‘የቅኖች ድንኳን ይስፋፋል’
የአርማጌዶን ጦርነት ፈንድቶ የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት ወደ ፍጻሜ በሚያመጣበት ጊዜ “የክፉዎች ቤት ይፈርሳል።” ‘የቅኖች ድንኳንስ’ ምን ይሆናል? መልሱ ግልጽ ነው፣ የቅኖች ድንኳን አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ “ይስፋፋል።”—ምሳሌ 14:11
ይሁን እንጂ ‘ክፉዎች ከምድሪቱ የሚወገዱበትና ታማኝነት የጎደላቸው ከእርሷ የሚነቀሉበት’ ጊዜ እስኪመጣ ድረስ ነቀፋ የሌለባቸው ሰዎች ከእነሱ ጋር አብረው ለመኖር ይገደዳሉ። (ምሳሌ 2:21, 22) ቅኖች እንደዚህ ባለው ሁኔታ ተመችቷቸው ሊኖሩ ይችላሉ? ጥበብ ንግግራችንንና ተግባራችንን እንዲመራልን በመፍቀድ አሁንም እንኳን በተወሰነ መጠን አስደሳችና የተረጋጋ ሕይወት ማግኘት እንደምንችል የምሳሌ መጽሐፍ ምዕራፍ 14 ከቁጥር 1-11 ያሳያል።
ቤት በጥበብ ሲገነባ
የጥንቷ እስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን አንዲት ሚስት ለቤተሰቧ ደኅንነት ስለምታበረክተው ድርሻ ሐሳብ ሲሰጥ “ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች፤ ተላላ ሴት ግን በገዛ እጇ ታፈርሰዋለች” ብሏል። (ምሳሌ 14:1) ጥበበኛ ሴት ቤቷን የምትሠራው እንዴት ነው? ጠቢብ ሴት አምላክ ያወጣውን የራስነት ዝግጅት ታከብራለች። (1 ቆሮንቶስ 11:3) በሰይጣን ዓለም ተንሰራፍቶ የሚገኘውን በራስ ፈቃድ የመመራት መንፈስ አትከተልም። (ኤፌሶን 2:2) ለባሏ የምትገዛና ስለ እሱ መልካም ነገር የምትናገር በመሆኗ ሌሎች ለእሱ ያላቸው አክብሮት እንዲጨምር ታደርጋለች። ጥበበኛ ሴት ለልጆቿ መንፈሳዊና ሌሎች ጠቃሚ ትምህርቶችን በመስጠት ረገድ የበኩሏን ድርሻ ታበረክታለች። ለቤተሰቧ ደኅንነት ተግታ በመሥራት የቤተሰቡ አባላት ተደስተውና ተመችቷቸው እንዲኖሩ ታደርጋለች። የቤት አያያዟ አስተዋይና ቆጣቢ መሆኗን ያሳያል። ጥበበኛ ሴት ለቤተሰቧ ደኅንነትና ሰላም አስተዋጽኦ ታደርጋለች።
ተላላ ወይም ሰነፍ ሴት አምላክ ላወጣው የራስነት ዝግጅት አክብሮት የላትም። ስለ ባሏ አክፋፍታ ከመናገር ወደኋላ አትልም። ጠንቃቃ ስላልሆነች ቤተሰቡ በብዙ ድካም ያገኘውን ገንዘብ ታባክናለች። ጊዜም አባካኝ ናት። በመሆኑም ቤቱ በጥሩ ሁኔታ አይያዝም፤ እንዲሁም ልጆቹ አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ችግር ይደርስባቸዋል። አዎን፣ ሰነፍ ሴት ቤቷን ታፈርሳለች።
ይሁንና አንድን ሰው ጠቢብ ወይም ተላላ የሚያስብለው ምንድን ነው? ምሳሌ 14:2 እንዲህ ይላል:- “አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው እግዚአብሔርን ይፈራል፤ መንገዱ ጠማማ የሆነ ግን ይንቀዋል።” ቅን የሆነ ሰው እውነተኛውን አምላክ ይፈራል፤ ደግሞም “እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ ነው።” (መዝሙር 111:10) እውነተኛ ጥበብ ያለው ሰው ‘እውነተኛውን አምላክ የመፍራትና ትእዛዙን የመጠበቅ’ ግዴታ እንዳለበት ያውቃል። (መክብብ 12:13) በሌላ በኩል ደግሞ ሰነፍ ሰው አምላክ ስለ ቅንነት ካወጣው የአቋም ደረጃ ጋር የማይስማማ አካሄድ ይከተላል። አካሄዱ ጠማማ ነው። እንዲህ ዓይነቱ ሰው ለአምላክ ካለው ንቀት የተነሳ በልቡ “እግዚአብሔር የለም” ይላል።—መዝሙር 14:1
በጥበብ የሚመሩ ከንፈሮች
ይሖዋን በሚፈራና በሚንቅ ሰው መካከል ምን የአነጋገር ልዩነት ይታያል? ንጉሥ ሰሎሞን “የተላላ ሰው ንግግር ለጀርባው በትር ታስከትልበታለች፤ የጥበበኛ ከንፈር ግን ትጠብቃቸዋለች” ብሏል። (ምሳሌ 14:3) ሰነፍ ሰው ላይኛይቱ ጥበብ ስለሌለችው ሰላማዊም ሆነ ምክንያታዊ አይደለም። እርምጃውን የሚመራበት ጥበብ ምድራዊ፣ እንስሳዊና አጋንንታዊ ነው። የሚናገራቸው ቃላት ጠብ የሚጭሩና የዕብሪተኝነት መንፈስ የሚንጸባረቅባቸው ናቸው። የአፉ ትዕቢት በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ብዙ ችግር ያስከትላል።—ያዕቆብ 3:13-18
የጠቢብ ሰው ከንፈር ከጉዳት ስለሚጠብቀው እርካታና ደስታ ያመጣለታል። እንዴት? ቅዱስ ጽሑፉ “ግድ የለሽ ቃል እንደ ሰይፍ ይወጋል፤ የጠቢብ አንደበት ግን ፈውስን ያመጣል” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 12:18) የጠቢብ ሰው ቃላት የሚጎዱ ወይም የሚያቆስሉ አይደሉም። መልስ ከመስጠቱ በፊት በልቡ ያመዛዝናል። (ምሳሌ 15:28) በሚገባ የታሰበበት ንግግሩ ፈዋሽ ስለሆነ የተከዙትን ነፍሳት ያበረታታል፤ በግፍ የተደቆሱትን ደግሞ ያጽናናል። ከንፈሮቹ ሌሎችን ከማበሳጨት ይልቅ ሰላምና ጸጥታ እንዲሰፍን ያደርጋሉ።
ሥራቸውን በጥበብ የሚያከናውኑ ሰዎች
ሰሎሞን በመቀጠል አንድን ሥራ መጀመር ያለውን ጥቅምና ጉዳት ማመዛዘን አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ የሚያመራምር ምሳሌ ተናግሯል። እንዲህ ይላል:- “በሬዎች በሌሉበት ገንዳው ባዶ ይሆናል፤ በበሬ ጒልበት ግን ብዙ ምርት ይገኛል።”—ምሳሌ 14:4
አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ምሳሌ ሲፈታ እንደሚከተለው ብሏል:- “ገንዳው ባዶ መሆኑ የሚቀለቡ ከብቶች እንደሌሉ የሚያሳይ ስለሆነ አንድ ሰው የእንስሳቱን ንጽሕና መጠበቅና እነሱን መንከባከብ ከሚያስከትለው ችግር ነፃ ይሆናል፤ ወጪም ይቀንሳል ማለት ነው። ይሁን እንጂ በቁጥር 4ለ ላይ እንደተገለጸው በሬዎች ከሌሉ ምርት ስለሚቀንስ አንድ ሰው በሬዎች የሌሉት መሆኑ የሚያስገኝለት ‘ጥቅም’ የይምሰል ነው።” ስለዚህ ገበሬው በጥበብ ምርጫ ማድረግ አለበት።
ሥራ ለመለወጥ ስናስብ፣ መኖሪያ ቤት ስንመርጥ፣ መኪና ስንገዛ ወይም የቤት እንስሳ ማሳደግ ስንፈልግና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮች ስናደርግ ይህ መሠረታዊ ሥርዓት አይጠቅመንም? ጥበበኛ ሰው ሊሠራው ያቀደው ነገር ሊደከምለትና ገንዘብ ሊፈስበት የሚገባ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ጥቅምና ጉዳቱን ያመዛዝናል።
ጥበበኛ የሆነ ምሥክር
ሰሎሞን በመቀጠል “ታማኝ ምስክር አይዋሽም፤ ሐሰተኛ ምስክር ግን ውሸትን ይዘከዝካል” ብሏል። (ምሳሌ 14:5) ሐሰተኛ ምሥክር የሚናገረው ውሸት ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ምንም ጥርጥር የለውም። ኢይዝራኤላዊው ናቡቴ በድንጋይ ተወግሮ የተገደለው ሁለት የሐሰት ምሥክሮች በሐሰት ስለመሰከሩበት ነበር። (1 ነገሥት 21:7-13) ደግሞስ በኢየሱስ ላይ መስክረው ያስገደሉት የሐሰት ምሥክሮች አልነበሩም? (ማቴዎስ 26:59-61) የሐሰት ምሥክሮች በእስጢፋኖስም ላይ የመሰከሩበት ሲሆን እርሱም በእምነቱ ምክንያት የተገደለው የመጀመሪያው የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ለመሆን በቅቷል።—የሐዋርያት ሥራ 6:10, 11
የሚዋሽ ሰው ለጊዜው ሳይጋለጥ ያመልጥ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ወደፊት የሚገጥመውን ተመልከት። ይሖዋ “በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር” እንደሚጠላ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 6:16-19) እንዲህ ያለው ሰው ዕጣ ፈንታ ከነፍሰ ገዳዮች፣ ከአመንዝሮችና ከጣዖት አምላኪዎች ጋር በእሳትና በዲን በሚቃጠል የእሳት ባሕር ውስጥ መጣል ይኸውም ሁለተኛው ሞት ይሆናል።—ራእይ 21:8
ታማኝ ምሥክር የምሥክርነት ቃሉን በሚሰጥበት ጊዜ አይዋሽም። የምሥክርነት ቃሉ ውሸት የተቀላቀለበት አይደለም። ይሁን እንጂ የይሖዋ ሕዝቦችን በሆነ መልኩ መጉዳት ለሚፈልጉ ሰዎች የተሟላ መረጃ የመስጠት ግዴታ አለበት ማለት አይደለም። የእምነት አባቶች የሆኑት አብርሃምና ይስሐቅ ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች አንዳንድ ነገሮችን ደብቀዋል። (ዘፍጥረት 12:10-19፤ 20:1-18፤ 26:1-10) የኢያሪኮዋ ረዓብ የንጉሡን መልእክተኞች በተሳሳተ አቅጣጫ መርታቸዋለች። (ኢያሱ 2:1-7) ኢየሱስ ክርስቶስም የተሟላ መረጃ መስጠት አላስፈላጊ ችግር እንደሚያስከትል በተሰማው ጊዜ እንደዚያ ከማድረግ ተቆጥቧል። (ዮሐንስ 7:1-10) ኢየሱስ “የተቀደሰ ነገር ለውሾች አትስጡ” ብሏል። ለምን? “ተመልሰውም ነክሰው እንዳይቦጫጭቋችሁ” በማለት ምክንያቱን ገልጿል።—ማቴዎስ 7:6
‘ዕውቀት በቀላሉ ስትገኝ’
ጥበብን ሁሉም ሰው ማግኘት ይችላል? ምሳሌ 14:6 እንዲህ ይላል:- “ፌዘኛ ጥበብን ይሻል፤ ሆኖም አያገኛትም፤ ዕውቀት ግን ለአስተዋዮች በቀላሉ ትገኛለች።” ፌዘኛ ወይም አሿፊ ሰው ጥበብን ይፈልግ ይሆናል፤ ሆኖም እውነተኛ ጥበብ ትሰወርበታለች። ፌዘኛ ሰው በአምላካዊ ነገሮች ላይ በትዕቢት ስለሚያሾፍ ጥበብ ለማግኘት የሚያስፈልገውን ትልቁን ነገር ይኸውም ስለ እውነተኛው አምላክ ትክክለኛ እውቀት ሳያገኝ ይቀራል። ኩራትና ዕብሪት የተጠናወተው መሆኑ ስለ አምላክ እንዳይማርና ጥበብን እንዳያገኝ ያግደዋል። (ምሳሌ 11:2) ለመሆኑ ጥበብ ለማግኘት የሚፈልገው ለምንድን ነው? የምሳሌ መጽሐፍ የዚህን ጥያቄ መልስ አይነግረንም። ይሁንና ፌዘኛው ሰው ጥበብ የሚፈልገው ምናልባት በሌሎች ዘንድ ጠቢብ መስሎ ለመታየት ይሆናል።
ለአስተዋይ ሰው “ዕውቀት . . . በቀላሉ ትገኛለች።” ማስተዋል “የአእምሮ የመቀበል፣ የመረዳት ችሎታ” እንዲሁም “የዝርዝር ጉዳዮችን አጠቃላይ ዝምድና የመገንዘብ ችሎታ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። የአንድን ጉዳይ የተለያዩ ክፍሎች ለየብቻ ከማየት ይልቅ አንድ ላይ በማያያዝ አጠቃላዩን ይዘት የማየት ችሎታ ነው። ይህ ምሳሌ የሚናገረው እንዲህ ዓይነት ችሎታ ያለው ሰው እውቀት በቀላሉ ማግኘት የሚችል መሆኑን ነው።
በዚህ ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተማርክበትን መንገድ በተመለከተ የራስህን ተሞክሮ መለስ ብለህ አስብ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት በጀመርክበት ጊዜ መጀመሪያ ከተማርካቸው ነገሮች መካከል ስለ አምላክ፣ ስለ ተስፋዎቹና ስለ ልጁ የሚገልጹት መሠረታዊ ትምህርቶች ይገኙበታል። መጀመሪያ ላይ እነዚህ ትምህርቶች እርስ በርሳቸው ምንም ዝምድና የሌላቸው ነገሮች እንደሆኑ ተሰምቶህ ነበር። በጥናትህ እየገፋህ ስትሄድ ግን እነዚህ የተነጣጠሉ ይመስሉ የነበሩ ትምህርቶች የተያያዙ እንደሆኑና ይሖዋ ለሰዎችና ለምድር ካለው አጠቃላይ ዓላማ ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ በግልጽ መገንዘብ ቻልክ። ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማርከው እውነት ትርጉም የሚሰጥና የተያያዘ ሆነልህ። ትምህርቶቹ እርስ በርሳቸውና ከአጠቃላዩ መልእክት ጋር እንዴት እንደሚዛመዱ ስለገባህ አሁን ተጨማሪ ሐሳቦችን መማርና ማስታወስ እየቀለለህ ሄደ።
ይሁን እንጂ ጠቢቡ ንጉሥ እውቀት ማን ጋር እንደማይገኝ አሳውቆናል። “ከተላላ ሰው ራቅ፣ ከከንፈሮቹ ዕውቀት አታገኝምና።” (ምሳሌ 14:7) ተላላ ሰው እውነተኛ እውቀት የለውም። እውቀትን የሚናገሩ ከንፈሮችም የሉትም። የተሰጠን ምክር እንዲህ ካለው ሰው መራቅና ወደ እርሱ አለመቅረብ ነው። “የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
ሰሎሞን ቀጥሎ “የአስተዋዮች ጥበብ መንገዳቸውን ልብ ማለት ነው፤ የተላሎች ሞኝነት ግን መታለል ነው” ብሏል። (ምሳሌ 14:8) ጠቢብ ሰው ስለሚያደርገው ነገር ያስባል። ያሉትን አማራጮች ሁሉ ከግምት በማስገባት እያንዳንዱ አማራጭ ሊያስከትልበት ስለሚችለው ውጤት በጥንቃቄ ያመዛዝናል። አካሄዱን በጥበብ ይመርጣል። ሰነፍ ሰውስ ምን ያደርጋል? የሚያደርገውን ነገር እንደሚያውቅና ከሁሉ የተሻለ ምርጫ እንዳደረገ በማመን የሞኝነት አካሄድ ይመርጣል። ስንፍናው ያታልለዋል።
በጥበብ ላይ የተመሠረተ ግንኙነት
በጥበብ የሚመራ ሰው ከሌሎች ሰዎች ጋር ሰላማዊ ዝምድና ይኖረዋል። የእስራኤል ንጉሥ “ተላሎች በሚያቀርቡት የበደል ካሳ ያፌዛሉ፤ በቅኖች መካከል ግን በጎ ፈቃድ ትገኛለች።” (ምሳሌ 14:9) ለሰነፍ ሰው የጥፋተኝነት ስሜት ወይም ጸጸት የሚያስቅ ነገር ነው። “ከትዕቢቱ የተነሳ ይቅርታ መጠየቅ ስለማይፈልግ” እና ሰላምን ስለማይሻ በቤቱም ሆነ በሌላ ቦታ ከሰዎች ጋር ጥሩ ዝምድና የለውም። (ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል) ቅን የሆነ ሰው የሌሎችን ጉድለት ችሎ ለማለፍ ፈቃደኛ ነው። እሱ ራሱ ሌሎችን ከበደለ ይቅርታ ለመጠየቅና ለመካስ ዝግጁ ነው። ሰላምን ስለሚከታተል ከሌሎች ጋር አስደሳችና ዘላቂ ዝምድና አለው።—ዕብራውያን 12:14
ሰሎሞን ቀጥሎ ከሌላ ሰው ጋር ባለን ግንኙነት ስለዚያ ሰው ያለንን ግንዛቤ ውስን የሚያደርግብንን ነገር ጠቁሟል። እንዲህ ይላል:- “እያንዳንዱ ልብ የራሱን መራራ ሐዘን ያውቃል፤ ደስታውንም ማንም ሊጋራው አይችልም።” (ምሳሌ 14:10) ውስጣዊ ስሜታችንን ማለትም ሐዘናችንንም ሆነ ደስታችንን ሁልጊዜ ለሌሎች መግለጽና በትክክል ምን እንደሚሰማን መንገር እንችላለን? ደግሞስ አንድ ሰው ሌላው ምን እንደሚሰማው ሁልጊዜ ሙሉ በሙሉ መረዳት ይችላል? ለሁለቱም ጥያቄዎች መልሱ አይቻልም የሚል ነው።
ለምሳሌ ያህል ራስን የማጥፋትን ሐሳብ እንውሰድ። ይህ ስሜት ያለው ሰው አብዛኛውን ጊዜ ስሜቱን ለአንድ የቤተሰቡ አባል ወይም ለጓደኛው በግልጽ አያሳውቅም። ሌሎችም አንድ ሰው እንደዚህ ዓይነት ስሜት እንዳለው የሚያሳዩ ምልክቶችን ሳይረዱ የሚቀሩባቸው ጊዜያት አሉ። እነዚህን ምልክቶች ለይተን ባለማወቃችንና የእርዳታ እርምጃ ሳንወስድ በመቅረታችን የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማን አይገባም። በተጨማሪም ስሜታዊ ድጋፍ ለማግኘት ችግራችንን የሚረዳልን ጓደኛችን ጋር መሄዱ የሚያጽናና ቢሆንም ሰዎች ሊሰጡ በሚችሉት ማጽናኛ ረገድ ውስን መሆናቸውን ይህ ምሳሌ ያስተምራል። አንዳንድ ችግሮችን በመጽናት ለማሳለፍ በይሖዋ ላይ ብቻ መመካት ሊኖርብን ይችላል።
“ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል”
የእስራኤል ንጉሥ “የክፉዎች ቤት ይፈርሳል፤ የቅኖች ድንኳን ግን ይስፋፋል” ብሏል። (ምሳሌ 14:11) ክፉ ሰው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሊበለጽግና ያማረ ቤት ሊኖረው ይችላል፤ እሱ ራሱ በሕይወት ከሌለ ግን ይህ ምን ይጠቅመዋል? (መዝሙር 37:10) በሌላ በኩል ደግሞ የቅኖች መኖሪያ ተራ ቤት ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ መዝሙር 112:3 “ሀብትና ብልጽግና በቤቱ ይሞላል” ይላል። እነዚህ ነገሮች ምንድን ናቸው?
ንግግራችንም ሆነ ድርጊታችን በጥበብ የሚመራ ከሆነ ከጥበብ ጋር አብሮ የሚመጣው “ሀብትና ክብር” ይኖረናል። (ምሳሌ 8:18) “ሀብትና ክብር” ከአምላክና ከሰዎች ጋር የሚኖረንን ሰላማዊ ዝምድና፣ የደኅንነትና የደስታ ስሜት እንዲሁም የተረጋጋ ሕይወትን ይጨምራል። አዎን፣ “የቅኖች ድንኳን” በአሁኑ ጊዜም እንኳን ሊስፋፋ ይችላል።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጠቢብ ሴት ቤቷን ትሠራለች
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“የጠቢብ አንደበት . . . ፈውስን ያመጣል”