የሰይጣን አገዛዝ እንደማይሳካ የተረጋገጠ ነው
“ክፉዎች . . . መልካም አይሆንላቸውም።”—መክ. 8:13
1. በቅርቡ ክፉዎች ለፍርድ እንደሚቀርቡ ማወቃችን የምሥራች ነው የምንለው ለምንድን ነው?
ይዋል ይደር እንጂ ክፉዎች ለፍርድ መቅረባቸው አይቀርም። ለሠሩት ክፋት ከተጠያቂነት አያመልጡም። (ምሳሌ 5:22፤ መክ. 8:12, 13) በተለይ ጽድቅን ለሚወዱ እንዲሁም በክፉዎች በደልና እንግልት ለደረሰባቸው ሰዎች ይህ ትልቅ ምሥራች ነው። ለፍርድ ከሚቀርቡት ክፉ አድራጊዎች ዋነኛው፣ የክፋት አባት የሆነው ሰይጣን ዲያብሎስ ነው።—ዮሐ. 8:44
2. በኤደን የተነሳው ወሳኝ ጉዳይ እልባት እንዲያገኝ ጊዜ መስጠት ያስፈለገው ለምንድን ነው?
2 በኤደን የተከሰተውን ሁኔታ እንመልከት፤ ሰይጣን ራሱን ከመጠን በላይ ከፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌ ስለተጠናወተው ሰዎች ለይሖዋ አገዛዝ ጀርባቸውን እንዲሰጡ ለማድረግ ተነሳሳ። የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችንም ከሰይጣን ጋር በመተባበር የይሖዋን የመግዛት መብት ተገዳደሩ፤ በዚህ መንገድ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠሩ። (ሮም 5:12-14) ይሖዋ እነዚህ ፍጥረታት የእሱን አገዛዝ በመናቅ የተከተሉት የዓመፀኝነት ጎዳና ምን እንደሚያስከትልባቸው ያውቅ እንደነበር ጥርጥር የለውም። አካሄዳቸው መጥፎ ውጤት ማስከተሉ የማይቀር ቢሆንም የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታት በሙሉ ይህንን መመልከት እንዲችሉ አጋጣሚ ሊያገኙ ይገባል። በመሆኑም ለዚህ ጉዳይ እልባት ለማስገኘትና ዓመፀኞቹ እንደተሳሳቱ በማያሻማ መንገድ ለማሳየት ጊዜ መስጠት ያስፈልግ ነበር።
3. ለሰብዓዊ መንግሥታት ምን አመለካከት አለን?
3 የሰው ልጆች የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን በማለታቸው የራሳቸውን አገዛዝ ማቋቋም ግድ ሆነባቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ በጻፈው ደብዳቤ ላይ እነዚህን ሰብዓዊ መንግሥታት ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ በማለት ጠርቷቸዋል። በጳውሎስ ዘመን ‘የበላይ ባለሥልጣናት’ የሚለው አገላለጽ በዋነኝነት የሚያመለክተው በንጉሠ ነገሥት ኔሮ (የገዛው ከ54-68 ዓ.ም. ነው) የሚመራውን የሮም መንግሥት ነበር። ጳውሎስ እነዚህ የበላይ ባለሥልጣናት “አንጻራዊ ሥልጣናቸውን ያገኙት ከአምላክ ነው” በማለት ጽፏል። (ሮም 13:1, 2ን አንብብ።) ጳውሎስ ይህን ሲል ሰብዓዊ አገዛዝ ከአምላክ አገዛዝ የተሻለ እንደሆነ መናገሩ ነበር? በጭራሽ። ጳውሎስ ሊገልጽ የፈለገው ነጥብ ይሖዋ ሰብዓዊ አገዛዝ እንዲኖር እስከፈቀደ ድረስ ክርስቲያኖች “አምላክ ያደረገውን ዝግጅት” ማክበርና እነዚህን ገዢዎች መቀበል ያለባቸው መሆኑን ነው።
ወደ ጥፋት የሚመራ መንገድ
4. ሰብዓዊ አገዛዝ እንደማይሳካ ሳይታለም የተፈታ ነው የምንለው ለምን እንደሆነ አብራራ።
4 ያም ሆኖ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ሰብዓዊ አገዛዝ እንደማይሳካ ሳይታለም የተፈታ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ዋነኛው ምክንያት ሰብዓዊው አገዛዝ በመለኮታዊ ጥበብ የሚመራ አለመሆኑ ነው። ፍጹም ጥበብ የሚገኘው በይሖዋ ዘንድ ብቻ ነው። በመሆኑም የተሳካ አገዛዝ ለማቋቋም ምን እንደሚያስፈልግ ከይሖዋ በስተቀር አስተማማኝ መመሪያ መስጠት የሚችል አንድም አካል የለም። (ኤር. 8:9፤ ሮም 16:27) የሰው ልጆች ትክክለኛውን አካሄድ በአብዛኛው የሚያውቁት በሙከራ ሲሆን ይሖዋ ግን ከሁሉ የተሻለው መንገድ የቱ እንደሆነ ምንጊዜም ያውቃል። የይሖዋን መመሪያ የማይከተል ማንኛውም አገዛዝ እንደማይሳካ አንድና ሁለት የለውም። ሰይጣን የተነሳበት ዝንባሌ መጥፎ መሆኑ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ከላይ የተጠቀሰው ምክንያት ብቻ እንኳ ሰይጣን በሰዎች አማካኝነት ለመግዛት ያቀረበው አማራጭ ፈጽሞ እንደማያዋጣ ገና ከጅምሩ ያሳይ ነበር።
5, 6. ሰይጣን ይሖዋን እንዲቃወም ያነሳሳው ምን ሊሆን ይችላል?
5 በአብዛኛው ሲታይ አስተዋይ የሆነ ሰው እንደማይሳካ የሚያስታውቀን ሥራ ለመጀመር አይነሳም። አሻፈረኝ ብሎ እንዲህ ያለውን ሥራ ለመሥራት ከተነሳ ግን ሳይወድ በግዱ ከስህተቱ ይማራል። ታሪክ በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳሳየው ሁሉን ቻይ የሆነውን ፈጣሪ መቃወም ከንቱ ነው። (ምሳሌ 21:30ን አንብብ።) ይሁን እንጂ ሰይጣን ራሱን ከመጠን በላይ ከፍ አድርጎ የመመልከት ዝንባሌና ኩራት ስላሳወረው ይሖዋን ለመቃወም ተነሳ። ዲያብሎስ፣ የመረጠው መንገድ መጨረሻው ጥፋት እንደሆነ እያወቀ ገባበት።
6 ሰይጣን የነበረው ዓይነት የእብሪተኝነት መንፈስ ያንጸባረቀ አንድ የባቢሎን ንጉሥ እንዲህ ሲል በጉራ ተናግሮ ነበር፦ “ወደ ሰማይ ዐርጋለሁ፤ ዙፋኔንም ከእግዚአብሔር ከዋክብት በላይ ከፍ አደርጋለሁ፤ በተራራው መሰብሰቢያ፣ በተቀደሰውም ተራራ ከፍታ ላይ በዙፋኔ እቀመጣለሁ፤ ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።” (ኢሳ. 14:13-15) ይህ ንጉሥ የተከተለው የሞኝነት አካሄድ ከንቱ ሆኗል፤ የባቢሎን ሥርወ መንግሥትም አሳፋሪ ውድቀት ደርሶበታል። በተመሳሳይም ሰይጣንና እሱ የሚመራው ዓለም በቅርቡ ሙሉ በሙሉ ድል ይነሳል።
የፈቀደው ለምንድን ነው?
7, 8. ይሖዋ ክፋት ለተወሰነ ጊዜ እንዲቀጥል መፍቀዱ ያስገኛቸው አንዳንድ ጥቅሞች የትኞቹ ናቸው?
7 አንዳንዶች ‘ይሖዋ፣ ሰዎች ከሰይጣን ጎን እንዳይቆሙ ለምን አልከለከላቸውም? ሰይጣን ከአገዛዝ ጋር በተያያዘ ያቀረበውን የማያዋጣ አማራጭ እንዳይከተሉስ ለምን አላደረገም?’ ብለው ያስቡ ይሆናል። ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ በመሆኑ ይህንን ማድረግ ይችል እንደነበረ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘፀ. 6:3) ያም ቢሆን እንዲህ አላደረገም። ጥበበኛ አምላክ በመሆኑ የሰው ልጆች የመረጡትን የዓመፅ አካሄድ ለማስቆም ጣልቃ ሳይገባ የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ መፍቀዱ ውሎ አድሮ የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። ይሖዋ ጻድቅና አፍቃሪ ገዥ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ መረጋገጡ አይቀርም፤ ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆችም አምላክ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ በማድረጉ ይጠቀማሉ።
8 የሰው ልጆች ሰይጣን ያቀረበላቸውን ግብዣ ባይቀበሉና ከአምላክ አገዛዝ ነፃ ሆነው ራሳቸውን ለመምራት ባይነሱ ኖሮ ሰብዓዊው ኅብረተሰብ እዚህ ሁሉ መከራ ውስጥ ባልገባ ነበር! ያም ቢሆን ይሖዋ፣ ሰዎች ለተወሰነ ጊዜ ያህል ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ ያስገኛቸው ጥቅሞች አሉ። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች አምላክን መስማትና በእሱ መታመን የጥበብ አካሄድ መሆኑን በግልጽ እንዲገነዘቡ አስችሏቸዋል። ባለፉት ዘመናት ሁሉ የሰው ልጆች የተለያዩ ዓይነት አገዛዞችን የሞከሩ ቢሆንም አንዳቸውም ቢሆኑ ሙሉ በሙሉ ስኬታማ አልሆኑም። ይህ ሐቅ የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋ አገዛዝ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ የነበራቸውን እምነት አጠናክሮላቸዋል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ክፉ የሆነው የሰይጣን አገዛዝ እንዲቀጥል መፍቀዱ ታማኝ የሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን ጨምሮ በመላው የሰው ዘር ላይ መከራ አምጥቷል። ይሁንና ይሖዋ ክፋት ለጊዜው እንዲቀጥል መፍቀዱ ለእነዚህ ታማኝ አምላኪዎቹ የሚያስገኛቸው ሌሎች ጥቅሞችም አሉ።
ይሖዋ እንዲከበር ምክንያት የሆነ ዓመፅ
9, 10. የሰይጣን አገዛዝ ይሖዋ እንዲከበር ምክንያት የሆነው እንዴት እንደሆነ አብራራ።
9 ይሖዋ፣ የሰው ልጆች በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንዲሆኑና ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ መፍቀዱ የእሱ አገዛዝ ትክክለኛ አለመሆኑን የሚያሳይ አይደለም። እንዲያውም ሁኔታው የተገላቢጦሽ ነው! ኤርምያስ የሰው ልጅ ራሱን መግዛት እንደማይችል በመንፈስ ተመርቶ የጻፈው ሐሳብ ትክክል መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል። (ኤርምያስ 10:23ን አንብብ።) ከዚህም በተጨማሪ ሰይጣን ያስነሳው ዓመፅ ይሖዋ ግሩም የሆኑትን ባሕርያቱን ጉልህ በሆነ ሁኔታ እንዲያሳይ አጋጣሚ ከፍቶለታል። እንዴት?
10 የሰይጣን አገዛዝ ላስከተለው ከፍተኛ ጉዳት የዓይን ምሥክሮች መሆናችን የይሖዋ ፍጹም ባሕርያት ይበልጥ ጎልተው እንዲታዩን አድርጓል፤ እንዲህ ያለው አጋጣሚ ባይፈጠር ኖሮ እነዚህን ባሕርያት በዚህ መልኩ ማየት አንችልም ነበር። ይህ መሆኑ ይሖዋ በሚወዱት ዘንድ እንዲከበር አድርጓል። በእርግጥም፣ ነገሩ ፈጽሞ የማይመስል ቢሆንም የሰይጣን አገዛዝ አምላክ እንዲከበር ምክንያት ሆኗል። የሰይጣን አገዛዝ፣ ይሖዋ በሉዓላዊነቱ ላይ ለተነሳው ለዚህ ግድድር በላቀ መንገድ ምላሽ መስጠቱ ግልጽ ሆኖ እንዲታይ አድርጓል። ይህንን ሐቅ ይበልጥ ለመረዳት እንድንችል አንዳንዶቹን የይሖዋ ባሕርያት እንደ ምሳሌ በመውሰድ የሰይጣን ክፉ አገዛዝ ይሖዋ እነዚህን ባሕርያቱን በተለየ መንገድ እንዲያሳይ ምክንያት የሆነው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
11. የይሖዋ ፍቅር የታየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
11 ፍቅር። መጽሐፍ ቅዱስ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐ. 4:8) አምላክ የሰው ልጆችን መፍጠሩ በራሱ የፍቅሩ መግለጫ ነው። ግሩምና ድንቅ የሆነው አፈጣጠራችንም አምላክ አፍቃሪ ለመሆኑ ማስረጃ ነው። በተጨማሪም ይሖዋ የሰው ልጆች ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች አሟልታ የያዘች ውብ መኖሪያ በፍቅር ተነሳስቶ ሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 1:29-31፤ 2:8, 9፤ መዝ. 139:14-16) ሰብዓዊው ቤተሰብ ኃጢአት ከሠራ በኋላ ደግሞ ይሖዋ ፍቅሩን በተለየ መንገድ ገልጿል። እንዴት? ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሎ እንደተናገረ ጽፏል፦ “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) አምላክ፣ አንድያ ልጁን ለኃጢአተኞች ቤዛ እንዲሆን ወደ ምድር ከመላክ የበለጠ ለሰው ዘር ያለውን ፍቅር ሊገልጽ የሚችልበት ምን መንገድ ይኖራል? (ዮሐ. 15:13) ይህ ታላቅ የፍቅር መግለጫ ለሰው ልጆችም ምሳሌ ይሆናቸዋል፤ ምክንያቱም በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው አምላክ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳየው ዓይነት ፍቅር እንዲያንጸባርቁ አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ኢየሱስም እንዲህ አድርጎ ነበር።—ዮሐ. 17:25, 26
12. የይሖዋ ኃይል የታየው በምን መንገድ ነው?
12 ኃይል። ሕይወትን ለመፍጠር የሚያስችል ኃይል ያለው ‘ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ’ ብቻ ነው። (ራእይ 11:17፤ መዝ. 36:9) አንድ ሰው ሲወለድ የሚኖረው ሁኔታ ምንም ካልተጻፈበት ወረቀት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውየው ሲሞት ግን ወረቀቱ የግለሰቡን ማንነትና ባሕርያት በቀረጹት በሕይወቱ ውስጥ ባደረጋቸው ውሳኔዎች፣ በወሰዳቸው እርምጃዎችና ባሳለፋቸው ተሞክሮዎች የተሞላ ይሆናል። ይሖዋ ይህን ሁሉ መረጃ በማስታወሻ መዝገቡ ላይ ያሰፈረው ያህል ያስታውሰዋል። ይሖዋ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ግለሰቡ የቀድሞ ስብዕናውን እንደተላበሰ ከሞት ሊያስነሳው ይችላል። (ዮሐ. 5:28, 29) የአምላክ የመጀመሪያ ዓላማ ሰዎች እንዲሞቱ ባይሆንም ሞት፣ ይሖዋ በመቃብር ውስጥ ያሉ ሙታንን እንኳ ሕያው የማድረግ ኃይል እንዳለው ለማሳየት አጋጣሚ ከፍቷል። በእርግጥም ይሖዋ ‘ሁሉን ቻይ አምላክ’ ነው።
13. ኢየሱስ መሥዋዕት መሆኑ የይሖዋ ፍትሕ ፍጹም መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
13 ፍትሕ። ይሖዋ አይዋሽም፤ ፍትሕ የጎደለው ነገርም አያደርግም። (ዘዳ. 32:4፤ ቲቶ 1:2) መሥዋዕትነት የሚያስከፍለው ቢሆንም እንኳ ላቅ ያሉ የእውነትና የፍትሕ መሥፈርቶቹን ምንጊዜም ይጠብቃል። (ሮም 8:32) ይሖዋ፣ የሚወደው ልጁ አምላክን እንደተሳደበ ከሃዲ ተቆጥሮ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ሲመለከት ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም! ይሁንና ይሖዋ ፍጹም የሆነውን የፍትሕ መሥፈርቱን ለመጠበቅና ኃጢአተኛ ለሆኑት የሰው ልጆች ያለውን ፍቅር ለማሳየት ሲል ይህ አሳዛኝ ክንውን እንዲፈጸም ፈቅዷል። (ሮም 5:18-21ን አንብብ።) ዓለም በፍትሕ መጓደል የተሞላ መሆኑ ይሖዋ በፍትሑ አቻ የማይገኝለት አምላክ መሆኑን ለማሳየት አጋጣሚ ከፍቷል።
14, 15. የይሖዋ የላቀ ጥበብና ትዕግሥት ከታየባቸው መንገዶች አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?
14 ጥበብ። አዳምና ሔዋን ኃጢአት እንደሠሩ ይሖዋ የእነሱ ዓመፅ ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ ለማስተካከል የሚጠቀምበትን መንገድ ገለጸ። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ እንዲህ ዓይነት አፋጣኝ እርምጃ መውሰዱና ከዚህ ዓላማው ጋር የተያያዙ ዝርዝር ጉዳዮችን ደረጃ በደረጃ ለአገልጋዮቹ መግለጡ ጥበቡን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። (ሮም 11:33) አምላክ ነገሮችን በተሳካ ሁኔታ እንዳያከናውን ምንም ነገር ሊያግደው አይችልም። የሥነ ምግባር ብልግናና ጦርነት በተስፋፋበት እንዲሁም ምክንያታዊነት የጎደላቸው፣ የማይታዘዙ፣ ምሕረት የለሽ፣ አድልዎ የሚያደርጉና ግብዝ የሆኑ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ይሖዋ እውነተኛ ጥበብ ምን እንደሆነ ለፍጥረታቱ ለማሳየት ሰፊ አጋጣሚ አግኝቷል። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ ብሏል፦ “ከላይ የሆነው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም በአድልዎ ሰዎችን የማይለያይና ግብዝነት የሌለበት ነው።”—ያዕ. 3:17
15 ትዕግሥትና ቻይነት። ይሖዋ ፍጽምና ከጎደላቸው፣ ኃጢአተኞች ከሆኑና ድክመቶች ካሉባቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት ማድረግ ባያስፈልገው ኖሮ ትዕግሥቱንና ቻይነቱን በግልጽ የምናይበት አጋጣሚ አይኖርም ነበር። ይሖዋ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የሰው ልጆችን ለመታገሥ ፈቃደኛ መሆኑ እነዚህን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ ማሳየት እንደሚችል ማስረጃ ይሆናል፤ ለዚህም በጣም አመስጋኞች ልንሆን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ “የጌታችንን ትዕግሥት እንደ መዳን ቁጠሩት” ማለቱ የተገባ ነው።—2 ጴጥ. 3:9, 15
16. ይሖዋ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑ በጣም አስደሳች ነው የምንለው ለምንድን ነው?
16 ይቅር ለማለት ፈቃደኛ የሆነ። ሁላችንም ኃጢአተኞች በመሆናችን ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን። (ያዕ. 3:2፤ 1 ዮሐ. 1:8, 9) ይሖዋ “ይቅርታው ብዙ” በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! (ኢሳ. 55:7) ልንዘነጋው የማይገባ ሌላም ነገር አለ፦ ፍጽምና የጎደለን ኃጢአተኞች ሆነን በመወለዳችን አምላክ ስህተታችንን ይቅር ማለቱ የሚያስገኘውን ደስታ ማጣጣም ችለናል። (መዝ. 51:5, 9, 17) ግሩም የሆነውን ይህን የይሖዋ ባሕርይ በግለሰብ ደረጃ በሕይወታችን መመልከታችን ለእሱ ያለንን ፍቅር የሚያጠናክረው ከመሆኑም በላይ ከሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ምሳሌውን እንድንከተል ያነሳሳናል።—ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።
ዓለም የታመመው ለምንድን ነው?
17, 18. የሰይጣን አገዛዝ ስኬታማ እንዳልሆነ የታየው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
17 ባለፉት ዘመናት ሁሉ በተደጋጋሚ እንደታየው የሰይጣን አገዛዝ ውጤት የሆነው መላው የዓለም ሥርዓት ስኬታማ መሆን አልቻለም። ዚ ዩሮፒያን የተባለው ጋዜጣ በ1991 እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዓለም ታሟል? አዎ፣ በእርግጥ ታሟል፤ ይሁንና የሕመሙ መንስኤ አምላክ ሳይሆን ራሳቸው ሰዎች ናቸው።” ይህ ምንኛ እውነት ነው! የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሰይጣን ተጽዕኖ ተሸንፈው ከይሖዋ አገዛዝ ይልቅ ሰብዓዊ አገዛዝን መረጡ። ይህን በማድረጋቸውም ስኬታማ ሊሆን የማይችል አገዛዝ እንዲቋቋም መንገድ ከፈቱ። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሰዎች የሚደርስባቸው ሥቃይና መከራ ሰብዓዊ አገዛዝ በክፉ ደዌ እንደተጠቃ የሚያሳይ ምልክት ነው።
18 የሰይጣን አገዛዝ በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረተ ነው። ይሁንና ራስ ወዳድነት ለይሖዋ አገዛዝ መሠረት የሆነውን ፍቅርን በፍጹም ሊያሸንፈው አይችልም። የሰይጣን አገዛዝ መረጋጋት፣ ደስታ ወይም ደኅንነት ማምጣት አልቻለም። የይሖዋ አገዛዝ ግን የላቀ መሆኑ ተረጋግጧል! በዘመናችን ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እናገኛለን? አዎን፣ የሚቀጥለው ርዕስ ይህንን ያብራራል።
የሚከተሉትን ጥቅሶች በማንበባችን ስለ አገዛዝ ምን ትምህርት አግኝተናል?
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሰይጣን አገዛዝ ለሰው ልጆች ጥቅም አምጥቶ አያውቅም
[ምንጭ]
U.S. Army photo
WHO photo by P. Almasy
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በመቃብር ውስጥ ያሉ ሙታንን እንኳ ሕያው ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አለው
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ ልጁ መሥዋዕት እንዲሆን መፍቀዱ ፍቅሩንና ፍትሑን የሚያሳይ ነው