። እሱም የታሰረው ልክ እኔ በታሰርኩበት ምክንያት ነበር።
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ አገልግሎቱን በአዲስ መልክ ጀመርኩ
መጀመሪያ ላይ የተፈረደብኝ የ20 ዓመት እስር ቢሆንም ሦስት ዓመት ብቻ ታስሬ ተፈታሁ። ከእስር ከተፈታሁ በኋላ አቴንስ ለመኖር ወሰንኩ። ሆኖም ብዙም ሳልቆይ ፕሎሪሲ የተባለ የሳንባ በሽታ ያዘኝና ወደ ተሰሎንቄ ለመመለስ ተገደድኩ። ለሁለት ወር ያህል የአልጋ ቁራኛ ሆንኩ። ከጊዜ በኋላ ኩላ ከምትባል ከአንዲት ቆንጆ ልጅ ጋር ተዋወቅሁና ታኅሣሥ 1959 ተጋባን። በ1962 ኩላ የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች በሚጠሩበት በአቅኚነት ማገልገል ጀመረች። ከሦስት ዓመት በኋላ እኔም ከእሷ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ቻልኩ።
በጥር 1965 ጉባኤዎችን እየጎበኘን በመንፈሳዊ ለማጠናከር በወረዳ አገልጋይነት እንድንሠራ ተመደብን። በተጨማሪም በዚያው ዓመት ክረምት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦስትሪያ፣ ቬይና በትልቅ የአውራጃ ስብሰባ ላይ የመካፈል መብት አገኘን። ይህ ስብሰባ ግሪክ ውስጥ በሥራችን ላይ ተጥሎ በነበረው እገዳ ምክንያት በምስጢር ጫካ ውስጥ ከምናደርጋቸው ስብሰባዎች የተለየ ነበር። በ1965 ማብቂያ ላይ አቴንስ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድንሠራ ጥሪ ቀረበልን። ይሁን እንጂ አንዳንድ የቤተሰቤ አባላት በገጠማቸው የጤና እክል ምክንያት በ1967 ወደ ተሰሎንቄ መመለስ ግድ ሆነብን።
የቤተሰብ ኃላፊነቶቻችንን ከመወጣታችን በተጨማሪ ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ በትጋት መካፈላችንን ቀጠልን። በአንድ ወቅት ከአጎቴ ልጅ ከኮስታስ ጋር ስንወያይ የአምላክ ድርጅት አስደናቂ እንደሆነና በውስጡም ፍቅር፣ ስምምነትና ለአምላክ የመታዘዝ መንፈስ መኖሩን ገለጽኩለት። “የምትላቸው ነገሮች ሁሉ ጥሩ ነበሩ፤ ግን ምን ያደርጋል አምላክ ቢኖር ነበራ” አለኝ። አምላክ መኖር አለመኖሩን እንዲመረምር ያቀረብኩለትን ግብዣ ተቀበለ። በነሐሴ 1969 በጀርመን፣ ኑረምበርግ በሚደረገው ብሔራት አቀፍ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመካፈል እንደምንሄድ ነገርኩት። ከእኛ ጋር መምጣት ይችል እንደሆነ ጠየቀን፤ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠናው የነበረው ጓደኛው አሌኮስም መምጣት ፈለገ።
በኑረምበርግ የተደረገው ስብሰባ ልዩ የሚያደርገው ነገር ነበረው! ስብሰባው የተካሄደው ሂትለር ወታደራዊ ድሎቹን ባከበረበት ግዙፍ ስታዲዮም ውስጥ ነበር። ከፍተኛው የተሰብሳቢዎች ቁጥር ከ150,000 በላይ ሲሆን በሁሉም ክንውኖች ላይ የይሖዋ መንፈስ ተንጸባርቋል። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኮስታስም ሆነ አሌኮስ ተጠምቀዋል። ባሁኑ ጊዜ ሁለቱም ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ ቤተሰቦቻቸውም የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።
ፍላጎት ያላት አንዲት ሴት አስጠና ነበር። ባለቤቷ የኛን እምነት መመርመር እንደሚፈልግ ገለጸ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የግሪክ ኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ ምሁር ከሆኑት ከሚስተር ሳኮስ ጋር እንድንከራከር እንደጋበዛቸው ነገረኝ። ባልየው ለሁለታችንም ጥያቄዎች ሊያቀርብልን ፈለገ። አቶ ሳኮስ አንድ ቄስ ይዘው መጡ። የቤቱ ባለቤት “በመጀመሪያ ሚስተር ሳኮስ ሦስት ጥያቄዎች እንዲመልሱልኝ እፈልጋለሁ” ሲል ውይይቱን ከፈተ።
በውይይታችን እንጠቀምበት የነበረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በእጁ ከፍ አድርጎ ይዞ “አንደኛ ጥያቄ:- ይህ ትክክለኛ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ወይስ ምሥክሮቹ ያዘጋጁት?” ሲል ጠየቀ። አቶ ሳኮስ መጽሐፍ ቅዱሱ እውቅና ያገኘ ትርጉም መሆኑን ከተናገሩ በኋላ የይሖዋ ምሥክሮችን “የመጽሐፍ ቅዱስ አፍቃሪዎች” ሲሉ ገለጿቸው።
ሰውዬው በመቀጠልም “ሁለተኛ ጥያቄ:- የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ሥነ ምግባር ይከተላሉ?” ሲል ጠየቀ። በእርግጥ እሱ የፈለገው ሚስቱ ከምን ዓይነት ሰዎች ጋር እንደገጠመች ለማወቅ ነበር። የሃይማኖት ምሁሩ በትክክል ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸው ሰዎች ናቸው ሲል መለሰ።
ሰውየው እንዲህ ሲል ቀጠለ:- “ሦስተኛ ጥያቄ:- የይሖዋ ምሥክሮች ደሞዝ ይከፈላቸዋል?” የሃይማኖት ምሁሩ “አይከፈላቸውም” ሲል መለሰ።
ሰውየው “ጥያቄዎቼ የተመለሱልኝ ከመሆኑም በላይ ምን ማድረግ እንዳለብኝ ወስኛለሁ” ሲል ደመደመ። ከዚያ በኋላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ቀጠለና ብዙ ጊዜ ሳይፈጅ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
ለዛ ያለው አርኪ ሕይወት
በጥር 1976 እንደገና የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ማገልገል ጀመርኩ። ከስድስት ዓመታት ገደማ በኋላ ግሪክ ውስጥ አዲስ በነበረው የመንገድ ላይ ምሥክርነት ግንባር ቀደም ሆኜ አገልግያለሁ። ከዚያም ከጥቅምት 1991 ጀምሮ እኔና ባለቤቴ ልዩ አቅኚ ሆነን ማገልገል ጀመርን። ከጥቂት ወራት በኋላ አራት ጊዜ የልብ የደም ሥር ቀዶ ሕክምና አደረግኩ፤ ደግነቱ ሕክምናው በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል። ባሁኑ ጊዜ ጥሩ ጤንነት ያለኝ ሲሆን የሙሉ ጊዜ የስብከት ሥራዬንም መቀጠል ችያለሁ። ከዚህም በተጨማሪ ተሰሎንቄ ውስጥ ካሉት ጉባኤዎች በአንዱ ሽማግሌ ሆኜ አገለግላለሁ፤ እንዲሁም ከሕክምና ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ችግር የገጠማቸውን ለመርዳት በአካባቢያችን ካለው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጋር እሠራለሁ።
ያሳለፍኩትን ሕይወት መለስ ብዬ ስመለከት በሰማይ ያለውን አባታችንን የሚያስደስት ነገር መሥራት ምን ያህል አርኪ እንደሆነ እገነዘባለሁ። “ልጄ ሆይ ጠቢብ ሁን፣ ልቤንም ደስ አሰኘው ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ” የሚለውን ልብ የሚነካ ግብዣ ከረጅም ጊዜ በፊት በመቀበሌ ደስተኛ ነኝ። (ምሳሌ 27:11) በዓለም አቀፍ ደረጃ ወደ ይሖዋ ድርጅት እየመጡ ያሉት ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሄዱን ማየቴ ልቤ በደስታ እንዲሞላ አድርጓል። በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አማካኝነት ሰዎችን ነፃ በማውጣቱ ሥራ መካፈልና በዚህም መንገድ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ መክፈት ልዩ መብት ነው!—ዮሐንስ 8:32፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
የይሖዋ አገልጋይ የሆኑ ወጣቶች የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ አድርገው እንዲይዙና ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለእሱ እንዲሠዉ ምንጊዜም እናበረታታቸዋለን። በእርግጥም በይሖዋ መታመንና የእሱን ልብ በማስደሰት እርካታ ማግኘት ከምንም ነገር በላይ የሚያረካ ሕይወት ነው!—ምሳሌ 3:5፤ መክብብ 12:1
[በገጽ 21 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
(ከግራ ወደ ቀኝ)
በ1965 ቤቴል ውስጥ በወጥ ቤት ስሠራ
በ1970 የስብከት ሥራችን ታግዶ በነበረበት ጊዜ ንግግር ስሰጥ
በ1959 ከባለቤቴ ጋር ሆኜ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ከኩላ ጋር