የክሎቪስ ጥምቀት—በፈረንሳይ 1,500 ዓመት ያስቆጠረው የካቶሊክ እምነት
“በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ስም፣ ቡም።” ይህ መልእክት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዳግማዊ ጆን ፖል መስከረም 1996 ፈረንሳይ ውስጥ ይጎበኙታል ተብሎ በታቀደው አንድ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከጓዳ ሠራሽ ቦምብ ጋር የተገኘ ነበር። መልእክቱ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በፈረንሳይ የሚያደርጉት አምስተኛ ጉብኝት ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት እንደነበረ የሚጠቁም ጉልህ ምሳሌ ነው። የሆነ ሆኖ በዚያ ዓመት 200, 000 የሚያክሉ ሰዎች የፍራንካውያን ንጉሥ ክሎቪስ ወደ ካቶሊክ እምነት የተለወጠበትን 1, 500ኛ ዓመት ከጳጳሱ ጋር ለማክበር የፈረንሳይ ከተማ ወደሆነችው ወደ ሪምዝ ጎርፈዋል። ጥምቀቱ የፈረንሳይ ጥምቀት የተባለለት ይህ ንጉሥ ማን ነው? ክብረ በዓሉ ይህን ያክል ውዝግብ ያስነሳውስ ለምንድን ነው?
እየከሰመ የመጣ የዘውድ አገዛዝ
የሳሊያን ፍራንካውያን ንጉሥ የነበረው የቀዳማዊ ቺልደሪክ ልጅ ክሎቪስ በ466 እዘአ ገደማ ተወለደ። ፍራንካውያን ከ358 እዘአ ጀምሮ በሮማውያን ቁጥጥር ሥር ከወደቁ በኋላ ይህ የጀርመን ጎሣ ዳር ድንበር የመጠበቅና ለሮማ ሠራዊት ወታደር የመመልመል ግዴታ ተጥሎበት በዛሬዋ ቤልጅየም እንዲሰፍር ተፈቀደለት። ፍራንካውያን በአካባቢው ከሚኖሩት ጋሎ ሮማን ሕዝብ ጋር የቀረበ ግንኙነት መመሥረታቸው ቀስ በቀስ የሮማ ዜግነት አስገኝቶላቸዋል። ቀዳማዊ ቺልደሪክ የሮማውያን ወዳጅ ስለነበር ቪዚጎዝ እና ሳክሰን የመሳሰሉ ሌሎች የጀርመን ጎሣዎች የሚሰነዝሩትን ጥቃት ለመከላከል ይዋጋ ነበር። ይህም የጋሎ ሮማን ሕዝብ አድናቆት አስገኝቶለታል።
የሮማ ግዛት የሆነችው ጋውል በስተሰሜን ከሚገኘው ከሪን ወንዝ አንስቶ በስተደቡብ እስከሚገኘው እስከ ፒሬኔ ድረስ ያለውን ክልል ይሸፍን ነበር። ይሁን እንጂ ሮማዊው ጄኔራል ኤይሸስ በ454 እዘአ መሞቱ አገሪቱን መንግሥት አልባ እንድትሆን አደረጋት። ከዚህም በተጨማሪ የሮም የመጨረሻ ንጉሠ ነገሥት የነበረው ሮሚለስ ኦጉስቹለስ በ476 እዘአ መሞቱና የሮም ንጉሠ ነገሥት ምዕራባዊ ግዛት መክሰሙ በአካባቢው ከፍተኛ የፖለቲካ አለመረጋጋት እንዲሰፍን አደረገ። በዚህም ምክንያት ጎል በአጎራባች ከሚኖሩት ጎሣዎች መካከል በአንዱ ለመበላት የደረሰች ፍሬ መስላ ነበር። ክሎቪስ በአባቱ እግር ከተተካ በኋላ ግዛቱን ለማስፋፋት መቋመጡ ምንም የሚያስደንቅ አይደለም። በ486 እዘአ በስዋሶህ ከተማ አቅራቢያ በተደረገ ጦርነት ሮም በጎል ያስቀመጠችውን የመጨረሻ ወኪል ድል አደረገ። ይህ ድል በስተሰሜን ከሚገኘው የሶም ወንዝ አንስቶ በመካከለኛውና ምዕራባዊ ጎል እስከሚገኘው ልዋር ወንዝ ድረስ ያለውን ክልል በሙሉ በቁጥጥሩ ሥር እንዲያደርግ አስችሎታል።
ንጉሥ የሚሆነው ሰው
ፍራንካውያን እንደ ሌሎቹ የጀርመን ጎሣዎች አረማዊ እምነታቸውን አልለወጡም ነበር። ይሁን እንጂ ክሎቪስ የቡርጉንዲያንን ልዕልት ክለቲልዳን ማግባቱ በሕይወቱ ላይ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። አጥባቂ ካቶሊክ የነበረችው ክለቲልዳ ባለቤትዋ እንዲለወጥ ያላሰለሰ ጥረት ታደርግ ጀመር። በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ የቱር ከተማ ነዋሪ በነበረው በግሬግሪ የተመዘገበው ታሪክ እንደሚያስረዳው በ496 እዘአ በቶልቢያክ (በጀርመንኛ ጹልፒክና) እና በአሌማኒ ጎሣ መካከል ይደረግ በነበረው ጦርነት የክለቲልዳ አምላክ ድል እንዲያደርግ ከረዳው የአረማዊ እምነቱን እንደሚተው ክሎቪስ ቃል ገባ። ምንም እንኳ የክሎቪስ ወታደሮች ድል ሊደረጉ ተቃርበው የነበረ ቢሆንም የአልማኒ ንጉሥ ተገደለና ሠራዊቱ እጅ ሰጠ። እንደ ክሎቪስ እምነት ከሆነ ድሉን የሰጠው የክለቲልዳ አምላክ ነበር። በአፈ ታሪክ እንደሚነገረው ክሎቪስ ታኅሣሥ 25, 496 እዘአ ሪምስ በሚገኝ ካቴድራል ውስጥ “በቅዱስ” ሬሚጂየስ ተጠመቀ። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ክሎቪስ የተጠመቀው ከዚያ ቆይቶ በ498/9 እዘአ መሆን አለበት የሚል እምነት አላቸው።
ክሎቪስ የቡርጉንዲያን ደቡባዊ ምሥራቅ ለመያዝ ያደረገው ሙከራ ከሽፏል። ይሁን እንጂ ቪዝጎዛውያንን ለመያዝ ያደረገው ዘመቻ በ507 እዘአ በፕዋቲኤ አቅራቢያ ቩዬ ከተማ ላይ ድባቅ በመታቸው ጊዜ በድል ተጠናቅቋል። ይህም አብዛኛውን የጎልን ደቡብ ምዕራባዊ ክልል በቁጥጥሩ ሥር እንዲያደርግ አስችሎታል። የምሥራቃዊው የሮማ ግዛት ንጉሠ ነገሥት አናስታዚየስ ለዚህ ድል እውቅና በመስጠት ለክሎቪስ ከፍተኛ የክብር ማዕረግ ሰጡት። በዚህ መንገድ ከሌሎች የምዕራብ ነገሥታት ሁሉ የሚበልጥ ሥልጣን ያገኘ ሲሆን አገዛዙም በጋሎ ሮማን ሕዝብ ዘንድ ሕጋዊ እውቅናን አገኘ።
ክሎቪስ በራይን ወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ የፍራንካውያንን ክልል በግዛቱ ሥር ከጠቀለለ በኋላ ፓሪስን መናገሻ ከተማው አደረጋት። በሕይወቱ ማክተሚያ ዓመታት ላይ ሌክስ ሳሊካ የሚባል በጽሑፍ የሰፈረ ሕግ በማውጣትና ኦርሊንስ ላይ የቤተ ክርስቲያን ምክር ቤቱን ጠርቶ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ሊኖር የሚገባው ግንኙነት ምን መሆን እንዳለበት በመደንገግ መንግሥቱን አጠናከረ። ኅዳር 27, 511 እዘአ ሳይሆን አይቀርም ክሎቪስ ሲሞት የጎል ሦስት አራተኛ ገዥ ነበር።
ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ የክሎቪስን ወደ ካቶሊክ እምነት መለወጥ “በምዕራብ አውሮፓ ታሪክ አንድ ወሳኝ ምዕራፍ” በማለት ጠርቶታል። የዚህ አረማዊ ንጉሥ ሃይማኖተኛ መሆን ይህን ያህል ትልቅ ግምት የሚሰጠው ለምንድን ነው? ቁም ነገሩ ክሎቪስ ከአርዮስ እምነት ይልቅ ካቶሊክን መምረጡ ነው።
የአርዮስ እምነት የፈጠረው ውዝግብ
በ320 እዘአ ገደማ በግብፅ እስክንድርያ ውስጥ ቄስ የነበረው አርዮስ የሥላሴን ትምህርት አስመልክቶ ፍጹም የተለየ ሐሳብ ማራመድ ጀመረ። አርዮስ ወልድ በባሕርይም ሆነ በአካል ከአብ አይተናነስም የሚለውን ትምህርት አልቀበልም አለ። ወልድ መጀመሪያ ያለው በመሆኑ እግዚአብሔር ሊሆን ወይም ከአብ ጋር እኩል ሊሆን አይችልም። (ቆላስይስ 1:15) አርዮስ መንፈስ ቅዱስን በተመለከተ አካል እንደሆነ ቢቀበልም ከአብም ሆነ ከወልድ ያንሳል የሚል እምነት ነበረው። ሰፊ ተቀባይነት ያገኘው ይህ ትምህርት በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነሳ። በ325 እዘአ በተደረገው የኒቂያ ጉባኤ ላይ አርዮስ ወደ ግዞት እንዲወርድ ከመደረጉም በላይ ትምህርቶቹ ተወገዙ።a
ይሁን እንጂ ይህ ለውዝግቡ መቋጫ አላበጀለትም። መሠረተ ትምህርቱን በማስመልከት የተነሳው ይህ ውዝግብ አንዱን ወይም ሌላውን በሚደግፉ በተከታታይ በተነሱ ነገሥታት እየተደገፈ 60 ለሚያክሉ ዓመታት ቀጥሎ ነበር። በመጨረሻ በ392 እዘአ ቀዳማዊ ንጉሠ ነገሥት ቲኦዶሲየስ የሥላሴ መሠረተ ትምህርት የምታስተምረውን ጥንታዊቷን የካቶሊክ እምነት የሮማ ግዛት የመንግሥት ሃይማኖት እንድትሆን አደረገ። በዚህ ወቅት ጎቶች በጀርመናዊው ቄስ በኢልፊላስ አማካኝነት የአርዮስ እምነት ተከታዮች ሆነው ነበር። በሌሎቹ የጀርመን ጎሣዎችም ይህ “የክርስትና እምነት” በፍጥነት ተዛምቶ ነበር።b
በክሎቪስ ዘመን በጎል የነበረው የካቶሊክ እምነት ቀውስ ገጥሞት ነበር። የአርዮስ እምነት ተከታይ የነበሩት ቪሲጎቶች ሟች በመሆናቸው ምክንያት በሌላ የሚተኩ ሰብዓዊ ጳጳሳት አያስፈልጉንም በማለት የካቶሊክን እምነት አስጨንቀው ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱ ሮም ውስጥ እርስ በርስ በሚገዳደሉ ቀሳውስት ሁለት ተቃራኒ አንጃዎችን በሚመሩ ጳጳሳት ተከፋፍላ ውጥረት ነግሦባት ነበር። አንዳንድ የካቶሊክ ጸሐፊዎች በ500 እዘአ ዓለም ትጠፋለች የሚል ትምህርት መስጠታቸው ውጥረቱን ይበልጥ አባብሶታል። ስለሆነም ፍራንካዊው ድል አድራጊ ወደ ካቶሊክ እምነት መለወጡ “አዲስ የቅዱሳን ሺህ ዓመት” እንደሚመጣ የሚያበስር ተስፋ ሰጪ ምልክት ተደርጎ ታይቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የክሎቪስ ዓላማ ምን ነበር? ሃይማኖታዊ ዓላማ አልነበረውም ማለት ባይቻልም የፖለቲካ ዓላማ እንደነበረው ምንም ጥርጥር የለውም። ክሎቪስ የካቶሊክን እምነት መምረጡ አብዛኞቹ የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑትን የጋሎ ሮማን ሕዝብ ወዳጅነትንና ከፍተኛ ተደማጭነት የነበረውን የቤተ ክርስቲያን አመራር ድጋፍ አስገኝቶለታል። ይህ ደግሞ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የበላይነት እንዲያገኝ አስችሎታል። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ “በጎል ላይ የተቀዳጀው ድል ከፍተኛ ውግዘት ከደረሰባቸው መናፍቅ ከአርዮሳዊ እምነት ቀንበር የሚያላቅቅ ጦርነት እንደሆነ ተደርጎ ተቆጥሯል” በማለት አመልክቷል።
በእርግጥ ክሎቪስ ምን ዓይነት ሰው ነበር?
ከ1996ቱ ክብረ በዓል ቀደም ብሎ የሪምስ ሊቀ ጳጳስ ዤራር ዲፏ ስለ ክሎቪስ ሲናገሩ “በጣም ለታሰበበትና ሚዛናዊነት ለሚታይበት ለውጥ ግሩም ምሳሌ ነው” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ላቪስ “ክሎቪስ ወደ ካቶሊክ እምነት መለወጡ በጠባዩ ላይ ምንም ለውጥ ያላስገኘ ሲሆን ደግና ሰላማዊ የሆነው የወንጌል ግብረ ገብነት ልቡን አልነካውም” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አንድ ሌላ ታሪክ ጸሐፊ ደግሞ “ከኦዲን [ከኖርስ አምላክ] ይልቅ ክርስቶስን ቢለምንም አድሮ ቃሪያ ሆኗል” በማለት ተናግሯል። ክሎቪስ ዙፋኔን ይቀናቀኑኛል የሚላቸውን ሰዎች በሙሉ በዘዴ እየገደለ ሥልጣኑን በማደላደል ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና እምነት ተለውጧል ከተባለ በኋላ የፈጸመውን ድርጊት የሚያስታውስ ባሕርይ አሳይቷል። “የሩቅ ዘመዶቹን እንኳን ሳይቀር” ጨርሷቸዋል።
ክሎቪስ ከሞተ በኋላ ጨካኝ የሆነውን ይህን ጦረኛ ቅዱስ እንደሆነ አድርጎ የሚያቀርብ የተለያየ የፈጠራ ታሪክ ይነገር ጀመረ። ከአንድ መቶ ዓመት ገደማ በኋላ የቱር ከተማ ነዋሪ የሆነው ግሪጎሪ የጻፈው ዘገባ ክሎቪስን “ክርስትናን” ለመቀበል የመጀመሪያ ሮማዊ ንጉሠ ነገሥት ከሆነው ከቆስጠንጢኖስ ጋር ለማመሳሰል ታስቦ የተጻፈ እንደሆነ ተደርጎ ታይቷል። እንዲሁም ግሪጎሪ፣ ክሎቪስ ሲጠመቅ ዕድሜው 30 ዓመት እንደነበረ አድርጎ መጥቀሱ ከክርስቶስ ጋር ለማመሳሰል ያደረገው ሙከራ እንደሆነ አስመስሎታል።—ሉቃስ 3:23
እንዲህ ያለው ጥረት በዘጠነኛው መቶ ዘመንም በሪም ጳጳስ በአንክማር ቀጥሎ ነበር። አንክማር ካቴድራሎች መንፈሳዊ ጉዞን የሚያስተናግድ ደብር ለመሆን እርስ በርስ ፉክክር ባደረጉበት ወቅት ከእርሱ በፊት የነበረውን “የቅዱስ” ሪሚጂየስን የሕይወት ታሪክ የጻፈው ቤተ ክርስቲያኑን ስመ ጥር ለማድረግና ለማበልጸግ አስቦ ነበር። በታሪኩ ውስጥ ክሎቪስ በተጠመቀ ጊዜ አንዲት ነጭ እርግብ እሱን ለመቀባት በብልቃጥ ዘይት እንዳመጣች ተገልጿል። ይህ ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ስለመቀባቱ የሚገልጸውን መኮረጁ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ማቴዎስ 3:16) አንክማር በዚህ መንገድ ክሎቪስን፣ ሪምስንና ንጉሣዊ አገዛዙን በማያያዝ ክሎቪስ የጌታ ቅቡዕ ነው የሚለውን ሐሳብ ለማሳመን ሞክሯል።c
አወዛጋቢ ክብረ በዓል
የቀድሞ የፈረንሳይ ፕሬዚዳንት ቻርል ደ ጎል በአንድ ወቅት “በእኔ አመለካከት የፈረንሳይ ታሪክ የጀመረው ፈረንሳይ ተብሎ የተጠራው የፍራንክ ጎሣ ንጉሥ አድርጎ ከመረጠው ከክሎቪስ ነው” ብለው ነበር። ይሁን እንጂ ይህን አመለካከት የሚጋራው ሁሉም ሰው አይደለም። ክሎቪስ የተጠመቀበት ዕለት እንደሆነ ተደርጎ የተከበረው 1, 500ኛው ክብረ በዓል አወዛጋቢ ነበር። ከ1905 ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት በሕግ በተለያዩበት አገር ውስጥ መንግሥት ብዙዎች ሃይማኖታዊ ክብረ በዓል አድርገው የሚያዩትን በዓል ለመደገፍ ሽር ጉድ ማለቱን ተችተዋል። የሪምስ ከተማ ምክር ቤት ሊቀ ጳጳሱ ጉብኝት ሲያደርጉ የሚጠቀሙበትን መድረክ ማሠሪያ የመሸፈን ዕቅድ እንዳለው ሲያስታውቅ አንድ ድርጅት ውሳኔው ሕገ መንግሥቱን እንደሚቃረን በመግለጽ በፍርድ ቤት እንዲሻር አድርጓል። ሌሎች ደግሞ ቤተ ክርስቲያኒቱ የሥነ ምግባር ሥልጣኗን እንደገና በፈረንሳይ ላይ ለመጫን ጥረት በማድረግ ላይ እንዳለች ሆኖ ተሰምቷቸዋል። ክብረ በዓሉን ይበልጥ አወዛጋቢ ያደረገው ደግሞ ክሎቪስን የቀኝ ክንፍ ብሔራዊ ግንባር እና የአክራሪ ካቶሊክ ቡድኖች ተምሳሌት አድርጎ ማቅረቡ ያስነሳው ጥያቄ ነው።
ሌሎች ደግሞ በዓሉን ከታሪክ አንጻር በመመልከት ይቃወማሉ። የካቶሊክ እምነት ቀደም ሲል በጋሎ ሮማ ሕዝቦች ውስጥ ሥር ሰድዶ ስለነበር የክሎቪስ መጠመቅ ፈረንሳይን ወደዚህ እምነት አልለወጣትም ይላሉ። እንዲሁም የእርሱ መጠመቅ ፈረንሳይ ለምትባል አገር መወለድ መሠረት አልጣለም ይላሉ። ከዚህ ይልቅ ፈረንሳይ የተወለደችው ብለው የሚቀበሉት በ843 እዘአ የሻርለማኝ መንግሥት ከተከፈለ በኋላ ቻርለስ ዘ ባልድ የመጀመሪያው የፈረንሳይ ንጉሥ በሆነ ጊዜ እንጂ ክሎቪስ በነገሠ ጊዜ አይደለም።
1, 500 ዓመታት ያስቆጠረው የካቶሊክ እምነት
“የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ልጅ” የምትባለው የፈረንሳይ የካቶሊክ እምነት ከ1, 500 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ ትገኛለች? ፈረንሳይ እስከ 1938 ድረስ በዓለም ውስጥ በተጠመቁ ካቶሊኮች ቁጥር በአንደኛ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር። አሁን ግን ፊልፒንስንና ዩናይትድ ስቴትስን ከመሳሰሉ አገሮች በኋላ በስድስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። በፈረንሳይ 45 ሚልዮን የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ቢኖሩም ቤተ ክርስቲያን ሄደው የሚያስቀድሱት 6 ሚልዮን የሚያክሉት ብቻ ናቸው። በቅርቡ ፈረንሳይ በሚኖሩ የካቶሊክ እምነት ተከታዮች ላይ የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው 65 በመቶ የሚያክሉት አማኞች “ቤተ ክርስቲያኒቱ ፆታን አስመልክቶ ለምትሰጠው ትምህርት ግዴለሽ” ሲሆኑ ከእነዚህ መካከል 5 በመቶ የሚያክሉት ኢየሱስ በሕይወታቸው ውስጥ “ምንም ቦታ የለውም።” ይህ አሉታዊ ገጽታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ በ1980 ፈረንሳይን በጎበኙበት ወቅት “ፈረንሳይ በተጠመቅሽ ጊዜ የገባሽውን ቃል ኪዳን እምን አደረስሽው?” ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የነሐሴ 1, 1984 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 24ን ተመልከት።
b የግንቦት 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8-9 ላይ ተመልከት።
c ሉዊ የሚለው ስም የመጣው ክሎቪስ ከሚለው ስም ሲሆን (ሉዊ አሥራ ሰባተኛንና ሉዊ ፊሊፕን ጨምሮ) 19 የፈረንሳይ ነገሥታት ተጠርተውበታል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ሳክሰናውያን
የሪን ወንዝ
የሶም ወንዝ
ስዋሶህ
ሪምስ
ፓሪስ
ጎል
የልዋር ወንዝ
ቩዬ
ፕዋቲኤ
ፒሬኔ
ቪሲጎቶች
ሮም
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የክሎቪስን ጥምቀት የሚያሳይ የ14ኛው መቶ ዘመን ሥዕል
[ምንጭ]
© Cliché Bibliothèque nationale de France, Paris
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፈረንሳይ በሪምስ ካቴድራል በውጭ በኩል የሚገኝ የክሎቪስን ጥምቀት (የመካከለኛው) የሚያሳይ ቅርፅ
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ክሎቪስ የተጠመቀበትን በዓል ለማክበር ወደ ፈረንሳይ መምጣታቸው ውዝግብ አስነስቷል