በኢፍትሐዊነቱ አቻ የማይገኝለት የፍርድ ሂደት
በጥንት ዘመን ከተሰየሙት ችሎቶች መካከል የዚህን ያህል በጣም የሚታወቅ የፍርድ ሂደት የለም ማለት ይቻላል። ወንጌሎች ተብለው የሚጠሩት አራቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ኢየሱስ ክርስቶስ መታሰሩን፣ ለፍርድ መቅረቡንና መገደሉን አስመልክተው በዝርዝር ተናግረዋል። ስለዚህ የፍርድ ሂደት ማወቅ የሚያስፈልግህ ለምንድን ነው? ይህ የፍርድ ሂደት ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲያስቡት ወዳዘዛቸው ወደሞቱ የሚያደርስ አስፈላጊ ክንውን በመሆኑ ነው፤ እንዲሁም በኢየሱስ ላይ የተሰነዘሩት ክሶች እውነት መሆን አለመሆናቸውን ማረጋገጥ ስለሚኖርብን ነው፤ በተጨማሪም ኢየሱስ በፈቃደኝነት ሕይወቱን በመስጠት የከፈለው መሥዋዕትነት ለአሁኑም ሆነ ለመጪው ሕይወታችን በጣም ከፍተኛ ጠቀሜታ ስላለው ነው።—ሉቃስ 22:19፤ ዮሐንስ 6:40
ኢየሱስ ለፍርድ በቀረበበት ወቅት የፓለስቲና ምድር በሮም ቁጥጥር ሥር ነበረች። ሮማውያን፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሕዝባቸውን በራሳቸው ሕግ እንዲዳኙ ቢፈቅዱላቸውም ወንጀለኞችን በሞት የመቅጣት ሥልጣን ግን የሰጧቸው አይመስልም ነበር። በመሆኑም ኢየሱስ የታሰረው ጠላቶቹ በሆኑት የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ቢሆንም የተገደለው ግን በሮማውያን ነበር። የኢየሱስ ስብከት በዘመኑ የነበሩትን ሃይማኖታዊ መሪዎች ማንነት ስላጋለጠ የሸንጎው አባላት መሞት እንዳለበት ወሰኑ። ሆኖም የሞት ቅጣቱ ሕጋዊ መሠረት እንዳለው ለማስመሰል ፈለጉ። አይሁዶች ይህን ግባቸውን ለማሳካት ያደረጉትን ጥረት አስመልክተው ትንታኔ ያቀረቡ አንድ የሕግ ፕሮፌሰር ጠቅላላ ሂደቱን “በፍርድ አፈጻጸም ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነው ወንጀል” በማለት ሰይመውታል።a
በርካታ ስህተቶች የተፈጸሙበት ችሎት
ሙሴ ለእስራኤላውያን የሰጠው ሕግ “እስከዛሬ ከጸደቁት የሕግ ሥርዓቶች ሁሉ እጅግ የላቀና ምክንያታዊ” እንደሆነ ተገልጿል። ይሁን እንጂ በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ለሁሉም ነገር ሕግ የማውጣት ዝንባሌ የተጠናወታቸው ረቢዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በርካታ ደንቦችን በሕጉ ላይ የጨመሩ ሲሆን ብዙዎቹ ደንቦች ታልሙድ በሚባለው የአይሁድ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ከጊዜ በኋላ ተካተዋል። (“በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት የነበሩት የአይሁድ ሕጎች” የተሰኘውን በገጽ 20 ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።) ታዲያ የኢየሱስን ጉዳይ ለማየት የተሰየመው ችሎት ቅዱስ ጽሑፋዊ ከሆኑትም ሆነ ከዚያ ውጪ ከነበሩት ሕጎች አንጻር ሲታይ ምን ይመስል ነበር?
ኢየሱስ የታሰረው ሁለት ምሥክሮች ወንጀል እንደፈጸመ የሚያረጋግጥ ተመሳሳይ የምሥክርነት ቃል ለፍርድ ቤት ካቀረቡ በኋላ ነበር? የኢየሱስ መታሰር ሕጋዊ መሠረት እንዲኖረው ይህ ቅድመ ሁኔታ መሟላት ይገባው ነበር። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በፓለስቲና ምድር አንድ አይሁዳዊ ሕግ እንደተጣሰ ሲሰማው ችሎት ፊት ቀርቦ ክሱን መመሥረት የሚኖርበት በመደበኛ የሥራ ሰዓት ነበር። ፍርድ ቤቶች የቀረበላቸውን ክስ መመርመር እንጂ ክስ እንዲመሠረት ሌሎችን የማነሳሳት ሥልጣን አልነበራቸውም። ክስ መመሥረት የሚችሉት ተፈጽሟል ለሚባለው ወንጀል የዓይን ምሥክሮች የሆኑ ሰዎች ብቻ ነበሩ። የፍርድ ሂደቱ የሚጀምረው ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች ስለተፈጸመው ወንጀል ተመሳሳይ የሆነ ምሥክርነት ሲሰጡ ነበር። በመሆኑም አንድ ግለሰብ የሚታሰረው ምሥክሮቹ የሰጡትን ቃል መሠረት በማድረግ ነው። አንድ ምሥክር ብቻ የሚሰጠው ቃል ተቀባይነት አልነበረውም። (ዘዳግም 19:15) ከኢየሱስ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎችን ይበልጥ ያሳሰባቸው እሱን ማስወገድ የሚያስችላቸውን “ከሁሉ የተሻለ መንገድ” መፈለግ ብቻ ነበር። “ምቹ አጋጣሚ” ሲያገኙ ማለትም “ሕዝብ በሌለበት” በሌሊት በቁጥጥር ሥር አዋሉት።—ሉቃስ 22:2, 5, 6, 53
ኢየሱስ ሲታሰር በእሱ ላይ የቀረበ ምንም ዓይነት ክስ አልነበረም። ካህናቱንና የሳንሄድሪን ሸንጎ አባላትን ያቀፈው የአይሁድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ምሥክሮች መፈለግ የጀመረው ኢየሱስ ከታሰረ በኋላ ነበር። (ማቴዎስ 26:59) ቃላቸው እርስ በርሱ የሚስማማ ሁለት ምሥክሮች ማግኘት አልቻሉም ነበር። ለነገሩ ምሥክሮችን የመፈለጉ ሥራ የፍርድ ቤቱ መሆን አልነበረበትም። ደግሞም ጠበቃና ደራሲ የሆኑት አሌክሳንደር ቴይለር ኢነስ እንደተናገሩት “አንድ ሰው ምን ወንጀል እንደሠራ አስቀድሞ ሳይገለጽ ያውም የሞት ቅጣት እንዲበየንበት ለማድረግ በፍርድ ወንበር ፊት ማቅረብ ትልቅ በደል ነው ቢባል ተገቢ ነው።”
ኢየሱስን የያዙት ሰዎች የቀድሞ ሊቀ ካህናት ወደነበረው ወደ ሐናንያ ቤት የወሰዱት ሲሆን እሱም ጥያቄ ያቀርብለት ጀመር። (ሉቃስ 22:54፤ ዮሐንስ 18:12, 13) ለሞት የሚያበቃ ክስ የሚመረመረው በሌሊት ሳይሆን በቀን ስለነበር የሐናንያ ድርጊት ግልጽ የሆነ የሕግ ጥሰት ነበር። ከዚህም በላይ ማንኛውም ምርመራ በዝግ ችሎት መካሄድ አልነበረበትም። ኢየሱስ፣ ሐናንያ እሱን በዚህ መንገድ መመርመሩ ሕገ ወጥ ድርጊት እንደሆነ ያውቅ ስለነበር “እኔን ለምን ትጠይቀኛለህ? እኔ የነገርኳቸውን የሰሙትን ሰዎች ጠይቃቸው። እነዚህ የተናገርኩትን ያውቃሉ” በማለት መልስ ሰጠው። (ዮሐንስ 18:21) ሐናንያ መመርመር የነበረበት ተከሳሹን ሳይሆን ምሥክሮቹን ነው። ሐናንያ ቅን አስተሳሰብ ያለው ዳኛ ቢሆን ኖሮ ኢየሱስ የሰጠው መልስ ትክክለኛውን የሕግ ሥርዓት እንዲከተል ያነሳሳው ነበር፤ ይሁን እንጂ ሐናንያ ለፍትሕ ምንም ደንታ አልነበረውም።
ኢየሱስ ይህን መልስ በመስጠቱ አንድ ወታደር በጥፊ የመታው ሲሆን በዚያ ሌሊት የተፈጸመበት ግፍ ይህ ብቻ አልነበረም። (ሉቃስ 22:63፤ ዮሐንስ 18:22) የመማጸኛ ከተሞችን አስመልክቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆነው በዘኍልቍ መጽሐፍ ምዕራፍ 35 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ሕግ ተከሳሹ ወንጀል መፈጸሙ እስኪረጋገጥ ድረስ ምንም ዓይነት እንግልት እንዳይደርስበት ያዛል። ኢየሱስም እንዲህ ያለው የሕግ ከለላ ሊሰጠው ይገባ ነበር።
ከዚያም ኢየሱስን ያሰሩት ሰዎች ወደ ሊቀ ካህናቱ ወደ ቀያፋ ከወሰዱት በኋላ በሌሊት የተጀመረው ሕገ ወጥ ችሎት ቀጠለ። (ሉቃስ 22:54፤ ዮሐንስ 18:24) በዚያም ካህናቱ ሁሉንም የፍትሕ መሠረታዊ ደንቦች ከመጤፍ ሳይቆጥሩ “ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል” መፈላለግ ጀመሩ፤ ሆኖም ኢየሱስ ተናግሯል የተባለውን ነገር በተመለከተ አንድ ዓይነት ቃል መስጠት የቻሉ ሁለት ምሥክሮች እንኳ ማግኘት አልቻሉም። (ማቴዎስ 26:59፤ ማርቆስ 14:56-59) በዚህ ጊዜ ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ በሕግ የሚያስጠይቀውን ነገር እንዲናገር ለማድረግ ዘዴ መፈላለግ ጀመረ። በመሆኑም “ምንም መልስ አትሰጥም? እነዚህ በአንተ ላይ የሚሰጡት ምሥክርነት ምንድን ነው?” በማለት ጠየቀው። (ማርቆስ 14:60) ይህ ዘዴ ከሕጋዊው አሠራር ጋር የሚጣረስ ነበር። ቀደም ሲል የተጠቀሱት ኢነስ እንደገለጹት “ተከሳሹን ጥያቄ ከጠየቁ በኋላ በመልሱ ላይ ተንተርሶ ግለሰቡን መወንጀል መደበኛውን የፍትሕ ደንብ መጣስ ነው።”
በመጨረሻም ሸንጎው ኢየሱስ ከተናገረው ውስጥ ሰበብ የሚሆን አንድ ነገር አገኘ። ኢየሱስን “የብሩኩ ልጅ ክርስቶስ አንተ ነህ?” ብለው ሲጠይቁት “አዎን ነኝ፤ እናንተም የሰው ልጅ በኃያሉ ቀኝ ተቀምጦ በሰማይ ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” አላቸው። በዚህ ጊዜ ካህናቱ በሙሉ አምላክን እንደ ተሳደበ በመቁጠር “ሞት ይገባዋል ብለው ፈረዱበት።”—ማርቆስ 14:61-64b
ለሙሴ በተሰጠው ሕግ መሠረት አንድ ችሎት ለሕዝብ ክፍት መሆን ነበረበት። (ዘዳግም 16:18፤ ሩት 4:1) ኢየሱስ ግን የቀረበው በሚስጥር በተካሄደ ችሎት ፊት ነበር። ኢየሱስን በመደገፍ ሊናገር የሞከረ ወይም እንዲናገር የተፈቀደለት አንድም ሰው አልነበረም። ኢየሱስን መሲሕ ነኝ ለማለት ያስቻሉት መልካም ሥራዎችም አልተመረመሩም። ኢየሱስ የመከላከያ ምሥክሮችን የማቅረብ አጋጣሚ አልተሰጠውም። ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን ዳኞቹ ሥርዓቱን የጠበቀ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አልተከተሉም።
በጲላጦስ ፊት ቀረበ
አይሁዶች ኢየሱስን በሞት ለመቅጣት ሥልጣን ስላልነበራቸው ሳይሆን አይቀርም ሮማዊ ገዥ ወደነበረው ወደ ጳንጥዮስ ጲላጦስ ወሰዱት። ጲላጦስ ያቀረበላቸው የመጀመሪያው ጥያቄ “በዚህ ሰው ላይ የምታቀርቡት ክስ ምንድን ነው?” የሚል ነበር። አይሁዳውያኑ አምላክን ተሳድቧል ብለው በኢየሱስ ላይ የመሠረቱት የሐሰት ክስ ለጲላጦስ ምንም ትርጉም እንደሌለው ስላወቁ ያለ ምርመራ እንዲፈርድበት ለማድረግ ይሞክሩ ጀመር። “ይህ ሰው ጥፋተኛ ባይሆን ኖሮ ለአንተ አሳልፈን አንሰጠውም ነበር” አሉት። (ዮሐንስ 18:29, 30) ጲላጦስ ያቀረቡትን ምክንያት አለመቀበሉ አይሁዳውያን “ይህ ሰው ሕዝባችንን ሲያሳምፅ፣ ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ሲከለክልና ‘እኔ ክርስቶስ ንጉሥ ነኝ’ ሲል አግኝተነዋል” የሚል አዲስ ክስ እንዲመሠርቱ አስገደዳቸው። (ሉቃስ 23:2) በመሆኑም አምላክን ተሳድቧል የሚለው ክስ ተጠምዝዞ አገርን ወደ መክዳት ወንጀል ተቀየረ።
‘ለቄሳር ግብር እንዳይከፈል ከልክሏል’ የሚለው ክስ ፈጽሞ ሐሰት ከመሆኑም በላይ ከሳሾቹም ቢሆኑ ይህን በደንብ ያውቃሉ። እንዲያውም ኢየሱስ ያስተማረው የዚህን ተቃራኒ ነበር። (ማቴዎስ 22:15-22) ኢየሱስ ራሱን ንጉሥ አድርጓል የሚል ክስ ቢሰነዘርበትም ጲላጦስ ከፊቱ የቆመው ሰው ለሮም መንግሥት ምንም ዓይነት ሥጋት እንደማይፈጥር ለመገንዘብ ጊዜ አልፈጀበትም። ስለዚህ ጲላጦስ “እኔ ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም” አላቸው። (ዮሐንስ 18:38) ‘ኢየሱስ ጥፋተኛ አይደለም’ የሚለው የጲላጦስ አቋም ችሎቱ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ አልተለወጠም።
መጀመሪያ ላይ ጲላጦስ በወቅቱ በነበረው አንድን እስረኛ በፋሲካ ዕለት የመፍታት ልማድ ተጠቅሞ ኢየሱስን በነፃ ለመልቀቅ ሞክሮ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ጲላጦስ በኢየሱስ ፈንታ በሕዝብ ዓመፅና በነፍስ ግድያ ታስሮ የነበረውን በርባንን ፈታው።—ሉቃስ 23:18, 19፤ ዮሐንስ 18:39, 40
ቀጥሎም ሮማዊው ገዥ አስታራቂ ሐሳብ በማቅረብ ኢየሱስን ለመፍታት ሙከራ አደረገ። ኢየሱስን ከገረፉትና የእሾህ አክሊል ደፍተውበት ሐምራዊ ልብስ ካለበሱት በኋላ እንዲደበድቡት ብሎም እንዲያሾፉበት አደረገ። ከዚያም ጲላጦስ ኢየሱስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት በድጋሚ ተናገረ። ጲላጦስ ‘እናንተ ካህናት፣ ይህ አይበቃችሁም?’ ብሎ የተናገረ ያህል ነበር። ምናልባት በሮማውያን ግርፋት የተንገላታውን ይህን ሰው ሲያዩ የበቀል ምኞታቸው ይረካል ወይም ይራሩለት ይሆናል ብሎ ተስፋ አድርጎ ሊሆን ይችላል። (ሉቃስ 23:22) ሆኖም ያሰበው አልተሳካም።
“ጲላጦስ ኢየሱስን መፍታት የሚችልበትን መንገድ ያስብ ጀመር። አይሁዳውያኑ ግን ‘ይህን ሰው ከፈታኸው አንተ የቄሳር ወዳጅ አይደለህም። ራሱን ንጉሥ የሚያደርግ ሰው ሁሉ የቄሳር ተቃዋሚ ነው’ እያሉ ጮኹ።” (ዮሐንስ 19:12) በዚያ ዘመን ቄሳር የነበረው ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ ከፍተኛ ሥልጣን ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ እምነት አጉዳይ እንደሆነ የተሰማውን ማንኛውንም ሰው በሞት በመቅጣት ይታወቅ ነበር። ጲላጦስ ደግሞ ከዚህ ቀደም አይሁዳውያንን አበሳጭቷቸዋል፤ በመሆኑም በእምነት አጉዳይነት ወንጀል ተጠያቂ መሆን ይቅርና ከአይሁዳውያን ጋር ሌላ ግጭት መፍጠር እንኳ አልፈለገም። ጲላጦስ የሕዝቡ ዛቻ ውስጠ ወይራ እንደሆነ ወይም በተዘዋዋሪ እያስፈራሩት እንደሆነ ስለገባው ፍርሃት አደረበት። በዚህ ምክንያት ለዛቻቸው በመንበርከክ ምንም ጥፋት የሌለበትን ኢየሱስን እንዲሰቅሉት አሳልፎ ሰጣቸው።—ዮሐንስ 19:16
ማስረጃው እንደገና ሲመረመር
ብዙ የሕግ ተንታኞች በኢየሱስ ላይ ስለፈረደው ችሎት የሚገልጹትን የወንጌል ዘገባዎች መርምረዋል። ተንታኞቹ ችሎቱ ‘ፍትሕ የሌለበትና ለይስሙላ የተሰየመ ነው’ የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። አንድ ጠበቃ እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ችሎቱ በእኩለ ሌሊት ተጀምሮ በጠዋት ማለቁ እንዲሁም በዚህ ጊዜ ውስጥ የፍርድ ብይን መሰጠቱ የዕብራውያንን ሕግና ደንብም ሆነ የፍትሕ መሠረታዊ ደንቦችን የሚጥስ ተግባር ነው።” አንድ የሕግ ፕሮፌሰር “ጠቅላላው ሂደት ከባድ ሕገ ወጥነትና እንደዚህ ያሉ ዓይን ያወጡ ጉድለቶች የሞሉበት በመሆኑ ግድያው የሸንጎው አባላት እንደፈጸሙት ተደርጎ ቢታይ ምንም አያስገርምም” በማለት ተናግረዋል።
ኢየሱስ ንጹሕ ሰው ነበር። ሆኖም የእሱ ሞት ታዛዥ ለሆኑ የሰው ዘሮች መዳን አስፈላጊ እንደሆነ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 20:28) ኢየሱስ ለፍትሕ ታላቅ ፍቅር ስለነበረው እስከ ዛሬ ከተፈጸሙት የግፍ ድርጊቶች ሁሉ እጅግ ኢፍትሐዊ የሆነውን ዓይን ያወጣ ድርጊት ለመቀበል ፈቃደኛ ሆኗል። ይህን ያደረገው እኛን ለመሰሉ ኃጢአተኞች ሲል ነው። ይህን ፈጽሞ መርሳት አይኖርብንም።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ስለ ኢየሱስ ሞት የሚገልጹትን የወንጌል ዘገባዎች ፀረ አይሁድ ስሜት ለማነሳሳት መጠቀማቸው አሳፋሪ ነገር ነው፤ አይሁዳውያን የነበሩት የወንጌል ጸሐፊዎች እንዲህ ያለ አመለካከት ጨርሶ አልነበራቸውም።
b አምላክን መሳደብ መለኮታዊውን ስም አክብሮት በጎደለው መንገድ መጠቀምን ወይም የአምላክን ሥልጣን ወይም ቦታ መውሰድን ያጠቃልላል። ከሳሾቹ ኢየሱስ ከዚህ ውስጥ አንዱንም እንኳ እንዳደረገ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ማቅረብ አይችሉም።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት የነበሩት የአይሁድ ሕጎች
እጅግ ጥንታዊ እንደሆኑ ከሚታመኑትና በመጀመሪያዎቹ መቶ ዘመናት ዓ.ም. በጽሑፍ ከሰፈሩት በቃል ሲተላለፉ የቆዩ የአይሁድ ወጎች መካከል የሚከተሉት ሕጎች ይገኙበታል፦
▪ ሞት የሚያስፈርዱ ክሶች በሚታዩበት ጊዜ ቀድሞ የሚሰማው ተከሳሹን ነፃ ሊያደርግ የሚችል የመከላከያ ሐሳብ ነበር
▪ ዳኞቹ ተከሳሹን ለማዳን የቻሉትን ያህል ጥረት ማድረግ ነበረባቸው
▪ ዳኞች መከራከር የሚችሉት ተከሳሹን በመደገፍ እንጂ በመቃወም አልነበረም
▪ ምሥክሮቹ ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት እንደተጣለባቸው የሚያስገነዝብ ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸው ነበር
▪ ምሥክሮቹ ምርመራ የሚደረግላቸው ሌሎች ምሥክሮች በሌሉበት ነበር
▪ ምሥክሮቹ በእያንዳንዱ ዝርዝር ጉዳይ ማለትም ቀንን፣ ቦታን፣ ወንጀሉ የተፈጸመበትን ዕለት እንዲሁም እነዚህን የመሳሰሉ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚሰጡት ሐሳብ እርስ በርሱ መስማማት ነበረበት
▪ ሞት የሚያስፈርዱ ክሶች መመርመርም ሆነ ውሳኔ ማግኘት ያለባቸው በቀን መሆን ነበረበት
▪ ሞት የሚያስፈርዱ ክሶች በሰንበት ወይም በበዓል ዋዜማ አይታዩም ነበር
▪ ብይኑ ሞት በሚያስፈርድ ወንጀል የተከሰሰውን ሰው የሚደግፍ ከሆነ ውሳኔው ክሱ በተመሠረተበት ዕለት ሊሰጥ ይችል ነበር፤ ተከሳሹን የማይደግፍ ከሆነ ግን ችሎቱ የሚጠናቀቀው፣ ብይኑ የሚነገረውም ሆነ የሞት ቅጣቱ የሚፈጸመው በቀጣዩ ቀን ነበር
▪ ሞት የሚያስፈርዱ ክሶች ቢያንስ በ23 ዳኞች ይመረመሩ ነበር
▪ ዳኞቹ ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም በሚለው ጉዳይ ላይ ድምፅ ሲሰጡ በዕድሜ ከሁሉ ከሚያንሰው ዳኛ ጀምረው በየተራ መናገር ነበረባቸው፤ ጸሐፍት ደግሞ ወንጀለኛው በነፃ እንዲለቀቅም ሆነ በጥፋተኝነት እንዲፈረድበት ሐሳብ ያቀረቡትን ዳኞች ቃል ይመዘግቡ ነበር
▪ ተከሳሹ ከወንጀል ነፃ ነው የሚል ፍርድ ለመስጠት የአንድ ሰው የድምፅ ብልጫ የሚበቃ ሲሆን በጥፋተኝነት ለመፍረድ ግን ቢያንስ የሁለት ሰው የድምፅ ብልጫ ያስፈልግ ነበር፤ በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ለማሳለፍ የተሰጠው ድምፅ የሚበልጠው በአንድ ብቻ ከሆነ ተቀባይነት ያለው ውሳኔ ላይ እስኪደረስ ድረስ በተደጋጋሚ ሁለት ዳኞች እየተጨመሩ ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ይቀጥል ነበር
▪ የጥፋተኝነት ፍርድ ሲፈረድ ተከሳሹን ደግፎ የሚከራከር ቢያንስ ቢያንስ አንድ ዳኛ ካልተገኘ የሚተላለፈው ፍርድ ተቀባይነት አይኖረውም ነበር፤ በአንድ ድምፅ የጥፋተኝነት ብይን ማሳለፍ “አንድ ሴራ መኖሩን የሚያመለክት” እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር
የኢየሱስን ጉዳይ ያየው ችሎት የፈጸማቸው የሕግ ጥሰቶች
▪ ፍርድ ቤቱ ኢየሱስ ንጹሕ ሰው ለመሆኑ የሚቀርቡ የመከራከሪያ ነጥቦችንም ሆነ የምሥክሮችን ቃል አላዳመጠም
▪ ከዳኞቹ መካከል አንዱም እንኳ ኢየሱስን ደግፎ አልተናገረም፤ ሁሉም ጠላቶቹ ነበሩ
▪ ካህናቱ በኢየሱስ ላይ የሞት ቅጣት እንዲፈረድ ለማድረግ የሐሰት ምሥክሮችን ያፈላልጉ ነበር
▪ የፍርድ ሂደቱ የተከናወነው በሌሊት በዝግ ችሎት ነበር
▪ ችሎቱ ተጀምሮ ያለቀው በአንድ ቀን ያውም በበዓል ዋዜማ ነበር
▪ ኢየሱስ ከመታሰሩ በፊት የቀረበበት ክስ አልነበረም
▪ ኢየሱስ መሲሕ እንደሆነ መናገሩ “አምላክን ተሳድቧል” ያስባለው ሲሆን ይህን ለማረጋገጥ የተደረገ ምርመራም አልነበረም
▪ በጲላጦስ ፊት ከቀረበ በኋላ የክሱ መልክ ተቀየረ
▪ ክሶቹ ሐሰት ነበሩ
▪ ጲላጦስ ኢየሱስ ምንም ጥፋት እንደሌለበት ቢገነዘብም አስገድሎታል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ምሥክሮች በደም ተጠያቂ ናቸው
የአይሁድ ፍርድ ቤቶች ሞት ከሚያስፈርድ ክስ ጋር በተያያዘ የቀረቡ ምሥክሮች ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት የሕይወትን ክቡርነት አስመልክቶ የሚከተለውን ማስጠንቀቂያ ይሰጧቸው ነበር፦
“ምናልባት ምሥክርነት ልትሰጡ የመጣችሁት በይሆናል፣ በአሉባልታ ወይም አንዳችሁ ለሌላው በነገራችሁት ላይ ተመሥርታችሁ አሊያም ‘ከታመነ ሰው የሰማነው ነው’ በማለት አስባችሁ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ በኋላ ላይ ተገቢ በሆኑ ጥያቄዎች እንደምንመረምራችሁ አላወቃችሁ ይሆናል። አንድ ችሎት ከንብረት ጋር በተያያዘ ክስ ሲመሠረት የሚመራበት ሕግ ሞት የሚያስፈርድ ክስን ሲመለከት ከሚመራበት ሕግ የተለየ እንደሆነ ማወቅ ይኖርባችኋል። አንድ ግለሰብ በንብረት ጉዳይ ተከሶ ቢፈረድበት ገንዘብ በመክፈል ራሱን ነፃ ማድረግ ይችላል። ሞት ከሚያስፈርድ የፍርድ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ግን የእሱም [የተከሳሹም] ሆነ ከእሱ [በሐሰት ከተፈረደበት ግለሰብ] ሊወለዱ የሚችሉ ልጆች ደም በእሱ [በሐሰት ምሥክሩ] ላይ ይሆናል።”—የባቢሎናውያን ታልሙድ፣ ሳንሄድሪን፣ 37ሀ
ተከሳሹ ከተፈረደበት የሞት ቅጣቱን በማስፈጸም ረገድ ቅድሚያውን የሚወስዱት ምሥክሮቹ ነበሩ።—ዘሌዋውያን 24:14፤ ዘዳግም 17:6, 7