የሕይወት ታሪክ
ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠናል
ሪሞ ክዎካነን እንደተናገረው
በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮፓ ሲፈነዳ ሶቪየት ሕብረት የትውልድ አገሬን ፊንላንድን ወረረች። አባቴም ለፊንላንድ ሊዋጋ ወደ ጦር ግንባር ዘመተ። ብዙም ሳይቆይ የሩሲያ የጦር አውሮፕላኖች በከተማችን ላይ ቦምብ መጣል ስለጀመሩ እናቴ የተሻለ ደኅንነት ባለበት አካባቢ እንድኖር በማሰብ ወደ አያቴ ቤት ላከችኝ።
በ1971 በምሥራቅ አፍሪካ በምትገኘው በኡጋንዳ በሚስዮናዊነት አገለግል ነበር። አንድ ቀን ከቤት ወደ ቤት እያገለገልኩ ሳለ በፍርሃት የተዋጡ ብዙ ሰዎች በአጠገቤ እየሮጡ ሲያልፉ ተመለከትኩ። ወዲያውም የተኩስ ድምፅ ስለሰማሁ ወደ ቤቴ መሮጥ ጀመርኩ። ተኩሱ ይበልጥ እየቀረበኝ ሲመጣ መንገዱ ዳር ባለው ቦይ ውስጥ ዘልዬ ገባሁ። በተኩስ እሩምታ መሃል በደረቴ እየተሳብኩ ቤቴ ደረስኩ።
ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተላቸውን ውጤቶች ለማስወገድ ማድረግ የምችለው ነገር ባይኖርም እኔና ባለቤቴ አለመረጋጋት ወደነገሠበት ወደ ምሥራቅ አፍሪካ የሄድነው ለምንድን ነው? መልሱ ይሖዋን ለማገልገል ካደረግነው ቁርጥ ውሳኔ ጋር የሚዛመድ ነው።
አምላክን እንዳገለግል ማበረታቻ አገኘሁ
በ1934 ሄልሲንኪ፣ ፊንላንድ ተወለድኩ። ቀለም ቀቢ የሆነው አባቴ አንድ ቀን ፊንላንድ ወደሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ሄዶ ሕንጻውን እንዲቀባ ተላከ። በዚህ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮቹ ስለሚያደርጓቸው የጉባኤ ስብሰባዎች ነገሩት። እቤት ከመጣ በኋላ ለእናቴ ስለ ስብሰባዎቹ አጫወታት። እናቴ ወዲያውኑ በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ባትጀምርም እንኳ ከጊዜ በኋላ ከአንዲት የይሖዋ ምሥክር የሥራ ባልደረባዋ ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መወያየት ጀመረች። ከዚያም የተማረችውን ነገር በተግባር በማዋል በ1940 ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር ሆነች።
እናቴ ከመጠመቋ ትንሽ ቀደም ብሎ አያቴ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እስኪያልፍ ድረስ ገጠር ወደሚገኘው የትውልድ ቀዬዋ ወስዳኝ ነበር። እናቴ ከሄልሲንኪ ሆና ለታናሽ እህቷና ለአያቴ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች እምነት ትጽፍላቸው ጀመር። ሁለቱም ለመልእክቱ ፍላጎት ያሳዩ ሲሆን የተማሩትንም ነገር ያካፍሉኝ ጀመር። ተጓዥ ተወካዮች ወደ አያቴ ቤት መጥተው ሁላችንንም በሚገባ አበረታቱን። ይሁንና በዚህ ጊዜ ይሖዋን ለማገልገል ገና አልወሰንኩም ነበር።
ቲኦክራሲያዊ ሥልጠና ማግኘት ጀመርኩ
ጦርነቱ በ1945 ሲጠናቀቅ ወደ ሄልሲንኪ የተመለስኩ ሲሆን እናቴም የይሖዋ ምሥክሮች ወደሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ይዛኝ መሄድ ጀመረች። አንዳንዴ ወደ ስብሰባዎች ከመሄድ ይልቅ ፊልም ቤት እገባ ነበር። ይሁንና እናቴ በስብሰባው ላይ የሰማችውን ንግግር ትከልስልኝ እንዲሁም “አርማጌዶን በጣም ቀርቧል” እያለች ደጋግማ ትነግረኝ ነበር። እኔም አርማጌዶን እንደቀረበ እምነት ስላደረብኝ በሁሉም ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ መገኘት ጀመርኩ። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ይበልጥ እየተረዳሁ ስሄድ በሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል ያለኝ ፍላጎት እያደገ መጣ።
በተለይ ደግሞ በልዩ፣ በወረዳና በአውራጃ ስብሰባዎች ላይ መገኘት በጣም ያስደስተኝ ነበር። በ1948 የበጋ ወቅት የእረፍት ጊዜዬን ያሳለፍኩት አያቴ ጋር ስለነበር እዚያው አካባቢ በተደረገ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። አንድ ጓደኛዬ በዚያ ስብሰባ ላይ ይጠመቅ ስለነበር እኔም እንድጠመቅ አበረታታኝ። የዋና ቁምጣዬን እንዳላመጣሁ ስነግረው እርሱ ከተጠመቀ በኋላ የእሱን የዋና ልብስ እንደሚያውሰኝ ነገረኝ። በሐሳቡ ስለተስማማሁ ሰኔ 27, 1948 በ13 ዓመቴ ተጠመቅሁ።
ከስብሰባው በኋላ አንዳንድ የእናቴ ጓደኞች እንደተጠመቅሁ ነገሯት። በሚቀጥለው ጊዜ ስንገናኝ እሷን ሳላማክር እንዲህ ዓይነቱን ወሳኝ እርምጃ ለምን እንደወሰድኩ ጠየቀችኝ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ትምህርቶች እንደተረዳሁና ለማደርገው ነገር ሁሉ በይሖዋ ፊት የምጠየቅ መሆኑን እንደማውቅ ነገርኳት።
ያደረግኩት ውሳኔ ተጠናከረ
በጉባኤያችን ያሉ ወንድሞች ይሖዋን ለማገልገል ያደረግኩትን ውሳኔ እንዳጠናክር ረድተውኛል። አገልግሎት አብረውኝ የሚወጡ ከመሆኑም ሌላ በየሳምንቱ ማለት ይቻላል በስብሰባዎች ላይ የሚቀርብ ክፍል ይሰጡኝ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 20:20) ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ንግግር ያቀረብኩት በ16 ዓመቴ ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የጉባኤያችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። እነዚህ ሁሉ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንድጎለምስ ረድተውኛል። ይሁን እንጂ ሰውን የመፍራት ድክመቴን ማሸነፍ ነበረብኝ።
በዚያን ወቅት በአውራጃ ስብሰባ ላይ የሚሰጠውን የሕዝብ ንግግር ለማስተዋወቅ ትላልቅ ማስታወቂያዎችን እንይዝ ነበር። እያንዳንዱ ማስታወቂያ ሁለት ማስታወቂያዎችን ያቀፈ ነው። እነዚህ ሁለት ማስታወቂያዎች በገመድ ይያያዙና በአንገታችን እናጠልቀዋለን። ከዚያም አንደኛው ደረታችንን ሌላኛው ደግሞ ጀርባችንን ይሸፍናል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዎች ‘ሳንድዊች’ እያሉ ይጠሩን ነበር።
በአንድ ወቅት ጭር ባለ መንገድ ላይ ማስታወቂያዬን አንግቤ እንደቆምኩ የክፍል ጓደኞቼ ወደ እኔ አቅጣጫ ሲመጡ ተመለከትኩ። በአጠገቤ ሲያልፉ አስተያየታቸው አሸማቀቀኝ። ይሖዋ ድፍረት እንዲሰጠኝ ከጸለይኩ በኋላ ማስታወቂያዬን እንደያዝኩ ቆምኩ። በዚህ ወቅት ሰው ምን ይለኛል የሚለውን ፍርሃት ማሸነፌ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነትን በተመለከተ ወደፊት ለሚጠብቀኝ ከባድ ፈተና አዘጋጅቶኛል።
ከጊዜ በኋላ የአገሪቱ መንግሥት እኔም ሆንኩ ሌሎች በርካታ ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች ለወታደራዊ አገልግሎት እንድንመዘገብ አዘዘ። በታዘዝነው መሠረት ወደ ወታደሮች ጦር ሰፈር ብንሄድም የደንብ ልብስ እንደማንለብስ በአክብሮት ነገርናቸው። የጦር መኮንኖቹ በጥበቃ ሥር ካዋሉን በኋላ ብዙም ሳይቆይ ፍርድ ቤት ቀርበን የስድስት ወር እስራት ተበየነብን። ከዚህም በላይ ወታደራዊ አገልግሎት እንድንሰጥ የሚጠበቅብንን ጊዜ ለማካካስ ብለው ተጨማሪ ስምንት ወር ፈረዱብን። ስለዚህ በገለልተኝነት አቋማችን ምክንያት በጠቅላላው ለአንድ ዓመት ከሁለት ወር ወኅኒ ቤት ቆየን።
በእስር ቤት እያለን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት በየቀኑ እንገናኝ ነበር። በእነዚያ ወራት ብዙዎቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ሁለት ጊዜ አንብበነዋል። የእስራት ጊዜያችንን ጨርሰን ከወኅኒ ስንወጣ አብዛኞቻችን ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይሖዋን ለማገልገል ቆርጠን ነበር። በወቅቱ ከነበሩት ወጣት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አብዛኞቹ በአሁኑ ሰዓት ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
ከእስር ቤት እንደወጣሁ ከወላጆቼ ጋር መኖር ጀመርኩ። ከትንሽ ጊዜ በኋላም ቬራ ከተባለች በቅርቡ ከተጠመቀች ቀናተኛ እህት ጋር ተዋወቅንና በ1957 ተጋባን።
ሕይወታችንን የለወጠ ምሽት
አንድ ምሽት ላይ በቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት ከሚሠሩ የተወሰኑ ወንድሞች ጋር እየተጨዋወትን ሳለ ከመካከላቸው አንዱ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል እንፈልግ እንደሆነ ጠየቀን። ሌሊቱን ሙሉ ስንጸልይ ካደርን በኋላ በማግሥቱ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮ ደውዬ ፈቃደኛ መሆናችንን ገልጽኩላቸው። ለእኔ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት ጠቀም ያለ ገንዘብ የሚያስገኝልኝን ሥራ መተው ይጠይቅብኝ ነበር፤ ሆኖም በሕይወታችን ውስጥ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ቆርጠን ነበር። በታኅሣሥ 1957 የወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ስንጀምር እኔ 23 ቬራ ደግሞ 19 ዓመቷ ነበር። በፊንላንድ የሚገኙትን ጉባኤዎች በመጎብኘትና የይሖዋን ሕዝቦች በማበረታታት ያሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት አስደሳች ነበሩ።
በ1960 መጨረሻ አካባቢ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ በሚገኘው ጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት እንድካፈል ግብዣ ቀረበልኝ። ከፊንላንድ የሄድነው ሦስት ወንድሞች የቅርንጫፍ ቢሮን በበላይነት ለመከታተል የሚያስችል አሥር ወር የሚፈጅ ልዩ ኮርስ ተሰጠን። ሚስቶቻችን ግን አብረውን አልሄዱም፤ ከዚህ ይልቅ በፊንላንድ የቅርንጫፍ ቢሮ እያገለገሉ ቆዩን።
ኮርሱ ከማለቁ ትንሽ ቀደም ብሎ የዓለም አቀፉን የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ በበላይነት ወደሚመራው ወደ ናታን ኖር ሄጄ ሪፖርት እንዳደርግ ተነገረኝ። ወንድም ኖር፣ እኔና ባለቤቴ አሁን ማዳጋስካር ተብላ በምትጠራው በማላጋሲ ሪፑብሊክ በሚስዮናዊነት ማገልገል እንችል እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ቬራ ወደዚያ ሄዳ ማገልገል ትፈልግ እንደሆነ በደብዳቤ ጠይቅኋት፤ እርሷም በፍጥነት “አዎን” የሚል መልስ ላከችልኝ። ፊንላንድ ከተመለስኩ በኋላ ወደ ማዳጋስካር ቶሎ ለመሄድ ዝግጅት ማድረግ ጀመርን።
ደስታና ሐዘን
በጥር 1962 የአገሪቷ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ አንታናናሪቮ በረርን። ፊንላንድ ክረምት ስለነበር ባለ ጸጉር ኮፍያ አድርገን እንዲሁም ወፍራም ካፖርት ደርበን ነበር። ሞቃታማ ወደሆነው ወደ ማዳጋስካር ስንደርስ ግን አለባበሳችንን በፍጥነት ቀየርን። መጀመሪያ የኖርነው አንድ መኝታ ክፍል ብቻ ባላት ትንሽ የሚስዮናውያን ቤት ውስጥ ነበር። በዚያች ቤት ውስጥ አንድ ሚስዮናውያን ባልና ሚስት ይኖሩባት ስለነበር እኔና ቬራ በረንዳው ላይ አደርን።
ብዙም ሳይቆይ የማዳጋስካር ብሔራዊ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛን መማር ጀመርን። ሆኖም ትምህርቱ በጣም አስቸጋሪ ነበር፤ ምክንያቱም ከአስተማሪያችን ከእህት ካርቦኖ ጋር የሚያግባባን አንድ የጋራ ቋንቋ አልነበረንም። እህት ካርቦኖ ፈረንሳይኛ የምታስተምረን በእንግሊዝኛ ሲሆን ቬራ ደግሞ እንግሊዝኛ መናገር አትችልም። ስለዚህ እህት ካርቦኖ የምትሰጠንን ትምህርት በፊንላንድ ቋንቋ ተርጉሜ ለቬራ መንገር ነበረብኝ። ይሁንና ቬራ ከሰዋስው ጋር የተያያዙ ነጥቦችን በተሻለ መንገድ የምትረዳው በስዊድንኛ ቋንቋ መሆኑን ስላስተዋልን የፈረንሳይኛን ሰዋስው በስዊድንኛ አስረዳት ጀመር። ፈረንሳይኛን በደንብ እያወቅን ስንመጣ የአገሪቱን ቋንቋ ማለጋሲን ማጥናት ጀመርን።
ማዳጋስካር ውስጥ የመጀመሪያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ የሚናገረው ቋንቋ ማለጋሲ ብቻ ነበር። ጥቅሶችን በፊንላንድ ቋንቋ ከተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱሴ ካወጣሁ በኋላ ከማለጋሲ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ደግሞ መፈለግ እንጀምራለን። ጥቅሶችን ያን ያህል ላብራራለት ባልችልም እንኳ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ዘር በልቡ ውስጥ አድጎ እስከ መጠመቅ ደርሷል።
በ1963 ብሩክሊን በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚሠራው ሚልተን ሄንሽል ወደ ማዳጋስካር መጥቶ ነበር። በኋላም በማዳጋስካር አዲስ ቅርንጫፍ ቢሮ የተቋቋመ ሲሆን የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኜ ከማከናውነው ሥራ በተጨማሪ የቢሮው የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተሾምኩ። ይሖዋ በእነዚህ ጊዜያት ሁሉ ብዙ በረከቶች አፍስሶልናል። ከ1962 እስከ 1970 ባሉት ዓመታት በማዳጋስካር የነበረው የመንግሥቱ አስፋፊዎች ቁጥር ከ85 ወደ 469 አድጓል።
በ1970 አንድ ቀን ከአገልግሎት ስንመለስ የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሚስዮናውያን በሙሉ ለአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚያዝዝ ወረቀት በራችን ላይ ተቀምጦ አገኘን። በሚኒስትሩ ቢሮ የሚሠራ አንድ ባለ ሥልጣን፣ መንግሥት በፍጥነት አገሪቷን ለቅቀን እንድንወጣ ማዘዙን ነገረን። ምን ወንጀል እንደሠራን ስጠይቀው “ሚስተር ክዎካነን፣ ምንም አላጠፋችሁም” ብሎ መለሰልኝ።
“ለስምንት ዓመት ያህል እዚህ ኖረናል፤ ማዳጋስካር እኮ አገራችን ናት። ያለምንም ምክንያት እንዴት እንባረራለን?” አልኩት። ብዙ ጥረት ብናደርግም ሁላችንም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንድንለቅ ተወሰነብን። ቅርንጫፍ ቢሮው የተዘጋ ሲሆን የአገሬው ተወላጅ የሆነ አንድ ወንድም የስብከት ሥራውን በበላይነት መከታተል ጀመረ። በማዳጋስካር የሚገኙትን ውድ ወንድሞቻችንን ትተን ከመሄዳችን በፊት በኡጋንዳ እንድናገለግል አዲስ ምድብ ተሰጠን።
እንደ አዲስ ጀመርን
ከማዳጋስካር ከወጣን ከጥቂት ቀናት በኋላ የኡጋንዳ ዋና ከተማ ካምፓላ ደረስን። ወዲያውኑም ማራኪ ቅላጼ ያለውን ሆኖም ለመማር አስቸጋሪ የሆነውን ሉጋንዳ ቋንቋ መማር ጀመርን። ከሁሉም በፊት ግን ሌሎች ሚስዮናውያን ቬራን እንግሊዝኛ ስላስተማሯት በእንግሊዝኛ ቋንቋ ውጤታማ ምሥክርነት መስጠት ቻልን።
ሞቃታማና እርጥበት አዘል የሆነው የካምፓላ የአየር ንብረት ለቬራ ጤንነት ስላልተስማማት የተሻለ የአየር ንብረት ወዳለው ወደ እምባራራ ከተማ ተዛወርን። በቦታው የነበርነው የይሖዋ ምሥክሮች እኛ ብቻ ብንሆንም አገልግሎት በወጣንበት በመጀመሪያው ቀን አስደሳች ሁኔታ አጋጠመን። ከአንድ ሰው ጋር እቤቱ ሆነን እየተነጋገርን ሳለ ባለቤቱ ከማድቤት ወጣች። ማርጋሬት የምትባለው ይህች ሴት የምናገረውን ነገር ታዳምጥ ነበር። ማርጋሬት ከቬራ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከጀመረች በኋላ በመንፈሳዊ ፈጣን እድገት በማድረግ የተጠመቀች ቀናተኛ የመንግሥቱ አስፋፊ ሆነች።
የጎዳና ላይ ጦርነት
በ1971 የተቀሰቀሰው የእርስ በርስ ጦርነት በኡጋንዳ የነበረንን ሰላም አደፈረሰው። አንድ ቀን እምባራራ በሚገኘው ሚስዮናዊ ቤታችን አቅራቢያ ጦርነት ተነሳ። በዚህ ተሞክሮ መጀመሪያ ላይ የጠቀስኩት ሁኔታ የተከሰተው ይኼኔ ነበር።
ወታደሮቹ እንዳያዩኝ በቦዩ ውስጥ በደረቴ እየተሳብኩ በመሄድ ወደ ሚስዮናውያን ቤታችን ስደርስ ቬራን እዚያው አገኘኋት። ፍራሾችንና የቤት ዕቃዎቻችንን አነባብረን በቤታችን አንድ ጥግ ላይ “ምሽግ” አበጀን። ከዚያም ሁኔታውን በሬዲዮ እየተከታተልን ለአንድ ሳምንት ከቤታችን ሳንወጣ ቆየን። ምሽጋችን ውስጥ ኩርምት ብለን ተቀምጠን እንዳለ አንዳንድ ጊዜ ጥይት የቤታችንን ግድግዳ ሲመታ እንሰማ ነበር። እቤት ውስጥ መሆናችን እንዳይታወቅ ብለን ማታ ማታ መብራት አናበራም። አንድ ቀን ወታደሮች ደጃፍ ላይ ቆመው መጮህ ጀመሩ። በልባችን ወደ ይሖዋ እየጸለይን ዝም ብለን ቁጭ አልን። ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ጎረቤቶቻችን ይሖዋ ሁላችንንም እንደጠበቀን ስለተሰማቸው ወደ እኛ እየመጡ አመሰገኑን፤ እኛም በሐሳባቸው ተስማምተናል።
አንድ ቀን ጠዋት በሬዲዮ የኡጋንዳ መንግሥት የይሖዋ ምሥክሮችን እንቅስቃሴ እንዳገደ የሚናገር ዜና እስከሰማንበት ጊዜ ድረስ ሁኔታዎች ተረጋግተው ነበር። ዜናውን ያቀረበው ሰው ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቀድሞው ሃይማኖታቸው መመለስ እንዳለባቸው ተናገረ። የእኛን ጉዳይ በተመለከተ ለመንግሥት ባለ ሥልጣናት አቤቱታ ባቀርብም እንኳ ምንም ውጤት አላገኘሁም። ከዚያም ወደ ፕሬዚዳንት ኢዲ አሚን ቢሮ ሄድኩና ቀጠሮ እንዲያዝልኝ ጠየቅኳቸው። እንግዳ መቀበያ ክፍል የሚሠራው ሰው ፕሬዚዳንቱ ሥራ እንደበዛባቸው ነገረኝ። ብዙ ጊዜ ተመላልሼ ብሄድም ፕሬዚዳንቱን ገብቼ ማነጋገር አልቻልኩም። በመጨረሻም ሐምሌ 1973 ከኡጋንዳ እንድንወጣ ተደረገ።
ለአንድ ዓመት ሄደን አሥር ዓመት ቆየን
በኡጋንዳ ያሉትን ውድ ወንድሞቻችንን ስንለይ የተሰማን የሐዘን ስሜት ከማዳጋስካር ስንባረር የነበረንን ሁኔታ አስታወሰን። ወደ አዲሱ የሥራ ምድባችን ወደ ሴኔጋል ከመጓዛችን በፊት ፊንላንድ ሄድን። ፊንላንድ እያለን በአፍሪካ የተሰጠን የሥራ ምድብ ተሰረዘና እዚያው እንድንቆይ ተነገረን። ከዚያ በኋላ በሚስዮናዊነት መቀጠል የማንችል መስሎን ነበር። በፊንላንድ ልዩ አቅኚዎች ሆነን ካገለገልን በኋላ እንደገና በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ማገልገል ጀመርን።
በ1990 ማዳጋስካር ውስጥ በሥራችን ላይ ተነስቶ የነበረው ተቃውሞ ጋብ በማለቱ ለአንድ ዓመት ያህል በዚያ ማገልገል እንችል እንደሆነ የሚጠይቅ ደብዳቤ ብሩክሊን ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤት ሲደርሰን በጣም ተገረምን። የመሄድ ፍላጎት ቢኖረንም ሁለት ከባድ ችግሮች ተጋርጠውብን ነበር። አረጋዊው አባቴ እንክብካቤ የሚያስፈልገው ሲሆን ቬራ ደግሞ ጥሩ ጤንነት አልነበራትም። አባቴ ኅዳር 1990 ሲሞት በጣም አዘንኩ። ይሁንና የቬራ ጤንነት መሻሻሉ ወደ ሚስዮናዊነት የመመለስ ተስፋችንን ብሩህ አደረገው። ከዚያም መስከረም 1991 ወደ ማዳጋስካር ተመለስን።
ወደ ማዳጋስካር የተላክነው ለአንድ ዓመት ቢሆንም አሥር ዓመት ቆየን። በዚህ ወቅት የአስፋፊዎች ቁጥር ከ4,000 ወደ 11,600 አድጓል። ሚስዮናዊ ሆኜ በማገልገሌ በጣም ተደስቻለሁ። ሆኖም የባለቤቴን አካላዊና ስሜታዊ ፍላጎቶች ችላ ብዬ ይሆን? እያልኩ በማሰብ ያዘንኩባቸው ወቅቶች ነበሩ። ይሖዋ ሁለታችንም በሥራችን እንድንቀጥል ጥንካሬ ሰጥቶናል። በመጨረሻም ከ2001 ጀምሮ ወደ ፊንላንድ ተመልሰን በቅርንጫፍ ቢሮው እየሠራን ነው። ለመንግሥቱ ሥራ ያለን ቅንዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረ ሲሆን በአፍሪካ ስላሳለፍነው ልዩ ጊዜም ስናስብ እንደሰታለን። ይሖዋ የትም ቦታ ቢመድበን የእርሱን ፈቃድ ለመፈጸም ቆርጠናል።—ኢሳይያስ 6:8
[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ፊንላንድ
አውሮፓ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
አፍሪካ
ማዳጋስካር
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
አፍሪካ
ኡጋንዳ
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሠርጋችን ዕለት
[በገጽ 14 እና 15 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በ1960 በፊንላንድ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ስናገለግል
በ1962 በማዳጋስካር በሚስዮናዊነት ስንሠራ
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአሁኑ ጊዜ ከቬራ ጋር