“ንቁዎች ሁኑ”
“የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። . . . በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ።”—1 ጴጥ. 4:7
1. የኢየሱስ ትምህርት ጭብጥ ምን ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የትምህርቱ ጭብጥ የአምላክ መንግሥት ነበር። ይሖዋ በዚህ መንግሥት አማካኝነት ጽንፈ ዓለማዊ ሉዓላዊነቱን ያረጋግጣል እንዲሁም ስሙን ያስቀድሳል። ስለሆነም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” በማለት ወደ አምላክ እንዲጸልዩ አስተምሯል። (ማቴ. 4:17፤ 6:9, 10) ይህ የአምላክ መንግሥት መስተዳድር በቅርቡ የሰይጣንን ዓለም ካጠፋ በኋላ የአምላክ ፈቃድ በመላው ምድር ላይ እንዲፈጸም ያደርጋል። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው የአምላክ መንግሥት “እነዚያን [በዛሬው ጊዜ ያሉትን] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።”—ዳን. 2:44
2. (ሀ) ኢየሱስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን ተከታዮቹ ማወቅ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ምልክቱ ከኢየሱስ መገኘት ሌላ ምን የሚጠቁመው ነገር አለ?
2 የአምላክ መንግሥት መምጣት ለኢየሱስ ተከታዮች በጣም አስፈላጊ በመሆኑ “የመገኘትህና የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክትስ ምንድን ነው?” በማለት ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 24:3) ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ በሚገኝበት ወቅት በምድር ላይ ያሉ ሰዎች በዓይን ሊያዩት ስለማይችሉ ይህን የሚጠቁም የሚታይ ምልክት መኖር አለበት። ይህ ምልክት በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድመው የተነገሩ የተለያዩ ገጽታዎችን ያቀፈ ነው። ምልክቱ በሚታይበት ጊዜ በሕይወት የሚኖሩ የኢየሱስ ተከታዮች ክርስቶስ በሰማይ መግዛት እንደ ጀመረ ማስተዋል ይችላሉ። በተጨማሪም ይህ ምልክት መጽሐፍ ቅዱስ በአሁኑ ወቅት በምድር ላይ የሰፈነው ክፉ ሥርዓት ‘የመጨረሻ ቀኖች’ ብሎ የሚጠራው ጊዜ እንደ ጀመረ የሚጠቁም ነው።—2 ጢሞ. 3:1-5, 13፤ ማቴ. 24:7-14
በመጨረሻዎቹ ቀኖች ንቁዎች ሁኑ
3. ክርስቲያኖች ንቁዎች መሆን የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
3 ሐዋርያው ጴጥሮስ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ ጤናማ አስተሳሰብ ይኑራችሁ፤ እንዲሁም በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 4:7) የኢየሱስ ተከታዮች እሱ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ እንደተገኘ የሚጠቁሙትን በዓለም ላይ የሚከሰቱ ነገሮች በትኩረት በመከታተል ንቁዎች ሆነው መኖር ያስፈልጋቸዋል። የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ እየተቃረበ በሄደ መጠን ንቁ ሆነው መኖራቸው ይበልጥ አጣዳፊ ይሆናል። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “የቤቱ ባለቤት፣ . . . [በሰይጣን ዓለም ላይ የፍርድ እርምጃ ለመውሰድ] መቼ እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏቸዋል።—ማር. 13:35, 36
4. የሰይጣን ዓለም ክፍል የሆኑ ሰዎች ያላቸውን አመለካከት የይሖዋ አገልጋዮች ካላቸው አመለካከት ጋር አነጻጽር። (ሣጥኑ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ጨምረህ መልስ።)
4 አብዛኞቹ ሰዎች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ከመሆናቸውም ሌላ በዓለም ላይ የሚከሰቱት ነገሮች ያላቸውን ትርጉም በትኩረት አይከታተሉም። በተጨማሪም ክርስቶስ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን አያስተውሉም። የክርስቶስ እውነተኛ ተከታዮች ግን ንቁዎች ከመሆናቸውም ባሻገር ባለፈው መቶ ዘመን የተከሰቱት ነገሮች ያላቸውን ትርጉም በትክክል ይረዳሉ። ከ1925 አንስቶ የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው የዓለም ጦርነትና ከዚያ በኋላ የተከሰቱት ነገሮች ክርስቶስ በ1914 በሰማይ በንጉሣዊ ሥልጣኑ ላይ መገኘቱን የሚያረጋግጡ ጠንካራ ማስረጃዎች እንደሆኑ ተገንዝበዋል። በመሆኑም በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ይህ ክፉ ሥርዓት የሚገኘው በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ ነው። አስተዋይ የሆኑ በርካታ ሰዎች ትርጉሙ ባይገባቸውም እንኳ ከመጀመሪያው የዓለም ጦርነት በፊት በነበረውና ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ መካከል አስገራሚ ልዩነት እንዳለ ይገነዘባሉ።—“የነውጥ ዘመን ጀመረ” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
5. ምንጊዜም ንቁዎች ሆነን መኖራችን አንገብጋቢ የሆነው ለምንድን ነው?
5 ወደ መቶ ለሚጠጉ ዓመታት በዓለም ዙሪያ የተከሰቱት አሠቃቂ ነገሮች በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ እንደምንገኝ ያረጋግጣሉ። ይሖዋ፣ ክርስቶስ ኃያላን የሆኑትን የመላእክት ሠራዊት እየመራ በሰይጣን ዓለም ላይ እርምጃ እንዲወስድ ትእዛዝ የሚሰጥበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። (ራእይ 19:11-21) እውነተኛ ክርስቲያኖች ምንጊዜም ነቅተው እንዲጠብቁ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። በመሆኑም የዚህን ሥርዓት ፍጻሜ ስንጠባበቅ ዘወትር ንቁዎች ሆነን መኖራችን አንገብጋቢ ነው። (ማቴ. 24:42) ምንጊዜም ትኩረታችን ሳይከፋፈል መኖራችንና የክርስቶስን አመራር በመከተል በመላው ምድር ላይ እንድናከናውነው የተሰጠንን ሥራ መፈጸማችን በጣም አስፈላጊ ነው።
በምድር ዙሪያ የሚከናወን ሥራ
6, 7. በመጨረሻዎቹ ቀኖች ውስጥ የመንግሥቱ የስብከት ሥራ እድገት ያሳየው እንዴት ነው?
6 የይሖዋ አገልጋዮች እንዲያከናውኑ የተሰጣቸው ሥራ በዚህ ክፉ ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ እንደምንኖር ከሚጠቁሙት የተለያዩ የምልክቱ ገጽታዎች አንዱ እንደሆነ አስቀድሞ ተነግሯል። ኢየሱስ በፍጻሜው ዘመን የሚከናወኑትን የተለያዩ ነገሮች በዘረዘረበት ወቅት ዓለም አቀፋዊ ይዘት ያለውን ይህን ሥራ ጠቅሶ ነበር። ከተናገረው ትንቢት መካከል ከፍተኛ ትርጉም ያለው የሚከተለው ሐሳብ ይገኝበታል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴ. 24:14
7 ኢየሱስ ከተናገረው ከዚህ የትንቢቱ ገጽታ ጋር የተያያዙ አንዳንድ መረጃዎችን እንመልከት። የመጨረሻዎቹ ቀኖች በጀመሩበት በ1914 ምሥራቹን ይሰብኩ የነበሩት ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ግን ቁጥሩ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። ከ100,000 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ከ7,000,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ምሥራቹን በዓለም ዙሪያ እየሰበኩ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች በ2008 የክርስቶስን ሞት መታሰቢያ ባከበሩበት ወቅት ከእነሱ በተጨማሪ 10,000,000 የሚያህሉ ሌሎች ሰዎች በበዓሉ ላይ ተገኝተዋል። ይህ አኃዝ ከዚያ በፊት በነበረው ዓመት በበዓሉ ላይ ከተገኙት ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አለው።
8. ተቃውሞ የስብከቱ ሥራችን ውጤት እንዳያስገኝ ሊያደርግ ያልቻለው ለምንድን ነው?
8 የዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ከመምጣቱ በፊት ለሁሉም ሕዝቦች ስለ አምላክ መንግሥት ከፍተኛ ምሥክርነት እየተሰጠ ነው። “የዚህ ሥርዓት አምላክ” ሰይጣን ሆኖ እያለ ይህ ሥራ መከናወኑ የሚያስገርም ነው። (2 ቆሮ. 4:4) የዚህ ዓለም የፖለቲካ፣ የሃይማኖትና የንግድ ተቋማት እንዲሁም ፕሮፖጋንዳ የሚተላለፍባቸው የመገናኛ ዘዴዎች በእሱ ቁጥጥር ሥር ናቸው። ታዲያ በዚህ የምሥክርነት ሥራ አስገራሚ ውጤት ሊገኝ የቻለው እንዴት ነው? ሥራው የይሖዋ ድጋፍ ስላልተለየው ነው። በመሆኑም ሰይጣን የመንግሥቱን የስብከት ሥራ ለማስቆም ሙከራ ቢያደርግም እንኳ ሥራው በአስደናቂ ሁኔታ መከናወኑን ቀጥሏል።
9. ያገኘነው መንፈሳዊ ብልጽግና ተአምር ነው ሊባል የሚችለው ለምንድን ነው?
9 በመንግሥቱ የስብከት ሥራ የተገኘው ውጤት እንዲሁም የይሖዋ ሕዝቦች ያገኙት እድገትና መንፈሳዊ ብልጽግና ተአምር ነው ሊባል ይችላል። አምላክ ለሕዝቡ የሚሰጠውን አመራርና የሚያደርገውን ጥበቃ ጨምሮ የእሱ ድጋፍ ባይኖር ኖሮ የስብከቱን ሥራ ማከናወን አይቻልም ነበር። (ማቴዎስ 19:26ን አንብብ።) የአምላክ ቅዱስ መንፈስ እሱን ለማገልገል ፈቃደኛ በሆኑ ንቁ ሰዎች ልብ ውስጥ የሚሠራ በመሆኑ የስብከቱ ሥራ ስኬታማ በሆነ መልኩ እንደሚደመደም እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ‘ከዚያ በኋላ መጨረሻው ይመጣል።’ ይህ ጊዜ በፍጥነት እየቀረበ ነው።
‘ታላቁ መከራ’
10. ኢየሱስ መጪውን ታላቅ መከራ የገለጸው እንዴት ነው?
10 ይህ ክፉ ሥርዓት ‘በታላቁ መከራ’ ፍጻሜውን ያገኛል። (ራእይ 7:14) መጽሐፍ ቅዱስ ታላቁ መከራ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ ባይገልጽም ኢየሱስ “በዚያን ጊዜ ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ ይከሰታል” ብሏል። (ማቴ. 24:21) ከ50 እስከ 60 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈውን ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት የመሳሰሉ በዚህ ዓለም ላይ የደረሱ አስከፊ ሁኔታዎች ስናስብ ወደፊት የሚመጣው ታላቅ መከራ ምን ያህል ከባድ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ታላቁ መከራ በአርማጌዶን ጦርነት ይደመደማል። ይሖዋ በዚህ ጦርነት ወቅት የቅጣት ፍርዱን የሚፈጽሙ ኃይሎችን በመላክ የሰይጣንን ምድራዊ ሥርዓት ርዝራዥ ያስወግዳል።—ራእይ 16:14, 16
11, 12. ታላቁ መከራ መጀመሩን የሚጠቁመው ክስተት ምንድን ነው?
11 መጽሐፍ ቅዱስ የታላቁ መከራ አንደኛው ምዕራፍ የሚጀምርበትን ቀን ለይቶ ባይገልጽም ይህ መከራ ሲጀምር የሚፈጸመውን አስደናቂ ክስተት ይጠቁመናል። ይህ ክስተት፣ የፖለቲካ ኃይሎች የሐሰት ሃይማኖትን በጠቅላላ ለማጥፋት የሚወስዱት እርምጃ ነው። በራእይ ምዕራፍ 17 እና 18 ላይ በሚገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ላይ የሐሰት ሃይማኖት ከምድር የፖለቲካ ሥርዓቶች ጋር ባመነዘረች ጋለሞታ ተመስሏል። ራእይ 17:16 እንደሚያመለክተው በቅርብ ጊዜ ውስጥ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች “ጋለሞታይቱን ይጠሏታል፤ ከዚያም ያወድሟታል፣ እርቃኗንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።”
12 ይህ ሁኔታ የሚፈጸምበት ጊዜ ሲደርስ አምላክ፣ የፖለቲካ ገዥዎች የሐሰት ሃይማኖትን ሙሉ በሙሉ በማጥፋት “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው” ያኖራል። (ራእይ 17:17) ስለሆነም ይህን ጥፋት የሚያመጣው አምላክ ነው ሊባል ይችላል። በዚያ ወቅት አምላክ ለረጅም ጊዜ ከእሱ ፈቃድ ጋር የሚቃረኑ መሠረተ ትምህርቶችን ሲያስተምርና አገልጋዮቹን ሲያሳድድ በነበረው ግብዝ ሃይማኖት ላይ የፍርድ እርምጃ ይወስዳል። አብዛኛው የዓለም ሕዝብ በሐሰት ሃይማኖት ላይ እንዲህ ያለ ጥፋት ይደርሳል ብሎ አይጠብቅም። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ግን ይህ ጥፋት እንደሚመጣ ያውቃሉ። በመሆኑም እነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ከጀመሩበት ጊዜ አንስቶ ስለዚህ ጥፋት ለሰዎች ሲናገሩ ቆይተዋል።
13. በሐሰት ሃይማኖት ላይ የሚደርሰው ጥፋት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም የሚጠቁመው ምንድን ነው?
13 የሐሰት ሃይማኖት ሲጠፋ ሰዎች ያልጠበቁት ነገር ስለሚሆንባቸው በታላቅ ድንጋጤ ይዋጣሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው አንዳንድ “የምድር ነገሥታት” እንኳ ሳይቀሩ ጥፋቱን አስመልክተው “በጣም ያሳዝናል፣ በጣም ያሳዝናል፣ . . . ፍርድሽ በአንድ ሰዓት ተፈጽሟልና!” ይላሉ። (ራእይ 18:9, 10, 16, 19) “አንድ ሰዓት” የሚሉት ቃላት ክስተቱ በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ በአጭር ጊዜ የሚፈጸም መሆኑን ያሳያሉ።
14. የይሖዋ ጠላቶች በአገልጋዮቹ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ አምላክ ምን ምላሽ ይሰጣል?
14 የሐሰት ሃይማኖት ከጠፋ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የፍርድ መልእክት የሚያውጁት የይሖዋ አገልጋዮች ጥቃት እንደሚሰነዘርባቸው እናውቃለን። (ሕዝ. 38:14-16) ይህ ጥቃት ሲሰነዘር ጥቃቱን የሚያደርሱት ኃይሎች፣ ታማኝ ሕዝቦቹን እንደሚጠብቅ ቃል ከገባው ከይሖዋ ጋር መፋጠጥ ግድ ይሆንባቸዋል። ይሖዋ ‘በዚያን ጊዜ በቅናቴና በሚያስፈራው ቍጣዬ እናገራለሁ። ከዚያም እኔ ይሖዋ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ’ ሲል ተናግሯል። (ሕዝቅኤል 38:18-23ን አንብብ።) አምላክ በቃሉ ላይ “እናንተን [ታማኝ አገልጋዮቹን] የሚነካ ውድ የሆነውን የዐይኔን ብሌን እንደሚነካ ነው” በማለት ተናግሯል። (ዘካ. 2:8 የ1980 ትርጉም) በመሆኑም ይሖዋ፣ ጠላቶቹ በዓለም ዙሪያ በሚገኙት አገልጋዮቹ ላይ ጥቃት ሲሰነዝሩ ምላሽ ይሰጣል። በዚህ ጊዜ አምላክ የሚወስደው እርምጃ ወደ ታላቁ መከራ የመጨረሻ ምዕራፍ ይሸጋገርና በአርማጌዶን ይደመደማል። ኃያላን መላእክት ክርስቶስ የሚሰጣቸውን አመራር በመከተል በሰይጣን ዓለም ላይ የይሖዋን ፍርድ ይፈጽማሉ።
ልንወስደው የሚገባ እርምጃ
15. የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እንደተቃረበ ማወቃችን ምን እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል?
15 የዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በጣም እንደቀረበ ማወቃችን ምን እርምጃ እንድንወስድ ሊያነሳሳን ይገባል? ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “እነዚህ ሁሉ ነገሮች እንዲህ የሚቀልጡ ከሆነ ቅዱስ ሥነ ምግባር በመከተልና ለአምላክ ያደራችሁ መሆናችሁን የሚያሳዩ ተግባሮች በመፈጸም ምን ዓይነት ሰዎች መሆን እንዳለባችሁ ልታስቡበት ይገባል!” (2 ጴጥ. 3:11) ይህ ሐሳብ ምንጊዜም ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ሥነ ምግባር ሊኖረን እንደሚገባ ያስገነዝበናል፤ እንዲሁም ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮችን በመፈጸም ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማንጸባረቅ እንዳለብን ያሳስበናል። ይህም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበኩ ሥራ ለመካፈል የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግን ይጨምራል። ከዚህም በተጨማሪ ጴጥሮስ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። . . . በጸሎት ረገድ ንቁዎች ሁኑ” ሲል ጽፏል። (1 ጴጥ. 4:7) ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱና በዓለም አቀፉ ጉባኤ አማካኝነት መመሪያ እንዲሰጠን አዘውትረን በመጸለይ ወደ እሱ መቅረብና ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን።
16. የአምላክን ምክር በጥብቅ መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
16 በእነዚህ አስቸጋሪ ጊዜያት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን የሚከተለውን ምክር በጥብቅ መከተል ይኖርብናል፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሰዎች ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ ለራሳችሁ አመቺ የሆነውን ጊዜ ግዙ።” (ኤፌ. 5:15, 16) በታሪክ ዘመናት ውስጥ የዛሬውን ያህል ክፋት የነገሠበት ጊዜ የለም። ሰይጣን፣ ሰዎች የይሖዋን ፈቃድ እንዳይፈጽሙ ለማድረግ ወይም ትኩረታቸውን ለመከፋፈል ብዙ ዘዴዎችን ቀይሷል። የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ይህን በሚገባ እንገነዘባለን፤ በመሆኑም ለአምላክ ያለንን የታማኝነት አቋም ምንም ነገር እንዲያላላብን አንፈቅድም። በተጨማሪም በቅርቡ ምን እንደሚፈጸም ስለምናውቅ በይሖዋም ሆነ በዓላማዎቹ ላይ ሙሉ እምነት አለን።—1 ዮሐንስ 2:15-17ን አንብብ።
17. ከአርማጌዶን የተረፉ ሰዎች ትንሣኤ በሚከናወንበት ጊዜ ምን እንደሚሰማቸው ግለጽ።
17 ‘ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት ስለሚነሱ’ አምላክ ሙታንን ዳግመኛ ሕያው ለማድረግ የሰጠው አስደናቂ ተስፋ ፍጻሜውን ያገኛል። (ሥራ 24:15) የሞቱ ሰዎች “እንደሚነሱ” የሚገልጸው ሐሳብ አስተማማኝ ተስፋ ያዘለ እንደሆነ ልብ በል። ይህን ቃል የገባው ይሖዋ ስለሆነ ተስፋው እንደሚፈጸም ምንም ጥርጥር የለውም! ኢሳይያስ 26:19 የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል፦ “ሙታንህ ሕያዋን ይሆናሉ፤ . . . እናንት በዐፈር ውስጥ የምትኖሩ፣ ተነሡ፤ በደስታም ዘምሩ። . . . ምድር ሙታንን ትወልዳለች።” እነዚህ ቃላት የጥንት የአምላክ ሕዝቦች ወደ ትውልድ አገራቸው በተመለሱበት ጊዜ የመጀመሪያ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል፤ ይህ ደግሞ በሚመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ ቃል በቃል ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ እንድንተማመን ያደርገናል። ከሞት የሚነሱት ሰዎች ከሚወዷቸው ዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ዳግም ሲገናኙ እንዴት ያለ የደስታ ጊዜ ይሆናል! አዎን፣ የሰይጣን ዓለም የሚጠፋበትና የአምላክ አዲስ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ በጣም ቀርቧል። በአሁኑ ጊዜ ንቁ ሆነን መኖራችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
ታስታውሳለህ?
• የኢየሱስ ትምህርት ጭብጥ ምን ነበር?
• በዛሬው ጊዜ የአምላክን መንግሥት የመስበኩ ሥራ ምን ያህል ተስፋፍቷል?
• ንቁ መሆናችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
• በሐዋርያት ሥራ 24:15 ላይ ከተገለጸው ተስፋ ጋር በተያያዘ አበረታች ሆኖ ያገኘኸው ነገር ምንድን ነው?
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የነውጥ ዘመን ጀመረ
አለን ግሪንስፓን የተባሉ ሰው በ2007 ዚ ኤጅ ኦቭ ተርቢዩለንስ፦ አድቬንቸርስ ኢን ኤ ኒው ወርልድ የሚል ርዕስ ያለው መጽሐፍ አሳትመው ነበር። እኚህ ሰው የዩናይትድ ስቴትስን አጠቃላይ የባንክ ሥርዓት የሚቆጣጠረው ቦርድ ሊቀ መንበር በመሆን ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት አገልግለዋል። ግሪንስፓን ከ1914 በፊት በነበረውና ከዚያ ወዲህ ባለው የዓለም ሁኔታ መካከል ጉልህ ልዩነቶች እንዳሉ ሲገልጹ እንዲህ ብለዋል፦
“ከ1914 በፊት የተጻፉ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት በዚያ ጊዜ የነበረው ዓለም ምንም ነገር ሊገታው የማይችል በሚመስል ሁኔታ ወደ ከፍተኛ የሥልጣኔ ደረጃ እያመራ የነበረ ሲሆን በሰዎች መካከል የሚታየው እርስ በርስ የመከባበር ባሕልም እየዳበረ ሄዶ ነበር። ሰብዓዊው ኅብረተሰብ ከፍተኛ መሻሻል በማሳየቱ ፍጽምና ደረጃ ላይ የሚደርስ ይመስል ነበር። በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን፣ አስከፊ የነበረው የባሪያ ንግድ ሙሉ በሙሉ አቁሞ ነበር። ከዚህም ሌላ ሰብዓዊነት በጎደለው መንገድ የሚፈጸሙ የጭካኔ ድርጊቶች እየቀነሱ የሄዱ ይመስል ነበር። . . . በአሥራ ዘጠነኛው መቶ ዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ የቴክኖሎጂው እድገት በመፋጠኑ የባቡር ሐዲድ፣ ስልክ፣ የኤሌክትሪክ መብራት፣ ሲኒማ፣ በሞተር የሚሠራ መኪና እንዲሁም ሥፍር ቁጥር የሌላቸው በጣም ጠቃሚ የሆኑ የቤት ውስጥ ዕቃዎችና መሣሪያዎች ተፈልስፈዋል። የሕክምና ሳይንስ ማደጉ፣ የሰዎች የአመጋገብ ልማድ መሻሻሉና ንጹሕ የመጠጥ ውኃ በስፋት ለሕዝቡ መዳረሱ የሰው ልጆች የዕድሜ ጣሪያ እንዲጨምር አስተዋጽኦ አድርገዋል። . . . ሁሉም ሰው፣ ይህን እድገት ምንም ነገር ሊገታው እንደማይችል ይሰማው ነበር።”
ይሁን እንጂ . . . “አንደኛው የዓለም ጦርነት በሰውና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ካስከተለው ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በባሰ ሁኔታ የሰው ልጆችን ሥልጣኔም ሆነ በሰዎች መካከል የነበረውን እርስ በርስ የመከባበር ባሕል ክፉኛ ጎድቶታል፤ ከዚህም በላይ የሰው ልጆችን ሐሳብ አፋልሶታል። የሰው ልጆች ፈጣንና ማቆሚያ ያለው የማይመስል እድገት ያደረጉባቸው ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት የነበሩት ዓመታት ከአእምሮዬ ሊፋቁ አይችሉም። በዛሬው ጊዜ ያለን አመለካከት ከመቶ ዓመት በፊት ከነበረው ፈጽሞ የተለየ ነው፤ ይህ የሆነው በአሁኑ ጊዜ ያለን አመለካከት ዛሬ ያለውን እውነታ ስለሚያንጸባርቅ ሊሆን ይችላል። አንደኛው የዓለም ጦርነት ቀደም ሲል በነበረው ዓለም ላይ ለውጥ እንዳመጣ ሁሉ አሁንም ሽብርተኝነት፣ የምድር ሙቀት መጠን መጨመር ወይም ለተራው ሕዝብ ጥቅም ቅድሚያ መሰጠት አለበት የሚለው ዳግመኛ እያንሰራራ የመጣው አመለካከት፣ የሰዎች ሕይወት እንዲሻሻል ባደረገው በዚህ የግሎባላይዜሽን ዘመን ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣ ይሆን? ማንም ሰው ስለዚህ ጉዳይ በእርግጠኝነት ሊናገር አይችልም።”
ግሪንስፓን ተማሪ በነበሩበት ወቅት ቤንጃሚን አንደርሰን (1886-1949) የተባሉ አንድ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር የተናገሩትን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሳሉ፦ “ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት የነበረውን ዓለም በደንብ የሚያውቁና ማስታወስ የሚችሉ ሰዎች ያንን ጊዜ መለስ ብለው ሲያስቡ ከፍተኛ ቁጭት ይሰማቸዋል። በዚያን ወቅት የነበሩ ሰዎች ከዚያን ጊዜ ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ የደኅንነትና የመረጋጋት ስሜት ነበራቸው።”—ኢኮኖሚክስ ኤንድ ዘ ፐብሊክ ዌልፌር
በ2006 በጄራልድ ሜየር የተዘጋጀው ኤ ወርልድ አንደን የተባለውም መጽሐፍ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ደርሷል። መጽሐፉ እንዲህ ይላል፦ “ብዙውን ጊዜ ታሪካዊ ክስተቶች ‘ሁሉንም ነገር ይለውጣሉ’ ይባላል። በተለይ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት [1914-1918] ጋር በተያያዘ ይህ አባባል እውነት መሆኑ ታይቷል። ጦርነቱ ሁሉንም ነገር ለውጧል። ድንበሮችን፣ መስተዳድሮችንና የብሔራትን የወደፊት ዕጣ ብቻ ሳይሆን ሰዎች ለራሳቸውና ለዓለም ያላቸውን አመለካከት ጭምር ለውጦታል። ከጦርነቱ በኋላ ያለው ዓለም ከዚያ በፊት ከነበረው ዓለም ፈጽሞ የተለየ እንዲሆን በማድረግ በታሪክ ሂደት ውስጥ ትልቅ ክፍተት ፈጥሯል።”
[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በአርማጌዶን ወቅት ይሖዋ ኃያላን መላእክቱን ይልካል