ምድር ትጠፋ ይሆን?
“ቢያንስ የፊልሙ ዓለም እስካለ ድረስ የዓለም መጨረሻ የሚለው ርዕሰ ጉዳይ የመወያያ ርዕስ መሆኑ አይቀርም።” ይህን የተናገሩት ጆን ስካልዚ የተባሉ የአንድ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ ናቸው። ሰዎች ስለ ዓለም መጨረሻ የሚናገሩ ፊልሞች የሚማርኳቸው ለምንድን ነው? ስካልዚ ምክንያቱን ሲናገሩ “ፍርሃታችንን አውጥተው ስለሚያሳዩ ነው” ብለዋል። አንተስ በዚህ ሐሳብ ትስማማለህ? ምድርና በላይዋ ላይ ያሉት ፍጥረታት በሙሉ የሚጠፉት እንዴትና መቼ ነው እያልን እንድንፈራ የሚያደርገን በቂ ምክንያት አለ?
በየዕለቱ ማለት ይቻላል የተፈጥሮ አደጋዎች በዓለማችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱ የሚናገሩ ዜናዎችን እንሰማለን። እንዲህ ባሉ አሰቃቂ አደጋዎች ሳቢያ የደረሱ ጉዳቶችን የሚያሳዩ ምስሎች በቴሌቪዥንም ሆነ በኢንተርኔት በተደጋጋሚ ይታያሉ። በገሃዱ ዓለም ያሉ ሰዎች ሲያልቁና አንዳንድ አካባቢዎች ሲወድሙ የሚያሳዩ በርካታ ምስሎችን ነጋ ጠባ ስንመለከት የዓለም መጨረሻ የሚባለው ነገር የፊልም ጉዳይ ብቻ ሳይሆን በእርግጥም አደገኛ ክስተት እንደሆነ ሊሰማን ይችላል።
ከዚህም ባሻገር ሳይንቲስቶች ምድር ልትጠፋ ስለምትችልበት መንገድ የሚናገሩት መላምት ሰዎች የሚሰማቸው ፍርሃት እንዲጨምር ያደርጋል። እንዲያውም አንዳንዶች፣ ምድር ትጠፋለች የሚሉበትን ጊዜ ጭምር ይናገራሉ። መንዝሊ ኖቲስስ ኦቭ ዘ ሮያል አስትሮኖሚካል ሶሳይቲ መጋቢት 2008 ላይ ሪፖርት እንዳደረገው ሁለት የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ፀሐይ ከ7.59 ቢሊዮን ዓመታት ገደማ በኋላ ፕላኔታችንን እንደምትውጣትና ወደ ተንነት እንደምትለውጣት ተንብየዋል።
ምድር በእርግጥ አንድ ቀን ትጠፋ ይሆን?
ፕላኔታችን የምትጠፋበት የመጨረሻ ቀን አለ?
መጽሐፍ ቅዱስ “ትውልድ ይሄዳል፤ ትውልድ ይመጣል፤ ምድር ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል። (መክብብ 1:4) ይሖዋ አምላክ ‘ምድርን እንዳትናወጥ አድርጎ በመሠረቷ ላይ ያጸናት’ ሲሆን የፈጠራትም “ለዘላለም” እንድትኖር አድርጎ ነው። (መዝሙር 104:5) አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፋቸው እነዚህ ቃላት ለማመን የሚከብዱ ናቸው? አንዳንድ ሳይንቲስቶች ምድር እንደምትጠፋ እየተናገሩ አንተ አትጠፋም ብለህ ማመን ያለብህ ለምንድን ነው?
እስቲ በአንድ መደብር መደርደሪያ ላይ ስላሉ ዕቃዎች ለአንድ አፍታ አስብ። አንዳንዶቹ ዕቃዎች ጊዜያቸው የሚያልፍበት ቀን ተጽፎባቸዋል። የሚበላሹበትን ቀን የወሰነው ማን ነው? የመደብሩ ባለቤት ባካበተው ተሞክሮና እውቀት ላይ ተመሥርቶ የሰጠው ግምታዊ ሐሳብ ነው? እንዳልሆነ የታወቀ ነው! ቀኑን የሚወስነው ዕቃውን ያመረተው ፋብሪካ ነው። ፋብሪካው ያመረተውን ዕቃ ከማንም በተሻለ ስለሚያውቅ የሰጠውን ቀን አንጠራጠርም። ታዲያ ፕላኔቷ ምድራችንን በፈጠረው አምላክ የበለጠ መተማመን አይገባንም? ቃሉ ምድር ለዘላለም እንድትኖር አምላክ በጽኑ መሠረት ላይ ‘እንደመሠረታት’ በግልጽ ይናገራል። ምድር የምትጠፋበት ቀን አልተወሰነላትም።—መዝሙር 119:90
ኃላፊነት የጎደላቸው ሰዎች ፕላኔቷ ምድራችንን ፈጽሞ እንዳታገግም አድርገው ያበላሿት ይሆን? በፍጹም! የሚያመርቱትን ዕቃ እንዳይበላሽ አድርገው መሥራት ከማይችሉት የፋብሪካ ባለቤቶች በተለየ መልኩ ይሖዋ ‘ሁሉን ማድረግ ይችላል።’ (ኢዮብ 42:2) ይሖዋ “ከአፌ የሚወጣውም ቃሌ፣ . . . የተላከበትንም ዐላማ ይፈጽማል” በማለት በእርግጠኝነት ሊናገር የቻለው ለዚህ ነው። (ኢሳይያስ 55:11) “ፈጣሪያችን” ለምድር ያለውን ዓላማ ከመፈጸም የሚያግደው ምንም ነገር እንደሌለ መተማመን እንችላለን። (መዝሙር 95:6) ይህ የአምላክ ዓላማ ምንድን ነው? የሚፈጸመውስ እንዴት ነው?
አምላክ በመንግሥቱ አማካኝነት ዓላማውን ይፈጽማል
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ምድር እንደማትጠፋ ዋስትና የሚሰጠን ከመሆኑም በተጨማሪ አምላክ ምድርን የሠራት “የሰው መኖሪያ” እንድትሆን አስቦ እንደሆነ ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) ምድራችን በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው መኖሪያ ብትሆንም የአምላክ ዓላማ ተፈጽሟል ማለት አይደለም።
ይሖዋ “ደስተኛ” አምላክ ከመሆኑም ሌላ “ፍትሕን ይወዳል።” (1 ጢሞቴዎስ 1:11፤ መዝሙር 37:28) ዓላማው ሰዎች ሁሉ ፍትሕ በሰፈነበት ሁኔታ ውስጥ በደስታ እንዲኖሩ ነው። አምላክ ይህን ዓላማውን ከግብ ለማድረስ በሰማይ አንድ መንግሥት እንደሚመሠርትና መንግሥቱ መላዋን ምድር እንደሚገዛ አስቀድሞ ተናግሯል። (ዳንኤል 2:44) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ስለ አምላክ መንግሥት አዘውትሮ ይናገር ነበር። ኢየሱስ፣ ምድር በዚህ መንግሥት በምትተዳደርበት ጊዜ ይሖዋ አስቦት የነበረውን የተትረፈረፈ በረከት እንደምታገኝ ስለሚያውቅ ደቀ መዛሙርቱ ስለዚህ መንግሥት እንዲጸልዩ አበረታቷቸዋል። (ማቴዎስ 6:9, 10፤ 24:14) ከእነዚህ በረከቶች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
▪ አምላክ ጦርነትን በሙሉ እንደሚያስወግድ ቃል ስለገባ ሰላምና ደኅንነት ይሰፍናል። —መዝሙር 46:9
▪ ሁሉም ሰው በቂ ምግብ ይኖረዋል። —መዝሙር 72:16
▪ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል ሰው [ስለማይኖር]” የጤና ጉዳይ አሳሳቢ አይሆንም። —ኢሳይያስ 33:24
▪ ‘ሞት ስለማይኖር’ ሐዘን ያከትማል። —ራእይ 21:4
▪ አምላክ ሕዝቦቹ የራሳቸውን ቤት ሠርተው ያለ ስጋት ‘ለዘላለም ደስ ብሏቸው’ እንደሚኖሩ ቃል ገብቷል።—ኢሳይያስ 65:17-24
ከላይ ያሉትን በረከቶች ለማግኘት እንደምትናፍቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ አስቀድሞ የተናገራቸውን ነገሮች ለመፈጸም ከፍተኛ ጉጉት አለው። (ኢሳይያስ 9:6, 7) ሆኖም ‘አምላክ ቃል የገባቸው ነገሮች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተመዘገቡ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት አልፈዋል። ታዲያ እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያላገኙት ለምንድን ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።
የአምላክ ትዕግሥት ለመዳን ያበቃናል
“ይሖዋ የገባውን ቃል ለመፈጸም [እንደማይዘገይ]” እርግጠኛ ሁን። አምላክ በፍቅሩ ተነሳስቶ ትዕግሥት እንዳሳየን መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። በዚህም ምክንያት ‘የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን እንድንቆጥር’ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። (2 ጴጥሮስ 3:9, 15) ይሁንና የአምላክ ትዕግሥት ለመዳናችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
በመጀመሪያ ደረጃ፣ አምላክ ምድርን አስተማማኝና የተትረፈረፈ በረከት ያለባት መኖሪያ አድርጎ ጻድቅ ለሆኑ ሰዎች ከመስጠቱ በፊት ‘ምድርን እያጠፉ ያሉትን ማጥፋት’ እንዳለበት ያውቃል። (ራእይ 11:18) ሆኖም ይሖዋ ሰዎችን ስለሚወድ ‘ማንም እንዲጠፋ አይፈልግም።’ በመሆኑም በሰማይ የሚኖረው ታጋሹ አባታችን ሰዎች ‘ከክፉ ሥራቸው እንዲመለሱ እያስጠነቀቀ’ ነው። በዚህም ምክንያት ይሖዋ የመንግሥቱ መልእክት በዓለም ዙሪያ እንዲሰበክ እያደረገ ነው።a (ሕዝቅኤል 3:17, 18) አምላክ የሚሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ሰምተው ከጽድቅ መሥፈርቶቹ ጋር ተስማምተው ለመኖር ጥረት የሚያደርጉ ሁሉ መዳን የሚያገኙ ከመሆኑም ባሻገር ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።
ለመዳን ወደ አምላክ ተመለስ
መጽሐፍ ቅዱስ “ምሥራች” እንደያዘልን ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 24:14) አምላክ ምድራችን ፈጽሞ እንደማትጠፋ የተናገረውን መሬት ጠብ የማይል ተስፋ ይዟል! ከዚህም በተጨማሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙት ትንቢቶች መሠረት ‘ለአፍታ እንጂ ክፉ ሰው እንደማይዘልቅ’ እምነት ልናሳድር እንችላለን። በቅርቡ በአምላክ ዓይን ጻድቅ የሆኑ ሰዎች ብቻ “ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።” (መዝሙር 37:9-11, 29፤ ማቴዎስ 5:5፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያው ጊዜ ድረስ ግን አምላክ በትዕግሥት ‘እናንተ በምድር ዳርቻ የምትገኙ ሁሉ ትድኑ ዘንድ ወደ እኔ ተመለሱ’ የሚል ጥሪ ማቅረቡን ይቀጥላል። (ኢሳይያስ 45:22) አንተ ለዚህ ጥሪ ምን ምላሽ ትሰጣለህ?
ወደ አምላክ ለመመለስ ለምን ቁርጥ ውሳኔ አታደርግም? መዝሙር 37:34 እንዲህ በማለት ያሳስበናል፦ “[የይሖዋን] ደጅ ጥና፤ መንገዱንም ጠብቅ፤ ምድሪቱን ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል።” የይሖዋ ምሥክሮች፣ አምላክ ለምድር ስላለው ዘላለማዊ ዓላማ ይበልጥ እንድትገነዘብ እንዲሁም ይህ ዓላማው ሲፈጸም ከሚመለከቱት ሰዎች መካከል ለመገኘት ምን ማድረግ እንዳለብህ እንድታውቅ አንተን ለመርዳት ፈቃደኞች ናቸው።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በ236 አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ከሰባት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ የሰጠውን ትእዛዝ በመከተል አምላክ ለምድር ስላወጣው ታላቅ ዓላማ እንዲያውቁ ሰዎችን ለመርዳት በየዓመቱ አንድ ቢሊዮን ተኩል ሰዓት ያሳልፋሉ።
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
NASA photo