ትሑት የነበረው ኢዮስያስ የይሖዋን ሞገስ አግኝቷል
የአምስት ዓመቱ የይሁዳ መስፍን ኢዮስያስ ፈርቶ መሆን አለበት። እናቱ ይዲዳ እያለቀሰች ነው። የምታለቅሰው የኢዮስያስ አያት ንጉሥ ምናሴ ስለሞተ ነው።—2 ነገሥት 21:18
አሁን የኢዮስያስ አባት አሞጽ የይሁዳ ንጉሥ ሊሆን ነው። (2 ዜና መዋዕል 33:20) አሞጽ ከሁለት ዓመት በኋላ (በ659 ከዘአበ) በገዛ አገልጋዮቹ ተገደለ። ሕዝቡ ሴረኞቹን ገደለና ገና ልጅ የሆነውን ኢዮስያስን አነገሡት። (2 ነገሥት 21:24፤ 2 ዜና መዋዕል 33:25) በአሞጽ የግዛት ዘመን ለሐሰት አማልክት የሚሰግደው ሕዝብ በጣሪያዎቻቸው ላይ መሠዊያዎች ስለነበራቸው ኢዮስያስ የኢየሩሳሌምን አየር የሚሞላውን የዕጣን ጭስ ማሽተቱን ለምዶት ነበር። አረማዊ ካህናት ከወዲያ ወዲህ ሽር ጉድ ሲሉ ይታያል፤ ተከታዮቻቸው ደግሞ ሌላው ቀርቶ ይሖዋን እናመልካለን የሚሉ እንኳ ሳይቀሩ በሚልኮም አምላክ ስም መማል ጀምረው ነበር።—ሶፎንያስ 1:1, 5
ኢዮስያስ፣ አሞጽ የሐሰት አማልክትን በማምለክ ኃጢአት እንደሠራ ያውቃል። እንዲሁም ወጣቱ የይሁዳ ንጉሥ የአምላክ ነቢይ የሆነው ሶፎንያስ ስለተናገረው መልእክት በደንብ ተረድቶ ነበር። ኢዮስያስ 15 ዓመት ሲሞላው (በ652 ከዘአበ) ለስምንት ዓመታት የገዛ ሲሆን ሶፎንያስ የተናገረውን ተግባራዊ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። ኢዮስያስ ይሖዋን መፈለግ የጀመረው ገና ልጅ ሳለ ነው።—2 ዜና መዋዕል 33:21, 22፤ 34:3
ኢዮስያስ ለሥራ ተንቀሳቀሰ!
ከአራት ዓመታት በኋላ (648 ከዘአበ) ኢዮስያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የሐሰት ሃይማኖት ማጥፋት ጀመረ። ጣዖታትን፣ የማምለኪያ ዐፀዶችንና ለበኣል አምልኮ ዕጣን የሚታጠንባቸውን መሠዊያዎች አጠፋ። የሐሰት አማልክት ምስሎችን ካደቀቀ በኋላ ለእነርሱ መሥዋዕት በተደረጉ ሰዎች መቃብር ላይ በተነው። ለሐሰት አምልኮ የሚያገለግሉ መሠዊያዎች እንዲረክሱ ከተደረገ በኋላ እርምጃ ተወሰደባቸው።—2 ነገሥት 23:8-14
የሌዋዊው ካህን ልጅ ኤርምያስ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ (647 ከዘአበ) ኢዮስያስ እርምጃውን አጧጡፎት ነበር። ይሖዋ አምላክ ወጣቱን ኤርምያስን ነቢይ አድርጎ የሾመለት ሲሆን እሱም ይሖዋ የሐሰት ሃይማኖትን እንደሚያጠፋ የሚገልጸውን መልእክት በግለት ያውጅ ነበር! ኢዮስያስ የኤርምያስ እኩያ ነበር። ምንም እንኳ ኢዮስያስ በድፍረት ቢንቀሳቀስም ኤርምያስ ያለ ፍርሃት ቢያውጅም ሕዝቡ ወዲያውኑ ወደ ሐሰት አምልኮ ተመለሰ።—ኤርምያስ 1:1-10
በዋጋ የማይተመን ግኝት!
አምስት የሚያክሉ ዓመታት አለፉ። የሃያ አምስት ዓመቱ ኢዮስያስ ለ18 ዓመታት ያክል ገዛ። ኢዮስያስ ጸሐፊውን ሳፋንንና የከተማይቱን አለቃ መዕሤያን እንዲሁም ታሪክ ጸሐፊውን ኢዮአክን ወደ እርሱ ጠራቸው። ንጉሡ ሳፋንን ‘ወደ ካህናቱ አለቃ ወደ ኬልቅያስ ሄደህ የመቅደሱ ጠባቂዎች ከሕዝቡ የሰበሰቡትን ገንዘብ የተናደውን የይሖዋን ቤት እንዲያድሱ ለሠራተኞች እንዲሰጡ ንገራቸው’ ሲል አዘዘው።—2 ነገሥት 22:3-6፤ 2 ዜና መዋዕል 34:8
መቅደሱን የሚያድሱት ሠራተኞቹ ከማለዳ አንስተው በትጋት ሥራቸውን አከናወኑ። ኢዮስያስ ክፉ የነበሩት አንዳንድ የቀድሞ አባቶቹ በአምላክ ቤት ላይ ያደረሱትን ጥፋት ሠራተኞቹ መልሰው በማደሳቸው ይሖዋን ባለ ውለታው አድርጎ እንደተመለከተው ጥርጥር የለውም። ሥራው በመፋጠን ላይ ሳለ ሳፋን ሪፖርት ሊያደርግ መጣ። በእጁ የያዘው ምንድን ነው? አንድ የሆነ ጥቅልል ይዟል! ሳፋን ሊቀ ካህኑ ኬልቅያስ “በሙሴ እጅ የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ” እንዳገኘ ነገረው። (2 ዜና መዋዕል 34:12-18) የሚያስደንቅ ነው፤ የተገኘው የሕጉ የመጀመሪያ ቅጂ መሆኑ ጥርጥር የለውም!
ኢዮስያስ መጽሐፉ ምን እንደሚል የመስማት ጉጉት አደረበት። ሳፋን ሲያነብብለት ንጉሡ እሱም ሆነ ሕዝቡ እያንዳንዱን ትእዛዝ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ያወጣ ያወርድ ነበር። በተለይ ደግሞ መጽሐፉ ስለ እውነተኛው አምልኮ በአጽንዖት ስለሚናገር እንዲሁም ሕዝቡ የሐሰት አምልኮን ከተከተለ መቅሰፍት እንደሚደርስበትና በግዞት እንደሚወሰድ ትንቢት እንደሚናገር ሲገነዘብ በጣም ተገረመ። ኢዮስያስ የአምላክን ትእዛዛት በጥብቅ እንዳልተከተሉ ሲገነዘብ ልብሱን ቀደደና ለኬልቅያስ፣ ለሳፋን እንዲሁም ለሌሎቹ ‘አባቶቻችን በዚህ መጽሐፍ የተጻፈውን ቃል ሁሉ ስላልጠበቁ የይሖዋ ቁጣ በላያችን በጣም ስለነደደ ሄዳችሁ ስለተገኘው የመጽሐፍ ቃል ይሖዋን ጠይቁ’ የሚል ትእዛዝ ሰጣቸው።—2 ነገሥት 22:11-13፤ 2 ዜና መዋዕል 34:19-21
የይሖዋ ቃል ተላለፈ
የኢዮስያስ መልእክተኞች በኢየሩሳሌም ወደምትኖረው ወደ ነቢይቱ ሕልዳና ሄደው መልስ ይዘው መጡ። ሕልዳና አዲስ በተገኘው መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው መቅሰፍት በከሃዲው ብሔር ላይ እንደሚደርስ በመጠቆም የይሖዋን ቃል አስተላለፈች። ይሁን እንጂ ኢዮስያስ በይሖዋ ፊት ትሑት ሆኖ ስለተገኘ መቅሰፍቱ አያገኘውም። በሰላም ወደ አባቶቹ ይሰበሰባል።—2 ነገሥት 22:14-20፤ 2 ዜና መዋዕል 34:22-28
ኢዮስያስ የሞተው በጦርነት ሆኖ ሳለ ሕልዳና የተናገረችው ትንቢት በትክክል ተፈጽሟል ማለት ይቻላል? (2 ነገሥት 23:28-30) ወደ አባቶቹ ‘በሰላም’ ተሰብስቧል ሊባል የሚቻለው በይሁዳ ላይ ከሚደርሰው መቅሰፍት ጋር ሲወዳደር ነው። (2 ነገሥት 22:20፤ 2 ዜና መዋዕል 34:28) ኢዮስያስ የሞተው ባቢሎናውያን ከ609-607 ከዘአበ ኢየሩሳሌምን ከብበው ባጠፉበት ወቅት ከደረሰው መቅሰፍት በፊት ነው። እንዲሁም ‘ወደ አባቶቹ መቃብር በሰላም ይሰበሰባል’ ሲባል መጥፎ አሟሟት አያጋጥመውም ማለት አይደለም። መጥፎ ለሆነ አሟሟትም ሆነ ሰላማዊ ለሆነ አሟሟት የሚያገለግለው ተመሳሳይ አገላለጽ ነው።—ዘዳግም 31:16፤ 1 ነገሥት 2:10፤ 22:34, 40
እውነተኛው አምልኮ ተስፋፋ
ኢዮስያስ የኢየሩሳሌምን ሕዝብ ወደ ቤተ መቅደሱ ሰብስቦ በይሖዋ ቤት የተገኘውን “የቃል ኪዳኑን መጽሐፍ ቃል ሁሉ” አነበበላቸው። እሱም “እግዚአብሔርን ተከትሎ ይሄድ ዘንድ ትእዛዙንና ምስክሩን ሥርዓቱንም በፍጹም ልቡና በፍጹም ነፍሱ ይጠብቅ ዘንድ በዚሁም መጽሐፍ የተጻፈውን የቃል ኪዳን ቃል ያጸና ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ቃል ኪዳን አደረገ።” ሕዝቡም ሁሉ በቃል ኪዳኑ ተስማሙ።—2 ነገሥት 23:1-3
ንጉሥ ኢዮስያስ በጣዖት አምልኮ ላይ ይበልጥ የተጠናከረ ሌላ ዘመቻ ጀመረ። በይሁዳ የሚገኙት የባዕድ አምላክ ካህናት ከሥራ ውጪ ተደረጉ። በርኩስ አምልኮ የተካፈሉ ሌዋውያን ካህናት በይሖዋ መሠዊያ ላይ የማገልገል መብታቸውን ያጡ ሲሆን በንጉሥ ሰሎሞን የግዛት ዘመን የተሠሩ የኮረብታ መስገጃዎች ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ ተደረገ። ዘመቻው ቀደም ብሎ (740 ከዘአበ) በአሦራውያን የተገለበጠውን የአሥሩን ነገድ የእስራኤል መንግሥትም ይጨምራል።
ስሙ ያልተጠቀሰ አንድ “የእግዚአብሔር ሰው” ከ300 ዓመታት በፊት የተናገረው ቃል ፍጻሜውን እንዲያገኝ ኢዮስያስ ንጉሥ ኢዮርብዓም ቀዳማዊ በቤቴል በሠራው መሠዊያ ላይ የበዓልን ካህናት አጥንት አቃጠለ። በቤቴልም ሆነ በሌሎች ከተማዎች የሚገኙት የኮረብታ መስገጃዎች የተወገዱ ሲሆን ጣዖት አምላኪ ካህናት በሚያገለግሉበት መሠዊያ ላይ መሥዋዕት ተደረጉ።—1 ነገሥት 13:1-4፤ 2 ነገሥት 23:4-20
ታላቅ የማለፍ በዓል ተከበረ
ኢዮስያስ ንጹሑን አምልኮ ለማስፋፋት የወሰደው እርምጃ መለኮታዊ ድጋፍ ነበረው። ንጉሡ በሕይወት እስካለ ድረስ ሕዝቡ “የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን ከመከተል” ባለመራቃቸው አምላክን አመስግኗል። (2 ዜና መዋዕል 34:33) ኢዮስያስ በ18ኛው የግዛት ዘመኑ ላይ የተከናወነውን አስደናቂ ነገር እንዴት ሊረሳው ይችላል?
ንጉሡ “በዚህ [በቅርብ በተገኘው] በቃል ኪዳን መጽሐፍ እንደ ተጻፈው ለአምላካችሁ ለእግዚአብሔር ፋሲካ አድርጉ” በማለት ሕዝቡን አዘዘ። (2 ነገሥት 23:21) ኢዮስያስ ሕዝቡ በሰጠው ግሩም ምላሽ ተደሰተ። ለበዓሉ እሱ ራሱ 30, 000 የበግና የፍየል ጠቦቶች እንዲሁም 3, 000 ወይፈኖች አዋጣ። እንዴት ያለ ታላቅ የማለፍ በዓል ነበር! በቀረበው መሥዋዕት ብዛት፣ በጥሩ እቅድ በተደረገው ዝግጅት እንዲሁም በበዓሉ ላይ በተገኙት አምላኪዎች ብዛት ከነቢዩ ሳሙኤል በኋላ ከተከበሩት የማለፍ በዓሎች ሁሉ ይበልጣል።—2 ነገሥት 23:22, 23፤ 2 ዜና መዋዕል 35:1-19
ለሞቱ የተደረገ ታላቅ ሐዘን
ኢዮስያስ በቀሪዎቹ 31 ዓመታት የግዛት ዘመኑ ሁሉ (659-629 ከዘአበ) ጥሩ ንጉሥ በመሆን ገዝቷል። ኢዮስያስ በግዛት ዘመኑ ማብቂያ አካባቢ ፈርዖን ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ ባለው በከርከሚሽ የባቢሎንን ሠራዊት ግስጋሴ በመግታት ለአሦር ንጉሥ ድጋፍ ለመስጠት በሚወጣበት ጊዜ ይሁዳን አቋርጦ የማለፍ እቅድ እንዳለው ተገንዝቦ ነበር። ኢዮስያስ ባልታወቀ ምክንያት ከግብጻውያን ጋር ለመዋጋት ወጣ። ኒካዑ “ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ይህን ከእርሱ ላይ ከማድረግ ተመለስ” ብሎ መልእክተኞች ላከበት። ሆኖም ኢዮስያስ ራሱን በመደበቅ ግብጻውያንን ወደ መጊዶ ለመመለስ ሞከረ።—2 ዜና መዋዕል 35:20-22
ለይሁዳ ንጉሥ ይህ መጥፎ አጋጣሚ ነበር! የጠላት ቀስተኞች አነጣጥረው ስለመቱት አገልጋዮቹን “አጥብቄ ቆስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” ብሎ ነገራቸው። ኢዮስያስን ከጦር ሰረገላው አውርደው በሌላ ሰረገላ ላይ ካስቀመጡት በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ሸሹ። ኢዮስያስ ከተማ ከገባ በኋላ የመጨረሻዋን እስትንፋስ ተነፈሰ። ቅዱስ ጽሐፉ “እርሱም ሞተ፣ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ” በማለት ይዘግባል። ኤርምያስ የሐዘን እንጉርጉሮ የገጠመለት ሲሆን ከዚያ ጊዜ ወዲህ ስለ ሐዘን እንጉርጉሮ ሲነሳ ንጉሡን ያስታውሱ ነበር።—2 ዜና መዋዕል 35:23-25
አዎን፣ ንጉሥ ኢዮስያስ ከግብጻውያን ጋር በመዋጋት አሳዛኝ ስህተት ሠርቷል። (መዝሙር 130:3) የሆነ ሆኖ ትሕትናውና ለእውነተኛው አምልኮ ያሳየው ቆራጥነት የአምላክን ሞገስ አስገኝቶለታል። የኢዮስያስ ሕይወት ይሖዋ ትሑት ልብ ላላቸው አገልጋዮቹ ሞገሱን እንደሚሰጣቸው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።—ምሳሌ 3:34፤ ያዕቆብ 4:6
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወጣቱ ንጉሥ ኢዮስያስ ይሖዋን አጥብቆ ፈለገ
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢዮስያስ የኮረብታ መስገጃዎችን በማስወገድ እውነተኛውን አምልኮ አስፋፍቷል