“ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው”
ይሖዋን የሚያወድሱ ወጣቶች ይባረካሉ
“ሕይወት የምትለግሰኝን ማንኛውንም መልካም አጋጣሚ በሚገባ መጠቀም እፈልጋለሁ።” እንዲህ በማለት ምኞቱን የገለጸው በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ አንድ ወጣት ነው። ይሁንና አንድ ወጣት ሕይወት የምትለግሰውን መልካም አጋጣሚ በሚገባ ሊጠቀምበት የሚችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ለጥያቄው የማያሻማ መልስ ይሰጣል።—መክብብ 12:1
ይሖዋን ማወደስና ማገልገል ለትልልቅ ሰዎች ብቻ የተተወ ጉዳይ አይደለም። የሕልቃና እና የሐና ልጅ የሆነው ሳሙኤል በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ይሖዋን ማገልገል የጀመረው ገና ትንሽ ልጅ ሳለ ነበር። (1 ሳሙኤል 1:19, 20, 24፤ 2:11) በተመሳሳይም በዕድሜ ገና ለጋ የነበረችው እስራኤላዊቷ ልጃገረድ ንዕማን የተባለው ሶርያዊ የጦር አዛዥ ወደ ነቢዩ ኤልሳዕ ቢሄድ ከነበረበት የሥጋ ደዌ በሽታ እንደሚፈወስ በመናገር በይሖዋ ላይ የጸና እምነት እንዳላት አሳይታለች። (2 ነገሥት 5:2, 3) በመዝሙር 148:7, 12 ላይ ወጣት ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይሖዋን እንዲያወድሱ ታዘዋል።a ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ አባቱን ለማገልገል ጉጉት እንዳለው አሳይቷል። (ሉቃስ 2:41-49) በተመሳሳይም ከቅዱሳን ጽሑፎች ሥልጠና አግኝተው የነበሩ ልጆች ኢየሱስን ቤተ መቅደስ ውስጥ ባዩት ጊዜ “ሆሣዕና፤ ለዳዊት ልጅ” በማለት ጮኸዋል።—ማቴዎስ 21:15, 16
በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ማወደስ
በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ብዙ ወጣቶች በእምነታቸው ይኮራሉ እንዲሁም የሚያምኑባቸውን ነገሮች በትምህርት ቤትም ሆነ በሌላ ቦታ በድፍረት ይናገራሉ። እስቲ የሚከተሉትን ሁለት ምሳሌዎች እንመልከት።
በእንግሊዝ የምትኖር ስቴፋኒ የተባለች አንዲት የ18 ዓመት ወጣት የክፍሏ ተማሪዎች ጽንስ ማስወረድንና ሌሎች ሥነ ምግባር ነክ ጉዳዮችን በሚመለከት ውይይት በማድረግ ላይ ነበሩ። በዚህ ወቅት አስተማሪያቸው ጽንስ ማስወረድ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ ማንኛዋም ወጣት ጉዳዩን ለመቃወም የሚያስችል በቂ ምክንያት ሊኖራት እንደማይችል ተናገረ። በክፍል ውስጥ የነበሩት ሁሉ በሐሳቡ ሲስማሙ ስቴፋኒ ግን በዚህ ረገድ ያላትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ አመለካከት መናገር እንዳለባት ተሰማት። በነገሩ ላይ ያላትን ሐሳብ እንድትናገር አስተማሪው በጋበዛት ጊዜ ይህንን ለማድረግ ጥሩ አጋጣሚ አገኘች። በመጀመሪያ ላይ ትንሽ የፍርሃት ስሜት ቢሰማትም አጋጣሚውን በመጠቀም ስለ ጉዳዩ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተናገረች። ዘፀአት 21:22-24ን በቃሏ ከጠቀሰች በኋላ በማሕጸን ውስጥ ባለ ልጅ ላይ አደጋ ማድረስ የሚያስጠይቅ ከሆነ ሆነ ብሎ ጽንስ ማስወረድ ከአምላክ ፈቃድ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚጋጭ መሆኑን ተናገረች።
ቄስ የነበረው አስተማሪዋ ይህንን ጥቅስ በጭራሽ አንብቦ አያውቅም። ስቴፋኒ በድፍረት የሰጠችው ምሥክርነት አብረዋት ከሚማሩት ልጆች ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውይይት ለማድረግ በር ከፈተላት። በዚህም ምክንያት አንዲት የክፍል ጓደኛዋ የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔቶች ደንበኛ ስትሆን ሌሎች ሁለት አብረዋት የሚማሩ ልጆች ደግሞ ስቴፋኒ ስትጠመቅ ለማየት በአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል።
በደቡብ አሜሪካ ሱሪናም ውስጥ የምትኖረው የስድስት ዓመቷ ቫሬተ አስተማሪዋ ከቅዱሳን ጽሑፎች ማጽናኛ ባስፈለጋት ጊዜ አጋጣሚውን አምላክን ለማወደስ ተጠቅማበታለች። አስተማሪያቸው ከትምህርት ቤት ለሦስት ተከታታይ ቀናት ቀርታ ነበር። ስትመጣ ግን የቀረችበትን ምክንያት ያውቁ እንደሆነ የክፍሉን ተማሪዎች ጠየቀቻቸው። እነሱም “አሞሽ ስለነበረ ነው አይደል?” በማለት መልሰው ጠየቋት። እሷ ግን “አይደለም ታላቅ እህቴ ስለ ሞተች ነው። በሁኔታው በጣም አዝኛለሁ። አሁንም ቢሆን ራሴን እያመመኝ ስለሆነ ጸጥታ እፈልጋለሁ” አለቻቸው።
በዚያን ዕለት ከሰዓት በኋላ እናቷ እንቅልፍ ሸለብ አድርጓት እያለ ቫሬተ የቆዩ መጽሔቶችን እያገላበጠች ርዕሳቸውን ማንበብ ጀመረች። በሐምሌ 15, 2001 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከሞት በኋላ ሕይወት አለን?” የሚለውን ርዕስ ስታገኝ በደስታ እየፈነደቀች ወደ እናቷ ሮጠች። ከዚያም እናቷን ቀስቅሳ “እማማ፣ እማማ ተመልከቺ ለአስተማሪዬ ልሰጣት የምችለው ስለ ሙታን ሁኔታ የሚገልጽ መጽሔት አገኘሁ!” አለቻት። ቫሬተ ከደብዳቤ ጋር መጽሔቱን ለአስተማሪዋ ላከችላት። ደብዳቤው እንዲህ ይላል:- “ይህ መጽሔት ይጠቅምሻል ብዬ አምናለሁ። ይሖዋ በፍጹም ስለማይዋሽ ከእህትሽ ጋር በገነት ውስጥ መገናኘታችሁ አይቀርም። ይሖዋ ሰማይን ሳይሆን ወደፊት ይህችን ምድር ገነት እንደሚያደርጋት ቃል ገብቷል።” አስተማሪዋ ከጽሑፉ ላገኘችው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ማጽናኛዎች የተሰማትን ጥልቅ አድናቆት ገልጻለች።
ለወደፊቱ ጊዜ መሠረት መጣል
ይሖዋ “ደስተኛ አምላክ” በመሆኑ ወጣቶችም ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 1:11 NW) ቃሉ “በወጣትነትህ ጊዜ ደስ ይበልህ፤ በወጣትነትህም ዘመን ልብህ ደስ ያሰኝህ” በማለት ይናገራል። (መክብብ 11:9) ሆኖም ይሖዋ የወደፊቱን ጊዜ አሻግሮ ስለሚመለከት አሁን ያላችሁ ጥሩ ወይም መጥፎ ባሕርይ የሚያስከትለውን ዘላቂ ውጤት ማየት ይችላል። ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ “የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ ‘ደስ አያሰኙኝም’ የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣ በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን አስብ” በማለት ወጣቶችን አጥብቆ የሚመክረው በዚህ ምክንያት ነው።—መክብብ 12:1
አዎን፣ ይሖዋ ወጣቶች ሕይወት የምትለግሳቸውን መልካም ስጦታዎች በሚገባ እንዲያጣጥሙ ይፈልጋል። ስለዚህ ወጣቶች ይሖዋን በማሰብና በማወደስ ትርጉም ያለው አርኪ ሕይወት መምራት ይችላሉ። ችግሮች በሚያጋጥሟቸው ጊዜ እንኳ በሙሉ ልብ “ረዳቴ . . . ይሖዋ ነው” ማለት ይችላሉ።—መዝሙር 121:2 NW
[የግርጌ ማስታወሻ]
a የ2005 የይሖዋ ምሥክሮች የቀን መቁጠሪያ መጋቢት/ሚያዝያ የሚለውን ተመልከት።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ የተቀነበጨበ ሐሳብ]
“እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት . . . ወጣት ወንዶችና ደናግል።”—መዝሙር 148:7, 12
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ይሖዋ ወጣቶችን ይረዳል
“ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ተስፋዬ፤ ከልጅነቴም ጀምሮ መታመኛዬ ነህና።”—መዝሙር 71:5
“ጐልማሳነትሽም እንደ ንስር ይታደስ ዘንድ፣ ምኞትሽን በበጎ ነገር የሚያረካ [አምላክ] ነው።”—መዝሙር 103:5