‘የአምላክ ጥበብ እንዴት ጥልቅ ነው!’
“የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱም ፈጽሞ የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይደረስበት ነው!”—ሮም 11:33
1. ለተጠመቁ ክርስቲያኖች ከሁሉ የላቀው መብት ምንድን ነው?
እስከ ዛሬ ካገኘሃቸው መብቶች ሁሉ የላቀው ምንድን ነው? መጀመሪያ ወደ አእምሮህ የሚመጣው አንድ ኃላፊነት መቀበልህ ሊሆን ይችላል፤ አሊያም እንደ ክብር የምትቆጥረውን አንድ ነገር ማግኘትህ ትዝ ይልህ ይሆናል። ለተጠመቅን ክርስቲያኖች ግን ከሁሉ የላቀው መብት ብቻውን እውነተኛ አምላክ ከሆነው ከይሖዋ ጋር የቅርብ ዝምድና መመሥረት መቻላችን ነው። ይህ ደግሞ ‘በአምላክ ዘንድ ለመታወቅ’ በር ከፍቶልናል።—1 ቆሮ. 8:3፤ ገላ. 4:9
2. ይሖዋን ማወቅና በእሱ ዘንድ መታወቅ ትልቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
2 ይሖዋን ማወቅና በእሱ ዘንድ መታወቅ ትልቅ መብት ነው የምንለው ለምንድን ነው? ይሖዋ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው አካል እሱ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለሚወዳቸው ሁሉ ጥበቃ የሚያደርግ አምላክ በመሆኑም ጭምር ነው። ነቢዩ ናሆም በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግዚአብሔር መልካም ነው፣ በመከራ ቀንም መሸሸጊያ ነው፤ በእርሱ የሚታመኑትንም ያውቃል።” (ናሆም 1:7 የ1954 ትርጉም፤ መዝ. 1:6 የ1954 ትርጉም) የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው እውነተኛውን አምላክና ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን በማወቃችን ላይ ነው።—ዮሐ. 17:3
3. አምላክን ማወቅ ምን ነገሮችን ያካትታል?
3 አምላክን ማወቅ ሲባል ስሙን ከማወቅ የበለጠ ነገርን ይጨምራል። ልክ እንደ አንድ ወዳጃችን ልንቀርበው እንዲሁም የሚወደውንና የሚጠላውን ነገር ልናውቅ ይገባል። ካወቅነው ነገር ጋር ተስማምተን መኖራችን አምላክን በቅርበት እንደምናውቀው ከምናሳይባቸው ዋነኛ መንገዶች አንዱ ነው። (1 ዮሐ. 2:4) ያም ሆኖ ይሖዋን ለማወቅ ከልብ የምንፈልግ ከሆነ ሌላም የሚያስፈልገን ነገር አለ። ይሖዋ ያደረጋቸውን ነገሮች ብቻ ሳይሆን እንዲህ ያደረገው ለምንና እንዴት እንደሆነም ጭምር መረዳት ይኖርብናል። የይሖዋን ዓላማዎች ይበልጥ በተረዳን መጠን ‘የአምላክ ጥበብ’ ባለው ‘ጥልቀት’ እንደመማለን።—ሮም 11:33
የዓላማ አምላክ
4, 5. (ሀ) “ዓላማ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት መንገድ ምን ትርጉም ያስተላልፋል? (ለ) ዓላማን ከዳር ለማድረስ በተለያዩ መንገዶች መጠቀም እንደሚቻል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።
4 ይሖዋ የዓላማ አምላክ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አምላክ “ዘላለማዊ ዓላማ” ይናገራል። (ኤፌ. 3:10, 11) ይህ አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? “ዓላማ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት በግልጽ የተቀመጠ ግብን ለማመልከት ነው፤ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችሉ ከአንድ በላይ መንገዶች ሊኖሩ ይችላሉ።
5 ይህን በምሳሌ ለማስረዳት ያህል፣ አንድ ሰው በአእምሮው ወደያዘው አንድ ቦታ ለመሄድ ይፈልግ ይሆናል። የዚህ ሰው ግብ ወይም ዓላማ እዚያ ቦታ መድረስ ነው። ወዳሰበው ቦታ ሊያደርሱት የሚችሉ የተለያዩ መጓጓዣዎች እንዲሁም አማራጭ መንገዶች ይኖሩ ይሆናል። ከእነዚህ መንገዶች አንዱን መርጦ በሚጓዝበት ጊዜ ያልተጠበቀ የአየር ለውጥና የትራፊክ መጨናነቅ ሊያጋጥመው እንዲሁም መንገድ ሊዘጋበት ይችላል፤ ይህ ደግሞ ሌላ አማራጭ መንገድ እንዲጠቀም ያስገድደዋል። ይህ ሰው በጉዞው ላይ እያለ ምንም ዓይነት ማስተካከያ ማድረግ ቢያስፈልገውም ያሰበው ቦታ ሲደርስ ግቡን ማሳካት ችሏል።
6. ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ እንደ ሁኔታው ለውጦችን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ይሖዋም በተመሳሳይ ዘላለማዊ ዓላማውን ዳር ለማድረስ እንደ ሁኔታው አስደናቂ የሆኑ ለውጦችን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን አሳይቷል። የማሰብ ችሎታ ያላቸው ፍጥረታቱ ነፃ ምርጫ የማድረግ መብት እንዳላቸው ከግምት በማስገባት ዓላማውን ዳር ለማድረስ የሚጠቀምበትን መንገድ እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ፈቃደኛ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ተስፋ ከተሰጠበት ዘር ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። መጀመሪያ ላይ አምላክ፣ አዳምንና ሔዋንን “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም” ብሏቸው ነበር። (ዘፍ. 1:28) ይሖዋ በግልጽ የተናገረው ይህ ዓላማው በኤደን ገነት በተነሳው ዓመፅ የተነሳ ሳይፈጸም ይቀር ይሆን? አይቀርም! የተፈጠረውን አዲስ ሁኔታ ለማስተናገድ ይሖዋ ወዲያውኑ እርምጃ በመውሰድ ዓላማውን ዳር ለማድረስ አማራጭ “መንገድ” ተጠቅሟል። ዓመፀኞቹ ያስከተሉትን ጉዳት የሚያስተካክል ‘ዘር’ እንደሚያስነሳ ትንቢት ተናግሯል።—ዘፍ. 3:15፤ ዕብ. 2:14-17፤ 1 ዮሐ. 3:8
7. በዘፀአት 3:14 ላይ ይሖዋ ራሱን ከገለጸበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?
7 ይሖዋ ዓላማውን ዳር ለማድረስ ሲል እንደ አስፈላጊነቱ ለውጥ በማድረግ የሚፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎች የማስተናገድ ችሎታው ራሱን ከገለጸበት መንገድ ጋር የሚስማማ ነው። ሙሴ የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት እንቅፋት የሚሆኑበትን ምክንያቶች በተናገረ ጊዜ ይሖዋ “መሆን የሚያስፈልገኝን እሆናለሁ” የሚል ማረጋገጫ ሰጠው። በመቀጠልም “ለእስራኤል ልጆች ‘መሆን የሚያስፈልገኝን እሆናለሁ ወደ እናንተ ልኮኛል’ በላቸው” አለው። (ዘፀ. 3:14 NW) አዎን፣ ይሖዋ ዓላማውን በተሟላ ሁኔታ ዳር ለማድረስ ሲል መሆን የሚያስፈልገውን ሁሉ መሆን ይችላል! ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ምዕራፍ 11 ላይ ይህን የሚያስረዳ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሟል። በዚህ ጥቅስ ላይ ስለ አንድ ምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ተናግሯል። ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ እዚህ ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት ማግኘት ይህን ምሳሌ መመርመራችን የይሖዋ ጥበብ ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ይበልጥ እንድንረዳና እንድናደንቅ ያደርገናል።
በትንቢት ከተነገረለት ዘር ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓላማ
8, 9. (ሀ) ስለ ወይራው ዛፍ የሚገልጸውን ምሳሌ ለመረዳት የሚያግዙን የትኞቹ አራት እውነታዎች ናቸው? (ለ) ይሖዋ ዓላማውን በመፈጸም ረገድ እንደ ሁኔታው ለውጦችን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን የሚያሳየው የየትኛው ጥያቄ መልስ ነው?
8 ስለ ወይራው ዛፍ የሚገልጸውን ምሳሌ ለመረዳት እንድንችል በትንቢት ከተነገረለት ዘር ጋር በተያያዘ የይሖዋ ዓላማ ፍጻሜ የሚያገኝበትን መንገድ በተመለከተ አራት እውነታዎችን ማወቅ ያስፈልገናል። አንደኛ፣ ይሖዋ ለአብርሃም “የምድር ሕዝቦች ሁሉ” በዘሩ ወይም በእሱ ተወላጆች አማካኝነት እንደሚባረኩ ቃል ገብቶለት ነበር። (ዘፍ. 22:17, 18) ሁለተኛ፣ ከአብርሃም የዘር ሐረግ የተገኘው የእስራኤል ብሔር “የመንግሥት ካህናት” የማስገኘት መብት ተሰጥቶት ነበር። (ዘፀ. 19:5, 6) ሦስተኛ፣ አብዛኞቹ ሥጋዊ እስራኤላውያን መሲሑን ለመቀበል አሻፈረን ባሉ ጊዜ ይሖዋ “የመንግሥት ካህናት” ለማስገኘት ሌሎች እርምጃዎችን ወስዷል። (ማቴ. 21:43፤ ሮም 9:27-29) በመጨረሻም የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል ኢየሱስ ቢሆንም ሌሎችም የዚህ ዘር ክፍል የመሆን መብት ተሰጥቷቸዋል።—ገላ. 3:16, 29
9 እነዚህ አራት ነጥቦች እንዳሉ ሆነው የራእይ መጽሐፍ ደግሞ ነገሥታትና ካህናት በመሆን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የሚገዙት 144,000 እንደሆኑ ይነግረናል። (ራእይ 14:1-4) እነዚህ ሰዎች “የእስራኤል ልጆች” ተብለውም ተጠርተዋል። (ራእይ 7:4-8) ታዲያ 144,000ዎቹ በሙሉ ሥጋዊ እስራኤላውያን ወይም አይሁዳውያን ናቸው ማለት ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ይሖዋ ዓላማውን በመፈጸም ረገድ እንደ ሁኔታው ለውጦችን የሚያደርግ አምላክ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ሐዋርያው ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።
“የመንግሥት ካህናት”
10. የእስራኤል ብሔር ለእነሱ ብቻ የተሰጠ ምን መብት ነበራቸው?
10 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው “የመንግሥት ካህናት [እና] የተቀደሰ ሕዝብ” የሚሆኑትን ሰዎች የማስገኘት መብት የተሰጠው ለእስራኤል ብሔር ብቻ ነበር። (ሮም 9:4, 5ን አንብብ።) ይሁንና ተስፋ የተሰጠበት ዘር ሲመጣ ምን ይፈጸም ይሆን? ሥጋዊ እስራኤላውያን፣ የአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል የሚሆኑትን 144,000 መንፈሳዊ እስራኤላውያን በሙሉ ያስገኙ ይሆን?
11, 12. (ሀ) በሰማይ ያለው መንግሥት ክፍል የሚሆኑት ሰዎች መመረጥ የጀመሩት መቼ ነው? በወቅቱ የነበሩት አብዛኞቹ አይሁዳውያን ለዚህ ግብዣ ምን ምላሽ ሰጡ? (ለ) ይሖዋ የአብርሃም ዘር የሚሆኑት ‘ቁጥር እንዲሞላ’ ያደረገው እንዴት ነው?
11 ሮም 11:7-10ን አንብብ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን በብሔር ደረጃ ኢየሱስን አልተቀበሉትም። በመሆኑም የአብርሃም ዘር የሚመጣው ከሥጋዊ እስራኤላውያን ብቻ መሆኑ ቀረ። ይሁንና በሰማይ “የመንግሥት ካህናት” የሚሆኑት ሰዎች በ33 ዓ.ም. በዋለው በጴንጤቆስጤ ዕለት መመረጥ በጀመሩበት ወቅት አንዳንድ ቅን ልብ ያላቸው አይሁዳውያን ይህን ግብዣ ተቀብለዋል። በጥቂት ሺዎች የሚቆጠሩት እነዚህ አይሁዳውያን ከአጠቃላዩ የአይሁድ ብሔር ጋር ሲነጻጸሩ ጥቂት “ቀሪዎች” ነበሩ።—ሮም 11:5
12 ታዲያ ይሖዋ፣ የአብርሃም ዘር የሚሆኑት ‘ቁጥር እንዲሞላ’ የሚያደርገው እንዴት ነው? (ሮም 11:12, 25) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን መልስ እንመልከት፦ “የአምላክ ቃል ከንቱ ሆኖ ቀርቷል ማለት አይደለም። [ከሥጋዊ እስራኤል] የተወለደ ሁሉ በእርግጥ ‘እስራኤል’ አይደለምና። በተጨማሪም የአብርሃም ዘር [ተወላጅ] ስለሆኑ ሁሉም ልጆች [በአብርሃም በኩል የመጣው ዘር ክፍል] ናቸው ማለት አይደለም፤ . . . ይህም ሲባል በሥጋ ልጆች የሆኑ በእርግጥ የአምላክ ልጆች አይደሉም፤ በተስፋው ልጆች የሆኑት ግን ዘሩ እንደሆኑ ተደርገው ይቆጠራሉ።” (ሮም 9:6-8) እንግዲያው ይሖዋ ከዘሩ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ እንዲፈጸም፣ አስቀድሞ የተነገረለት ዘር ክፍል የሚሆኑት የግድ ከአብርሃም የዘር ሐረግ መገኘት የለባቸውም።
ምሳሌያዊው የወይራ ዛፍ
13. (ሀ) የወይራ ዛፉ፣ (ለ) ሥሩና (ሐ) ግንዱ ምን ያመለክታል? (መ) ቅርንጫፎቹስ ምን ያመለክታሉ?
13 ሐዋርያው ጳውሎስ የአብርሃም ዘር ክፍል የሚሆኑትን ሰዎች ከምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ጋር አነጻጽሯቸዋል።a (ሮም 11:21) በእርሻ ላይ የተተከለው ይህ የወይራ ዛፍ፣ አምላክ ከአብርሃም ቃል ኪዳን ጋር በተያያዘ ያለውን ዓላማ አፈጻጸም ያመለክታል። የዚህ ዛፍ ሥር ቅዱስ ሲሆን ይህ ሥር ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን ሕይወት የሰጣቸውን ይሖዋን የሚወክል ነው። (ኢሳ. 10:20፤ ሮም 11:16) ግንዱ የአብርሃም ዘር ዋነኛ ክፍል የሆነውን ኢየሱስን ይወክላል። ቅርንጫፎቹ በአጠቃላይ ደግሞ በአብርሃም ዘር ሁለተኛ ክፍል ውስጥ የሚካተቱትን ሰዎች ‘ሙሉ ቁጥር’ ያመለክታሉ።
14, 15. በእርሻ ላይ ከተተከለው የወይራ ዛፍ ‘የተሰበሩት’ ቅርንጫፎች እነማን ናቸው? ከዚህ ዛፍ ጋር የተጣበቁትስ እነማን ናቸው?
14 ኢየሱስን ያልተቀበሉት ሥጋዊ እስራኤላውያን ስለ ወይራው ዛፍ በሚገልጸው ምሳሌ ላይ ከወይራው ዛፍ ላይ ‘በተሰበሩ’ ቅርንጫፎች ተመስለዋል። (ሮም 11:17) በመሆኑም የአብርሃም ዘር ክፍል የመሆን አጋጣሚ አጥተዋል። ታዲያ ማን ይተካቸው ይሆን? ከአብርሃም የዘር ሐረግ በመገኘታቸው የሚኩራሩት ሥጋዊ አይሁዳውያን ማንም ሊተካቸው እንደማይችል ይሰማቸው ነበር። ይሁንና አጥማቂው ዮሐንስ፣ ይሖዋ ከፈለገ ለአብርሃም ከድንጋዮች እንኳ ልጆች ማስነሳት እንደሚችል ነግሯቸዋል።—ሉቃስ 3:8
15 ታዲያ ይሖዋ ዓላማውን ለማሳካት ምን አደረገ? ጳውሎስ የተሰበሩትን ቅርንጫፎች ለመተካት ሲባል ከዱር የወይራ ዛፍ የተወሰዱ ቅርንጫፎች በእርሻ ላይ በተተከለው የወይራ ዛፍ ላይ እንደተጣበቁ ገልጿል። (ሮም 11:17, 18ን አንብብ።) በመሆኑም ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ቅቡዓን (ለምሳሌ በሮም በሚገኘው ጉባኤ የነበሩት አንዳንድ ክርስቲያኖች) በዚህ ምሳሌያዊ የወይራ ዛፍ ላይ ተጣበቁ። በዚህ መንገድ የአብርሃም ዘር ክፍል ሆኑ። እነዚህ ክርስቲያኖች መጀመሪያ ላይ እንደ ዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች ስለነበሩ የዚህ ልዩ ቃል ኪዳን ክፍል የመሆን አጋጣሚ አልነበራቸውም። ይሁንና ይሖዋ መንፈሳዊ አይሁዳውያን መሆን የሚችሉበትን በር ከፈተላቸው።—ሮም 2:28, 29
16. ሐዋርያው ጴጥሮስ አዲሱ መንፈሳዊ ብሔር የተቋቋመበትን መንገድ የገለጸው እንዴት ነው?
16 ሐዋርያው ጴጥሮስ ሁኔታውን እንደሚከተለው በማለት ገልጾታል፦ “ስለዚህ እናንተ አማኞች ስለሆናችሁ [ኢየሱስ ክርስቶስ] ክቡር የሆነው ለእናንተ [አሕዛብ ክርስቲያኖችን ጨምሮ ለመንፈሳዊ እስራኤላውያን] ነው፤ የማያምኑትን በተመለከተ ግን እንዲህ ተብሎ ተጽፏል፦ ‘ይህን ድንጋይ ግንበኞች ቢንቁትም ይኸው ድንጋይ የማዕዘኑ ራስ ሆነ’፤ እንዲሁም ‘የሚያደናቅፍ ድንጋይና የሚያሰናክል ዐለት ሆነ።’ . . . እናንተ ግን ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ የጠራችሁን የእሱን ‘ድንቅ ባሕርያት በስፋት እንድታስታውቁ የተመረጠ ዘር፣ ንጉሣዊ ካህናት፣ ቅዱስ ብሔር፣ ልዩ ንብረት እንዲሆን የተለየ ሕዝብ’ ናችሁ። ምክንያቱም እናንተ በአንድ ወቅት አንድ ሕዝብ አልነበራችሁም፣ አሁን ግን የአምላክ ሕዝብ ናችሁ፤ ቀደም ሲል ምሕረት ያልተደረገላችሁ ሰዎች ነበራችሁ፣ አሁን ግን ምሕረት የተደረገላችሁ ሰዎች ናችሁ።”—1 ጴጥ. 2:7-10
17. ይሖዋ የወሰደው እርምጃ “ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ” የተከናወነ ነው ሊባል የሚችለው እንዴት ነው?
17 ይሖዋ፣ ብዙዎች ፈጽሞ የማይመስል እንደሆነ የሚሰማቸውን ነገር አድርጓል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ የወሰደው እርምጃ “ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ” የተከናወነ እንደሆነ ገልጿል። (ሮም 11:24) ይህ የሆነው እንዴት ነው? የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍን በእርሻ ላይ በተተከለ የወይራ ዛፍ ላይ ማጣበቅ ያልተለመደ እንዲያውም ከተፈጥሮ ውጭ የሆነ ተግባር ይመስል ይሆናል፤ ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ገበሬዎች እንዲህ ያደርጉ ነበር።b ከዚህ ጋር በሚመሳሰል መንገድ ይሖዋም በጣም አስገራሚ የሆነ ነገር አድርጓል። አይሁዳውያን፣ አሕዛብ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ፍሬ ማፍራት እንደማይችሉ ይሰማቸው ነበር። ይሁንና ይሖዋ፣ አሕዛብን የመንግሥት ፍሬ የሚያፈራ “ሕዝብ” ክፍል አደረጋቸው። (ማቴ. 21:43) ወደ ክርስትና የተለወጠ የመጀመሪያው ያልተገረዘ አሕዛብ የሆነው ቆርኔሌዎስ በ36 ዓ.ም. በመንፈስ ከተቀባበት ጊዜ ጀምሮ አይሁዳውያን ያልሆኑ ያልተገረዙ ሰዎች በምሳሌያዊው የወይራ ዛፍ ላይ የመጣበቅ አጋጣሚ ተከፈተላቸው።—ሥራ 10:44-48c
18. ሥጋዊ አይሁዳውያን ከ36 ዓ.ም. በኋላ ምን አጋጣሚ ነበራቸው?
18 እንዲህ ሲባል ሥጋዊ አይሁዳውያን ከ36 ዓ.ም. በኋላ የአብርሃም ዘር ክፍል ለመሆን ምንም አጋጣሚ አልነበራቸውም ማለት ነው? አይደለም። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እነሱም [ሥጋዊ አይሁዳውያን] ቢሆኑ እምነት የለሽ ሆነው በዚያው ካልቀጠሉ ተመልሰው ይጣበቃሉ፤ ምክንያቱም አምላክ ዳግመኛ ሊያጣብቃቸው ይችላል። አንተ በተፈጥሮ የዱር ከሆነው የወይራ ዛፍ ተቆርጠህ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ መንገድ በጓሮ የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ ከቻልክ እነዚህ ተፈጥሯዊ የሆኑት ቅርንጫፎችማ በራሳቸው የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቅ እንደሚችሉ የታወቀ ነው!”d—ሮም 11:23, 24
“እስራኤል ሁሉ ይድናል”
19, 20. የወይራው ዛፍ ምሳሌ እንደሚያሳየው ይሖዋ ምን አከናውኗል?
19 አዎን፣ ይሖዋ ‘ከአምላክ እስራኤል’ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ አስገራሚ በሆነ መንገድ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። (ገላ. 6:16) ጳውሎስ እንደተናገረው “እስራኤል ሁሉ ይድናል።” (ሮም 11:26) ይሖዋ በወሰነው ጊዜ “እስራኤል ሁሉ” ይኸውም መንፈሳዊ እስራኤላውያን በሙሉ በሰማይ ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። ምንም ነገር የይሖዋ ዓላማ ዳር እንዳይደርስ ሊያደርግ አይችልም!
20 አስቀድሞ እንደተነገረው የአብርሃም ዘር ይኸውም ኢየሱስ ክርስቶስና 144,000ዎቹ “ለአሕዛብ በረከት” ያመጣሉ። (ሮም 11:12፤ ዘፍ. 22:18) በዚህ መንገድ የአምላክ ሕዝቦች በሙሉ ከዚህ ዝግጅት ተጠቃሚ ይሆናሉ። በእርግጥም የይሖዋ ዘላለማዊ ዓላማ ስለሚፈጸምበት መንገድ ስናሰላስል “የአምላክ ብልጽግናና ጥበብ እንዲሁም እውቀት እንዴት ጥልቅ ነው” በሚለው ሐሳብ እንደምንስማማ ጥርጥር የለውም!—ሮም 11:33
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ጳውሎስ የወይራውን ዛፍ ሥጋዊ እስራኤላውያንን ለማመልከት እንደ ምሳሌ አልተጠቀመበትም። የእስራኤል ብሔር ነገሥታትና ካህናት የነበሩት ቢሆንም ብሔሩ የመንግሥት ካህናት አልሆነም። በሙሴ ሕግ መሠረት የእስራኤል ነገሥታት ካህናት መሆን አይችሉም ነበር። በመሆኑም የወይራው ዛፍ ለዚህ ብሔር ተምሳሌት ሊሆን አይችልም። ጳውሎስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው አምላክ “የመንግሥት ካህናት” ለማስገኘት ያለው ዓላማ ከመንፈሳዊ እስራኤል ጋር በተያያዘ ፍጻሜውን የሚያገኘው እንዴት እንደሆነ ለማስረዳት ነው። ይህ በነሐሴ 15, 1983 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 14-19 [መ.ግ. 8-104 ከገጽ 8-10] ላይ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረገ ማስተካከያ ነው።
b “የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎችን ማጣበቅ—ለምን አስፈለገ?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
c ይህ የሆነው ሥጋዊ አይሁዳውያን አዲስ የተቋቋመው መንፈሳዊ ብሔር አባላት እንዲሆኑ ለሦስት ዓመት ተኩል አጋጣሚ ከተሰጣቸው በኋላ ነበር። ስለ 70 ሱባዔ ወይም የዓመታት ሳምንታት የተነገረው ትንቢት ይህ እንደሚሆን ይጠቁማል።—ዳን. 9:27
d በሮም 11:24 ላይ ‘የጓሮ’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛው ቅጥያ “ጥሩ፣ በጣም ጥሩ” ወይም “ለታሰበለት ነገር ምቹ የሆነ” የሚል ትርጉም ካለው ቃል የመጣ ነው። ይህ ቃል በተለይ የተሠሩበትን ዓላማ የሚፈጽሙ ነገሮችን ለማመልከት ያገለግላል።
ታስታውሳለህ?
• ይሖዋ ዓላማውን የሚፈጽምበት መንገድ ስለ እሱ ምን ያስተምረናል?
• በሮም ምዕራፍ 11 ላይ የተጠቀሰው
የወይራው ዛፍ፣
ሥሩ፣
ግንዱና
ቅርንጫፎቹ ምን ያመለክታሉ?
• የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎች በእርሻ ላይ በተተከለው የወይራ ዛፍ ላይ መጣበቃቸው “ከተፈጥሮ ውጭ” የሆነ ድርጊት ነው የምንለው ለምንድን ነው?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፎችን ማጣበቅ—ለምን አስፈለገ?
▪ ሉሺየስ ጁንየስ ማደሬተስ ካልየመላ፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረ የሮም ወታደርና ገበሬ ነው። ይህ ሰው ይበልጥ ታዋቂ የሆነው ስለ ገጠር ሕይወትና ስለ ግብርና በጻፋቸው 12 መጻሕፍት ነው።
በአምስተኛው መጽሐፉ ላይ የሚከተለውን ጥንታዊ ምሳሌ ጠቅሶ ነበር፦ “በወይራ ዛፎች ዙሪያ ያለውን መሬት ቆፈር ቆፈር በማድረግ አፈሩን የሚያገላብጥ ሰው የወይራ ዛፉ ፍሬ እንዲሰጠው እየጠየቀ ነው፤ ፍግ የሚያደርግበት ሰው ዛፉ ፍሬ እንዲሰጠው እየለመነ ነው፤ ዛፉን የሚገርዘው ሰው ደግሞ ፍሬ እንዲያፈራ እያስገደደው ነው።”
ሉሺየስ፣ በደንብ ቢመቻቸውም ፍሬ ስለማያፈሩ ዛፎች በመጽሐፉ ላይ ከገለጸ በኋላ የሚከተለውን ዘዴ መጠቀም ጥሩ እንደሆነ ሐሳብ አቅርቧል፦ “የዛፉን ግንድ በመብሻ ከቦረቦሩ በኋላ የዱር የወይራ ዛፍ ቅርንጫፍ ቀዳዳው ውስጥ በደንብ አድርጎ መሸጎጥ ጥሩ ዘዴ ነው፤ በዚህ መንገድ ዛፉ፣ ፍሬያማ ከሆነ ዘር ጋር ስለተዳቀለ የበለጠ ምርታማ ይሆናል።”
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ስለ ምሳሌያዊው የወይራ ዛፍ የሚገልጸው ጥቅስ ምን ትርጉም እንዳለው ታውቃለህ?