ኢየሱስ የተወለደው እንዴት ነው? ለምንስ ዓላማ?
ክርስቲያን ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ስለ ኢየሱስ ልደት የሚያወሳውን ታሪክ ሲሰሙ “ፈጽሞ ሊሆን አይችልም!” በማለት ይናገራሉ። አንዲት ድንግል ሴት ከወንድ ጋር የጾታ ግንኙነት ሳትፈጽም ጸንሳ መውለድ ትችላለች ብሎ ማመኑ ኢ-ሳይንሳዊ እንደሆነ ይሰማቸዋል። የአንተስ አመለካከት ምንድን ነው?
የለንደኑ ዘ ታይምስ ጋዜጣ በ1984 ይህንን ጉዳይ የሚመለከት አንድ ደብዳቤ አውጥቶ ነበር። ደብዳቤው እንዲህ ይላል:- “ተአምራት ሊፈጸሙ እንደማይችሉ ለማረጋገጥ ሳይንስን እንደ ማስረጃ አድርጎ ማቅረብ ምክንያታዊ አይደለም። ተአምራት ሊፈጸሙ አይችሉም ብሎ ማመን ሊፈጸሙ ይችላሉ ብሎ የማመንን ያህል እምነት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።” ደብዳቤው ላይ በተለያዩ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሠሩ 14 የሳይንስ ፕሮፌሰሮች የፈረሙ ሲሆን “ድንግል መውለዷ፣ በወንጌል ውስጥ የተዘገቡ ተአምራትና የክርስቶስ ትንሣኤ ታሪካዊ ክንውኖች መሆናቸውን ያለአንዳች ጥርጥር እንቀበላለን” በማለት ተናግረዋል።
ይሁን እንጂ አንድ ሰው ኢየሱስ ከድንግል መወለዱን ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰማ ግራ መጋባቱ አይቀርም። ድንግል የነበረችው እናቱ ማርያም እንኳ የአምላክ መልአክ “እነሆም፣ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ፣ ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ” ብሎ ሲነግራት ለማመን ተቸግራ ነበር። ከዚህም የተነሳ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል?” በማለት መልአኩን ጠየቀችው። እርሱም መልሶ አምላክ ይህንን ተአምር የሚፈጽመው በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንደሆነ ከገለጸላት በኋላ “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለምና” ሲል ተናገረ። (ሉቃስ 1:31, 34-37) በእርግጥም የሰው ልጆችን አስደናቂ የመዋለድ ሂደት የፈጠረው አምላክ ኢየሱስን ከአንዲት ድንግል እንዲወለድ ማድረግ አያቅተውም። አምላክ አጽናፈ ዓለሙንና በውስጡ ያለውን ዝንፍ የማይል የተፈጥሮ ሥርዓት ከፈጠረ በማርያም ማሕጸን ውስጥ ያለን አንድ እንቁላል ተጠቅሞ ፍጹም የሆነ ሰው መፍጠር እንዴት ሊሳነው ይችላል?
በምድር ላይ መወለድ ያስፈለገው ለምንድን ነው?
ማርያም በጸነሰችበት ወቅት አምላካዊ አክብሮት ያለው የዮሴፍ እጮኛ ነበረች። የአምላክ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ታይቶት ድንግል የሆነችው እጮኛው ያረገዘችበትን አሳማኝ ምክንያት እንደሚከተለው ሲል ነገረው:- “ከእርስዋ የተፀነሰው ከመንፈስ ቅዱስ ነውና እጮኛህን ማርያምን ለመውሰድ አትፍራ። ልጅም ትወልዳለች፤ እርሱ ሕዝቡን ከኃጢአታቸው ያድናቸዋልና ስሙን ኢየሱስ ትለዋለህ።” (ማቴዎስ 1:20, 21) ኢየሱስ የሚለው ስም በዕብራይስጥ ቋንቋ “ይሖዋ ያድናል” ማለት ሲሆን ይህ ስም ከኃጢአትና ከሞት መዳን አስፈላጊ መሆኑን እንዲሁም አምላክ እንዲህ ዓይነቱን መዳን እንድናገኝ ሲል በክርስቶስ በኩል ያደረገውን ዝግጅት ያስታውሰናል።
የመጀመሪያው ሰው አዳም ኃጢአት በመሥራቱ ምክንያት ልጆቹ በሙሉ ፍጽምና የጎደላቸውና የአምላክን ሕግ የመጣስ ዝንባሌ ያላቸው ሆነው ተወለዱ። (ሮሜ 5:12) ታዲያ የአዳም ዘሮች ከኃጢአትና ከሞት ድነው ፍጹም መሆን የሚችሉት እንዴት ነው? የፍትህን ሚዛን ለማስተካከል አዳም ከነበረው ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት ጋር የሚተካከል ሌላ ፍጹም ሰብዓዊ ሕይወት መከፈል ነበረበት። አምላክ፣ ፍጹም ሰው የሆነው ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ እንዲወለድ ያደረገውና ኢየሱስም ጠላቶቹ እንዲገድሉት የፈቀደው በዚህ ምክንያት ነበር። (ዮሐንስ 10:17, 18፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:5, 6) ኢየሱስ ትንሣኤ ካገኘና ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ “ሞቼም ነበርሁ እነሆም፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ሕያው ነኝ፣ የሞትና የሲኦልም [የሰው ልጆች የጋራ መቃብር] መክፈቻ አለኝ” ብሎ በልበ ሙሉነት መናገር ችሏል።—ራእይ 1:18
ኢየሱስ የሞትንና የሲኦልን ምሳሌያዊ ቁልፎች ተጠቅሞ ኃጢአተኛው የሰው ዘር አዳም ያጣውን ፍጹም ሕይወት መልሶ የሚያገኝበትን መንገድ ይከፍታል። ኢየሱስ “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 11:25, 26) ይህ ምንኛ አስደናቂ ተስፋ ነው! ይሁን እንጂ ኢየሱስ በምድር ላይ የተወለደበት ዋነኛው ምክንያት ይህ አይደለም።
ዋነኛው ምክንያት
ኢየሱስ በሕይወት መኖር የጀመረው በማርያም ማህፀን ውስጥ አልነበረም። ኢየሱስ “ከሰማይ ወርጃለሁ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐንስ 6:38) ኢየሱስ ከፍጥረት መጀመሪያ አንስቶ ከሰማያዊ አባቱ ጋር በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ አብሮ ኖሯል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን “በእግዚአብሔርም ፍጥረት መጀመሪያ የነበረው” በማለት ይገልጸዋል። (ራእይ 3:14) ኢየሱስ ከሰማይ ሆኖ አንድ ክፉ መልአክ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች በአምላክ አገዛዝ ላይ እንዲያምፁ ሲያደርግ ተመልክቷል። ኢየሱስ የአምላክ ፍጹም ሰብዓዊ ልጅ ሆኖ እንዲወለድ ያነሳሳው ከሁሉ የላቀው ምክንያት ይህ ነው። ታዲያ ወደ ምድር መምጣቱ ምን ነገር እንዲያከናውን አስችሎታል?
ወደ ምድር መምጣቱ ሰማያዊ አባቱ አጽናፈ ዓለሙን የመግዛት መብት እንዳለው ለማረጋገጥ አስችሎታል። ኢየሱስ በምድር ላይ ተወልዶ እስከሞተበት ጊዜ ድረስ ታማኝነቱን በመጠበቅ ይሖዋ ፍጥረታቱን ለሚያስተዳድርበት ሥርዓት ራሱን ለማስገዛት ያለውን ፈቃደኝነት አሳይቷል። ኢየሱስ በአምላክ ጠላቶች ከመገደሉ በፊት መሥዋዕታዊ ሞት ለመሞት ፈቃደኛ የሆነው አባቱን እንደሚወድድ ዓለም እንዲያውቅ እንደሆነ ተናግሯል። (ዮሐንስ 14:31) የመጀመሪያዎቹ ሰብዓዊ ፍጡራን ማለትም አዳምና ሔዋን ለአምላክ እንዲህ ያለውን ፍቅር አዳብረው ቢሆን ኖሮ የደረሰባቸውን ቀላል ፈተና ማለፍ በቻሉ ነበር።—ዘፍጥረት 2:15-17
ኢየሱስ ያሳየው ታማኝነት ክፉው መልአክ ሰይጣን ውሸታም መሆኑንም ጭምር አጋልጧል። ሰይጣን በሰማይ መላእክት ፊት “ሰው ያለውን ሁሉ ስለ ሕይወቱ ይሰጣል” ብሎ በመናገር አምላክንና ሰውን ተሳድቧል። (ኢዮብ 2:1, 4) ሰዎች አምላክን የሚታዘዙት ሕይወታቸው አደጋ ላይ እስካልወደቀ ድረስ ብቻ ነው የሚል የሐሰት ክስ ሰንዝሮባቸዋል።
ይህ ግድድር የአምላክን አገዛዝ ትክክለኛነት አጠያያቂ አድርጎታል። ለዚህ ግድድር እልባት ለማስገኘት ሲባል ኢየሱስ ሰው ሆኖ ለመወለድና እስከሞት ድረስ ታማኝነቱን ለመጠበቅ ፈቃደኛ ሆኗል።
ኢየሱስ “ለእውነት ልመሰክር” በማለት በምድር ላይ የተወለደበትን ዋነኛ ምክንያት ተናግሯል። (ዮሐንስ 18:37) የአምላክ አገዛዝ ሙሉ በሙሉ ትክክል እንደሆነና ራስን ለእርሱ ማስገዛት ዘላቂ ደስታ እንደሚያስገኝ በቃልም ሆነ በድርጊት በማሳየት ለእውነት መስክሯል። በተጨማሪም ኢየሱስ ወደ ምድር የመጣው ሰብዓዊ ሕይወቱን “ለብዙዎች ቤዛ” አድርጎ በመስጠት ኃጢአተኛ የሰው ዘሮች ፍጽምናና የዘላለም ሕይወት የሚያገኙበትን መንገድ ለመክፈት እንደሆነም ተናግሯል። (ማርቆስ 10:45) የሰው ልጆች እነዚህን አስፈላጊ ነጥቦች እንዲገነዘቡ ሲባል የኢየሱስን መወለድ የሚያወሳው ታሪክ በጽሑፍ እንዲሰፍር ተደርጓል። በተጨማሪም ቀጣዩ ርዕስ እንደሚያሳየው ከኢየሱስ መወለድ ጋር በተያያዘ ከተፈጸሙት ነገሮች ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶች ማግኘት ይቻላል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአዳም ዘሮች ከኃጢአት መዳን የሚችሉት እንዴት ነው?