“ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው?”
“ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አንዋ[ን]ዋሩ ሥራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ።”—ያዕ. 3:13 የ1954 ትርጉም
1, 2. ጥበበኛ እንደሆኑ ተደርገው ስለሚታዩ ብዙ ሰዎች ምን ለማለት ይቻላል?
ጥበበኛ እንደሆነ አድርገህ የምትመለከተው ማንን ነው? ምናልባት ወላጆችህን፣ በዕድሜ የገፉ ሰዎችን አሊያም የኮሌጅ ፕሮፌሰሮችን ይሆን? አስተዳደግህና በአካባቢህ ያሉት ሁኔታዎች ጥበበኛ እንደሆነ ስለምታስበው ሰው ባለህ አመለካከት ላይ ተጽዕኖ ያሳድሩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የአምላክን አገልጋዮች በዋነኝነት የሚያሳስባቸው አንድን ሰው በይሖዋ ዓይን ጥበበኛ ነው እንዲባል የሚያደርገው ነገር ነው።
2 ዓለም ጥበበኛ እንደሆኑ አድርጎ የሚቆጥራቸው ሰዎች ሁሉ በአምላክ ዘንድ ጥበበኛ ላይሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢዮብ ንግግራቸው ጥበብ የተሞላበት እንደሆነ አድርገው ከሚቆጥሩ ሰዎች ጋር የተወያየ ቢሆንም ‘ከመካከላቸው አንድም ጠቢብ እንዳላገኘ’ ተናግሯል። (ኢዮብ 17:10) ሐዋርያው ጳውሎስ የአምላክን እውቀት ለመቀበል ፈቃደኛ ስላልሆኑ አንዳንድ ሰዎች ሲጽፍ “ጥበበኞች ነን ቢሉም፣ ሞኞች ሆኑ” ብሏል። (ሮሜ 1:22) በተጨማሪም ይሖዋ ራሱ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት “በራሳቸውም አመለካከት ጥበበኛ ለሆኑ ወዮላቸው!” በማለት ተናግሯል።—ኢሳ. 5:21
3, 4. አንድን ሰው እውነተኛ ጥበብ አለው የሚያስብለው ምንድን ነው?
3 በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው አንድን ሰው ጠቢብ የሚያሰኘውና የአምላክን ሞገስ የሚያስገኝለት ምን መሆኑን ማወቃችን አስፈላጊ ነው። ይህን በተመለከተ ምሳሌ 9:10 “የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ ቅዱሱንም ማወቅ ማስተዋል ነው” ይላል። ጥበበኛ ሰው ለአምላክ ተገቢ የሆነ ፍርሃት ሊያድርበትና ላወጣቸው መሥፈርቶች አክብሮት ሊኖረው ይገባል። ይሁን እንጂ አምላክ መኖሩንና ያወጣቸው መሥፈርቶች እንዳሉ አምኖ መቀበል ብቻ በቂ አይደለም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ይህን በተመለከተ ትኩረት የሚስብ ሐሳብ ተናግሯል። (ያዕቆብ 3:13ን በ1954 ትርጉም አንብብ።) ‘በመልካም አኗኗሩ ሥራውን ያሳይ’ የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። እውነተኛ ጥበብ በየዕለቱ በምታከናውናቸው ነገሮችና በንግግርህ መንጸባረቅ ይኖርበታል።
4 እውነተኛ ጥበብ ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ ማዳበርን እንዲሁም እውቀትንና ማስተዋልን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀምን ይጨምራል። እንዲህ ዓይነቱ ጥበብ እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ያዕቆብ ጥበበኛ መሆናችንን ማሳየት የምንችልባቸውን የተለያዩ መንገዶች ዘርዝሯል።a ያዕቆብ ከእምነት አጋሮቻችንም ሆነ ከጉባኤ ውጪ ካሉ ሰዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የሚረዳ ምን ምክር ሰጥቶናል?
ድርጊታችን እውነተኛ ጥበብ እንዳለን ያሳያል
5. እውነተኛ ጥበብ ያለው ሰው ምን ዓይነት ምግባር ያሳያል?
5 ያዕቆብ ጥበብን ከመልካም አኗኗር ጋር አያይዞ መግለጹን ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት በመሆኑ ጥበበኛ የሆነ ሰው ከአምላክ መንገድና መሥፈርት ጋር ተስማምቶ ለመኖር ይጥራል። አምላካዊ ጥበብ በተፈጥሮ የምናገኘው ባሕርይ አይደለም። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ማጥናታችንና ማሰላሰላችን ይህን ባሕርይ እንድናዳብር የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ በኤፌሶን 5:1 ላይ እንደተገለጸው ‘አምላክን እንድንመስል’ ይረዳናል። ይሖዋን ይበልጥ እየመሰልነው በሄድን መጠን ድርጊታችን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ይሆናል። የይሖዋ መንገድ ከሰዎች መንገድ እጅግ የላቀ ነው። (ኢሳ. 55:8, 9) ይሖዋ ነገሮችን የሚያከናውንበትን መንገድ የምንኮርጅ ከሆነ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ያሉ ሰዎች ከሌሎች የተለየን መሆናችንን ያስተውላሉ።
6. የዋህነት አምላክን የምንመስልበት አንዱ መንገድ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው ይህ ባሕርይ እንዳለው የሚያሳየው እንዴት ነው?
6 ያዕቆብ ይሖዋን የምንመስልበት አንዱ መንገድ ከጥበብ የመነጨ የዋህነት ማሳየት መሆኑን ገልጿል። የዋህነት ገር መሆንን የሚጠይቅ ቢሆንም አንድ ክርስቲያን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ጥብቅና ጠንካራ የሥነ ምግባር አቋም ሊኖረው ይገባል። ይህ ደግሞ ሚዛናዊ እንዲሆን ይረዳዋል። ይሖዋ ገደብ የለሽ ኃይል ያለው ቢሆንም የዋህ ስለሆነ ወደ እሱ ለመቅረብ አንፈራም። የአምላክ ልጅ የአባቱን የየዋህነት ባሕርይ በሚገባ በማንጸባረቁ እንዲህ ለማለት ችሏል:- “እናንት ሸክም የከበዳችሁና የደከማችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ በልቤ የዋህና ትሑት ነኝና፤ ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።”—ማቴ. 11:28, 29፤ ፊልጵ. 2:5-8
7. የዋህነትን ወይም ትሕትናን በማሳየት ረገድ ሙሴ ጥሩ ምሳሌ ነው የምንለው ለምንድን ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ የዋህነትን ወይም ትሕትናን በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ስለሆኑ ሰዎች ይናገራል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዱ ሙሴ ነው። ሙሴ ትልቅ ኃላፊነት የነበረው ሰው ቢሆንም “በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት” እንደሆነ ተገልጿል። (ዘኍ. 11:29፤ 12:3) በተጨማሪም ይሖዋ ፈቃዱን መፈጸም እንዲችል ለሙሴ ታላቅ ኃይል ሰጥቶት እንደነበር አስታውስ። ይሖዋ ዓላማውን ለማስፈጸም የዋህ ወይም ትሑት በሆኑ ሰዎች ይጠቀማል።
8. ፍጹማን ያልሆኑ የሰው ልጆች ከጥበብ የመነጨ የዋህነት ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?
8 በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ከጥበብ የመነጨ የዋህነት ማሳየት ይችላሉ። እኛስ ይህን ባሕርይ በማሳየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ገርነት ወይም የዋህነት የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ የሚያፈራው ፍሬ ክፍል ነው። (ገላ. 5:22, 23) አምላክ የዋህነትን ይበልጥ ማንጸባረቅ እንድንችል እንደሚረዳን በመተማመን መንፈሱን እንዲሰጠን መጸለይና ይህን ባሕርይ ለማዳበር የታሰበበት ጥረት ማድረግ እንችላለን። መዝሙራዊው ‘[አምላክ] ለትሑታን መንገዱን ያስተምራቸዋል’ በማለት መናገሩ ይህን እንድናደርግ ያነሳሳናል።—መዝ. 25:9
9, 10. የዋህነትን ለማሳየት ምን ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል? ለምንስ?
9 የሆነ ሆኖ የዋህነትን በማሳየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ ልባዊ ጥረት ሊጠይቅ ይችላል። አንዳንዶቻችን በአስተዳደጋችን የተነሳ ይህንን ባሕርይ ማሳየት ይከብደን ይሆናል። ከዚህም በላይ በአካባቢያችን ያሉት ሰዎች ለሚደርስብን ነገር “እሾህን በእሾህ” እንድንመልስ በማበረታታት የዋሆች እንዳንሆን ይገፋፉናል። ይሁን እንጂ ይህ የጥበብ እርምጃ ነው? ቤትህ ውስጥ እሳት ቢነሳ እሳቱን የምታጠፋው በነዳጅ ነው ወይስ በውኃ? እሳቱ ላይ ነዳጅ መጨመር ቃጠሎውን ይበልጥ ያባብሰዋል፤ ውኃ ግን ሊያጠፋው ይችላል። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ “የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል” የሚል ምክር ይሰጠናል። (ምሳሌ 15:1, 18) በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጪ አለመግባባት ሲያጋጥመን ጉዳዩን በየዋህነት በመፍታት እውነተኛ ጥበብ እንዳለን ማሳየት እንችላለን።—2 ጢሞ. 2:24
10 ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ ያሳደረባቸው ብዙ ሰዎች ገር፣ ሰላማዊና የተረጋጉ አይደሉም። በዙሪያችን ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ቁጡና ዕብሪተኞች ናቸው። ያዕቆብ ይህን ያውቅ ስለነበር በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በዚህ ዓይነቱ መንፈስ እንዳይበከሉ አስጠንቅቋል። ያዕቆብ ከሰጠው ምክር ምን ተጨማሪ ትምህርት እናገኛለን?
ጥበበኛ ያልሆኑ ሰዎች የሚያሳዩት ባሕርይ
11. የትኞቹ ባሕርያት ከአምላካዊ ጥበብ ጋር ይቃረናሉ?
11 ያዕቆብ ከአምላካዊ ጥበብ ጋር የሚቃረኑ ባሕርያትን አስመልክቶ በግልጽ ጽፏል። (ያዕቆብ 3:14ን አንብብ።) ቅንዓትና ጭቅጭቅ መንፈሳዊ አስተሳሰብ የሌላቸው ሰዎች የሚያንጸባርቋቸው ባሕርያት ናቸው። ሥጋዊ አስተሳሰብ እያየለ ሲሄድ ምን ሊከሰት እንደሚችል ተመልከት። ክርስቲያን ነን የሚሉ ስድስት ቡድኖች ኢየሱስ የተገደለበትና የተቀበረበት ሥፍራ ነው ተብሎ በሚታሰብ ቦታ ላይ የተገነባን አንድ ሕንፃ የተለያዩ ክፍሎች ይዘው ነበር። በእነዚህ ቡድኖች መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ አለመግባባት ነበር። በ2006 ታይም መጽሔት በዚያ ይኖሩ በነበሩት ቀሳውስት መካከል በአንድ ወቅት ተፈጥሮ ስለነበረ ሁኔታ ሲዘግብ “በትልልቅ የሻማ ማስቀመጫዎች ለረጅም ሰዓታት ተደባድበዋል” ብሏል። እንዲያውም እርስ በርስ ስለማይተማመኑ የቤተ ክርስቲያኑን ቁልፍ የእስልምና እምነት ተከታይ ለሆነ ሰው እስከ መስጠት ደርሰው ነበር።
12. ጥበብ በጎደላቸው ሰዎች መካከል ምን ሊከሰት ይችላል?
12 ይህን የመሰለው ያለመግባባት መንፈስ በእውነተኛ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ መታየት የለበትም። ያም ሆኖ አንዳንዶች በአለፍጽምና ምክንያት እኔ ያልኩት ካልሆነ የሚል ስሜት ሊያንጸባርቁ ይችላሉ። ይህ ደግሞ ወደ ጠብና ግጭት ሊያመራ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ ጉባኤ ውስጥ እንዲህ ያለውን ሁኔታ ተመልክቶ ስለነበር እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመካከላችሁ ቅናትና ክርክር አለ፤ ታዲያ፣ ሥጋውያን መሆናችሁ አይደለምን? ተግባራችሁስ እንደ ማንኛውም ሰው ተግባር መሆኑ አይደለምን?” (1 ቆሮ. 3:3) በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው በዚህ ጉባኤ ውስጥ ይህ አሳዛኝ ሁኔታ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቆይቶ ነበር። በመሆኑም ዛሬም እንዲህ ያለው መንፈስ ወደ ጉባኤ እንዳይገባ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።
13, 14. ሥጋዊ አስተሳሰብ እንዴት ሊንጸባረቅ እንደሚችል የሚያሳዩ ምሳሌዎችን ጥቀስ።
13 እንዲህ ያለው መንፈስ ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሰርጎ ሊገባ የሚችለው እንዴት ነው? ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮች ሊጀምር ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የመንግሥት አዳራሽ ሲገነባ ሥራው እንዴት መካሄድ አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ የአመለካከት ልዩነት ሊፈጠር ይችላል። አንድ ወንድም፣ ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ምክንያት ሊበሳጭና ምናልባትም የተደረጉትን ውሳኔዎች መተቸት ሊጀምር ይችላል። ከዚያም አልፎ ምንም ዓይነት ሥራ ላለመሥራት ይወስን ይሆናል! እንዲህ የሚያደርግ ሰው፣ ከጉባኤ ጋር የተያያዙ ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸው የተመካው በጉባኤ ውስጥ በሚኖረው የሰላም መንፈስ እንጂ በአሠራር ዘዴው ላይ አለመሆኑን ዘንግቷል። የይሖዋን ሞገስ የሚያስገኘው ተጨቃጫቂ መሆን ሳይሆን የየዋህነት መንፈስ ማሳየት ነው።—1 ጢሞ. 6:4, 5
14 ከዚህ ጋር የተያያዘ ሌላም ሁኔታ ማየት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሽማግሌዎች ለተወሰኑ ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ አንድ ወንድም በአሁኑ ወቅት ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን እንደማያሟላ በግልጽ አስተዋሉ እንበል። ጉባኤውን የሚጎበኘው የወረዳ የበላይ ተመልካች ይህ ወንድም ከዚህ በፊት ምክር እንደተሰጠውና ምንም ማሻሻያ አለማድረጉን ካገናዘበ በኋላ ከሽምግልናው እንዲወርድ በቀረበው ሐሳብ ተስማማ። ይህ ሽማግሌ ሁኔታውን እንዴት ማየት ይኖርበታል? ሽማግሌዎቹ ያስተላለፉትን ውሳኔ እንዲሁም የተሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር በየዋህነትና በትሕትና ተቀብሎ ወደዚህ ኃላፊነት በድጋሚ ለመድረስ የሚያስችሉትን ብቃቶች ለማሟላት ይጥራል? ወይስ ቀደም ሲል የነበረውን መብት በማጣቱ ቂም ይይዛል አሊያም ቅናት ያድርበታል? ሌሎቹ ሽማግሌዎች በሙሉ ብቃቱ እንደሌለው ካመኑበት ይህ ወንድም ብቃቱ አለኝ በማለት ለምን ይሟገታል? በዚህ ወቅት ትሕትና ለማሳየትና የሌሎችን ሐሳብ ለመረዳት መጣር ምንኛ የተሻለ ነው!
15. በያዕቆብ 3:15, 16 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ ምክር አስፈላጊ እንደሆነ የሚሰማህ ለምንድን ነው?
15 አንድ ሰው እንዲህ ያለ ባሕርይ እንዲያሳይ ምክንያት የሚሆኑ ሌሎች ሁኔታዎችም ሊኖሩ እንደሚችሉ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ሁኔታው ምንም ይሁን ምን እነዚህን ባሕርያት ላለማሳየት መጣር ይኖርብናል። (ያዕቆብ 3:15, 16ን አንብብ።) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ያሉት ባሕርያት ሥጋዊ አስተሳሰብ የሚንጸባረቅባቸውና ከሰማይ ከሆነችው ጥበብ የራቁ በመሆናቸው “ከምድር” እንደሆኑ ተናግሯል። እንዲሁም የማሰብ ችሎታ የሌላቸው እንስሳት የሚያሳዩአቸውና ከሥጋዊ አስተሳሰብ የሚመነጩ ስለሆኑ “ከሥጋ” እንደሆኑ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የአምላክ ጠላት የሆኑትን መንፈሳዊ ፍጥረታት አስተሳሰብ የሚያንጸባርቁ ስለሆኑ “ከአጋንንት” ናቸው። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያሉ ባሕርያትን ማንጸባረቁ ፈጽሞ ተገቢ አይደለም።
16. ምን ማስተካከያዎችን ማድረግ ይኖርብን ይሆናል? በዚህ ረገድ ስኬታማ ለመሆንስ ምን ሊረዳን ይችላል?
16 እያንዳንዱ የጉባኤ አባል ራሱን መመርመርና እንዲህ ያሉ ባሕርያትን ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። የበላይ ተመልካቾች በጉባኤ ውስጥ አስተማሪዎች እንደመሆናቸው መጠን ከአሉታዊ አመለካከቶች ራሳቸውን መጠበቃቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ባለብን አለፍጽምና እንዲሁም ዓለም በሚያሳድርብን ተጽዕኖ የተነሳ እነዚህን ባሕርያት ማስወገድ ብርቱ ጥረት ይጠይቃል። እንዲህ ማድረግ አንድን የሚያዳልጥ ዳገት ከመውጣት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ዳገቱን ስንወጣ አንድ የምንይዘው ነገር ከሌለ ወደኋላ ልንንሸራተት እንችላለን። ይሁንና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ምክር በጥብቅ በመከተል እንዲሁም በምድር ዙሪያ የሚገኘው የአምላክ ጉባኤ በሚሰጠን እርዳታ በመታገዝ ወደፊት መግፋት እንችላለን።—መዝ. 73:23, 24
ጥበበኛ የሆነ ሰው ለማፍራት የሚጥራቸው ባሕርያት
17. ጥበበኛ የሆነ ሰው መጥፎ ነገር ሲያጋጥመው ብዙውን ጊዜ ምን ያደርጋል?
17 ያዕቆብ 3:17ን አንብብ። “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ” ከምታፈራቸው ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹን በመመርመር ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ንጹሕ መሆን ሲባል በድርጊታችንም ሆነ በአስተሳሰባችን ከመጥፎ ነገሮች መራቅን ይጨምራል። ከክፉ ነገሮች ለመራቅ ፈጣን መሆን ይኖርብናል። እንዲህ ማድረግ ቅጽበታዊ እርምጃ መውሰድ ይጠይቃል። አንድ ሰው ጣቱን ወደ ዓይንህ ቢሰነዝር ወዲያውኑ ፊትህን ታዞራለህ ወይም ዓይንህን በእጅህ ትከልላለህ። ይህ ቅጽበታዊ እርምጃ ነው። እንዲህ የምታደርገው አስበህ አይደለም። መጥፎ ነገሮች ሲያጋጥሙን የምንወስደው እርምጃም ተመሳሳይ መሆን ይኖርበታል። ንጽሕናችንን ጠብቀን ለመኖር ያለን ጠንካራ ፍላጎትና በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን፣ ከመጥፎ ነገሮች ወዲያውኑ ዞር እንድንል ሊያደርጉን ይገባል። (ሮሜ 12:9) መጽሐፍ ቅዱስ ዮሴፍንና ኢየሱስን ጨምሮ ይህን የመሰለ እርምጃ ስለወሰዱ ሰዎች የሚገልጹ ምሳሌዎችን ይዟል።—ዘፍ. 39:7-9፤ ማቴ. 4:8-10
18. (ሀ) ሰላማዊ፣ (ለ) ሰላም ፈጣሪ መሆን ሲባል ምን ማለት ነው?
18 በተጨማሪም መለኮታዊ ጥበብ ሰላማዊ እንድንሆን ያደርገናል። ይህ ደግሞ እንደ ንዴትና ቁጣ ያሉትን ባሕርያት ማስወገድን እንዲሁም ሰላም የሚያደፈርሱ ድርጊቶችን ከመፈጸም መቆጠብን ይጨምራል። ያዕቆብ በዚህ ረገድ ተጨማሪ ሐሳብ ሲሰጥ “የጽድቅም ፍሬ ሰላምን ለሚያደርጉ በሰላም ይዘራል” ብሏል። (ያዕ. 3:18) ‘ሰላም አድራጊዎች’ ወይም ሰላም ፈጣሪዎች የሚለውን አገላለጽ ልብ በል። በጉባኤ ውስጥ የምንታወቀው ሰላም ፈጣሪ በመሆን ነው ወይስ ችግር ፈጣሪ? ብዙውን ጊዜ ከሌሎች ጋር እንጋጫለን? በቀላሉ የምንቀየም ወይም ሌሎችን የምናስከፋ ነን? ሌሎች የእኛን አመለካከት እንዲቀበሉ እናስገድዳለን ወይስ ሌሎችን ቅር የሚያሰኙ ባሕርያት ካሉን ለማስወገድ በትሕትና ጥረት እናደርጋለን? በሰዎች ዘንድ የምንታወቀው ከሌሎች ጋር ያለንን ሰላም ለመጠበቅ ጥረት የምናደርግ፣ ቂም የማንይዝና ይቅር ለማለት ፈጣኖች በመሆናችን ነው? ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመራችን መለኮታዊ ጥበብ በማሳየት ረገድ ምን ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል።
19. አንድ ሰው ምክንያታዊ መሆኑን ከሚያሳዩት ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
19 ያዕቆብ ከሰማይ የሆነችው ጥበብ ከምታንጸባርቃቸው ባሕርያት መካከል አንዱ ‘ታጋሽነት’ (እንደ አዲስ ዓለም ትርጉም ‘ምክንያታዊነት’) መሆኑን ገልጿል። ግልጽ የሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓት በማይኖርበት ጊዜ ሌሎች የእኛን አቋም እንዲቀበሉ ከመጫን እንርቃለን? በሌሎች ዘንድ የምንታወቀው የዋህና በቀላሉ የምንቀረብ በመሆናችን ነው? እነዚህ ነገሮች ምክንያታዊ ሰዎች እንደሆንን የሚያሳዩ ናቸው።
20. ቀደም ሲል የተጠቀሱትን አምላካዊ ባሕርያት ማንጸባረቃችን ምን ውጤት ያስገኛል?
20 ወንድሞችና እህቶች ያዕቆብ የገለጻቸውን አምላካዊ ባሕርያት ለማንጸባረቅ ይበልጥ ሲጥሩ በጉባኤው ውስጥ እጅግ አስደሳች ሁኔታ ይኖራል! (መዝ. 133:1-3) የዋህ፣ ሰላማዊና ምክንያታዊ መሆናችን ከሌሎች ጋር ያለንን ግንኙነት የሚያሻሽለው ከመሆኑም ባሻገር ‘ከሰማይ በሆነችው ጥበብ’ እንደምንመራ በግልጽ ያሳያል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ሌሎችን በይሖዋ ዓይን ማየት መቻላችን የዋህ፣ ሰላማዊና ምክንያታዊ በመሆን ረገድ እንዴት ሊረዳን እንደሚችል እንመለከታለን።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በጥቅሱ ዙሪያ ያለው ሐሳብ ያዕቆብ መልእክቱን በዋነኝነት የጻፈው ለጉባኤ ሽማግሌዎች ወይም ‘አስተማሪዎች’ እንደሆነ ይጠቁማል። (ያዕ. 3:1) እነዚህ ሰዎች አምላካዊ ጥበብ በማሳየት ረገድ ምሳሌ መሆን ነበረባቸው። ይሁንና ሁላችንም ከዚህ ምክር ትምህርት ማግኘት እንችላለን።
ልታብራራ ትችላለህ?
• አንድን ክርስቲያን እውነተኛ ጥበብ አለው የሚያስብለው ምንድን ነው?
• አምላካዊ ጥበብን በማሳየት ረገድ ማሻሻያ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
• “ከሰማይ የሆነችው ጥበብ” የሌላቸው ሰዎች ምን ባሕርያት ያሳያሉ?
• አንተ በግልህ የትኞቹን ባሕርያት ይበልጥ ለማዳበር ወስነሃል?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዛሬው ጊዜ በወንድሞች መካከል ግጭት ሊፈጠር የሚችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከመጥፎ ነገር ለመራቅ ቅጽበታዊ እርምጃ ትወስዳለህ?