ይሖዋ ባደረገልህ ነገሮች ላይ አሰላስል
ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሁለት ደቀ መዛሙርቱ ከኢየሩሳሌም ወደ ኤማሁስ እየተጓዙ ነበር። የሉቃስ ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “እየተነጋገሩና እየተወያዩ ሳሉም ኢየሱስ ራሱ ቀርቦ አብሯቸው መሄድ ጀመረ፤ ነገር ግን እንዳይለዩት ዓይናቸው ተይዞ ነበር።” ከዚያም ኢየሱስ “‘እየሄዳችሁ እንዲህ እርስ በርስ የምትወያዩበት ጉዳይ ምንድን ነው?’ አላቸው። በዚህ ጊዜ በሐዘን እንደተዋጡ ባሉበት ቆሙ።” ደቀ መዛሙርቱ ያዘኑት ለምን ነበር? ኢየሱስ፣ እስራኤላውያንን ከአሕዛብ አገዛዝ ነፃ እንደሚያወጣቸው ያስቡ ነበር፤ ይሁንና ያሰቡት ነገር አልተፈጸመም። እንዲያውም ኢየሱስ ተገደለ። ደቀ መዛሙርቱ ያዘኑት በዚህ ምክንያት ነበር።—ሉቃስ 24:15-21፤ ሥራ 1:6
ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር መወያየት ጀመረ። “ከሙሴና ከነቢያት ሁሉ ጀምሮ ስለ እሱ በቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ የተጻፈውን በሚገባ አብራራላቸው።” በእርግጥም ኢየሱስ በምድር ላይ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ትልቅ ትርጉም ያላቸውና እምነትን የሚያጠናክሩ በርካታ ክንውኖች ተፈጽመዋል! ደቀ መዛሙርቱ የኢየሱስን ማብራሪያ ሲያዳምጡ ሐዘናቸው ወደ ደስታ ተለወጠ። በዚያው ምሽት እርስ በርስ ሲያወሩ “በመንገድ ላይ ሲያነጋግረንና ቅዱሳን መጻሕፍትን ግልጽልጽ አድርጎ ሲያስረዳን ልባችን እንደ እሳት ይቃጠልብን አልነበረም?” ተባባሉ። (ሉቃስ 24:27, 32) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ከሰጡት ምላሽ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
የጠበቅናቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው ምን ይሰማናል?
ወደ ኤማሁስ ይጓዙ የነበሩት ሁለቱ ደቀ መዛሙርት የጠበቋቸው ነገሮች ባለመፈጸማቸው እጅግ አዝነው ነበር። በምሳሌ 13:12 ላይ እንደተገለጸው ዓይነት ስሜት ተሰምቷቸው ነበር፤ ጥቅሱ “ለነገ የሚባል ተስፋ ልብን ያሳምማል” ይላል። በተመሳሳይም አንዳንዶቻችን ይሖዋን ለበርካታ አሥርተ ዓመታት በታማኝነት ስናገለግል በመቆየታችን ‘ታላቁ መከራ’ እስከ አሁን መምጣት እንደነበረበት አስበን ነበር። (ማቴ. 24:21፤ ራእይ 7:14) እንደነዚህ ያሉ የጠበቅናቸው ነገሮች ሳይፈጸሙ በመቅረታቸው ለተወሰነ ጊዜ ብናዝን የሚያስገርም አይሆንም።
ይሁንና ቀደም ሲል የጠቀስናቸው ሁለት ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ ፍጻሜያቸውን ባገኙት ትንቢቶች ላይ እንዲያተኩሩ ከረዳቸው በኋላ እንደገና ደስተኛ እንደሆኑ አስታውስ፤ ከእነዚህ ትንቢቶች መካከል አንዳንዶቹ የተፈጸሙት ደቀ መዛሙርቱ በኖሩበት ዘመን ነበር። እኛም በተመሳሳይ ፍጻሜያቸውን ባገኙ ነገሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ውስጣዊ ደስታችንን ጠብቀን መኖር እንዲሁም የተስፋ መቁረጥ ስሜትን ማሸነፍ እንችላለን። ማይክል የተባለ ለረጅም ዓመታት በሽምግልና ያገለገለ አንድ ክርስቲያን “ይሖዋ ገና ባልፈጸማቸው ነገሮች ላይ አታተኩሩ። ከዚህ ይልቅ እስከ አሁን ባደረጋቸው ነገሮች ላይ አሰላስሉ” በማለት ተናግሯል። ይህ በእርግጥም ግሩም ምክር ነው!
ይሖዋ ያደረጋቸው ነገሮች
ይሖዋ እስከ አሁን ያደረጋቸውን አንዳንድ አስደናቂ ክንውኖች እስቲ እንመልከት። ኢየሱስ “በእኔ እንደሚያምን በተግባር የሚያሳይ እኔ የምሠራቸውን ሥራዎች ይሠራል፤ እንዲያውም . . . ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል” ብሎ ነበር። (ዮሐ. 14:12) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች፣ ክርስቲያኖች በታሪክ ውስጥ ካከናወኗቸው ሁሉ የሚበልጠውን ሥራ እያከናወኑ ነው። ከሰባት ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ታላቁን መከራ በሕይወት እንደሚያልፉ ተስፋ ያደርጋሉ። እስቲ አስበው፣ የዚህን ያህል ብዛት ያላቸው ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች ውስጥ በዚህ ሥራ ተካፍለው አያውቁም! በእውነትም፣ ኢየሱስ እንደተናገረው የአምላክ አገልጋዮች “ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች” እንዲሠሩ ይሖዋ ረድቷቸዋል።
ይሖዋ ሌላስ ምን አድርጎልናል? ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በምሳሌያዊ አነጋገር ከዚህ ክፉ ዓለም ወጥተው እሱ ወዳዘጋጀው መንፈሳዊ ገነት መግባት እንዲችሉ አጋጣሚ ከፍቷል። (2 ቆሮ. 12:1-4) በእጃችን ስላሉት የዚህ ገነት አንዳንድ ገጽታዎች እስቲ ቆም ብለህ አሰላስል። ለምሳሌ ያህል፣ በቤትህ ወይም በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ያለውን የመጻሕፍት መደርደሪያ ለአፍታ ያህል ተመልከት። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫን (እንግሊዝኛ) ገለጥ ገለጥ እያደረግህ መመልከት አሊያም ዎችታወር ላይብረሪን መቃኘት እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማዎችን ማዳመጥ ትችላለህ። በቅርብ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተመለከትካቸውንና ያዳመጥካቸውን ነገሮች መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር። ከዚህም በተጨማሪ ከክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር ስለምናሳልፈው አስደሳች ጊዜ አስብ። ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብና አፍቃሪ የወንድማማች ማኅበር በመስጠት በእጅጉ ባርኮናል፤ በእርግጥም ያለነው በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው!
መዝሙራዊው ዳዊት “ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ ለእኛ ያደረግካቸው ድንቅ ሥራዎች ብዙ ናቸው፣ ለእኛ ያሰብካቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው” ብሏል። (መዝ. 40:5 NW) አዎን፣ ይሖዋ እስከ አሁን ባደረገልንና በፍቅር ተነሳስቶ ለእኛ ባሰባቸው አስደናቂ ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን በሰማይ ለሚገኘው አባታችን ለይሖዋ በሙሉ ልባችን በምናቀርበው አገልግሎት በታማኝነት እንድንጸና ኃይላችንን ያድስልናል።—ማቴ. 24:13
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱን ይሖዋ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ እንዲያሰላስሉ ረድቷቸዋል
[በገጽ 32 ላይ የሚገኙ ፎቶግራፎች]
በቅርብ በተደረገው የአውራጃ ስብሰባ ላይ የተመለከትካቸውንና ያዳመጥካቸውን ነገሮች መለስ ብለህ ለማሰብ ሞክር