እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል
በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ሐሩራማው የበጋ ወቅት የጥላ ያለህ ያሰኛል። ከኃይለኛው የፀሐይ ንዳድ አረፍ የሚባልበት ጥላ ያለው ዛፍ በተለይ ደግሞ በመኖሪያ ቤት አጠገብ ያደገ ከሆነ በእጅጉ የሚፈለግ ነው። ሰፋፊ ቅጠሎችና ወደ ጎን በረጅሙ የተዘረጉ ቅርንጫፎች ያሉት የበለስ ዛፍ በአካባቢው ካሉት ዛፎች ሁሉ የተሻለ ጥላ አለው።
ፕላንትስ ኦቭ ዘ ባይብል የተሰኘው መጽሐፍ እንደገለጸው “[የበለስ ዛፍ] ከድንኳን ይልቅ መንፈስን የሚያድስና ሰውነትን ቀዝቀዝ የሚያደርግ ጥላ እንዳለው ይነገርለታል።” በጥንቷ እስራኤል በወይን እርሻዎች ዳርቻ ላይ የሚበቅሉ የበለስ ዛፎች ሠራተኞቹ አረፍ የሚሉበት አመቺ ጥላ ይፈጥሩላቸዋል።
ሞቃታማው ቀን ሲገባደድ የቤተሰብ አባላት በመኖሪያቸው አቅራቢያ በሚገኝ የበለስ ዛፍ ሥር ቁጭ ብለው ይጫወታሉ። ከዚህም በላይ የበለስ ዛፍ ገንቢ በሆኑ ንጥረ ነገሮች የበለጸገ ብዙ ፍሬ ያፈራል። በመሆኑም ከንጉሥ ሰሎሞን ዘመን አንስቶ በበለስ ዛፍ ሥር መቀመጥ ሰላምንና ብልጽግናን ያመለክት ነበር።—1 ነገሥት 4:24, 25
ከዚያ ጥቂት መቶ ዓመታት ቀደም ብሎ ነቢዩ ሙሴ ተስፋይቱን ምድር ‘በለስ የሞላባት ምድር’ በማለት ገልጿት ነበር። (ዘዳግም 8:8) ተስፋይቱን ምድር የሰለሉት አሥራ ሁለቱ ሰላዮች የምድሪቱን ለምነት ለማሳየት በለስንና ሌሎች ፍሬዎችን ወደ እስራኤላውያን ሠፈር አምጥተው ነበር። (ዘኍልቍ 13:21-23) በ19ኛው መቶ ዘመን ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የተጓዙ አንድ ጎብኚ በአካባቢው በብዛት ከሚገኙት ዛፎች መካከል አንዱ የበለስ ዛፍ መሆኑን ተናግረዋል። እንግዲያው በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በለስና የበለስ ዛፍ በርካታ ጊዜ መጠቀሱ ብዙም አያስገርምም!
በዓመት ሁለቴ የሚያፈራ ዛፍ
የበለስ ዛፍ አብዛኞቹ የአፈር ዓይነቶች የሚስማሙት ሲሆን ሥሮቹን በጥልቀት የመስደድ ባሕርይ ስላለው ረዘም ላሉ ወራት የሚዘልቀውን ደረቁን የበጋ ወቅት ተቋቁሞ ማለፍ ይችላል። ዛፉ በሰኔ ወር ላይ ጥቂት ፍሬዎችን ካፈራ በኋላ ዋናውን ምርት በነሐሴ ላይ መስጠቱ ከሌሎች ዛፎች ልዩ ያደርገዋል። (ኢሳይያስ 28:4) እስራኤላውያን ብዙውን ጊዜ ከመከር በፊት የሚደርሰውን ፍሬ በእሸትነት ይበሉታል። በመከር ጊዜ የሚደርሰውን ግን አድርቀው ዓመቱን ሙሉ ይጠቀሙበታል። የደረቀ በለስ ይጠፈጠፍና ለውዝ ተጨምሮበት የበለስ ቂጣ ይሆናል። ይህ የበለስ ቂጣ ለጤና ተስማሚና ሰውነት ገንቢ ከመሆኑም በላይ እጅ ያስቆረጥማል።
ልባም ሴት የነበረችው አቢግያ ለዳዊት 200 የበለስ ጥፍጥፍ አምጥታለት ነበር። ይህን ያደረገችው የበለስ ጥፍጥፍ በዱር በገደሉ ለሚንከራተቱ ሰዎች ተስማሚ ምግብ መሆኑን አስባ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (1 ሳሙኤል 25:18, 27) የበለስ ጥፍጥፍ ለመድኃኒትነትም ያገለግል ነበር። ንጉሥ ሕዝቅያስ ለሕይወቱ ያሰጋው የነበረው እባጭ የዳነለት የበለስ ጥፍጥፍ ተደርጎለት ነው።a ይሁን እንጂ ለሕዝቅያስ መዳን ዋነኛው ምክንያት መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ነበር።—2 ነገሥት 20:4-7
በጥንቱ ዘመን በመላው የሜዲትራንያን አካባቢ የደረቀ በለስ በጣም ተወዳጅ ነበር። ሮማዊው መሪ ካቶ በካርቴጅ ላይ ሦስተኛው የፑትኒክ ጦርነት እንዲከፈት የሮማን ምክር ቤት ለማሳመን በእጁ በለስ ይዞ እያወዛወዘ ንግግር አቅርቧል። ሮም ከፍተኛ ጥራት ያለው የደረቀ በለስ የምታገኘው በትንሹ እስያ ከምትገኘው ከካሪያ ነበር። በዚህም ምክንያት የደረቀ በለስ በላቲንኛ ካሪካ የሚል ስያሜ ሊያገኝ ችሏል። የዛሬዋ ቱርክ የምትገኝበት ይህ አካባቢ አሁንም ከፍተኛ ጥራት ያለው የደረቀ በለስ በማምረት ይታወቃል።
እስራኤል ውስጥ ገበሬዎች ብዙውን ጊዜ በወይን እርሻቸው ውስጥ የበለስ ዛፍ የሚተክሉ ሲሆን ፍሬ የማያፈሩ ዛፎችን የመቁረጥ ልማድ ነበራቸው። ፍሬ የማያፈራ ዛፍ ያላቸውን ውስን ለም መሬት እንዲይዝባቸው አይፈልጉም። ኢየሱስ ፍሬ ስለማያፈራ የበለስ ዛፍ በተናገረው ምሳሌ ላይ ገበሬው ለወይን አትክልት ሠራተኛው “ከዚህች በለስ ፍሬ ልፈልግ ሦስት ዓመት እየመጣሁ ምንም አላገኘሁም፤ ቍረጣት፤ ስለ ምን ደግሞ መሬቱን ታጐሳቍላለች?” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 13:6, 7) ኢየሱስ በምድር ላይ በነበረበት ወቅት የፍራፍሬ ዛፎች ግብር ይከፈልባቸው ስለነበር ምርት የማይሰጥ ዛፍ አላስፈላጊ ለሆነ ወጪ ይዳርግ ነበር።
በለስ እስራኤላውያን ትልቅ ግምት የሚሰጡት ምግባቸው ነበር። በመሆኑም ምናልባት በይሖዋ የቅጣት ፍርድ የተነሳ በቂ የበለስ ምርት ሳያገኙ ቢቀሩ ከባድ ቀውስ ያስከትልባቸዋል። (ሆሴዕ 2:12፤ አሞጽ 4:9) ነቢዩ ዕንባቆም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ምንም እንኳ በለስም ባታፈራ፣ በወይንም ሐረግ ፍሬ ባይገኝ፣ የወይራ ሥራ ቢጐድል፣ እርሾችም መብልን ባይሰጡ፣ . . . እኔ ግን በእግዚአብሔር ደስ ይለኛል፤ በመድኃኒቴ አምላክ ሐሤት አደርጋለሁ።”—ዕንባቆም 3:17, 18
እምነት የለሽ ለሆነው ብሔር ተምሳሌት
በለስ ወይም የበለስ ዛፍ በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በምሳሌያዊ ሁኔታ ተሠርቶበታል። ለምሳሌ ያህል ኤርምያስ ታማኝ አይሁዳውያን ግዞተኞችን ከመከር በፊት ደርሶ በእሸትነት የሚበላ መልካም በለስ ከያዘ ቅርጫት ጋር አወዳድሯቸዋል። በሌላ በኩል ታማኝ ያልሆኑ ግዞተኞችን ከመበላሸቱ የተነሳ ለመብልነት ከማይሆን በለስ ጋር አመሳስሏቸዋል።—ኤርምያስ 24:2, 5, 8, 10
ኢየሱስ ፍሬ ስለማያፈራ በለስ በተናገረው ምሳሌ ውስጥ ይሖዋ ለአይሁድ ብሔር ያሳየውን ትዕግሥት ገልጿል። ከላይ እንደተጠቀሰው በወይን እርሻው ውስጥ የበለስ ዛፍ ስላለው አንድ ሰው ተናግሮ ነበር። ዛፉ ለሦስት ዓመታት ፍሬ ሳያፈራ በመቅረቱ የእርሻው ባለቤት ዛፉን ለማስቆረጥ አሰበ። የወይኑ ቦታ ሠራተኛ ግን እንዲህ አለ:- “ጌታ ሆይ፣ ዙሪያዋን እስክኰተኵትላትና ፋንድያ እስካፈስላት ድረስ በዚች ዓመት ደግሞ ተዋት። ወደ ፊትም ብታፈራ፣ ደኅና ነው፤ ያለዚያ ግን ትቈርጣታለህ።”—ሉቃስ 13:8, 9
ኢየሱስ ምሳሌውን በተናገረበት ወቅት ከአይሁድ ብሔር መካከል በእርሱ የሚያምኑ ሰዎች ለማግኘት ለሦስት ዓመታት ያህል ሰብኮ ነበር። በበለስ ዛፍ የተመሰለው የአይሁድ ብሔር ፍሬ እንዲያፈራ ምሳሌያዊ “ፍግ” አደረገለት፤ ማለትም አገልግሎቱን በስፋት አጧጧፈ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ከመሞቱ ከአንድ ሳምንት ቀደም ብሎ ብሔሩ መሢሑን ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆኑ በግልጽ ታየ።—ማቴዎስ 23:37, 38
ኢየሱስ በሌላ ጊዜም ብሔሩ የነበረበትን መጥፎ መንፈሳዊ ሁኔታ በምሳሌ ለማስረዳት የበለስን ዛፍ ተጠቅሟል። ከመሞቱ ከአራት ቀናት በፊት ከቢታንያ ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዝ እጅብ ያለ ቅጠል ያላት ነገር ግን ምንም ፍሬ ያላፈራች የበለስ ዛፍ ተመለከተ። ከመከር በፊት የሚደርሰው ፍሬ ከቅጠሉ እኩል አንዳንዴም ከቅጠሉ ቀድሞ የሚወጣ በመሆኑ ዛፏ ፍሬ አለማፍራቷ ምንም ተስፋ እንደሌላት የሚያመለክት ነበር።—ማርቆስ 11:13, 14b
የአይሁድ ብሔር ልክ ፍሬ እንደማያፈራው በለስ ከላይ ሲታይ ጥሩ ገጽታ ነበረው። ሆኖም አምላካዊ ፍሬዎችን ማፍራት የተሳነው ከመሆኑም በላይ የአምላክን ልጅ አልቀበልም ብሏል። ኢየሱስ ፍሬ አልባውን የበለስ ዛፍ የረገመው ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ በማግሥቱ ዛፉ መድረቁን ተመልክተዋል። የዛፉ መድረቅ አምላክ አይሁዳውያንን የተመረጡ ሕዝቦቹ አድርጎ መመልከቱን እንደሚያቆም የሚያመለክት ነበር።—ማርቆስ 11:20, 21
“ከበለስ ተማሩ”
ኢየሱስ ዳግም ስለሚመጣበት ጊዜ ጠቃሚ ትምህርት ለማስጨበጥ በለስን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። እንዲህ አለ:- “ምሳሌውንም ከበለስ ተማሩ፤ ጫፍዋ ሲለሰልስ ቅጠልዋም ሲያቈጠቊጥ፣ ያን ጊዜ በጋ እንደ ቀረበ ታውቃላችሁ፤ እንዲሁ እናንተ ደግሞ ይህን ሁሉ ስታዩ በደጅ እንደ ቀረበ እወቁ።” (ማቴዎስ 24:32, 33) የበለስ ዛፍ ያሉት ፈካ ያሉ አረንጓዴ ቅጠሎች ጎልተው የሚታዩና የበጋው ወቅት መቃረቡን የሚጠቁሙ ናቸው። በተመሳሳይም ኢየሱስ በማቴዎስ ምዕራፍ 24, በማርቆስ ምዕራፍ 13 እና በሉቃስ ምዕራፍ 21 ላይ የተናገራቸው ትንቢቶች በአሁኑ ወቅት በሰማይ ንጉሣዊ ሥልጣኑን መያዙን የሚያሳዩ ግልጽ ማስረጃዎች ናቸው።—ሉቃስ 21:29-31
የምንኖረው በታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ እንደመሆኑ መጠን ከበለስ ዛፍ መማር እንደምንፈልግ አያጠራጥርም። እንዲህ በማድረግ በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን የምንኖር ከሆነ “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና ሰው እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም” የሚለው ታላቅ ተስፋ ፍጻሜውን ሲያገኝ መመልከት እንችላለን።—ሚክያስ 4:4
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ መካከለኛውን ምሥራቅ የጎበኙ ኤች ቢ ትሪስትራም የተባሉ አንድ የሥነ ተፈጥሮ ተመራማሪ የአካባቢው ሰዎች እባጭን ለማከም አሁንም የበለስ ፍሬ እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል።
b ይህ የሆነው በቤተ ፋጌ አቅራቢያ ነበር። ቤተ ፋጌ ማለት “በለስ ከመከር በፊት የሚያፈራበት መንደር” ማለት ነው። ይህ ስያሜ አካባቢው ከመከር በፊት በሚደርስ የበለስ ምርት የታወቀ እንደነበር ይጠቁማል።