የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 7—መሳፍንት
ጸሐፊው:- ሳሙኤል
የተጻፈበት ቦታ:- እስራኤል
ተጽፎ ያለቀው:- በ1100 ከዘአበ ገደማ
የሚሸፍነው ጊዜ:- ከ1450 ገደማ እስከ 1120 ከዘአበ ገደማ
የመሳፍንት መጽሐፍ እስራኤላውያን በአደገኛ ሁኔታ በአጋንንታዊ አምልኮ ከመጠላለፋቸው አንስቶ ይሖዋ በመለኮታዊ ምርጫ የተሾሙ መሳፍንት በማስነሣት ንስሐ የገቡትን ሕዝቦቹን ነፃ በማውጣት እስካሳየው ምህረት ድረስ የተለያዩ ክንውኖችን በሚገልጹ ታሪኮች የተሞላ ነው። ጎቶንያል፣ ናዖድ፣ ሰሜጋር እና ከዚያ በኋላ የተነሱት ሌሎችም መሳፍንት ያደረጓቸው ታላላቅ ሥራዎች እምነት የሚጨምሩ ናቸው። የዕብራውያን መጽሐፍ ጸሐፊ እንዲህ ብሏል:- “ስለ ጌዴዎንና ስለ ባርቅ ስለ ሳምሶንም ስለ ዮፍታሔም . . . እንዳልተርክ ጊዜ ያጥርብኛልና። እነርሱ በእምነት መንግሥታትን ድል ነሱ፣ ጽድቅን አደረጉ . . . ከድካማቸው በረቱ፣ በጦርነት ኃይለኞች ሆኑ የባዕድ ጭፍሮችን አባረሩ።” (ዕብ. 11:32-34) በዚህ ዘመን የነበሩ 12 መሳፍንትን ለመጥቀስ ያህል ቶላ፣ ኢያዕር፣ ኢብጻን፣ ኤሎምና ዓብዶን ይገኙበታል። (በአብዛኛው ሳሙኤል ከእነዚህ መሳፍንት እንደ አንዱ ሆኖ አይቆጠርም።) ይሖዋ መሳፍንቱ በሚያደርጉት ውጊያ የተዋጋላቸው ሲሆን በግል ችሎታዎቻቸው ያከናወኗቸው ነገሮችም የእርሱ መንፈስ እርዳታ የታከለባቸው ነበሩ። ለተከናወነው ነገር ምስጋናውንም ሆነ ክብሩን የሰጡት ለአምላካቸው ነው።
2 ይህ መጽሐፍ በሰፕቱጀንት ትርጉም ውስጥ ክሪታይ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን በዕብራይስጥ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ደግሞ “ዳኞች” የሚል ትርጉም ያለው ሾፌቲም የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ሾፌቲም የሚለው ቃል ሻፋት ከሚለው ግስ የተገኘ ሲሆን የግሱ ትርጉም ‘መዳኘት፣ እውነቱን ማረጋገጥ፣ መቅጣት፣ ማስተዳደር’ የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን ይህም “የሁሉም ዳኛ” የሆነው አምላክ በቲኦክራሲያዊ መንገድ የሾማቸውን የእነዚህን ሰዎች ሥልጣን በሚገባ የሚገልጽ ነው። (ዕብ. 12:23) እነዚህ ይሖዋ አምላክ ሕዝቡን ከባዕድ ኃይሎች ተጽዕኖ ነፃ ለማውጣት በተወሰኑ ወቅቶች ያስነሳቸው ሰዎች ናቸው።
3 የመሳፍንት መጽሐፍ የተጻፈው መቼ ነው? በመጽሐፉ ውስጥ የሚገኙ ሁለት መግለጫዎች ለዚህ ጥያቄ መልሱን እንድናገኝ ይረዱናል። የመጀመሪያው “ኢያቡሳውያንም . . . እስከ ዛሬ ድረስ በኢየሩሳሌም ተቀምጠዋል” የሚለው ነው። (መሳ. 1:21) ዳዊት “አምባይቱን ጽዮንን” ከኢያቡሳውያን የነጠቀው በስምንተኛው ዓመት የግዛት ዘመኑ ወይም በ1070 ከዘአበ በመሆኑ የመሳፍንት መጽሐፍ የተጻፈው ከዚያ በፊት መሆን ይኖርበታል። (2 ሳሙ. 5:4-7) ሁለተኛው መግለጫ ደግሞ አራት ጊዜ ያህል ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን “በዚያ ዘመን በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ አልነበረም” ይላል። (መሳ. 17:6፤ 18:1፤ 19:1፤ 21:25) በመሆኑም ይህ ዘገባ የተጻፈው “በእስራኤል ዘንድ ንጉሥ” በነበረበት ዘመን ማለትም ሳኦል በ1117 ከዘአበ የመጀመሪያው ንጉሥ ከሆነ በኋላ ነው። እንግዲያው መጽሐፉ የተጻፈው በ1117 እና በ1070 ከዘአበ መካከል ባለው ጊዜ ውስጥ መሆን ይኖርበታል።
4 ጸሐፊው ማን ነበር? ለይሖዋ አምላክ ያደረ አገልጋይ እንደነበረ ምንም አያጠያይቅም። ከመሳፍንት ወደ ነገሥታት ዘመን መሸጋገሪያ ላይ ለይሖዋ አምልኮ ዋነኛ ጠበቃ ሆኖ በመቆም ረገድ ብቻውን ጎላ ብሎ የሚጠቀሰው ሰው ሳሙኤል ነው። ሳሙኤል ከታመኑ ነቢያትም የመጀመሪያው ነው። ከዚህ ሁሉ አንጻር የመሳፍንትን ታሪክ የመዘገበው ሳሙኤል መሆኑ ምክንያታዊ ነው።
5 የመሳፍንት መጽሐፍ የሚሸፍነው የጊዜ ርዝማኔ ምን ያህል ነው? ሰሎሞን በአራተኛው የግዛት ዘመኑ ለይሖዋ ቤት መሥራት እንደጀመረ ከሚናገረው ከ1 ነገሥት 6:1 [NW ] በመነሣት ይህንን ጊዜ ማስላት ይቻላል። ‘የእስራኤል ልጆች ከግብጽ የወጡበት አራት መቶ ሰማንያኛ ዓመትም’ ይኸው ነው። (“አራት መቶ ሰማንያኛ” የሚለው መግለጫ የስርቶሽ ቁጥር (ordinal number) በመሆኑ 479 ሙሉ ዓመታት ማለት ነው።) በእነዚህ 479 ዓመታት ውስጥ የተካተቱ በውል የሚታወቁ ታሪኮች ሙሴ በበረሃ እስራኤላውያንን የመራበት 40 ዓመት (ዘዳ. 8:2)፣ ሳኦል በንግሥና የቆየበት 40 ዓመት (ሥራ 13:21)፣ ዳዊት በንግሥና የቆየበት 40 ዓመት (2 ሳሙ. 5:4, 5) እንዲሁም ሰሎሞን የገዛባቸው የመጀመሪያዎቹ 3 ሙሉ ዓመት ናቸው። የእነዚህን ዓመታት ድምር ማለትም 123 ዓመት በ1 ነገሥት 6:1 ላይ ከተጠቀሱት 479 ዓመታት ላይ ስንቀንስ እስራኤላውያን ከነዓን ከገቡበት ጊዜ አንስቶ እስከ ሳኦል የግዛት ዘመን መጀመሪያ ድረስ ያለው 356 ዓመት ይሆናል።a ከኢያሱ ሞት አንስቶ እስከ ሳሙኤል ዘመን ድረስ በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ክንውኖች ከእነዚህ 356 ዓመታት መካከል የ330ዎቹን ዓመታት ጊዜ የሚሸፍኑ ናቸው።
6 የመሳፍንት መጽሐፍ ትክክለኛነት ምንም አያጠራጥርም። አይሁዳውያን ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱ እንደሆነ አድርገው ተቀብለውት ኖረዋል። የዕብራይስጥንም ሆነ የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን የጻፉት ሰዎች እንደ መዝሙር 83:9-18፤ ኢሳይያስ 9:4፤ 10:26 እና ዕብራውያን 11:32-34 ላይ ባሉት ቦታዎች ላይ ከዚሁ መጽሐፍ በመጥቀስ ጽፈዋል። መጽሐፉ እስራኤላውያን ስለነበሩባቸው ድክመቶችና ወደኋላ ስላሉባቸው ጊዜያት በሐቀኝነት የሚያስቀምጥ ሲሆን ወሰን የሌለውን የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትም ጎላ አድርጎ ይገልጻል። የእስራኤል አዳኝ ተደርገው ከፍ ከፍ የተደረጉት ተራ የነበሩት ሰብዓዊ መሳፍንት ሳይሆኑ ይሖዋ አምላክ ነው።
7 ከዚህም በተጨማሪ የአርኪኦሎጂ ግኝቶችም የመሳፍንትን መጽሐፍ እውነተኝነት ይደግፋሉ። ይበልጥ አስገራሚ የሆኑት ደግሞ የከነዓናውያኑ የበኣል ሃይማኖት ምን መልክ እንደነበረው የሚጠቁሙት ናቸው። በ1929 በጥንቷ የከነዓን ከተማ ዑጋሪት (ከቆጵሮስ ደሴት ሰሜን ምስራቅ ጫፍ በተቃራኒ በሶርያ የባሕር ዳርቻ የምትገኘው የዛሬዋ ራስሻምራ ማለት ነው) ቁፋሮ እስከተጀመረበት ጊዜ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚሰጠው መግለጫ ውጭ ስለ በኣል ሃይማኖት የሚታወቀው ነገር በጣም ውስን ነበር። በዚህ ስፍራ የታየው ነገር የበኣል ሃይማኖት ፍቅረ ነዋይ፣ የተጋነነ ብሔራዊ ስሜትንና የፆታ አምልኮ ያቀፈ መሆኑን የሚያንጸባርቅ ነበር። እያንዳንዱ የከነዓናውያን ከተማ የበኣል ማምለኪያ መቅደስና የኮረብታ መስገጃዎች በመባል የሚታወቁ የአምልኮ ቦታዎች እንደነበሩት ከሁኔታዎቹ መረዳት ይቻላል። በእነዚህ የአምልኮ ቦታዎች ውስጥ የበኣል ምስሎች ሳይኖሩ አይቀሩም። እንዲሁም ውጭ ከመሠዊያው አጠገብ የድንጋይ ምሰሶዎች ይገኙ ነበር። ምናልባትም እነዚህ ምሰሶዎች የበኣል መለያ ምልክት የሆነውን የወንድ የፆታ ብልት መልክ የያዙ ሳይሆኑ አይቀሩም። እነዚህ የአምልኮ ስፍራዎች ዘግናኝ በሆነ ሁኔታ መሥዋዕት ተደርገው በቀረቡት ሰዎች ደም የጨቀዩ ነበሩ። እስራኤላውያንም በበኣል አምልኮ በተበከሉ ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን መሥዋዕት አድርገው አቅርበዋል። (ኤር. 32:35) የበኣል እናት የሆነችውን አሼራህን የሚያመለክት የማምለኪያ አፀድ ነበረ። የመራባት ሴት አምላክና የበኣል ሚስት የሆነችው አስታሮት በቤተ መቅደሱ ውስጥ ‘ተለይተው ከተቀመጡ’ ወንዶችና ሴቶች ጋለሞታዎች ጋር በሚፈጸም ልቅ የሆነ የፆታ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዓት አማካኝነት አምልኮ ይቀርብላት ነበር። ይሖዋ አምላክ የበኣል አምልኮንም ሆነ ርኩስ የሆኑ ደጋፊዎቻቸውን ጨርሶ ከምድሪቱ እንዲያጠፉ ማዘዙ ምንም አያስገርምም። “አይንህም አታዝንላቸውም፤ . . . አማልክቶቻቸውንም አታምልካቸው።”—ዘዳ. 7:16b
ጠቃሚ የሆነበት ምክንያት
26 የመሳፍንት መጽሐፍ እንዲሁ ግጭትና ደም መፋሰስ የሞላባቸውን ታሪኮች የሚዘግብ መጽሐፍ ሳይሆን የሕዝቦቹ ታላቅ ነፃ አውጪ የሆነውን ይሖዋን ከፍ ከፍ የሚያደርግ መጽሐፍ ነው። በስሙ የተጠራው ሕዝብ የንስሐ ልብ ይዞ ወደ እርሱ በተመለሰ ጊዜ ዳርቻ የሌለውን ምሕረቱንና ትዕግሥቱን እንዴት እንዳሳያቸው ይገልጻል። የመሳፍንት መጽሐፍ የይሖዋን አምልኮ አጥብቆ የሚደግፍና ከንቱ የሆነውን የአጋንንት አምልኮ፣ እምነትን መቀላቀልንና ብልግና ያለበትን ኅብረት በተመለከተ ጥብቅ የሆነ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ በመሆኑ እጅግ ጠቃሚ ነው። ይሖዋ የበኣልን አምልኮ አጥብቆ ማውገዙ በዘመናችን ካሉት እንደ ፍቅረ ነዋይ፣ የብሔረተኝነት ስሜትና የፆታ ብልግና የመሰሉ ነገሮች ፈጽሞ እንድንርቅ ግድ ሊለን ይገባል።—2:11-18
27 መሳፍንቱ ያሳዩትን ድፍረት የተሞላበት ጠንካራ እምነት መመርመራችን በልባችን ውስጥ ተመሳሳይ እምነት እንድናሳድር ይረዳናል። ዕብራውያን 11:32-34 ላይ ባሉት ቃላት መወደሳቸው ምንም አያስገርምም! ለይሖዋ ስም መቀደስ የተዋጉ ሰዎች ቢሆኑም በራሳቸው ብርታት ያከናወኑት ውጊያ አልነበረም። የኃይላቸው ምንጭ የይሖዋ መንፈስ እንደሆነ ያውቁ ነበር፤ ይህንንም በትህትና አምነው ተቀብለዋል። አምላክ ለባርቅ፣ ለጌዴዎን፣ ለዮፍታሔና ለሌሎችም እንዳደረገው ሁሉ ኃይል እንደሚሰጠን በመተማመን ዛሬም ‘የመንፈስ ሰይፍ’ የሆነውን የአምላክ ቃል ልናነሳ እንችላለን። አዎን፣ ወደ ይሖዋ የምንጸልይና በእርሱ ላይ የምንደገፍ ከሆነ ከባድ የሆኑ እንቅፋቶችን በይሖዋ መንፈስ በማሸነፍ ረገድ ሳምሶን ከነበረው አካላዊ ጥንካሬ የማይተናነስ መንፈሳዊ ብርታት ሊኖረን ይችላል።—ኤፌ. 6:17, 18፤ መሳ. 16:28
28 ነቢዩ ኢሳይያስ ይሖዋ በምድያማውያን ዘመን እንዳደረገው ሁሉ ጠላቶቹ በሕዝቡ ላይ የሚጭኑትን ቀንበር እንደሚያፈራርስ ለማሳየት ከመሳፍንት ሁለት ጊዜ ጠቅሷል። (ኢሳ. 9:4፤ 10:26) ይህ ደግሞ እንደሚከተለው በሚለው ልባዊ ጸሎት የተደመደመውን የዲቦራንና የባርቅን መዝሙር ያስታውሰናል:- “አቤቱ፣ ጠላቶችህ ሁሉ እንዲሁ ይጥፉ፤ ወዳጆችህ ግን ፀሐይ በኃይሉ በወጣ ጊዜ እንደሚሆን፣ እንዲሁ ይሁኑ።” (መሳ. 5:31) እዚህ ላይ ወዳጆች የተባሉት እነማን ናቸው? ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱ እነዚህ የመንግሥቱ ወራሾች መሆናቸውን ሲጠቁም በማቴዎስ 13:43 ላይ “በዚህም ጊዜ ጻድቃን በአባታቸው መንግሥት እንደ ፀሐይ ይበራሉ” በማለት ተመሳሳይ መግለጫ ተጠቅሟል። በዚህ መንገድ የመሳፍንት መጽሐፍ ጻድቅ የሆነው መስፍንና የመንግሥቱ ዘር ኢየሱስ ሥልጣን የሚይዝበትን ጊዜ በተመለከተ አስቀድሞ ተናግሯል። በእርሱም አማካኝነት መዝሙራዊ የአምላክን ጠላቶች በተመለከተ ከዘመረው መዝሙር ጋር በሚስማማ መንገድ ይሖዋ ለስሙ ክብርና ቅድስና ያመጣል። “እንደ ምድያምና እንደ ሲሣራ፣ በቂሶንም ወንዝ እንደ ኢያቢስ አድርግባቸው . . . ስምህም እግዚአብሔር እንደ ሆነ፣ በምድር ሁሉ ላይም አንተ ብቻ ልዑል እንደ ሆንህ ይወቁ።”—መዝ. 83:9, 18፤ መሳ. 5:20, 21
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በሥራ 13:20 ላይ የተጠቀሰው “አራት መቶ ሃምሳ ዓመት” የመሳፍንትን ዘመን ሳይሆን ከዚያ በፊት የነበረውን ጊዜ እንደሚያመለክት ይናገራሉ። እነዚህ ዓመታት ይስሐቅ ከተወለደበት ከ1918 ከዘአበ አንስቶ የተስፋይቱ ምድር በ1467 ከዘአበ እስከተከፋፈለችበት ጊዜ ድረስ ያለውን የሚሸፍኑ ይመስላሉ። (ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል ጥራዝ 1 ገጽ 462) በዕብራውያን 11:32 ላይ የተጠቀሱት መሳፍንት የተዘረዘሩበት ቅደም ተከተል መሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ ካለው ቅደም ተከተል የተለየ ነው። ይሁን እንጂ ይህ በመሳፍንት መጽሐፍ ውስጥ የተዘገቡት ክንውኖች የጊዜ ቅደም ተከተላቸውን አልጠበቁም ለማለት የሚያስችል አይደለም። ሳሙኤል ከዳዊት በኋላ እንዳልመጣ የተረጋገጠ ነው።