መጥፎ ልማዶችን ማስወገድና እንዳያገረሹብን መከላከል
“አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ።”—ቆላ. 3:9
1, 2. አንዳንዶች የይሖዋ ምሥክሮችን በተመለከተ ምን አስተያየት ሰጥተዋል?
የይሖዋ ምሥክሮች ያላቸውን ጥሩ ባሕርይ በተመለከተ በርካታ ሰዎች አስተያየት ሰጥተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አንቶን ጊል የተባሉት ደራሲ በናዚ ጀርመን የነበሩትን የይሖዋ ምሥክሮች አስመልክተው እንዲህ በማለት ጽፈዋል፦ “ናዚዎቹ ለይሖዋ ምሥክሮች ለየት ያለ ጥላቻ ነበራቸው። . . . በ1939 [በማጎሪያ ካምፖቹ] ውስጥ 6,000 የይሖዋ ምሥክሮች ነበሩ።” አክለውም የይሖዋ ምሥክሮች ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም “እምነት የሚጣልባቸውና በአስቸጋሪ ሁኔታዎችም ሥር የተረጋጉ” እንዲሁም “ታማኞችና አንድነት ያላቸው” እንደነበሩ ጽፈዋል።
2 በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ሰዎችም የይሖዋ ሕዝቦች ማራኪ ባሕርይ እንዳላቸው ታዝበዋል። ደቡብ አፍሪካ ውስጥ፣ የተለያየ የቆዳ ቀለም ያላቸው የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት አብረው መሰብሰብ የማይችሉበት ወቅት ነበር። ይሁንና እሁድ፣ ታኅሣሥ 18, 2011 በደቡብ አፍሪካና በአጎራባች አገሮች የሚኖሩ ከተለያየ ዘር የተውጣጡ ከ78,000 በላይ የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀላቸው መንፈሳዊ ፕሮግራም ለመካፈል በጆሃንስበርግ በሚገኘው ትልቁ ስታዲየም ውስጥ ተሰብስበው ነበር። ከስታዲየሙ ሥራ አስኪያጆች መካከል አንዱ በዚያ ስለተሰበሰቡት ሰዎች እንዲህ ሲል አስተያየት ሰጥቷል፦ “እስካሁን ድረስ በዚህ ስታዲየም ከተሰበሰቡት ሰዎች መካከል እንዲህ ያለ ጥሩ ምግባር ያላቸው ሰዎች አጋጥመውኝ አያውቁም። ሁሉም ሥርዓታማ አለባበስ አላቸው። ደግሞም ስታዲየሙን በጣም ጥሩ አድርጋችሁ አጽድታችሁታል። ከሁሉ በላይ ያስገረመኝ ግን ከተለያየ ዘር የተውጣጣችሁ መሆናችሁ ነው።”
3. ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችንን ልዩ እንዲሆን ያደረገው ምንድን ነው?
3 የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች የሰጡት እንዲህ ያለው አስተያየት ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበራችን በእርግጥም ልዩ እንደሆነ ያሳያል። (1 ጴጥ. 5:9) ይሁንና ከሌሎች ድርጅቶች ልዩ እንድንሆን ያደረገን ምንድን ነው? በአምላክ ቃልና በቅዱስ መንፈሱ እርዳታ ‘አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣል’ እና “አዲሱን ስብዕና [ለመልበስ]” ከፍተኛ ጥረት ማድረጋችን ነው።—ቆላ. 3:9, 10
4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ነገሮችን እንመረምራለን? እንዲህ ማድረጋችን አስፈላጊ የሆነውስ ለምንድን ነው?
4 አሮጌውን ስብዕና ገፎ በመጣል መጥፎ ልማዶችን ማስወገድ አንድ ነገር ነው፤ እነዚህ ልማዶች እንዳያገረሹብን መከላከል ደግሞ ሌላ ነገር ነው። በዚህ ርዕስ ውስጥ አሮጌውን ስብዕና ገፈን መጣል የምንችለው እንዴት እንደሆነና እንዲህ ማድረጋችን አጣዳፊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። እንዲሁም አንድ ሰው የቱንም ያህል በመጥፎ ልማዶች የተዘፈቀ ቢሆን ለውጥ ማድረግ ይችላል የምንልበትን ምክንያት እንመረምራለን። በተጨማሪም በእውነት ውስጥ ለበርካታ ዓመታት የኖሩ ክርስቲያኖች መጥፎ ልማዶች እንዳያገረሹባቸው ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለባቸው እናያለን። እንዲህ ያሉ ማሳሰቢያዎችን መስጠት ያስፈለገው ለምንድን ነው? የሚያሳዝነው፣ ይሖዋን ያገለግሉ የነበሩ አንዳንዶች ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው ወደ ቀድሞ ልማዶቻቸው ተመልሰዋል። በመሆኑም ሁላችንም “የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ” የሚለውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ያስፈልገናል።—1 ቆሮ. 10:12
ከፆታ ብልግና ራቁ
5. (ሀ) አሮጌውን ስብዕና ገፈን ለመጣል አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያለብን ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) በቆላስይስ 3:5-9 ላይ የተጠቀሱት የአሮጌው ስብዕና ክፍል የሆኑ መጥፎ ልማዶች የትኞቹ ናቸው?
5 ልብሳችሁ ቢቆሽሽና መጥፎ ጠረን ቢያመጣ ምን ታደርጋላችሁ? የቆሸሸውን ልብሳችሁን በተቻለ ፍጥነት እንደምታወልቁት ምንም ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ከአምላክ ባሕርይ ጋር የሚጋጩ ልማዶችን ገፈን እንድንጥል የተሰጠንን መመሪያ ለመታዘዝ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን። ጳውሎስ በዘመኑ ለነበሩት ክርስቲያኖች “[እነዚህን ልማዶች] ሁሉ ከእናንተ አስወግዱ” በማለት የሰጠውን ግልጽ መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ እንፈልጋለን። ጳውሎስ ከጠቀሳቸው መጥፎ ልማዶች መካከል ሁለቱን ማለትም የፆታ ብልግናንና ርኩሰትን እንመልከት።—ቆላስይስ 3:5-9ን አንብብ።
6, 7. (ሀ) ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ አሮጌውን ስብዕና ገፎ መጣል ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚጠይቅ የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ሳኩራ ምን ዓይነት ሕይወት ትመራ ነበር? የቀድሞ አኗኗሯን ለመቀየር የሚያስችል ጥንካሬ ያገኘችውስ እንዴት ነው?
6 የፆታ ብልግና። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የፆታ ብልግና” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ሕጋዊ ጋብቻ ባልፈጸሙ ሰዎች መካከል የሚደረገውን የፆታ ግንኙነትና ግብረ ሰዶማዊነትን የሚያካትት ነው። ጳውሎስ ለእምነት ባልንጀሮቹ ‘የአካል ክፍሎቻቸውን እንዲገድሉ’ ማለትም ‘ከፆታ ብልግና’ ጋር ተያያዥነት ያለውን ማንኛውንም ፍላጎት እንዲያስወግዱ ነግሯቸዋል። ጳውሎስ የተጠቀመበት አገላለጽ መጥፎ ፍላጎቶችን ማስወገድ ጠንካራ እርምጃ መውሰድን እንደሚጠይቅ በግልጽ ያሳያል። ያም ሆኖ በትግሉ ልናሸንፍ እንችላለን።
7 በጃፓን የምትኖረውን የሳኩራንa ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ልጅ ሳለች ከብቸኝነትና ከባዶነት ስሜት ጋር ትታገል ነበር። ከ15 ዓመቷ ጀምሮ የብቸኝነት ስሜቷን ለጊዜውም ቢሆን ለመርሳት ስትል ከተለያዩ ወንዶች ጋር የፆታ ግንኙነት ትፈጽም ነበር። በዚህም ምክንያት ሦስት ጊዜ ውርጃ ፈጽማለች። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ፣ የፆታ ግንኙነት ስፈጽም በሌሎች ዘንድ ተፈላጊ እንደሆንኩና እንደምወደድ ስለሚሰማኝ እረጋጋ ነበር። በዚህ ድርጊቴ እየገፋሁበት ስሄድ ግን የሚሰማኝ ያለመረጋጋት ስሜት እየባሰ ሄደ።” ሳኩራ 23 ዓመት እስኪሞላት ድረስ እንዲህ ያለ ሕይወት መምራቷን ቀጠለች። ከዚያም ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ሳኩራ የተማረችውን ነገር እየወደደችው መጣች፤ በውስጧ የሚሰማትን ከፍተኛ የጥፋተኝነትና የኃፍረት ስሜት በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ የቻለች ሲሆን ሥነ ምግባር የጎደለውን አኗኗሯንም እርግፍ አድርጋ ተወች። አሁን በዘወትር አቅኚነት እያገለገለች ከመሆኑም ሌላ በብቸኝነት ስሜት አትሠቃይም። በአሁኑ ጊዜ ያላትን ሕይወት አስመልክታ ስትናገር “የይሖዋን ጥልቅ ፍቅር ያለማቋረጥ ማጣጣም በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች።
ርኩስ ልማዶችን ማሸነፍ
8. በአምላክ ፊት ርኩስ እንድንሆን የሚያደርጉን አንዳንድ ልማዶች የትኞቹ ናቸው?
8 ርኩሰት። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ርኩሰት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከፆታ ብልግና በተጨማሪ ሌሎች በርካታ ልማዶችን የሚያካትት ሰፊ ትርጉም ያለው ቃል ነው። እንደማጨስና የብልግና ቀልዶችን እንደመናገር ያሉ ጎጂ ልማዶችን ያካትታል። (2 ቆሮ. 7:1፤ ኤፌ. 5:3, 4) እንዲሁም የፆታ ስሜትን የሚቀሰቅሱ መጻሕፍትን እንደማንበብ ወይም የብልግና ምስሎችን እንደመመልከት ያሉ አንድ ግለሰብ ከሰው እይታ ውጭ ሆኖ የሚያደርጋቸውን ርኩስ ነገሮች ይጨምራል። እነዚህ ነገሮች ርኩስ ልማድ የሆነውን ማስተርቤሽንን ወደመፈጸም ሊያመሩ ይችላሉ።—ቆላ. 3:5b
9. በውስጣችን “ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት” እንዲቀሰቀስ መፍቀድ ምን መዘዝ ሊያስከትል ይችላል?
9 የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ያላቸው ሰዎች በውስጣቸው “ልቅ የሆነ የፍትወት ስሜት” ይቀሰቀሳል፤ ይህም የፆታ ግንኙነት የመፈጸም ሱስ እንዲጠናወታቸው ያደርጋል። በውስጣቸው የብልግና ምስሎችን የመመልከት ኃይለኛ ግፊት ያላቸው ሰዎች፣ የአልኮል መጠጥና የዕፅ ሱስ ካለባቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ምልክት እንደሚታይባቸው በምርምር መረዳት ተችሏል። በእርግጥም የብልግና ምስሎችን መመልከት ብዙ መዘዞች የሚያስከትል መሆኑ አያስገርምም፤ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ልማድ ከፍተኛ ለሆነ የኃፍረት ስሜት ይዳርጋል፣ በሥራ ቦታ ውጤታማነትን ይቀንሳል፣ በቤተሰብ ሕይወት የሚገኝ ደስታን ያሳጣል እንዲሁም ለትዳር መፍረስና ራስን ለማጥፋት ምክንያት ሊሆን ይችላል። የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ሱስ የተላቀቀበትን አንደኛ ዓመት ያከበረ አንድ ግለሰብ “አጥቼው የነበረውን ውስጣዊ ንጽሕና መልሼ ማግኘት ችያለሁ” በማለት ጽፏል።
10. ሪቤሮ የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ሱስ መላቀቅ የቻለው እንዴት ነው?
10 የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሱስ የተጠናወታቸው በርካታ ሰዎች ከዚህ ልማድ ለመላቀቅ ቀጣይ የሆነ ትግል ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ይሁንና በብራዚል የሚኖረው የሪቤሮ ታሪክ እንደሚያሳየው በዚህ ትግል ማሸነፍ ይቻላል። ሪቤሮ በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለ ከቤት ጥሎ የወጣ ሲሆን ያገለገሉ ወረቀቶች መልሰው ጥቅም ላይ እንዲውሉ በሚያደርግ ፋብሪካ ውስጥ መሥራት ጀመረ፤ በዚያ ሲሠራ የብልግና ምስሎችን የሚያሳዩ መጽሔቶችን አገኘ። እንዲህ ብሏል፦ “ቀስ በቀስ የብልግና ምስሎችን የመመልከት ሱስ ተጠናወተኝ። ይህ ሱስ በጣም እያየለብኝ ከመሄዱ የተነሳ የብልግና ምስሎችን የሚያሳዩ ቪዲዮዎችን ለመመልከት ስል አብራኝ የምትኖረው ሴት ከቤት እስክትወጣልኝ ድረስ እቸኩል ነበር።” አንድ ቀን ሪቤሮ በሥራ ቦታው ሳለ፣ በፋብሪካው ውስጥ ከተቆለሉ መጻሕፍት መካከል ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? የሚለውን መጽሐፍ አገኘ። መጽሐፉን አንስቶ ማንበብ ጀመረ። ከመጽሐፉ ላይ ያነበበው ነገር ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት አነሳሳው፤ ይሁንና ከመጥፎ ልማዱ ለመላቀቅ ረጅም ጊዜ ፈጅቶበታል። ታዲያ ከጊዜ በኋላ ይህን ልማድ ለማሸነፍ የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ መጸለዬ፣ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናቴ እንዲሁም በተማርኩት ነገር ላይ ማሰላሰሌ የአምላክን ባሕርያት ይበልጥ እንዳደንቅ አስችሎኛል፤ ይህም ለይሖዋ ያለኝ ፍቅር የብልግና ምስሎችን እንድመለከት ከሚገፋፋኝ ስሜት እንዲያይል ረድቶኛል።” ሪቤሮ ከአምላክ ቃል እንዲሁም ከመንፈስ ቅዱስ ያገኘው እርዳታ አሮጌውን ስብዕና ገፎ እንዲጥልና እንዲጠመቅ የረዳው ሲሆን በአሁኑ ጊዜ በጉባኤ ሽማግሌነት በማገልገል ላይ ይገኛል።
11. አንድ ሰው የብልግና ምስሎችን ከመመልከት እንዲርቅ ምን ሊረዳው ይችላል?
11 ሪቤሮ የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ሱስ እንዲላቀቅ የረዳው መጽሐፍ ቅዱስን ማንበቡ ብቻ እንዳልሆነ ልብ በል። የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ወደ ልቡ ዘልቆ እንዲገባ፣ ባነበበው ነገር ላይ ጊዜ ወስዶ ማሰላሰል አስፈልጎታል። እንዲሁም ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮአል። እንዲህ ማድረጉ ለአምላክ ያለው ፍቅር የብልግና ምስሎችን እንዲመለከት ከሚገፋፋው ስሜት እንዲያይል ረድቶታል። የብልግና ምስሎችን ከመመልከት ለመራቅ ቁልፉ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግና መጥፎ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ ማዳበር ነው።—መዝሙር 97:10ን አንብብ።
ቁጣን፣ ስድብንና ውሸትን አስወግዱ
12. ስቲቨን ቁጣንና ስድብን እንዲያስወግድ የረዳው ምንድን ነው?
12 በቀላሉ ቱግ የሚሉ ሰዎች ቁጣቸውን የሚገልጹት በስድብ ነው። እንዲህ ያለው ባሕርይ በቤተሰብ ሕይወት ውስጥ ደስታን እንደሚያሳጣ ግልጽ ነው። በአውስትራሊያ የሚኖር ስቲቨን የተባለ አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “በጣም የምሳደብና በረባ ባልረባው በቁጣ የምገነፍል ሰው ነበርኩ። በዚህ ምክንያት እኔና ባለቤቴ ሦስት ጊዜ የተለያየን ሲሆን በኋላም ለመፋታት ወስነን ነበር።” ከዚያም ስቲቨንና ባለቤቱ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመሩ። ስቲቨን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር ምን ውጤት ተገኘ? እንዲህ ብሏል፦ “የቤተሰብ ሕይወታችን አስገራሚ በሆነ መንገድ ተሻሻለ። ከዚህ ቀደም፣ ትንሽ የሚያበሳጭ ነገር ሲያጋጥመኝ ቱግ እል ነበር፤ በውስጤ የታመቀው ምሬትና ብስጭት በማንኛውም ጊዜ ሊፈነዳ እንደሚችል ቦምብ አድርጎኝ ነበር። አሁን ግን በይሖዋ እርዳታ ውስጣዊ ሰላምና መረጋጋት አግኝቻለሁ።” በአሁኑ ጊዜ ስቲቨን የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ በማገልገል ላይ ሲሆን ባለቤቱ ደግሞ ላለፉት ዓመታት በዘወትር አቅኚነት በማገልገል ላይ ትገኛለች። ስቲቨን ባለበት ጉባኤ ውስጥ የሚያገለግሉ ሽማግሌዎች “ስቲቨን በጣም የተረጋጋ፣ ትጉና ትሑት ወንድም ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። አንድም ቀን ሲበሳጭ አይተውት አያውቁም። ስቲቨን እንዲህ ያለ ለውጥ ሊያደርግ የቻለው በራሱ ጥረት እንደሆነ አድርጎ ያስባል? እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ስብዕናዬ ሙሉ በሙሉ እንዲለወጥ ሲል ያደረገልኝን እርዳታ ባልቀበል ኖሮ እነዚህን ሁሉ በረከቶች ላገኝ አልችልም ነበር።”
13. ቁጣ አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል?
13 መጽሐፍ ቅዱስ ቁጣን፣ ስድብንና ጩኸትን እንድናስወግድ የሚመክረን አለምክንያት አይደለም። (ኤፌ. 4:31) የሚያሳዝነው እንዲህ ያለው ምግባር አብዛኛውን ጊዜ ወደ ጠብ ይመራል። በምንኖርበት ዓለም ውስጥ በተለያየ መንገድ ቁጣን መግለጽ የተለመደ ነገር እንደሆነ ተደርጎ ይታያል፤ ይሁንና እንዲህ ያለው ምግባር ፈጣሪያችንን አያስከብርም። በመሆኑም በርካታ ሰዎች እነዚህን ጎጂ ልማዶች ማስወገድና አዲሱን ስብዕና መልበስ አስፈልጓቸዋል።—መዝሙር 37:8-11ን አንብብ።
14. ጠበኛ የነበረ ሰው ተለውጦ ገር ሊሆን ይችላል?
14 በኦስትሪያ ባለ አንድ ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለውን የሃንስን ተሞክሮ እንመልከት። ሃንስ ያለበት ጉባኤ የሽማግሌዎች አካል አስተባባሪ “እንደ እሱ ያለ ገር ሰው ፈጽሞ አይቼ አላውቅም” በማለት ተናግሯል። ከዚህ በፊት ግን ሃንስ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያለው ሰው አልነበረም። በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለ የአልኮል መጠጥ ከልክ በላይ መጠጣት የጀመረ ሲሆን በዚህም ምክንያት ጠበኛ ሆነ። አንድ ቀን በስካር መንፈስ በጣም ተበሳጭቶ የሴት ጓደኛውን ገደላት፤ በዚህም የተነሳ የ20 ዓመት እስራት ተፈርዶበት ወህኒ ቤት ገባ። ሃንስ እስር ቤት መግባቱ የጠበኝነት ባሕርይውን እንዲያሻሽል አልረዳውም። ከጊዜ በኋላ እናቱ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እስር ቤት ሄዶ ሃንስን እንዲያነጋግረው አደረገች፤ ከዚያም ሃንስ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “አሮጌውን ስብዕናዬን ገፍፌ ለመጣል ከፍተኛ ትግል ማድረግ አስፈልጎኛል። በዚያን ወቅት ካበረታቱኝ ጥቅሶች መካከል አንዱ ‘ክፉ ሰው መንገዱን ይተው’ የሚለው በኢሳይያስ 55:7 ላይ የሚገኘው ጥቅስ ነው። በተጨማሪም በ1 ቆሮንቶስ 6:11 ላይ የሚገኘው የኃጢአት መንገዳቸውን ስለተዉ ሰዎች የሚናገረው ‘አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ’ የሚለው ጥቅስ በጣም አበረታቶኛል። ይሖዋ አዲሱን ስብዕና እንድለብስ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለበርካታ ዓመታት በትዕግሥት ረድቶኛል።” ሃንስ ለ17 ዓመት ተኩል በእስር ከቆየ በኋላ የተጠመቀ ክርስቲያን ሆኖ ከእስር ቤት ወጣ። ሃንስ “ይሖዋ ይቅር ስላለኝና ይገባኛል የማልለው ምሕረት ስላደረገልኝ በጣም አመስጋኝ ነኝ” በማለት ተናግሯል።
15. በአሁኑ ጊዜ ምን ማድረግ የተለመደ ነው? ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ይህን አስመልክቶ ምን ይላል?
15 ከስድብ በተጨማሪ የመዋሸት ልማድም የአሮጌው ስብዕና አንዱ ክፍል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ ሰዎች የሚጠበቅባቸውን ግብር ላለመክፈል ወይም ለሠሩት ስህተት ኃላፊነት ላለመውሰድ ሲሉ መዋሸታቸው የተለመደ ነው። ይሖዋ ግን “የእውነት አምላክ” ነው። (መዝ. 31:5) በመሆኑም የእሱ አገልጋይ የሆነ ‘እያንዳንዱ’ ግለሰብ ‘ከባልንጀራው ጋር እውነትን እንዲነጋገር’ እንዲሁም ‘እንዳይዋሽ’ ይጠብቅበታል። (ኤፌ. 4:25፤ ቆላ. 3:9) ስለዚህ ሊያሳፍረን ወይም ከባድ ሊሆንብን ቢችልም እንኳ እውነቱን መናገር ይኖርብናል።—ምሳሌ 6:16-19
በትግሉ ሊያሸንፉ የቻሉት እንዴት ነው?
16. አንድ ሰው አሮጌውን ስብዕና ገፎ በመጣል ረገድ ሊሳካለት የሚችለው እንዴት ነው?
16 አንድ ሰው በራሱ ጥንካሬ አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፎ መጣል አይችልም። በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ሳኩራ፣ ሪቤሮ፣ ስቲቨን እና ሃንስ መጥፎ ልማዶቻቸውን ለማስወገድ ከፍተኛ ትግል ማድረግ አስፈልጓቸዋል። በትግሉ ሊያሸንፉ የቻሉት የአምላክ ቃልና የቅዱስ መንፈሱ ኃይል በሕይወታቸው ውስጥ እንዲሠራ በመፍቀዳቸው ነው። (ሉቃስ 11:13፤ ዕብ. 4:12) ከአምላክ ቃልና ከቅዱስ መንፈሱ ከሚገኘው ኃይል ተጠቃሚ ለመሆን መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብ፣ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለንን ጥበብና ጥንካሬ እንዲሰጠን ወደ ይሖዋ አዘውትረን መጸለይ ይኖርብናል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 119:97፤ 1 ተሰ. 5:17) በተጨማሪም ጥሩ ዝግጅት አድርገን በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከአምላክ ቃልና ከቅዱስ መንፈሱ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። (ዕብ. 10:24, 25) እንዲሁም በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ የአምላክ ሕዝቦች በተለያየ መልኩ ከሚቀርበው መንፈሳዊ ምግብ በሚገባ መጠቀም ይኖርብናል።—ሉቃስ 12:42
17. በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?
17 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ክርስቲያኖች ሊያስወግዷቸውና እንዳያገረሹባቸው ሊከላከሏቸው የሚገቡ አንዳንድ ልማዶችን ተመልክተናል። ይሁንና የአምላክን ሞገስ ለማግኘት አሮጌውን ስብዕና ገፎ መጣል ብቻ በቂ ነው? አይደለም። አዲሱን ስብዕና መልበስም ያስፈልጋል። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምንጊዜም የምሳሌያዊው ልብሳችን ክፍል ሊሆኑ የሚገባቸውን የአዲሱን ስብዕና አንዳንድ ገጽታዎች እንመረምራለን።
a በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።