በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ፊት የተገኘ ድል
በጀርመን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች መቀመጫው በካርልዝሩው በሆነው በፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ ፊት አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ድል ተቀዳጁ። በዚህ መንገድ ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያስችላቸውን የላቀ ግምት የሚሰጠው እርምጃ ወስደዋል።
የይሖዋ ምሥክሮች በጀርመን ከ100 ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ምሥራቹን ሲሰብኩ ቆይተዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን በሁለት አምባገነናዊ አገዛዞች ማለትም በብሔራዊ ሶሻሊስቶች እና በኮሚኒስቶች እጅ የደረሰባቸውን መራራ ስደት ተቋቁመው አልፈዋል። ከ1990 አንስቶ ምሥክሮቹ እንደ አንድ ሕጋዊ ሰውነት ያለው ድርጅት በመሆን እውቅና ለማግኘት ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምሥክሮቹ በሁለት ጉዳዮች ላይ የተፈረደላቸው ቢሆንም የሦስተኛውን ጉዳይ ውድቅ መደረግ ተከትሎ ለፌዴራሉ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ይግባኝ የጠየቁ ሲሆን ፍርድ ቤቱም በታኅሣሥ 19, 2000 ውሳኔ ሰጠ።
ለይሖዋ ምሥክሮች በአንድ ድምፅ ተፈረደላቸው
ሰባቱም ዳኞች በአንድ ድምፅ ለይሖዋ ምሥክሮች ፈረዱ። ዳኞቹ የፌዴራል አስተዳደር ፍርድ ቤት በ1997 ያስተላለፈውን ብይን ከመሻራቸውም በላይ ፍርድ ቤቱ የይሖዋ ምሥክሮች ያስገቡትን ማመልከቻ በድጋሚ እንዲያጤን ትእዛዝ ሰጥተዋል።
የፌዴራሉ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም በመንግሥት እና በሃይማኖታዊ ቡድኖች መካከል ባለው መሠረታዊ ዝምድና ላይ ሐሳብ ሰጥቷል። በመሠረቱ የአንድ ሃይማኖት ምንነት “የሚለካው በሚከተላቸው እምነቶች ሳይሆን በሥነ ምግባሩ ነው።”
በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች በ“ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት” ሰበብ “የዲሞክራሲን መሠረታዊ ሥርዓቶች አይጋፉም” እንዲሁም “ዲሞክራሲን በሌላ ዓይነት መስተዳድር የመተካት ዓላማ የላቸውም” ሲል ተናግሯል። ስለሆነም የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካ ምርጫ አለመሳተፋቸው ሕጋዊ እውቅና ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጥያቄ ላለመቀበል ማስረጃ ተደርጎ መቅረብ የለበትም።—ዮሐንስ 18:36፤ ሮሜ 13:1
ከዚህም በላይ ጉባኤው አንድ አማኝ፣ የይሖዋ ምሥክርም ሆነ የሌላ እምነት ተከታይ መንግሥት የሚያወጣው መመሪያና እምነቱ እንዲያሟላ የሚጠይቅበት ግዴታ አንዳንድ ጊዜ እርስ በርስ የሚቃረኑበት ሁኔታ ሊደቀንበት እንደሚችል ጠቅሷል። ግለሰቡ “ከሕጉ ይልቅ ሃይማኖታዊ እምነቶቹን በማክበር” ሕሊናውን መታዘዝ ከመረጠ መንግሥት የግለሰቡ ምርጫ ተቀባይነት እንዳለውና ከሃይማኖታዊ ነፃነት ድንበር እንዳልወጣ አድርጎ ሊመለከተው ይችላል።—ሥራ 5:29
ይህ ውሳኔ ርዕሰ ዜና ሆኖ ቀርቧል። ጀርመን ውስጥ የሚታተሙ ጋዜጦች በሙሉ ለማለት ያስደፍራል ጉዳዩን የሚመለከት ዘገባ ይዘው ወጥተዋል። ታላላቅ የቴሌቪዥን እና የራዲዮ ጣቢያዎች በሙሉ ጉዳዩን የሚመለከት ሐተታ አሊያም ቃለ ምልልስ አቅርበዋል። ጀርመን ውስጥ የይሖዋ ስም ይህን ያህል በሰፊው የተነገረበት ጊዜ የለም።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
AP Photo/Daniel Maurer