የጌታ እራት ለአንተ ምን ትርጉም አለው?
“ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት።”—1 ቆሮንቶስ 11:27
1. በ2003 ከታቀዱት ሁሉ የላቀው ክንውን የትኛው ነው? በዓሉ መከበር የጀመረውስ እንዴት ነው?
በ2003 ከታቀዱት ሁሉ እጅግ የላቀው ክንውን ሚያዝያ 16 ቀን ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የሚከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ነው። በዚያን ዕለት የይሖዋ ምሥክሮች ይህን በዓል ለማክበር ይሰበሰባሉ። በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተብራራው ኢየሱስ ኒሳን 14, 33 እዘአ የዋለውን የማለፍ በዓል ከሐዋርያቱ ጋር ካከበረ በኋላ ይህን በዓል (የጌታ እራት ተብሎም ይታወቃል) አቋቋመ። የመታሰቢያው በዓል ምሳሌያዊ ያልቦካ ቂጣና ቀይ ወይን የሰውን ዘር ከወረሰው ኃጢአትና ሞት ለማንጻት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ኃጢአት የሌለበትን የክርስቶስን ሥጋና የፈሰሰውን ደም ያመለክታሉ።—ሮሜ 5:12፤ 6:23
2. በ1 ቆሮንቶስ 11:27 ላይ የሰፈረው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው?
2 ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን የሚካፈሉት ሰዎች በአክብሮት መካፈል ይኖርባቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጌታ እራት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ይከበር በነበረበት በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ ለነበሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ይህንን ጉዳይ ግልጽ አድርጓል። (1 ቆሮንቶስ 11:20-22) ጳውሎስ “ሳይገባው ይህን እንጀራ የበላ ወይም የጌታን ጽዋ የጠጣ ሁሉ የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ አለበት” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 11:27) እነዚህ ቃላት ምን መልእክት ይዘዋል?
አንዳንዶች ሳይገባቸው ተካፍለዋል
3. በቆሮንቶስ የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖች የጌታ እራት በሚከበርበት ጊዜ ምን ዓይነት ጠባይ ያሳዩ ነበር?
3 በቆሮንቶስ የሚገኙ በርካታ ክርስቲያኖች ሳይገባቸው ከቂጣውና ከወይኑ ተካፍለዋል። በመካከላቸው መከፋፈል ነበር፤ አንዳንዶች ራታቸውን በዓሉ ወደሚከበርበት ቦታ አምጥተው በዓሉ ከመከበሩ በፊት ወይም እየተከበረ እያለ ይበሉ ነበር። በዚህም ወቅት አብዛኛውን ጊዜ ከልክ በላይ ይበሉና ይጠጡ ነበር። በአእምሮም ሆነ በመንፈስ ዝግጁ አልነበሩም። ይህም “የጌታ ሥጋና ደም ዕዳ” እንዲኖርባቸው አድርጓል። እራታቸውን ሳይበሉ ወደ በዓሉ የመጡት ደግሞ ስለሚርባቸው ትኩረታቸውን በበዓሉ ላይ ማድረግ ያቅታቸዋል። አዎን፣ ብዙዎች ምንም አክብሮት ሳይኖራቸውና በዓሉ ያለውን ከፍተኛ ትርጉም ሳይገነዘቡ ከቂጣውና ከወይኑ ይካፈሉ ነበር። ስለዚህም በራሳቸው ላይ ፍርድ ማምጣታቸው ምንም አያስገርምም!—1 ቆሮንቶስ 11:27-34
4, 5. ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን የመካፈል ልማድ ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን መመርመር ያለባቸው ለምንድን ነው?
4 ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን የሚካፈሉ ሁሉ የመታሰቢያው በዓል ሲቃረብ በየዓመቱ ራሳቸውን መመርመራቸው በጣም አስፈላጊ ነው። ከዚህ የሕብረት ማዕድ በተገቢው ሁኔታ ለመካፈል መንፈሳዊ ጤንነታቸው የተጠበቀ መሆን አለበት። አንድ እስራኤላዊ ረክሶ እያለ ከሕብረት መሥዋዕቱ ማዕድ ቢበላ ከሕዝቡ ተለይቶ እንደሚጠፋ ሁሉ ለኢየሱስ መሥዋዕት አክብሮት የጎደለው ከዚያም አልፎ ንቀት የሚያሳይ ማንኛውም ክርስቲያን ‘ከአምላክ ሕዝብ ተለይቶ የመጥፋት’ አደጋ ሊገጥመው ይችላል።—ዘሌዋውያን 7:20፤ ዕብራውያን 10:28-31
5 ጳውሎስ የመታሰቢያውን በዓል በጥንቷ እስራኤል ይቀርብ ከነበረው የሕብረት መሥዋዕት ጋር አመሳስሎታል። ከመታሰቢያው በዓል የሚካፈሉ ሰዎች ከክርስቶስ ጋር ሕብረት እንዳላቸው ከተናገረ በኋላ “የጌታን ጽዋና የአጋንንትን ጽዋ ልትጠጡ አትችሉም፤ ከጌታ ማዕድና ከአጋንንት ማዕድ ልትካፈሉ አትችሉም” በማለት ተናግሯል። (1 ቆሮንቶስ 10:16-21) ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን የመካፈል ልማድ ያለው አንድ ክርስቲያን ከባድ ኃጢአት ቢሠራ ኃጢአቱን ለይሖዋ መናዘዝና በጉባኤው ካሉ የጎለመሱ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እርዳታ ማግኘት ይኖርበታል። (ምሳሌ 28:13፤ ያዕቆብ 5:13-16) እውነተኛ ንስሐ ከገባና ለንስሐ የሚገባ ፍሬ ካፈራ ከመታሰቢያው በዓል ሳይገባው እንደተካፈለ ተደርጎ አይቆጠርም።—ሉቃስ 3:8
በበዓሉ ላይ ተገኝቶ ሥነ ሥርዓቱን በአክብሮት መመልከት
6. አምላክ የጌታን እራት የመካፈል ልዩ መብት የሰጠው ለእነማን ነው?
6 በምድር ላይ ለሚገኙት የክርስቶስ ወንድሞች ለሆኑት የ144, 000 ቀሪ አባላት መልካም እያደረጉ ያሉ ከጌታ እራት መካፈል ይኖርባቸዋልን? (ማቴዎስ 25:31-40፤ ራእይ 14:1) አይኖርባቸውም። አምላክ ይህን ልዩ መብት የሰጠው ‘ከክርስቶስ ጋር አብረው ወራሾች’ እንዲሆኑ በመንፈስ ቅዱስ ለቀባቸው ግለሰቦች ነው። (ሮሜ 8:14-18፤ 1 ዮሐንስ 2:20) ታዲያ በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ሰዎችስ የሚያገኙት ቦታ ምንድን ነው? (ሉቃስ 23:43፤ ራእይ 21:3, 4) ከኢየሱስ ጋር አብረው የሚወርሱና ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ስላልሆኑ በመታሰቢያው በዓል ላይ ተገኝተው የበዓሉን ሥነ ሥርዓት በአክብሮት ይከታተላሉ።—ሮሜ 6:3-5
7. የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን መካፈል እንዳለባቸው ያውቁ የነበረው እንዴት ነው?
7 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ እውነተኛ ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ነበሩ። ብዙዎቹ በልሳን እንደመናገር ያሉ አንድ ወይም ከዚያ በላይ ተአምራዊ የሆኑ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ነበሯቸው። ስለዚህም እንደነዚህ ያሉ ሰዎች በመንፈስ የተቀቡ መሆናቸውንና ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን መካፈል እንዳለባቸው ማወቅ አይቸግራቸውም ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን አንድ ክርስቲያን በመንፈስ የተቀባ መሆኑን የሚያውቀው “በእግዚአብሔር መንፈስ የሚመሩ ሁሉ እነዚህ የእግዚአብሔር ልጆች ናቸውና። አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደ ገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና” እንደሚሉ ያሉትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን ቃላት መሠረት በማድረግ ነው።—ሮሜ 8:14, 15
8. ማቴዎስ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሱት “ስንዴ” እና “እንክርዳድ” ምን ያመለክታሉ?
8 ባለፉት መቶ ዘመናት እውነተኛ ቅቡዓን ክርስቲያኖች “እንክርዳድ” ወይም ሃሰተኛ ክርስቲያኖች በተዘሩበት መስክ ላይ እንደ “ስንዴ” በቅለው ነበር። (ማቴዎስ 13:24-30, 36-43) ከ1870 ጀምሮ ‘የስንዴው’ ማንነት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ የመጣ ሲሆን ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ የተቀቡ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች እንዲህ ተብለው ነበር:- “ሽማግሌዎች . . . [በመታሰቢያው በዓል] ላይ የተገኙትን ሁሉ (1) [በክርስቶስ] ደም ማመንና (2) ለጌታና ለአገልግሎቱ እስከ ሞት ድረስ ራሳቸውን መወሰን . . . እንዳለባቸው ሊያስገነዝቧቸው ይገባል። ከዚያም እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉት ሁሉ መካፈል እንደሚችሉ መንገር ይኖርባቸዋል።”—ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ፣ ክፍል 6፤ ዘ ኒው ክሪኤሽን፣ ገጽ 473a
‘ሌሎች በጎችን’ መፈለግ
9. ‘የእጅግ ብዙ ሰዎች’ ማንነት በ1935 ግልጽ ሆኖ የተብራራው እንዴት ነው? ይህ ማብራሪያ ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን ይካፈሉ የነበሩ አንዳንዶች ምን እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል?
9 ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ድርጅት ከቅቡዓኑ የክርስቶስ ተከታዮች በተጨማሪ ትኩረቱን በሌሎች ላይ ማድረግ ጀመረ። በ1930ዎቹ አጋማሽ ላይ ይህንን ጉዳይ ይበልጥ ግልጽ የሚያደርግ ሁኔታ ተከሰተ። ከዚህ ቀደም የአምላክ ሕዝቦች በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹት “እጅግ ብዙ ሰዎች” ትንሣኤ አግኝተው በሰማይ ከሚገኙት የ144, 000 ቅቡዓን አባላት ጋር የሚተባበሩ ሁለተኛ ደረጃ መንፈሳዊ ጥሪ ያላቸው የክርስቶስ ሙሽራ ሚዜዎች ወይም አጃቢዎች እንደሆኑ አድርገው ያስቡ ነበር። (መዝሙር 45:14, 15፤ ራእይ 7:4፤ 21:2, 9) ሆኖም ግንቦት 31, 1935 በዩ ኤስ ኤ፣ ዋሽንግተን ዲ ሲ በተደረገ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃ ስብሰባ ላይ በቀረበ ንግግር “እጅግ ብዙ ሰዎች” በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩትን “ሌሎች በጎች” እንደሚያመለክቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያ ተሰጠ። (ዮሐንስ 10:16) ከዚህ ቀደም ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን ይካፈሉ የነበሩ አንዳንድ ወንድሞች ተስፋቸው ሰማያዊ ሳይሆን ምድራዊ መሆኑን በመገንዘባቸው ከስብሰባው በኋላ ከምሳሌያዊው ቂጣና ወይን መካፈላቸውን አቆሙ።
10. በዛሬው ጊዜ ያሉት “ሌሎች በጎች” ተስፋቸው ምንድን ነው? ምን ኃላፊነቶችስ አሉባቸው?
10 በተለይ ከ1935 ጀምሮ በቤዛው ላይ እምነት ያላቸውን፣ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑትንና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ‘ታናሹን መንጋ’ የሚደግፉትን ‘የሌሎች በጎች’ አባላት መፈለግ ተጀመረ። (ሉቃስ 12:32) እነዚህ ሌሎች በጎች በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ አላቸው። በሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ግን በዘመናችን ከሚገኙት የመንግሥት ወራሾች ጋር ይመሳሰላሉ። በጥንቷ እስራኤል ይሖዋን ያመልኩና ሕጉን ይታዘዙ እንደነበሩት መጻተኞች በዘመናችን ያሉት ሌሎች በጎችም ከመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ጋር ሆነው ምሥራቹን መስበክን የመሳሰሉ ክርስቲያናዊ ኃላፊነቶችን ይቀበላሉ። (ገላትያ 6:16) ሆኖም መጻተኞች በእስራኤል ንጉሥ ወይም ካህን እንደማይሆኑ ሁሉ ሌሎች በጎችም በሰማያዊው መንግሥት የመግዛትም ሆነ ካህን ሆኖ የማገልገል መብት አይኖራቸውም።—ዘዳግም 17:15
11. አንድ ሰው ራሱን ለአምላክ የወሰነበት ጊዜ ወደፊት በሚያገኘው ሕይወት ላይ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው እንዴት ነው?
11 ከዚያም በ1930ዎቹ ለሰማያዊው ጥሪ የሚደረገው ምርጫ መጠናቀቁ እያደር ግልጽ ሆነ። ላለፉት በርካታ አሥርተ ዓመታት ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ሌሎች በጎች የመፈለጉ ሥራ ሲካሄድ ቆይቷል። አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ታማኝነቱን ቢያጎድል በ144, 000ዎቹ መካከል የተፈጠረውን ክፍተት ለመሙላት የሚመረጠው አምላክን ለረዥም ዓመታት በታማኝነት ሲያገለግል የቆየ የሌሎች በጎች አባል እንደሚሆን ይጠበቃል።
አንዳንዶች በስህተት ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ሆኖ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
12. አንድ ክርስቲያን ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን መካፈሉን እንዲያቆም የሚያደርጉት አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ለምንስ?
12 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለሰማያዊ ሕይወት እንደተጠሩ ቅንጣት ያህል እንኳ አይጠራጠሩም። ሆኖም አንዳንዶች ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን የሚካፈሉት ለሰማያዊ ሕይወት ሳይጠሩ ቢሆንስ? ሰማያዊ ተስፋ እንዳልነበራቸው ከተገነዘቡ በኋላ ከመታሰቢያው በዓል ቂጣና ወይን መካፈላቸውን እንዲያቆሙ ሕሊናቸው እንደሚነግራቸው የተረጋገጠ ነው። ለሰማያዊ ንግሥናና የክህነት አገልግሎት እንዳልተጠራ እያወቀ ለዚህ መብት እንደተጠራ አድርጎ ራሱን በሚያቀርብ ግለሰብ አምላክ አይደሰትም። (ሮሜ 9:16፤ ራእይ 20:6) ሌዋዊው ቆሬ በትዕቢት ተነሳስቶ አሮናዊውን የክህነት አገልግሎት ለመያዝ በፈለገ ጊዜ ይሖዋ በሞት ቀጥቶታል። (ዘጸአት 28:1፤ ዘኍልቍ 16:4-11, 31-35) ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን የሚካፈለው በስህተት እንደነበረ ከተሰማው (ወይም ከተሰማት) ይህን ድርጊቱን አቁሞ ይሖዋ ይቅር እንዲለው በትሕትና መጸለይ ይኖርበታል።—መዝሙር 19:13
13, 14. አንዳንዶች በተሳሳተ መንገድ ሰማያዊ ጥሪ እንዳላቸው ሆኖ ሊሰማቸው የሚችለው ለምንድን ነው?
13 አንዳንዶች ሰማያዊ ጥሪ እንዳላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው የሚያደርጋቸው ምን ሊሆን ይችላል? የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ማጣታቸው ወይም በሌላ ምክንያት የደረሰ አንድ አሳዛኝ መከራ ምድራዊውን ሕይወት እንዲጠሉ ሊያደርጋቸው ይችላል። ወይም የተቀባ ክርስቲያን እንደሆነ የሚናገር የቅርብ ወዳጅ ካላቸው እነርሱም ይህን ሕይወት መመኘት እንዲጀምሩ ሊያደርጋቸው ይችላል። እርግጥ ነው፣ አምላክ ሌሎች ለዚህ መብት እንዲነሳሱ ለማድረግ በማንም ሰው አይጠቀምም። እንዲሁም አንድ ሰው የሰማያዊ ሕይወት ወራሽ መሆኑን የሚገልጽ ድምፅ እንዲሰማ በማድረግ ማንንም ለመንግሥት ንግሥና አይቀባም።
14 ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለው የሃሰት ሃይማኖት ትምህርት አንዳንዶች ለሰማያዊ ሕይወት እንደተጠሩ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ስለዚህ በፊት እናምንባቸው የነበሩ አንዳንድ የተሳሳቱ ትምህርቶች ወይም ሌሎች አመለካከቶች ተጽዕኖ እንዳያደርጉብን ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል አንዳንዶች ‘ስሜቴን ሊለውጥ የሚችል የወሰድኩት መድኃኒት ይኖር ይሆን? እንዲህ ያለው ዝንባሌ ሊያድርብኝ የቻለው ስሜታዊ ሰው ስለሆንኩ ይሆን?’ እያሉ ራሳቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ።
15, 16. አንዳንዶች በመንፈስ ተቀብተናል ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምን ሊሆን ይችላል?
15 አንዳንዶችም ‘በውስጤ ታዋቂ የመሆን ምኞት አለኝ? በአሁኑ ጊዜ ወይም ወደፊት ከክርስቶስ ጋር አብሮ በመግዛት ሥልጣን የመያዝ ምኞት አለኝ?’ ብለው ራሳቸውን ሊጠይቁ ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የመንግሥቱ ወራሽ እንዲሆኑ ከተመረጡት ክርስቲያኖች መካከል በጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የሌላቸው ነበሩ። እንዲሁም ሰማያዊ ጥሪ የተቀበሉ ክርስቲያኖች ታዋቂ ሆኖ የመታየት ምኞትም ሆነ የተቀቡ በመሆናቸው የሚኩራሩ ሰዎች አልነበሩም። “የክርስቶስ ልብ” ካላቸው ክርስቲያኖች የሚጠበቀውን የትሕትና ባሕርይ ያሳያሉ።—1 ቆሮንቶስ 2:16
16 አንዳንዶች ከፍተኛ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ያላቸው መሆኑ ሰማያዊ ጥሪ እንዳገኙ ሆኖ እንዲሰማቸው ሊያደርጋቸው ይችላል። ሆኖም ጳውሎስ አንዳንድ ቅቡዓንን ማስተማርና መምከር አስፈልጎት ስለነበር በመንፈስ መቀባት ልዩ የሆነ እውቀት አያስገኝም። (1 ቆሮንቶስ 3:1-3፤ ዕብራውያን 5:11-14) አምላክ ለሕዝቦቹ በሙሉ መንፈሳዊ ምግብ የሚያቀርብበት የራሱ የሆነ ዝግጅት አለው። (ማቴዎስ 24:45-47) ስለዚህ በመንፈስ መቀባት ምድራዊ ተስፋ ካላቸው ክርስቲያኖች የሚበልጥ ጥበብ ያስገኛል ብሎ ማንም ሰው ማሰብ አይኖርበትም። ቅዱስ ጽሑፋዊ መልስ በመስጠት፣ በመመሥከር ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር በማቅረብ ልዩ ችሎታ ማዳበር በመንፈስ መቀባትን አያመለክትም። በዚህ ረገድ የተዋጣላቸው በርካታ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም አሉ።
17. አንድ ሰው በመንፈስ መቀባቱ የተመካው በምንና በማን ላይ ነው?
17 አንድ ክርስቲያን ሰማያዊ ጥሪን በሚመለከት ጥያቄ ቢያቀርብ አንድ ሽማግሌ ወይም ሌላ የጎለመሰ ክርስቲያን ጉዳዩን ሊያብራራለት ይችላል። ይሁን እንጂ ማንም ሰው ለሌላው ውሳኔ ማድረግ አይችልም። ለሰማያዊ ሕይወት በትክክል የተጠራ ግለሰብ የዚህ ተስፋ ተካፋይ መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ ሌሎችን መጠየቅ አያስፈልገውም። ቅቡዓን ‘ዳግመኛ የተወለዱት ከሚጠፋ ዘር ሳይሆን በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው።’ (1 ጴጥሮስ 1:23) አምላክ በመንፈሱና በቃሉ አማካኝነት ግለሰቡ ሰማያዊ ተስፋ ያለው “አዲስ ፍጥረት” እንዲሆን የሚያደርገውን “ዘር” በውስጡ ይተክላል። (2 ቆሮንቶስ 5:17) ምርጫውን የሚያከናውነውም ይሖዋ ነው። አንድ ሰው የሚቀባው ‘ስለወደደ ወይም ስለ ሮጠ ሳይሆን ከአምላክ ነው።’ (ሮሜ 9:16) ታዲያ አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ እንዳለው የሚያውቀው እንዴት ነው?
ሰማያዊ ጥሪ እንዳገኙ እርግጠኞች የሚሆኑት እንዴት ነው?
18. የአምላክ መንፈስ ከቅቡዓኑ መንፈስ ጋር የሚመሰክረው እንዴት ነው?
18 የአምላክ መንፈስ የሚሰጠው ምሥክርነት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸው ያረጋግጥላቸዋል። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነትን መንፈስ ተቀበላችሁ . . . የእግዚአብሔር ልጆች መሆናችንን ያ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ይመሰክራል። ልጆች ከሆንን ወራሾች ደግሞ ነን፣ አብረንም ደግሞ እንድንከበር አብረን መከራ ብንቀበል ከክርስቶስ ጋር አብረን ወራሾች ነን።” (ሮሜ 8:15-17) መንፈስ ቅዱስ በቅቡዓኑ መንፈስ ላይ የሚያሳድረው ተጽእኖ ስለ ይሖዋ መንፈሳዊ ልጆች የሚናገሩት ጥቅሶች ለእነርሱ እንደተጻፉ እንዲሰማቸው ያደርጋል። (1 ዮሐንስ 3:2) የአምላክ መንፈስ የልጅነት መንፈስ ይሰጣቸዋል እንዲሁም ልዩ የሆነ ተስፋ በውስጣቸው ይተክልባቸዋል። (ገላትያ 4:6, 7) አዎን፣ በወዳጅ ዘመድ ተከብቦ ፍጹም ሕይወት አግኝቶ በምድር ላይ ለዘላለም መኖር ልዩ ስጦታ ቢሆንም አምላክ ለእነርሱ የሰጣቸው ተስፋ ግን ይህ አይደለም። አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት በውስጣቸው የተከለው በሰማይ የመኖር ተስፋ በጣም ጠንካራ ከመሆኑ የተነሳ ከምድራዊ ሕይወት ጋር የተያያዘ ማንኛውንም ዓይነት ዝምድናና የወደፊት ተስፋ መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው።—2 ቆሮንቶስ 5:1-5, 8፤ 2 ጴጥሮስ 1:13, 14
19. አዲሱ ቃል ኪዳን በቅቡዓን ክርስቲያኖች ሕይወት ላይ ምን ሚና ይጫወታል?
19 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋ እንዳላቸውና በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንደታቀፉ እርግጠኞች ናቸው። ኢየሱስ የመታሰቢያውን በዓል ሲያቋቁም ይህን ጉዳይ በመጥቀስ “ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 22:20) በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ የታቀፉት ሁለቱ ወገኖች አምላክና ቅቡዓን ናቸው። (ኤርምያስ 31:31-34፤ ዕብራውያን 12:22-24) ኢየሱስ መካከለኛ ነው። አዲሱ ቃል ኪዳን ሥራ ላይ የዋለው በፈሰሰው የክርስቶስ ደም አማካኝነት እንደመሆኑ በአዲሱ ቃል ኪዳን ውስጥ እንዲታቀፉ የተመረጡት ሰዎች አይሁዳውያን ብቻ ሳይሆኑ ይሖዋ ለስሙ የመረጣቸውና የአብርሃም “ዘር” ክፍል ያደረጋቸው አሕዛብም ይገኙበታል። (ገላትያ 3:26-29፤ ሥራ 15:14) ይህ ‘ዘላለማዊ ቃል ኪዳን’ ሁሉም መንፈሳዊ እስራኤላውያን በትንሣኤ አማካኝነት የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።—ዕብራውያን 13:20
20. ቅቡዓን ከክርስቶስ ጋር የገቡት ቃል ኪዳን ምንድን ነው?
20 ቅቡዓን ስለ ተስፋቸው እርግጠኞች ናቸው። የመንግሥት ቃል ኪዳን በሚባል ተጨማሪ ቃል ኪዳን ውስጥ ገብተዋል። ከክርስቶስ ጋር ያላቸውን ሕብረት በተመለከተ ኢየሱስ “እናንተ በፈተናዎቼ ከእኔ ጋር ጸንታችሁ የኖራችሁ ናችሁ፤ አባቴ እኔን እንደ ሾመኝ እኔ ደግሞ . . . ለመንግሥት እሾማችኋለሁ” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 22:28-30) በክርስቶስ እና በእርሱ ተባባሪ ነገሥታት መካከል ያለው ይህ ቃል ኪዳን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ራእይ 22:5
የመታሰቢያው በዓል ሰሞን አስደሳች ወቅት ነው
21. ከመታሰቢያው በዓል ሰሞን ከፍተኛ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?
21 በመታሰቢያው በዓል ሰሞን የሚያስደስቱ በርካታ እንቅስቃሴዎች አሉ። በበዓሉ ሰሞን እንድናነባቸው ከወጡልን የመጽሐፍ ቅዱስ ንባቦች ጥቅም እናገኛለን። ለጸሎት፣ ስለ ኢየሱስ ምድራዊ ሕይወትና ስለሞቱ ለማሰላሰልና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለመካፈልም ተስማሚ ጊዜ ነው። (መዝሙር 77:12፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) በዓሉም ቢሆን ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ጋር በተያያዘ አምላክና ክርስቶስ ያሳዩንን ፍቅር እንድናስታውስ ያደርገናል። (ማቴዎስ 20:28፤ ዮሐንስ 3:16) ይህ ዝግጅት ተስፋና ማጽናኛ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በላይ ክርስቶስ የተከተለው ዓይነት የሕይወት ጎዳና ለመከተል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክርልን ይሆናል። (ዘጸአት 34:6፤ ዕብራውያን 12:3) ከዚህም በተጨማሪ የመታሰቢያው በዓል አምላክን ለማገልገል የገባነውን ቃል እንድንፈጽምና የውድ ልጁ ታማኝ ተከታዮች እንድንሆን ያጠናክረናል።
22. አምላክ ለሰው ዘር ከሰጠው ሁሉ የላቀው ስጦታ የትኛው ነው? ለዚህ ስጦታው አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት አንደኛው መንገድ ምንድን ነው?
22 ይሖዋ የሰጠን ስጦታ ምንኛ ታላቅ ነው! (ያዕቆብ 1:17) የቃሉ መመሪያ፣ የመንፈስ ቅዱሱ እርዳታና ለዘላለም የመኖር ተስፋ ሰጥቶናል። አምላክ የሰጠው ከሁሉ የላቀ ስጦታ ለቅቡዓንና እምነት ላላቸው ሌሎች ሰዎች የተከፈለው የኢየሱስ መሥዋዕት ነው። (1 ዮሐንስ 2:1, 2) ታዲያ የኢየሱስ ሞት ለአንተ ያለው ትርጉም ምን ያህል ጥልቅ ነው? ሚያዝያ 16, 2003 ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የጌታን እራት ለማክበር ከሚሰበሰቡት ሰዎች ጋር አብረህ በመገኘት ለዚህ ዝግጅት አድናቆት እንዳለህ ታሳያለህ?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በይሖዋ ምሥክሮች የታተሙ። አሁን ግን መታተም አቁመዋል።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ከመታሰቢያው ቂጣና ወይን መካፈል ያለባቸው እነማን ናቸው?
• “ሌሎች በጎች” በተመልካችነት ብቻ በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው?
• ቅቡዓን ክርስቲያኖች በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይኑ መካፈል እንዳለባቸው የሚያውቁት እንዴት ነው?
• የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ምን ለማድረግ አጋጣሚ ይሰጠናል?
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል/ግራፍ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የመታሰቢያው በዓል ተሰብሳቢዎች ብዛት
በሚልዮን
15,597,746
15
14
13,147,201
13
12
11
10
9
8
7
6
5
4,925,643
4
3
2
1
878,303
63,146
1935 1955 1975 1995 2002
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዚህ ዓመት በሚከበረው የጌታ እራት በዓል ላይ ትገኛለህ?
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመታሰቢያው በዓል ሰሞን ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ለማድረግና በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ለመካፈል አመቺ ወቅት ነው