የይሖዋ ቃል ሕያው ነው
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆነው የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ የሚጀምረው የአንደኛ ነገሥት መጽሐፍ የእስራኤልንና የይሁዳን ታሪክ መተረክ ካቆመበት ነው። መጽሐፉ በድምሩ የ29 ነገሥታትን ታሪክ ያወሳል፤ ከእነዚህ ውስጥ 12ቱ በሰሜናዊው የእስራኤል መንግሥት የነገሡ ሲሆኑ ቀሪዎቹ 17ቱ ደግሞ ደቡባዊውን የይሁዳ መንግሥት ያስተዳደሩ ናቸው። ከዚህም በተጨማሪ የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ኤልያስ፣ ኤልሳዕና ኢሳይያስ የተባሉት ነቢያት ያከናወኗቸውን ድርጊቶች አስፍሯል። የጊዜ ቅደም ተከተሉን ጠብቆ የተቀመጠ ባይሆንም እንኳ ዘገባው ሰማርያና ኢየሩሳሌም እስከጠፉበት ድረስ ያለውን ክንውን ይተርካል። ይህ መጽሐፍ ከ920 እስከ 580 ከክርስቶስ ልደት በፊት ማለትም ነቢዩ ኤርምያስ መጽሐፉን ጽፎ እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ያሉትን የ340 ዓመታት ታሪክ ይሸፍናል።
ሁለተኛ ነገሥት ለእኛ ምን ጥቅም አለው? ስለ ይሖዋና እርሱ ከሰው ልጆች ጋር ስለነበረው ግንኙነት ምን ያስተምረናል? ነገሥታቱ፣ ነቢያቱና በመጽሐፉ ውስጥ የተጠቀሱ ሌሎች ሰዎች ካከናወኗቸው ድርጊቶች ምን እንማራለን? ከሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ምን ትምህርት ልናገኝ እንደምንችል እስቲ እንመልከት።
ኤልሳዕ በኤልያስ እግር ተተካ
የእስራኤል ንጉሥ የነበረው አካዝያስ ከቤቱ ሰገነት ላይ በመውደቁ በጠና ታመመ፤ ነቢዩ ኤልያስም እንደሚሞት ነገረው። አካዝያስ ሲሞት ወንድሙ ኢዮራም ዙፋኑን ወረሰ። በዚህ ወቅት ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ነግሦ ነበር። ኤልያስ በዐውሎ ነፋስ ከተወሰደ በኋላ ረዳቱ ኤልሳዕ ነቢይ ሆኖ በእግሩ ተተካ። ኤልሳዕ ባገለገለባቸው በቀጣዮቹ ወደ 60 የሚጠጉ ዓመታት በርካታ ተአምራትን ፈጽሟል።—“ኤልሳዕ የፈጸማቸው ተአምራት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
የሞዓብ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ባመጸ ጊዜ ኢዮራም፣ ኢዮሣፍጥና የኤዶም ንጉሥ በአንድነት ዘመቱበት። በኢዮሣፍጥ ታማኝነት የተነሳም ድል አደረጉት። ብዙም ሳይቆይ የሶርያ ንጉሥ በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ለመሰንዘር አቀደ። ሆኖም ኤልሳዕ እቅዱ እንዲከሽፍ አደረገ። ሁኔታው እጅግ ያበሳጨው የሶርያ ንጉሥ ኤልሳዕን ለመያዝ “ፈረሶችና ሠረገሎች እንዲሁም ብዙ ሰራዊት” አዘመተ። (2 ነገሥት 6:14) በጊዜው ኤልሳዕ ሁለት ተአምራት የፈጸመ ሲሆን ሶርያውያኑ በሰላም ወደመጡበት እንዲመለሱ አድርጓል። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የሶርያው ንጉሥ ቤን ሀዳድ ሰማርያን በመክበቡ ምክንያት በከተማይቱ ውስጥ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ ያም ሆኖ ኤልሳዕ ረሃቡ እንደሚወገድ ተነበየ።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ኤልሳዕ ወደ ደማስቆ አቀና። በጊዜው ንጉሥ ቤን ሀዳድ ታሞ ስለነበር ከበሽታው ይድን እንደሆነ እንዲጠይቅለት አዛሄልን ላከው። ኤልሳዕ ግን ንጉሡ እንደሚሞትና በእርሱ ፋንታ አዛሄል እንደሚነግሥ ተናገረ። በማግሥቱ አዛሄል ንጉሡን እርጥብ በሆነ “ወፍራም ልብስ” አፍኖ በመግደል ንግሥናውን ያዘ። (2 ነገሥት 8:15) በይሁዳ የኢዮሣፍጥ ልጅ ኢዮራም ነገሠ፤ በኋላም ልጁ አካዝያስ በእርሱ ቦታ ተተካ።—“የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
2:9—ኤልሳዕ ‘የኤልያስ መንፈስ በዕጥፍ’ እንዲወርድበት የጠየቀው ለምን ነበር? ኤልሳዕ በእስራኤል ላይ ነቢይ ሆኖ እንዲያገለግል የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ኤልያስ የነበረውን ዓይነት መንፈስ ማሳየት ማለትም ደፋርና ቆራጥ መሆን ያስፈልገው ነበር። ይህን የተገነዘበው ኤልሳዕ የኤልያስ መንፈስ በእጥፍ እንዲወርድበት ለመነ። ኤልሳዕን ተተኪው አድርጎ የሾመው ኤልያስ ሲሆን ከዚያ በፊት ለስድስት ዓመታት አገልግሎታል። በመሆኑም ኤልሳዕ ኤልያስን የሚመለከተው መንፈሳዊ አባቱ አድርጎ ነበር። በሌላ አነጋገር ኤልሳዕ ለኤልያስ በመንፈሳዊ ልክ እንደ በኩር ልጁ ነበር። (1 ነገሥት 19:19-21፤ 2 ነገሥት 2:12) ስለዚህ አንድ የበኩር ልጅ ከአባቱ ውርስ ሁለት እጅ ያገኝ እንደነበረ ሁሉ ኤልሳዕም ከኤልያስ ሁለት እጥፍ መንፈሳዊ ውርስ ጠይቆ አግኝቷል።
2:11—‘ኤልያስ በዐውሎ ነፋስ ያረገው’ ወደየትኛው “ሰማይ” ነው? ይህ ሰማይ በግዑዙ አጽናፈ ዓለም ውስጥ የሚገኝን ሩቅ ቦታ ወይም አምላክና መላእክቱ የሚኖሩበትን መንፈሳዊ ሥፍራ አያመለክትም። (ዘዳግም 4:19፤ መዝሙር 11:4፤ ማቴዎስ 6:9፤ 18:10) ኤልያስ ያረገበት “ሰማይ” የሚያመለክተው በዓይናችን የምናየውን ሰማይ ነው። (መዝሙር 78:26፤ ማቴዎስ 6:26) ኤልያስ በእሳት ሰረገላ አማካኝነት በአየር ላይ ወደ ሌላ የምድር ክፍል ከተጓዘ በኋላ በተወሰደበት ሥፍራ ለተወሰኑ ጊዜያት ኖሯል። ዓመታት ካለፉ በኋላ ኤልያስ የይሁዳ ንጉሥ ለነበረው ለኢዮራም ደብዳቤ ልኮለታል።—2 ዜና መዋዕል 21:1, 12-15
5:15, 16—ኤልሳዕ የንዕማንን ስጦታ ያልተቀበለው ለምንድን ነው? ኤልሳዕ ስጦታውን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልነበረው ተዓምሩን የፈጸመው በራሱ ችሎታ ሳይሆን በይሖዋ ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ ስለነበር ነው። ኤልሳዕ አምላክ የሰጠውን ኃላፊነት ለራሱ መጠቀሚያ የማድረግ ሐሳብ አልነበረውም። በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ እውነተኛ ክርስቲያኖችም የይሖዋን አገልግሎት የግል ጥቅም ማግኛ ለማድረግ አይሞክሩም። ኢየሱስ “በነጻ የተቀበላችሁትንም በነጻ ስጡ” ሲል የሰጠውን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ያደርጋሉ።—ማቴዎስ 10:8
5:18, 19—ንዕማን ይቅርታ እንዲደረግለት የለመነው በሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ ስለሚካፈል ነበር? በጊዜው የሶርያ ንጉሥ አርጅቶና አቅሙ ደክሞ ስለነበር የንዕማን ድጋፍ ያሻው ነበር። ንጉሡ ለሬሞን በሚሰግድበት ጊዜ እሱም አብሮት ማጎንበስ ነበረበት። ንዕማን እንደዚያ የሚያደርገው ንጉሡን ለመደገፍ እንጂ አምልኮ ለማቅረብ አልነበረም። ንዕማን ይሖዋ ይቅር እንዲለው የተማጸነው ይህን መሰሉን ሥራ ያከናውን ስለነበር ነው። ኤልሳዕ ንዕማን የነገረውን በማመን “በሰላም ሂድ” ብሎታል።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
1:13, 14፦ ከተመለከቱት ነገር ትምህርት ማግኘትና በትሕትና ተገቢውን እርምጃ መውሰድ ሕይወትን ሊያተርፍ ይችላል።
2:2, 4, 6፦ ምንም እንኳ ኤልሳዕ የኤልያስ አገልጋይ ሆኖ ስድስት ዓመት ገደማ ቢያሳልፍም ከእሱ ላለመለየት የሙጥኝ ብሏል። ታማኝነትንና ጥሩ ጓደኝነትን የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!—ምሳሌ 18:24
2:23, 24፦ ልጆቹ እንዲያፌዙ ያደረጋቸው ዋነኛ ምክንያት ራሰ በራ የነበረው ኤልሳዕ የኤልያስን ካባ ለብሶ መታየቱ ነው። ልጆቹ ኤልሳዕ የይሖዋ ወኪል እንደሆነ ተገንዝበዋል፤ በተጨማሪም በአካባቢው እንዲቆይ አልፈለጉም ነበር። ስለሆነም “ውጣ!” በማለት ወደ ቤቴል እንዲያቀና ወይም ልክ እንደ ኤልያስ ወደ ሰማይ እንዲወጣ ነገሩት። እነዚህ ልጆች ወላጆቻቸው የነበራቸውን የጥላቻ ስሜት አንጸባርቀዋል። ወላጆች ልጆቻቸው ለአምላክ ወኪሎች ተገቢውን አክብሮት እንዲያሳዩ ማስተማራቸው ምንኛ አስፈላጊ ነው!
3:14, 18, 24፦ አምላክ የተናገረው ሁሉ መፈጸሙ አይቀርም።
3:22፦ ምናልባትም አዲስ የተቆፈሩት የውኃ ጉድጓዶች ቀይ አፈር ስለነበራቸው የማለዳ ፀሐይ በውኃው ላይ ሲያርፍ ውኃው ደም መስሎ እንዲታያቸው አድርጎ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ዓላማውን ለማሳካት የተፈጥሮ ክስተቶችን ሊጠቀም ይችላል።
4:8-11፦ ሱነማዪቱ ሴት ኤልሳዕ “ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው” እንደሆነ ስለተገነዘበች በእንግድነት ተቀብላዋለች። እኛስ ይሖዋን በታማኝነት ለሚያመልኩ ሰዎች እንዲህ ማድረግ አይገባንም?
5:3፦ ትንሿ እስራኤላዊት ልጃገረድ አምላክ ተአምራት የመፈጸም ችሎታ እንዳለው ታምን ነበር። ስለ እምነቷም ለመናገር ድፍረት ነበራት። እናንተ ወጣቶች በአምላክ ተስፋዎች ላይ ያላችሁን እምነት ለማጠንከር ትጥራላችሁ? ለአስተማሪዎቻችሁና አብረዋችሁ ለሚማሩ ልጆች እውነትን ለማካፈል የሚያስችል ድፍረት አዳብራችኋል?
5:9-19፦ በአንድ ወቅት ኩሩ የነበረ ሰው ትሕትና ሊማር እንደሚችል የንዕማን ምሳሌ አያሳይም?—1 ጴጥሮስ 5:5
5:20-27፦ ለማታለል መሞከር እንዴት ያለ ከባድ መዘዝ ያስከትላል! ሁለት ዓይነት ሕይወት መምራት የሚያስከትለውን ችግርና መከራ ማሰብ ከእንዲህ ዓይነት አካሄድ ራሳችንን እንድንጠብቅ ያደርገናል።
እስራኤልና ይሁዳ በግዞት ተወሰዱ
ኢዩ ተቀብቶ በእስራኤል ላይ ነገሠ፤ ወዲያውኑም በአክዓብ ቤት ላይ እርምጃ መውሰድ ጀመረ። ኢዩ በዘዴ ‘የበአልን አምልኮ ከእስራኤል ማስወገድ’ ችሏል። (2 ነገሥት 10:28) የአካዝያስ እናት ጎቶልያ ልጅዋ በኢዩ መገደሉን ስትሰማ ‘የይሁዳን ንጉሣዊ ቤተሰቦች በሙሉ በማጥፋት’ ዙፋኑን ለመውረስ ተነሳች። (2 ነገሥት 11:1) በሕይወት የተረፈው የአካዝያስ ሕጻን ልጅ ኢዮአስ ብቻ ነበር፤ እሱም ለስድስት ዓመት ተሸሽጎ ከቆየ በኋላ በይሁዳ ነገሠ። ኢዮአስ በካህኑ ዮዳሄ በመመራት በይሖዋ ፊት መልካም የሆነውን አደረገ።
ከኢዩ በኋላ የተነሡት የእስራኤል ነገሥታት በሙሉ በይሖዋ ፊት ክፉ ድርጊት ፈጽመዋል። ኤልሳዕ በኢዩ የልጅ ልጅ የግዛት ዘመን በዕድሜ መግፋት ሳቢያ ሞተ። ከኢዮአስ በኋላ ከተነሱት የይሁዳ ንጉሦች ውስጥ አራተኛ የሆነው ንጉሥ አካዝ ሲሆን እሱም ‘በእግዚአብሔር ፊት መልካም የሆነውን ሳያደርግ’ ቀርቷል። (2 ነገሥት 16:1, 2) ሆኖም ልጁ ሕዝቅያስ ‘ከእግዚአብሔር ጋር ጥብቅ’ ዝምድና የነበረው ንጉሥ መሆኑን አስመስክሯል። (2 ነገሥት 17:20፤ 18:6) በ740 ከክርስቶስ ልደት በፊት፣ ሕዝቅያስ የይሁዳ ንጉሥ እያለ እንዲሁም ሆሴዕ እስራኤልን በሚገዛበት ወቅት የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር “ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤላውያንንም በምርኮ ወደ አሦር አፈለሳቸው።” (2 ነገሥት 17:6) ከዚያም እስራኤላውያን ያልሆኑ ሌሎች ሕዝቦችን በእስራኤል ግዛት ውስጥ አሰፈረ፤ በዚያም የሳምራውያን ሃይማኖት ተወለደ።
ከሕዝቅያስ በኋላ ከተነሱት ሰባት የይሁዳ ነገሥታት መካከል ምድሪቱን ከሐሰት አምልኮ ለማጽዳት እርምጃ የወሰደው ኢዮስያስ ብቻ ነበር። በመጨረሻም፣ በ607 ከክርስቶስ ልደት በፊት ባቢሎናውያን ኢየሩሳሌምን ያዙ፤ ‘ይሁዳም ከምድሩ ተማርኮ ሄደ።’—2 ነገሥት 25:21
ቅዱስ ጽሑፋዊ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው፦
13:20, 21—ይህ ተአምር እንደ ቅዱስ ተደርገው ለሚታዩ ነገሮች ክብር መስጠት እንዳለብን አያሳይም? በፍጹም አያሳይም። መጽሐፍ ቅዱስ የኤልሳዕ አጽም ክብር ተሰጥቶት እንደነበር አንድም ቦታ ላይ አያመለክትም። ኤልሳዕ በሕይወት በነበረበት ጊዜ እንዳከናወናቸው ሌሎች ተአምራት ሁሉ ይህንንም ያደረገው የአምላክ ኃይል ነው።
15:1-6—ይሖዋ ዓዛርያስን (“ዖዝያን፣” 15:13) በለምጽ የመታው ለምን ነበር? “ዖዝያን ከበረታ በኋላ . . . ዕብሪቱ ለውድቀት ዳረገው። በዕጣን መሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመግባቱ እግዚአብሔርን በደለ።” በዚህ ጊዜ ካህናቱ ዖዝያን “ፊት ለፊት በመጋፈጥ” ‘ከመቅደሱ እንዲወጣ’ ሲነግሩት ካህናቱን በመቆጣቱ በለምጽ ሊመታ ችሏል።—2 ዜና መዋዕል 26:16-20
18:19-21, 25—ሕዝቅያስ ከግብፅ ጋር ወታደራዊ ጥምረት ፈጥሮ ነበር? በጭራሽ፤ የአሦር ሠራዊት የጦር አዛዥ የመጣሁት ‘በእግዚአብሔር ፈቃድ’ ነው ብሎ እንደዋሸ ሁሉ ሕዝቅያስ በግብፅ ተመክቷል ማለቱም የሐሰት ውንጀላ ነበር። ታማኙ ንጉሥ ሕዝቅያስ የታመነው በይሖዋ ላይ ብቻ ነበር።
ምን ትምህርት እናገኛለን?
9:7, 26፦ በአክዓብ ቤት ላይ የተላለፈው ከባድ የቅጣት ፍርድ ይሖዋ የሐሰት አምልኮንና የንጹሐንን ደም ማፍሰስን አጥብቆ እንደሚጠላ ያሳያል።
9:20፦ ኢዩ ሰረገላውን በኃይል በመንዳት የሚታወቅ ሰው መሆኑ ተልእኮውን ለመፈጸም የነበረውን ቅንዓት ያሳያል። አንተስ፣ ‘ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ ነው’ የሚል ስም አትርፈሃል?—2 ጢሞቴዎስ 4:2
9:36, 37፤ 10:17፤ 13:18, 19, 25፤ 14:25፤ 19:20, 32-36፤ 20:16, 17፤ 24:13፦ ከይሖዋ ‘አፍ የሚወጣ ቃል የተላከበትን ዐላማ እንደሚፈጽም’ ትምክህት ሊኖረን ይገባል።—ኢሳይያስ 55:10, 11
10:15:- ኢዮናዳብ ኢዩ ወደ ሰረገላው እንዲወጣ ያቀረበለትን ግብዣ በሙሉ ልብ እንደተቀበለ ሁሉ ‘እጅግ ብዙ ሕዝቦችም’ ዘመናዊውን ኢዩ ኢየሱስ ክርስቶስንና ቅቡዓን ተከታዮቹን በፈቃደኝነት ይደግፋሉ።—ራእይ 7:9
10:30, 31፦ ኢዩ እንከን የለሽ ባይሆንም እንኳ ያከናወናቸውን ሥራዎች ይሖዋ ከፍ አድርጎ ተመልክቶለታል። በእርግጥም ‘እግዚአብሔር ያደረግነውን ሥራ ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለም።’—ዕብራውያን 6:10
13:14-19፦ የኢዩ የልጅ ልጅ የነበረው ዮአስ መሬቱን በቀስት ሦስት ጊዜ ብቻ በመውጋት በቂ ቅንዓት ሳያሳይ በመቅረቱ በሶርያውያን ላይ የተሟላ ድል ሳያገኝ ቀርቷል። ይሖዋ የሰጠንን ሥራ በሙሉ ልብና በቅንዓት እንድናከናውን ይፈልጋል።
20:2-6፦ ይሖዋ ‘ጸሎትን ይሰማል።’—መዝሙር 65:2
24:3, 4፦ ምናሴ ደም በማፍሰሱ የተነሳ ይሖዋ ለይሁዳ “ይቅርታ ለማድረግ አልፈለገም።” አምላክ ለንጹሐን ደም አክብሮት አለው። ይሖዋ ለደም መፍሰሱ ተጠያቂ የሆኑትን በማጥፋት የንጹሐንን ደም እንደሚበቀል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—መዝሙር 37:9-11፤ 145:20
ምን ጥቅም እናገኛለን?
የሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ይሖዋ የሰጠውን የተስፋ ቃል የሚፈጽም አምላክ እንደሆነ ያሳያል። ሁለቱ መንግሥታት ማለትም በመጀመሪያ የእስራኤል ኋላም የይሁዳ ነዋሪዎች ለግዞት መዳረጋቸው በዘዳግም 28:15 እስከ 29:28 የሰፈሩትን ትንቢታዊ የፍርድ ቃላት እውነተኝነት በሚገባ ያረጋግጥልናል። ሁለተኛ ነገሥት ኤልሳዕ ለይሖዋ ስምና ለእውነተኛው አምልኮ ከፍተኛ ቅንዓት ያለው ነቢይ እንደነበረ ይገልጻል። ሕዝቅያስና ኢዮስያስ ለአምላክ ሕግ አክብሮት የነበራቸው ትሑት ነገሥታት እንደነበሩም ይናገራል።
በሁለተኛ ነገሥት መጽሐፍ ላይ የተጠቀሱ ነገሥታት፣ ነቢያትና ሌሎች ሰዎች በነበሯቸው አመለካከቶችና ባከናወኗቸው ድርጊቶች ላይ በማሰላሰላችን ማድረግ ስለሚገባንና ስለማይገባን ነገር ጠቃሚ ትምህርቶችን አላገኘንም? (ሮሜ 15:4፤ 1 ቆሮንቶስ 10:11) አዎን፣ “የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሠራ ነው።”—ዕብራውያን 4:12
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ኤልሳዕ የፈጸማቸው ተአምራት
1. የዮርዳኖስን ወንዝ ከፍሏል።—2 ነገሥት 2:14
2. በኢያሪኮ የነበረውን መጥፎ ውኃ ፈውሷል።—2 ነገሥት 2:19-22
3. ጋጠወጦቹ ልጆች በድቦች እንዲጠቁ አድርጓል።—2 ነገሥት 2:23, 24
4. ሠራዊቱ ውኃ እንዲያገኝ አድርጓል።—2 ነገሥት 3:16-26
5. አንዲት መበለት የምግብ ዘይት እንድታገኝ አድርጓል።—2 ነገሥት 4:1-7
6. መካን የነበረች ሱነማይት ሴት ልጅ የመውለድ ችሎታዋን እንድታገኝ አድርጓል።—2 ነገሥት 4:8-17
7. አንድ ትንሽ ልጅ ከሞት አስነስቷል።—2 ነገሥት 4:18-37
8. መርዛማ የነበረውን ወጥ ጉዳት የማያስከትል እንዲሆን አድርጓል።—2 ነገሥት 4:38-41
9. በ20 ሙልሙል ዳቦ አንድ መቶ ሰው መግቧል።—2 ነገሥት 4:42-44
10. ንዕማንን ከለምጹ ፈውሷል።—2 ነገሥት 5:1-14
11. የንዕማን ለምጽ ወደ ግያዝ እንዲተላለፍ አድርጓል።—2 ነገሥት 5:24-27
12. መጥረቢያውን ውኃ ላይ አንሳፍፏል።—2 ነገሥት 6:5-7
13. አገልጋዩ የእሳት ፈረሶችንና ሠረገሎችን እንዲያይ አድርጓል።—2 ነገሥት 6:15-17
14. የሶርያውያንን ሠራዊት ዓይን አሳውሯል።—2 ነገሥት 6:18
15. ሶርያውያኑ እንደገና ማየት እንዲችሉ አድርጓል።—2 ነገሥት 6:19-23
16. አንድ ሰው ከሞት አስነስቷል።—2 ነገሥት 13:20, 21
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕል]
የይሁዳና የእስራኤል ነገሥታት
ሳኦል/ዳዊት/ሰሎሞን:- 1117/1077/1037 ከክርስቶስ ልደት በፊትa
የይሁዳ መንግሥት ዘመን (ከክ.ል.በፊት) የእስራኤል መንግሥት
ሮብዓም ․․․․․․ 997 ․․․․․․ ኢዮርብዓም
አብያ/አሳ ․․․․ 980/978 ․․․․
․․ 976/975/952 ․․ ናዳብ/ባኦስ/ኤላ
․․ 951/951/951 ․․ ዘምሪ/ዖምሪ/ታምኒ
․․․․․․ 940 ․․․․․․ አክዓብ
ኢዮሣፍጥ ․․․․․․ 937 ․․․․․․
․․․․ 920/917 ․․․․ አካዝያስ/ኢዮራም
ኢዮሆራም ․․․․․․ 913 ․․․․․․
አካዝያስ ․․․․․․ 906 ․․․․․․
(ጎቶልያ) ․․․․․․ 905 ․․․․․․ ኢዩ
ኢዮአስ ․․․․․․ 898 ․․․․․
․․․․ 876/859 ․․․․ ኢዮአካዝ/ዮአስ
አሜስያስ ․․․․․․ 858 ․․․․․․
․․․․․․ 844 ․․․․․․ ዳግማዊ ኢዮርብዓም
ዓዛርያስ (ዖዝያን) ․․․․․․ 829 ․․․․․․
․․ 803/791/791 ․․ ዘካርያስ/ሰሎም/ምናሔም
․․․․ 780/778 ․․․․ ፋቂስያስ/ፋቁሔ
ኢዮአታም/አካዝ ․․․․ 777/762 ․․․․
․․․․․․ 758 ․․․․․․ ሆሴዕ
ሕዝቅያስ ․․․․․․ 746 ․․․․․․
․․․․․․ 740 ․․․․․․ ሰማርያ ተያዘች
ምናሴ/አሞን/ኢዮስያስ ․․ 716/661/659 ․․
ኢዮአክስ/ኢዮአቄም ․․․․ 628/628 ․․․․
ዮአኪን/ሴዴቅያስ ․․․․ 618/617 ․․․․
ኢየሩሳሌም ጠፋች ․․․․․․ 607 ․․․․․․
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንድ ዘመናት የሚያመለክቱት የግዛቱ መጀመሪያ ተደርጎ የሚገመተውን ዓመት ነው።
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ንዕማን ትሑት በመሆን በይሖዋ ኃይል መፈወስ ችሏል
[በገጽ 8 እና 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኤልያስ ‘በዓውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ በዐረገ’ ጊዜ የተከናወነው ምን ነበር?