መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ይዟል የምንለው ለምንድን ነው?
“ቅዱስ መጽሐፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ ነው፤ . . . ለመምከር ይጠቅማል።”—2 ጢሞቴዎስ 3:16
ባለፉት ዘመናት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ የተለያየ ባሕል ያላቸው ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ በጎ ለውጥ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ከላይ ካለው ጥቅስ መገንዘብ እንደምንችለው መጽሐፍ ቅዱስ በዚህ ረገድ ውጤታማ ሊሆን የቻለው በውስጡ የያዘው ጥበብ ምንጭ አምላክ ስለሆነ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በሰዎች ቢሆንም እንኳ የአምላክን ሐሳብ እንድንረዳ ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው ተናገሩ” ይላል።—2 ጴጥሮስ 1:21
መጽሐፍ ቅዱስ ተግባራዊ መሆን የሚችል መመሪያ ይሰጣል እንድንል የሚያደርጉን ቢያንስ ሁለት ምክንያቶች አሉ። በመጀመሪያ ደረጃ፣ ‘ጥሩ ሕይወት የሚባለው ምን ዓይነት ነው?’ በሚለው ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ሐሳብ በእውነታ ላይ የተመሠረተ ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሰዎች እንዲህ ዓይነቱን ጥሩ ሕይወት ለማግኘት አስፈላጊውን ለውጥ እንዲያደርጉ የማነሳሳት ኃይል አለው። እስቲ እነዚህን ሁለት ነጥቦች እንመልከት።
ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ግቦች ላይ ለመድረስ የሚያስችል ትምህርት
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው አምላክ እንዲህ በማለት ቃል ገብቷል፦ “አስተምርሃለሁ፤ በምትሄድበትም መንገድ እመራሃለሁ፤ እመክርሃለሁ፤ በዐይኔም እከታተልሃለሁ።” (መዝሙር 32:8) አምላክ ጥበበኞች እንድንሆን የሚረዳንን ምክርና ትምህርት እንደሚሰጠን ልብ በል። ዘላቂ ጥቅም ያላቸው ግቦች የትኞቹ እንደሆኑ ለማስተዋል የሚረዳንን ትምህርት ማግኘታችን እርባና ቢስ የሆኑ ግቦችን በመከታተል ሕይወታችንን ከማባከን ይጠብቀናል።
ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት ለዝና ወይም ለሀብት ነው። ራስ አገዝ መጻሕፍት፣ ሌሎችን በማታለል ሀብት ማግኘት ወይም ትልቅ ቦታ ላይ መድረስ የሚቻልባቸውን መንገዶች የሚገልጹ በርካታ ሐሳቦችን ይዘዋል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው በባልንጀራው ላይ ያለው ቅናት ከንቱ፣ ነፋስንም እንደ መከተል ነው’ ይላል። እንዲሁም “ብርን የሚወድድ ሰው ብርን አይጠግብም” በማለት ይናገራል። (መክብብ 4:4፤ 5:10 የ1954 ትርጉም) እነዚህ ምክሮች በዘመናችን ተግባራዊ መሆን ይችላሉ?
መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠው ምክር ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው እንዴት እንደሆነ ለመመልከት በጃፓን የሚኖረውን አኪኖሪ የተባለ ግለሰብ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አኪኖሪ ስመ ጥር ከሆነ ዩኒቨርሲቲ ለመመረቅና በታወቀ ድርጅት ውስጥ ሥራ ለማግኘት ባደረገው ጥረት ከባድ ፉክክር ቢያጋጥመውም ግቡ ላይ መድረስ ችሎ ነበር። ሁሉም ነገር የተሳካለት ይመስል ነበር። ያም ሆኖ ግን ያገኘው ስኬት እንዳሰበው ደስታ አላስገኘለትም። ከዚህ ይልቅ ሕይወቱ በውጥረት የተሞላ መሆኑና በከፍተኛ ድካም መዋጡ የጤና መቃወስ አስከተለበት። በሥራ ቦታ የሚገኙት ጓደኞቹ ችግሮቹን እንዲያሸንፍ እምብዛም ሊረዱት አልቻሉም። አኪኖሪ በከፍተኛ ጭንቀት በመዋጡ የአልኮል ሱሰኛ ከመሆኑም በላይ ራሱን ለማጥፋት ያስብ ነበር። ከጊዜ በኋላ ይህ ሰው ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኘው ትምህርት በሕይወት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ ስለሆነው ነገር ያለውን አመለካከት እንዲያስተካክል ረዳው። ውጥረቱ ያስከተለበት የጤና መቃወስ ቀስ በቀስ እየለቀቀው ሄደ። አኪኖሪ ኩራቱንና ትልቅ ቦታ የመድረስ ፍላጎቱን ያስወገደ ሲሆን “ሰላም ያለው ልብ ለሰውነት ሕይወት ይሰጣል” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እውነተኝነት በሕይወቱ መመልከት ችሏል።—ምሳሌ 14:30
አንድ ሰው በሕይወቱ ውስጥ ሊከታተለው የሚገባው ትልቅ ትርጉም ያለው ግብ ምን ይመስልሃል? እውነተኛ ደስታ ለማግኘት የሚያስችልህ ምንድን ነው? የሠመረ ትዳር እንዲኖርህ ማድረግ ነው? ወይስ ልጆችህን ጥሩ አድርገህ ማሳደግ? ብዙ ወዳጆች ማፍራት ነው? ወይስ በሕይወት መደሰት? እነዚህ ሁሉ ተገቢ የሆኑ ግቦች ናቸው። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ እንደነዚህ ዓይነት ግቦች እንዲኖሩን ያበረታታል፤ ይሁንና በሕይወታችን ውስጥ ዋነኛ ቦታ ልንሰጣቸው እንደማይገባ ይገልጻል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ በሕይወት ውስጥ እርካታ ለማግኘት የሚያስፈልገው መሠረታዊ ነገር ምን እንደሆነ ሲገልጽ የሚከተለውን ጥበብ የተንጸባረቀበት ሐሳብ ሰጥቷል፦ “እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና።” (መክብብ 12:13) ይህንን ተግባር አለማከናወናችን ሕይወታችን ዓላማ ቢስና በብስጭት የተሞላ እንዲሆን ውሎ አድሮም ተስፋ እንድንቆርጥ ያደርገናል። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔርም የሚታመን ቡሩክ [“ደስተኛ፣” NW] ነው” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል።—ምሳሌ 16:20
ሰዎች ለውጥ እንዲያደርጉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያነሳሳቸው እንዴት ነው?
ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ ነው” በማለት ጽፏል። መጽሐፍ ቅዱስ በሁለት በኩል ስለት እንዳለው ስለታም ሰይፍ፣ የአንድን ሰው የልብ ሐሳብና ዓላማ ዘልቆ መግባት ይችላል። (ዕብራውያን 4:12) መጽሐፍ ቅዱስ፣ ሰዎች ስለ ራሳቸው ካላቸው አመለካከት በተቃራኒ እውነተኛ ማንነታቸውን በግልጽ መመልከት እንዲችሉ ስለሚረዳቸው ሕይወታቸውን የመለወጥ ኃይል አለው። በመሆኑም ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች ለውጥ ማድረግ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት ሌቦች፣ ሰካራሞችና አመንዝሮች ስለነበሩትና ሌሎች መጥፎ ድርጊቶችን ይፈጽሙ ስለነበሩት የቆሮንቶስ ጉባኤ አባላት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም . . . በአምላካችን መንፈስ ታጥባችሁ ነጽታችኋል።” (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ዛሬም የሚሠራና ኃይል ያለው በመሆኑ ሰዎች አስፈላጊ የሆነውን ለውጥ እንዲያደርጉ ሊያነሳሳቸው ይችላል።
በአውሮፓ የሚኖረው ማሪዮ እጅግ ጠበኛ የነበረ ከመሆኑም ሌላ ማሪዋና ያጨስ እንዲሁም ይሸጥ ነበር። በአንድ ወቅት አንድ ፖሊስ ማሪዮ የያዛቸውን አደገኛ ዕፆች ሲወስድበት ማሪዮ በጣም ከመናደዱ የተነሳ ፖሊሱን የደበደበው ሲሆን መኪናውንም ከጥቅም ውጭ አደረገበት። ማሪዮ ሥራ የሌለው ከመሆኑም ሌላ በከባድ ዕዳ ውስጥ ተዘፍቆ ነበር። እነዚህን ችግሮች በራሱ ሊወጣቸው እንደማይችል ሲረዳ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። በጥናቱ እየበረታ ሲሄድ ንጽሕናውን መጠበቅ የጀመረ ሲሆን አደገኛ ዕፆችን መውሰድም ሆነ መሸጡን አቆመ፤ እንዲሁም የጠበኝነት ባሕርይውን አስተካከለ። የቀድሞ አኗኗሩን የሚያውቁ በርካታ ሰዎች ባደረገው ለውጥ በጣም ከመደነቃቸው የተነሳ መንገድ ላይ ሲያገኙት “እውነት አንተ ማሪዮ ነህ?” እያሉ ይጠይቁታል።
እንደ አኪኖሪ እና ማሪዮ ያሉ ሰዎች በሕይወታቸው ውስጥ እውነተኛ እርካታና ደስታ ለማግኘት የሚያስችላቸውን ለውጥ እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው ምንድን ነው? ይህን እንዲያደርጉ ያነሳሳቸው መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ አምላክ እውቀት ማግኘታቸው እንደሆነ ግልጽ ነው። በአሁኑ ጊዜ የተሳካ ሕይወት ለመምራት የሚያስችለንንም ሆነ ወደፊት የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዲኖረን የሚረዳንን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል መመሪያ ሊሰጠን የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። ይሖዋ አምላክ የሚከተለውን አባታዊ ምክር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስፍሮልናል፦ “ልጄ ሆይ፤ አድምጠኝ፤ ቃሌንም ልብ በል፤ የሕይወት ዘመንህም ትበዛለች። . . . ስትሄድ እርምጃህ አይሰናከልም፤ ስትሮጥም አትደናቀፍም። ምክርን አጥብቀህ ያዛት፤ አትልቀቃት፤ ጠብቃት፤ ሕይወትህ ናትና።” (ምሳሌ 4:10-13) የፈጣሪያችንን መመሪያ እንድንሻ ከሚያበረታታን ምክር የተሻለ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር ሊኖር ይችላል?
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በዘመናችን ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ምክር
መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ መሠረታዊ መመሪያዎችን ይዟል። ከዚህ በታች አንዳንድ ምሳሌዎች ቀርበዋል፦
• ከሌሎች ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን ማድረግ
“እንግዲህ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ነገር ሁሉ እናንተም እንደዚሁ ልታደርጉላቸው ይገባል።”—ማቴዎስ 7:12
“ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።”—ሉቃስ 9:48
“የእንግዳ ተቀባይነትን ባሕል አዳብሩ።”—ሮም 12:13
• ጎጂ ልማዶችን ማሸነፍ
“ከጠቢብ ጋር የሚሄድ ጠቢብ ይሆናል፤ የተላሎች ባልንጀራ ግን ጕዳት ያገኘዋል።”—ምሳሌ 13:20
“ብዙ የወይን ጠጅ ከሚጠጡ . . . ጋር አትወዳጅ።”—ምሳሌ 23:20
“ከግልፍተኛ ጋር ወዳጅ አትሁን።”—ምሳሌ 22:24
• ጠንካራ መሠረት ያለው ትዳር
“ከእናንተ እያንዳንዱ ራሱን እንደሚወድ ሁሉ ሚስቱንም ይውደድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሚስት ባሏን በጥልቅ ልታከብር ይገባል።”—ኤፌሶን 5:33
“ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ። . . . እርስ በርስ መቻቻላችሁንና እርስ በርስ በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።”—ቆላስይስ 3:12, 13
• ልጆችን ማሳደግ
“ልጅን የሚሄድበትን መንገድ አስተምረው፤ በሚሸመግልበት ጊዜ ከዚያ ፈቀቅ አይልም።”—ምሳሌ 22:6
“እናንተም አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን አታስመርሯቸው፤ ከዚህ ይልቅ በይሖዋ ተግሣጽ እንዲሁም የእሱን አስተሳሰብ በውስጣቸው በመቅረጽ አሳድጓቸው።”—ኤፌሶን 6:4
• ግጭትን ማስወገድ
“የለዘበ መልስ ቍጣን ያበርዳል፤ ክፉ ቃል ግን ቍጣን ይጭራል።”—ምሳሌ 15:1
“አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።”—ሮም 12:10
ጓደኛሞችም እንኳ የንግድ ውላቸውን በጽሑፍ ማስፈራቸው አብዛኛውን ጊዜ በመካከላቸው አለመግባባት እንዳይፈጠር ያደርጋል። የአምላክ አገልጋይ የነበረው ኤርምያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በውሉም ሰነድ ላይ ፈረምሁ፤ አሸግሁትም። ብሩንም በምስክሮች ፊት በሚዛን መዘንሁለት።”—ኤርምያስ 32:10
• አዎንታዊ አመለካከት ማዳበር
“እውነት የሆነውን ነገር ሁሉ፣ . . . ተወዳጅ የሆነውን ነገር ሁሉ፣ በመልካም የሚነሳውን ነገር ሁሉ፣ በጎ የሆነውን ሁሉና ምስጋና የሚገባውን ነገር ሁሉ ማሰባችሁን አታቋርጡ።”—ፊልጵስዩስ 4:8
መጽሐፍ ቅዱስ አሉታዊ በሆኑ ነገሮች ላይ ማውጠንጠን ተገቢ እንዳልሆነ የሚገልጽ ሲሆን “ስለ ኑሯቸው የሚያማርሩ” ሰዎችም ተግሣጽ ተሰጥቷቸዋል። የአምላክ ቃል “በተስፋው ደስ ይበላችሁ” የሚል ማበረታቻ ይሰጣል።—ይሁዳ 4, 16፤ ሮም 12:12
እነዚህን ግሩም መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋላችን በአሁኑ ጊዜ ሰላምና እርካታ የሚያስገኝልን ከመሆኑም በተጨማሪ የአምላክን ብቃቶች አሟልተን የእሱን በረከት ለማጨድ ያስችለናል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።—መዝሙር 37:29
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አኪኖሪ ታዋቂ ድርጅት ውስጥ ይሠራ በነበረበት ወቅት (በስተ ግራ) እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ከባለቤቱ ጋር የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ሲያካፍል