መንፈሳዊ ገነት ምንድን ነው?
ጉስታቩ ያደገው በአንዲት ትንሽ የብራዚል ከተማ ውስጥ ነው።a ጥሩ ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚል ትምህርት ከሕፃንነቱ ጀምሮ ሲማር ቆይቷል። ታማኝ የሰው ዘሮች ወደፊት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም ሕይወት እንደሚያገኙ ስለሚገልጸው የአምላክ ዓላማ ምንም አያውቅም ነበር። (ራእይ 21:3, 4) ሌላም የማያውቀው ነገር ነበር። አሁንም እንኳ ቢሆን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር እንደሚችል አያውቅም።
ስለዚህ መንፈሳዊ ገነት ሰምተህ ታውቃለህ? ይህ መንፈሳዊ ገነት ምን እንደሆነና በዚያ ለመኖር ምን ማሟላት እንደሚጠይቅ ታውቃለህ? እውነተኛ ደስታ ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ስለዚህ መንፈሳዊ ገነት ማወቅ ይኖርበታል።
መንፈሳዊ ገነት የት እንደሚገኝ ለይቶ ማወቅ
አንድ ሰው ከፈለገ ዛሬም እንኳ ቢሆን በገነት ውስጥ መኖር ይችላል ብሎ መናገር የማይመስል ነው። ይህ ዓለም ገነት ለመባል የሚያበቃ ምንም ነገር የለውም። አንድ የጥንት ዕብራዊ ንጉሥ “እነሆም፣ የተገፉት ሰዎች እንባ ነበረ፤ የሚያጽናናቸውም አልነበረም፤ በሚገፉአቸውም እጅ ኃይል ነበረ፣ እነርሱን ግን የሚያጽናናቸው አልነበረም” በማለት የተናገረው ነገር እየደረሰባቸው ያሉ ሰዎች በጣም ብዙ ናቸው። (መክብብ 4:1) በብዙ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ብልሹ በሆኑ ፖለቲካዊ፣ ሃይማኖታዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ምክንያት ፍዳቸውን እየቆጠሩ ሲሆን የሚያሳርፋቸው ወይም “የሚያጽናናቸው” የለም። ሌሎች ብዙ ሰዎች ደግሞ የወር ወጪያቸውን ለመሸፈን፣ ልጆቻቸውን ለማሳደግና ሌሎች ብዙ ነገሮች ለማከናወን ከላይ ታች ይዋትታሉ። እነዚህም ለአፍታም እንኳ ቢሆን ከሸክም የሚያሳርፋቸው አጽናኝ ቢያገኙ እንዴት ደስ ባላቸው። እነዚህ ሁሉ ከገነት ፈጽሞ ተቃራኒ የሆነ ሕይወት ይመራሉ።
ታዲያ መንፈሳዊ ገነት የሚባለው ነገር የት አለ? “ፓራዳይዝ” የሚለው እንግሊዝኛ ቃል ሰላም የሰፈነበትና መንፈስን የሚያድስ መናፈሻ ወይም የአትክልት ቦታ የሚል ሐሳብ ከሚያስተላልፉት የግሪክ፣ የፋርስና የዕብራይስጥ ቃላት ጋር ተዛማጅነት አለው። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቀን ምድር ከኃጢአት ለጸዳው የሰው ዘር መናፈሻ መሰል መኖሪያ እንደምትሆን ማለትም ቃል በቃል ወደ ገነትነት እንደምትለወጥ ተስፋ ሰጥቷል። (መዝሙር 37:10, 11) ይህን በአእምሯችን በመያዝ መንፈሳዊ ገነት አንድ ሰው አብረውት ከሚኖሩ ሰዎችና ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲኖረው የሚያደርግ ለዓይን የሚማርክና መንፈስን የሚያድስ ሁኔታ ነው። ይህን የመሰለውን ገነት አሁንም ቢሆን ማግኘት የሚቻል ሲሆን እንደ ጉስታቩ ሁሉ ሌሎች ብዙ ሰዎችም ሊያገኙ ይችላሉ።
ጉስታቩ የ12 ዓመት ልጅ ሳለ የሮማ ካቶሊክ ቄስ የመሆን ፍላጎት አደረበት። ወላጆቹ በሐሳቡ ስለተስማሙ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ገባ። እዚያም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶችን ለመሳብ በምታዘጋጃቸው በሙዚቃ፣ በቲያትርና በፖለቲካ እንቅስቃሴዎች መሳተፍ ጀመረ። አንድ ቄስ መላ ጊዜውን ሕዝቡን ለማገልገል ማዋል እንዳለበትና ማግባት እንደሌለበት ያውቅ ነበር። ሆኖም ጉስታቩ የሚያውቃቸው አንዳንድ ቀሳውስትና ተማሪዎች ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ድርጊቶች ይፈጽሙ ነበር። ጉስታቩ እንደዚህ ያለውን ሁኔታ ሲመለከት ኃይለኛ ጠጪ ሆነ። አሁንም መንፈሳዊ ገነትን እንዳላገኘ ግልጽ ነው።
አንድ ቀን ጉስታቩ ስለ ምድራዊ ገነት የሚናገር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክት አነበበ። ትራክቱ ስለ ሕይወት ዓላማ እንዲያስብ አደረገው። “መጽሐፍ ቅዱስን ደጋግሜ ማንበብ ጀመርኩ፤ ሆኖም አይገባኝም ነበር። አምላክ ስም እንዳለው እንኳ አላውቅም ነበር” ብሏል። ከመንፈሳዊ ትምህርት ቤቱ ወጣና መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እንዲያስረዱት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ተገናኘ። ከዚያ በኋላ ፈጣን እድገት አድርጎ ብዙም ሳይቆይ ሕይወቱን ለአምላክ ወሰነ። ጉስታቩ ስለ መንፈሳዊ ገነት በመማር ላይ ነበር።
ለአምላክ ስም የሚሆን ወገን
ጉስታቩ ይሖዋ የሚለው የአምላክ ስም ለአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዲሁ እንደ ተጨማሪ እውቀት የሚታይ ነገር አለመሆኑን ተገነዘበ። (ዘጸአት 6:3) የእውነተኛው አምልኮ አብይ ክፍል ነው። ኢየሱስ ተከታዮቹ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴዎስ 6:9) ሐዋርያው ያዕቆብ ወደ ክርስትና ስለተለወጡ አሕዛብ ሲናገር “እግዚአብሔር ለስሙ የሚሆንን ወገን ከአሕዛብ ይወስድ ዘንድ አስቀድሞ [ጎብኝቷል]” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 15:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን “ለስሙ የሚሆን ወገን” የተባለው የክርስቲያን ጉባኤ ነበር። ዛሬስ ለአምላክ ስም የሚሆን ወገን አለ? አዎን፣ ጉስታቩ የይሖዋ ምሥክሮች ለአምላክ ስም የተለዩ ሕዝቦች መሆናቸውን ተገንዝቧል።
የይሖዋ ምሥክሮች በ235 አገሮችና ግዛቶች ውስጥ ይገኛሉ። ቁጥራቸው ከስድስት ሚልዮን በላይ ሲሆን ስምንት ሚልዮን የሚያክሉ ፍላጎት ያላቸው ሌሎች ሰዎች ደግሞ በስብሰባዎቻቸው ላይ ይገኛሉ። በሰፊው የሚታወቁበት ሕዝባዊ አገልግሎታቸው “ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ፍጻሜያቸውን እንዲያገኙ አስችሏል። (ማቴዎስ 24:14) ታዲያ ጉስታቩ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ግንኙነት በመፍጠሩ ምክንያት መንፈሳዊ ገነት እንዳገኘ የተሰማው ለምንድን ነው? “ከይሖዋ ምሥክሮች የተማርኩትን ነገር በዓለም ውስጥ በተለይ ደግሞ በመንፈሳዊ ትምህርት ቤት ውስጥ ካየሁት ጋር አወዳደርኩ። ትልቅ ልዩነት ሆኖ ያገኘሁት በምሥክሮቹ መካከል የሚታየው ፍቅር ነው” ብሏል።
ሌሎች ሰዎችም ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ተመሳሳይ አስተያየቶችን ሰንዝረዋል። ሚሪያም የምትባል ወጣት ብራዚላዊት “እንዴት ደስተኛ መሆን እንደሚቻል አላውቅም ነበር። ሌላው ቀርቶ በቤተሰብ ሕይወቴ እንኳ ደስተኛ አልነበርኩም። ፍቅር በተግባር ሲገለጽ ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁት በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ነው” ብላለች። ክሪስቲያን የሚባል አንድ ሰው “አልፎ አልፎ በመናፍስታዊ ሥራዎች እካፈል የነበረ ቢሆንም ስለ ሃይማኖት ግድ አልነበረኝም። ትልቅ ቦታ እሰጥ የነበረው በኅብረተሰቡ ውስጥ ላለኝ ቦታና በመሃንዲስነት ለማከናውነው ሥራ ነበር። ያም ሆኖ ግን ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር ለውጥ አየሁባት። እሷን ለመጠየቅ የሚመጡ ክርስቲያን ሴቶች ባላቸው ደስታና በሚያሳዩት ቅንዓት በጣም ተማረክሁ” በማለት ተናግሯል። ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን የመሳሰሉ አስተያየቶች የሚሰነዝሩት ለምንድን ነው?
መንፈሳዊ ገነት ምንድን ነው?
የይሖዋ ምሥክሮችን ከሌሎች የሚለያቸው አንዱ ነገር ለመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ትልቅ ቦታ መስጠታቸው ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንደሆነና የአምላክ ቃል መሆኑን ያምናሉ። በዚህ የተነሳ ሃይማኖታቸው የሚያስተምራቸውን መሠረተ ትምህርቶች ስላወቁ ብቻ ረክተው አይቀመጡም። የግል ጥናት የሚያደርጉበትና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነቡበት ቀጣይ የሆነ ፕሮግራም አላቸው። አንድ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ረጅም ጊዜ ባሳለፈ መጠን ስለ አምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተገለጸው ፈቃዱ ይበልጥ ይገነዘባል።
እንደዚህ ያለው እውቀት እንደ አጉል እምነትና ጎጂ አስተሳሰብ ከመሳሰሉት ሰዎችን ደስታ ከሚያሳጡ ነገሮች የይሖዋ ምሥክሮችን ነፃ ያወጣቸዋል። ኢየሱስ “እውነትም አርነት ያወጣችኋል” በማለት የተናገረ ሲሆን የይሖዋ ምሥክሮች ይህ እውነት ሆኖ አግኝተውታል። (ዮሐንስ 8:32) በአንድ ወቅት በመናፍስታዊ ድርጊቶች ይካፈል የነበረው ፌርናንዱ “ስለ ዘላለም ሕይወት መማር ይህ ነው የማይባል እፎይታ ያስገኛል። ወይ እኔ ወይ ወላጆቼ ይሞቱ ይሆናል ብዬ እሰጋ ነበር” በማለት ተናግሯል። እውነትን ማወቁ ከመንፈሳዊው ዓለም ጥቃት ይደርስብኛል ከሚል ፍርሃትና ከሞት በኋላ አለ ስለሚባለው ሕይወት ከመስጋት ገላግሎታል።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የአምላክ እውቀት ከገነት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ “በተቀደሰው ተራራዬ ሁሉ ላይ አይጐዱም አያጠፉምም፤ ውኃ ባሕርን እንደሚከድን ምድር እግዚአብሔርን በማወቅ ትሞላለችና” ብሏል።—ኢሳይያስ 11:9
እርግጥ ነው፣ እውቀት ብቻውን ኢሳይያስ የተናገረለትን ሰላም አያመጣም። አንድ ሰው የተማረውን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርበታል። ፌርናንዱ “አንድ ሰው የመንፈስ ፍሬዎችን ሲያፈራ መንፈሳዊው ገነት እንዲዳብር የበኩሉን አስተዋጽዖ ያደርጋል” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል። ፌርናንዱ ሐዋርያው ጳውሎስ “የመንፈስ ፍሬ” በማለት የጠራቸውን አንድ ክርስቲያን ሊያፈራቸው የሚገቡ ጥሩ ጥሩ ባሕርያት መጥቀሱ ነበር። ጳውሎስ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ሲል በዝርዝር አስቀምጧቸዋል።—ገላትያ 5:22, 23
እነዚህን ባሕርያት ለማፍራት ከሚጣጣሩ ሰዎች ጋር መቀላቀል በገነት ውስጥ ከመሆን ጋር ለምን እንደተመሰለ ታውቃለህ? እነዚህ ሰዎች ነቢዩ ሶፎንያስ በትንቢት የተናገረው መንፈሳዊ ገነት አላቸው። ነቢዩ “ኃጢአትን አይሠሩም፣ ሐሰትንም አይናገሩም፣ በአፋቸውም ውስጥ ተንኰለኛ ምላስ አይገኝም፤ እነርሱም ይሰማራሉ፣ ይመሰጉማል፣ የሚያስፈራቸውም የለም” ብሏል።—ሶፎንያስ 3:13
ፍቅር የሚጫወተው ወሳኝ ሚና
ጳውሎስ የመንፈስ ፍሬዎችን ሲዘረዝር ፍቅርን በመጀመሪያ ላይ እንደጠቀሰ ሳታስተውል አልቀረህም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ባሕርይ ብዙ ጊዜ ይጠቅሳል። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ” ሲል ተናግሯል። (ዮሐንስ 13:35) የይሖዋ ምሥክሮች ፍጹማን አለመሆናቸው የታወቀ ነው። በኢየሱስ ሐዋርያት መካከል አለመግባባት የተፈጠረበት ጊዜ እንደነበረ ሁሉ በይሖዋ ምሥክሮች መካከልም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሊከሰት ይችላል። ሆኖም እርስ በርስ ከልብ የሚዋደዱ ሲሆን ይህን ባሕርይ ለማፍራት በሚያደርጉት ጥረት የመንፈስ ቅዱስን እርዳታ እንዲያገኙ ይጸልያሉ።
በመሆኑም ከሌሎች የተለየ ወዳጅነት አላቸው። በመካከላቸው የጎሣ ክፍፍል ወይም ብሔረተኝነት የለም። እንዲያውም በ20ኛው መቶ ዘመን ማክተሚያ ላይ የዘር ማጥፋትና የጎሣ ምንጠራ በተካሄደባቸው ቦታዎች ይኖሩ የነበሩ ብዙ ምሥክሮች ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ቢሆንም እንኳ አንዳቸው ሌላውን ደብቀው አስጥለዋል። ‘ከሕዝብ፣ ከነገድ፣ ከወገን ከቋንቋ’ የመጡ ቢሆኑም እንኳ አንተ ራስህ በመካከላቸው ሆነህ ካላየኸው በስተቀር ለመረዳት የሚያስቸግር ልዩ የሆነ አንድነት አላቸው።—ራእይ 7:9
የአምላክን ፈቃድ በሚያደርጉ ሰዎች መካከል ያለ ገነት
በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ስግብግብነት፣ የሥነ ምግባር ብልግና እና ራስ ወዳድነት ቦታ የላቸውም። ክርስቲያኖች “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” ተብለዋል። (ሮሜ 12:2) በንጹሕ ሥነ ምግባር ስንመላለስና በተለያዩ መንገዶች የአምላክን ፈቃድ ስናደርግ መንፈሳዊው ገነት እንዲዳብር ከመርዳት በተጨማሪ ለራሳችን ደስታም አስተዋጽዖ እናደርጋለን። ካርላ ይህ እውነት መሆኑን በራስዋ ሕይወት አይታዋለች። “አባቴ ራሴን እንድችል ጠንክሬ መሥራት እንዳለብኝ አስተምሮኛል። ዩኒቨርሲቲ መማሬ እንድረጋጋ ቢያደርገኝም የቤተሰብ አንድነትና ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውቀት የሚሰጠው መረጋጋት ቀርቶብን ነበር” በማለት ተናግራለች።
በመንፈሳዊው ገነት መኖር ሙሉ በሙሉ ከችግር ነፃ እንደማያደርግ የታወቀ ነው። ክርስቲያኖች ሊታመሙ ይችላሉ። የሚኖሩበት አገር በእርስ በርስ ግጭት ይታመስ ይሆናል። ብዙዎች ከድህነት ጋር ይታገላሉ። ያም ሆኖ ግን ለመንፈሳዊ ገነት ወሳኝ ከሆነው ከይሖዋ አምላክ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረታችን ከእርሱ እርዳታ እንድናገኝ ያስችለናል። እርግጥ ነው፣ ‘ሸክማችንን በእርሱ ላይ እንድንጥል’ የሚጋብዘን ሲሆን ብዙዎች በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ጊዜ በአስደናቂ መንገድ እንደረዳቸው ሊመሰክሩ ይችላሉ። (መዝሙር 55:22፤ 86:16, 17) አምላኪዎቹ “በሞት ጥላ መካከል” በሚሆኑበት ጊዜ እንኳ እንደማይለያቸው ቃል ገብቷል። (መዝሙር 23:4) አምላክ እኛን ለመደገፍ ምን ጊዜም ዝግጁ መሆኑን በትምክህት የምናምን ከሆነ መንፈሳዊ ገነት ለማግኘት ቁልፍ የሆነውን “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም” ጠብቀን እንድንኖር ይረዳናል።—ፊልጵስዩስ 4:7
ለመንፈሳዊ ገነት የበኩላችንን አስተዋጽዖ ማበርከት
ብዙ ሰዎች መናፈሻ ወይም የአትክልት ቦታ መጎብኘት ይወዳሉ። በውስጡ ወዲያ ወዲህ ማለት ወይም አረፍ ብለው አካባቢውን መመልከት ያስደስታቸዋል። በተመሳሳይም ብዙ ሰዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መወዳጀት ያስደስታቸዋል። ወዳጅነቱ መንፈስን የሚያነቃቃ፣ ሰላማዊና መንፈስን የሚያድስ ይሆንላቸዋል። ይሁን እንጂ አንድ የአትክልት ቦታ ገነታዊ ሁኔታው እንዳለ እንዲቀጥል እንክብካቤ ያስፈልገዋል። በተመሳሳይም በመንፈሳዊ ምድረ በዳ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ መንፈሳዊ ገነት ሊኖር የቻለው የይሖዋ ምሥክሮች ጥረት ስላደረጉና አምላክም ጥረታቸውን ስለ ባረከላቸው ነው። ታዲያ አንድ ሰው ለመንፈሳዊው ገነት ትርጉም ያለው አስተዋጽዖ ማበርከት ይችላልን?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ መገኘት፣ ከእነርሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና ለመንፈሳዊ ገነት መሠረት የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት ይኖርብሃል። ካርላ “መንፈሳዊ ምግብ ከሌለ መንፈሳዊ ገነት አይኖርም” ብላለች። ይህ ደግሞ የአምላክን ቃል አዘውትሮ ማንበብንና ስላነበብከው ነገር ማሰብን ይጨምራል። ያገኘኸው እውቀት ከይሖዋ አምላክ ጋር እንድትቀራረብና እሱን እንድትወደው ያደርግሃል። በተጨማሪም በጸሎት ከእርሱ ጋር በመነጋገር መመሪያ እንዲሰጥህና ፈቃዱን ስታደርግ በመንፈሱ እንዲረዳህ መጠየቅ ትችላለህ። ኢየሱስ በጸሎት እንድንጸና ነግሮናል። (ሉቃስ 11:9-13) ሐዋርያው ጳውሎስ “ሳታቋርጡ ጸልዩ” ብሏል። (1 ተሰሎንቄ 5:17) እንደሚሰማህ እርግጠኛ በመሆን በጸሎት ከአምላክ ጋር የመነጋገር መብት የመንፈሳዊ ገነት አቢይ ክፍል ነው።
ትምህርቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕይወትህ እንዲሻሻል የሚያደርግ ሲሆን ቀስ በቀስም ስለተማርከው ነገር ለሌሎች ለመናገር ትገፋፋለህ። እንዲህ ስታደርግ ኢየሱስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ትፈጽማለህ። (ማቴዎስ 5:16) ስለ ይሖዋ አምላክና ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚገልጸውን እውቀት ለሌሎች ማካፈል እንዲሁም ለሰው ዘር ያሳዩትን ታላቅ ፍቅር ከልብ መናገር ከፍተኛ ደስታ ያስገኛል።
መላዋ ምድር ከአካባቢ ብክለት የጸዳችና ታማኝ የሰው ዘሮች በምቾት የሚኖሩባት ገነት የምትሆንበት ጊዜ ቀርቧል። ‘አስጨናቂ’ በሆነው በዚህ ዘመን መንፈሳዊ ገነት መኖሩ የአምላክ ኃይል አሁንም እንደሚሠራ የሚያረጋግጥና አምላክ ወደፊት ለሚያከናውነው ነገር እንደ ቅምሻ ያክል ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1
አሁንም ቢሆን በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ያሉ ሰዎች “የሚራራላቸውም ይመራቸዋልና፣ በውኃም ምንጮች በኩል ይነዳቸዋልና አይራቡም፣ አይጠሙም፣ ትኩሳት ወይም ፀሐይ አይጐዳቸውም” የሚሉት የኢሳይያስ 49:10 ቃላት በመንፈሳዊ ሁኔታ ተፈጽሞላቸዋል። ዦዜ ይህ እውነት መሆኑን ይመሠክራል። ታዋቂ ሙዚቀኛ የመሆን ምኞት ነበረው፤ ሆኖም ከክርስቲያን ጉባኤ ጋር ሆኖ አምላክን በማገልገል የበለጠ እርካታ አግኝቷል። “አሁን ትርጉም ያለው ሕይወት እየመራሁ ነው። በክርስቲያን የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ስላለሁ ምንም ስጋት አይሰማኝም። ይሖዋ ልንተማመንበት የምንችል አፍቃሪ አባት መሆኑን አውቃለሁ” ብሏል። ዦዜ እና በሚልዮን የሚቆጠሩ እንደርሱ ያሉ ሌሎች ሰዎች ያገኙት ደስታ “ጻድቅ በእግዚአብሔር ደስ ይለዋል፣ በእርሱም ይታመናል፤ ልባቸውም የቀና ሁሉ እልል ይላሉ” በሚሉት የመዝሙር 64:10 ቃላት ውስጥ በጥሩ ሁኔታ ተገልጸዋል። ስለ መንፈሳዊው ገነት የተነገረ እንዴት ያለ ግሩም መግለጫ ነው!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እዚህ ላይ የተጠቀሱት የአንዳንዶቹ ሰዎች ስም ተቀይሯል።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ያገኘኸው መንፈሳዊ ገነት እየሰፋ እንዲሄድ የበኩልህን አድርግ!