የጥናት ርዕስ 8
አድናቆታችንን መግለጽ ያለብን ለምንድን ነው?
“አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።”—ቆላ. 3:15
መዝሙር 46 ይሖዋ እናመሰግንሃለን
የትምህርቱ ዓላማa
1. ኢየሱስ የፈወሰው ሳምራዊ አድናቆቱን የገለጸው እንዴት ነው?
አሥሩ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው። እነዚህ ሰዎች የሥጋ ደዌ በሽተኞች ሲሆኑ ከዚህ በሽታ የመላቀቅ ተስፋ የላቸውም። አንድ ቀን ግን ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ሲመጣ ከሩቅ ተመለከቱ። ኢየሱስ ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እንደሚፈውስ ሰምተዋል፤ ስለዚህ እነሱንም ሊፈውሳቸው እንደሚችል እርግጠኞች ነበሩ። በመሆኑም “ኢየሱስ፣ መምህር፣ ምሕረት አድርግልን!” በማለት ጮኹ። ከዚያም አሥሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከሕመማቸው ተፈወሱ። ሁሉም ኢየሱስ ላሳያቸው ደግነት የአመስጋኝነት ስሜት እንደተሰማቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከመካከላቸው አንዱ ግን አመስጋኝነቱን በውስጡ ከመያዝ ይልቅ ወደ ኢየሱስ ሄዶ ለተደረገለት ነገር ያለውን አድናቆትb ገልጿል። ከበሽታው የተፈወሰው ይህ ሳምራዊ “አምላክን በታላቅ ድምፅ [ለማመስገን]” ተገፋፍቷል።—ሉቃስ 17:12-19
2-3. (ሀ) አንዳንድ ጊዜ አድናቆታችንን ሳንገልጽ የምንቀረው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 እኛም ልክ እንደዚህ ሳምራዊ፣ ደግነት ላሳዩን ሰዎች አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንፈልጋለን። አንዳንድ ጊዜ ግን አድናቆታችንን በቃል ወይም በተግባር መግለጽ ልንረሳ እንችላለን።
3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ አድናቆታችንን በቃልም ሆነ በተግባር መግለጻችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ አመስጋኝ የሆኑና አመስጋኝ ያልሆኑ ሰዎች ታሪክ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመረምራለን። ከዚያም አድናቆታችንን መግለጽ የምንችልባቸውን አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች እንመለከታለን።
አድናቆታችንን መግለጽ ያለብን ለምንድን ነው?
4-5. አድናቆታችንን መግለጽ ያለብን ለምንድን ነው?
4 ይሖዋ አድናቆትን በመግለጽ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ይህን ያደረገበት አንዱ መንገድ ደስ ለሚያሰኙት አገልጋዮቹ ወሮታ በመክፈል ነው። (2 ሳሙ. 22:21፤ መዝ. 13:6፤ ማቴ. 10:40, 41) ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” የሚል ማበረታቻ ይሰጡናል። (ኤፌ. 5:1) በመሆኑም አድናቆታችንን የምንገልጽበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ መከተል ስለምንፈልግ ነው።
5 አድናቆታችንን እንድንገልጽ የሚያነሳሳንን ሌላ ምክንያት ደግሞ እንመልከት። አድናቆት ልክ እንደ ጣፋጭ ምግብ ነው፤ አንድን ጣፋጭ ምግብ ከሌሎች ጋር ተካፍለን ስንበላው ይበልጥ ደስ ይለናል። በተመሳሳይም ሌሎች ላደረግነው ነገር አድናቆታቸውን ሲገልጹልን እኛ እንደሰታለን። ሌሎች ላደረጉልን ነገር አድናቆታችንን ስንገልጽ ደግሞ እነሱ ይደሰታሉ። አድናቆታችንን የምንገልጽለት ሰው እኛን ለመርዳት ወይም የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት ያደረገው ጥረት ምን ያህል እንደጠቀመን ይገነዘባል። በውጤቱም በእኛና በዚያ ሰው መካከል ያለው ወዳጅነት ይጠናከራል።
6. በምንናገራቸው የአድናቆት ቃላትና ከወርቅ በተሠራ ፖም መካከል ምን ተመሳሳይነት አለ?
6 ለሌሎች የምንናገራቸው የአድናቆት መግለጫዎች ትልቅ ዋጋ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው” ይላል። (ምሳሌ 25:11) በብር መደብ ላይ ያለ ከወርቅ የተሠራ ፖም ምን ያህል ውብ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር! ደግሞም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚኖረው ምንም ጥርጥር የለውም! እንዲህ ያለ ስጦታ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? ለሌሎች የምትናገራቸው የምስጋና ቃላትም የዚህን ያህል ዋጋ አላቸው። በተጨማሪም የሚከተለውን አስብ፦ ከወርቅ የተሠራ ፖም ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። በተመሳሳይም አድናቆታችንን የገለጽንለት ሰው የተናገርናቸውን ቃላት ዕድሜ ልኩን ሊያስታውሳቸውና ከፍ አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል።
አድናቆታቸውን ገልጸዋል
7. በመዝሙር 27:4 መሠረት ዳዊት አድናቆቱን የገለጸው እንዴት ነው? የአሳፍ ዘሮችስ አድናቆታቸውን የገለጹት እንዴት ነው?
7 በጥንት ጊዜ የነበሩ በርካታ የአምላክ አገልጋዮች አመስጋኝነታቸውን ገልጸዋል። ከእነዚህ መካከል አንዱ ዳዊት ነው። (መዝሙር 27:4ን አንብብ።) ዳዊት ለንጹሕ አምልኮ ጥልቅ አድናቆት የነበረው ሲሆን ይህን ስሜቱን በተግባር ገልጿል። ለቤተ መቅደሱ ግንባታ ከፍተኛ መጠን ያለው መዋጮ አድርጓል። የአሳፍ ዘሮች የውዳሴ መዝሙሮችን በመጻፍ አድናቆታቸውን አሳይተዋል። ከጻፏቸው መዝሙሮች መካከል በአንዱ ላይ አምላክን ያመሰገኑ ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ “ድንቅ ሥራዎች” ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። (መዝ. 75:1) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዳዊትና የአሳፍ ዘሮች ከይሖዋ ላገኟቸው በረከቶች ምን ያህል አድናቆት እንዳላቸው ማሳየት ፈልገዋል። አንተስ የእነዚህን ሰዎች ምሳሌ መከተል የምትችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?
8-9. ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ያለውን አድናቆት የገለጸው እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቶ መሆን አለበት?
8 ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አድናቆት ነበረው፤ ይህን አድናቆቱን ደግሞ ስለ እነሱ በሚናገራቸው ነገሮች አሳይቷል። በግሉ ጸሎት ሲያቀርብ ሁልጊዜ እነሱን አስመልክቶ አምላክን ያመሰግን ነበር። በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይም ለእነሱ ያለውን አድናቆት ገልጿል። በሮም ምዕራፍ 16 ላይ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 15 ቁጥሮች ላይ ብቻ 27 የሚያህሉ ክርስቲያኖችን ስም ዘርዝሯል። ለምሳሌ ጵርስቅላና አቂላ ለእሱ ሲሉ “ሕይወታቸውን ለአደጋ [እንዳጋለጡ]” ለይቶ ጠቅሷል፤ በተጨማሪም ፌበን እሱን ጨምሮ “ለብዙ ወንድሞች ድጋፍ” እንደሆነች ተናግሯል። ጳውሎስ እነዚህን ተወዳጅና ትጉ ክርስቲያኖች አመስግኗቸዋል።—ሮም 16:1-15
9 ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ ፍጽምና የጎደላቸው እንደሆኑ ያውቃል፤ ሆኖም ለሮም ክርስቲያኖች የጻፈውን ደብዳቤ ሲደመድም በእነሱ ጥሩ ባሕርያት ላይ ለማተኮር መርጧል። ደብዳቤው በጉባኤ መካከል ጮክ ተብሎ ሲነበብ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ምን ያህል ተበረታተው ሊሆን እንደሚችል መገመት ትችላለህ! ይህም በእነሱና በጳውሎስ መካከል ያለውን ወዳጅነት እንዳጠናከረው ምንም ጥርጥር የለውም። አንተስ የጉባኤህ አባላት ለሚናገሯቸውና ለሚያደርጓቸው ጥሩ ነገሮች ያለህን አድናቆት የመግለጽ ልማድ አለህ?
10. ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያለውን አድናቆት ከገለጸበት መንገድ ምን ትምህርት እናገኛለን?
10 ኢየሱስ በትንሿ እስያ ለነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች በላከው መልእክት ላይ ተከታዮቹ ላከናወኑት ሥራ ያለውን አድናቆት ገልጿል። ለምሳሌ ያህል፣ በትያጥሮን ላለው ጉባኤ የላከውን መልእክት የጀመረው በሚከተሉት ቃላት ነው፦ “ሥራህን፣ ፍቅርህን፣ እምነትህን፣ አገልግሎትህንና ጽናትህን አውቃለሁ፤ ደግሞም ከመጀመሪያው ሥራህ ይልቅ የአሁኑ እንደሚበልጥ አውቃለሁ።” (ራእይ 2:19) ኢየሱስ እነዚህ ክርስቲያኖች እንቅስቃሴያቸውን ከፍ እንዳደረጉ በመጥቀስ ብቻ አልተወሰነም፤ ከዚህ ይልቅ ለመልካም ሥራ እንዲነሳሱ ያደረጓቸውን ባሕርያት ጭምር ጠቅሶ አመስግኗቸዋል። ኢየሱስ በትያጥሮን ጉባኤ ላሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ምክር መስጠት ቢያስፈልገውም መልእክቱን የጀመረውም ሆነ የጨረሰው የሚያበረታቱ ሐሳቦችን በመናገር ነው። (ራእይ 2:25-28) ኢየሱስ የጉባኤዎች ሁሉ ራስ እንደመሆኑ መጠን ምን ያህል ሥልጣን እንዳለው ለማሰብ ሞክር። ለእሱ ስንል ላከናወንናቸው ነገሮች እኛን የማመስገን ግዴታ የለበትም። ያም ቢሆን አድናቆቱን መግለጹ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል። ኢየሱስ በዚህ ረገድ ለጉባኤ ሽማግሌዎች እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትቷል!
አድናቆት እንደሌላቸው አሳይተዋል
11. በዕብራውያን 12:16 ላይ እንደተገለጸው ኤሳው ለቅዱስ ነገሮች ምን አመለካከት ነበረው?
11 የሚያሳዝነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች አድናቆት እንደሌላቸው አሳይተዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኤሳው ይሖዋን በሚወድና በሚያከብር ቤተሰብ ውስጥ ያደገ ቢሆንም ለቅዱስ ነገሮች አድናቆት አልነበረውም። (ዕብራውያን 12:16ን አንብብ።) ኤሳው አመስጋኝ እንዳልሆነ ያሳየው እንዴት ነው? አንድ ጊዜ ለሚበላው ቀይ ወጥ ሲል የብኩርና መብቱን ለታናሽ ወንድሙ ለያዕቆብ ሸጧል። (ዘፍ. 25:30-34) በኋላ ላይ ኤሳው በውሳኔው በጣም ተጸጽቷል። ሆኖም ለነበረው ነገር አድናቆት እንደሌለው ስላሳየ ‘የብኩርና መብቴ ተወሰደብኝ’ ብሎ ማማረር አይችልም ነበር።
12-13. እስራኤላውያን አድናቆት እንደሌላቸው ያሳዩት እንዴት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስከትሏል?
12 እስራኤላውያን አድናቆት እንዲኖራቸው የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች ነበሯቸው። ይሖዋ በግብፅ ላይ አሥር መቅሰፍቶችን በማምጣት ከባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። ከዚያም መላውን የግብፅ ሠራዊት ቀይ ባሕር ውስጥ በማስጠም ከጥፋት ታድጓቸዋል። እስራኤላውያን ለተደረገላቸው ነገር በጣም አመስጋኝ ከመሆናቸው የተነሳ የድል መዝሙር በመዘመር ይሖዋን አወድሰዋል። ታዲያ እንዲህ ያለውን የአድናቆት ስሜት ይዘው ቀጥለው ይሆን?
13 እስራኤላውያን ከዚህ በፊት አጋጥመዋቸው የማያውቁ ፈተናዎች ሲያጋጥሟቸው፣ ይሖዋ ያደረገላቸውን መልካም ነገር በሙሉ ወዲያውኑ ረሱ። በመሆኑም አድናቆት እንደጎደላቸው የሚያሳይ ነገር አደረጉ። (መዝ. 106:7) እንዴት? “መላው የእስራኤል ማኅበረሰብ . . . በሙሴና በአሮን ላይ ማጉረምረም ጀመረ።” እንደ እውነቱ ከሆነ ግን እነዚህ ሰዎች ያጉረመረሙት በይሖዋ ላይ ነበር። (ዘፀ. 16:2, 8) ይሖዋም ሕዝቡ ምስጋና ቢስ በመሆኑ በጣም አዘነ። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ፣ ከኢያሱና ከካሌብ በቀር ያ የእስራኤላውያን ትውልድ በሙሉ በምድረ በዳ እንደሚያልቅ ተናገረ። (ዘኁ. 14:22-24፤ 26:65) ከዚህ በመቀጠል በመጥፎ ምሳሌነታቸው የተጠቀሱ ሰዎች ካሳዩት ምግባር መራቅና ጥሩ ምሳሌ የሆኑ ሰዎችን ፈለግ መከተል የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንመለከታለን።
በዛሬው ጊዜ አድናቆት ማሳየት
14-15. (ሀ) ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን አድናቆት መግለጽ የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) ወላጆች ልጆቻቸው አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?
14 በቤተሰብ ውስጥ። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አድናቆቱን የሚገልጽ ከሆነ መላው ቤተሰብ ይጠቀማል። ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው አድናቆታቸውን የሚገልጹ ከሆነ ዝምድናቸው ይበልጥ ይጠናከራል። በተጨማሪም እርስ በርስ ይቅር መባባል ቀላል ይሆንላቸዋል። ለሚስቱ አድናቆት ያለው ባል፣ ሚስቱ የምትናገራቸውንና የምታደርጋቸውን መልካም ነገሮች አስተውሎ ዝም ከማለት ይልቅ “ተነስቶ ያወድሳታል።” (ምሳሌ 31:10, 28) ጥበበኛ የሆነች ሚስት ደግሞ የምታደንቅለትን ነገሮች ለይታ በመጥቀስ ባሏን ታመሰግነዋለች።
15 ወላጆች፣ ልጆቻችሁ አድናቆታቸውን እንዲገልጹ ማሠልጠን የምትችሉት እንዴት ነው? ልጆቻችሁ የምትናገሩትንና የምታደርጉትን ነገር እንደሚኮርጁ አትርሱ። በመሆኑም ልጆቻችሁ አንድ ነገር ሲያደርጉላችሁ በማመስገን ጥሩ ምሳሌ ተዉላቸው። በተጨማሪም ሰዎች የሆነ ነገር ሲያደርጉላቸው ‘አመሰግናለሁ’ እንዲሉ አስተምሯቸው። የሚያቀርቡት ምስጋና ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበትና የሚናገሯቸው የምስጋና ቃላት በሌሎች ላይ ትልቅ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩ እንዲገነዘቡ እርዷቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ክላዲ የተባለች ወጣት እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ገና በ32 ዓመቷ ሦስት ልጆችን ለብቻዋ የማሳደግ ኃላፊነት ወደቀባት። ልክ 32 ዓመት ሲሆነኝ እናቴ በዚያ ዕድሜዋ ያን ኃላፊነት መቀበሏ ምን ያህል ከብዷት ሊሆን እንደሚችል አሰብኩ። ስለዚህ እኔንም ሆነ ወንድሞቼን ለማሳደግ ስትል የከፈለችውን መሥዋዕትነት በጣም እንደማደንቅ ነገርኳት። እናቴ ያኔ የነገርኳት ነገር ልቧን በጥልቅ እንደነካው፣ በተደጋጋሚ እንደምታስበውና ሁልጊዜ የደስታ ምንጭ እንደሚሆንላት በቅርቡ ነገረችኝ።”
16. አድናቆታችንን መግለጻችን ሌሎችን ሊያበረታታ እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።
16 በጉባኤ ውስጥ። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን አድናቆታችንን መግለጻችን እነሱን ያበረታታቸዋል። ለምሳሌ፣ በጉባኤ ሽማግሌነት የሚያገለግል ሆርሄ የተባለ የ28 ዓመት ወንድም በጠና ታመመ። በመሆኑም ለአንድ ወር ያህል በስብሰባዎች ላይ መገኘት አልቻለም። በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመረ በኋላም እንኳ ክፍል ማቅረብ አይችልም ነበር። ሆርሄ እንዲህ ብሏል፦ “ባለብኝ የአቅም ገደብ የተነሳ የጉባኤ ኃላፊነቶችን መወጣት ባለመቻሌ የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማኝ ነበር። ሆኖም አንድ ቀን ከስብሰባ በኋላ አንድ ወንድም እንዲህ አለኝ፦ ‘ለቤተሰቤ ግሩም ምሳሌ ስለሆንክ ላመሰግንህ እፈልጋለሁ። ባለፉት ዓመታት ያቀረብካቸው ክፍሎች በጣም አበረታተውናል። መንፈሳዊ እድገት እንድናደርግ ረድተውናል።’ በዚህ ጊዜ ልቤ በጥልቅ ስለተነካ ማልቀስ ጀመርኩ። በወቅቱ የሚያስፈልገኝ እንዲህ ያለ ማበረታቻ ነበር።”
17. በቆላስይስ 3:15 መሠረት፣ ይሖዋ ላሳየን ልግስና አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው?
17 ለጋስ ለሆነው አምላካችን። ይሖዋ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አቅርቦልናል። ለምሳሌ በጉባኤ ስብሰባዎቻችን፣ በመጽሔቶቻችንና በድረ ገጾቻችን አማካኝነት ጠቃሚ ትምህርት እናገኛለን። አንድን ንግግር አዳምጠህ፣ ጽሑፍ ላይ የወጣ ርዕስ አንብበህ ወይም ብሮድካስቲንግ ላይ አንድ ቪዲዮ ተመልክተህ ‘የሚያስፈልገኝ ይህ ነበር’ ያልክበት ጊዜ የለም? ታዲያ ይሖዋ ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን መግለጽ የምንችለው እንዴት ነው? (ቆላስይስ 3:15ን አንብብ።) አንዱ መንገድ በጸሎታችን ላይ ይሖዋን ለእነዚህ መልካም ስጦታዎች አዘውትረን ማመስገን ነው።—ያዕ. 1:17
18. ለስብሰባ አዳራሻችን አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
18 ለይሖዋ ያለንን አድናቆት መግለጽ የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ የአምልኮ ቦታዎቻችንን ንጹሕና ሥርዓታማ አድርገን መያዝ ነው። የስብሰባ አዳራሾቻችንን በማጽዳቱና በመጠገኑ ሥራ አዘውትረን መካፈል ይኖርብናል። በተጨማሪም የጉባኤው ንብረት በሆኑ የድምፅና የቪዲዮ መሣሪያዎች ላይ እንዲያገለግሉ የተመደቡ ወንድሞች እነዚህን መሣሪያዎች በጥንቃቄ መያዝ ይኖርባቸዋል። የስብሰባ አዳራሻችንን ጥሩ አድርገን የምንይዝ ከሆነ ለረጅም ጊዜ የሚያገለግለን ከመሆኑም በላይ ያን ያህል ከባድ ጥገና አያስፈልገውም። ይህም በዓለም ዙሪያ ተጨማሪ የስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባትና ለማደስ የሚያገለግል ተጨማሪ ገንዘብ እንዲገኝ ያስችላል።
19. አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ ካጋጠማቸው ሁኔታ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
19 ለእኛ ሲሉ በትጋት ለሚሠሩ። አድናቆታችንን መግለጻችን ሰዎች ለሚገጥማቸው ተፈታታኝ ሁኔታ ያላቸው አመለካከት እንዲቀየር ሊያደርግ ይችላል። እስቲ አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። እነዚህ ባልና ሚስት በአንድ የክረምት ዕለት አገልግሎት ውለው ወደ ማረፊያ ክፍላቸው ሲመለሱ በጣም ዝለው ነበር። ከብርዱ የተነሳ እህት ካፖርቷን እንደለበሰች ተኛች። ከዚያም በማግስቱ ጠዋት በዚህ ሥራ መቀጠል እንደማትችል ለባለቤቷ ነገረችው። በዚያኑ ዕለት ጠዋት ትንሽ ቆየት ብሎ ከቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ደረሳቸው። ደብዳቤው ለእህት የተላከ የምስጋና ደብዳቤ ነበር። በየሳምንቱ ከአንድ ማረፊያ ቦታ ወደ ሌላ ማረፊያ ቦታ መዘዋወር ከባድ ቢሆንም አገልግሎቷን በትጋትና በጽናት እያከናወነች መሆኗ የሚደነቅ ነገር እንደሆነ በደብዳቤው ላይ ተገልጾ ነበር። ባለቤቷ እንዲህ ብሏል፦ “በዚህ የምስጋና ደብዳቤ በጥልቅ በመነካቷ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራችንን ስለማቆም አንስታ አታውቅም። እንዲያውም እኔ ለማቆም ሳስብ እንድቀጥል ብዙ ጊዜ አበረታታኛለች።” እነዚህ ባልና ሚስት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራ ለ40 ዓመት ያህል አገልግለዋል።
20. በየዕለቱ ምን ለማድረግ መጣር ይኖርብናል? ለምንስ?
20 እንግዲያው በየዕለቱ በቃልም ሆነ በተግባር አመስጋኝነታችንን ለመግለጽ ጥረት እናድርግ። ምስጋና ቢስ በሆነው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች በየቀኑ አስጨናቂ ሁኔታዎችን መጋፈጥ ያስፈልጋቸዋል፤ አድናቆታችንን ለመግለጽ ከልብ ተነሳስተን የምንናገራቸውና የምናደርጋቸው ነገሮች ጭንቀታቸውን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል ሊሰጣቸው ይችላል። በተጨማሪም አመስጋኝነታችንን መግለጻችን ከሌሎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ይረዳናል። ከሁሉ በላይ ግን ለጋስና አድናቂ የሆነውን አባታችንን ይሖዋን ለመምሰል ያስችለናል።
መዝሙር 20 ውድ ልጅህን ሰጠኸን
a ይሖዋ፣ ኢየሱስና የሥጋ ደዌ በሽተኛ የነበረው ሳምራዊ አድናቆት በማሳየት ረገድ ምን ምሳሌ ትተውልናል? ይህ ርዕስ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል። እንዲሁም በዚህ ረገድ ምሳሌ የሚሆኑንን ሌሎች ሰዎች ይጠቅሳል። በተጨማሪም አመስጋኝ መሆናችንን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነና እንዲህ ማድረግ የምንችልባቸው አንዳንድ ተግባራዊ መንገዶች የትኞቹ እንደሆኑ ይገልጻል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ አንድን ሰው ወይም አንድን ነገር ማድነቅ ማለት ያ ሰው ወይም ያ ነገር ያለውን ዋጋ መገንዘብ ማለት ነው። ቃሉ ከልብ የመነጨ የአመስጋኝነት ስሜትን ሊያመለክት ይችላል።
c የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ የጻፈው ደብዳቤ ለሮም ጉባኤ ሲነበብ፤ አቂላ፣ ጵርስቅላ፣ ፌበንና ሌሎች ክርስቲያኖች ስማቸው ሲጠቀስ በመስማታቸው ደስ ብሏቸዋል።
d የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እናት ግሩም ምሳሌ ለሆነች አንዲት በዕድሜ የገፋች እህት አድናቆቷን እንድትገልጽ ልጇን ስታሠለጥናት።