በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ መገንባት
“ልጆቻችሁን በጌታ ምክርና በተግሣጽ አሳድጉአቸው።”—ኤፌሶን 6:4
1. አምላክ ለቤተሰብ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር? ሆኖም ምን ነገር ተከሰተ?
“ብዙ፣ ተባዙ፣ ምድርንም ሙሏት።” (ዘፍጥረት 1:28) ይሖዋ አምላክ እነዚህን ቃላት ለአዳምና ለሔዋን በመንገር የቤተሰብን ዝግጅት መሠረተ። (ኤፌሶን 3:14, 15) እነዚህ የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ምድር ታላቁን ፈጣሪያቸውን አንድ ሆነው በሚያመልኩ ፍጹም በሆኑ ዘሮቻቸው ስትሞላ ማለትም ዘመድ አዝማዶቻቸው ገነት በሆነች ምድር ላይ በደስታ ሲኖሩ በዓይነ ሕሊናቸው መመልከት ይችሉ ነበር። ይሁን እንጂ አዳምና ሔዋን ኃጢአት ውስጥ በመውደቃቸው ምክንያት ምድር አምላክን በሚፈሩ ጻድቃን ሰዎች ሳትሞላ ቀረች። (ሮሜ 5:12) ከዚያ ይልቅ የቤተሰብ ሕይወት በፍጥነት እየተበላሸ ከመሄዱም በላይ በተለይ በዚህ ‘በመጨረሻው ዘመን’ ጥላቻና ዓመፅ በመንገሱ ‘የተፈጥሮ ፍቅር’ ጠፍቷል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ዘፍጥረት 4:8, 23፤ 6:5, 11, 12
2. የአዳም ዘሮች ምን ችሎታዎች ነበሯቸው? ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ ለመገንባት ምን ያስፈልጋል?
2 አዳምና ሔዋን የተፈጠሩት በአምላክ መልክ ነበር። ምንም እንኳ አዳም ኃጢአተኛ ቢሆንም ልጆችን እንዲወልድ ይሖዋ ፈቅዶለታል። (ዘፍጥረት 1:27፤ 5:1-4) እንደ አባታቸው ሁሉ የአዳም ዘሮችም በውስጣቸው ተፈጥሯዊ የሥነ ምግባር ደንብ ያላቸው በመሆኑ ክፉና በጎውን መለየትን መማር ይችላሉ። ፈጣሪያቸውን እንዴት ማምለክ እንደሚችሉና በፍጹም ልባቸው፣ ነፍሳቸው፣ ሐሳባቸውና ኃይላቸው እርሱን መውደድ አስፈላጊ መሆኑን ሊማሩ ይችላሉ። (ማርቆስ 12:30፤ ዮሐንስ 4:24፤ ያዕቆብ 1:27) ከዚህም በላይ ‘ፍትሕንና ፍቅራዊ ደግነትን እንዲያንጸባርቁ እንዲሁም ልካቸውን አውቀው ከአምላክ ጋር እንዲሄዱ’ መሠልጠን ይችላሉ። (ሚክያስ 6:8) ይሁን እንጂ ኃጢአተኞች እንደመሆናቸው መጠን በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ ለመገንባት ከፍተኛ ትኩረት መስጠት ይገባቸው ነበር።
ጊዜ ዋጁ
3. ወላጆች ክርስቲያን ልጆችን ለማሳደግ ‘ጊዜ መዋጀት’ የሚችሉት እንዴት ነው?
3 በዚህ ውሉ በጠፋበት አስጨናቂ ዘመን ውስጥ ልጆች ‘ይሖዋን የሚወድዱና ክፋትን የሚጠሉ’ እንዲሆኑ ለመርዳት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ የግድ አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 97:10) አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት ‘ጊዜ ይዋጃሉ።’ (ኤፌሶን 5:15-17) ወላጅ ከሆንክ ይህንን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ልጆችህን ማስተማርንና ማሠልጠንን ጨምሮ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ‘ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች’ ለይ። (ፊልጵስዩስ 1:10, 11) ሁለተኛ፣ ኑሮህን ቀላል አድርግ። እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎችን መተው ይኖርብህ ይሆናል። ወይም ጊዜህን የሚሻሙ አስፈላጊ ያልሆኑ ንብረቶችን ማስወገድ ይኖርብህ ይሆናል። ክርስቲያን ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ልጆች ለማሳደግ ስትል የምትከፍለው ማንኛውም መሥዋዕትነት ፈጽሞ አያስቆጭህም።—ምሳሌ 29:15, 17
4. አንድ ቤተሰብ አንድነቱን ጠብቆ መቀጠል የሚችለው እንዴት ነው?
4 ከልጆች ጋር ጊዜ ማሳለፍ፣ በተለይ ይህንን ጊዜ መንፈሳዊ ለሆኑ ጉዳዮች መጠቀም የሚክስ ከመሆኑም በላይ የቤተሰብን አንድነት ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ከሁሉ የተሻለ መንገድ ነው። ሆኖም ይህን እንዲያው ሲመቻችሁ ብቻ የምታደርጉ አትሁኑ። አንድ ላይ ሆናችሁ ጊዜ የምታሳልፉበት ፕሮግራም አውጡ። ይህ እንዲሁ በአንድ ጣራ ሥር ሆኖ ሁሉም በየፊናው ደስ ያለውን ያደርጋል ማለት አይደለም። ልጆች በግለሰብ ደረጃ በየዕለቱ ትኩረት ካገኙ ጥሩ ሆነው ያድጋሉ። ፍቅራችሁንና አሳቢነታችሁን ምንም ሳትቆጥቡ አሳዩአቸው። እንዲያውም የተጋቡ ባልና ሚስት ልጆች ለመውለድ ከመወሰናቸው በፊት እንኳ ሳይቀር ይህን አስፈላጊ የሆነ ኃላፊነት በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። (ሉቃስ 14:28) እንደዚያ ካደረጉ ልጆችን ማሳደግ እንደ ሸክም ሆኖ አይታያቸውም። ከዚያ ይልቅ የተባረከ መብት እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል።—ዘፍጥረት 33:5፤ መዝሙር 127:3
በቃልና በተግባር አስተምሩ
5. (ሀ) ልጆች ይሖዋን እንዲወድዱ ማስተማር የሚጀመረው ከየት ነው? (ለ) ዘዳግም 6:5-7 ለወላጆች ምን ምክር ይዟል?
5 ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወድዱ ማስተማር መጀመር የምትችሉት እናንተ ለእርሱ ባላችሁ ፍቅር ነው። ለአምላክ ጠንካራ ፍቅር ማዳበራችሁ መመሪያዎቹን በሙሉ በታማኝነት እንድትከተሉ ያንቀሳቅሳችኋል። ይህም ልጆችን “በጌታ ምክርና በተግሣጽ” ማሳደግን ይጨምራል። (ኤፌሶን 6:4) ወላጆች ለልጆቻቸው ምሳሌ እንዲሆኑ፣ ከእነርሱ ጋር የሐሳብ ግንኙነት እንዲያደርጉና እንዲያስተምሯቸው አምላክ ምክር ይሰጣቸዋል። ዘዳግም 6:5-7 እንዲህ ይላል:- “አንተም አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹምም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ። እኔም ዛሬ አንተን የማዝዘውን ይህን ቃል በልብህ ያዝ። ለልጆችህም አስተምረው፣ በቤትህም ስትቀመጥ፣ በመንገድም ስትሄድ፣ ስትተኛም፣ ስትነሣም ተጫወተው።” ያልተቋረጠ ምክር በመስጠትና በመደጋገም በልጆቻችሁ ውስጥ የአምላክን ትእዛዛት መቅረጽ ትችላላችሁ። በዚህ መንገድ ልጆቻችሁ ለይሖዋ ፍቅር እንዳላችሁ ይገነዘባሉ፣ ይህም ከእርሱ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲመሠርቱ ይገፋፋቸዋል።—ምሳሌ 20:7
6. ልጆች የሌሎችን ምሳሌ በማየት ያላቸውን የመማር ችሎታ ወላጆች በጥሩ መንገድ ሊጠቀሙበት የሚችሉት እንዴት ነው?
6 ልጆች ከፍተኛ የማወቅ ጉጉት አላቸው። የሚሰሙትም ሆነ የሚያዩት ነገር አያመልጣቸውም። የእናንተን ምሳሌ ለመኮረጅ ፈጣኖች ናቸው። ቁሳዊ ሀብት የማሳደድ ዝንባሌ የሌላችሁ መሆኑን ከተመለከቱ የኢየሱስን ምክር እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ይማራሉ። ለቁሳዊ ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ ‘የአምላክን መንግሥት እንዲያስቀድሙ’ አስተምሯቸው። (ማቴዎስ 6:25-33) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት፣ ስለ አምላክ ጉባኤና ስለ ተሾሙት ሽማግሌዎች ጤናማና የሚያንጽ ጭውውት በማድረግ ልጆቻችሁ ለይሖዋ አክብሮት እንዲኖራቸውና ለመንፈሳዊ ዝግጅቶቹ አድናቆት እንዲያዳብሩ ታስተምሯቸዋላችሁ። ልጆች እርስ በርስ የማይጣጣሙ ነገሮችን ለመመልከት ፈጣኖች ስለሆኑ በቃል የምትሰጡት ትምህርት ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዳላችሁ በሚያሳዩ ድርጊቶችና ባሕርያት መደገፍ ይኖርበታል። ወላጆች የሚያሳዩት ምሳሌነት ልጆቻቸው ይሖዋን ከልብ እንዲወድዱ እንዳደረጋቸው ሲመለከቱ ምንኛ በረከት ነው!—ምሳሌ 23:24, 25
7, 8. ልጆችን ገና ከጨቅላነታቸው ጊዜ አንስቶ ማሠልጠን ጥቅም እንዳለው የትኛው ምሳሌ ያሳያል? ለተገኘው ስኬት ሊመሰገን የሚገባው ማን ነው?
7 ልጆችን ገና ከጨቅላነታቸው አንስቶ ማሠልጠን ጥቅም እንዳለው ከአንድ የቬኔዙዌላ ተሞክሮ ማየት ይቻላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:15) ተሞክሮው ፌሊክስ እና ማየርሊን የተባሉትን ሁለት ወጣት ባልና ሚስት የሚመለከት ነው። ሁለቱም አቅኚዎች ናቸው። ልጃቸው ፌሊቶ በተወለደ ጊዜ እውነተኛ የይሖዋ አምላኪ አድርገው ለማሳደግ የተቻላቸውን ሁሉ ለማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አደረባቸው። ማየርሊን የይሖዋ ምሥክሮች ካሳተሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ የተባለውን መጽሐፍ ድምጿን ከፍ አድርጋ ለፌሊቶ ማንበብ ጀመረች። ፌሊቶ ሙሴንና በመጽሐፉ ላይ በሥዕል የተገለጹትን ሌሎች ሰዎች መለየት የቻለው በሕፃንነቱ ነበር።
8 ፌሊቶ ገና ሕፃን ሳለ ራሱን ችሎ መመሥከር ጀመረ። የመንግሥቱ አስፋፊ የመሆን ምኞቱ ከተሳካለት በኋላ ትንሽ ቆየት ብሎ ተጠመቀ። ከዚያም ከጊዜ በኋላ የዘወትር አቅኚ ሆነ። ወላጆቹ “ልጃችን የሚያደርገውን እድገት ስንመለከት ይሖዋና የሰጠን መመሪያዎች ባለ ውለታዎቻችን እንደሆኑ እንገነዘባለን” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ልጆች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ እርዷቸው
9. በታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል አማካኝነት ለምናገኛቸው መንፈሳዊ መመሪያዎች አመስጋኝ መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
9 ልጆችን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል ምክር የሚሰጡ በደርዘን የሚቆጠሩ መጽሔቶች፣ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ መጻሕፍትና በሺዎች የሚቆጠሩ የኢንተርኔት ዌብ ገጾች አሉ። ኒውስዊክ ልጆችን አስመልክቶ ባወጣው ልዩ እትሙ ላይ ብዙውን ጊዜ “ምክሮቹ እርስ በርሳቸው ይጋጫሉ” በማለት ይናገራል። “ይባስ ብሎ ደግሞ ትክክለኛ ነው ብላችሁ የተማመናችሁበት ምክር ጭራሽ ስህተት ሆኖ መገኘቱ ነው።” ይሖዋ ቤተሰቦች መመሪያ እንዲሆናቸውና በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለማስቻል የተትረፈረፈ ዝግጅት በማድረጉ ምንኛ አመስጋኞች ነን! የታማኝና ልባም ባሪያ ክፍል የሚያቀርባቸውን ሁሉንም ዝግጅቶች ትጠቀሙባቸዋላችሁ?—ማቴዎስ 24:45-47
10. ውጤታማ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወላጆችንም ሆነ ልጆችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?
10 አንዱ አስፈላጊ የሆነ ነገር ዘና ባለ መንፈስ የሚደረግ ወጥነት ያለው ቋሚ የቤተሰብ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው። ጥናቱ ትምህርት የሚገኝበት፣ አስደሳችና አበረታች እንዲሆን ጥሩ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል። ወላጆች ልጆቻቸው ሐሳባቸውን እንዲገልጹ በማድረግ በልባቸውና በአእምሯቸው ውስጥ ያለውን ነገር ማወቅ ይችላሉ። የቤተሰብ ጥናቱ ውጤታማ መሆኑን ማወቅ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የጥናቱን ሰዓት በጉጉት የሚጠባበቁ መሆናቸውን በመመልከት ነው።
11. (ሀ) ወላጆች ልጆቻቸው ምን ዓይነት ግቦችን እንዲያወጡ ሊረዷቸው ይችላሉ? (ለ) አንዲት ጃፓናዊት ልጅ ያወጣችውን ግብ በመከተሏ ምን ውጤት አገኘች?
11 ቅዱስ ጽሑፋዊ ግቦችን ማውጣትም በተመሳሳይ በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ ለመመሥረት አስተዋጽዖ የሚያበረክት ሲሆን ልጆች እነዚህን ግቦች እንዲያወጡ ወላጆች ሊረዷቸው ይገባል። እነዚህ ግቦች በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን፣ አዘውታሪ የምሥራቹ አስፋፊ መሆንና ራስን ወደ መወሰንና ወደ መጠመቅ እድገት ማድረግን ያካትታሉ። ሌሎች ግቦች ደግሞ እንደ አቅኚ፣ ቤቴላዊ ወይም ሚስዮናዊ በመሳሰሉ በሙሉ ጊዜ አገልግሎቶች መካፈልን ሊጨምር ይችላል። አዩሚ የተባለች አንዲት ጃፓናዊት ልጅ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችበት ጊዜ ለእያንዳንዱ የክፍል ተማሪ የመመሥከር ግብ አወጣች። የአስተማሪዋንና የክፍሏን ተማሪዎች ፍላጎት ለመቀስቀስ በቤተ መጻሕፍቱ ውስጥ በርከት ያሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማስቀመጥ እንድትችል ፈቃድ አገኘች። በውጤቱም የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበረችባቸው ስድስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ 13 የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን መምራት ችላለች። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቿ መካከል አንዷና ሌሎቹ የቤተሰቧ አባላት ተጠምቀው ክርስቲያኖች ሆነዋል።
12. ልጆች ከክርስቲያን ስብሰባዎች ከፍተኛ ጥቅም ሊያገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?
12 በመንፈሳዊ ጠንካራ ቤተሰብ ለመገንባት የሚረዳ ሌላው አስፈላጊ ነገር ዘወትር በስብሰባዎች ላይ መገኘት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘በአንዳንዶች ዘንድ ልማድ እንደ ሆነው መሰብሰባቸውን እንዳይተዉ’ የእምነት ባልደረቦቹን አጥብቆ መክሯቸዋል። ወጣትም ሆንን በዕድሜ የገፋን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን ከፍተኛ ጥቅም ስለሚያስገኝልን ከስብሰባ መቅረትን ልማድ ማድረግ አይገባንም። (ዕብራውያን 10:24, 25፤ ዘዳግም 31:12) ልጆች በትኩረት ማዳመጥን መማር ይኖርባቸዋል። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ከፍተኛ ጥቅም ስለሚያስገኝ ለስብሰባዎች መዘጋጀትም አስፈላጊ ነው። አንድ ልጅ ጥቂት ቃላትን በመናገር ወይም ከአንድ አንቀጽ ላይ የተወሰነ ነገር በማንበብ መጀመር ቢችልም ልጆች መልሱን ራሳቸው ፈልገው እንዲያገኙ ማሠልጠንና በራሳቸው አባባል እንዲመልሱ ማበረታታት የተሻለ ጥቅም ያስገኝላቸዋል። እናንት ወላጆች፣ ዘወትር ትርጉም ያለው ሐሳብ በመስጠት ራሳችሁ ምሳሌ ትሆናላችሁ? በተጨማሪም እያንዳንዱ የቤተሰቡ አባል የራሱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የመዝሙር ቡክሌትና ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት የሚደረግበት ጽሑፍ ቅጂ ቢኖረው ጥሩ ነው።
13, 14. (ሀ) ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር በአገልግሎት መካፈል የሚኖርባቸው ለምንድን ነው? (ለ) ልጆች ከመስክ አገልግሎት ጥቅምና ደስታ እንዲያገኙ የሚረዳቸው ምንድን ነው?
13 አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ልጆቻቸው የወጣትነት ጉልበታቸውን ለይሖዋ አገልግሎት እንዲጠቀሙበት ይመክሯቸዋል እንዲሁም የስብከቱን ሥራ ዋነኛ የሕይወታቸው ክፍል እንዲያደርጉ ይረዷቸዋል። (ዕብራውያን 13:15) ወላጆች ‘የእውነትን ቃል በቅንነት የሚናገሩ የማያሳፍር ሠራተኞች’ ለመሆን የሚያበቃቸውን ሥልጠና ለልጆቻቸው መስጠት የሚችሉት በአገልግሎት አብረዋቸው ሲሠሩ ብቻ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 2:15) ታዲያ በዚህ ረገድ እናንተ እንዴት ናችሁ? ወላጅ ከሆናችሁ ለመስክ አገልግሎት እንዲዘጋጁ ልጆቻችሁን ትረዷቸዋላችሁ? እንዲህ ማድረጋችሁ አገልግሎት አስደሳች፣ ትርጉም ያለውና ፍሬያማ እንዲሆንላቸው ይረዳቸዋል።
14 ወላጆችና ልጆቻቸው በአገልግሎት አብረው መሥራታቸው ጠቃሚ የሚሆነው ለምንድን ነው? ልጆች የወላጆቻቸውን ጥሩ ምሳሌ መመልከትና መቅዳት የሚችሉት በዚህ መንገድ ስለሆነ ነው። እግረ መንገዳቸውንም ወላጆች የልጆቻቸውን ዝንባሌ፣ ጠባይና ችሎታ ሊመለከቱ ይችላሉ። ልጆቻችሁን በተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች አብረዋችሁ እንዲካፈሉ አድርጉ። በተቻለ መጠን እያንዳንዱ ልጅ የራሱ የአገልግሎት ቦርሳ እንዲኖረው አድርጉ እንዲሁም ንጹሕና ለዓይን ማራኪ አድርጎ እንዲይዘው አስተምሩት። ቀጣይ የሆነ ሥልጠናና ማበረታቻ መስጠቱ ልጆች ለአገልግሎቱ እውነተኛ አድናቆት እንዲኖራቸው ያደርጋል እንዲሁም የስብከቱ ሥራ ለአምላክና ለጎረቤት ፍቅር የሚገለጥበት መንገድ እንደሆነ ይመለከታሉ።—ማቴዎስ 22:37-39፤ 28:19, 20
መንፈሳዊነታችሁን ጠብቁ
15. የቤተሰብን መንፈሳዊነት መጠበቅ እጅግ አስፈላጊ እንደመሆኑ መጠን ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
15 የቤተሰብን መንፈሳዊነት መጠበቅ የግድ አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 119:93) ይህን ማድረግ የሚቻልበት አንደኛው መንገድ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከቤተሰባችሁ ጋር ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መወያየት ነው። የዕለቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከቤተሰባችሁ ጋር ትወያዩበታላችሁ? ‘በመንገድም ስትሄዱ’ በመስክ አገልግሎት የተገኙ ተሞክሮዎችን ወይም በቅርቡ ከወጡ ከመጠበቂያ ግንብ እና ከንቁ! መጽሔቶች የተገኙ ነጥቦችን የመነጋገር ልማድ አላችሁ? ስለ ቀኑ ውሏችሁና ስላገኛችኋቸው የተትረፈረፉ ስጦታዎቹ ‘ስትተኙም፣ ስትነሡም’ ይሖዋን ታመሰግናላችሁ? (ዘዳግም 6:6-9) ለአምላክ ያላችሁ ፍቅር በምታደርጓቸው ነገሮች ሁሉ ሲንጸባረቅ ሲመለከቱ ልጆች እውነትን የራሳቸው እንዲያደርጉ ይረዳቸዋል።
16. ልጆች ራሳቸው ምርምር እንዲያደርጉ ማበረታታቱ ምን ጥቅም አለው?
16 ልጆች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ወይም ሁኔታዎች ስኬታማ በሆነ መንገድ መወጣት እንዲችሉ አልፎ አልፎ መመሪያ ማግኘት ይኖርባቸዋል። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ሁልጊዜ ከምትነግሯቸው ይልቅ ራሳቸው ምርምር እንዲያደርጉ በማበረታታት አምላክ ለነገሮች ያለውን አመለካከት እንዴት ማግኘት እንደሚችሉ ለምን አታሳዩዋቸውም? ‘ታማኝና ልባም ባሪያ’ የሚያቀርባቸውን ሁሉንም ዓይነት መሣሪያዎችና ጽሑፎች ጥሩ አድርጎ መጠቀም የሚቻልበትን ዘዴ ልጆችን ማስተማር ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና እንዲያዳብሩ ይረዳቸዋል። (1 ሳሙኤል 2:21ለ) ካደረጉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምርምር ያገኟቸውን ጥቅሞች ለተቀሩት የቤተሰቡ አባላት ሲያካፍሉ የቤተሰቡ መንፈሳዊነት ይበልጥ እያደገ ይሄዳል።
ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኑ
17. ነጠላ ወላጆች ልጆቻቸውን ክርስቲያን አድርገው ለማሳደግ በሚያደርጉት ጥረት ተስፋ መቁረጥ የማይኖርባቸው ለምንድን ነው?
17 በነጠላ ወላጅ ስለሚተዳደሩ ቤተሰቦችስ ምን ለማለት ይቻላል? እነዚህ ቤተሰቦች ልጆችን በማሳደግ ረገድ ተጨማሪ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል። ሆኖም ነጠላ ወላጅ የሆናችሁ አይዟችሁ! በአምላክ ከሚታመኑ፣ እርሱ የሚሰጣቸውን ምክር በታዛዥነት ሥራ ላይ ካዋሉ፣ ጥሩና በመንፈሳዊ ጠንካራ ልጆች ካሳደጉ ነጠላ ወላጆች ሁኔታ ማየት እንደሚቻለው ስኬታማ መሆን ትችላላችሁ። (ምሳሌ 22:6) እርግጥ ነው፣ ነጠላ ወላጅ የሆኑ ክርስቲያኖች ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመንና አስፈላጊውን እርዳታ እንደሚሰጣቸው እምነት ማሳደር ይኖርባቸዋል።—መዝሙር 121:1-3
18. ወላጆች ትኩረት መስጠት ያለባቸው ለየትኞቹ የልጆች አእምሯዊና አካላዊ ፍላጎት ነው? ሆኖም ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
18 አስተዋይ የሆኑ ወላጆች ‘ለመሳቅ ጊዜ እንዳለው፣ ለመዝፈንም ጊዜ እንዳለው’ ይገነዘባሉ። (መክብብ 3:1, 4) ልጆች ዘና እንዲሉና ሚዛናዊና ጤናማ በሆነ መዝናኛ እንዲካፈሉ በማድረግ አእምሯቸውና አካላቸው እንዲታነጽ ማድረጉ የግድ አስፈላጊ ነው። የሚያንጹ ሙዚቃዎችና በተለይ ደግሞ ለአምላክ የውዳሴ መዝሙር መዘመር አንድ ልጅ ጤናማ አስተሳሰብ እንዲያዳብር የሚረዳው ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ ጋር የመሠረተው ዝምድና እንዲጠናከር በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ሊጫወት ይችላል። (ቆላስይስ 3:16) በተጨማሪም የወጣትነት ጊዜ ከሕይወት የምናገኘው ደስታ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ይቀጥል ዘንድ አምላክን የምንፈራ አዋቂዎች ሆነን ለመገኘት የምንዘጋጅበት ወቅት ነው።—ገላትያ 6:8
19. ወላጆች ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚያደርጉትን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክላቸው እርግጠኛ መሆን የሚችሉት ለምንድን ነው?
19 ይሖዋ ሁሉም ቤተሰቦች ጠንካራ መንፈሳዊ ተቋም ለመሆን የሚያደርጉት ጥረት የተሳካ እንዲሆን ይፈልጋል። አምላክን ከልብ የምንወድድና ቃሉን ለመታዘዝ የተቻለንን ያህል ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ ከሆነ እርሱም ጥረታችንን ይባርክልናል እንዲሁም በመንፈስ አነሳሽነት የሰፈሩ መመሪያዎቹን መከተል እንችል ዘንድ ጥንካሬ ይሰጠናል። (ኢሳይያስ 48:17፤ ፊልጵስዩስ 4:13) ልጆቻችሁን ለማስተማርና ለማሠልጠን አሁን ያላችሁ አጋጣሚ የሚያልፍና ዳግመኛ ልታገኙት የማትችሉት እንደሆነ ሁልጊዜ አስታውሱ። በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ምክሮች በሥራ ላይ ለማዋል የተቻላችሁን ሁሉ አድርጉ፤ ይሖዋም በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ ለመገንባት የምታደርጉትን ጥረት ይባርክላችኋል።
ምን ትምህርት አገኘን?
• ልጆችን በማሠልጠን ረገድ ጊዜ መዋጀት እጅግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ወላጆች ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ልጆች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ጠቃሚ የሆኑ አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው?
• አንድ ቤተሰብ መንፈሳዊነቱን ጠብቆ ማቆየት የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመንፈሳዊ ጠንካራ የሆነ ቤተሰብ አዘውትሮ የአምላክን ቃል ያጠናል፣ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ይገኛል እንዲሁም አንድ ላይ በአገልግሎት ይካፈላል