ምሥራቹ ሕጋዊ ከለላ እንዲያገኝ ማድረግ
የሰው ልጅ ከተማዎችን መቆርቆር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዙሪያቸውን ቅጥር ሲገነባ ኖሯል። በተለይ በድሮ ጊዜ ዙሪያውን ቅጥር መገንባቱ ለከተማው ትልቅ ጥበቃ ነበር። ቅጥሩን ጠላት እንዳይቦረቡረው ወይም እንዳያፈርሰው ጠባቂዎች አናቱ ላይ ቆመው መዋጋት ይችላሉ። ጥበቃ የሚያገኙት የከተማዋ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ አብዛኛውን ጊዜ በአካባቢው በሚገኙ ትናንሽ ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችም ጭምር በቅጥሩ ውስጥ በመሆን ከለላ ያገኙ ነበር።—2 ሳሙኤል 11:20–24፤ ኢሳይያስ 25:12
በተመሳሳይም የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ የመከላከያ ቅጥር ገንብተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚታወቁት በተግባቢነታቸውና በሰው ወዳድነታቸው በመሆኑ ይህ ቅጥር የተገነባው ምሥክሮቹን ከተቀረው ኅብረተሰብ ለማግለል እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ቅጥሩ፣ ሁሉም ሰዎች መሠረታዊ የሆነ ነፃነት ለማግኘት ያላቸውን ሕጋዊ ዋስትና እንዲጠናከር አድርጓል። የዚያኑ ያክል ምሥክሮቹ አምልኳቸውን በነፃነት ማካሄድ እንዲችሉ ሕጋዊ መብታቸውን ያስጠብቅላቸዋል። (ከማቴዎስ 5:14–16 ጋር አወዳድር።) ይህ ቅጥር አምልኳቸውን የሚያከናውኑበትን መንገድና የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለመስበክ ያላቸውን መብት ያስከብርላቸዋል። ቅጥሩ ምንድን ነው? የተገነባውስ እንዴት ነው?
ሕጋዊ የመከላከያ ቅጥር መገንባት
የይሖዋ ምሥክሮች በአብዛኞቹ አገሮች ውስጥ የሃይማኖት ነፃነት ቢኖራቸውም እንኳ በአንዳንድ አገሮች ግን ሕጋዊ መሠረት የሌለው በደል ይፈጸምባቸዋል። አንድ ላይ የመሰብሰብ ወይም ከቤት ወደ ቤት ሄዶ የመስበክ የአምልኮ ነፃነታቸው ተቃውሞ ሲገጥመው ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ይከታተሉታል። በምድር ዙሪያ የይሖዋ ምሥክሮችን የሚመለከቱ በሺህዎች የሚቆጠሩ ፍርድ ነክ ጉዳዮች ተከስተዋል።a መርታት የተቻለው ሁሉንም ክሶች ባይሆንም መለስተኛ ፍርድ ቤቶች በእነሱ ላይ ሲበይኑ አብዛኛውን ጊዜ ለከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ይግባኝ ይጠይቃሉ። ምን ውጤት አግኝተዋል?
በ20ኛው መቶ ዘመን አሥርተ ዓመታት በሙሉ በበርካታ አገሮች ውስጥ የተገኙት ሕጋዊ ድሎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ይግባኝ ለጠየቁባቸው ተከታታይ ክሶች አስተማማኝ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎችን ፈጥረዋል። ጡቦች ወይም ድንጋዮች ሲገነቡ ቅጥር እንደሚሆኑ ሁሉ እነዚህ ጠቃሚ ውሳኔዎችም ሕጋዊ የመከላከያ ቅጥር ለመገንባት ያስችላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች አስቀድሞ ከተገነባው ቅጥር ዓናት ላይ በመሆን አምልኳቸውን ማካሄድ የሚያስችላቸውን ሃይማኖታዊ ነፃነት ማስጠበቃቸውን ቀጥለዋል።
ግንቦት 3, 1943 ላይ በዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተዳኘውን በከሳሽ መርደክ እና በተከሳሽ ኮመንዌልዝ ኦቭ ፔንሲልቬኒያ መካከል የነበረውን ክስ እንደ ምሳሌ ውሰድ። በዚህ ክስ ላይ የተነሳው ጥያቄ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ጽሑፎቻቸውን ለማሰራጨት ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ መሸጥ የሚያስችላቸው የንግድ ፈቃድ የግድ ሊኖራቸው ያስፈልጋል? የሚል ነበር። የይሖዋ ምሥክሮች የንግድ ፈቃድ እንድናወጣ ሊጠበቅብን አይገባም የሚል አቋም ነበራቸው። የስብከት ሥራቸው ከንግድ ጋር ግንኙነት የለውም፤ ኖሮትም አያውቅም። ዓላማቸው መነገድ ሳይሆን ምሥራቹን መስበክ ነው። (ማቴዎስ 10:8፤ 2 ቆሮንቶስ 2:17) ፍርድ ቤቱ መርደክን በሚመለከት ባሳለፈው ውሳኔ ሃይማኖታዊ ጽሑፎችን ለማሰራጨት የንግድ ፈቃድ ግብር ክፍያን እንደ አንድ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ ሕገ መንግሥቱ የማይደግፈው መሆኑን በመግለጽ ከይሖዋ ምሥክሮች አቋም ጋር ተስማማ።b ይህ ውሳኔ አንድ አስፈላጊ የሆነ መሠረት የጣለ ሲሆን ምሥክሮቹም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይህን ውሳኔ እንደ ማስረጃ በመጥቀስ በርካታ ክሶችን ይግባኝ በማለት በተሳካ ሁኔታ ለመርታት ችለዋል። መርደክን በሚመለከት የተላለፈው ውሳኔ ጠንካራ የመከላከያ የሕግ ቅጥር ሆኖ ተገኝቷል።
እንዲህ የመሳሰሉት የክስ ጉዳዮች የሁሉንም ሰዎች ሃይማኖታዊ ነፃነት ለማስከበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። የይሖዋ ምሥክሮች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶችን በማስከበር ረገድ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ የሲንሲናቲ ሎው ሪቪው ዩኒቨርሲቲ የሚከተለውን ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ለሕገ መንግሥታዊው ሕግ መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። በተለይ ደግሞ የሃይማኖትና ሐሳብን የመግለጽ መብት እንዲከበር በማድረግ ረገድ የሕጉ አድማስ እንዲሰፋ አድርገዋል።”
ቅጥሩን ማጠናከር
በሕግ ድል በተገኘ ቁጥር ቅጥሩ ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል። በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችም ሆነ ነፃነት አፍቃሪ ለሆኑ ሰዎች በሙሉ የሚጠቅሙ በ1990ዎቹ የተላለፉ አንዳንድ ውሳኔዎችን ተመልከት።
ግሪክ። ግንቦት 25, 1993 ላይ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብት ፍርድ ቤት አንድ የግሪክ ተወላጅ ሃይማኖታዊ እምነቱን ለሌሎች ሰዎች ለማስተማር ያለውን መብት አስከበረ። ጉዳዩ በወቅቱ የ84 ዓመት ዕድሜ የነበረውን ሚኖስ ኮኪናኪስን የሚመለከት ነበር። ኮኪናኪስ የይሖዋ ምሥክር በመሆኑ ምክንያት ከ1938 ወዲህ ከ60 ጊዜ በላይ የታሰረ ሲሆን 18 ጊዜ ያህል በግሪክ ፍርድ ቤቶች ፊት እንዲቀርብ ተደርጓል፤ በተጨማሪም ከስድስት ዓመት በላይ በእስር አሳልፏል። በአብዛኛው ጥፋተኛ ነህ ተብሎ የተወነጀለው በ1930ዎቹ በተደነገገው ሃይማኖትን ማስቀየር በሚከለክለው የግሪክ ሕግ ሳቢያ ነበር። ይህ ሕግ ከ1938 እስከ 1992 ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ 20,000 ለሚጠጉ የይሖዋ ምሥክሮች መያዝና መታሰር መንስዔ ሆኗል። የአውሮፓ ፍርድ ቤት የግሪክ መንግሥት የኮኪናኪስን ሃይማኖታዊ ነፃነት መጣሱን በመግለጽ 14,400 የአሜሪካ ዶላር የሞራል ካሳ እንዲከፈለው ወሰነ። ፍርድ ቤቱ ባስተላለፈው ውሳኔ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖት በትክክል “የታወቀ ሃይማኖት” መሆኑን ወስኗል።—የመስከረም 1, 1993 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 27–31ን ተመልከት።
ሜክሲኮ። ሐምሌ 16, 1992 ላይ ሜክሲኮ ውስጥ ሃይማኖታዊ ነፃነትን በማስከበር ረገድ ከፍተኛ እርምጃ ተወስዷል። በዚያን ዕለት የሃይማኖታዊ ማኅበራትና የሕዝባዊ አምልኮ ሕግ ተደነገገ። በዚህ ሕግ መሠረት አንድ ሃይማኖታዊ ቡድን አስፈላጊውን ምዝገባ በማጠናቀቅ እንደ ሃይማኖታዊ ተቋም ተቆጥሮ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ይችላል። ከዚህ ቀደም የይሖዋ ምሥክሮች በአገሪቱ ውስጥ እንዳሉት ሌሎች ሃይማኖቶች ሁሉ ሕልውና ይኑራቸው እንጂ ሕጋዊ እውቅና አልነበራቸውም። ሚያዝያ 13, 1993 ምሥክሮቹ ለመመዝገብ አመለከቱ። ግንቦት 7, 1993 ላ ቶሪ ዴል ቪኪያ፣ ኤ አር እና ሎስ ቴስቲጎስ ደ ሐኦቫ ኤን ሜሂኮ፣ ኤ አር በሚሉ ሁለት ስሞች በሃይማኖታዊ ማኅበርነት ሕጋዊ እውቅና በማግኘት ተመዘገቡ።—የሐምሌ 22, 1994 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ከገጽ 12–14ን ተመልከት።
ብራዚል። ኅዳር 1990 ላይ በብራዚል የማኅበራዊ ዋስትና ብሔራዊ ተቋም (አይ ኤን ኤስ ኤስ) በቤቴል (የይሖዋ ምሥክሮች የቅርንጫፍ ቢሮ ሕንፃዎች የሚጠሩበት ስም ነው) ነፃ አገልግሎት የሚሰጡ አገልጋዮች ካሁን በኋላ ሃይማኖታዊ አገልጋይ ተደርገው እንደማይታዩና በዚህም ምክንያት በብራዚል የሠራተኞች መተዳደሪያ ደንብ ሥር እንደሚጠቃለሉ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ አስታወቀ። ምሥክሮቹ በተላለፈው ውሳኔ ላይ ይግባኝ ጠየቁ። ሰኔ 7, 1996 ላይ የብራዚሊያ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ ቢሮ የሕግ አማካሪ ክፍሉ በቤቴል የሚሠሩ አገልጋዮች ተቀጣሪ ሠራተኞች ሳይሆኑ ሕጋዊ የሆነ ሃይማኖታዊ ድርጅት አባል እንደሆኑ በመቁጠር አቋማቸውን የሚደግፍ ውሳኔ አስተላለፈ።
ጃፓን። መጋቢት 8, 1996 ላይ የጃፓን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ትምህርትንና የሃይማኖት ነፃነትን በሚመለከት ማንኛውንም የጃፓን ነዋሪ የሚጠቅም ውሳኔ አስተላለፈ። ፍርድ ቤቱ የኮቤ ራስ ገዝ መስተዳደር የኢንዱስትሪ ቴክኒካል ኮሌጅ ኩኒሂቶ ኮባያሺ እንደ ጁዶና ካራቴ ባሉ ሥልጠናዎች ለመሳተፍ ፈቃደኛ ባለመሆኑ ከኮሌጁ እንዲባረር በማድረግ ሕግ መጣሱን በአንድ ድምፅ ወሰነ። ከፍተኛው ፍርድ ቤት የጃፓን ሕገ መንግሥት ባጸደቀው ሃይማኖታዊ ነፃነት ላይ ተመሥርቶ ውሳኔ ሲያስተላልፍ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነበር። ይህ ወጣት ምሥክር በመጽሐፍ ቅዱስ የሰለጠነ ሕሊናውን በመከተል እነዚህ ሥልጠናዎች በኢሳይያስ 2:4 ላይ እንደሚገኘው ካሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር እንደማይጣጣሙ ተሰማው። ጥቅሱ እንዲህ ይላል:- “ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።” የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ወደፊት በዚህ ረገድ የሚነሱ ክሶች ለሚታዩበት መንገድ ጥሩ መሠረት ጥሏል።—የኅዳር 1, 1996 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 19–21ን ተመልከት።
የካቲት 9, 1998 ላይ የቶኪዮ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሚሳኢ ታኬዳ የምትባል የይሖዋ ምሥክር መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከደም ስለ መራቅ’ ከሚሰጠው ትእዛዝ ጋር የሚጋጭ የሕክምና ዓይነት ላለመቀበል ያላትን መብት በማስከበር ሌላ ታሪካዊ የሆነ ውሳኔ አስተላልፏል። (ሥራ 15:28, 29) ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ይግባኝ የቀረበ ሲሆን የከፍተኛ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ድጋፍ ማግኘት አለማግኘቱ ወደፊት የሚታይ ነገር ነው።
ፊሊፒንስ። የፊሊፒንስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ለባንዲራ ሰላምታ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን አክብሮት በተሞላበት መንገድ በመግለጻቸው ከትምህርት ቤት የተባረሩ ወጣት ምሥክሮችን ጉዳይ በሚመለከት በመጋቢት 1, 1993 በአንድ ድምፅ የይሖዋ ምሥክሮችን አቋም የሚደግፍ ውሳኔ አስተላልፏል።
እያንዳንዱ ጠቃሚ የሆነ የፍርድ ቤት ውሳኔ የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ሳይሆን ባጠቃላይ የሰዎችን መብት የሚያስጠብቀውን ሕጋዊ ቅጥር እንደሚያጠናክር ተጨማሪ ድንጋይ ወይም ጡብ ይቆጠራል።
ቅጥሩን ከጥቃት መከላከል
የይሖዋ ምሥክሮች በ153 አገሮች ውስጥ ሕጋዊ እውቅና አግኝተው የተመዘገቡ ሲሆን እውቅና ያገኙ ሌሎች ሃይማኖቶች ያሏቸው ሃይማኖታዊ ነፃነቶች ሁሉ አላቸው። የይሖዋ ምሥክሮች በምሥራቅ አውሮፓና በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስደትና እገዳ ከደረሰባቸው በኋላ በአሁኑ ጊዜ እንደ አልባኒያ፣ ቤላሩስ፣ የቼክ ሪፑብሊክ፣ ጆርጂያ፣ ሃንጋሪ፣ ካዛክስታን፣ ኪርጊስታን፣ ሩማንያ እና ስሎቫኪያ ባሉ አገሮች ሕጋዊ እውቅና አግኝተዋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ አንዳንድ የምዕራብ አውሮፓ አገሮችን ጨምሮ ከጥንት ጀምሮ የተደነገገ ሕጋዊ መዋቅር ባላቸው በተወሰኑ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች መብት ከፍተኛ ፈተና እየገጠመው ወይም እየተጣሰ ነው። ተቃዋሚዎች በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ‘ሕግን ተንተርሰው ችግር ለመፍጠር’ ደፋ ቀና በማለት ላይ ናቸው። (መዝሙር 94:20) የይሖዋ ምሥክሮች ምላሽ ምንድን ነው?c
የይሖዋ ምሥክሮች ከሁሉም መንግሥታት ጋር ተባብረው መሥራት ይፈልጋሉ፤ ሆኖም አምልኳቸውን ለማካሄድ የሚያስችላቸው ሕጋዊ ነፃነት እንዲኖራቸውም ጭምር ይፈልጋሉ። ምሥራቹን እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ትእዛዝ ጨምሮ የአምላክን ትእዛዛት ከመከተል የሚያግዳቸው ማንኛውም ሕግ ወይም የፍርድ ቤት ውሳኔ በእነሱ ዘንድ ጨርሶ ተቀባይነት የለውም። (ማርቆስ 13:10) ጉዳዩ በስምምነት ሊፈታ ካልቻለ የይሖዋ ምሥክሮች በሕግ ይሟገታሉ። ይህንም ሲያደርጉ አምልኳቸውን ማካሄድ እንዲችሉ አምላክ ለሰጣቸው መብት የሕግ ከለላ ለማግኘት አስፈላጊ የሆኑትን የይግባኝ እርምጃዎች በሙሉ ይወስዳሉ። የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ “በአንቺ ላይ የተሠራ መሣሪያ ሁሉ አይከናወንም” ሲል በሰጠው ተስፋ ላይ ሙሉ ትምክህት አላቸው።—ኢሳይያስ 54:17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ሕግ ነክ ታሪክ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት እባካችሁ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪ የሆኑት የይሖዋ ምሥክሮች (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 30ን ተመልከቱ።
b ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ መርደክን በሚመለከት ባስተላለፈው ውሳኔ የከሳሽ ጆንስ እና የተከሳሽ ሲቲ ኦቭ ኦፔሊካን ጉዳይ በተመለከተ ይዞት የነበረውን የራሱን አቋም ቀልብሷል። ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በ1942 የጆንስን ጉዳይ በተመለከተበት ጊዜ መለስተኛው ፍርድ ቤት የይሖዋ ምሥክር የሆነው ሮስኮ ጆንስ የንግድ ፈቃድ ግብር ሳይከፍል በአላባማ ኦፔሊካ ጎዳናዎች ላይ ጽሑፎች ሲያሰራጭ በመገኘቱ ጥፋተኛ ነው ሲል ያስተላለፈውን ውሳኔ ደግፎ ነበር።
c ከገጽ 8–18 ላይ “በእምነታቸው የተጠሉ ሰዎች” እና “ለእምነታችን መከላከያ ማቅረብ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የይሖዋ ምሥክሮችን መብት ማስከበር
◻ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የደረሰው ስደት በዓለም ዙሪያ በዳኞችና በመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት እንዲቀርቡ አድርጓቸዋል። (ሉቃስ 21:12, 13) የይሖዋ ምሥክሮች መብታቸውን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ለማስከበር ከመጣር አልቦዘኑም። በብዙ አገሮች ውስጥ የተገኙ የፍርድ ቤት ድሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ሕጋዊ ነፃነት ለማስከበር እገዛ አድርገዋል። ከተቀዳጅዋቸው መብቶች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-
◻ በንግድ ሥራ በተሰማሩ ነጋዴዎች ላይ ከተጣሉት ገደቦች ነፃ በመሆን ከቤት ወደ ቤት መስበክ—በከሳሽ መርደክና በተከሳሽ ኮመንዌልዝ ኦቭ ፔንሲልቬኒያ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (1943)፤ በከሳሽ ኮኪናኪስና በተከሳሽ ግሪክ፣ የአውሮፓ የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት (ኢ ሲ ኤች አር) (1993)
◻ ለአምልኮ በነፃነት መሰብሰብ—ከሳሽ ማኖሳኪስና ሌሎች፣ ተከሳሽ ግሪክ ኢ ሲ ኤች አር (1996)
◻ ሕሊናቸውን ሳያጎድፉ ለአገሩ ባንዲራ ወይም ሰንደቅ ዓላማ አክብሮት የሚያሳዩበትን መንገድ መወሰን—በከሳሽ የዌስት ቨርጂኒያ ስቴት የትምህርት ቦርድና በተከሳሽ ባርኔት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (1943)፤ የፊሊፒንስ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (1993)፤ የሕንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (1986)
◻ ክርስቲያናዊ ሕሊናቸውን የሚያስጥስ የውትድርና አገልግሎት አለመቀበል—በከሳሽ ያኦርያቲስ እና በተከሳሽ ግሪክ፣ ኢ ሲ ኤች አር (1997)
◻ ሕሊናቸውን የማያጎድፉ የሕክምና ዓይነቶችና መድኃኒቶች መምረጥ—በከሳሽ ማሌትና በተከሳሽ ሹልማን፣ ካናዳ ኦንታሪዮ ይግባኝ ፍርድ ቤት (1990)፤ በከሳሽ ዎች ታወርና በተከሳሽ ኢ ኤል ኤ፣ የፑርቶ ሪኮ ሳን ጁአን ጠቅላይ ፍርድ ቤት (1995)፤ በከሳሽ ፎስሚር እና በተከሳሽ ኒኮላ፣ ዩ ኤስ ኤ፣ ኒው ዮርክ፣ የይግባኝ ፍርድ ቤት (1990)
◻ ልጆችን በማሳደግ መብት ላይ አለመግባባት ኖሮ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶቹ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተ እምነታቸው መሠረት ልጆቻቸውን ማሳደግ—በከሳሽ ሳ ሎራ እና በተከሳሽ ሱሲ፣ የካናዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት (1997)፤ በከሳሽ ሆፍማንና በተከሳሽ ኦስትሪያ፣ ኢ ሲ ኤች አር (1993)
◻ ሌሎች እውቅና ያላቸው ሃይማኖቶች ለሚያቋቁሙት ማኅበር እንደሚደረገው ሁሉ ከቀረጥ ነፃ የሆነ ሕጋዊ ማኅበር መመሥረትና ማንቀሳቀስ—በከሳሽ ፒፕል እና በተከሳሽ ሔሪንግ፣ ዩ ኤስ ኤ ኒው ዮርክ የይግባኝ ፍርድ ቤት (1960)
◻ ከሙሉ ጊዜ የአገልግሎት ዘርፎች በአንዱ የሚሳተፉት በሌሎች ሃይማኖቶች ውስጥ ላሉ የሙሉ ጊዜ ሃይማኖታዊ ሠራተኞች ከሚሰጠው ጋር ተመሳሳይ የሆነ አመቺ የቀረጥ አሠራር ማግኘት—በብራዚል የማኅበራዊ ዋስትና ብሔራዊ ተቋም፣ ብራዚሊያ (1996)
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሚኖስ ኮኪናኪስ ከባለቤቱ ጋር
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኩኒሂቶ ኮባያሺ
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
The Complete Encyclopedia of Illustration/J. G. Heck