ብዙዎች የማመዛዘን ችሎታ የሚጎድላቸው ለምንድን ነው?
“ሰውየው ምን ነካው? ከእርሱ ይኼ አይጠበቅም” በማለት ሁኔታውን ይመለከት የነበረ አንድ ሰው ተናገረ። በአካባቢው የነበረ ሌላ ግለሰብ ደግሞ በጉዳዩ በጣም መገረሙን በሚገልጽ አኳኋን ራሱን እየነቀነቀ “ትንሽ ቢያመዛዝን ኖሮ ፈጽሞ እንዲህ አያደርግም ነበር” አለ። እንደነዚህ ያሉ አስተያየቶች ሲሰነዘሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ለመሆኑ “ማመዛዘን” ሲባል ምን ማለት ነው?
“ማመዛዘን” የሚለው ቃል “ትክክለኛ ግንዛቤ፣” “መረዳት” እንዲሁም “ጥበብ ወይም ማስተዋል” የሚል ፍቺ አለው። ቃሉ አንድ ሰው በማስተዋል የመፍረድና ውሳኔ የማድረግ ችሎታ እንዳለው ያመለክታል። የማመዛዘን ችሎታ ነገሮችን በጥሞና ማጤን እንደሚጠይቅ ግልጽ ነው። ሆኖም ብዙ ሰዎች በማሰብ ችሎታቸው ከመጠቀም ይልቅ በሌሎች ሐሳብ መመራት ይመርጣሉ። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለመወሰን በመገናኛ ብዙኃን ወይም በእኩዮቻቸው አሊያም በብዙኃኑ አመለካከት ይመራሉ።
በዚህም የተነሳ ሁኔታውን ያጤነ አንድ ሰው ‘ሐቁን ለመናገር ብዙዎች የማመዛዘን ችሎታ ይጎድላቸዋል’ በማለት ተናግሮ ነበር። የማመዛዘን ችሎታ ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ ማድረጋችንስ ምን ጥቅም አለው?
የማመዛዘን ችሎታ ማዳበር የሚቻለው እንዴት ነው?
ብስለት የታከለበት ውሳኔ ማድረግ መቻል ማለትም የማመዛዘን ችሎታ ማዳበር ጊዜን፣ ነገሮችን ከተለያየ አቅጣጫ ማገናዘብን እንዲሁም የማያቋርጥ ጥረትን ቢጠይቅም ይህን ባሕርይ ማዳበር ይቻላል። የማመዛዘን ችሎታ ለማዳበር የሚረዱንን ሦስት ነጥቦች ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስን አጥና፤ ምክሩንም በተግባር አውል። መጽሐፍ ቅዱስ ለመረዳት የማያስቸግርና አሳማኝ በሆነ መንገድ የተጻፈ በመሆኑ ጥበብና ማስተዋል ለማግኘት የሚረዳ ግሩም መሣሪያ ነው። (ኤፌሶን 1:8) ለአብነት ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸውን የሚከተለውን ምክር እንመልከት:- “እውነት የሆነውን ሁሉ፣ ክቡር የሆነውን ሁሉ፣ ትክክል የሆነውን ሁሉ፣ ንጹሕ የሆነውን ሁሉ፣ ተወዳጅ የሆነውን ሁሉ፣ መልካም የሆነውን ሁሉ፣ በጎነት ቢሆን ወይም ምስጋና፣ እንደ እነዚህ ስላሉት ነገሮች አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 4:8) ይህንን ምክር ሁልጊዜ ተግባራዊ የምናደርግ ከሆነ ትክክለኛ ውሳኔ ማድረግና አርቆ አሳቢነትን ማዳበር እንችላለን።
ከተሞክሮ ተማር። አንድ የስዊስ ገጣሚ የማመዛዘን ችሎታ በሕይወት ውስጥ ከሚገኝ ተሞክሮ ጋር እንደሚዛመድ ሲገልጽ “የማመዛዘን ችሎታ . . . የተሞክሮና የአርቆ አስተዋይነት ጥምረት ነው” ብሏል። በእርግጥም “ተላላ ሰው ሁሉን ያምናል፤ አስተዋይ ግን ርምጃውን ያስተውላል።” (ምሳሌ 14:15) የማመዛዘን ችሎታ አስተውሎ በመመልከት፣ በሥልጠናና በተሞክሮ ሊዳብር ይችላል። በጊዜ ሂደት ሥራችንን በተሻለ መንገድ ማከናወን ልንማር እንችላለን። ያም ሆኖ ከስሕተታችን መማር ገርነትና ትሕትና ይጠይቃል። በዚህ የመጨረሻ ዘመን ሰዎች የሚታይባቸው የትምክህተኝነት፣ የትዕቢትና የግትርነት ባሕርይ የማመዛዘን ችሎታ እንደሚጎድላቸው ያሳያል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ወዳጆችህን በጥበብ ምረጥ። ወዳጆቻችን ጥበበኞች እንድንሆንና በማመዛዘን ችሎታችን እንድንጠቀም ሊረዱን ወይም ይህንን እንዳናደርግ እንቅፋት ሊሆኑብን ይችላሉ። ምሳሌ 13:20 “ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጒዳት ያገኘዋል” ይላል። አምላክን የማይታዘዙና ቃሉን ችላ የሚሉ ሰዎችን አመለካከት ወይም ሐሳብ መቀበል አይኖርብንም። ምሳሌ 17:12 ጉዳዩን እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል:- “ተላላን በቂልነቱ ከመገናኘት፣ ግልገሎቿን የተነጠቀችን ድብ መጋፈጥ ይሻላል።”
የማመዛዘን ችሎታ ምን ጥቅሞች ያስገኛል?
የማመዛዘን ችሎታን ማዳበር ሕይወት ይበልጥ አስደሳች እንዲሆን ስለሚያደርግና ጊዜ ስለሚቆጥብ ጠቃሚ ነው። ይህ ባሕርይ ሳያስቡ መሥራት የሚያስከትለውን ብስጭት ሊቀንስም ይችላል። ብስለት የጎደላቸው ሰዎች በገዛ እጃቸው ሕይወታቸውን አስቸጋሪ ያደርጉታል። መጽሐፍ ቅዱስ “የሞኝ ሥራ ራሱን ያደክመዋል” ይላል። (መክብብ 10:15) እንደዚህ ያሉ ግለሰቦች ቀን ከሌት በመልፋት ራሳቸውን ያደክሙ ይሆናል፤ ያም ሆኖ ግን አንዳችም የሚረባ ነገር አያከናውኑም።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንጽሕና፣ ከሰዎች ጋር ሐሳብ ስለ መለዋወጥ፣ ትጉ ሠራተኛ ስለመሆን፣ ድህነትን ስለ መቋቋምና የተለያዩ የሕይወት ዘርፎችን ስለሚዳስሱ ሌሎች ጉዳዮች በርካታ ምክሮች ይዟል። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ስኬታማ መሆን አለመሆናቸው በጥበብ እንዲኖሩ የሚያስችላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ ተግባራዊ በማድረጋቸው ወይም ባለማድረጋቸው ላይ የተመካ እንደሆነ ይመሰክራሉ።
የማመዛዘን ችሎታ በዝርዝር የተቀመጡ ሕግጋትን ወይም ደንቦችን ከመከተል አልፈን እንድናስብ ያደርገናል። ኃላፊነቶቻችንን እንድንወጣም ይረዳናል። ይህ ሲባል ግን የማመዛዘን ችሎታ ካዳበርን እውቀት መቅሰም አያስፈልገንም ማለት አይደለም። ምሳሌ 1:5 “ጥበበኞች ያድምጡ፤ ትምህርታቸውንም ያዳብሩ” ይላል። ከዚህም በተጨማሪ የቀሰምነውን እውቀት በማገናዘብ ተገቢ ድምዳሜ ላይ መድረስን መማር ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን ‘በጥበብ ለመመላለስ’ ያስችለናል።—ምሳሌ 28:26
የማመዛዘን ችሎታ ከትሕትና ጋር የሚዛመድ ባሕርይ ነው። በርካታ ኃላፊነቶችን መወጣት ብንፈልግም አስተዋዮች በመሆን አቅማችንን ማወቅ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለጌታ ሥራ ዘወትር የምትተጉ ሁኑ” እንዳለን አይካድም። (1 ቆሮንቶስ 15:58) ሆኖም ይህን ምክር ተግባራዊ ስናደርግ በመክብብ 9:4 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን “በሕይወት ያለ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓትም ልብ ልንል ይገባል። ይሖዋን ስናገለግል ለጤንነታችን ማሰባችን ረዘም ላለ ጊዜ ለመኖርና በአገልግሎታችን ለመቀጠል ያስችለናል። የማመዛዘን ችሎታ ሚዛናዊ በመሆን ደስታችንን ሳናጣ አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮችን ለማከናወን ያስችለናል። በእርግጥም የማመዛዘን ችሎታ በርካታ ጥቅሞች አሉት።
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጣም ብዙ ጠቃሚ ምክሮች ይገኛሉ
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የማመዛዘን ችሎታ አስተውሎ በመመልከት፣ በሥልጠናና በተሞክሮ ሊዳብር ይችላል