‘ሰዓቱ ደረሰ!’
‘ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት ደረሰ።’ —ዮሐንስ 13:1
1. በ33 እዘአ የማለፍ በዓል ሲቃረብ ኢየሩሳሌም ውስጥ ምን ዓይነት ግምታዊ ወሬ እየተናፈሰ ነበር? ለምንስ?
ኢየሱስ በ29 እዘአ ሲጠመቅ ወደሚሞትበት እንዲሁም ትንሣኤና ክብር ወደሚያገኝበት “ሰዓት” የሚመራውን የሕይወት ጎዳና ጀመረ። አሁን 33 እዘአ የጸደይ ወቅት ገብቷል። የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ ሳንሄድሪን ኢየሱስን ለመግደል ከተማከረ ገና ጥቂት ሳምንታት ማለፋቸው ነው። ኢየሱስ የወዳጅነት መንፈስ ካሳየው የሳንሄድሪን አባል፣ ከኒቆዲሞስ ሳይሆን አይቀርም ዕቅዳቸውን በመስማቱ ኢየሩሳሌምን ለቅቆ ከዮርዳኖስ ባሻገር ወዳለ መንደር ሄደ። የማለፍ በዓል እየተቃረበ ሲመጣ ብዙ ሰዎች ከያሉበት ወደ ኢየሩሳሌም እየጎረፉ ሲሆን ኢየሱስን በተመለከተ በከተማዋ የተለያየ ግምታዊ ወሬ ይናፈሳል። ሰዎች “ምን ይመስላችኋል ወደ በዓሉ አይመጣም ይሆንን?” በማለት እርስ በርሳቸው ይጠያየቃሉ። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን ኢየሱስን ያየ ማንኛውም ሰው ያለበትን ቦታ ለእነሱ መጠቆም እንዳለበት ትእዛዝ ማስተላለፋቸው የሕዝቡን ጉጉት አሳድጓል።—ዮሐንስ 11:47-57
2. ማርያም ያደረገችው ውዝግብ ያስነሳው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ እሷን በመደገፍ የሰጠው መልስ ‘ሰዓቱን’ በተመለከተ ምን የተገነዘበው ነገር እንዳለ ያሳያል?
2 የማለፍ በዓል ከሚከበርበት ከስድስት ቀናት በፊት ኒሳን 8 ላይ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም አቅራቢያ ተመልሶ መጣ። ከኢየሩሳሌም ውጭ ወደ ሦስት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ ወደምትገኘው የወዳጆቹ የማርታ፣ የማርያምና የአልዓዛር መኖሪያ ወደሆነችው ከተማ ወደ ቢታንያ መጣ። ወደዚህ የመጣው አርብ ምሽት ሲሆን ሰንበትን የሚያሳልፈው በዚህ ነው። በሚቀጥለው ቀን ምሽት ማርያም የከበረ ሽቱ አምጥታ ስታገለግለው ደቀ መዛሙርቱ አድራጎቷን ተቃወሙ። ኢየሱስ “ለምቀበርበት ቀን እንድትጠብቀው ተውአት፤ ድሆችስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ይኖራሉና፣ እኔ ግን ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር አልኖርም” ሲል መለሰላቸው። (ዮሐንስ 12:1-8፤ ማቴዎስ 26:6-13) ኢየሱስ “ከዚህ ዓለም ወደ አብ የሚሄድበት ሰዓት እንደ ደረሰ” ያውቃል። (ዮሐንስ 13:1) ከአምስት ቀን በኋላ ‘ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ይሰጣል።’ (ማርቆስ 10:45) ከዚህ የተነሳ ኢየሱስ በሚያደርገውም ሆነ በሚያስተምረው ነገር ሁሉ ላይ የጥድፊያ ስሜት ይታያል። የዚህን የነገሮች ሥርዓት መጨረሻ በጉጉት ስንጠባበቅ ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል! ኢየሱስ ልክ በሚቀጥለው ቀን ምን እንዳጋጠመው ተመልከት።
ኢየሱስ በድል አድራጊነት የገባበት ቀን
3. (ሀ) ኢየሱስ እሁድ ኒሳን 9 ወደ ኢየሩሳሌም የገባው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው? አጅበውት የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች የሰጡት ምላሽስ ምን ይመስላል? (ለ) ሕዝቡን በተመለከተ ቅሬታ ላሰሙት ፈሪሳውያን ኢየሱስ ምን መልስ ሰጠ?
3 ኢየሱስ እሁድ ኒሳን 9 በድል አድራጊነት ወደ ኢየሩሳሌም ገባ። በዘካርያስ 9:9 ፍጻሜ መሠረት በአህያ ውርንጭላ ላይ ተቀምጦ ወደ ከተማይቱ ሲደርስ ሊቀበሉት ከወጡት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ ልብሳቸውን መንገድ ላይ ያነጠፉለት ሲሆን ሌሎች ደግሞ የዛፍ ቅርንጫፎች እየቆረጡ ይጎዘጉዙለት ነበር። “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው” እያሉ ጮኹ። በሕዝቡ መካከል የነበሩ ፈሪሳውያን ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ገሥጾ ዝም እንዲያሰኛቸው ፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “እላችኋለሁ፣ እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ” ሲል መለሰላቸው።—ሉቃስ 19:38-40፤ ማቴዎስ 21:6-9
4. ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የከተማዋ ሕዝብ እንዳለ ግልብጥ ብሎ የወጣው ለምንድን ነው?
4 በሕዝቡ መካከል ካሉት አብዛኞቹ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሳው ተመልክተዋል። እነሱ ደግሞ ይህን ተአምር አስመልክቶ ለሌሎች ሲያወሩ ነው የከረሙት። ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ የከተማዋ ነዋሪ እንዳለ ግልብጥ ብሎ የወጣው ለዚህ ነው። ሰዎች “ይህ ማን ነው?” ሲሉ ጠየቁ። ሕዝቡም “ይህ ከገሊላ ናዝሬት የመጣ ነቢዩ ኢየሱስ ነው” ብለው መለሱ። ፈሪሳውያን የሆነውን ነገር በመመልከት “ዓለሙ በኋላው ተከትሎት ሄዶአል” በማለት ምሬታቸውን ገለጹ።—ማቴዎስ 21:10, 11፤ ዮሐንስ 12:17-19
5. ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ ሲሄድ ምን ተከሰተ?
5 ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ቁጥር በሚያደርገው መሠረት ለማስተማር ወደ ቤተ መቅደስ ሄደ። እዚያ እያለ ዓይነ ስውራንና አንካሶች ወደ እሱ መጡ፤ እሱም ፈወሳቸው። የካህናት አለቆችና ጻፎች ይህን ሲመለከቱና በቤተ መቅደሱ ያሉት ልጆች “ሆሣዕና ለዳዊት ልጅ” እያሉ የሚያሰሙትን ጩኸት ሲሰሙ ተቆጥተው “እነዚህ የሚሉትን አትሰማምን?” ሲሉ ተቃውሞ አሰሙ። ኢየሱስ “እሰማለሁ፣ ከሕፃናትና ከሚጠቡት አፍ ምስጋናን ለራስህ አዘጋጀህ የሚለውን ቃል ከቶ አላነበባችሁምን?” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ እያስተማረ ሳለ ቤተ መቅደሱ ውስጥ የሚካሄደውን ነገር በጥሞና ቃኘ።—ማቴዎስ 21:15, 16፤ ማርቆስ 11:11
6. በዚህ ጊዜ የኢየሱስ አቀራረብ ከበፊቱ የተለየ የሆነው እንዴት ነው? ለምንስ?
6 የአሁኑ የኢየሱስ አቀራረብ ከስድስት ወር በፊት ከነበረው ምንኛ የተለየ ነው! ያን ጊዜ የዳስ በዓልን ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም ‘የመጣው በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ ነበር።’ (ዮሐንስ 7:10) እንዲሁም ለሕይወቱ የሚያሰጋ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ጉዳት ሳያገኘው ቀስ ብሎ የሚያመልጥበትን እርምጃ ይወስድ ነበር። አሁን ግን እንዲይዙት ትእዛዝ በተላለፈበት ቦታ በግልጽ ወደ ከተማ ገባ! በተጨማሪም ኢየሱስ መሲሕ ነኝ ብሎ ራሱን የማስተዋወቅ ልማድ አልነበረውም። (ኢሳይያስ 42:2፤ ማርቆስ 1:40-44) ሌሎችም ቢሆኑ መሲህ ነው እያሉ እንዲያውጁለት ወይም ስለ እሱ የተዛባ ወሬ እንዲዛመት አይፈልግም ነበር። አሁን ሕዝቡ ንጉሥና አዳኝ እንዲሁም መሲህ እያሉ በይፋ እየጠሩት ነው። እሱም የሃይማኖት መሪዎቹ ሕዝቡን ፀጥ እንዲያሰኝ ያቀረቡለትን ጥያቄ ሳይቀበለው ቀርቷል! የአመለካከት ለውጥ ያደረገው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ኢየሱስ በማግስቱ እንደተናገረው ‘የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ስለደረሰ’ ነው።—ዮሐንስ 12:23
ድፍረት የተሞላበት እርምጃና ሕይወት አድን ትምህርቶች
7, 8. ኢየሱስ ኒሳን 10, 33 እዘአ ላይ የወሰደው እርምጃ በ30 እዘአ በቤተ መቅደሱ በተከበረው የማለፍ በዓል ላይ ያደረገውን ነገር የሚያስታውስ የሆነው እንዴት ነው?
7 ኢየሱስ ሰኞ ኒሳን 10 ቤተ መቅደሱ እንደደረሰ እሁድ ከሰዓት በኋላ በተመለከተው ነገር ላይ እርምጃ ወሰደ። “በመቅደስ የሚሸጡትንና የሚገዙትን ያወጣ ጀመር፣ የገንዘብ ለዋጮችንም ገበታዎች የርግብ ሻጭዎችንም ወንበሮች ገለበጠ፤ ዕቃም ተሸክሞ ማንም በመቅደስ ሊያልፍ አልፈቀደም።” ኢየሱስ ጥፋተኞቹን በማውገዝ “ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት” አላቸው።—ማርቆስ 11:15-17
8 ኢየሱስ የወሰደው እርምጃ ከሦስት ዓመት በፊት በ30 እዘአ በማለፍ በዓል ወደ ቤተ መቅደሱ ሲመጣ ያደረገውን ነገር የሚያስታውስ ነው። ሆኖም በዚህ ጊዜ የሰነዘረባቸው ውግዘት ከበፊቱ ጠንከር ያለ ነው። አሁን ቤተ መቅደሱ ውስጥ ያሉትን ነጋዴዎች “ወንበዴዎች” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ሉቃስ 19:45, 46፤ ዮሐንስ 2:13-16) እንዲህ የተባሉበት ምክንያት ለመሥዋዕት የሚቀርብ እንስሳ ለመግዛት ከሚፈልጉ ሰዎች በጣም ውድ ዋጋ ያስከፍሉ ስለነበር ነው። የካህናት አለቆች፣ ጻፎችና የሕዝቡ ታላላቆች ኢየሱስ እያደረገ ስላለው ነገር ሰምተው እሱን ማስገደል የሚችሉበትን መንገድ እንደገና ይፈልጉ ጀመር። ሆኖም ሕዝቡ ባጠቃላይ በትምህርቱ ተገርመው እሱን ለመስማት ሥር ሥሩ ይከተሉት ስለነበር ኢየሱስን እንዴት አድርገው እንደሚያጠፉት ግራ ገባቸው።—ማርቆስ 11:18፤ ሉቃስ 19:47, 48
9. ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ለነበሩት አድማጮች ያስተማራቸው ትምህርት ምንድን ነው? ምንስ ግብዣ አቀረበላቸው?
9 ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ማስተማሩን በመቀጠል “የሰው ልጅ ይከብር ዘንድ ሰዓቱ ደርሶአል” ሲል ገለጸ። አዎን፣ ሰው ሆኖ የሚያሳልፈው ጥቂት ቀናት ብቻ እንደቀረው ያውቃል። ከራሱ ሞትና ሌሎች የዘላለም ሕይወት እንዲያገኙ መንገድ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ አንዲት የስንዴ ቅንጣት ማፍራት እንድትችል መሞት እንዳለባት ከገለጸ በኋላ ኢየሱስ ለአድማጮቹ እንዲህ ሲል ግብዣ አቀረበላቸው:- “የሚያገለግለኝ ቢኖር ይከተለኝ፣ እኔም ባለሁበት አገልጋዬ ደግሞ በዚያ ይሆናል፣ የሚያገለግለኝም ቢኖር አብ ያከብረዋል።”—ዮሐንስ 12:23-26
10. ኢየሱስ ከፊቱ ስለሚጠብቀው የስቃይ ሞት ምን ተሰማው?
10 ኢየሱስ አራት ቀናት ብቻ የቀረውን አሳዛኝ የሆነ አሟሟቱን በማሰብ እንዲህ በማለት ቀጠለ:- “አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፣ ከዚህ ሰዓት አድነኝ።” ሆኖም ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀው ነገር ሊወገድ የሚችል አይደለም። “ነገር ግን ስለዚህ ወደዚህ ሰዓት መጣሁ” አለ። በእርግጥም ኢየሱስ ከአጠቃላዩ የአምላክ ዝግጅት ጋር ስምም ነው። እስከ መሥዋዕታዊ ሞቱ ድረስ የሚያከናውነው ነገር ሁሉ በመለኮታዊ ፈቃድ እንዲመራ ቁርጥ ውሳኔ አድርጓል። (ዮሐንስ 12:27) ለመለኮታዊ ፈቃድ ሙሉ በሙሉ በመገዛት ረገድ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል!
11. ኢየሱስ ከሰማይ የመጣ ድምፅ ለሰሙት ሰዎች ምን ትምህርት ሰጣቸው?
11 የእሱ ሞት በአባቱ ስም ላይ ሊያስከትል የሚችለው ነገር በጥልቅ ስላሳሰበው ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ስምህን አክብረው” ሲል ጸለየ። በቤተ መቅደሱ የተሰበሰበውን ሕዝብ በሚያስገርም ሁኔታ ከሰማይ የመጣ ድምፅ “አከበርሁት ደግሞም አከብረዋለሁ” ሲል ተሰማ። ታላቁ አስተማሪ ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ድምፁ የተሰማበትን ምክንያት፣ የእሱ ሞት ምን እንደሚያስከትልና እምነት ማሳየት ያለባቸው ለምን እንደሆነ ለሕዝቡ ተናገረ። (ዮሐንስ 12:28-36) በእርግጥም ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ሁለት ቀናት በርካታ ሥራዎች አከናውኗል። ሆኖም ከፊቱ ወሳኝ የሆነ ቀን ይጠብቀዋል።
ተቃዋሚዎቹን ያወገዘበት ዕለት
12. ማክሰኞ፣ ኒሳን 11 የሃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን ለማጥመድ የሞከሩት እንዴት ነው? ውጤቱስ ምን ሆነ?
12 ማክሰኞ ኒሳን 11 ኢየሱስ በድጋሚ ወደ ቤተ መቅደሱ ለማስተማር ሄደ። እዚያ የጠላትነት መንፈስ ያለው አድማጭ ይጠብቀዋል። የካህናት አለቆችና የሕዝብ ሽማግሌዎች ኢየሱስ በበፊተኛው ቀን ያደረገውን ነገር አስመልክተው “በምን ሥልጣን እነዚህን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?” ብለው ጠየቁት። ታላቁ አስተማሪ በመልሱ የሚናገሩትን አሳጣቸው። እንዲሁም በወይን እርሻ ላይ የተመሠረቱ ሁለት ምሳሌዎችና በሠርግ ግብዣ ላይ የተመሠረተ አንድ ምሳሌ በመናገር ተቃዋሚዎቹ ምን ያህል ክፉ መሆናቸውን አጋለጠ። የሃይማኖት መሪዎቹ የሰሙት ነገር ስላስቆጣቸው ሊይዙት ፈለጉ። ሆኖም ሕዝቡ ኢየሱስን እንደ ነቢይ ስለሚመለከቱት ፈሩ። ስለዚህ አሳስተው የሆነ ነገር በማናገር እሱን ማሳሰር የሚችሉበትን መንገድ ፈለጉ። ኢየሱስ የሰጣቸው መልስ አፋቸውን አስያዛቸው።—ማቴዎስ 21:23–22:46
13. ኢየሱስ ጻፎችና ፈሪሳውያንን አስመልክቶ ለአድማጮቹ ምን ምክር ሰጠ?
13 ጻፎችና ፈሪሳውያን የአምላክን ሕግ እናስተምራለን ብለው ስለሚናገሩ ኢየሱስ አድማጮቹን እንዲህ ሲል አጥብቆ አሳሰባቸው:- “ያዘዙአችሁን ሁሉ አድርጉ ጠብቁትም፣ ነገር ግን እየተናገሩ አያደርጉትምና እንደ ሥራቸው አታድርጉ።” (ማቴዎስ 23:1-3) በሕዝብ ፊት ከባድ ውግዘት ሰነዘረባቸው! ሆኖም በዚህ ብቻ አላበቃም። ይህ በቤተ መቅደሱ የሚያሳልፈው የመጨረሻው ቀን ሲሆን ልክ እንደሚያስተጋባ ነጎድጓድ ምንም ሳያስቀር ሥራቸውን አንድ በአንድ በድፍረት አጋለጠ።
14, 15. ኢየሱስ በጻፎችና በፈሪሳውያን ላይ ምን ኃይለኛ የውግዘት ቃል ተናገረ?
14 ኢየሱስ ‘እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፣ ወዮላችሁ’ በማለት ስድስት ጊዜ ደጋግሞ ተናገረ። ግብዞች የሆኑበት ምክንያት ወደ መንግሥተ ሰማያት የሚገቡትን ሰዎች እንዳይገቡ በመከልከል መንግሥተ ሰማያትን በሰው ፊት ስለሚዘጉ መሆኑን ገለጸ። እነዚህ ግብዞች አንድን ሰው ለማሳመን በባሕርና በደረቅ በመዞር ለዘላለም ጥፋት ይዳርጉታል። “ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፣ በሕግ ያለውን ዋና ነገር” ችላ እያሉ አሥራት ማውጣትን በተመለከተ የላቀ ትኩረት ይሰጣሉ። በሌላ አባባል “በውስጡ ቅሚያና ስስት ሞልቶ ሳለ የጽዋውንና የወጭቱን ውጭ” ስለሚያጠሩ የበሰበሰና የተላ ውስጣዊ ማንነታቸው ከውጭ በሚታይ ቅድስና ይሸፈናል። በተጨማሪም ምንም እንኳ “የነቢያት ገዳዮች ልጆች” ቢሆኑም የደግነት ሥራቸውን ሌሎች እንዲያዩላቸው ለነቢያት መቃብር መሥራትና ማስጌጥ ይወዳሉ።—ማቴዎስ 23:13-15, 23-31
15 ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹ በመንፈሳዊ ባዶ መሆናቸውን በማውገዝ ‘እናንተ ዕውሮች መሪዎች፣ ወዮላችሁ’ ብሏቸዋል። የአምልኮ ቦታው ካለው መንፈሳዊ ጠቀሜታ ይልቅ ቤተ መቅደሱ ውስጥ ላለው ወርቅ የበለጠ ትኩረት በመስጠታቸው በሥነ ምግባር ዕውሮች ናቸው። ኢየሱስ ንግግሩን በመቀጠል በጣም ጠንከር ያለ የውግዘት ቃል ተናገረ። “እናንተ እባቦች፣ የእፉኝት ልጆች፣ ከገሃነም ፍርድ እንዴት ታመልጣላችሁ?” አላቸው። አዎን፣ ኢየሱስ መጥፎ አካሄድ በመከተላቸው ዘላለማዊ ጥፋት እንደሚጠብቃቸው መናገሩ ነው። (ማቴዎስ 23:16-22, 33) እኛም የመንግሥቱ መልእክት የሐሰት ሃይማኖትን ማጋለጥ የሚያካትት በሚሆንበት ጊዜም እንኳ መልእክቱን ለማወጅ ድፍረት እናሳይ።
16. በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ተቀምጠው ሳሉ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የነገራቸው ክብደት ያዘለ ትንቢት ምንድን ነው?
16 አሁን ኢየሱስ ከቤተ መቅደሱ ወጥቶ ሄደ። እሱና ሐዋርያቱ እያዘቀዘቀች ባለችው የከሰዓት በኋላ ጀምበር የደብረ ዘይትን ተራራ ወጡ። እዚያ ተቀምጠው ኢየሱስ ስለ ቤተ መቅደሱ መፍረስ፣ ስለ መገኘቱና ስለ ነገሮች ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት ትንቢት ተናገረ። እነዚህ ትንቢታዊ ቃላት እስከ ዘመናችን የሚደርስ ቁም ነገር ይዘዋል። በተጨማሪም ኢየሱስ የዚያን ዕለት ምሽት ለደቀ መዛሙርቱ “ከሁለት ቀን በኋላ ፋሲካ እንዲሆን ታውቃላችሁ፣ የሰው ልጅም ሊሰቀል አልፎ ይሰጣል” አላቸው።—ማቴዎስ 24:1-14፤ 26:1, 2
ኢየሱስ “ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው”
17. (ሀ) በኒሳን 14 የማለፍ በዓል ወቅት ኢየሱስ ለ12ቱ የሰጣቸው ትምህርት ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የአስቆሮቱ ይሁዳን ካሰናበተ በኋላ ያቋቋመው በዓል ምንድን ነው?
17 በቀጣዮቹ ሁለት ቀናት ማለትም ኒሳን 12 እና 13 ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በግልጽ አልታየም። የሃይማኖት መሪዎቹ እሱን ለመግደል ፍለጋ ላይ ናቸው። እሱ ደግሞ ከሐዋርያቱ ጋር የሚያከብረውን የማለፍ በዓል አንድም ነገር እንዲያስተጓጉልበት አልፈለገም። ሐሙስ ዕለት ፀሐይ ስትጠልቅ ኢየሱስ ሰው ሆኖ በምድር የሚያሳልፈው ሕይወት የመጨረሻ ቀን ማለትም ኒሳን 14 ጀመረ። የዚያን ዕለት ምሽት ኢየሱስና ሐዋርያቱ የማለፍን በዓል ለማክበር በተዘጋጀላቸው በኢየሩሳሌም በሚገኝ ቤት ውስጥ አብረው ተቀምጠዋል። የማለፍን በዓል እያከበሩ ሳለ ኢየሱስ የ12ቱን እግር በማጠብ ትሕትናን በተመለከተ ግሩም ትምህርት ሰጣቸው። በሙሴ ሕግ መሠረት የአንድ ባሪያ ዋጋ በሆነ በ30 ብር ጌታውን አሳልፎ ለመስጠት የተስማማውን የአስቆሮቱ ይሁዳን ካሰናበተ በኋላ ኢየሱስ የሞቱን መታሰቢያ በዓል አቋቋመ።—ዘጸአት 21:32፤ ማቴዎስ 26:14, 15, 26-29፤ ዮሐንስ 13:2-30
18. ኢየሱስ ለ11ዱ ታማኝ ሐዋርያት በፍቅራዊ መንገድ ያካፈላቸው ተጨማሪ ትምህርቶች ምንድን ናቸው? እንዲሁም እየቀረበ ላለው ተለይቷቸው ለሚሄድበት ጊዜ ያዘጋጃቸው እንዴት ነው?
18 የሞቱ መታሰቢያ በዓል ከተቋቋመ በኋላ ሐዋርያቱ ከመካከላቸው ማን ታላቅ እንደሆነ በጦፈ ስሜት ይከራከሩ ጀመር። ኢየሱስ እነሱን ከመዝለፍ ይልቅ ሌሎችን ማገልገል ስላለው ዋጋ በትዕግሥት አስተማራቸው። በፈተናዎቹ ከእሱ ጋር የጸኑ መሆናቸውን በማድነቅ ከእነሱ ጋር በግሉ የመንግሥት ቃል ኪዳን አደረገ። (ሉቃስ 22:24-30) በተጨማሪም እሱ እንደወደዳቸው ሁሉ እርስ በርሳቸውም እንዲዋደዱ ትእዛዝ ሰጣቸው። (ዮሐንስ 13:34) ኢየሱስ ክፍሉ ውስጥ ባደረገው ቆይታ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ተለይቷቸው ለሚሄድበት ጊዜ በፍቅራዊ መንገድ አዘጋጃቸው። ወዳጃቸው መሆኑን አረጋገጠላቸው፣ እምነት እንዲኖራቸው አበረታታቸው እንዲሁም የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንደሚያገኙ ቃል ገባላቸው። (ዮሐንስ 14:1-17፤ 15:15) ኢየሱስ ከቤቱ ከመውጣቱ በፊት ለአባቱ እንዲህ ሲል ልመና አቀረበ:- “አባት ሆይ፣ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ . . . ልጅህን አክብረው።” በእርግጥም ኢየሱስ ሐዋርያቱን ተለይቷቸው ለሚሄድበት ጊዜ አዘጋጅቷቸዋል፤ ደግሞም ‘ወገኖቹን የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።’—ዮሐንስ 13:1፤ 17:1
19. ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የአትክልት ሥፍራ ከመጠን በላይ የተጨነቀው ለምንድን ነው?
19 ኢየሱስና 11ዱ ታማኝ ሐዋርያት በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሲደርሱ እኩለ ሌሊት አልፏል። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ወደዚህ ቦታ በተደጋጋሚ ይሄድ ነበር። (ዮሐንስ 18:1, 2) በጥቂት ሰዓታት ውስጥ እንደ ተራ ወንጀለኛ ተቆጥሮ ሊገደል ነው። ከፊቱ የሚጠብቀው ይህ መከራና በአባቱ ላይ ሊደርስ የሚችለው ነቀፋ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በሚጸልይበት ጊዜ ወዙ እንደ ደም ነጠብጣብ በምድር ላይ ወረደ። (ሉቃስ 22:41-44) ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “ሰዓቲቱ ደረሰች። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል” አላቸው። ገና ተናግሮ ሳይጨርስ የአስቆሮቱ ይሁዳ ችቦ፣ ፋኖስና መሣሪያ በታጠቁ በርካታ ሰዎች ታጅቦ መጣ። የመጡት ኢየሱስን ለመያዝ ነው። እሱም ራሱን ለማስጣል አልሞከረም። “እንዲህ ከሆነስ:- እንደዚህ ሊሆን ይገባል የሚሉ መጻሕፍት እንዴት ይፈጸማሉ?” ሲል ገለጸ።—ማርቆስ 14:41-43፤ ማቴዎስ 26:48-54
የሰው ልጅ ክብር ተጎናጸፈ!
20. (ሀ) ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ ምን ጭካኔ የተሞላበት ድርጊት ተፈጸመበት? (ለ) ኢየሱስ ሊሞት ሲል “ተፈጸመ” ብሎ የጮኸው ለምንድን ነው?
20 ኢየሱስ ከተያዘ በኋላ የሐሰት ምሥክሮች ወነጀሉት፣ አድሏዊ የሆኑ ዳኞች ጥፋተኛ ነህ ብለው ፈረዱበት፣ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ሞት በየነበት፣ ካህናትና ሕዝቡ አፌዙበት፣ ወታደሮች ደግሞ ዘበቱበት እንዲሁም አሠቃዩት። (ማርቆስ 14:53-65፤ 15:1, 15፤ ዮሐንስ 19:1-3) አርብ እኩለ ቀን ኢየሱስ የመከራ እንጨት ላይ በምስማር ተቸንክሮ እጅና እግሩ የተበሳበት ቦታ በሰውነቱ ክብደት ሲቀደድ ከፍተኛ ሥቃይ ደረሰበት። (ዮሐንስ 19:17, 18) ከሰዓት በኋላ ወደ ዘጠኝ ሰዓት ገደማ ኢየሱስ “ተፈጸመ” ሲል ጮኸ። አዎን፣ ወደ ምድር መጥቶ መሥራት የነበረበትን ሁሉ ፈጽሟል። መንፈሱን ለአምላክ አደራ ሰጥቶ ራሱን አዘንብሎ ሞተ። (ዮሐንስ 19:28, 30፤ ማቴዎስ 27:45, 46፤ ሉቃስ 23:46) ከዚያ በኋላ ይሖዋ ልጁን በሦስተኛው ቀን ከሞት አስነሣው። (ማርቆስ 16:1-6) ኢየሱስ ከትንሣኤው ከአርባ ቀን በኋላ ወደ ሰማይ አርጎ ክብር አገኘ።—ዮሐንስ 17:5፤ ሥራ 1:3, 9-12፤ ፊልጵስዩስ 2:8-11
21. ኢየሱስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
21 ‘የኢየሱስን ፍለጋ’ በቅርብ ልንከተል የምንችለው እንዴት ነው? (1 ጴጥሮስ 2:21) እሱ እንዳደረገው ሁሉ በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በሙሉ ኃይላችን እንሳተፍ እንዲሁም የአምላክን ቃል በመናገር ረገድ ደፋርና ቆራጥ እንሁን። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20፤ ሥራ 4:29-31፤ ፊልጵስዩስ 1:14) በጊዜ ሂደት የት ላይ እንደደረስን ፈጽሞ አንዘንጋ ወይም አንዳችን ሌላውን ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ለማነቃቃት ቸል አንበል። (ማርቆስ 13:28-33፤ ዕብራውያን 10:24, 25) አኗኗራችን ባጠቃላይ በይሖዋ ፈቃድና በ“ፍጻሜ ዘመን” እንደምንኖር ባለን ግንዛቤ የሚመራ እንዲሆን እንፍቀድ።—ዳንኤል 12:4
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ መቃረቡን ማወቁ በኢየሩሳሌም በሚገኘው ቤተ መቅደስ ለመጨረሻ ጊዜ ባከናወነው አገልግሎት ላይ ያሳደረው ተጽእኖ ምንድን ነው?
• ኢየሱስ ‘ወገኖቹን እስከ መጨረሻ እንደወደዳቸው’ የሚያሳየው ምንድን ነው?
• በኢየሱስ ሕይወት የመጨረሻዎቹ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ የተከሰቱት ነገሮች ስለ እሱ ምን ይጠቁማሉ?
• በአገልግሎታችን ክርስቶስ ኢየሱስን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ “እስከ መጨረሻ ወደዳቸው ”