ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ እርዷቸው
“አግሪጳም ጳውሎስን ‘አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው! ’ አለው።”—የሐዋርያት ሥራ 26:28 የ1980 ትርጉም
1, 2. ሐዋርያው ጳውሎስ በአገረ ገዢው ፊስጦስና በዳግማዊ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ፊት የቀረበው ለምን ነበር?
በ58 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ዳግማዊ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ እና እህቱ በርኒቄ ሮማዊውን አገረ ገዢ ጶርቅዮስ ፊስጦስን ለመጠየቅ ወደ ቂሣርያ መጥተው ነበር። በዚያም አገረ ገዢው ባቀረበላቸው ግብዣ “በብዙ ግርማ . . . ከሻለቆችና ከከተማው ታላላቆች ጋር ወደ ፍርድ ቤት ገቡ።” ከዚያም ፊስጦስ ሐዋርያው ጳውሎስ በፊታቸው እንዲቀርብ አዘዘ። ይሁንና የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ የነበረው ይህ ሰው በአገረ ገዢው በፊስጦስ የፍርድ ወንበር ፊት የቀረበው ለምን ነበር?—የሐዋርያት ሥራ 25:13-23
2 የዚህን ጥያቄ መልስ የምናገኘው ፊስጦስ ለእንግዶቹ ከተናገረው ነገር ነው። እንዲህ አለ:- “አግሪጳ ንጉሥ ሆይ እናንተም ከእኛ ጋር ያላችሁ ሰዎች ሁሉ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በሕይወት ይኖር ዘንድ እንዳይገባው እየጮኹ የአይሁድ ሕዝብ ሁሉ በኢየሩሳሌም በዚህም ስለ እርሱ የለመኑኝን ይህን ሰው ታዩታላችሁ። እኔ ግን ሞት የሚገባውን ነገር እንዳላደረገ አስተዋልሁ፣ እርሱም ወደ አውግስጦስ ይግባኝ ስላለ እሰደው ዘንድ ቈረጥሁ። ስለ እርሱም ወደ ጌታዬ የምጽፈው እርግጥ ነገር የለኝም፤ ስለዚህ ከተመረመረ በኋላ የምጽፈውን ነገር አገኝ ዘንድ በፊታችሁ ይልቁንም በፊትህ፣ ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ አመጣሁት፤ እስረኛ ሲላክ የተከሰሰበትን ምክንያት ደግሞ አለማመልከት ሞኝነት መስሎኛልና።”—የሐዋርያት ሥራ 25:24-27
3. በኢየሩሳሌም የሚኖሩት የሃይማኖት መሪዎች ጳውሎስን የከሰሱት ለምን ነበር?
3 የፊስጦስ ቃላት ጳውሎስ በመንግሥት ላይ ሕዝባዊ ዓመጽ ያነሳሳል የሚል የሞት ፍርድ የሚያስከትል የሐሰት ክስ እንደተመሠረተበት ያመለክታሉ። (የሐዋርያት ሥራ 25:11) ይሁን እንጂ ጳውሎስ የተከሰሰው ባልሠራው ወንጀል ነበር። ይህን ክስ ያቀረቡበት በኢየሩሳሌም የሚኖሩት ቅናት ያበገናቸው ሃይማኖታዊ መሪዎች ነበሩ። ጳውሎስ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን የሚያከናውነውን ሥራ ይቃወሙ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሌሎች የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች እንዲሆኑ መርዳቱ በጣም አበሳጭቷቸው ነበር። ጳውሎስ ከኢየሩሳሌም በታጠቁ ወታደሮች ታጅቦ የወደብ ከተማ ወደሆነችው ወደ ቂሣርያ የተወሰደ ሲሆን እዚያም ወደ ቄሳር ይግባኝ በማለቱ ወደ ሮም የሚወሰድበትን ጊዜ ይጠባበቅ ነበር።
4. ንጉሥ አግሪጳ ምን የሚያስገርም ነገር ተናገረ?
4 ጳውሎስ የሮማ ግዛት ከፍተኛ ባለ ሥልጣንን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በተገኙበት በአገረ ገዢው ሸንጎ ፊት ቀረበ። ንጉሥ አግሪጳ ወደ ጳውሎስ ዘወር ብሎ “ስለ ራስህ ትናገር ዘንድ ተፈቅዶልሃል” አለው። ጳውሎስ የመከላከያ ሐሳቡን ሲያቀርብ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ተፈጸመ። ንጉሥ አግሪጳ በጳውሎስ ንግግር ልቡ ተነካ። በዚህም ምክንያት “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው” አለው።—የሐዋርያት ሥራ 26:1-28 የ1980 ትርጉም
5. ጳውሎስ ለአግሪጳ የተናገራቸው ቃላት ውጤት ያስገኙት ለምን ነበር?
5 እስቲ አስበው! ጳውሎስ ባቀረበው ግሩም የመከላከያ ሐሳብ ምክንያት የአምላክ ቃል ያለው ልብን የመንካት ኃይል በአንድ ንጉሥ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ችሏል። (ዕብራውያን 4:12) ጳውሎስ ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ውጤታማ የሆነው ለምን ነበር? እኛስ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራችን ከጳውሎስ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጳውሎስ ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ ጠለቅ ብለን ስንመረምር ሁለት ዋና ዋና ነጥቦችን እናገኛለን:- (1) ጳውሎስ አሳማኝ አቀራረብ ነበረው። (2) አንድ የእጅ ባለሙያ አንድን መሣሪያ ውጤታማ በሆነ መንገድ እንደሚጠቀምበት ሁሉ ጳውሎስም የነበረውን የአምላክ ቃል እውቀት በሚገባ ተጠቅሞበታል።
የማሳመን ችሎታ ይኑራችሁ
6, 7. (ሀ) “ማሳመን” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ አገባቡ መሠረት ምን ትርጉም አለው? (ለ) ሰዎች አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲቀበሉ በመርዳት ረገድ ማሳመን ምን ሚና ይጫወታል?
6 በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ማሳመን ተብለው የተተረጎሙት የተለያዩ የግሪክኛ ቃላት ከጳውሎስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ ተሠርቶባቸዋል። የማሳመን ችሎታ ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራችን ጋር ምን ግንኙነት አለው?
7 በቫይን የተዘጋጀው ኤክስፖዚተሪ ዲክሽነሪ ኦቭ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ እንደሚለው የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች በተጻፉበት የመጀመሪያ ቋንቋ “ማሳመን” ማለት “አጥጋቢ ምክንያት በማቅረብ ወይም ከሥነ ምግባር አኳያ በማስረዳት ማግባባት” ወይም “አስተሳሰብን ማስለወጥ” ነው። ማሳመን የሚለውን ግስ መሠረታዊ ትርጉም መመርመራችን ተጨማሪ ግንዛቤ ያስጨብጠናል። ቃሉ አመኔታ ማሳደር የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ስለሆነም አንድ ሰው አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲቀበል አሳመንከው ማለት በምትናገረው ነገር ላይ አመኔታ እንዲያሳድርና የትምህርቱን እውነተኝነት አምኖ እንዲቀበል አደረግኸው ማለት ነው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አንድ ሰው በመጽሐፍ ቅዱስ እንዲያምንና እንዲመራበት ከተፈለገ በውስጡ የያዘውን ሐሳብ መንገሩ ብቻውን በቂ አይደለም። የምታነጋግረው ሰው ልጅህም ይሁን ዘመድህ፣ ጎረቤትህ፣ የሥራ ባልደረባህ ወይም የትምህርት ቤት ጓደኛህ የምትናገረው ነገር እውነት መሆኑን ልታሳምነው ይገባሃል።—2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15
8. ሰዎች አንድን መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት እንዲቀበሉ ማሳመን ምን ማድረግን ይጨምራል?
8 ከአምላክ ቃል የምትናገረው መልእክት እውነት መሆኑን አንድን ሰው ማሳመን የምትችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ አእምሮን በማመራመርና አሳማኝ ማስረጃ በማቅረብ አድማጮቹ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዲያደርጉ ለመርዳት ልባዊ ጥረት ያደርግ ነበር።a አንድ ነገር እውነት መሆኑን መናገር ብቻ ሳይሆን ሐሳብህን የሚደግፍ አጥጋቢ ማስረጃ ማቅረብ ይኖርብሃል። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የምትናገረው ሐሳብ በራስህ አመለካከት ላይ ሳይሆን ሙሉ በሙሉ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። እንዲሁም የምትናገራቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ሐሳቦች የሚደግፉ ተጨማሪ ማስረጃዎች አቅርብ። (ምሳሌ 16:23) ለምሳሌ ያህል ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ በደስታ እንደሚኖሩ እየተናገርክ ከሆነ ይህንን ነጥብ ለመደገፍ እንደ ሉቃስ 23:43 እና ኢሳይያስ 65:21-25 ያሉ ጥቅሶችን በማስረጃነት መጥቀስ ትችላለህ። ይህን ሐሳብህን የሚደግፍ ተጨማሪ ማስረጃ ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው? አድማጭህ ከሚያውቃቸው ነገሮች በመነሳት ምሳሌዎች መጠቀም ትችላለህ። ጀምበር ስትጠልቅ የሚፈጠረውን ውብ ትዕይንት መመልከት፣ ደስ የሚል መዓዛ ያለው አበባ ማሽተት፣ ጣፋጭ ፍሬ መብላት ወይም አንዲት ወፍ ጫጩቶቿን ስትመግብ ማየት የሚፈጥረውን በቀላሉና በነጻ የሚገኝ ደስታ ልታስታውሰው ትችላለህ። እነዚህ አስደሳች ሁኔታዎች ፈጣሪያችን በምድር ላይ በደስታ እንድንኖር እንደሚፈልግ የሚያሳዩ ማስረጃዎች እንደሆኑ እንዲገነዘብ አድርግ።—መክብብ 3:11, 12
9. በስብከቱ ሥራችን ምክንያታዊ መሆናችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
9 ሰዎች አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እንዲቀበሉ ለማሳመን ጥረት በምታደርግበት ጊዜ ግለት የታከለበት አነጋገርህ የሌሎችን አመለካከት በጭፍን የምትቃወም እንዳያስመስልህ ተጠንቀቅ። ይህ አድማጭህ አእምሮውንና ልቡን ከፍቶ እንዳያዳምጥህ ሊያደርገው ይችላል። የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፍ እንዲህ በማለት ያስጠነቅቃል:- “ሰዎች ከልብ የሚያምኑበት ነገር ሐሰት እንደሆነ ፊት ለፊት የምንናገር ከሆነ ብዙ የጥቅስ ማስረጃ ብናቀርብ እንኳ በአብዛኛው መቀበል ሊከብዳቸው ይችላል። ለምሳሌ ያህል ብዙ ሰዎች የሚያከብሯቸውን በዓላት አመጣጣቸው አረማዊ እንደሆነ በመናገር ማውገዝ ብቻ ሰዎቹ ለበዓላቱ ያላቸውን አመለካከት ላይለውጠው ይችላል። ብዙውን ጊዜ ጥሩ ውጤት የሚኖረው ምክንያታዊ ሆኖ መቅረብ ነው።” ምክንያታዊ ለመሆን ጥረት ማድረግ የሚኖርብን ለምንድን ነው? መጽሐፉ እንዲህ ይላል:- “አሳማኝ በሆነ መንገድ መናገር ግን ሰዎችን ለውይይት ይጋብዛል፣ ቆም ብለው ስለ ጉዳዩ እንዲያስቡ ያደርጋል እንዲሁም ወደፊት ለመወያየት ፈቃደኛ እንዲሆኑ በር ይከፍታል። የምንነግራቸውን ነገር እንዲቀበሉ ሊያደርጋቸውም ይችላል።”—ቆላስይስ 4:6
አሳማኝ ነጥብ በማንሳት ልብን መንካት
10. ጳውሎስ በንጉሥ አግሪጳ ፊት ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ የከፈተው በምን ነበር?
10 አሁን ደግሞ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 26 ላይ የሚገኘውን ጳውሎስ ያቀረበውን የመከላከያ ሐሳብ እንመልከት። ንግግሩን እንዴት እንደከፈተ ልብ በል። ንጉሥ አግሪጳ ከእህቱ ከበርኒቄ ጋር አሳፋሪ የሆነ ግንኙነት የነበረው ቢሆንም ጳውሎስ በንግግሩ መግቢያ ላይ የንጉሡን በጎ ጎን አንስቶ አመሰገነው። እንዲህ አለው:- “ንጉሥ አግሪጳ ሆይ፣ የአይሁድን ሥርዓት ክርክርንም ሁሉ አጥብቀህ አውቀሃልና በአይሁድ በተከሰስሁበት ነገር ሁሉ ዛሬ በፊትህ ስለምመልስ ራሴን እጅግ እንደ ተመረቀ አድርጌ እቈጥረዋለሁ፤ ስለዚህ በትዕግሥት ትሰማኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።”—የሐዋርያት ሥራ 26:2, 3
11. ጳውሎስ ለአግሪጳ አክብሮት እንዳለው በአነጋገሩ ያሳየው እንዴት ነበር? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል?
11 ጳውሎስ አግሪጳን ‘ንጉሥ ሆይ’ ብሎ በማዕረግ ስሙ በመጥራት ለሥልጣኑ ያለውን አክብሮት እንዳሳየ አስተውለሃል? ይህ አገላለጽ አክብሮቱን የሚያንጸባርቅ ሲሆን ጳውሎስ በቃላት አመራረጡም ለአግሪጳ ክብር ሰጥቷል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ጳውሎስ፣ አግሪጳ የአይሁዳውያን ተገዢዎቹን የተወሳሰቡ ወጎችና ሕጎች ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን የጠቀሰ ሲሆን አስተዋይ በሆነ ገዢ ፊት የመከላከያ ሐሳቡን የማቅረብ መብት በማግኘቱ ደስተኛ እንደሆነም ገልጿል። ክርስቲያኑ ጳውሎስ ክርስቲያን ባልነበረው አግሪጳ ላይ የበላይነት ተሰምቶት እንደነበር የሚያሳይ ምንም ነገር አልተናገረም። (ፊልጵስዩስ 2:3) ከዚህ ይልቅ ንጉሡ በትዕግሥት እንዲያዳምጠው ተማጽኖታል። በዚህ መንገድ አግሪጳም ሆነ በቦታው የተገኙት ሌሎች ሰዎች ቀጥሎ የሚናገረውን ሐሳብ እንዲቀበሉ ለማድረግ ሁኔታውን አመቻችቷል። የመከላከያ ሐሳቡን ለማቅረብ የሚያስችለውን የጋራ መሠረት እየጣለ ነበር።
12. በመንግሥቱ ስብከት ሥራ ስንሳተፍ የሰዎችን ልብ መማረክ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት እንዳደረገው ሁሉ እኛም የመንግሥቱን መልእክት ስንናገር ከመግቢያው አንስቶ እስከ መደምደሚያው ድረስ የሰዎችን ልብ የሚማርክ እንዲሆን ጥረት እናድርግ። ምሥራቹን ለምንሰብክላቸው ሰዎች ልባዊ አክብሮት በማሳየትና ለባሕላቸውና ለአስተዳደጋቸው እንዲሁም ለአስተሳሰባቸው ትኩረት በመስጠት ልባቸውን መማረክ እንችላለን።—1 ቆሮንቶስ 9:20-23
በአምላክ ቃል በጥሩ ሁኔታ ተጠቀሙ
13. እንደ ጳውሎስ ሁሉ አንተም አድማጮችህን ለተግባር ማነሳሳት የምትችለው እንዴት ነው?
13 ጳውሎስ አድማጮቹ ምሥራቹን ሰምተው ለተግባር እንዲነሳሱ ይፈልግ ነበር። (1 ተሰሎንቄ 1:5-7) በዚህም ምክንያት ለተግባር የሚያነሳሳቸውን ምሳሌያዊ ልባቸውን ለመማረክ ጥረት ያደርግ ነበር። በአግሪጳ ፊት ባቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ላይ ሙሴና ሌሎች ነቢያት የጠቀሷቸውን ነገሮች በማንሳት እንዴት ‘በአምላክ ቃል በትክክል እንደተጠቀመ’ ልብ በል።—2 ጢሞቴዎስ 2:15
14. ጳውሎስ በአግሪጳ ፊት የመከላከያ ሐሳቡን ሲያቀርብ የማሳመን ችሎታውን የተጠቀመው እንዴት ነው?
14 ጳውሎስ፣ አግሪጳ አይሁዳዊ ነኝ ይል እንደነበር ያውቃል። ስለዚህ አግሪጳ ስለ አይሁድ እምነት የነበረውን ግንዛቤ በመጠቀም “ነቢያትና ሙሴ ይሆን ዘንድ ያለውን” ማለትም የመሲሑን ሞትና ትንሣኤ አስመልክተው “ከተናገሩት በቀር አንድ ስንኳ የተናገርሁት የለም” በማለት አስረዳ። (የሐዋርያት ሥራ 26:22, 23) ከዚያም በቀጥታ አግሪጳን “ነቢያትን ታምናለህን?” በማለት ጠየቀው። አግሪጳ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ። በነቢያት አላምንም ቢል የአይሁድ እምነት ተከታይ መሆኑ ጥያቄ ውስጥ ይገባል። በጳውሎስ ሐሳብ ከተስማማ ደግሞ እሱን እንደደገፈ ሊቆጠርበትና ክርስቲያን ሊባል ነው። ጳውሎስ ‘እንድታምናቸው አውቃለሁ’ በማለት የራሱን ጥያቄ መለሰ። (የሐዋርያት ሥራ 26:27) አግሪጳ ምን ብሎ ይሆን? “አንተ እኮ በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ክርስቲያን ልታደርገኝ ነው!” አለው። (የሐዋርያት ሥራ 26:28 የ1980 ትርጉም ) ምንም እንኳን አግሪጳ ክርስትናን ባይቀበልም ጳውሎስ የተናገረው ነገር በተወሰነ መጠን ልቡን እንደነካው አያጠራጥርም።—ዕብራውያን 4:12
15. ጳውሎስ በተሰሎንቄ ጉባኤ ለመመሥረት የቻለው እንዴት ነበር?
15 የጳውሎስ አቀራረብ ምሥራቹን መስበክንና ማሳመንን አጣምሮ የያዘ መሆኑን አስተውለሃል? ይህ አቀራረቡ ‘በአምላክ ቃል በትክክል እንዲጠቀም’ ስላስቻለው ከሚያነጋግራቸው ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ አድማጮች ብቻ ሳይሆኑ አማኞችም ለመሆን በቅተዋል። ጳውሎስ በተሰሎንቄ በሚገኝ ምኩራብ ውስጥ ከአይሁዳውያንና ፈሪሃ አምላክ ከነበራቸው አሕዛብ ጋር በተነጋገረበት ወቅት የተፈጸመው ሁኔታ ለዚህ ምሳሌ ይሆነናል። በሐዋርያት ሥራ 17:2-4 [አ.መ.ት ] ላይ ያለው ዘገባ እንዲህ ይላል:- ‘ጳውሎስም እንደ ልማዱ ወደ ምኩራብ ገባ፤ ሦስት ሰንበትም ከቅዱሳት መጻሕፍት እየጠቀሰ ከእነርሱ ጋር ተነጋገረ። ክርስቶስ መከራን መቀበል እንዳለበትና ከሙታንም መነሣት እንደሚገባው እያስረዳ አረጋገጠላቸው። ከአይሁድም አንዳንዶቹ የሰሙትን በመቀበል ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር ተባበሩ።’ ጳውሎስ አሳማኝ አቀራረብ ነበረው። ኢየሱስ ከረጅም ጊዜ በፊት እንደሚመጣ የተነገረለት መሲሕ መሆኑን ያስረዳቸው፣ ያብራራላቸውና ከቅዱሳን ጽሑፎች ማስረጃ ይጠቅስላቸው ነበር። ውጤቱስ ምን ሆነ? በተሰሎንቄ አንድ ጉባኤ ሊመሠረት ችሏል።
16. ስለ አምላክ መንግሥት በማወጁ ሥራ የበለጠ ደስታ ማግኘት የምትችለው እንዴት ነው?
16 አንተስ የአምላክን ቃል ለሰዎች በምታስረዳበት ጊዜ የማሳመን ችሎታህን ማዳበር ትችላለህ? ከሆነ ስለ አምላክ መንግሥት በመስበኩና በማስተማሩ ሥራህ ውጤታማ ልትሆንና ደስታ ልታገኝ ትችላለህ። በስብከቱ ሥራ ላይ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ስለመጠቀም የተሰጠውን ማበረታቻ ተግባራዊ ያደረጉ አስፋፊዎች እንዲህ ያለ ውጤት አግኝተዋል።
17. በአገልግሎታችን ላይ መጽሐፍ ቅዱስን መጠቀም ያለውን ጥቅም ለማሳየት በግል ያገኘኸውን ተሞክሮ ወይም ከተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ሐሳብ ፍሬ ነገሩን ተናገር።
17 ለምሳሌ ያህል በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት የሚያገለግል አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አሁን አሁን ብዙ ወንድሞችና እህቶች ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ መጽሐፍ ቅዱስ በእጃቸው ይይዛሉ። እንዲህ ማድረጋቸው ከሚያነጋግሯቸው ሰዎች ለአብዛኞቹ ጥቅስ እንዲያነብቡ አስችሏቸዋል። ይህ ደግሞ የምናነጋግራቸው ሰዎችም ሆኑ አስፋፊዎች አገልግሎታችን የተመሠረተው በመጽሔቶችና በመጻሕፍት ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መሆኑን እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል።” እርግጥ ነው፣ በአገልግሎት ላይ መጽሐፍ ቅዱስን በእጅ መያዛችን የአካባቢውን ልማድ ጨምሮ በሌሎች የተለያዩ ሁኔታዎች ላይ የተመካ ነው። ያም ሆነ ይህ ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ለማሳመን በምናደርገው ጥረት የአምላክን ቃል በሚገባ የምንጠቀም በመሆናችን ለመታወቅ እንፈልጋለን።
አገልግሎታችንን በሚመለከት የአምላክ አመለካከት ይኑራችሁ
18, 19. (ሀ) አምላክ አገልግሎታችንን የሚመለከተው እንዴት ነው? የእርሱን ዓይነት አመለካከት ማዳበር የሚኖርብንስ ለምንድን ነው? (ለ) ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ስኬታማ እንድንሆን ምን ሊረዳን ይችላል? (በገጽ 16 ላይ የሚገኘውን “ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻልበት መንገድ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
18 የምናነጋግራቸውን ሰዎች ልብ መንካት የምንችልበት ሌላው መንገድ አገልግሎታችንን በአምላክ ዓይን ማየትና የትዕግሥትን ባሕርይ ማዳበር ነው። የአምላክ ፈቃድ ሰዎች ሁሉ “እውነቱን ወደ ማወቅ” እንዲደርሱ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4) የእኛስ ፍላጎት ይኸው አይደለ? በተጨማሪም ይሖዋ ታጋሽ ነው፤ ይህ ባሕርዩም ብዙዎች ንስሐ እንዲገቡ አጋጣሚ ከፍቶላቸዋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) በመሆኑም የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ የሆነ ሰው ስናገኝ ፍላጎቱን ይበልጥ ለማሳደግ ደግመን ደጋግመን ሄደን ማነጋገራችን አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። የእውነት ዘር ሲያድግ ለመመልከት ጊዜና ትዕግሥት ይጠይቃል። (1 ቆሮንቶስ 3:6) ከዚህ ርዕስ ጋር ተያይዞ የቀረበው “ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻልበት መንገድ” የሚለው ሣጥን የሰዎችን ፍላጎት እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል የሚገልጹ ሐሳቦችን ይዟል። የሰዎች ሕይወት ማለትም ችግሮቻቸውና ያሉበት ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት የሚለዋወጥ መሆኑን አትዘንጋ። ሰዎቹን በቤታቸው ለማግኘት በተደጋጋሚ መሄድ ይጠይቅብን ይሆናል፤ ቢሆንም ቢደከምለት የሚያስቆጭ አይደለም። የአምላክን የመዳን መልእክት የመስማት አጋጣሚ እንዲያገኙ እንፈልጋለን። ስለሆነም ሌሎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ለመርዳት በምታደርገው ጥረት የማሳመን ችሎታህን ለማሻሻል እንዲረዳህ ወደ ይሖዋ አምላክ ጸልይ።
19 ስለ አምላክ መንግሥት ለመስማት ፍላጎት ያለው ሰው ካገኘን በኋላስ እንደ ክርስቲያንነታችን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል? የሚቀጥለው ርዕስ በዚህ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ማሳመንን በሚመለከት ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም ከተባለው መጽሐፍ ጥናት 48 እና 49ን ተመልከት።
ታስታውሳለህ?
• ጳውሎስ በንጉሥ አግሪጳ ፊት ያቀረበው የመከላከያ ሐሳብ ውጤታማ የሆነው ለምን ነበር?
• የምንናገረው መልእክት የሰዎችን ልብ የሚነካ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• የአምላክን ቃል ውጤታማ በሆነ መንገድ ተጠቅመን የሰዎችን ልብ ለመንካት እንድንችል የሚረዳን ምንድን ነው?
• አገልግሎታችንን በሚመለከት የአምላክ ዓይነት አመለካከት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግ ረገድ ስኬታማ መሆን የሚቻልበት መንገድ
• ለሰዎች በግል ልባዊ አሳቢነት አሳይ።
• የምትወያዩበትን አንድ ማራኪ የመጽሐፍ ቅዱስ ርዕስ ምረጥ።
• ለቀጣዩ ጉብኝት መሠረት ጣል።
• ተሰናብተህ ከሄድክ በኋላም ስለ ግለሰቡ አስብ።
• ፍላጎት ያሳዩትን ተከታትሎ ለመርዳት ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ተመልሰህ ሂድ።
• ዓላማህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር መሆኑን አትዘንጋ።
• ይሖዋ የግለሰቡን ፍላጎት እንዲያሳድገው ጸልይ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ በአገረ ገዢው ፊስጦስና በንጉሥ አግሪጳ ፊት በቀረበ ጊዜ የማሳመን ችሎታውን ተጠቅሟል