ለቺያፓስ ተራራማ አካባቢዎች የሰላም ምሥራች ደረሰ
“መሣሪያ የታጠቁ . . . የአንድ ቡድን አባላት 13 ጨቅላ ሕፃናትን ጨምሮ ራሳቸውን መከላከል በማይችሉ 45 ገበሬዎች ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ በቺያፓስ ታሪክ ከተፈጸሙት የጭካኔ ድርጊቶች ሁሉ ይበልጥ ዘግናኝ ነው” ሲል “ኤል ዩኒቨርሳል” የተባለው ጋዜጣ በታኅሣሥ 22, 1997 እትሙ በቺያፓስ ግዛት በኦክቲኦል የደረሰውን ሁኔታ አስመልክቶ ዘግቧል።
ቺያፓስ ከጓቲማላ ጋር የምትዋሰን የሜክሲኮ ደቡባዊ ጠረፍ ግዛት ናት። ረጅም የድህነት ታሪክ ያስቆጠሩት የአገሬው ተወላጆች የሆኑት የማያ ሕንዶች ቡድን ኢጀርሲቶ ዛፓቲስታ ዴ ሊበራሲዮን ናሲዮናል (EZLN ማለትም የዛፓቲስታ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ጦር) በሚል መጠሪያ ጥር 1994 መሣሪያ አነሳ። ሰላማዊ መፍትሄ ለማስገኘት የሚደረገው ድርድር ሲጓተት ቆይቷል። አማፂያኑም ሆኑ የመንግሥት ወታደሮች የሚያካሂዱት ወረራና የሚሰነዝሩት ጥቃት ከፍተኛ ደም መፋሰስና እልቂት አስከትሏል። ግጭቱ ብዙዎቹ ገበሬዎች አካባቢውን ጥለው እንዲሸሹ አድርጓል።
በዚህ ሁከት በነገሠበት ሁኔታ ውስጥ ከፖለቲካ ትግሉ ገለልተኛ የሆነ አንድ ሰላም አፍቃሪ ቡድን አለ። የዚህ ቡድን አባላት በዚያ አካባቢም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰው ልጆች ለገጠሟቸው ችግሮች መፍትሄ በማምጣት ረገድ ብቸኛው ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን በቅንዓት ይናገራሉ። (ዳንኤል 2:44) ለመሆኑ እነዚህ እነማን ናቸው? የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ራቅ ብለው በሚገኙ የቺያፓስ ተራራማ አካባቢዎች ሳይቀር የአምላክን መንግሥት ምሥራች ለማድረስ በመጣር ላይ ይገኛሉ። (ማቴዎስ 24:14) እንዲህ ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ መስበክ ምን ይመስላል? ውጤቱስ?
“እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ”
በቅርቡ የመንግሥቱ አስፋፊ የሆነው ወጣቱ አዶልፎ አንድ ቀን ኦኮሴንጎ በሚገኘው ራዲዮ ጣቢያ እየሠራ ሳለ በድንገት በሩ በኃይል ተንኳኳ። ፊታቸውን የሸፈኑ ሰዎች በሩን በርግደው ገብተው ጭንቅላቱ ላይ መሣሪያ ደገኑበት። ከዚያም ወደ ስቱዲዮው ከገቡ በኋላ በመንግሥት ላይ ጦርነት ማወጃቸውን በራዲዮ አሰራጩ።
የታጠቁት ሰዎች ወደ አዶልፎ ዘወር በማለት የእኛ ንቅናቄ አባል መሆን አለብህ አሉት። ምንም እንኳ ገና ያልተጠመቀ ቢሆንም “እኔ የይሖዋ ምሥክር ነኝ” ሲል መለሰላቸው። ብቸኛ የሰላም ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን የገለጸላቸው ሲሆን የሰጡትን የደንብ ልብስና መሣሪያም ፈጽሞ አልቀበልም አለ። ከአቋሙ ንቅንቅ እንደማይል ሲመለከቱ ለቀቁት። አዶልፎ ሁኔታውን ሲያስታውስ “ይህ ሁኔታ በእርግጥም እምነቴን አጠንክሮልኛል” በማለት ይገልጻል።
በመጨረሻ ሁኔታው ቢረጋጋም አካባቢው በወታደሮች ቁጥጥር ሥር ነበር። እንደዚያም ሆኖ አዶልፎ ራቅ ብሎ ከሚገኝ አንድ የክርስቲያኖች ቡድን ጋር እንዲያገለግል በአካባቢው የሚገኝ ጉባኤ ሽማግሌዎች ያቀረቡለትን ግብዣ በደስታ ተቀበለ። አልፎ በሚሄድባቸው የፍተሻ ጣቢያዎች የሚገኙ ወታደሮች የይሖዋ ምሥክር መሆኑን ሲነግራቸው በአክብሮት ያሳልፉት ነበር። አዶልፎ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን ያ ቡድን የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ወደ መሆን ደረጃ እንዲደርስ በመርዳት ደስታ አግኝቷል። “አሁን ተጠምቄያለሁ፤ ስለዚህ አፌን ሞልቼ የይሖዋ ምሥክር ነኝ ብዬ መናገር እችላለሁ” በማለት ይናገራል።
“ይሖዋ ብርታት ሰጠን”
አማፂ ቡድኑ በመንግሥት ላይ ጦርነት ማወጁን በራዲዮ እንዳስተላለፈ የከተማዋ ነዋሪዎች አካባቢውን ጥለው ሸሹ። ፍራንሴስኮ የተባለ አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ወይም አቅኚ ማለፍ የነበረባቸውን ችግሮች እንዲቋቋሙ ይሖዋ ለእሱና ለሚስቱ ምን ያህል ብርታት እንደሰጣቸው ገልጿል።
“ከመኖሪያችን ሦስት ሰዓት የእግር መንገድ ርቆ በሚገኝ ቦታ ለመቀመጥ ወሰንን። በዚያ ጉባኤ ስላለ ከወንድሞች ጋር እንሆናለን። በፖለንኬ የወረዳ ስብሰባ የሚደረግበት ቀንም ተቃርቦ ነበር። እኔና ባለቤቴ ከአቅኚዎች ጋር የሚደረገው ስብሰባ እንዲያመልጠን አልፈለግንም። ሆኖም የወረዳ ስብሰባው ወደሚደረግበት ቦታ የሚወስደው መንገድ በአማፂ ቡድኑ እንደተዘጋ ሰማን። ጫካ ለጫካ ተሽሎክልከን ለመሄድ የወሰንን ሲሆን ይህም ዘጠኝ ሰዓት ፈጀብን። የአቅኚዎች ስብሰባ ሳያመልጠን ከመድረሳችንም በላይ በጠቅላላ በወረዳ ስብሰባው ፕሮግራምም ሆነ በአቅኚዎች ስብሰባ በጣም ተደሰትን።
“ስንመለስ ቤታችን ተቃጥሎ ከብቶቻችንም ተሰርቀው ደረስን። የቀረ ነገር ቢኖር አንድ ትንሽ ሻንጣ ልብስ ብቻ ነበር። በደረሰብን ሁኔታ ብናዝንም በኦኮዚንጎ የሚገኙ ወንድሞች በደግነት ወደ ቤታቸው ወሰዱን። በተጨማሪም እኛ ገበሬዎች እንደመሆናችን መጠን ከዚህ በፊት ሠርተናቸው የማናውቃቸውን ሥራዎች አሳይተውናል። አንድ ወንድም ፎቶ ማንሳት ያስተማረኝ ሲሆን ሌላ ወንድም ደግሞ ጫማ መጠገን አሳየኝ። እኔና ባለቤቴ የአቅኚነት አገልግሎታችንን ሳናቋርጥ እስከ አሁን ድረስ ራሳችንን እየረዳን መኖር የቻልነው በዚህ መንገድ ነው። የደረሰብንን ሁኔታ ወደኋላ መለስ ብለን ስናስብ ምንም እንኳ መጽናት ቀላል ባይሆንም ይሖዋ ብርታት እንደሰጠን ተገንዝበናል።”
የስብከቱ ሥራ ያስገኘው ፍሬ
በቺያፓስ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ችግሩም ሆነ አደጋው በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ሰዎች ምሥራቹን ለማዳረስ እየተደረገ ባለው ልዩ ጥረት ከመካፈል አላገዳቸውም። ለምሳሌ ያህል በሚያዝያና ግንቦት 1995 የሰው ሕይወት በችግር የተሞላው ለምንድን ነው? የሚል በጣም ወቅታዊ የሆነ ርእስ ይዞ የወጣውን የመንግሥት ዜና ቁጥር 34 በማሰራጨቱ ዘመቻ በመካፈል በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ክርስቲያን ባልንጀሮቻቸው ጋር አንድ ሆነዋል።
በዚህ ዘመቻ ወቅት ሲሮ የሚባል አንድ አቅኚ ፐውብሎ ንዌቦ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ፍላጎት ያሳየ አንድ ቤተሰብ አገኘ። ከሦስት ቀን በኋላ ተመልሶ ሄዶ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አስጀመራቸው። ሆኖም በሌላ ቀን ሲሮ እና አንድ ጓደኛው ቤተሰቡን ሊያስጠኑ ሲሄዱ የቤቱ ባለቤት አልነበረም። ከዚህ ይልቅ በሲሮ ላይ ጉዳት ለማድረስ ይጠብቁት የነበሩ ራሳቸውን የሸፈኑ ሰዎች አገኙ። እነዚህ ፊታቸውን የሸፈኑ ሰዎች ሲሮንና ጓደኛውን እንደሚገድሏቸው በመዛት ምን እንደሚፈልጉ ጠየቋቸው። ሁለቱ ክርስቲያኖች በልባቸው ወደ ይሖዋ ከጸለዩ በኋላ ቤተሰቡን መጽሐፍ ቅዱስ ለማስጠናት መምጣታቸውን በድፍረት ተናገሩ። ከዚያም ምንም ሳያደርጓቸው ለቀቋቸው። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይታወቅም የቤቱ ባለቤት የዚያን ዕለት ፈጽሞ ወደ ቤት አልተመለሰም።
ከሦስት ዓመት ገደማ በኋላ አንድ ቀን ያ ሰው እቤቱ ሲመጣ ሲሮ ዓይኑን ማመን አቃተው። ሲሮ መላው ቤተሰብ እንደተጠመቀና አሁን ጓቲማላ በሚገኝ አንድ ጉባኤ እየተካፈለ እንዳለ ሲሰማ በጣም ተደሰተ! እንዲያውም አንዷ ሴት ልጁ የዘወትር አቅኚ ሆና በማገልገል ላይ ናት።
ለመንፈሳዊ ምግብ አድናቆት ማሳየት
ምንም እንኳ በቺያፓስ አካባቢ ያለው ችግር ባያቆምም አንድ የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሪፖርት እንዳደረገው በአካባቢው ያሉት ምሥክሮች ስብሰባ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ በሚገባ ተገንዝበዋል። (ዕብራውያን 10:24, 25) ይህ የአውራጃ የበላይ ተመልካች በቅርቡ ስለተደረገ የልዩ ስብሰባ ቀን ሲገልጽ የስብሰባው ተካፋዮች ሳይመሽባቸው በጊዜ ወደ ቤታቸው ቢመለሱ በመጠኑም ቢሆን ለደህንነታቸው ይበጃል በሚል ፕሮግራሙ ቀደም ብሎ በጠዋት እንዲጀመር ተደርጎ ነበር። ምንም እንኳ አብዛኞቹ ስብሰባው ቦታ ለመድረስ ከሦስት ሰዓት በላይ በጫካ ውስጥ መጓዝ ቢጠይቅባቸውም ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ስብሰባው ሲጀመር ሁሉም መቀመጫቸውን ይዘው ነበር። በስብሰባው ላይ ስድስት የአማፂ ቡድኑ አባላት ተገኝተው የነበረ ሲሆን በትኩረት ያዳምጡ እንዲሁም ያጨበጭቡ ስለነበር በፕሮግራሙ ተደስተው እንደነበር ግልጽ ነው። እነዚህም ቢሆኑ ስብሰባው ላይ የተገኙት ሦስት ሰዓት በእግር ተጉዘው ነው። በተጨማሪም ሃያ የአማፂው ቡድን አባላት በአንድ ጉባኤ መንግሥት አዳራሽ ተከብሮ በነበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ተገኝተዋል።
የደፈጣ ተዋጊ አባል የሆነ አንድ ወጣት አንድን የተወሰነ አካባቢ ቃኝቶ እንዲመለስ ከበላዮቹ ትእዛዝ ይሰጠዋል። ቦታው ሲደርስ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክር የሆኑት የአካባቢው ነዋሪዎች በሙሉ ሸሽተው ነበር። ስለዚህ አንዱ ቤት ውስጥ ገብቶ አረፍ አለ። ምንም ሥራ ስላልነበረው ቤቱ ውስጥ ያገኛቸውን አንዳንድ መጻሕፍት እያነሳ ማንበብ ይጀምራል። እነዚህ መጻሕፍት የይሖዋ ምሥክሮች ትተዋቸው የሄዱት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ናቸው። ወጣቱ ብቻውን ስለነበረ ባነበበው ነገር ላይ ለማሰላሰል ጊዜ ነበረው። ሕይወቱን መለወጥና ትጥቁን መፍታት እንዳለበት ይወስናል። ወዲያው የይሖዋ ምሥክሮችን ፈልጎ ካገኘ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ጀመረ። በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ምሥራቹን ለሌሎች እስከ መመስከር ደረሰ። እሱና የደፈጣ ቡድኑ ደጋፊ የነበሩ ሌሎች ሦስት የቤተሰቡ አባላት አሁን የተጠመቁ ክርስቲያኖች ናቸው።
አዎንታዊውን ጎን መመልከት
ምንም እንኳ ግጭቱ የሚያስከትለው መከራ ቀላል ባይሆንም ሰዎች ለስብከቱ ሥራ ባላቸው አመለካከት ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል። መጀመሪያ ግጭቱ በተቀሰቀሰባት ከተማ የሚኖር አንድ የጉባኤ ሽማግሌ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ውጊያው ከተቀሰቀሰ ከአምስት ቀን ገደማ በኋላ በከተማዋ ውስጥም ሆነ ከከተማዋ ውጭ የስብከቱን ሥራ በተቀናጀ ሁኔታ መሥራት ቀጠልን። ሰዎች በጉጉት ያዳምጡን ነበር። ብዙ ጽሑፎችን ያበረከትን ሲሆን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችንም አስጀምረናል። ቀደም ሲል ብዙዎቹ እውነትን ይቃወሙ የነበሩበት አንድ አካባቢ አሁን በግጭቱ ምክንያት በደንብ ያዳምጣሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ያጠናሉ እንዲሁም በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ።”
በአካባቢው አለመረጋጋት እያለም እንኳ ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ማካሄዳቸውን መቀጠል በመቻላቸው ወንድሞች ደስተኞች ናቸው። የመንግሥትም ሆነ የአማፂው ኃይሎች እያወቁ ትልቅ ስብሰባቸውን ማካሄዳቸውን የቀጠሉ ሲሆን ስብሰባውም በመንፈሳዊ አጠናክሯቸዋል። ተጓዥ የበላይ ተመልካቾት የሚያደርጉት ጉብኝትም በስብከቱ ሥራ እንዲቀጥሉ ትልቅ ማበረታቻ ሆኖላቸዋል። የሚገርመው ነገር፣ በፍጥጫው ውስጥ ያሉ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ምሥክሮቹ የስብከት ሥራቸውን እንዲገፉበት ያደፋፍሩ ነበር።
በቺያፓስ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ችግርና መከራ ከጊዜ በኋላ ትንሽ ቢቀንስም ሙሉ በሙሉ አላከተመም። ያም ሆነ ይህ አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ፣ የይሖዋ ምሥክሮች በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን የሰላም ወንጌል ለሰዎች ለማዳረስ የሚያደርጉትን ጥረት በቅንዓት ለመቀጠል ቆርጠዋል። (ሥራ 10:34-36፤ ኤፌሶን 6:15) ነቢዩ ኤርምያስ “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ አውቃለሁ፣ አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው አይደለም” ሲል የተናገረው ነገር እውነት መሆኑን ይገነዘባሉ። (ኤርምያስ 10:23) በዓለም ላይ ላለው ለፍትሕ መጓደልና ለድህነት መፍትሄ ማምጣት የሚችለው በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—ማቴዎስ 6:10
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሜክሲኮ ባሕረ ሰላጤ
ቺያፓስ
ጓቲማላ
ሰላማዊ ውቅያኖስ
[ምንጭ]
Mountain High Maps® Copyright © 1997 Digital Wisdom, Inc.
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በቺያፓስ ተራራማ አካባቢዎች የይሖዋ ምሥክሮች ለአገልግሎት ሲሰማሩ