የሕይወት ታሪክ
መልካም ምሳሌዎችን ለመከተል መጣጣር
“ስንት ዓመቴ እንደሆነ ታውቃለህ?” በማለት ጠየቅኩ። “ዕድሜህ ስንት እንደሆነ በሚገባ አውቃለሁ” በማለት ኢሳክ መሬ መለሰልኝ። ኢሳክ የደወለልኝ ከፓተርሰን፣ ኒው ዮርክ ሲሆን በዚህ ወቅት ኮሎራዶ ነበርኩ። ከወንድም መሬ ጋር ይህን ውይይት ከማድረጋችን በፊት ስላሳለፍኩት ሕይወት በቅድሚያ ልንገራችሁ።
የተወለድኩት ታኅሣሥ 10, 1936 በዊችታ፣ ካንሳስ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ሲሆን ከአራት ልጆች መካከል የመጀመሪያው ነኝ። ዊልያም እና ጂን የሚባሉት ወላጆቼ ቀናተኛ የይሖዋ አምላኪዎች ነበሩ። አባባ የቡድን አገልጋይ ነበር፤ በወቅቱ በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንድሞች የሚጠሩት በዚህ ስያሜ ነበር። ለእናቴ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ያስተማረቻት እናቷ ኤማ ዋግነር ነበረች። ኤማ፣ በፖርቶ ሪኮ ለዓመታት በሚስዮናዊነት ያገለገለችውን ገርትሩድ ስቲልን ጨምሮ ለብዙ ሰዎች እውነትን አስተምራለች።a ስለሆነም ልመስላቸው የምችል ብዙ ጥሩ ምሳሌዎች ነበሩኝ።
መልካም ምሳሌዎችን ማስታወስ
የአምስት ዓመት ልጅ ሳለሁ አንድ ቅዳሜ ምሽት ከአባቴ ጋር በመንገድ ላይ መጠበቂያ ግንብ እና መጽናኛ (አሁን ንቁ! ይባላል) እያበረከትን ነበር። በወቅቱ አገሪቱ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት እየታመሰች ነበር። አንድ የሰከረ ዶክተር መጣና አባባን በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋሙ ምክንያት ሰደበው፤ ሰውየው፣ አባባ ፈሪ እንደሆነና ጦር ሜዳ ከመሄድ ለማምለጥ እየሞከረ እንደሆነ ተናገረ። ዶክተሩ፣ አባባ ፊት ላይ ድንቅር ብሎ “ለምን አትመታኝም! ቦቅቧቃ!” አለው። በጣም ፈርቼ የነበረ ቢሆንም አባባ ያደረገውን ሳይ አደነቅኩት። ለዚህ ሰው መልስ ሳይሰጥ ለተሰበሰበው ሰው መጽሔት ማበርከቱን ቀጠለ። ከዚያም አንድ ወታደር ሲያልፍ ዶክተሩ “ይህን ፈሪ አንድ በለው እንጂ!” በማለት ጮኸ። ወታደሩ ሰውየው እንደሰከረ ስላየ “ስካርህ በረድ እስኪልልህ ቤትህ ብትሄድ ይሻልሃል!” አለው። ከዚያም ተያይዘው ሄዱ። መለስ ብዬ ሳስበው ይሖዋ ለአባቴ የሰጠው ድፍረት ያስደንቀኛል። አባቴ በዊችታ ሁለት ፀጉር ቤቶች ነበሩት፤ ዶክተሩም ከደንበኞቹ አንዱ ነበር።
ስምንት ዓመት ሲሆነኝ ወላጆቼ ቤታቸውንና ፀጉር ቤቶቻቸውን ከሸጡ በኋላ አነስተኛ ተንቀሳቃሽ ቤት ሠርተው የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ ኮሎራዶ ተዛወሩ። ከዚያም በግራንድ ጀንክሽን አቅራቢያ መኖር ጀመርን፤ ወላጆቼ በዚያ በአቅኚነት እያገለገሉ በግብርና እና በከብት እርባታ ሥራ ይተዳደሩ ነበር። በቅንዓት ያከናወኑትን ሥራ ይሖዋ ስለባረከው በዚያ አካባቢ ጉባኤ ተቋቋመ። ሰኔ 20, 1948 አባባ አንድ ወንዝ ውስጥ እኔንና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የተቀበሉ ሌሎች ሰዎችን አጠመቀን፤ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ቢሊ ኒኮልዝ እና ባለቤቱ የሚገኙበት ሲሆን ከጊዜ በኋላ እነሱ እንዲሁም ወንድ ልጃቸውና ባለቤቱ በወረዳ ሥራ ተካፍለዋል።
በሙሉ ልባቸው በመንግሥቱ ሥራ ይካፈሉ ከነበሩ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ጋር እንቀራረብ ነበር፤ የሚያንጹ መንፈሳዊ ጭውውቶችንም እናደርግ ነበር፤ ከእነዚህ መካከል በተለይ የስቲል ቤተሰብ አባላት ይኸውም ዶን እና ኧርሊን፣ ዴቭ እና ጁልያ እንዲሁም ሳይ እና ማርታ በሕይወቴ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድረዋል። እነዚህ ሰዎች መንግሥቱን ማስቀደም ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም ያለውና አስደሳች እንዲሆን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ እንድገነዘብ አስችለውኛል።
በድጋሚ መዘዋወር
አሥራ ዘጠኝ ዓመት ሲሆነኝ በድ ሄስቲ የተባለ የቤተሰባችን ወዳጅ በደቡባዊ ዩናይትድ ስቴትስ አብሬው በአቅኚነት እንዳገለግል ጠየቀኝ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ደግሞ ብዙ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ወዳሉበት ወደ ረስተን፣ ሉዊዚያና እንድንዛወር ጠየቀን። በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት ሰዎች ምንም ያህል ቢሆኑ በየሳምንቱ ሁሉንም ስብሰባዎች እንድናደርግ ተነገረን። ከዚያም ተስማሚ የስብሰባ ቦታ አገኘንና አደስነው። ሁሉንም ስብሰባዎች እናደርግ ነበር፤ እርግጥ ለተወሰነ ጊዜ በስብሰባዎቹ ላይ የምንገኘው ሁለታችን ብቻ ነበርን። ክፍሎቹን እየተቀያየርን የምናቀርብ ሲሆን አንዱ ክፍሉን የሚያቀርብ ከሆነ ሌላኛው ጥያቄዎቹን በሙሉ ይመልስ ነበር። ክፍሉ ሠርቶ ማሳያ ያለው ከሆነ ደግሞ ሁለታችንም መድረክ ላይ ስለምንወጣ ቁጭ ብሎ የሚከታተል አይኖርም! በመጨረሻም አንዲት በዕድሜ የገፋች እህት በስብሰባዎቹ ላይ መገኘት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንዲሁም የቀዘቀዙ ክርስቲያኖች ስብሰባ ላይ መገኘት ጀመሩ፤ ብዙም ሳይቆይ ጉባኤያችን እድገት እያደረገ ሄደ።
አንድ ቀን እኔና በድ፣ የቸርች ኦቭ ክራይስት ቄስ ከሆነ ሰው ጋር ተነጋገርን፤ ቄሱ የጠቀሰልንን ጥቅሶች አላውቃቸውም ነበር። ይህም ያስደነገጠኝ ከመሆኑም ሌላ ስለማምንበት ነገር በጥልቀት እንዳስብ አደረገኝ። ለአንድ ሳምንት ያህል እስከ ሌሊት ድረስ እያመሸሁ ላነሳቸው ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ሞከርኩ። ይህም እውነትን የራሴ ለማድረግ በጣም ረድቶኛል፤ ከዚያ በኋላ ሌላ ቄስ አግኝቼ ለማወያየት ጓጓሁ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ወደ ኤል ዶራዶ፣ አርከንሶ ተዛውሬ በዚያ የሚገኘውን ጉባኤ እንድረዳ ጠየቀኝ። በዚያ ሳለሁ፣ በምልመላ ቦርዱ ፊት ለመቅረብ በተደጋጋሚ ወደ ኮሎራዶ እመለስ ነበር። በአንድ ወቅት ከሌሎች አቅኚዎች ጋር በእኔ መኪና ስንሄድ ቴክሳስ ውስጥ አደጋ ስላጋጠመን መኪናዬ ከጥቅም ውጪ ሆነ። በመሆኑም አንድ ወንድም ጋ ደወልን፤ እሱም እኛ ወዳለንበት መጥቶ ወደ ቤቱ ከዚያም ወደ ጉባኤ ስብሰባ ወሰደን። በጉዟችን ላይ ችግር እንዳጋጠመን የሚገልጽ ማስታወቂያ በስብሰባው ላይ ተነገረ፤ ወንድሞችም በደግነት የገንዘብ እርዳታ አበረከቱልን። እንዲሁም የተቀበለን ወንድም መኪናዬን በ25 ዶላር ሸጠው።
ከዚያም የቤተሰባችን ወዳጅ የሆነው ኤቨሪጅ ፍራንክ ማካርትኒ (“ዶክ”) በአቅኚነት ወደሚያገለግልበት ወደ ዊችታ በመኪና የሚወስደን ሰው አገኘን። ፍራንክ እና ፍራንሲስ የተባሉት መንትያ የሆኑ ልጆቹ የቅርብ ጓደኞቼ ነበሩ፤ እስካሁንም ድረስ ወዳጅነታችን ቀጥሏል። ወንድማማቾቹ አሮጌ መኪና የነበራቸው ሲሆን መኪናውን በ25 ዶላር ሸጡልኝ፤ የቀድሞው መኪናዬ የተሸጠውም በዚሁ ዋጋ ነበር። የመንግሥቱን ጉዳዮች በማስቀደሜ ይሖዋ የሚያስፈልገኝን ነገር ሲያሟላልኝ ለመጀመሪያ ጊዜ በግልጽ ያየሁት በዚህ ወቅት ነበር። በዚያው ጊዜ የማካርትኒ ቤተሰብ፣ ቤቴል ክሬን ከምትባል ደስ የምትል አንዲት እህት ጋር አስተዋወቁኝ። የቤቴል እናት ሩት ቀናተኛ እህት ነበረች፤ በ90ዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሆናም እንኳ በዌሊንግተን፣ ካንሳስ በአቅኚነት ታገለግል ነበር። እኔና ቤቴል ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ (በ1958) ተጋባን፤ ከዚያም በኤል ዶራዶ አብረን በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን።
አስደሳች ግብዣዎች ቀረቡልን
ከልጅነታችን ጀምሮ የተመለከትናቸው ጥሩ ምሳሌዎች የይሖዋ ድርጅት በሚመድበን ቦታ ሁሉ ለማገልገል ራሳችንን እንድናቀርብ አነሳሱን። በመሆኑም በዎልነት ሪጅ፣ አርከንሶ በልዩ አቅኚነት እንድናገለግል ተመደብን። በኋላም በ1962 በጊልያድ ትምህርት ቤት 37ኛው ክፍል ላይ እንድንሠለጥን ስንጋበዝ በጣም ተደሰትን። ዶን ስቲል አብሮን እንደሚማር ማወቃችን ደግሞ ይበልጥ አስደሰተን። እኔና ቤቴል ከጊልያድ ትምህርት ቤት ከተመረቅን በኋላ በናይሮቢ፣ ኬንያ እንድናገለግል ተመደብን። ኒው ዮርክን ለቀን መሄድ ከብዶን የነበረ ቢሆንም በናይሮቢ አየር ማረፊያ ወንድሞቻችን ሲቀበሉን ጭንቀታችን በደስታ ተተካ!
ኬንያን ለመውደድ ጊዜ አልወሰደብንም፤ አገልግሎቱም አስደሳች ነበር። በኬንያ ካገኘናቸው እድገት ያደረጉ ጥናቶች መካከል የመጀመሪያዎቹ ክሪስ እና ሜሪ ካናያ ነበሩ። እነዚህ ባልና ሚስት አሁንም ድረስ ኬንያ ውስጥ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ነው። በቀጣዩ ዓመት ወደ ካምፓላ፣ ኡጋንዳ እንድንሄድ ተጠየቅን፤ በዚያ የተመደብነው የመጀመሪያዎቹ ሚስዮናውያን እኛ ነበርን። አገልግሎቱ በጣም አስደሳች ነበር፤ ምክንያቱም ብዙ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት የመማር ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን ከጊዜ በኋላም ወንድሞቻችን ሆነዋል። አፍሪካ ውስጥ ሦስት ዓመት ተኩል ካገለገልን በኋላ ግን ባለቤቴ ስላረገዘች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ተመለስን። አፍሪካን ለቀን መሄድ ኒው ዮርክን ከመልቀቅ የበለጠ ከብዶን ነበር። ሕዝቡን ስለወደድነው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ የተመለስነው አንድ ቀን ወደ አፍሪካ የመመለስ ተስፋ ይዘን ነበር።
አዲስ ኃላፊነት መቀበል
ወላጆቼ በሚኖሩበት ምዕራባዊ ኮሎራዶ መኖር ጀመርን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ ልጃችን ኪምበርሊ ተወለደች፤ ከ17 ወራት በኋላ ደግሞ ስቴፋኒ ተወለደች። አዲሱን የወላጅነት ኃላፊነታችንን አክብደን ስለተመለከትነው በእነዚህ ቆንጆ ልጆቻችን ልብ ውስጥ እውነትን ለመትከል ጥረት ማድረግ ጀመርን። ለእኛ ጥሩ ምሳሌ የተዉልንን ሰዎች ለመምሰል እንፈልግ ነበር። ልጆች ጥሩ ምሳሌ ማግኘታቸው ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድርባቸው ቢችልም ይህ ብቻውን፣ ሲያድጉ ይሖዋን ለማገልገል እንዲወስኑ እንደማያደርጋቸው ማስታወስ ነበረብን። ለምሳሌ ታናሽ ወንድሜና አንዷ እህቴ ከእውነት ወጥተዋል። በእርግጥ መልካም አርዓያ የተዉላቸውን ሰዎች ምሳሌ እንደገና መከተል እንደሚጀምሩ ተስፋ አደርጋለሁ።
ልጆቻችንን ማሳደግ በጣም አስደሳች ነበር፤ በቤተሰብ ሆነን አንዳንድ ነገሮችን ለማድረግ ሁልጊዜ እንጥር ነበር። የምንኖረው አስፐን፣ ኮሎራዶ አቅራቢያ በመሆኑ ሁላችንም የበረዶ ላይ ሸርተቴ ጨዋታ ተማርን፤ ይህን ያደረግነው አልፎ አልፎ አብረን ይህን ጨዋታ ለመጫወት ስለፈለግን ነው። በዚህ ዓይነት መዝናኛ አብረን መካፈላችን ወደ መንሸራተቻው አናት በሚወስደው መጓጓዣ አብረን በምንሄድበት ጊዜ ከልጆቹ ጋር መጨዋወት የምንችልበት አጋጣሚ ፈጥሮልናል። እንዲሁም ለሽርሽር ወጣ ብለን ድንኳን ውስጥ የምናድር ሲሆን ባቀጣጠልነው እሳት ዙሪያ ሰብሰብ ብለን ደስ የሚሉ ጭውውቶች እናደርግ ነበር። ልጆቻችን ትናንሾች እያሉም እንኳ “ሳድግ ምን አደርጋለሁ?” እና “ምን ዓይነት ሰው ነው የማገባው?” እንደሚሉት ዓይነት ጥያቄዎችን ይጠይቁ ነበር። በልጆቻችን አእምሮ እና ልብ ውስጥ መንፈሳዊ እሴቶችን ለመቅረጽ ጥረት እናደርግ ነበር። የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ግብ እንዲያደርጉ እናበረታታቸው እንዲሁም ተመሳሳይ ግብ ያለውን ሰው ማግባታቸው ጥበብ እንደሆነ እንነግራቸው ነበር። በልጅነት ማግባት ጥሩ እንዳልሆነ ልናስገነዝባቸው ሞክረናል። “ቢያንስ 23 ዓመት እስኪሆናችሁ ድረስ ሳታገቡ ቆዩ” እንላቸው ነበር።
ወላጆቻችን እኛን ሲያሳድጉ ያደርጉ እንደነበረው በቤተሰብ ሆነን አዘውትረን በስብሰባዎች ላይ ለመገኘትና በአገልግሎት ለመካፈል ከፍተኛ ጥረት እናደርግ ነበር። እንዲሁም አንዳንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋዮችን ቤታችን እናሳርፋለን። በተጨማሪም ሚስዮናዊ ሆነን ስናገለግል ስላሳለፍናቸው ጥሩ ትዝታዎች ብዙ ጊዜ እናነሳለን። አንድ ቀን አራታችንም አንድ ላይ ሆነን አፍሪካን መጎብኘት እንደምንፈልግም እናወራ ነበር። ልጆቻችን ይህን ለማድረግ ይጓጉ ነበር።
ቋሚ የቤተሰብ ጥናት ነበረን፤ እንዲሁም በጥናቱ ላይ ትምህርት ቤት ሊያጋጥሙ የሚችሉ ሁኔታዎችን በድራማ መልክ እንሠራ ነበር። በድራማው ላይ ልጆቻችን እንደ አንድ የይሖዋ ምሥክር ሆነው ጥያቄዎችን እንዲመልሱ እናደርግ ነበር። በዚህ መልኩ መማር አስደሳች ከመሆኑም ባሻገር ድፍረት ጨምሮላቸዋል። እያደጉ ሲሄዱ ግን የቤተሰብ ጥናት ማድረግ እንደሰለቻቸው የሚናገሩበት ጊዜ ነበር። አንድ ቀን በሁኔታቸው በመበሳጨቴ፣ የቤተሰብ ጥናት ስለማናደርግ ወደ ክፍላቸው እንዲሄዱ ነገርኳቸው። ይህን ስላቸው ደንግጠው ማልቀስ ጀመሩ፤ ከዚያም ማጥናት እንደሚፈልጉ ተናገሩ። በዚህ ወቅት፣ ልጆቻችን ትናንሾች ቢሆኑም ለመንፈሳዊ ነገሮች አድናቆት እንዲያዳብሩ እየረዳናቸው እንደሆነ ተገነዘብን። እያደር የቤተሰብ ጥናቱን እየወደዱት መጡ፤ እኛም በነፃነት ሐሳባቸውን እንዲገልጹ እንፈቅድላቸው ነበር። እርግጥ ነው፣ የማይስማሙባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች እንዳሉ አንዳንድ ጊዜ ይናገሩ ነበር፤ ይህን መስማት ከባድ ነው። ሆኖም የተናገሩት ነገር፣ በልባቸው ውስጥ ምን እንዳለ ለማወቅ አስችሎናል። ማስረጃ እየጠቀስን ካስረዳናቸው በኋላ ደግሞ ይሖዋ በጉዳዩ ላይ ያለው አመለካከት ትክክለኛ እንደሆነ ይገነዘቡ ነበር።
ተጨማሪ ለውጦችን ማስተናገድ
ልጆቻችንን የማሳደግ ኃላፊነታችንን ስንወጣ ዓመታቱ በፍጥነት አለፉ። በአምላክ ድርጅት እርዳታና መመሪያ በመታገዝ፣ ልጆቻችን ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳት የቻልነውን ጥረት አድርገናል። ሁለቱም ልጆቻችን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጨርሱ አቅኚዎች ሆነው ማገልገል በመጀመራቸው በጣም ተደሰትን፤ ራሳቸውን በቁሳዊ ለመደገፍ የሚያስችላቸው ሙያም ነበራቸው። ከሁለት ሌሎች እህቶች ጋር ሆነው የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ለማገልገል ወደ ክሊቭላንድ፣ ቴነሲ ተዛወሩ። በጣም ብንናፍቃቸውም ሕይወታቸውን ለሙሉ ጊዜ አገልግሎት በማዋላቸው ደስተኞች ነበርን። ከዚያ በኋላ እኔና ቤቴል በድጋሚ በአቅኚነት ማገልገል ጀመርን፤ ይህም ተጨማሪ አስደሳች መብቶች ለማግኘት አስችሎናል። ተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ አገልግያለሁ፤ ከክልል ስብሰባ ጋር በተያያዙ ሥራዎችም ተካፍለናል።
ልጆቻችን ወደ ቴነሲ ከመዛወራቸው በፊት ወደ ለንደን፣ እንግሊዝ በመሄድ በዚያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ ጎብኝተው ነበር። በወቅቱ የ19 ዓመት ልጅ የነበረችው ስቴፋኒ፣ ፖል ኖርተን ከተባለ ወጣት ቤቴላዊ ጋር እዚያ እያለች ተዋወቀች። ኪምበርሊ ደግሞ በሌላ ጊዜ ለንደን ስትሄድ ከፖል የሥራ ባልደረቦች አንዱ ከሆነው ከብራያን ለዌሊን ጋር ተገናኘች። ስቴፋኒ 23 ዓመት ከሞላት በኋላ ከፖል ጋር ተጋቡ። በቀጣዩ ዓመት ደግሞ ኪምበርሊ 25 ዓመት ሲሞላት ብራያንን አገባች። ስለዚህ ሁለቱም ቢያንስ 23 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ሳያገቡ ቆይተዋል። ልጆቻችን ጥሩ የትዳር ጓደኞች መምረጣቸው አስደስቶናል።
ልጆቻችን፣ የኢኮኖሚ ችግር ባጋጠማቸው ጊዜም እንኳ እኛና አያቶቻቸው የተውነው ምሳሌ ኢየሱስ ‘ከሁሉ አስቀድመን የአምላክን መንግሥት እንድንፈልግ’ የሰጠውን ምክር ለመታዘዝ እንደረዳቸው ነግረውናል። (ማቴ. 6:33) ሚያዝያ 1998 ፖልና ስቴፋኒ በጊልያድ ትምህርት ቤት 105ኛ ክፍል እንዲሠለጥኑ ተጋበዙ፤ ከዚያም አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በማላዊ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ብራያንና ኪምበርሊ በለንደን ቤቴል እንዲያገለግሉ ተጋበዙ፤ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ወደ ማላዊ ቤቴል ተዛወሩ። ወጣቶች ሕይወታቸውን ሊጠቀሙ የሚችሉበት ከዚህ የተሻለ መንገድ ስለሌለ ልጆቻችን ይህን ምርጫ በማድረጋቸው በጣም ተደሰትን።
ሌላ አስደሳች ግብዣ
መግቢያው ላይ እንደገለጽኩት ጥር 2001 አንድ ወንድም ስልክ ደወለልኝ። የትርጉም አገልግሎት ክፍል የበላይ ተመልካች የሆነው ወንድም መሬ፣ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ተርጓሚዎች የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥልጠና ሊሰጥ እንደታቀደና እኔም አስተማሪ ለመሆን ከሚሠለጥኑት መካከል አንዱ ሆኜ እንደተመረጥኩ ነገረኝ፤ በወቅቱ 64 ዓመቴ ነበር። እኔና ቤቴል ስለ ጉዳዩ የጸለይን ከመሆኑም ሌላ በዕድሜ ከገፉት እናቶቻችን ጋር ተማከርን። እኛ ከሄድን ልንረዳቸው ባንችልም እንኳ ሁለቱም እንድንሄድ ፈለጉ። በመሆኑም ወደ ፓተርሰን መልሼ በመደወል ይህን ግሩም መብት ለመቀበል ፈቃደኛ እንደሆንን ገለጽኩ።
ብዙም ሳይቆይ እናቴ ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ታወቀ። እዚያው ቆይተን እሷን ትንከባከብ የነበረችውን እህቴን ሊንዳን እንደምናግዛት ለእናቴ ነገርኳት። እማማ “በፍጹም እንዲህ አታደርጉም፤ ባትሄዱ የባሰ ይከፋኛል” አለችኝ። ሊንዳም ተመሳሳይ ስሜት ነበራት። ላሳዩት የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዲሁም በአካባቢው ያሉት ወንድሞች ላደረጉት እርዳታ በጣም አመስጋኞች ነን! በፓተርሰን ወደሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የትምህርት ማዕከል በሄድን ማግስት ሊንዳ ደውላ እማማ እንዳረፈች ነገረችኝ። እማማ በሕይወት ብትኖር በአዲሱ ሥራችን እንድንጠመድ እንደምትፈልግ ስለተገነዘብን ሥልጠናው ላይ ትኩረት አደረግን።
የመጀመሪያው ምድባችን ልጆቻችንና ባሎቻቸው የሚያገለግሉበት የማላዊ ቅርንጫፍ ቢሮ መሆኑን ስናውቅ በጣም ተደሰትን። እንደገና አንድ ላይ መሆን መቻላችን አስደስቶን ነበር! ቀጥሎም በዚምባብዌ ከዚያም በዛምቢያ ሥልጠናውን ሰጠን። ለሦስት ዓመት ተኩል ያህል ሥልጠናውን ስንሰጥ ከቆየን በኋላ፣ በማላዊ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነታቸውን በመጠበቃቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸውን ወንድሞች ተሞክሮ ለማጠናቀር ወደ ማላዊ እንድንመለስ ተጠየቅን።b
በ2005 ወደ ባሳልት፣ ኮሎራዶ ስንመለስ ልክ እንደ ቀድሞው በጣም አዝነን ነበር፤ በዚያ እኔና ቤቴል በአቅኚነት ማገልገላችንን ቀጠልን። በ2006 ብራያንና ኪምበርሊ፣ መኬንዚና ኤሊዛቤት የተባሉ ሁለት ሴቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ እኛ ጎረቤት መኖር ጀመሩ። ፖልና ስቴፋኒ አሁንም በማላዊ ሲሆኑ ፖል የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ እያገለገለ ነው። አሁን ዕድሜዬ ወደ 80 እየተጠጋ ነው፤ ባለፉት ዓመታት አብሬያቸው ስሠራ የነበሩ ከእኔ በዕድሜ የሚያንሱ ወንድሞች እኔ የነበሩኝን ኃላፊነቶች ሲሸከሙ ሳይ በጣም ደስ ይለኛል። ለደስታችን አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ፣ መልካም ምሳሌ የተዉልን ሰዎች መኖራቸው እንዲሁም የእነሱን ምሳሌ በማንጸባረቅ ለልጆቻችንና ለልጅ ልጆቻችን ጥሩ ምሳሌ ለመሆን መጣራችን ነው።
a የእህት ስቲል ቤተሰብ ስላከናወነው የሚስዮናዊነት ሥራ ለማንበብ የግንቦት 1, 1956 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 269-272 እና የመጋቢት 15, 1971 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ከገጽ 186-190 ተመልከት።
b ለምሳሌ ያህል፣ በሚያዝያ 15, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 14-18 ላይ የወጣውን የወንድም ትሮፊም ንሶምባን የሕይወት ታሪክ ተመልከት።