የእውነትን አምላክ መምሰል
“እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ።”—ኤፌሶን 5:1 አ.መ.ት
1. አንዳንዶች ስለ እውነት ምን አመለካከት አላቸው? ይህ አመለካከታቸው የተሳሳተ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
“እውነት ምንድር ነው?” (ዮሐንስ 18:38) የዛሬ 2,000 ዓመት ገደማ ጴንጤናዊው ጲላጦስ ያነሳው ይህ የምጸት ጥያቄ እውነት ተጨባጭ አይደለም የሚል አንድምታ አለው። ዛሬም ተመሳሳይ ሐሳብ ያላቸው ብዙ ሰዎች አሉ። የእውነት ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል ሊባል ይችላል። እውነት እንደየግለሰቡ አመለካከት ይለያያል፣ እውነት አንጻራዊ ነው ወይም እውነትን ጊዜ ይሽረዋል ሲባል ሰምተህ ይሆናል። እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ የተሳሳተ ነው። ሰዎች ምርምር የሚያደርጉበትና ትምህርት የሚማሩበት ዋነኛው ዓላማ ስለምንኖርበት ዓለም ሐቁን ወይም እውነቱን ለማወቅ ነው። እውነት እንደየሰዉ የሚለያይ የግል አመለካከት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ ነፍስ ሟች ናት ወይስ ዘላለማዊ? ሰይጣን የሚባል አካል አለ ወይስ የለም? ሕይወት ዓላማ አለው ወይስ የለውም? የሚሉት ጥያቄዎች ሊኖራቸው የሚችለው ትክክለኛ መልስ አንድ ብቻ ነው። አንደኛው እውነት ከሆነ ሌላኛው ሐሰት ይሆናል እንጂ ሁለቱም በአንድ ጊዜ እውነት ሊሆኑ አይችሉም።
2. ይሖዋ የእውነት አምላክ የሆነው እንዴት ነው? ቀጥሎ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
2 ከዚህ በፊት ባየነው ርዕስ ውስጥ ይሖዋ የእውነት አምላክ መሆኑን ተመልክተናል። ስለ እያንዳንዱ ነገር እውነቱን ያውቃል። አታላይ ከሆነው ባላጋራው ከሰይጣን ዲያብሎስ ፍጹም ተቃራኒ በሆነ መልኩ ምንጊዜም እውነተኛ ነው። ከዚህም በላይ ምንም ሳይደብቅ እውነትን ለሌሎች ይገልጣል። ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “እንደ ተወደዱ ልጆች እግዚአብሔርን ምሰሉ” በማለት አጥብቆ አሳስቧቸዋል። (ኤፌሶን 5:1 አ.መ.ት) የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን እውነትን በአንደበታችንም ሆነ በአኗኗራችን በማንጸባረቅ እርሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? የእውነትን መንገድ የሚከተሉ ሰዎች የይሖዋን ሞገስ እንደሚያገኙ ምን ማረጋገጫ አለን? እስቲ እነዚህን ጥያቄዎች እንመርምር።
3, 4. ሐዋርያው ጳውሎስና ሐዋርያው ጴጥሮስ ‘የመጨረሻውን ዘመን’ በተመለከተ ምን ብለዋል?
3 የምንኖረው ሃይማኖታዊ ውሸት በተስፋፋበት ዘመን ውስጥ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት በተናገረው ትንቢት መሠረት በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ብዙ ሰዎች የአምልኮት መልክ አላቸው፣ ኃይሉን ግን ክደዋል። አንዳንዶቹ ‘አእምሯቸው ስለጠፋባቸው’ እውነትን ይቃወማሉ። በተጨማሪም “ክፉዎች ሰዎችና አታላዮች፣ እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ ይሄዳሉ።” እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ምንም ያህል ቢማሩ ፈጽሞ “እውነትን ወደ ማወቅ ሊደርሱ” አይችሉም።—2 ጢሞቴዎስ 3:1, 5-8, 13
4 ሐዋርያው ጴጥሮስም በመንፈስ አነሳሽነት ስለ መጨረሻው ዘመን ጽፎ ነበር። በትንቢት እንደተናገረው ሰዎች እውነትን አንቀበልም ማለታቸው ሳያንስ በአምላክ ቃልና በውስጡ ያለውን እውነት በሚናገሩ ሰዎች ላይ ያፌዛሉ። “እንደ ራሳቸው ምኞት” የሚመላለሱት እነዚህ ዘባቾች በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም በውኃ እንደጠፋና ይህም ወደፊት ለሚመጣው የፍርድ ቀን ምሳሌ እንደሆነ መቀበል አይፈልጉም። በምኞት ላይ የተመረኮዘው ይህ አመለካከታቸው አምላክ ኃጢአተኞችን በሚያጠፋበት ጊዜ ትልቅ አደጋ ያስከትልባቸዋል።—2 ጴጥሮስ 3:3-7
የይሖዋ አገልጋዮች እውነትን ያውቃሉ
5. ነቢዩ ዳንኤል ‘ስለ ፍጻሜው ዘመን’ ምን ትንቢት ተናግሯል? ይህስ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
5 ነቢዩ ዳንኤል ‘ስለ ፍጻሜው ዘመን’ በተናገረው ትንቢት ላይ የአምላክ ሕዝቦች ስለ እውነት ያላቸው እውቀት ከሌሎች በተለየ እየጨመረ እንደሚሄድ ተናግሮ ነበር። እንዲህ ብሏል:- “ብዙ ሰዎች ይመረምራሉ፣ እውቀትም ይበዛል።” (ዳንኤል 12:4) የይሖዋ ሕዝቦች በታላቁ አታላይ ግራ አይጋቡም፤ መንፈሳዊ እይታቸውንም እንዲጋርድባቸው አይፈቅዱም። መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር በመመርመር ትክክለኛ እውቀት አግኝተዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የእውቀት ብርሃን ፈንጥቆላቸው ነበር። “መጻሕፍትን ያስተውሉ ዘንድ አእምሮአቸውን ከፈተላቸው።” (ሉቃስ 24:45) በዘመናችንም ይሖዋ ተመሳሳይ ነገር አድርጓል። በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እርሱ የሚያውቀውን ይህን እውነት እንዲገነዘቡ አድርጓል።
6. የአምላክ ሕዝቦች በዛሬው ጊዜ የተረዷቸው አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?
6 የአምላክ ሕዝቦች በመሆናችን በራሳችን ልናውቃቸው የማንችላቸውን ብዙ ነገሮች አውቀናል። የዓለም ጠቢባንን ለብዙ መቶ ዘመናት ሲያስጨንቁ ለነበሩት ጥያቄዎች መልስ አግኝተናል። ለምሳሌ ያህል ሰዎች ለምን መከራ እንደሚደርስባቸው፣ ለምን እንደሚሞቱና ዓለም አቀፋዊ ሰላምና አንድነት በሰዎች ጥረት ማምጣት ያልተቻለው ለምን እንደሆነ አውቀናል። ስለወደፊቱ ጊዜ ግልጽ የሆነ ግንዛቤ አለን፤ ይኸውም የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣ፣ ምድር ገነት እንደምትሆንና የሰው ልጆች በፍጽምና ለዘላለም እንደሚኖሩ እናውቃለን። የአጽናፈ ዓለሙ የበላይ ጌታ የሆነውን ይሖዋን አውቀናል። ግሩም ስለሆኑት ባሕርያቱ እንዲሁም የእርሱን በረከት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ተምረናል። እውነትን ማወቃችን ሐሰት የሆነውን ለይተን እንድናውቅ አስችሎናል። እውነትን ተግባራዊ ማድረጋችን ከንቱ የሆኑ ግቦችን ከመከተል ይጠብቀናል፣ ሕይወትን በደንብ እንድናጣጥም ያስችለናል እንዲሁም ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ ይፈነጥቅልናል።
7. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እነማን ሊረዱት ይችላሉ? እነማንስ መረዳት አይችሉም?
7 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት ችለሃል? ከሆነ በእጅጉ ተባርከሃል ለማለት ይቻላል። አንድ ደራሲ መጽሐፍ ሲጽፍ የተወሰኑ አንባቢያንን በአእምሮው ይዞ ነው። አንዳንድ መጽሐፎች የሚዘጋጁት ለምሑራን ሲሆን ሌሎች ደግሞ ለልጆች ነው። ልዩ በሆኑ የሥራ መስኮች ለተሰማሩ ሰዎችም የሚዘጋጁ ጽሑፎች አሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉም ሰው በቀላሉ ሊያገኘው የሚችለው መጽሐፍ ቢሆንም የተወሰኑ ዓይነት ሰዎች ብቻ እንዲረዱትና ጥቅም እንዲያገኙበት ተብሎ የተዘጋጀ ነው። ይሖዋ ያስጻፈው በምድር ላይ የሚኖሩ ትሑትና ቅን ሰዎች እንዲረዱት አድርጎ ነው። እንዲህ ያሉት ሰዎች የትምህርት ደረጃቸው፣ ባሕላቸው፣ የኑሮ ደረጃቸው ወይም ዘራቸው ምንም ይሁን ምን የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ መረዳት ይችላሉ። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) በሌላ በኩል ግን ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ የሌላቸው ሰዎች የቱንም ያህል አስተዋይ ወይም የተማሩ ቢሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መረዳት አይችሉም። ትዕቢተኛና ኩሩ የሆኑ ሰዎች በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት አይረዱትም። (ማቴዎስ 13:11-15፤ ሉቃስ 10:21፤ ሥራ 13:48) እንዲህ ዓይነቱን መጽሐፍ ሊያስጽፍ የሚችለው አምላክ ብቻ ነው።
የይሖዋ አገልጋዮች እውነተኞች ናቸው
8. ኢየሱስ ራሱ እውነት ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
8 እንደ ይሖዋ ሁሉ ታማኝ ምሥክሮቹም እውነተኞች ናቸው። የይሖዋ ዋነኛ ምሥክር የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ባስተማራቸው ነገሮች፣ በአኗኗሩ አልፎ ተርፎም በሞቱ ለእውነት የቆመ መሆኑን አሳይቷል። ይሖዋ የተናገራቸው ነገሮችና የገባቸው ተስፋዎች እውነት መሆናቸውን አሳይቷል። በዚህም ምክንያት እርሱ ራሱ ‘እኔ እውነት ነኝ’ ማለቱ ተገቢ ነው።—ዮሐንስ 14:6፤ ራእይ 3:14፤ 19:10
9. ቅዱሳን ጽሑፎች እውነትን ስለመናገር ምን ይላሉ?
9 ኢየሱስ ‘ጸጋንና እውነትን የተሞላ’ ከመሆኑም በላይ “በአፉም ተንኰል አልተገኘበትም።” (ዮሐንስ 1:14፤ ኢሳይያስ 53:9) እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ረገድ እውነተኞች በመሆን የኢየሱስን አርአያ ይከተላሉ። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “እርስ በርሳችን ብልቶች ሆነናልና እያንዳንዳችሁ ከባልንጀሮቻችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት መክሯቸዋል። (ኤፌሶን 4:25) ነቢዩ ዘካርያስም ከብዙ ዓመታት በፊት “እያንዳንዳችሁ ከባልንጀራችሁ ጋር እውነትን ተነጋገሩ” በማለት ጽፎ ነበር። (ዘካርያስ 8:16) ክርስቲያኖች አምላክን ማስደሰት ስለሚፈልጉ ምንጊዜም እውነትን ይናገራሉ። ይሖዋ እውነተኛ አምላክ ሲሆን ውሸትን መናገር የሚያስከትለውን ጉዳት ያውቃል። ስለዚህ አገልጋዮቹ ምንጊዜም እውነትን እንዲናገሩ መጠበቁ የተገባ ነው።
10. ሰዎች ለምን ይዋሻሉ? መዋሸት ምን ጉዳት አለው?
10 ብዙ ሰዎች መዋሸት ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል ብለው ያስባሉ። ሰዎች ከቅጣት ለማምለጥ፣ አንድ ዓይነት ጥቅም ለማግኘት ወይም የሌሎችን ከበሬታ ለማትረፍ ብለው ይዋሻሉ። ሆኖም ውሸት የመጥፎ ምግባር መገለጫ ነው። ከዚህም በላይ ውሸታም ሰው የአምላክን ሞገስ አያገኝም። (ራእይ 21:8, 27፤ 22:15) በእውነተኝነት የምንታወቅ ከሆነ ሌሎች የምንናገረውን የሚቀበሉ ከመሆኑም በላይ እምነት ይጥሉብናል። ይሁን እንጂ አንድ ውሸት እንኳን ቢገኝብን ከዚያ በኋላ የምንናገረውን ነገር በሙሉ ይጠራጠራሉ። አንድ የአፍሪካውያን ምሳሌ “አንዲት ውሸት አንድ ሺህ እውነቶችን ዋጋ ታሳጣለች” ይላል። ሌላ ምሳሌ ደግሞ “ቀጣፊ ሰው እውነት ቢናገር እንኳ አይታመንም” ይላል።
11. እውነተኝነት እውነትን መናገር ማለት ብቻ አይደለም ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው?
11 እውነተኝነት ሲባል እውነትን መናገር ማለት ብቻ አይደለም። በአኗኗራችን የሚንጸባረቅ ሲሆን ማንነታችንንም ያሳያል። እውነትን ለሌሎች የምንገልጸው በአንደበታችን ብቻ ሳይሆን በአኗኗራችንም ጭምር ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጠይቆ ነበር:- “አንተ ሌላውን የምታስተምር ራስህን አታስተምርምን? አትስረቅ ብለህ የምትሰብክ ትሰርቃለህን? አታመንዝር የምትል ታመነዝራለህን?” (ሮሜ 2:21, 22) ለሌሎች እውነትን ለማሳወቅ የምንፈልግ ከሆነ በአኗኗራችን እውነተኛ መሆናችንን ማሳየት አለብን። በእውነተኝነትና በሐቀኝነት ያተረፍነው ጥሩ ስም ሰዎች የምናስተምረውን እውነት እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸው ይችላል።
12, 13. አንዲት ወጣት እውነተኝነትን በሚመለከት ምን ብላ ጽፋለች? ይህን የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ እንድትከተል ያነሳሳትስ ምንድን ነው?
12 በይሖዋ አገልጋዮች መካከል የሚገኙ ወጣቶችም እውነተኛ መሆን ያለውን አስፈላጊነት ተገንዝበዋል። ጄኒ የተባለች አንዲት ወጣት የ13 ዓመት ልጅ በነበረችበት ወቅት ለትምህርት ቤት ባዘጋጀችው አንድ መጣጥፍ ላይ እንዲህ ብላ ነበር:- “ሐቀኝነት ትልቅ ቦታ የምሰጠው ባሕርይ ነው። የሚያሳዝነው ግን በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሐቀኝነት ይጎድላቸዋል። በሕይወት እስካለሁ ድረስ ምንጊዜም ሐቀኛ ለመሆን ለራሴ ቃል ገብቻለሁ። እውነትን መናገር ለእኔም ሆነ ለጓደኞቼ ጥቅም የማያስገኝ በሚሆንበት ጊዜም እንኳን እውነትን ከመናገር ወደ ኋላ አልልም። በጓደኝነት የምቀርበው እውነተኛና ሐቀኛ የሆኑ ሰዎችን ብቻ ነው።”
13 የጄኒ መምህር ይህን መጣጥፍ በሚመለከት አስተያየቷን ስትሰጥ እንዲህ ብላለች:- “ገና በዚህ ዕድሜሽ እንዲህ ዓይነቱን ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም መያዝሽ የሚያስገርም ነው። መንፈሰ ጠንካራ ወጣት ስለሆንሽ ይህን አቋምሽን ይዘሽ እንደምትቀጥይ ምንም አልጠራጠርም።” ይህች ተማሪ እንዲህ ያለ ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም እንዲኖራት የረዳት ምንድን ነው? ጄኒ በጽሑፏ መግቢያ ላይ “ሕይወቷን የምትመራበትን የሥነ ምግባር አቋም ያገኘችው” ከሃይማኖቷ እንደሆነ ገልጻለች። ይህ ከሆነ ሰባት ዓመታት አልፈዋል። አሁን የይሖዋ ምሥክር የሆነችው ጄኒ አስተማሪዋ እንደተናገረችው የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ በመከተል ላይ ትገኛለች።
የይሖዋ አገልጋዮች እውነትን ይገልጣሉ
14. የአምላክ አገልጋዮች ከሌሎች በተለየ ከእውነት ጎን የመቆም ኃላፊነት የተሰጣቸው ለምንድን ነው?
14 እርግጥ ነው፣ እውነተኛና ሐቀኛ ለመሆን የሚጥሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ አይደሉም። ይሁን እንጂ የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከሌሎች በተለየ መልኩ ከእውነት ጎን የመቆም ትልቅ ኃላፊነት አለብን። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በአደራ የተሰጠን ሲሆን ይህ እውነት የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ነው። በመሆኑም ይህን እውቀት ለሌሎች የማካፈል ግዴታ አለብን። ኢየሱስ “ብዙም ከተሰጠው ሰው ሁሉ ከእርሱ ብዙ ይፈለግበታል” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 12:48) ውድ የሆነው የአምላክ እውቀት ከተሰጣቸው ‘ብዙ የሚፈለግ’ መሆኑ እምብዛም አያስደንቅም።
15. የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈልህ ምን አስገኝቶልሃል?
15 የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈል ደስታ ያስገኛል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እኛም ምሥራቹን ይኸውም አስደሳች የሆነውን የተስፋ መልእክት ‘እረኛ እንደሌላቸው በጎች ለተጨነቁና ለተጣሉ’ እንዲሁም ‘በአጋንንት ትምህርት’ ለታወሩና ግራ ለተጋቡ ሰዎች እንሰብካለን። (ማቴዎስ 9:36፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:1) ሐዋርያው ዮሐንስ “ልጆቼ በእውነት እንዲሄዱ ከመስማት ይልቅ የሚበልጥ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል። (3 ዮሐንስ 4) ዮሐንስ “ልጆቼ” ብሎ የጠራቸው እውነትን የሰበከላቸውን ሰዎች ሳይሆን አይቀርም። የእነርሱ ታማኝነት ከፍተኛ ደስታ አስገኝቶለታል። እኛም ሰዎች ለአምላክ ቃል አድናቆት አድሮባቸው ምላሽ ሲሰጡ ስንመለከት እንደሰታለን።
16, 17. (ሀ) እውነትን የሚቀበሉት ሁሉም ሰዎች ያልሆኑት ለምንድን ነው? (ለ) የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች መስበክህ ደስታ የሚያስገኝልህ እንዴት ነው?
16 የሚያሳዝነው ግን እውነትን የሚቀበሉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። ኢየሱስ ብዙዎች እየተቃወሙትም ስለ አምላክ የሚናገረውን እውነት ለሌሎች ሰብኳል። ይቃወሙት ለነበሩት አይሁድ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ስለ ምን አታምኑኝም? ከእግዚአብሔር የሆነ የእግዚአብሔርን ቃል ይሰማል፤ እናንተ ከእግዚአብሔር አይደላችሁምና ስለዚህ አትሰሙም።”—ዮሐንስ 8:46, 47
17 እኛም እንደ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ የሚናገረውን ውድ እውነት ለሰዎች ከመናገር ወደኋላ ማለት የለብንም። ሁሉም ሰው የምንናገረውን ይቀበላል ብለን አንጠብቅም፤ ምክንያቱም ኢየሱስን የተቀበሉት ሁሉም ሰዎች አልነበሩም። የሆነ ሆኖ ትክክል የሆነውን እያደረግን እንዳለ ስለምናውቅ ደስታ እናገኛለን። ይሖዋ በፍቅራዊ ደግነቱ ተገፋፍቶ ሰዎች ሁሉ እውነትን እንዲያውቁ ይፈልጋል። ክርስቲያኖች እውነትን ስለያዙ በመንፈሳዊ ጨለማ በተዋጠው በዚህ ዓለም ውስጥ ብርሃን አብሪዎች ይሆናሉ። የእውነትን ብርሃን በአንደበታችንና በድርጊታችን በማንጸባረቅ ሌሎች በሰማይ የሚኖረውን አባታችንን እንዲያከብሩ ልንረዳቸው እንችላለን። (ማቴዎስ 5:14, 16) ሰይጣን እውነታውን አጣምሞ የሚያቀርብልንን ውሸት እንደማንቀበልና ያልተበረዘውን የአምላክ ቃል ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ለሰዎች እናሳውቃለን። እኛ የምናውቀውና ለሌሎች የምንናገረው እውነት ለሚቀበሉት ሰዎች ትክክለኛ ነጻነት ያጎናጽፋቸዋል።—ዮሐንስ 8:32
ምንጊዜም እውነተኞች ሁኑ
18. ኢየሱስ ናትናኤልን ያደነቀው ለምን ነበር? አድናቆቱን የገለጸውስ እንዴት ነው?
18 ኢየሱስ እውነትን ይወድና ይናገር ነበር። በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት እውነተኛ የሆኑ ሰዎችን ያደንቅ ነበር። ኢየሱስ ናትናኤልን በሚመለከት “ተንኰል የሌለበት በእውነት የእስራኤል ሰው እነሆ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 1:48) ከጊዜ በኋላ በርተሎሜዎስ ተብሎ የተጠራውን ናትናኤልን ከ12ቱ ሐዋርያት አንዱ እንዲሆን መርጦታል። (ማቴዎስ 10:2-4) እንዴት ያለ መታደል ነው!
19-21. ማየት ተስኖት የነበረው ሰው በድፍረት እውነቱን በመናገሩ የተባረከው እንዴት ነው?
19 በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የኢየሱስን አድናቆት ስላተረፈ አንድ ሐቀኛ ሰው የሚተርክ አንድ ሙሉ ምዕራፍ ይገኛል። የዚህ ሰው ስም ባይታወቅም ከልጅነቱ አንስቶ ማየት የተሳነው ለማኝ እንደነበር እናውቃለን። ኢየሱስ ለዚህ ሰው የማየት ችሎታውን ሲመልስለት ሕዝቡ በጣም ተደነቀ። የዚህ ተአምራዊ ፈውስ ወሬ የእውነት ጠላቶች ወደነበሩትና በኢየሱስ የሚያምኑትን ሰዎች ከምኩራብ ለማባረር ወደተማማሉት ፈሪሳውያን ጆሮ ደረሰ። የተፈወሰው ሰው ወላጆች ይህን የፈሪሳውያኑን ሴራ ስለሚያውቁ ፈርተው ልጃቸውን ማን እንደፈወሰውም ሆነ እንዴት እንደተፈወሰ እንደማያውቁ ሽምጥጥ አድርገው ካዱ።—ዮሐንስ 9:1-23
20 ፈሪሳውያኑ የተፈወሰውን ሰው በድጋሚ አስጠሩት። እርሱ ግን ምንም ሳይፈራ እውነቱን ነገራቸው። የፈወሰው ኢየሱስ እንደሆነና እንዴት እንደፈወሰው አስረዳቸው። እነዚህ ከፍተኛ ተሰሚነት ያላቸውና የተማሩ ሰዎች ኢየሱስ ከአምላክ የተላከ መሆኑን አለማመናቸው ስላስገረመው “ይህ ሰው ከእግዚአብሔር ባይሆን ምንም ሊያደርግ ባልቻለም ነበር” በማለት በድፍረት ሞገታቸው። ፈሪሳውያኑ የሚመልሱለት ሲያጡ ተዳፍሯል በሚል ሰበብ ከምኩራብ አባረሩት።—ዮሐንስ 9:24-34
21 ኢየሱስ ይህን ሲሰማ ሰውየውን ፈልጎ አገኘው። ከዚያም የነበረውን እምነት ይበልጥ አጠናከረለት። መሲሕ መሆኑንም በግልጽ ነገረው። ይህ ሰው እውነቱን በመናገሩ ምንኛ ተባርኳል! በእርግጥም እውነትን የሚናገሩ ሰዎች የአምላክን ሞገስ ያገኛሉ።—ዮሐንስ 9:35-37
22. ምንጊዜም እውነተኞች ሆነን ለመገኘት ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
22 ምንጊዜም እውነትን የመናገር ልማድ ሁላችንም በቁም ነገር ልናስብበት የሚገባ ጉዳይ ነው። ከሰዎችና ከአምላክ ጋር ጥሩ ዝምድና ለመመሥረትና ይህንን ዝምድና ጠብቆ ለማቆየት የሚያስችል ወሳኝ ባሕርይ ነው። እውነተኛ መሆን ማለት ግልጽ፣ ሐቀኛ፣ የሚቀረብና እምነት የሚጣልበት መሆን ማለት ሲሆን የይሖዋን ሞገስም ያስገኛል። (መዝሙር 15:1, 2) ሐሰተኛ መሆን ደግሞ አታላይ፣ እምነት የማይጣልበትና ውሸታም ማለት ሲሆን ይሖዋ የሚጠላው ባሕርይ ነው። (ምሳሌ 6:16-19) ስለዚህ ምንጊዜም እውነተኞች ሆነን ለመገኘት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። አዎን፣ የእውነትን አምላክ ለመምሰል እውነትን ማወቅ፣ እውነትን መናገርና በአኗኗራችን እውነትን ማንጸባረቅ ይኖርብናል።
ለክለሳ ያህል
• እውነትን በማወቃችን አመስጋኞች መሆን የሚገባን ለምንድን ነው?
• እውነተኛ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
• የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማካፈል ምን ጥቅሞች አሉት?
• ምንጊዜም እውነተኛ ለመሆን ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች በአደራ የተሰጣቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሌሎች በቅንዓት ይናገራሉ
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የፈወሰው ማየት የተሳነው ሰው እውነቱን በመናገሩ በእጅጉ ተባርኳል