የዘላለም ሕይወት ተስፋ የሰጠንን አምላክ ምሰሉ
“የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ።” —ኤፌ. 5:1
1. የአምላክን ባሕርያት ለማንጸባረቅ የሚረዳን የትኛው ችሎታ ነው?
ይሖዋ፣ ራሳችንን በሌሎች ቦታ አስቀምጠን የመመልከት ችሎታ ሰጥቶናል። በመሆኑም እኛ ያልደረሰብንን ሁኔታ በተወሰነ መጠንም ቢሆን መረዳት እንችላለን። (ኤፌሶን 5:1, 2ን አንብብ።) ለመሆኑ ከአምላክ ያገኘነውን ይህን ስጦታ በአግባቡ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? ይህ ችሎታችን ጉዳት እንዳያስከትልብንስ ምን ማድረግ እንችላለን?
2. ይሖዋ ስንጨነቅ ምን ይሰማዋል?
2 አምላክ ታማኝ ለሆኑት ቅቡዓን በሰማይ የማይሞት ሕይወት፣ ታማኝ ለሆኑት የኢየሱስ “ሌሎች በጎች” ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚሰጣቸው ቃል መግባቱ እንደሚያስደስተን ምንም ጥርጥር የለውም። (ዮሐ. 10:16፤ 17:3፤ 1 ቆሮ. 15:53) በሰማይ የማይሞት ሕይወት የሚሰጣቸውም ሆነ በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወት የሚያገኙት ሰዎች በዛሬው ጊዜ ያሉት መከራዎች ወደፊት እንደማይደርሱባቸው የታወቀ ነው። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት እያሉ ሥቃያቸውን እንደተረዳላቸው ሁሉ እኛም የሚያጋጥመንን መከራ በሚገባ ያውቃል። በእርግጥም ከእስራኤላውያን ጋር በተያያዘ “በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ” ተብሎ ነበር። (ኢሳ. 63:9) ከዘመናት በኋላ ደግሞ አይሁዳውያን ቤተ መቅደሱን እንደገና ሲገነቡ ጠላቶቻቸው በሰነዘሩባቸው ተቃውሞ የተነሳ ፈርተው ነበር፤ ይሁንና አምላክ “እናንተን የሚነካ ሁሉ የዓይኔን ብሌን ይነካል” ብሏቸዋል። (ዘካ. 2:8) አንዲት እናት ለሕፃን ልጇ ጥልቅ ፍቅር እንዳላት ሁሉ ይሖዋም ለሕዝቡ ያለው ፍቅር ለእነሱ ሲል እርምጃ እንዲወስድ ይገፋፋዋል። (ኢሳ. 49:15) በሌላ አባባል ይሖዋ ራሱን በሌሎች ቦታ አድርጎ መመልከት ይችላል፤ ይህንን ችሎታ ለእኛም ሰጥቶናል።—መዝ. 103:13, 14
ኢየሱስ የአምላክን ፍቅር ያንጸባረቀው እንዴት ነው?
3. ኢየሱስ ሩኅሩኅ እንደሆነ የሚያሳየው ምንድን ነው?
3 ኢየሱስ፣ እሱ ፈጽሞ ደርሶበት የማያውቅ ሁኔታ ያጋጠማቸውን ጨምሮ የሰዎችን ሥቃይ ይረዳ ነበር። ለምሳሌ ሕዝቡ፣ የሚያታልሏቸውን እንዲሁም በርካታ ሰው ሠራሽ ሕግጋትን የሚጭኑባቸውን የሃይማኖት መሪዎች ይፈሩ ነበር። (ማቴ. 23:4፤ ማር. 7:1-5፤ ዮሐ. 7:13) ኢየሱስ ፈርቶ ወይም ተታሎ ባያውቅም እሱ ያላለፈበትን ሁኔታ መረዳት ይችላል። በመሆኑም “[ሕዝቡን] ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) እንደ አባቱ ሁሉ ኢየሱስም አፍቃሪና ሩኅሩኅ ነው።—መዝ. 103:8
4. ኢየሱስ የሌሎችን ሥቃይ መመልከቱ ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?
4 ኢየሱስ ሰዎች ሲሠቃዩ በተመለከተ ጊዜ በፍቅር ተነሳስቶ ረድቷቸዋል። እንዲህ በማድረግ የአባቱን ፍቅር ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። በአንድ ወቅት ኢየሱስና ሐዋርያቱ ለስብከት ረጅም መንገድ ተጉዘው ነበር፤ ከዚያም ገለል ወዳለ አንድ ስፍራ በመሄድ ለማረፍ አሰቡ። ይሁን እንጂ ኢየሱስ፣ እሱን ለሚጠብቁት ሰዎች ስላዘነላቸው ጊዜ ወስዶ ‘ብዙ ነገር ያስተምራቸው ጀመር።’—ማር. 6:30, 31, 34
ይሖዋን በፍቅሩ መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?
5, 6. አምላክን በፍቅሩ መምሰል ከፈለግን ባልንጀራችንን እንዴት መያዝ ይኖርብናል? ምሳሌ ስጥ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)
5 አምላክን በፍቅሩ ለመምሰል ከፈለግን ባልንጀራችንን ስለምንይዝበት መንገድ ማሰብ ይኖርብናል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት፣ አቤል የሚባል አንድ ክርስቲያን ወጣት አለ እንበል፤ ይህ ወጣት፣ ዓይናቸው በመድከሙ የተነሳ ማንበብ የሚቸግራቸውን አንድ አረጋዊ ወንድም ለመርዳት አሰበ። አረጋዊው ወንድም ከቤት ወደ ቤት በእግር እየሄዱ ማገልገልም ይከብዳቸዋል። አቤል “ልክ ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” በማለት ኢየሱስ የተናገረውን ሐሳብ አስታወሰ። (ሉቃስ 6:31) በመሆኑም ‘ሰዎች ምን እንዲያደርጉልኝ ነው የምፈልገው?’ በማለት ራሱን ጠየቀ። ቶሎ ወደ አእምሮው የመጣው መልስ ‘አብረውኝ ኳስ እንዲጫወቱ!’ የሚል ነው። ይሁንና አረጋዊው ወንድም ኳስ መጫወት እንደማይችሉ የታወቀ ነው። ኢየሱስ የተናገረው ነገር ‘እኔ በባልንጀራዬ ቦታ ብሆን ኖሮ ምን እንዲያደርግልኝ እፈልግ ነበር?’ ብለን መጠየቅ እንዳለብን ይጠቁመናል።
6 አቤል፣ አረጋዊ ባይሆንም እሱ ያላጋጠሙትን ሁኔታዎች መረዳት እንደሚችል የታወቀ ነው። ከአረጋዊው ወንድም ጋር ጊዜ ያሳለፈ ከመሆኑም ሌላ እኚህ ወንድም ሲናገሩ በአሳቢነት አዳመጣቸው። ውሎ አድሮ አቤል፣ መጽሐፍ ቅዱስን ለማንበብ የሚቸግራቸውን ወይም ከቤት ወደ ቤት በእግራቸው እየሄዱ ማገልገል የሚከብዳቸውን አረጋዊ ወንድም ስሜት መረዳት ቻለ። አቤል፣ የአረጋዊው ወንድም ጭንቀት ሲሰማው፣ እሳቸውን እንዴት መርዳት እንደሚችል አስተዋለ፤ እንዲሁም እሳቸውን የመርዳት ፍላጎት አደረበት። እኛም እንዲህ ማድረግ እንችላለን። አምላክን በፍቅሩ ለመምሰል እንድንችል ራሳችንን በወንድማችን ቦታ ማስቀመጥ ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 12:26
7. ሌሎችን በሚገባ ማወቅና ሥቃያቸውን መረዳት የምንችለው እንዴት ነው?
7 የሌሎችን ሥቃይ መረዳት ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ብዙ ሰዎች እኛ ጨርሶ አጋጥሞን የማያውቅ ችግር ይደርስባቸዋል። አንዳንዶች በደረሰባቸው ጉዳት፣ በሕመም ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ አካላዊ ሥቃይ አለባቸው። ሌሎች ደግሞ ከስሜት ጋር የተያያዙ ፈተናዎች አሉባቸው፤ ከእነዚህም መካከል በመንፈስ ጭንቀት፣ ከመጠን ባለፈ የፍርሃት ስሜት ወይም የደረሰባቸው ጥቃት ባስከተለባቸው ጠባሳ የሚሠቃዩ ሰዎች ይገኙበታል። አንዳንዶች የሚኖሩት በሃይማኖት በተከፋፈለ ወይም በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ይሆናል። ሁሉም ሰው ችግር ያጋጥመዋል፤ አብዛኛውን ጊዜ ደግሞ ሌሎች ያሉባቸው ችግሮች እኛ ከሚገጥሙን የተለዩ ይሆናሉ። በዚህ ጊዜ የአምላክን ፍቅር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? የሌላውን ሰው ስሜት ቢያንስ በተወሰነ መጠን መረዳት እስክንችል ድረስ ግለሰቡን በጥሞና በማዳመጥ ነው። ይህን ማድረጋችን ግለሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ከግምት አስገብተን እርምጃ በመውሰድ ይሖዋን በፍቅሩ ለመምሰል ያነሳሳናል። እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስፈልገው ነገር የተለያየ ቢሆንም መንፈሳዊ ማበረታቻ ልንሰጠው እንዲሁም በሌሎች መንገዶች የሚያስፈልገውን ነገር ልናደርግለት እንችል ይሆናል።—ሮም 12:15ን እና 1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።
ይሖዋን በደግነቱ ምሰሉት
8. ኢየሱስ ደግ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው?
8 የአምላክ ልጅ፣ “ልዑሉ አምላክ . . . ለማያመሰግኑና ለክፉዎች ደግ ነው” በማለት ተናግሯል። (ሉቃስ 6:35) ኢየሱስ ራሱ አምላክን በደግነቱ መስሎታል። ይህን እንዲያደርግ የረዳው ምንድን ነው? የሚናገረውም ሆነ የሚያደርገው ነገር የሌላውን ግለሰብ ስሜት እንዴት ሊነካ እንደሚችል አስቀድሞ በማሰብ ሰዎችን በደግነት ይይዝ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በኃጢአተኝነቷ የምትታወቅን አንዲት ሴት እንዴት እንደያዛት እንመልከት፤ ሴትየዋ ወደ ኢየሱስ በመቅረብ እያለቀሰች በእንባዋ እግሩን ታርስ ጀመር። ኢየሱስ ሴትየዋ ንስሐ እንደገባች የተገነዘበ ሲሆን ደግነት በጎደለው መንገድ ቢያባርራት ስሜቷ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል ተረዳ። በመሆኑም ላደረገችው መልካም ነገር ያመሰገናት ከመሆኑም ሌላ ኃጢአቷን ይቅር አላት። አንድ ፈሪሳዊ፣ ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ባወገዘ ጊዜ ለእሱም ቢሆን በደግነት መልስ ሰጥቶታል።—ሉቃስ 7:36-48
9. አምላክን በደግነቱ ለመምሰል ምን ሊረዳን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
9 አምላክን በደግነቱ መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ “የጌታ ባሪያ ሊጣላ አይገባውም” ካለ በኋላ “ከሰው ጋር ባለው ግንኙነት ዘዴኛ” መሆን እንደሚገባው ገልጿል። (2 ጢሞ. 2:24 የግርጌ ማስታወሻ) ከሰው ጋር ባላቸው ግንኙነት ዘዴኛ የሆኑ ሰዎች፣ ቅር ሊያሰኙ የሚችሉ ሁኔታዎችን እንዴት ማስተናገድ እንዳለባቸው በማስተዋል የሌሎችን ስሜት ላለመጉዳት ይጠነቀቃሉ። ከዚህ በታች ከተጠቀሱት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ ደግነት ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክር፦ በሥራ ቦታችን አለቃችን ሥራውን ጥሩ አድርጎ አያከናውንም። ታዲያ ምን እናደርጋለን? አንድ ወንድም ከብዙ ወራት በኋላ ስብሰባ መጣ። ምን እንለዋለን? በአገልግሎት ላይ የቤቱ ባለቤት “ሥራ ስለበዛብኝ አሁን ላነጋግርህ አልችልም” አለን። አሳቢነት እናሳየዋለን? ባለቤትህ ‘ለቅዳሜ ያወጣኸውን ፕሮግራም ለምን ቀድመህ አልነገርከኝም?’ አለችህ። ደግነት የሚንጸባረቅበት ምላሽ ትሰጣለህ? ራሳችንን በሌሎች ቦታ ማስቀመጣችንና የምንናገረው ነገር እንዴት ሊነካቸው እንደሚችል አስቀድመን ማሰባችን በንግግራችን ብሎም በድርጊታችን የይሖዋን ደግነት ለማንጸባረቅ ያስችለናል።—ምሳሌ 15:28ን አንብብ።
ይሖዋን በጥበቡ ምሰሉት
10, 11. አምላክን በጥበቡ ለመምሰል ምን ሊረዳን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።
10 እኛ ያላለፍንበትን ሁኔታ መረዳት መቻላችን የይሖዋን ጥበብ እንድናንጸባርቅና የምናደርጋቸው ነገሮች ሊያስከትሉ የሚችሉትን ውጤት አስቀድመን እንድናስብም ይረዳናል። ጥበብ ከይሖዋ ዋነኛ ባሕርያት አንዱ ነው፤ ይሖዋ ከፈለገ አንዳንድ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ውጤት በሙሉ አስቀድሞ ማወቅ ይችላል። የሰው ልጆች የወደፊቱን ጊዜ የማወቅ ችሎታ ባይኖረንም ልንወስደው ያሰብነው እርምጃ ምን ውጤት እንደሚያስከትል አስቀድመን ማሰባችን ተገቢ ነው። እስራኤላውያን አምላክን አለመታዘዛቸው ሊያስከትል የሚችለውን መዘዝ ሳያገናዝቡ ቀርተዋል። አምላክ ብዙ ነገር ያደረገላቸው ቢሆንም በእሱ ዓይን መጥፎ የሆነውን አካሄድ እንደሚከተሉ ሙሴ ተገንዝቦ ነበር። ሙሴ፣ መላው የእስራኤል ጉባኤ እየሰማ የሚከተለውን ሐሳብ የያዘ መዝሙር ነገራቸው፦ “እነሱ ማመዛዘን የጎደለው ብሔር ናቸው፤ በመካከላቸውም ማስተዋል የሚባል ነገር የለም። ምነው ጥበበኛ በሆኑ ኖሮ! ይህን ሁሉ ያሰላስሉ ነበር። የሚደርስባቸውንም ያስቡ ነበር።”—ዘዳ. 31:29, 30፤ 32:28, 29
11 አምላክን በጥበቡ መምሰል ከፈለግን ድርጊታችን የሚያስከትለውን ውጤት ማሰብ አልፎ ተርፎም በዓይነ ሕሊናችን ለመሳል መሞከር ይኖርብናል። ለምሳሌ፣ እየተጠናናን ከሆነ በዚህ ወቅት የፆታ ስሜት ምን ያህል ሊያይል እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልገናል። ከይሖዋ ጋር ያለን ውድ ዝምድና አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሊያደርግ የሚችል ዕቅድ ላለማውጣት ወይም ምንም ዓይነት ነገር ላለማድረግ እንጠንቀቅ! በመንፈስ መሪነት የተጻፈውን የሚከተለውን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ እንጣር፦ “ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 22:3
መጥፎ በሆኑ ነገሮች ላይ አታሰላስሉ
12. ማሰላሰል አደገኛ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
12 ብልህ ሰው፣ ማሰላሰል እንደ እሳት እንደሆነ ይገነዘባል። እሳት በተገቢው መንገድ ከተሠራበት ጠቃሚ ነው፤ ለምሳሌ ምግባችንን ለማብሰል ይረዳናል። እሳት ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ ግን ቤት ሊያቃጥልና የነዋሪዎቹን ሕይወት ሊያጠፋ ስለሚችል አደገኛ ነው። በተመሳሳይም ማሰላሰል ይሖዋን እንድንመስል የሚረዳን ከሆነ ጠቃሚ ነው። የብልግና ምኞቶች እንዲፈጠሩብን የሚያደርግ ከሆነ ግን አደገኛ ነው። ለምሳሌ፣ በኃጢአት ድርጊቶች ላይ የማውጠንጠን ልማድ ካለን ይህ፣ የተመኘነውን ነገር ወደመፈጸም ሊመራን ይችላል። በእርግጥም በብልግና ድርጊቶች ላይ ማሰላሰል በመንፈሳዊ ሁኔታ ሞት ሊያስከትልብን ይችላል።—ያዕቆብ 1:14, 15ን አንብብ።
13. ሔዋን ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራት አስባ ሊሆን ይችላል?
13 የመጀመሪያዋ ሴት ሔዋን፣ “ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” ፍሬ እንዳትበላ ብትከለከልም ይህን የማድረግ ፍላጎት ያደረባት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። (ዘፍ. 2:16, 17) እባቡ ሔዋንን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም። አምላክ ከዛፉ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንደሚገለጡና መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ እንደ አምላክ እንደምትሆኑ ስለሚያውቅ ነው።” በዚህ ጊዜ ሔዋን “ዛፉ ለመብል መልካም፣ ሲያዩትም የሚያጓጓ እንደሆነ ተመለከተች።” ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? “ከዛፉ ፍሬ ወስዳ በላች። ባሏም አብሯት ሲሆን ለእሱም ሰጠችው፤ እሱም በላ።” (ዘፍ. 3:1-6) ሔዋን፣ ሰይጣን ያቀረበላት ሐሳብ ማርኳት ነበር። መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር ሌላ አካል ከሚነግራት ይልቅ ራሷ ይህን ማድረግ እንደምትችል አሰበች። እንዲህ ያለው ማሰላሰል ጎጂ እንደሆነ በግልጽ ታይቷል! ኃጢአተኛ በሆነው ባሏ ማለትም በአዳም አማካኝነት “ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ።”—ሮም 5:12
14. መጽሐፍ ቅዱስ ከሥነ ምግባር ብልግና እንድንርቅ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 እርግጥ ነው፣ ሔዋን በኤደን ገነት የፈጸመችው ኃጢአት ከፆታ ብልግና ጋር የተያያዘ አይደለም። ሆኖም ኢየሱስ ስለ ሥነ ምግባር ብልግና ማውጠንጠን ተገቢ እንዳልሆነ አስጠንቅቋል። “አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 5:28) ጳውሎስም “የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥቷል።—ሮም 13:14
15. ምን ዓይነት ሀብት ማከማቸት ይኖርብናል? ለምንስ?
15 ማሰላሰል አደገኛ የሚሆንበትን ሌላ አቅጣጫ ደግሞ እንመልከት፤ ከአምላክ ጋር ያለንን ዝምድና ግምት ውስጥ ሳናስገባ ሀብት ስለማካበት የምናልም ከሆነ ማሰላሰል ጎጂ ይሆናል። ባለጸጋ ሰው ሀብቱን ‘ጥበቃ እንደሚያስገኝ ግንብ አድርጎ በሐሳቡ እንደሚመለከተው’ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ምሳሌ 18:11) ኢየሱስ “ለራሱ ሀብት የሚያከማች በአምላክ ዘንድ ግን ሀብታም ያልሆነ ሰው” ያለበትን አሳዛኝ ሁኔታ የሚያሳይ ምሳሌ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:16-21) ይሖዋ እሱን የሚያስደስት ነገር ስናደርግ ልቡ ሐሴት ያደርጋል። (ምሳሌ 27:11) ‘በሰማይ ሀብት’ በማከማቸታችን የእሱን ሞገስ ማግኘት ምንኛ የሚያስደስት ነው! (ማቴ. 6:20) ደግሞም ሊኖረን ከሚችለው ውድ ሀብት ሁሉ የላቀው ከይሖዋ ጋር ያለን ወዳጅነት እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
የሚያስጨንቁ ሐሳቦችን መቆጣጠር
16. ጭንቀትን ለመቆጣጠር የሚረዳን አንዱ መንገድ ምንድን ነው?
16 ‘በምድር ላይ ሀብት ለማከማቸት’ የምናደርገው ጥረት ሕይወታችንን ከተቆጣጠረው ይህ ምን ያህል ጭንቀት ሊፈጥርብን እንደሚችል አስበው። (ማቴ. 6:19) ኢየሱስ፣ አንድ ምሳሌ በመጠቀም “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት እንዲሁም ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” የመንግሥቱን ቃል ሊያንቀው እንደሚችል ገልጿል። (ማቴ. 13:18, 19, 22) አንዳንድ ሰዎች የሚጨነቁት ስለ ገንዘብ ባይሆንም እንኳ ሁልጊዜ ክፉ ክፉውን ማሰብ ይቀናቸዋል። ይሁንና የሚያስጨንቁንን ሐሳቦች ካልተቆጣጠርናቸው በአካላዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ጉዳት ሊያደርሱብን ይችላሉ። በመሆኑም በይሖዋ መታመን ይኖርብናል፤ እንዲሁም “በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል” የሚለውን ጥቅስ ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። (ምሳሌ 12:25) ስሜታችንን የሚረዳልን ሰው የሚሰጠን ማበረታቻ ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል። ነገሮችን በአምላክ ዓይን መመልከት ለሚችል ሰው ለምሳሌ ለወላጆቻችን፣ ለትዳር ጓደኛችን ወይም ለምናምነው ወዳጃችን የውስጣችንን አውጥተን መናገራችን ጭንቀታችን እንዲቀለን ሊረዳን ይችላል።
17. ይሖዋ ጭንቀትን እንድንቋቋም የሚረዳን እንዴት ነው?
17 ከይሖዋ የበለጠ ጭንቀታችንን ሊረዳልን የሚችል ማንም የለም። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ስለ ምንም ነገር አትጨነቁ፤ ከዚህ ይልቅ ስለ ሁሉም ነገር በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር ልመናችሁን ለአምላክ አቅርቡ፤ ከመረዳት ችሎታ ሁሉ በላይ የሆነው የአምላክ ሰላም በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ልባችሁንና አእምሯችሁን ይጠብቃል።” (ፊልጵ. 4:6, 7) እንግዲያው የሚያስጨንቅ ነገር ሲያጋጥመን ከመንፈሳዊ ጉዳት የሚጠብቁንን አካላት ይኸውም የእምነት ባልንጀሮቻችንን፣ ሽማግሌዎችን፣ ታማኙን ባሪያ፣ መላእክትን፣ ኢየሱስንና ይሖዋን ለማሰብ እንሞክር።
18. ማሰላሰል ሊጠቅመን የሚችለው እንዴት ነው?
18 ማሰላሰል እንደ ፍቅር ያሉ የአምላክ ባሕርያትን እንድናንጸባርቅ ሊረዳን እንደሚችል ተመልክተናል። (1 ጢሞ. 1:11፤ 1 ዮሐ. 4:8) እውነተኛ ፍቅር የምናሳይ፣ ድርጊታችን የሚያስከትለውን ውጤት አስቀድመን የምናስብ እንዲሁም ደስታችንን የሚሰርቅ ጭንቀትን የምናስወግድ ከሆነ ልባችን ሐሴት ያደርጋል። እንግዲያው ስለ ወደፊቱ ጊዜ የተሰጠንን ተስፋ በዓይነ ሕሊናችን የመመልከት ችሎታችንን ጥሩ አድርገን እንጠቀምበት፤ እንዲሁም ይሖዋን በፍቅሩ፣ በደግነቱ፣ በጥበቡና ደስተኛ በመሆኑ እንምሰለው። —ሮም 12:12