ምድር ገነት ትሆናለች የሚለው ሐሳብ ቅዠት ነው?
ገነት! በመጽሔቶች ላይ ወይም በቴሌቪዥን የሚያማምሩ ቦታዎች ስንመለከት “ገነት” ወደሆኑት ወደነዚህ አካባቢዎች በመሄድ ችግሮቻችንን ሁሉ ረስተን ዘና ለማለት እንጓጓለን። ይሁን እንጂ ወደ ቤታችን ስንመለስ ትተነው የሄድነው ችግር ተወግዶ እንደማይጠብቀን የታወቀ ነው።
ብዙ ሰዎች ስለ ገነት ሲነሳ ትኩረታቸው ይሳባል። በመሆኑም የሚከተሉትን ጥያቄዎች ማንሳታችን ተገቢ ነው፦ ወደፊት ምድር ገነት ትሆናለች የሚለው ተስፋ ቅዠት ነው? ከሆነ ይህን ያህል ቀልባችንን የሚስበው ለምንድን ነው? ይህ ተስፋ በእርግጥ ይፈጸማል?
ስለ ገነት የሚያወሱ ታሪኮች
ባለፉት መቶ ዘመናት የኖሩ በርካታ ሰዎች ስለ ገነት የማወቅ ጉጉት ነበራቸው። ብዙዎች ስለ ገነት የማወቅ ፍላጎት ያደረባቸው “በስተ ምሥራቅ፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ” እንደነበረ የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ በመመልከታቸው ነው። ያንን የአትክልት ስፍራ በጣም ማራኪ እንዲሆን ያደረገው ምን ነበር? ዘገባው “ይሖዋ አምላክ ለማየት የሚያስደስተውንና ለምግብነት መልካም የሆነውን ዛፍ ሁሉ ከመሬት አበቀለ” ይላል። ይህ የአትክልት ስፍራ አስደሳችና የሚያምር ቦታ ነበር። ከሁሉ በላይ ደግሞ “በአትክልቱ ስፍራ መካከል የሕይወት ዛፍ” ነበር።—ዘፍጥረት 2:8, 9
በተጨማሪም የዘፍጥረት ዘገባ ከአትክልቱ ስፍራ ወጥተው የሚፈሱ አራት ወንዞችን ይጠቅሳል። ከእነዚህ ወንዞች መካከል ሁለቱ ማለትም ጤግሮስ (ወይም ሂዲኬል) እና ኤፍራጥስ ዛሬም ድረስ አሉ። (ዘፍጥረት 2:10-14 የግርጌ ማስታወሻ) እነዚህ ሁለት ወንዞች በድሮ ዘመን የጥንቷ ፋርስ ግዛት የነበረውን የአሁኗን የኢራቅ ምድር አቋርጠው ወደ ፋርስ ባሕረ ሰላጤ ይገባሉ።
በአሁኑ ጊዜ ገነት የሆነች ምድርን የሚያሳዩ በርካታ የፋርስ ባሕላዊ ቅርሶች ይገኛሉ። በፔንስልቬንያ ዩ ኤስ ኤ፣ በፊላደልፊያ የኪነ ጥበብ ሙዚየም ውስጥ በሚገኝ በ16ኛው መቶ ዘመን የተሠራ ምንጣፍ ላይ የተለያዩ ዛፎችና አበቦች ያሉበት አንድ የታጠረ የአትክልት ስፍራ ሥዕል ይታያል። “ገነት” የሚለው ቃል “የታጠረ የአትክልት ስፍራ” የሚል ትርጉም ካለው የፋርስ ቃል የመጣ ሲሆን በምንጣፉ ላይ የሚታየው ሥዕል መጽሐፍ ቅዱስ ውብና ለምለም ስለሆነችው ኤደን ገነት ከሚገልጸው ሐሳብ ጋር ተመሳሳይ ነው።
በዓለም ዙሪያ የተለያዩ ቋንቋዎችን በሚናገሩ ማኅበረሰቦች መካከል ስለ ገነት የሚገልጹ ታሪኮችን መስማት የተለመደ ነው። የሰው ልጆች ወደተለያዩ የምድር ክፍሎች ሲሰደዱ በየአካባቢያቸው ስለ ቀድሞዋ ገነት ይነገሩ የነበሩ ታሪኮችን ለሌሎች ማውሳታቸውን ቀጠሉ፤ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ታሪኩ በየቦታው ከተስፋፉት እምነቶችና አፈ ታሪኮች ጋር ተቀላቅሎ ይነገር ጀመር። በዛሬው ጊዜም እንኳ ሰዎች የተፈጥሮ ውበት የተላበሱ ቦታዎችን “ገነት” ብለው ይገልጿቸዋል።
ገነትን ለማግኘት የተደረገ ፍለጋ
አንዳንድ አገር አሳሾች የጠፋችውን ገነት እንዳገኙ ተናግረው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ የብሪታንያ የጦር ሠራዊት አዛዥ የነበረው ቻርልስ ጎርደን በ1881 ሲሸልስን በጎበኘ ጊዜ አሁን የዓለም ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው ቫሊ ደ ማይ የተባለው ቦታ ባለው ልምላሜና ውበት በጣም በመደነቁ ‘ይሄማ የኤደን የአትክልት ስፍራ ነው’ ብሎ ተናግሮ ነበር። በ15ኛው መቶ ዘመን ጣሊያናዊው መርከበኛ ክሪስቶፈር ኮሎምበስ አሁን ዶሚኒካን ሪፑብሊክና ሄይቲ ተብለው የሚጠሩት አገሮች ወደሚገኙባት የሂስፓኒዮላ ደሴት ሲደርስ የኤደንን የአትክልት ስፍራ ያገኘ መስሎት ነበር።
ማፒንግ ፓራዳይዝ የተሰኘ አንድ ዘመናዊ የታሪክ መጽሐፍ በኤደን የነበሩትን አዳምንና ሔዋንን የሚያሳዩ ከ190 የሚበልጡ የጥንት ካርታዎችን ይዟል። ከእነዚህ ካርታዎች መካከል በሊየባና ይኖር የነበረው ቤአተስ ባዘጋጀው ጥንታዊ ጽሑፍ ቅጂ ውስጥ ያለው ለየት ያለ ካርታ ይገኝበታል፤ ይህ ቅጂ በ13ኛው መቶ ዘመን የተዘጋጀ ነው። በዚህ ካርታ አናት ላይ ባለው አራት ማዕዘን ቅርፅ ውስጥ ገነት የምትገኝበት ቦታ ይታያል። “ጤግሮስ፣” “ኤፍራጥስ፣” “ፊሶን” እና “ግዮን” ተብለው የተሰየሙ አራት ወንዞች ከገነት ተነስተው ወደተለያዩ አራት አቅጣጫዎች ይፈሳሉ፤ እነዚህ ወንዞች ክርስትና ወደ አራቱ የምድር ማዕዘናት መስፋፋቱን ያመለክታሉ ተብሎ ይታሰባል። እንዲህ ዓይነቶቹ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ የመጀመሪያዋ ገነት የነበረችበት ቦታ ባይታወቅም እንኳ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፉ የኖሩት ታሪኮች ሰዎች ለገነት ያላቸው አድናቆት እንዳይጠፋ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ያሳያሉ።
በ17ኛው መቶ ዘመን የኖረው እንግሊዛዊ ገጣሚ ጆን ሚልተን አዳም ስለሠራው ኃጢአትና ከገነት ስለመባረሩ በሚገልጸው የዘፍጥረት ዘገባ ላይ ተመሥርቶ የጻፈው ፓራዳይዝ ሎስት የተባለው ግጥም ታዋቂነትን እንዲያተርፍ አድርጎታል። በዚህ ግጥም ውስጥ ሰዎች ዳግመኛ በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የተሰጠውን ተስፋ ጎላ አድርጎ የገለጸ ሲሆን “በዚያን ጊዜ መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች” ብሎ ተናግሯል። ከጊዜ በኋላም ሚልተን ፓራዳይዝ ሪጌይንድ የተሰኘውን ቀጣይ ግጥም ጽፏል።
ችላ የተባለ ርዕሰ ጉዳይ
ስለጠፋችው ምድራዊ ገነት የሚገልጸው ታሪክ ባለፉት ዘመናት ሁሉ የሰው ልጆችን ትኩረት የሳበ ጉዳይ እንደነበር በግልጽ መረዳት ይቻላል። ታዲያ አሁን ችላ የተባለው ለምንድን ነው? ማፒንግ ፓራዳይዝ የተባለው መጽሐፍ ይህ የሆነበትን ምክንያት ሲገልጽ “የሃይማኖት ምሁራን . . . ገነት ስለነበረችበት ቦታ የሚነሳውን ጥያቄ ሆን ብለው ወደ ጎን ገሸሽ ስላደረጉት ነው” ብሏል።
አብዛኞቹ ቤተ ክርስቲያን ተሳላሚዎች የመጨረሻው ዕጣ ፈንታቸው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ መኖር ሳይሆን ሰማይ መሄድ እንደሆነ ይነገራቸዋል። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 37:29 ላይ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። በዛሬው ጊዜ ዓለማችን ካለችበት ሁኔታ አንጻር ሲታይ ይህ ተስፋ ሊፈጸም እንደሚችል በምን እርግጠኛ መሆን እንችላለን?a
መላዋ ምድር ገነት ትሆናለች
የመጀመሪያዋን ገነት የፈጠረው ይሖዋ አምላክ ምድርን ዳግመኛ ገነት እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። ይህ ተስፋ የሚፈጸመው እንዴት ነው? ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይፈጸም” ብለን እንድንጸልይ እንዳስተማረን አስታውስ። (ማቴዎስ 6:10) ይህ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ የሚመራ ዓለም አቀፍ መስተዳድር ሲሆን ሰብዓዊ አገዛዝን በሙሉ አስወግዶ ምድርን ይገዛል። (ዳንኤል 2:44) በዚህ መንግሥት አገዛዝ ሥር አምላክ ምድርን ገነት ለማድረግ ያለው ዓላማ ወይም ፈቃድ ‘ይፈጸማል።’
ነቢዩ ኢሳይያስም በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ወደፊት በምትመጣው ገነት ውስጥ የሚኖሩትን ሁኔታዎች ገልጿል። በዛሬው ጊዜ ያሉት ችግሮችና ውጥረት የሚፈጥሩ ሁኔታዎች ያን ጊዜ ይወገዳሉ። (ኢሳይያስ 11:6-9፤ 35:5-7፤ 65:21-23) ጥቂት ደቂቃዎች ወስደህ እነዚህን ጥቅሶች እንድታነብ እናበረታታሃለን። እንዲህ ማድረግህ አምላክ ታዛዥ ለሆኑ ሰዎች የሰጠው ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኛ እንድትሆን ያስችልሃል። በዚያን ጊዜ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ አዳም ያጣቸውን ነገሮች ያገኛሉ፤ አዎ፣ የአምላክን ሞገስ አግኝተው በገነት ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ።—ራእይ 21:3
ታዲያ ምድር ገነት ትሆናለች የሚለው ተስፋ ቅዠት ሳይሆን በእርግጥ የሚፈጸም ነገር ነው የምንለው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሰማያት የይሖዋ ናቸው፤ ምድርን ግን ለሰው ልጆች ሰጣት” ብሎ ስለሚናገር ነው። ምድር ገነት እንደምትሆን የሚገልጸው ተስፋ “ሊዋሽ የማይችለው አምላክ ከረጅም ዘመናት በፊት” የሰጠው ተስፋ ነው። (መዝሙር 115:16፤ ቲቶ 1:2) ወደፊት የሰው ልጆች ገነት በሆነች ምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ አምላክ የገባው ቃል እንዴት ያለ አስደሳች ተስፋ ነው!
a ቁርዓንም ጭምር አል-አንቢያ [ነቢያት] በተባለው በሱራ 21 ቁጥር 105 ላይ “ምድርንም መልካሞቹ ባሮቼ ይወርሷታል” ብሎ የሚናገር መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው።