የሕይወት ታሪክ
ለብዙ ብሔራት ብርሃን አብሪ ሆኖ ያገለገለ ሰው
የጆርጅ ያንግ ታሪክ ሩት ያንግ ኒኮልሰን እንደተናገረችው
“በመስበኪያ ሰገነታችን ላይ ሆነን ዝም የምንለው ለምንድን ነው? . . . ትክክል ናቸው ብዬ የጻፍኳቸው እነዚህ ነገሮች እውነት መሆናቸውን ካረጋገጥን በኋላ ሳንናገር ዝም ብንል ምን ዓይነት ሰዎች መሆናችን ነው? ሕዝቡ ያለ እውቀት እንዲቀር ማድረግ የለብንም። ከዚህ ይልቅ ምንም ማስተዛዘኛ ወይም መሸፋፈኛ ሳንጠቀም እውነቱን በግልጽ እንናገር።”
እነዚህ አባቴ ከቤተ ክርስቲያኒቷ መዝገብ ላይ ስሙ እንዲሰረዝ በመጠየቅ በ1913 ከጻፈው ባለ 33 ገጽ ደብዳቤ ላይ የተወሰዱ ቃላት ናቸው። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ለብዙ ብሔራት ብርሃን አብሪ ሆኖ እንዲያገለግል መንገድ የከፈተለትን ሕይወት መምራት ጀመረ። (ፊልጵስዩስ 2:15) ከትንሽነቴ ጀምሮ አባቴ ስላጋጠሙት ተሞክሮዎች እንዲነግሩኝ ዘመዶቼን እጠይቅና ታሪካዊ ማስረጃዎችን አሰባስብ ነበር። ጓደኞቼም የአባቴን የሕይወት ታሪክ በማጠናቀሩ በኩል ረድተውኛል። የአባቴ ሕይወት በብዙ መንገዶች ሐዋርያው ጳወሎስ ያሳለፈውን ሕይወት እንዳስታውስ ያደርገኛል። “የአሕዛብ ሐዋርያ” የነበረው ጳውሎስ እንዳደረገው ሁሉ አባቴም የይሖዋን መልእክት ወደ ተለያዩ የምድር ክፍሎችና ደሴቶች ለማድረስ ሁል ጊዜ ለጉዞ ዝግጁ ነበር። (ሮሜ 11:13፤ መዝሙር 107:1-3) እስቲ ስለ አባቴ ስለ ጆርጅ ያንግ ልንገራችሁ።
የቀደሙት ዓመታት
አባቴ የስኮትላንድ ኘሪስባይቴርያን እምነት ተከታይ ለሆኑት ጆንና ማርጋሬት ያንግ የመጨረሻ ወንድ ልጃቸው ነበር። አባቴ የተወለደው ቤተሰቡ ከስኮትላንድ ኤዲንበርግ በካናዳ ምዕራባዊ ክፍል ወደምትገኘው ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ከተዛወረ በኋላ ብዙም ሳይቆይ መስከረም 8, 1886 ነው። አሌክሳንደር፣ ጆንና ማልኮም የተባሉት ሦስት ታላላቅ ወንድሞቹ የተወለዱት ጥቂት ዓመታት ቀደም ብሎ ስኮትላንድ ውስጥ ነበር። ወንዶቹ ልጆች በቁልምጫ ኔሊ እያሉ የሚጠሯት እህታቸው ከአባቴ በሁለት ዓመት ታንስ ነበር።
ልጆቹ ከቪክቶሪያ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ብዙም በማይርቀው የሳኒች እርሻ ቦታ ደስ የሚል የልጅነት ጊዜ ከማሳለፋቸውም በላይ ኃላፊነት ለመሸከም የሚያስችላቸውን ሥልጠናም አግኝተዋል። በመሆኑም ወላጆቻቸው ከሄዱበት ወደ ቪክቶሪያ ሲመለሱ ከቤት ውጭ ያሉት ሥራዎች ሁሉ ተጠናቀውና ቤቱ ጸድቶ ይጠብቃቸው ነበር።
ከጊዜ በኋላ አባቴና ወንድሞቹ ማዕድን በማውጣትና በጣውላ ንግድ ሥራ የመሰማራት ፍላጎት አደረባቸው። እነዚህ ወንድማማቾች ቲምበር ክሩዘርስ (ጣውላ ሊመረትባቸው የሚችሉ ቦታዎችን የሚፈልጉ ሰዎች) በመሆንና በጣውላ ግዥና ሽያጭ ሥራ ጥሩ ስም እያተረፉ መጡ። አባቴ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ይቆጣጠር ነበር።
አባቴ ለመንፈሳዊ ነገሮች የነበረው ዝንባሌ ውሎ አድሮ የኘሪስባይቴሪያን ቄስ እንዲሆን ገፋፍቶት ነበር። ሆኖም በዚህ ጊዜ የጽዮን የመጠበቂያ ግንብ ትራክት ማኅበር የመጀመሪያ ኘሬዚዳንት በነበረው ቻርልስ ቴዝ ራስል የሚያዘጋጀው የጋዜጣ ስብከት ሕይወቱን በጥልቅ ነካው። አባቴ የተማረው ነገር መግቢያው ላይ የተጠቀሰውን የመሰናበቻ ደብዳቤ አዘጋጅቶ እንዲልክ ገፋፍቶታል።
ነፍስ አትሞትም እንዲሁም አምላክ የሰውን ነፍስ በእሳታማ ሲኦል ለዘላለም ያቃጥላል የሚሉት የቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን ለማረጋገጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በደግነት ሆኖም ግልጽ በሆነ መንገድ ተጠቅሟል። የሥላሴ መሠረተ ትምህርት አመጣጡ ክርስቲያናዊ እንዳልሆነና ምንም የቅዱሳን ጽሑፎች ድጋፍ እንደሌለው የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ተጠቅሞ የትምህርቱን ሐሰተኛነት አጋልጧል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ባከናወነው ክርስቲያናዊ አገልግሎት ሙሉ ችሎታውንና ኃይሉን በትህትና ለይሖዋ ክብር ለማምጣት ተጠቅሞበታል።
በ1917 በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር አመራር ሥር ፒልግሪም ሆኖ ማገልገል ጀመረ። ፒልግሪም በወቅቱ የይሖዋ ምሥክሮች ተጓዥ ተወካዮች የሚጠሩበት ስም ነበር። በካናዳ ከተሞችና መንደሮች በመዘዋወር ንግግሮች ከመስጠቱም በላይ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ተንቀሳቃሽ የስላይድ ፊልም አሳይቷል። አባቴ ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት የቲያትር ቤት አዳራሾች ግጥም ብለው ይሞሉ ነበር። የፒልግሪም ጉብኝቱ ኘሮግራም እስከ 1921 ድረስ በመጠበቂያ ግንብ ላይ ይወጣ ነበር።
ዊኒፔግ የተባለ አንድ ጋዜጣ ወንጌላዊው ያንግ ለ2, 500 ሰዎች ንግግር እንዳደረገና አዳራሹ ሞልቶ ስለነበር ብዙዎች መግባት እንዳልቻሉ ዘግቧል። ኦታዋ ውስጥ “ሲኦል ገብቶ መውጣት” በሚል ርዕስ ንግግር ሰጥቶ ነበር። በቦታው ተገኝተው የነበሩ አንድ በዕድሜ የገፉ ሰው ስለ ሁኔታው ሪፖርት ሲያደርጉ እንዲህ ብለዋል:- “ንግግሩ ሲያልቅ ጆርጅ ያንግ በአንድ መደዳ ተደርድረው የነበሩትን ቄሶች በርዕሱ ላይ ከእርሱ ጋር እንዲወያዩ ወደ መድረኩ ጋበዛቸው። ሆኖም አንዳቸውም አልተንቀሳቀሱም። ወዲያውም እውነትን እንዳገኘሁ ተገነዘብኩ።”
አባቴ የፒልግሪም ጉብኝት በሚያደርግበት ወቅት የቻለውን ያህል ብዙ መንፈሳዊ ተግባሮችን ለማከናወን ይጥር ነበር። ከዚያም ወደሚቀጥለው ጉብኝቱ የሚሄድበት ባቡር እንዳያመልጠው እየተጣደፈ ይሄዳል። በመኪና የሚሄድ ከሆነ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ከቁርስ በፊት ቀደም ብሎ ጉዞውን ይጀምራል። አባቴ በአገልግሎቱ ቀናተኛ ከመሆኑም በላይ ለሌሎች አሳቢ በመሆን ረገድ ጥሩ ስም ያተረፈና በክርስቲያናዊ ተግባሮቹና በለጋስነቱ የሚታወቅ ሰው ነበር።
አባቴ የተገኘባቸው ቀደም ካሉት ብዙ ትልልቅ ስብሰባዎች መካከል በተለይ የማይረሳው አልቤርታ ኤድሞንቶን ውስጥ በ1918 የተካሄደው ስብሰባ ነበር። ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ለኔሊ ጥምቀት በቦታው ተገኝተዋል። ይህ ወቅት ወንዶቹ ልጆች አንድ ላይ የተሰባሰቡበት የመጨረሻ ጊዜም ነበር። ከሁለት ዓመታት በኋላ ማልኮልም በሳምባ ምች ሞተ። እንደ ሦስት ወንድሞቹና እንደ አባቱ ሁሉ እርሱም የሰማያዊ ሕይወት ተስፋ ነበረው። ሁሉም እስከሞት ድረስ ለአምላክ ታማኞች ሆነዋል።—ፊልጵስዩስ 3:14
በውጭ አገር መስኮች ማገልገል
አባቴ መስከረም 1921 የካናዳ የስብከት ዘመቻውን ከጨረሰ በኋላ ወደ ካሪቢያን ደሴቶች ሄዶ እንዲያገለግል በዚያን ወቅት የመጠበቂያ ግንብ ኘሬዚዳንት የነበረው ጆሴፍ ኤፍ ራዘርፎርድ ነገረው። አባቴ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ተንቀሳቃሽ የስላይድ ፊልም ባሳየባቸው በሁሉም ቦታዎች ጥሩ ተቀባይነት አግኝቶ ነበር። ትሪኒዳድ ሆኖ የጻፈው ደብዳቤ እንዲህ ይላል:- “ቦታው በመሙላቱ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። በቀጣዩ ምሽት ደግሞ አዳራሹ ግጥም ብሎ ሞልቶ ነበር።”
ከዚያም በ1923 አባቴ በብራዚል እንዲያገለግል ተመደበ። ብራዚል ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ላላቸው ተሰብሳቢዎች ንግግር ሲሰጥ አንዳንድ ጊዜ የሚጠቀመው በተቀጠሩ አስተርጓሚዎች ነበር። የታኅሣሥ 15, 1923 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ ብሎ ነበር:- “ከሰኔ 1 እስከ መስከረም 30 ባሉት ጊዜያት ውስጥ ወንድም ያንግ 21 የሕዝብ ስብሰባዎች አድርጎ በጠቅላላው 3, 600 ተሰብሳቢዎች ተገኝተው ነበር። አርባ ስምንት የቡድን ስብሰባዎች አድርጎ 1, 100 ሰዎች ተገኝተዋል። በፖርቱጋል ቋንቋ የተዘጋጁ በጠቅላላው 5, 000 ጽሑፎች አሰራጭቷል።” አባቴ “ዛሬ በሕይወት ያሉ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ፈጽሞ ሞትን አያዩም” የሚለውን ንግግር ሲሰጥ ብዙዎች ፍላጎት አሳይተዋል።
መጋቢት 8, 1997 ብራዚል ውስጥ ተጨማሪ ሕንጻዎች ለአምላክ አገልግሎት ሲወሰኑ የወጣው ብሮሹር እንዲህ ብሏል:- “1923:- ጆርጅ ያንግ ወደ ብራዚል ከመጣ በኋላ በመሐል ሪዮ ዲ ጄኔሮ የቅርንጫፍ ቢሮ አቋቋመ።” በስፓኒሽ የተዘጋጁ ጽሑፎች ቢኖሩም የብራዚል ዋነኛ ቋንቋ በሆነው በፖርቱጋል ቋንቋ የተዘጋጁ ጽሑፎች ያስፈልጉ ነበር። በዚህም ምክንያት ከጥቅምት 1, 1923 ወዲህ መጠበቂያ ግንብ በፖርቱጋል ቋንቋ መታተም ጀመረ።
አባቴ ብራዚል ውስጥ ከብዙ ሰዎች ጋር ያደረጋቸው ውይይቶች የማይረሱ ነበሩ። ከእነዚህም መካከል አንዱ ጆሴንቱ ፒሜንተል ካብራል ከተባለ ሃብታም ፖርቱጋላዊ ጋር ያደረገው ውይይት ይገኝበታል። ይህ ሰው ስብሰባዎች በቤቱ ውስጥ እንዲደረጉ ፈቃደኛ ሆኗል። ብዙም ሳይቆይ ጆሴንቱ ራሱ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተቀበለ። በኋላም የቅርንጫፍ ቢሮ አባል በመሆን ለማገልገል በቅቷል። ሌላው ደግሞ ማንዌል ዳ ሲልቫ የተባለ ወጣት ፖርቱጋላዊ አትክልተኛ ነበር። አባቴ ያቀረበውን የሕዝብ ንግግር ሲሰማ ወደ ፖርቱጋል ተመልሶ በኮልፖርተርነት ለማገልገል ተነሳስቷል። ኮልፖልተር የይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች የቀድሞ መጠሪያ ስም ነው።
አባቴ በመላዋ ብራዚል በባቡር ብዙ ይጓጓዝ ስለነበር ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ማግኘት ችሏል። በአንድ ጉዞው ወቅት ቦኒና ካታሬና ግሪን የተባሉ ባልና ሚስት አግኝቶ ስለነበር ቅዱሳን ጽሑፎችን እያብራራላቸው ለሁለት ሳምንት ያህል አብሯቸው ቆየ። ሰባት የሚያክሉ የቤተሰባቸው አባላት ራሳቸውን ለይሖዋ መወሰናቸውን በውኃ ጥምቀት አሳይተዋል።
በ1923 ደግሞ ሳራ ቤሎና ፈርግሰን ከተባለች ሴት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። ገና ልጅ ሳለች ማለትም በ1867 ኢራስመስ ፉልተን ስሚዝ ከተባለው ወንድሟና ከተቀሩት የቤተሰቧ አባላት ጋር በመሆን ከዩናይትድ ስቴትስ ወደ ብራዚል መጡ። ከ1899 ጀምሮ የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በፖስታ ቤት በኩል ሳያቋርጥ ይደርሳት ነበር። የአባቴ ጉብኝት ለሳራ፣ ለአራት ልጆቿና አክስት ሳሊ እያለ አባቴ ለሚጠራት ዘመዷ ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረውን የመጠመቅ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። ይህ የሆነው መጋቢት 11, 1924 ነበር።
ብዙም ሳይቆይ አባቴ በሌሎች የደቡብ አሜሪካ አገሮች ውስጥ መስበክ ጀመረ። ኅዳር 8, 1924 ከፔሩ እንዲህ ሲል ጽፎ ነበር:- “በሊማና ከያዎ 17, 000 ትራክቶች አበርክቼ ገና መጨረሴ ነው።” ቀጥሎም ትራክቶችን ለማሰራጨት ወደ ቦሊቪያ ሄዶ ነበር። ያንን ጉብኝት አስመልክቶም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባታችን የሚደረገውን ጥረት እየባረከው ነው። የአማዞን ወንዝ በሚነሳበት አካባቢ የሚኖር አንድ ህንዳዊ ረድቶኛል። ወደ አገሩ ሲመለስ 1, 000 ትራክቶችንና የተወሰኑ መጽሐፎችን ይዞ ለመሄድ ተስማምቷል።”
አባቴ ባደረገው ጥረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የእውነት ዘር በመካከለኛውና በደቡብ አሜሪካ በሚገኙ ብዙ አገሮች ውስጥ ተሰራጭቷል። የታኅሣሥ 1, 1924 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ጆርጅ ያንግ በደቡብ አሜሪካ ከሁለት ዓመት በላይ ቆይቷል። . . . ይህ ውድ ወንድም የእውነትን መልእክት በማጄላን የባሕር ወሽመጥ ወደምትገኘው ፑንታ አሬናስ የማድረስ መብት አግኝቷል።” አባቴ ግንባር ቀደም በመሆን የስብከቱን ሥራ በኮስታሪካ፣ በፓናማና በቬኔዝዌላ አስፋፍቷል። የወባ በሽታ ይዞት ጤናው ቢቃወስም አገልግሎቱን ቀጥሎ ነበር።
ቀጥሎ ደግሞ ወደ አውሮፓ
አባቴ 300, 000 መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን በስፔይንና በፖርቱጋል ለማሰራጨትና ወንድም ራዘርፎርድ የሕዝብ ንግግሮች የሚሰጥበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ሲል መጋቢት 1925 በመርከብ ወደ አውሮፓ ተጓዘ። ይሁን እንጂ ስፔይን ደርሶ ያለውን ሃይማኖታዊ አለመቻቻል ሲያይ ወንድም ራዘርፎርድ ንግግር ለመስጠት መምጣቱን እንደማይስማማበት ገለጸ።
ወንድም ራዘርፎርድም ኢሳይያስ 51:16ን ጠቅሶ መልስ ሰጠው። “ሰማያትን እዘረጋ ዘንድ ምድርንም እመሠርት ዘንድ፣ ጽዮንንም:- አንቺ ሕዝቤ ነሽ እል ዘንድ ቃሌን በአፍህ አድርጌአለሁ፣ በእጄም ጥላ ጋርጄሃለሁ።” አባቴ ይህንን ሲያነብ “በእርግጥም የጌታ ፈቃድ እኔ የበኩሌን አድርጌ የቀረውን ለሱ እንድተውለት ነው” በማለት ደመደመ።
ግንቦት 10, 1925 ወንድም ራዘርፎርድ ባርሴሎና በሚገኘው ኖቨዳዲስ ቲያትር ውስጥ በአስተርጓሚ ንግግር አቀረበ። በስብሰባው መድረክ ላይ የተቀመጡትን አንድ የመንግሥት ባለ ሥልጣንና ጠባቂውን ጨምሮ ከ2, 000 በላይ ሰዎች ተገኝተው ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ማድሪድ ውስጥ በተካሄደው ስብሰባ ላይ 1, 200 ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል። እነዚህ ንግግሮች የብዙዎችን ፍላጎት በማነሳሳታቸው የ1978 የዓመት መጽሐፍ እንደሚለው በስፔይን የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ “በጆርጅ ያንግ አመራር” ሊቋቋም በቅቷል።
ግንቦት 13, 1925 ወንድም ራዘርፎርድ የፖርቱጋል ዋና ከተማ በሆነችው ሊዝበን ንግግር ሰጠ። ቀሳውስቱ በመጮኽና ወንበሮችን በመሰባበር ስብሰባዎችን ለመበጥበጥ ቢሞክሩም ጉብኝቱ የተሳካ ውጤት አስገኝቷል። ወንድም ራዘርፎርድ በስፔይንና በፖርቱጋል ንግግሮች ከሰጠ በኋላ አባቴ “የፍጥረት ፎቶ ድራማ” የተባለውን ተንቀሳቃሽ የስላይድ ፊልም ማሳየቱን ቀጠለ። በተጨማሪም በእነዚህ ቦታዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች የሚታተሙበትንና የሚሰራጩበትን ዝግጅት አደረገ። በ1927 አባቴ ምሥራቹ “በእያንዳንዱ የስፔይን ከተማና መንደር እንደተዳረሰ” በመግለጽ ሪፖርት አድርጎ ነበር።
በሶቭየት ኅብረት መስበክ
ነሐሴ 28, 1928 አባቴ ቀጥሎ በሚስዮናዊነት እንዲያገለግል ወደተመደበበት ወደ ሶቭየት ኀብረት ተጓዘ። ጥቅምት 10, 1928 የጻፈው ደብዳቤ በከፊል እንዲህ ይነበባል:-
“ወደ ሩሲያ ከመጣሁ ጊዜ አንስቶ ‘መንግሥትህ ትምጣ’ ብዬ የማቀርበው ጸሎት የበለጠ ትርጉም ያዘለ ሆኖልኛል። ቋንቋውን እየተማርኩ ነው። ግን ገና ብዙ ይቀረኛል። አስተርጓሚዬ የሚያስገርም ሰው ነው። አይሁዳዊ ቢሆንም በክርስቶስ ያምናል እንዲሁም ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር አለው። አስደሳች የሆኑ ጥቂት ተሞክሮዎች አጋጥመውኛል። ነገር ግን ምን ያህል መቆየት እንደምችል አላወቅሁም። ባለፈው ሳምንት በ24 ሰዓት ውስጥ አገሪቱን ለቅቄ እንድወጣ ተነግሮኝ ነበር። ሆኖም ጉዳዩ መፍትሄ ስላገኘ እስከ አሁን መቆየት ችያለሁ።”
አባቴ በአሁኑ ወቅት የዩክሬይን ትልቅ ከተማ በሆነችው በካርኮቭ ከሚገኙ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ጋር ተገናኝቶ ነበር። ወንድሞች ከአባቴ ጋር ያደረጉት ሞቅ ያለ ውይይት የደስታ እንባ እንዲያነቡ አድርጓቸዋል። በእያንዳንዱ ምሽት እስከ እኩለ ሌሊት የሚቆይ ስብሰባ ያደርጉ ነበር። አባቴ ከእነዚህ ወንድሞች ጋር ስላደረገው ስብሰባ ከጊዜ በኋላ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ምስኪን ወንድሞች፣ የነበሯቸው ጥቂት መጻሕፍት የተያዘባቸው ከመሆኑም በላይ የመንግሥት ባለ ሥልጣናቱ ጥሩ ሰዎች ባይሆኑም ወንድሞች ደስተኞች ነበሩ።”
ሰኔ 21, 1997 በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ ለአምላክ አገልግሎት በተወሰነበት ኘሮግራም ላይ ለተገኙት ሰዎች የታደለው ልዩ ብሮሹር አባቴ በሶቭየት ኅብረት ያከናወነውን አገልግሎት ጎላ አድርጎ ገልጾ ነበር። ብሮሹሩ አባቴ ወደ ሞስኮ ተልኮ እንደነበረና በወቅቱም “ለሕዝቦች ነጻነት እንዲሁም ሙታን የት ናቸው? የሚል ርዕስ ያላቸውን 15, 000 ቡክሌቶች አትሞ በሩሲያ ለማሰራጨት” የሚያስችለውን ፈቃድ እንዳገኘ ገልጿል።
ከሩሲያ ከተመለሰ በኋላ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በፒልግሪም ሥራ እንዲያገለግል ተመደበ። እዚያም በደቡባዊ ዳኮታ የሚኖሩትን ኔሌናና ቬርዳ ፑል የተባሉትን እህትማማቾች ያነጋግራቸው ነበር። ከዓመታት በኋላ እነዚህ ሁለት እህትማማቾች በፔሩ ሚስዮናዊ ሆነው ማገልገል ጀምረዋል። አባቴ አለመታከት ላከናወነው አገልግሎት ያላቸውን አድናቆት እንዲህ ሲሉ ገልጸው ነበር:- “የቀድሞዎቹ ወንድሞች እውነተኛ የአቅኚነት መንፈስ አሳይተዋል። ከአገራቸው ወጥተው ወደ እነዚህ የውጭ አገር ምድቦች ሲሄዱ የነበራቸው የዚህ ዓለም ቁሳዊ ንብረት ጥቂት ቢሆንም ልባቸው በይሖዋ ፍቅር የተሞላ ነበር። ይህን የመሰለ ውጤት ያለው ነገር እንዲሠሩ የገፋፋቸውም ይህ ነበር።”
ትዳርና ሁለተኛ ጉዞ
በእነዚህ ዓመታት ሁሉ አባቴ ኦንታሪዮ ውስጥ ማናቱሊን በተባለች ደሴት ከምትኖረው ክላራ ሃባርት ጋር ይጻጻፍ ነበር። ሐምሌ 26, 1931 ኦሃዮ ኮሎምበስ ውስጥ በተደረገውና የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የይሖዋ ምሥክሮች የሚለውን ስም በተቀበሉበት ትልቅ ስብሰባ ላይ ሁለቱም ተገኝተው ነበር። (ኢሳይያስ 43:10-12) ከአንድ ሳምንት በኋላ ተጋቡ። ወዲያውኑ አባቴ ሁለተኛ የሚስዮናዊነት ጉዞውን በካሪቢያን ደሴቶች ጀመረ። በዚያም ስብሰባዎችን በማደራጀትና ሌሎችን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በማሰልጠን እርዳታ አበርክቷል።
እናቴ ከሱሪናም፣ ከሴንት ኪትስና ከሌሎች ብዙ ቦታዎች ሥዕሎች፣ ካርዶችና ደብዳቤዎች ይደርሷት ነበር። ደብዳቤዎቹ የስብከቱ ሥራ የሚያደርገውን እድገት የሚገልጹ ነበሩ። አንዳንድ ጊዜም አባቴ በቆየባቸው ቦታዎች ስለሚገኙት ወፎች፣ እንስሳትና ዕፅዋት የሚናገሩ ነበሩ። ሰኔ 1932 አባቴ የካሪቢያን ምድቡን ሲጨርስ እንደ ልማዱ ዝቅተኛ ዋጋ በሚጠይቀው የመርከብ ክፍል ተሳፍሮ ወደ ካናዳ ተመለሰ። ከዚያ ወዲህ እሱና እናቴ አንድ ላይ በመሆን በሙሉ ጊዜ የስብከቱ ሥራ ከመካፈላቸውም በላይ የ1932/33ን የክረምት ወቅት ከአንድ ትልቅ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ቡድን ጋር ኦታዋ አካባቢ አሳልፈዋል።
አጭር የቤተሰብ ሕይወት
በ1934 ዴቪድ የተባለው ወንድሜ ተወለደ። ገና ትንሽ ልጅ እያለ በእናቴ የባርኔጣ ማስቀመጫ ሳጥን ላይ ይወጣና “ንግግር” መስጠት ይለማመድ ነበር። ዴቪድ ሕይወቱን ሙሉ በይሖዋ አገልግሎት እንደ አባቱ ያለ ቅንዓት አሳይቷል። አባቴ ከምሥራቃዊው የካናዳ ድንበር እስከ ምዕራባዊው ድንበር ድረስ ያሉትን ጉባኤዎች ሲጎበኝ ሦስቱም አንድ ላይ ሆነው ጣራው ላይ የድምፅ መሣሪያ በተገጠመለት መኪና ይጓዙ ነበር። አባቴ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ውስጥ በማገልገል ላይ እንዳለ በ1938 እኔ ተወለድኩ። አባቴ አልጋዬ ላይ ካስቀመጠኝ በኋላ እርሱ፣ እናቴና ዴቪድ በአልጋዬ ዙሪያ ተንበርክከው አባቴ ስለ እኔ የምስጋና ጸሎት ያቀርብ እንደነበር ዴቪድ ያስታውሳል።
በ1939 የክረምት ወራት አባቴ ቫንኩቨር የሚገኙትን ጉባኤዎች ይጎበኝ ስለነበር እዚያ ቆየን። ለበርካታ ዓመታት ስናሰባስባቸው ከነበሩት ብዙ ደብዳቤዎች መካከል ጥር 14, 1939 ቬርኖን ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ሆኖ የጻፈው ደብዳቤ ይገኝበታል። “ፍቅሬና ሰላምታዬ ይድረሳችሁ” በማለት ደብዳቤውን የጻፈው ለክላራ፣ ለዴቪድና ለሩት ነበር። ደብዳቤው ለእያንዳንዳችን የተጻፈ መልእክት ነበረው። እሱ ባለበት ቦታ መከሩ ብዙ ቢሆንም ሠራተኞች ግን ጥቂት እንደሆኑ ገልጾልን ነበር።—ማቴዎስ 9:37, 38
አባቴ የተሰጠውን የሥራ ምድብ አጠናቅቆ ከቫንኩቨር በተመለሰ በሳምንቱ ጉባኤ ላይ እንዳለ ራሱን ስቶ ወደቀ። ወዲያው በተደረገለት ምርመራ አንጎሉ ውስጥ ወደ ካንሰር የተለወጠ ዕብጠት መኖሩ ተረጋገጠ። አባቴ ግንቦት 1, 1939 ምድራዊ ሕይወቱን ሲጨርስ እኔ የ9 ወር ሕፃን ነበርኩ። ዴቪድ ደግሞ አምስት ዓመት ሊሞላው የቀረው ትንሽ ነበር። ሰማያዊ ተስፋ የነበራት ተወዳጅዋ እናታችንም ሰኔ 19, 1963 እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆና ቆይታለች።
አባቴ ምሥራቹን ወደ ብዙ አገሮች ይዞ የመጓዝ መብት በማግኘቱ እንዴት ይሰማው እንደነበር ለእናቴ በጻፈላት አንድ ደብዳቤ ላይ ውብ አድርጎ ገልጾታል። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ ይገባኛል በማልለው ደግነቱ ስለ መንግሥቱ የሚናገረውን ብርሃን ወደ እነዚህ አገሮች ሄጄ እንዳበራ ፈቅዶልኛል። ቅዱስ ስሙ ይመስገን። በእኛ ድካም፣ ውስን አቅም እንዲሁም ጉድለት ክብሩ ያበራል።”
በአሁኑ ጊዜ የጆርጅና የክላራ ያንግ ልጆች፣ የልጅ ልጆችና ልጆቻቸው አፍቃሪውን አምላክ ይሖዋን በማገልገል ላይ ይገኛሉ። አባቴ ብዙ ጊዜ “እግዚአብሔር፣ . . . ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና” የሚለውን ዕብራውያን 6:10ን ይጠቅስ እንደነበር ተነግሮኛል። እኛም የአባታችንን ሥራ አልረሳንም።
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴ (በቀኝ በኩል) ከሦስት ወንድሞቹ ጋር
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴ (የቆመው) ከወንድም ዉድዎርዝ፣ ራዘርፎርድና ማክሚላን ጋር
ከታች:- አባቴ (በስተግራ ዳር) ከወንድም ራስልና ከሌሎች ጋር በቡድን ሆነው
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴና እናቴ
ከታች:- በሠርጋቸው ቀን
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አባቴ ከሞተ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ከዴቪድና ከእናቴ ጋር ሆነን