ወጣቶች ሆይ—አምላክን የሚያስከብር ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጉ
“ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን አሠልጥን።”—1 ጢሞቴዎስ 4:7
1, 2. (ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ያመሰገነው ለምን ነበር? (ለ) በዛሬው ጊዜ ወጣቶች ‘ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራሳቸውን እያሠለጠኑ’ ያሉት እንዴት ነው?
“ስለ እናንተ ደኅንነት ከልቡ የሚገደው እንደ እርሱ ያለ ማንም የለኝም፤ . . . ልጅ ከአባቱ ጋር እንደሚያገለግል፣ ከእኔ ጋር በወንጌል ሥራ አገልግሎአልና።” (ፊልጵስዩስ 2:20, 22) ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፊልጵስዩስ ለነበሩት ክርስቲያኖች በላከው ደብዳቤ ላይ ይህን ሞቅ ያለ ምስጋና አስፍሮ ነበር። ይህን የምስጋና ሐሳብ የጻፈው የጉዞ ባልደረባው ለነበረው ለወጣቱ ጢሞቴዎስ ነው። ጳውሎስ እንደሚወደውና እንደሚተማመንበት የሚገልጸው ይህ ደብዳቤ ጢሞቴዎስን ምን ያህል አበረታቶትና አስደስቶት እንደሚሆን መገመት ትችላለህ!
2 እንደ ጢሞቴዎስ ያሉ መንፈሳዊ አመለካከት ያላቸው ወጣቶች ምንጊዜም ቢሆን በይሖዋ ሕዝቦች መካከል እንደ ውድ ሀብት ይታያሉ። (መዝሙር 110:3) በዛሬው ጊዜ በአምላክ ድርጅት ውስጥ አቅኚዎች፣ ሚስዮናውያን፣ የግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኞች እንዲሁም ቤቴላውያን ሆነው የሚያገለግሉ ወጣቶች አሉ። ሌሎች ኃላፊነቶቻቸውን እየተወጡ በጉባኤ እንቅስቃሴዎች በቅንዓት የሚካፈሉት ወጣቶችም የላቀ ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። እንደነዚህ ያሉት ወጣቶች በሰማይ የሚገኘውን አባታችንን ይሖዋን የሚያስከብር ግብ ላይ ለመድረስ ጥረት በማድረጋቸው እውነተኛ እርካታ ያገኛሉ። በእርግጥም ‘ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራሳቸውን እያሠለጠኑ’ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8
3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?
3 ወጣት ከሆንክ መንፈሳዊ ግቦች አውጥተህ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግክ ነው? እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ የሚረዳህ እርዳታና ማበረታቻ ማግኘት የምትችለው ከየት ነው? ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ይህ ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ እንዴት መቋቋም ትችላለህ? አምላክን የሚያስከብሩ ግቦች ላይ ለመድረስ የምትጥር ከሆነ ምን በረከት እንደምታጭድ መጠበቅ ትችላለህ? የጢሞቴዎስን ሕይወትና የመረጠውን የሥራ መስክ በመመርመር ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት እንችላለን።
የጢሞቴዎስ አስተዳደግ
4. የጢሞቴዎስ ክርስቲያናዊ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር በአጭሩ ግለጽ።
4 ጢሞቴዎስ ያደገው የሮም ግዛት በሆነችው በገላትያ በምትገኘው ልስጥራን የምትባል ትንሽ ከተማ ውስጥ ነው። ጢሞቴዎስ ስለ ክርስትና የተማረው ጳውሎስ በልስጥራን በሰበከበት በ47 ከክርስቶስ ልደት በኋላ ገደማ ሳይሆን አይቀርም፤ በወቅቱ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ የነበረ ይመስላል። ብዙም ሳይቆይ ይህ ወጣት በአካባቢው በነበሩ ክርስቲያን ወንድሞች ዘንድ ጥሩ ስም አተረፈ። ጳውሎስ ከሁለት ዓመት በኋላ ወደ ልስጥራን በተመለሰበት ወቅት ጢሞቴዎስ ያደረገውን እድገት ሲያውቅ በሚስዮናዊነት አብሮት እንዲያገለግል መረጠው። (የሐዋርያት ሥራ 14:5-20፤ 16:1-3) ጢሞቴዎስ እየጎለመሰ ሲሄድ ተጨማሪ ኃላፊነቶችም ተሰጡት፤ ከእነዚህም መካከል ወንድሞችን ለማበረታታት የሚያስችሉ አስፈላጊ ተልእኮዎች ይገኙበታል። ጳውሎስ በ65 ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሮም እስር ቤት ሆኖ ለጢሞቴዎስ በጻፈለት ወቅት ጢሞቴዎስ በኤፌሶን ውስጥ ክርስቲያን ሽማግሌ ሆኖ ያገለግል ነበር።
5. በ2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15 መሠረት ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ውሳኔ እንዲያደርግ የረዱት ሁለት ነገሮች የትኞቹ ናቸው?
5 ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መርጦ እንደነበር በግልጽ መመልከት ይቻላል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት ምርጫ እንዲያደርግ ያነሳሳው ምን ነበር? ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በጻፈው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ሁለት ወሳኝ ነጥቦችን ጠቅሷል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፎለታል:- “በተማርኸውና በተረዳኸው ጽና፤ ይህን ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና፤ ከሕፃንነትህም ጀምረህ፣ . . . ቅዱሳት መጻሕፍትን ዐውቀሃል።” (2 ጢሞቴዎስ 3:14, 15) በመጀመሪያ፣ ጢሞቴዎስ እንዲህ ዓይነት ምርጫ እንዲያደርግ በመርዳት ረገድ ሌሎች ክርስቲያኖች ምን ሚና እንደተጫወቱ እንመልከት።
በጎ ተጽዕኖ ከሚያሳድሩ ሰዎች መጠቀም
6. ጢሞቴዎስ ምን ሥልጠና አግኝቷል? ለሥልጠናውስ ምን ምላሽ ሰጥቷል?
6 ጢሞቴዎስ ያደገው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነበር። አባቱ ግሪካዊ ሲሆን እናቱ ኤውንቄና አያቱ ሎይድ አይሁዳውያን ነበሩ። (የሐዋርያት ሥራ 16:1) ኤውንቄና ሎይድ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ለጢሞቴዎስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ አስተምረውታል። ኤውንቄና ሎይድ ክርስትናን ከተቀበሉ በኋላም ጢሞቴዎስ የክርስትና ትምህርቶችን አምኖ እንዲቀበል እንደረዱት ጥርጥር የለውም። ጢሞቴዎስም በዚህ ግሩም ሥልጠና ሙሉ በሙሉ እንደተጠቀመ ግልጽ ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ግብዝነት የሌለበት እምነትህን አስታውሳለሁ፤ ይህ እምነት ቀድሞ በአያትህ በሎይድ እንዲሁም በእናትህ በኤውንቄ ዘንድ ነበረ፤ አሁን ደግሞ በአንተ እንዳለ ተረድቻለሁ።”—2 ጢሞቴዎስ 1:5
7. ብዙ ወጣቶች በምን ረገድ ተባርከዋል? ይህስ ሊጠቅማቸው የሚችለው እንዴት ነው?
7 በዛሬው ጊዜም በርካታ ወጣቶች፣ እንደ ሎይድና ኤውንቄ ፈሪሃ አምላክ ያላቸውና የመንፈሳዊ ግቦችን አስፈላጊነት የሚገነዘቡ ወላጆችና አያቶች ስላሏቸው ተባርከዋል። ለአብነት ያህል፣ ሳሚራ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበረችበት ወቅት ከወላጆቿ ጋር ረዘም ያለ ውይይት ታደርግ እንደነበር ታስታውሳለች። እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “እማማና አባባ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት እንዲኖረኝና ለስብከቱ ሥራ ቅድሚያ እንድሰጥ አስተምረውኛል። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ጥረት እንዳደርግ ሁልጊዜ ያበረታቱኝ ነበር።” ሳሚራ የወላጆቿን ማበረታቻ ተግባራዊ ያደረገች ሲሆን አሁን በአገሯ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆና የማገልገል ልዩ መብት አግኝታለች። ወላጆችህ በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንድታተኩር የሚያበረታቱህ ከሆነ የሚሰጡህን ምክር በቁም ነገር አስብበት። እንዲህ ያለ ምክር የሚሰጡህ በሕይወትህ ደስተኛ የሚያደርግህ ጎዳና እንድትከተል ስለሚፈልጉ ነው።—ምሳሌ 1:5
8. ጢሞቴዎስ የሚያበረታቱ ክርስቲያን ወዳጆች በማፍራቱ የተጠቀመው እንዴት ነው?
8 ከክርስቲያን ወንድሞችህ መካከል የሚያበረታቱህ ወዳጆች ለማግኘት ጥረት ማድረግህም አስፈላጊ ነው። ጢሞቴዎስ በጉባኤውም ሆነ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው በኢቆንዮን ባሉ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ዘንድ መልካም ስም አትርፎ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 16:1, 2) ብርቱ ሠራተኛ ከነበረው ከጳውሎስ ጋር የተቀራረበ ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። (ፊልጵስዩስ 3:14) ከጳውሎስ ደብዳቤዎች መመልከት እንደሚቻለው ጢሞቴዎስ፣ የሚሰጠውን ምክር የሚቀበል ከመሆኑም በላይ ሌሎች የእምነት ምሳሌዎችን ለመኮረጅ ፈጣን ነበር። (1 ቆሮንቶስ 4:17፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:6, 12-16) ጳውሎስ “አንተ ግን ትምህርቴን፣ አካሄዴን፣ ዐላማዬን፣ እምነቴን፣ ትዕግሥቴን፣ ፍቅሬንና፣ ጽናቴን ሁሉ ታውቃለህ” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:10) በእርግጥም ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ምሳሌ ሙሉ በሙሉ ተከትሏል። በተመሳሳይ አንተም በጉባኤህ ከሚገኙ ጠንካራ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው ግለሰቦች ጋር ከተቀራረብህ በቁም ነገር የታሰበባቸው መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት ትችላለህ።—2 ጢሞቴዎስ 2:20-22
“ቅዱሳት መጻሕፍትን” አጥና
9. ‘ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን ለማሠልጠን’ እንድትችል የሚረዱህ ጓደኞች ከመምረጥ በተጨማሪ ምን ማድረግ ያስፈልግሃል?
9 መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ፣ በዚህ ረገድ የሚረዱህ ጓደኞች መምረጥ ብቻ በቂ ነው? አይደለም። ጢሞቴዎስ እንዳደረገው አንተም “ቅዱሳት መጻሕፍትን” በጥንቃቄ መመርመር ያስፈልግሃል። ማጥናት፣ የምትወደው ሥራ ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ጢሞቴዎስም እንኳ ‘ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራሱን ማሠልጠን አስፈልጎት’ እንደነበር አስታውስ። አብዛኛውን ጊዜ ስፖርተኞች ግባቸው ላይ ለመድረስ ለብዙ ወራት ከባድ ሥልጠና ያደርጋሉ። በተመሳሳይም መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መሥዋዕትነት መክፈልና ትጋት የታከለበት ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል። (1 ጢሞቴዎስ 4:7, 8, 10) ‘ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ግቦቼ ላይ ለመድረስ የሚረዳኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። ለዚህ ጥያቄ መልስ የሚሆኑ ሦስት መንገዶችን እንመርምር።
10, 11. ቅዱሳን መጻሕፍት መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ የሚያነሳሱህ እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።
10 በመጀመሪያ ደረጃ ቅዱሳን መጻሕፍት ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ እንዲኖርህ ይረዱሃል። እነዚህ መጻሕፍት በሰማይ የሚኖረው አባታችን ያሉትን ግሩም ባሕርያት፣ ለእኛ ያሳየውን ታላቅ ፍቅር እንዲሁም ወደፊት ለታማኝ አገልጋዮቹ ያዘጋጀውን ዘላለማዊ በረከት ይገልጻሉ። (አሞጽ 3:7፤ ዮሐንስ 3:16፤ ሮሜ 15:4) ስለ ይሖዋ ያለህ እውቀት እያደገ ሲሄድ ለእርሱ ያለህ ፍቅር ይጨምራል፤ እንዲሁም ሕይወትህን ለእርሱ ለመወሰን ትነሳሳለህ።
11 በርካታ ክርስቲያን ወጣቶች እውነትን የራሳቸው ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረው በግላቸው ማጥናታቸው ወሳኝ እንደሆነ ተናግረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አደል በክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ ያደገች ቢሆንም ምንም መንፈሳዊ ግቦች አልነበሯትም። “ወላጆቼ ወደ መንግሥት አዳራሽ ቢወስዱኝም የግል ጥናት አልነበረኝም፤ ሌላው ቀርቶ በስብሰባዎች ላይ እንኳ አላዳምጥም ነበር” በማለት ተናግራለች። ታላቅ እህቷ ከተጠመቀች በኋላ ግን አደል እውነትን ይበልጥ በቁም ነገር መመልከት ጀመረች። አደል እንዲህ ብላለች:- “መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር ለማንበብ ግብ አወጣሁ። ጥቂት ክፍሎችን ካነበብኩ በኋላ ከንባቤ ያገኘሁትን ሐሳብ በጽሑፍ አሰፍር ነበር። በዚያን ጊዜ የያዝኩት ማስታወሻ አሁንም ድረስ አለ። በአንድ ዓመት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቤ ጨረስኩ።” ይህን ማድረጓም ሕይወቷን ለይሖዋ ለመወሰን አነሳሳት። አደል ከባድ የአካል ጉዳት ቢኖርባትም እንኳ አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ ሆና እያገለገለች ነው።
12, 13. (ሀ) አንድ ወጣት መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቱ ምን ለውጦች እንዲያደርግ ይረዳዋል? እንዴት? (ለ) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚያሳዩ ምሳሌዎች ጥቀስ።
12 በሁለተኛ ደረጃ መጽሐፍ ቅዱስ በባሕርይህ ላይ አስፈላጊውን ለውጥ እንድታደርግ ይረዳሃል። ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን እንዲህ ብሎታል:- “ቅዱሳት መጻሕፍት . . . ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ፤ ይኸውም የእግዚአብሔር ሰው ለመልካም ሥራ ሁሉ ብቁ ሆኖ እንዲገኝ ነው።” (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) ከአምላክ ቃል ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ አዘውትረህ በማሰላሰልና የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ በማዋል የአምላክ መንፈስ ባሕርይህን እንዲያሻሽልልህ መፍቀድ ትችላለህ። የአምላክ መንፈስ እንደ ትሕትና፣ ጽናት፣ ታታሪነት እንዲሁም ለክርስቲያን ባልንጀሮችህ ከልብ የመነጨ ፍቅር እንደማሳየት የመሳሰሉ አስፈላጊ ባሕርያትን እንድታዳብር ይረዳሃል። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) ጢሞቴዎስ እነዚህ ባሕርያት ስለነበሩት ለሚያገለግልባቸው ጉባኤዎችም ሆነ ለጳውሎስ በረከት መሆን ችሏል።—ፊልጵስዩስ 2:20-22
13 በሦስተኛ ደረጃ፣ የአምላክ ቃል የጥበብ ጎተራ ነው። (መዝሙር 1:1-3፤ 19:7፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:7፤ 3:15) የአምላክ ቃል ወዳጆችህን በጥበብ ለመምረጥ፣ ጤናማ የሆኑ መዝናኛዎችን ለመለየት እንዲሁም ከባድ የሆኑ ሌሎች በርካታ ውሳኔዎችን ለማድረግ ያስችልሃል። (ዘፍጥረት 34:1, 2፤ መዝሙር 119:37፤ 1 ቆሮንቶስ 7:36 የ1954 ትርጉም) መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ እንድትችል በአሁኑ ጊዜ ጥበብ የታከለባቸው ውሳኔዎች ማድረግህ አስፈላጊ ነው።
‘መልካሙን ገድል ተጋደል’
14. መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ቀላል ያልሆነው ለምንድን ነው?
14 ይሖዋን ለሚያስከብሩ ግቦች ቅድሚያ መስጠት የጥበብ አካሄድ ቢሆንም እንዲህ ማድረጉ ግን ቀላል አይደለም። ለምሳሌ የምትሠማራበትን የሥራ መስክ በምትመርጥበት ጊዜ፣ እውነተኛ ስኬት ብሎም ደስታ ለማግኘት ከፍተኛ ትምህርትና ዳጎስ ያለ ደመወዝ የሚያስገኝ ሥራ አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማቸው ዘመዶችህ፣ እኩዮችህና አሳቢ የሆኑ አስተማሪዎችህ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያደርጉብህ ይሆናል። (ሮሜ 12:2) ይሖዋ ለአንተ ያዘጋጀውን ‘የዘላለም ሕይወት አጥብቀህ ለመያዝ’ እንድትችል፣ ጢሞቴዎስ እንዳደረገው ሁሉ ‘መልካሙን የእምነት ገድል መጋደል’ ይኖርብሃል።—1 ጢሞቴዎስ 6:12፤ 2 ጢሞቴዎስ 3:12
15. ጢሞቴዎስ ምን ተቃውሞ አጋጥሞት ሊሆን ይችላል?
15 የአንተን እምነት የማይጋሩ የቤተሰብህ አባላት በምርጫህ የማይስማሙ ከሆነ ደግሞ ፈተናው ይበልጥ ከባድ ሊሆን ይችላል። ጢሞቴዎስ እንዲህ ዓይነቱን ተቃውሞ መቋቋም ሳይኖርበት አልቀረም። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ እንደሚገልጸው የጢሞቴዎስ ቤተሰቦች “የተማሩና ሀብታሞች” ሳይሆኑ አይቀሩም። አባቱ ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተልና የቤተሰቡን ንግድ እንዲያካሂድ ጠብቆበት ሊሆን ይችላል።a ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር በሚስዮናዊነት በማገልገል በዚህ መስክ ሊያጋጥሙት የሚችሉትን አደገኛ ሁኔታዎችና ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ችግሮች ለመጋፈጥ እንደመረጠ ሲያውቅ አባቱ ምን ብሎ ሊሆን እንደሚችል ገምት!
16. አንድ ወጣት የአባቱን ተቃውሞ የተቋቋመው እንዴት ነው?
16 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያን ወጣቶችም ተመሳሳይ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሚያገለግለው ማቲው እንዲህ ብሏል:- “አቅኚ ሆኜ ማገልገል ስጀምር አባቴ በጣም አዝኖብኝ ነበር። በአቅኚነት እየተካፈልኩ ራሴን መርዳት እንድችል በጽዳት ሥራ በመቀጠሬ፣ የተማርኩት ሁሉ ‘ከንቱ’ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ሙሉ ቀን ብሠራ ምን ያህል ገንዘብ ላገኝ እችል እንደነበረ በመግለጽ ያፌዝብኝ ነበር።” ማቲው እንዲህ ያለ ተቃውሞ ሲሰነዘርበት ምን አደረገ? እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ቋሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ፕሮግራም የነበረኝ ሲሆን አዘውትሬም እጸልይ ነበር፤ በተለይ በቀላሉ የሚያስቆጣኝ ነገር ሲያጋጥመኝ አጥብቄ እጸልይ ነበር።” ማቲው በአቋሙ በመጽናቱ ተክሷል። ከጊዜ በኋላ ከአባቱ ጋር የነበረው ግንኙነት እየተሻሻለ ከመሄዱም በላይ ይበልጥ ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ችሏል። ማቲው እንዲህ ይላል:- “ይሖዋ የሚያስፈልገኝን አሟልቶልኛል፣ አበረታቶኛል እንዲሁም የተሳሳቱ ውሳኔዎችን እንዳላደርግ ረድቶኛል። መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ባላደርግ ኖሮ እነዚህን ሁሉ በረከቶች ማግኘት አልችልም ነበር።”
መንፈሳዊ ግቦች ላይ ትኩረት አድርግ
17. አንዳንዶች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ለሚፈልጉ ወጣቶች የተሳሳተ ምክር በመስጠት ተስፋ ሊያስቆርጧቸው የሚችሉት እንዴት ነው? (ማቴዎስ 16:22)
17 መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ስታደርግ የእምነት አጋሮችህም ጭምር የተሳሳተ ምክር በመስጠት ተስፋ ሊያስቆርጡህ ይችላሉ። አንዳንዶች ‘አቅኚ መሆን ለምን ያስፈልግሃል?’ ይሉህ ይሆናል። ‘እንደሌላው ሰው እየኖርክ በስብከቱ ሥራ መካፈል ትችላለህ። ይልቅስ ዳጎስ ያለ ደሞዝ የሚያስገኝልህ ሥራ ይዘህ ገንዘብ ብታጠራቅም ይሻልሃል’ በማለት ይናገሩ ይሆናል። እንዲህ ያለው ምክር ጠቃሚ ሊመስል ይችላል፤ ይሁን እንጂ ይህን ምክር ለመከተል ከመረጥክ ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን እያሠለጠንክ ነው ለማለት ይቻላል?
18, 19. (ሀ) ትኩረትህ በመንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲሆን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ወጣት ከሆንክ ለአምላክ መንግሥት ስትል ምን መሥዋዕትነት እየከፈልክ እንደሆነ ግለጽ።
18 በጢሞቴዎስ ዘመን ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት አመለካከት የነበራቸው ይመስላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:17) ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ግቦች ላይ እንዲያተኩር ለመርዳት ጳውሎስ “በውትድርና የሚያገለግል ሰው አዛዡን ለማስደሰት ይጥራል እንጂ በሌላ ሥራ ራሱን አያጠላልፍም” በማለት አበረታቶት ነበር። (2 ጢሞቴዎስ 2:4) በግዳጅ ላይ ያለ አንድ ወታደር በዕለታዊ ሕይወት ውስጥ የሚካሄዱ ሌሎች እንቅስቃሴዎች ትኩረቱን እንዲሰርቁበት አይፈልግም። የራሱም ሆነ የሌሎች ሕይወት የተመካው የአዛዡን ትእዛዝ ለመፈጸም ሁልጊዜ ዝግጁ በመሆኑ ላይ ነው። አንተም የክርስቶስ ወታደር እንደመሆንህ መጠን ሐሳብህ መከፋፈል የለበትም፤ ሕይወት አድን በሆነው አገልግሎት ሙሉ በሙሉ መካፈል እንዳትችል እንቅፋት የሚሆኑብህን አላስፈላጊ ቁሳዊ ነገሮች በማሳደድ መጠላለፍ የለብህም።—ማቴዎስ 6:24፤ 1 ጢሞቴዎስ 4:16፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:2, 5
19 የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት ግብ ከማውጣት ይልቅ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ አዳብር። “እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ወታደር፣ ምቾት የሌለው ሕይወት ለመምራት ዝግጁ ሁን።” (2 ጢሞቴዎስ 2:3 ዚ ኢንግሊሽ ባይብል ኢን ቤዚክ ኢንግሊሽ) ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ ጋር በሚያገለግልበት ጊዜ፣ በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ሳይቀር ባለው ረክቶ የመኖርን ምስጢር ተምሯል። (ፊልጵስዩስ 4:11, 12፤ 1 ጢሞቴዎስ 6:6-8) አንተም ቢሆን ተመሳሳይ ነገር ማድረግ ትችላለህ። ለአምላክ መንግሥት ስትል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነህ?
አሁንና ወደፊት የምታገኘው በረከት
20, 21. (ሀ) መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ የሚያስገኛቸውን አንዳንድ በረከቶች ግለጽ። (ለ) አንተስ ምን ለማድረግ ቆርጠሃል?
20 ጢሞቴዎስ ለ15 ዓመታት ያህል ከጳውሎስ ጋር አገልግሏል። በሰሜናዊ የሜድትራንያን አካባቢ በሙሉ ማለት ይቻላል ምሥራቹ ሲዳረስና አዳዲስ ጉባኤዎች ሲቋቋሙ ለመመልከት ችሏል። ጢሞቴዎስ “እንደ ሌላው ሰው” ለመኖር መርጦ ቢሆን ኖሮ ሕይወቱ የዚህን ያህል አስደሳችና አርኪ አይሆንም ነበር። አንተም መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት በማድረግ በዋጋ ሊተመን የማይችል መንፈሳዊ በረከት ማጨድ ትችላለህ። ወደ ይሖዋ ከመቅረብህም በላይ የክርስቲያን ባልንጀሮችህን ፍቅርና አክብሮት ታገኛለህ። ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ ከሚያመጣው ሥቃይና መከራ በተቃራኒ ከራስ ወዳድነት ነጻ በሆነ መንገድ በመስጠት የሚገኘውን እውነተኛ ደስታ መቋደስ ትችላለህ። ከሁሉም በላይ ደግሞ “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” ማግኘት ይኸውም ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም መኖር ትችላለህ።—1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10, 17-19፤ የሐዋርያት ሥራ 20:35
21 ለእውነተኛ መንፈሳዊ ሕይወት ራስህን እያሠለጠንክ ካልሆነ እንዲህ ማድረግ እንድትጀምር እናበረታታሃለን። በጉባኤ ውስጥ መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ሊረዱህ ከሚችሉ ሰዎች ጋር ተቀራረብ፤ እንዲሁም ምክር እንዲለግሱህ ጠይቃቸው። የአምላክን ቃል በግልህ አዘወትረህ ለማጥናት ቅድሚያ ስጥ። ይህ ዓለም የሚያንጸባርቀውን በፍቅረ ንዋይ ላይ ያተኮረ መንፈስ ለመቋቋም ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከዚህም በላይ ‘ደስም እንዲለን ሁሉን ነገር አትረፍርፎ የሚሰጠን’ አምላክ፣ እርሱን የሚያስከብሩ ግቦችን ከመረጥክ አሁንም ሆነ ወደፊት አብዝቶ ሊባርክህ ቃል እንደገባ ምንጊዜም አስታውስ።—1 ጢሞቴዎስ 6:17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የግሪክ ማኅበረሰብ ለትምህርት ከፍተኛ ቦታ ይሰጥ ነበር። ፕሉታርክ የተባለ በጢሞቴዎስ ዘመን የኖረ ሰው እንዲህ በማለት ጽፏል:- “ተገቢ ትምህርት ማግኘት የጥሩ ነገር ሁሉ ምንጭና መሠረት ነው። . . . በእኔ አመለካከት የላቀ ሥነ ምግባርና ደስታ የሚያስገኘው ይህ ነው። . . . ሌሎች ነገሮች ሁሉ ከንቱ፣ የማይረቡና ትኩረት ሊሰጣቸው የማይገቡ ናቸው።”—ሞራልያ፣ I፣ “የልጆች ትምህርት”
ታስታውሳለህ?
• ወጣቶች መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ እርዳታ ማግኘት የሚችሉት ከየት ነው?
• መጽሐፍ ቅዱስን በጥንቃቄ ማጥናት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• ወጣቶች ፍቅረ ንዋይ የተጠናወተው ይህ ዓለም የሚያሳድረውን ተጽዕኖ መቋቋም የሚችሉት እንዴት ነው?
• መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረግ ምን በረከት ያስገኛል?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጢሞቴዎስ መልካም ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት አድርጓል
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጢሞቴዎስ ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳደሩት እነማን ናቸው?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ ጥረት እያደረግክ ነው?