ጎረቤትን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
“ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ።”—ማቴዎስ 22:39
1. አምላክን እንደምንወድ እንዴት ማሳየት እንችላለን?
ይሖዋ እርሱን ከሚያመልኩት ሰዎች ምን ይፈልጋል? ኢየሱስ ቀለል ባሉ ግን ጥልቅ ትርጉም ባላቸው ቃላት የዚህን ጥያቄ መልስ በአጭሩ ገልጿል። ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ ይሖዋን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኃይልህ ውደድ የሚለው እንደሆነ ገልጿል። (ማቴዎስ 22:37፤ ማርቆስ 12:30) በፊተኛው ርዕስ ላይ እንደተመለከትነው አምላክን መውደድ ላሳየን ፍቅር ምላሽ ለመስጠት እርሱን መታዘዝንና ትእዛዛቱን መጠበቅን ይጨምራል። አምላክን የሚወድዱ ሰዎች ፈቃዱን ማድረግ ሸክም አይሆንባቸውም፤ ከዚህ ይልቅ ደስታ ያስገኝላቸዋል።—መዝሙር 40:8፤ 1 ዮሐንስ 5:2, 3
2, 3. ጎረቤቶቻችንን እንድንወድ የተሰጠንን ትእዛዝ በቁም ነገር መመልከት ያለብን ለምንድን ነው? ምን ጥያቄዎችስ ይነሳሉ?
2 ኢየሱስ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚለው ሁለተኛው ታላቅ ትእዛዝ ከፊተኛው ጋር ዝምድና እንዳለው ገልጿል። (ማቴዎስ 22:39) አሁን ትኩረት የምናደርገው በዚህ ትእዛዝ ላይ ሲሆን ይህን ለማድረግ ደግሞ በቂ ምክንያት አለን። የምንኖርበት ዓለም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍቅር በማሳየቱና ለፍቅር የተዛባ ትርጉም በመስጠቱ ተለይቶ ይታወቃል። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የመጨረሻውን ዘመን’ አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ላይ ሰዎች እርስ በርሳቸው ከመዋደድ ይልቅ ራሳቸውን፣ ገንዘብንና ተድላን የሚወዱ እንደሚሆኑ ተናግሯል። ብዙዎች “ፍቅር [“የተፈጥሮ ፍቅር፣” NW] የሌላቸው” ወይም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም እንዳለው “በቤተሰብ መካከል የሚታየው ተፈጥሯዊ የፍቅር ስሜት” የሌላቸው ሆነዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) ኢየሱስ ክርስቶስ “ብዙዎች . . . እርስ በርስ አሳልፈው ይሰጣጣሉ፤ ይጠላላሉም። . . . የብዙ ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” በማለት አስቀድሞ ተናግሯል።—ማቴዎስ 24:10, 12
3 ይሁንና ኢየሱስ የሁሉም ሰዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል እንዳላለ ልብ በል። ይሖዋ የሚፈልገውንና ለእርሱ የሚገባውን ፍቅር ያሳዩ ሰዎች ከዚህ በፊት ነበሩ፤ ወደፊትም ይኖራሉ። ለይሖዋ እውነተኛ ፍቅር ያላቸው ሰዎች ሌሎችን እርሱ እንደሚያያቸው ለማየት ይጥራሉ። ሆኖም ልንወዳቸው የሚገባን ጎረቤቶቻችን እነማን ናቸው? ጎረቤቶቻችንን እንደምንወድ እንዴት ማሳየት እንችላለን? መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊ ለሆኑት ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
ባልንጀራዬ ማን ነው?
4. በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 መሠረት አይሁዳውያን እነማንን መውደድ ነበረባቸው?
4 ኢየሱስ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጠው ትእዛዝ ጎረቤትህን እንደራስህ ውደድ የሚለው እንደሆነ ለፈሪሳዊው በነገረው ጊዜ ለእስራኤላውያን ተሰጥቷቸው የነበረውን አንድ ሕግ መጥቀሱ ነበር። ይህ ሕግ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። በዚሁ ምዕራፍ ላይ አይሁዳውያን እስራኤላውያንን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሰዎችንም እንደ ባልንጀሮቻቸው ወይም ጎረቤቶቻቸው አድርገው እንዲመለከቷቸው ተነግሯቸዋል። ቁጥር 34 እንዲህ ይላል:- “አብሮአችሁ የሚኖረው መጻተኛ እንደ ገዛ ወገናችሁ ይታይ፤ እንደ ራሳችሁም ውደዱት፤ እናንተም በግብፅ መጻተኞች ነበራችሁና።” በመሆኑም አይሁዳዊ ያልሆኑትን ጭምር በተለይ ደግሞ ወደ ይሁዲነት የተለወጡ ሰዎችን በፍቅር መያዝ ነበረባቸው።
5. አይሁዶች ‘ጎረቤትህን ውደድ’ የሚለውን ትእዛዝ የሚረዱት እንዴት ነበር?
5 ይሁንና በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ጉዳዩን የሚመለከቱት በተለየ መልኩ ነበር። አንዳንዶቹ “ወዳጅ” እና “ጎረቤት” የሚሉት ቃላት የሚያመለክቱት አይሁዳዊ የሆነን ሰው ብቻ እንደሆነ አድርገው ያስተምሩ ነበር። እንደ እነርሱ አመለካከት ከሆነ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች መጠላት ይኖርባቸዋል። እነዚህ አስተማሪዎች አምላክን የሚያመልኩ ሰዎች አምላክ የለሾችን መጥላት አለባቸው ብለው ይከራከራሉ። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ ጥላቻ እየከሰመ ሊሄድ አይችልም። እንዲያውም የሚያቀጣጥለው ሁኔታ ይበዛል” ብሏል።
6. ኢየሱስ ጎረቤትን ስለመውደድ በተናገረ ጊዜ ምን ሁለት ነጥቦችን ገልጿል?
6 ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ስለዚህ ጉዳይ በተናገረ ጊዜ ሊወደድ የሚገባው ማን እንደሆነ ግልጽ አድርጓል። እንዲህ አለ:- “‘ወዳጅህን ውደድ፤ ጠላትህን ጥላ’ እንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ጠላቶቻችሁን ውደዱ፤ ለሚያሳድዷችሁም ጸልዩ እላችኋለሁ። እንደዚህም በማድረጋችሁ በሰማይ ላለው አባታችሁ ልጆች ትሆናላችሁ፤ እርሱ ፀሓዩን ለክፉዎችና ለደጎች ያወጣል፤ ዝናቡንም ለኀጢአተኞችና ለጻድቃን ያዘንባል።” (ማቴዎስ 5:43-45) እዚህ ላይ ኢየሱስ ሁለት ነጥቦችን ጠቅሷል። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ይሖዋ ለደጎችም ሆነ ለክፉዎች ቸርነትንና ደግነት ያደርጋል። በሁለተኛ ደረጃ፣ እኛም የእርሱን ምሳሌ መከተል አለብን።
7. ስለ ደጉ ሳምራዊ ከሚናገረው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 በአንድ ወቅት ሕጉን ጠንቅቆ የሚያውቅ አንድ አይሁዳዊ ኢየሱስን “ባልንጀራዬ ማን ነው?” ሲል ጠየቀው። ኢየሱስም ወንበዴዎች ደብድበውትና ንብረቱን ዘርፈውት የሄዱትን አይሁዳዊ ስላገኘ አንድ ሳምራዊ የሚገልጸውን ምሳሌ በመንገር ጥያቄውን መለሰለት። በጥቅሉ ሲታይ አይሁዳውያን ለሳምራውያን ንቀት የነበራቸው ቢሆንም ሳምራዊው የሰውየውን ቁስል ጠራርጎ ካሰረለት በኋላ ማገገም የሚችልበትን ተጨማሪ ዝግጅት አድርጎለታል። ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር ከእኛ ጋር ተመሳሳይ ዘር፣ ብሔር ወይም ሃይማኖት ካላቸው ሰዎች አልፎ መሄድ አለበት።—ሉቃስ 10:25, 29, 30, 33-37
ጎረቤትን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
8. ዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ፍቅር ማሳየት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ምን ይላል?
8 አምላክን መውደድ ተግባርን እንደሚጨምር ሁሉ ጎረቤትን መውደድም እንዲያው የስሜት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በድርጊትም የሚገለጽ ነው። የአምላክ ሕዝቦች ጎረቤቶቻቸውን እንደራሳቸው መውደድ እንዳለባቸው አበክሮ በሚገልጸው በዘሌዋውያን ምዕራፍ 19 ላይ በሰፈረው ትእዛዝ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ጠለቅ ብለን መመርመራችን ጠቃሚ ነው። በዚህ ምዕራፍ ላይ እስራኤላውያን መከር በሚሰበስቡበት ጊዜ ያገኙትን ምርት ለችግረኞችና ለመጻተኞች እንዲያካፍሉ መታዘዛቸውን እናነባለን። ስርቆት፣ ማታለልና ውሸት በእነርሱ ዘንድ ቦታ ሊኖራቸው አይገባም። ፍርድ ነክ በሆኑ ጉዳዮች ረገድ አድሎ ከመፈጸም መቆጠብ ነበረባቸው። አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ወንድሞቻቸውን መገሠጽ ይችሉ የነበረ ቢሆንም “ወንድምህን በልብህ አትጥላው” የሚል ቀጥተኛ ትእዛዝ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህና ሌሎች በርካታ ትእዛዛት “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” በሚሉት ቃላት ሥር ተጠቃለዋል።—ዘሌዋውያን 19:9-11, 15, 17, 18
9. ይሖዋ እስራኤላውያንን ከሌሎች ብሔራት የተለዩ እንዲሆኑ ያዘዛቸው ለምንድን ነው?
9 እስራኤላውያን ሌሎችን መውደድ ያለባቸው ቢሆንም የሐሰት አማልክትን ከሚያመልኩ ሰዎች የተለዩ መሆን ነበረባቸው። ይሖዋ መጥፎ ወዳጅነት የሚያስከትለውን አደጋና መዘዝ በመንገር አስጠንቅቋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ እስራኤላውያን ከሚወርሱት ምድር ያባረሯቸውን ሰዎች አስመልክቶ ይሖዋ እንዲህ የሚል ትእዛዝ ሰጥቷቸዋል:- “ከእነርሱ ጋር ጋብቻ አታድርግ፤ ሴት ልጆችህን ለወንድ ልጆቻቸው አትስጥ፤ ወይም ለወንድ ልጆችህ ሴት ልጆቻቸውን አታምጣ፤ ምክንያቱም እኔን ከመከተል ልጆችህን መልሰው ሌሎችን አማልክት እንዲያመልኩ ስለሚያደርጉና ከዚህም የተነሣ የእግዚአብሔር ቍጣ በላይህ ነዶ፣ ፈጥኖ ስለሚያጠፋህ ነው።”—ዘዳግም 7:3, 4
10. ከምን ነገር ራሳችንን መጠበቅ ይኖርብናል?
10 በተመሳሳይም ክርስቲያኖች እምነታቸውን ሊያዳክሙባቸው ከሚችሉ ሰዎች ራሳቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። (1 ቆሮንቶስ 15:33) “ከማያምኑ” ይኸውም የክርስቲያን ጉባኤ አባል ካልሆኑ “ሰዎች ጋር አግባብ ባልሆነ መንገድ አትጠመዱ” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ከዚህም በተጨማሪ ክርስቲያኖች “በጌታ” ብቻ እንዲያገቡ ተመክረዋል። (1 ቆሮንቶስ 7:39) ይሁንና እንደ እኛ በይሖዋ ላይ እምነት የሌላቸውን ሰዎችን ፈጽሞ መናቅ የለብንም። ክርስቶስ የሞተው ለኃጢአተኞች ከመሆኑም ባሻገር ከዚህ ቀደም ክፉ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ የነበሩ ብዙዎች አካሄዳቸውን መለወጥና ከአምላክ ጋር መታረቅ ችለዋል።—ሮሜ 5:8፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9-11
11. የይሖዋ አገልጋይ ላልሆኑ ሰዎች ፍቅር እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ከሁሉ የላቀው መንገድ ምንድን ነው? ለምንስ?
11 የአምላክ አገልጋይ ላልሆኑ ሰዎች ፍቅርን ማሳየት የምንፈልግ ከሆነ ይሖዋን ከመኮረጅ የተሻለ ልናደርገው የምንችለው ነገር የለም። አምላክ ክፋትን የሚጠላ ቢሆንም ሰዎች ሁሉ ከመጥፎ ጎዳናቸው ተመልሰው የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉበትን አጋጣሚ በመክፈት ፍቅራዊ ደግነት አሳይቷቸዋል። (ሕዝቅኤል 18:23) ይሖዋ “ሁሉ ለንስሓ እንዲበቃ” ይፈልጋል። (2 ጴጥሮስ 3:9) የእርሱ ፈቃድ “ሰዎች ሁሉ እንዲድኑና እውነትን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ” ነው። (1 ጢሞቴዎስ 2:4) ኢየሱስም ለተከታዮቹ የመስበክ፣ የማስተማርና ‘ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት የማድረግ’ ተልእኮ የሰጣቸው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 28:19, 20) እኛም በዚህ ሥራ ላይ በመሳተፍ አምላክንም ሆነ ጎረቤቶቻችንን ሌላው ቀርቶ ጠላቶቻችንን ጭምር እንደምንወድ እናሳያለን!
ክርስቲያን ወንድሞቻችንን መውደድ
12. ሐዋርያው ዮሐንስ ለወንድማችን ፍቅር ማሳየትን አስመልክቶ ምን በማለት ጽፏል?
12 ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሰው ሁሉ፣ በተለይም ለእምነት ቤተ ሰቦች መልካም እናድርግ” በማለት ጽፏል። (ገላትያ 6:10) ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለእምነት ቤተሰቦቻችን ማለትም ለመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍቅር የማሳየት ግዴታ አለብን። እንዲህ መሰሉን ፍቅር ማሳየታችን ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ይህን ትልቅ ቁም ነገር አስመልክቶ እንደሚከተለው ሲል ጽፏል:- “ወንድሙን የሚጠላ ነፍሰ ገዳይ ነው። ማንም፣ ‘እግዚአብሔርን እወደዋለሁ’ እያለ ወንድሙን ቢጠላ፣ እርሱ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን መውደድ አይችልምና።” (1 ዮሐንስ 3:15፤ 4:20) እነዚህ ቃላት ኃይለኛ መልእክት ይዘዋል። ኢየሱስ ክርስቶስ “ነፍሰ ገዳይ” እና “ሐሰተኛ” የሚሉትን ቃላት ሰይጣን ዲያብሎስን ለማመልከት ተጠቅሞባቸዋል። (ዮሐንስ 8:44) እኛ ግን እንዲህ ተብለን መጠራት ፈጽሞ አንፈልግም!
13. የእምነት አጋሮቻችንን እንደምንወዳቸው በምን መንገዶች ማሳየት እንችላለን?
13 እውነተኛ ክርስቲያኖች ‘እርስ በርስ መዋደድ እንዳለባቸው ከአምላክ ተምረዋል።’ (1 ተሰሎንቄ 4:9) “በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ” መዋደድ የለብንም። (1 ዮሐንስ 3:18) ፍቅራችን “ያለ ግብዝነት” መሆን ይኖርበታል። (ሮሜ 12:9) ፍቅር የምንመቀኝ፣ የምንመካ፣ የምንታበይ ወይም ራሳችንን የምንወድ ከመሆን ይልቅ ቸር፣ ሩኅሩኅ፣ ይቅር ባይና ትዕግሥተኛ እንድንሆን ያነሳሳናል። (1 ቆሮንቶስ 13:4, 5፤ ኤፌሶን 4:32) ‘አንዳችን ሌላውን እንድናገለግል’ ይገፋፋናል። (ገላትያ 5:13) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እርሱ እንደወደዳቸው ሁሉ እነርሱም እርስ በርስ እንዲዋደዱ ነግሯቸዋል። (ዮሐንስ 13:34) በመሆኑም አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ አንድ ክርስቲያን ለእምነት አጋሮቹ ሲል ሕይወቱን እንኳ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆን ይኖርበታል።
14. በቤተሰብ ውስጥ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
14 ከዚህም ባሻገር ፍቅር በክርስቲያን ቤተሰቦች፣ በተለይም ደግሞ በባልና ሚስት መካከል በግልጽ ሊታይ ይገባል። ጳውሎስ የትዳር ጥምረት ምን ያህል የተቀራረበ መሆን እንዳለበት ሲገልጽ “ባሎችም እንደዚሁ ሚስቶቻቸውን እንደ ገዛ ሥጋቸው መውደድ ይገባቸዋል” ብሏል። አክሎም “ሚስቱን የሚወድ ራሱን ይወዳል” ሲል ተናግሯል። (ኤፌሶን 5:28) ጳውሎስ ከአምስት ቁጥሮች በኋላ ይህንኑ ማሳሰቢያ በድጋሚ መስጠቱን ማስተዋል እንችላለን። ሚስቱን የሚወድ ባል፣ የትዳር አጋሮቻቸውን የካዱትን በሚልክያስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ እስራኤላውያንን ምሳሌ መከተል አይፈልግም። (ሚልክያስ 2:14) ከዚህ ይልቅ ሚስቱን ይንከባከባታል። ልክ ክርስቶስ ጉባኤውን እንደወደደ እርሱም ሚስቱን ይወዳል። ፍቅር አንዲት ሚስትም ለባልዋ ተመሳሳይ ነገር እንድታደርግ ይገፋፋታል።—ኤፌሶን 5:25, 29-33
15. የወንድማማች ፍቅር በተግባር ሲገለጽ የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ምን ብለው ተናግረዋል? ምንስ ለማድረግ ተገፋፍተዋል?
15 እንዲህ መሰሉ ፍቅር የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ ምልክት መሆኑ ግልጽ ነው። ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ብትዋደዱ፣ ሰዎች ሁሉ የእኔ ደቀ መዛሙርት እንደ ሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐንስ 13:35) እርስ በርስ ያለን ፍቅር ሰዎች ወደምንወደውና ወደምንወክለው አምላክ እንዲሳቡ ያደርጋቸዋል። ለአብነት ያህል፣ ስለ አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤተሰብ የሚዘግብ ከሞዛምቢክ የተገኘ ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “እንዲህ ያለ ነገር ፈጽሞ አይተን አናውቅም። አንድ ቀን ከሰዓት በኋላ ከባድ ዝናብና በረዶ የቀላቀለ ኃይለኛ ነፋስ መንፈስ ጀመረ። ኃይለኛው ነፋስ በሣር የተሠራው ቤታችንን እንዳልነበረ አደረገው፤ እንዲሁም ቆርቆሮውን ይዞት ሄደ። በኋላም በአቅራቢያችን ካሉ ጉባኤዎች የመጡ ወንድሞች ቤታችንን መልሰን እንድንሠራ ሲያግዙን ጎረቤቶቻችን በአድናቆት ተውጠው ‘ሃይማኖታችሁ በጣም ጥሩ ነው። ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለ እርዳታ ተደርጎልን አያውቅም’ በማለት ተናግረዋል። እኛም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዮሐንስ 13:34, 35ን አሳየናቸው። አሁን አብዛኞቹ ጎረቤቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ይገኛሉ።”
ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ መውደድ
16. ለሰዎች በቡድን ደረጃ ፍቅር በማሳየትና እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ በመውደድ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
16 ጎረቤቶቻችንን በጥቅሉ ይኸውም በቡድን ደረጃ መውደድ ያን ያህል አስቸጋሪ አይደለም። ይሁንና እያንዳንዱን ሰው በግለሰብ ደረጃ መውደድ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ሰዎች ለጎረቤቶቻቸው ያላቸው ፍቅር ለአንድ በጎ አድራጎት ድርጅት የገንዘብ መዋጮ ከማድረግ አልፎ አይሄድም። እውነት ነው፣ ጎረቤቶቼን እወዳቸዋለሁ ብሎ መናገር፣ ለእኛ ደንታ የሌለው የሥራ ባልደረባችንን፣ ተጨቃጫቂ የሆነ ጎረቤታችንን አሊያም በጣም የሚያበሳጨን ወዳጃችንን ከመውደድ ጋር ሲነጻጻር እጅግ ቀላል ነው።
17, 18. ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነው? ይህን እንዲያደርግ ያነሳሳውስ ምን ነበር?
17 ሰዎችን በግለሰብ ደረጃ መውደድን በተመለከተ የአምላክን ባሕርያት በሚገባ ካንጸባረቀው ከኢየሱስ የምንማረው ነገር ይኖረናል። ወደ ምድር የመጣው የዓለምን ኃጢአት ለማስወገድ ቢሆንም እንኳ ታማ ለነበረች ሴት፣ በለምጽ ለተያዘ ሰውና ለአንዲት ልጅ እንዲሁም ለሌሎች ሰዎች በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት አሳይቷል። (ማቴዎስ 9:20-22፤ ማርቆስ 1:40-42፤ 7:26, 29, 30፤ ዮሐንስ 1:29) እኛም በተመሳሳይ በየቀኑ ከምናገኛቸው ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ጎረቤቶቻችንን እንደምንወድ እናሳያለን።
18 ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር ለአምላክ ካለን ፍቅር ጋር የተቆራኘ መሆኑን ፈጽሞ መዘንጋት አይኖርብንም። ኢየሱስ ድሆችን የረዳ፣ የታመሙትን የፈወሰና የተራቡትን የመገበ ቢሆንም ይህን ያደረገውና ሕዝቡን ያስተማረው ሰዎችን ከይሖዋ ጋር ለማስታረቅ ነበር። (2 ቆሮንቶስ 5:19) ኢየሱስ ሁሉን ያደረገው ለአምላክ ክብር ሲሆን የሚወደውን አምላክ እንደሚወክልና የእርሱን ማንነት እንደሚያንጸባርቅ ፈጽሞ ዘንግቶ አያውቅም። (1 ቆሮንቶስ 10:31) እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል፣ ለጎረቤቶቻችን እውነተኛ ፍቅር እንዳለን እናሳያለን፤ ከዚሁ ጎን ለጎን ምንጊዜም የዚህ ክፉ የሰው ዘር ዓለም ክፍል ላለመሆን እንጥራለን።
ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን መውደድ የምንችለው እንዴት ነው?
19, 20. ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
19 ኢየሱስ “ጎረቤትህን እንደ ራስህ ውደድ” ብሏል። ስለ ራሳችን ማሰባችንና ጤናማ አመለካከት ማዳበራችን ያለ ነገር ነው። እንዲህ ባይሆን ኖሮ ይህ ሕግ ትርጉም አይኖረውም ነበር። ራስን በተገቢው መንገድ መውደድ ሐዋርያው ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 3:2 ላይ ከጠቀሰው የራስ ወዳድነት ስሜት ጋር አንድ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ለራሳችን ምክንያታዊ የሆነ ጥሩ ግምት እንዳለን የሚያሳይ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑር “ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ራስን መውደድ ‘የሚያህለኝ የለም’ በሚል ስሜት ራስን ያለ ልክ ከፍ አድርጎ ከመመልከት ወይም ‘የማልረባ ሰው ነኝ’ በማለት ራስን ዝቅ ከማድረግ የተለየ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
20 ሌሎችን እንደራሳችን መውደድ ሲባል ሌሎች እኛን እንዲመለከቱንና እንዲይዙን በምንፈልግበት መንገድ ሌሎችን መመልከትና መያዝ ማለት ነው። ኢየሱስ “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12 የ1954 ትርጉም) ኢየሱስ፣ ሌሎች ከዚህ ቀደም ያደረጉላችሁን የደግነት ድርጊቶች በማሰብ ውለታቸውን መልሱ እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ እኛ በምን መንገድ መያዝ እንደምንፈልግ ማሰብና ለሌሎች እንደዚሁ ማድረግ ይገባናል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ይህን ለወዳጆቻችንና ለወንድሞቻችን ብቻ እንድናደርግ አለመናገሩን ልብ በል። ኢየሱስ እዚህ ላይ “ሰዎች” የሚለውን ቃል ተጠቅሟል፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው ለሁሉም ሰዎች ማለትም ለምናገኛቸው ሰዎች ሁሉ እንዲህ ማድረግ እንዳለብን ለመጠቆም ፈልጎ ሊሆን ይችላል።
21. ለሌሎች ሰዎች ፍቅር ማሳየታችን ምን እንዳለን ያሳያል?
21 ጎረቤቶቻችንን መውደድ ክፉ ነገሮችን ከማድረግ ይጠብቀናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል:- “‘አታመንዝር’፣ ‘አትግደል’፣ ‘አትስረቅ’፣ ‘አትመኝ’ የሚሉትና ሌሎችም ትእዛዛት ቢኖሩም፣ ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ አድርገህ ውደድ’ በሚለው በዚህ በአንድ ሕግ ተጠቃለዋል። ፍቅር በባልንጀራው ላይ ክፉ አያደርግም።” (ሮሜ 13:9, 10) ፍቅር ለሌሎች መልካም የምናደርግባቸውን መንገዶች እንድንፈልግ ይገፋፋናል። ሰዎችን በመውደድ ሰውን በመልኩ የፈጠረውን ይሖዋ አምላክን እንደምንወድ እናሳያለን።—ዘፍጥረት 1:26
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
• ፍቅር ማሳየት ያለብን ለማን ነው? ለምንስ?
• ይሖዋን ለማያመልኩ ሰዎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
• መጽሐፍ ቅዱስ ለወንድሞቻችን ሊኖረን የሚገባውን ፍቅር እንዴት ይገልጸዋል?
• ጎረቤቶቻችንን እንደራሳችን መውደድ ሲባል ምን ማለት ነው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ባልንጀራዬ ማን ነው?”
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በግለሰብ ደረጃ ሰዎችን እንደሚወድ አሳይቷል