ትክክለኛ ሪፖርት እንዲዘጋጅ የበኩልህን አስተዋጽኦ ታደርጋለህን?
1 በብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ውስጥ አኃዞች መሥፈራቸው የተፈጸመውን ሁኔታ በግልጽ ለመረዳት ያስችለናል። ለምሳሌ ያህል ጌዴዎን ምድያማውያንን ድል ያደረገው በ300 ሰዎች ብቻ ነው። (መሳ. 7:7) የይሖዋ መልአክ 185,000 አሦራውያን ወታደሮችን ገድሏል። (2 ነገ. 19:35) በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት 3, 000 የሚያህሉ ሰዎች የተጠመቁ ሲሆን ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የአማኞች ቁጥር ወደ 5, 000 አድጓል። (ሥራ 2:41፤ 4:4) በጥንት ጊዜያት የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች የተሟላና ትክክለኛ የሆነ ዘገባ ለማስፈር ከፍተኛ ጥረት ያደርጉ እንደነበር ከእነዚህ ዘገባዎች መረዳት ይቻላል።
2 በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ድርጅት የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴያችንን በየወሩ ሪፖርት እንድናደርግ ያሳስበናል። ከዚህ ዝግጅት ጋር በታማኝነት መተባበራችን የስብከቱን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ለመከታተል ያስችላል። የመስክ አገልግሎት ሪፖርቶች ትኩረት የሚያሻውን የአገልግሎት ዘርፍ ለይቶ ለማወቅ የሚያስችሉ ከመሆናቸውም በላይ በአንድ የአገልግሎት ክልል ተጨማሪ ሠራተኞች ያስፈልጉ እንደሆነ ሊጠቁሙ ይችላሉ። በጉባኤ ውስጥም ሽማግሌዎች አገልግሎታቸውን ማስፋት የሚችሉትንና እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለይተው እንዲያውቁ ያስችላቸዋል። የመንግሥቱን የስብከት ሥራ እድገት የሚያሳዩ ሪፖርቶች ደግሞ መላውን ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበር ያበረታታሉ። ትክክለኛ ሪፖርት ለማጠናቀር እንዲቻል የበኩልህን ድርሻ እየተወጣህ ነው?
3 በግል ያለብህ ኃላፊነት፦ በወሩ ውስጥ በአገልግሎት ምን ያህል እንዳከናወንክ በወሩ መጨረሻ ላይ ማስታወስ ይቸግርሃል? ይህ ዓይነቱ ችግር ካለብህ ለምን ወደ መስክ አገልግሎት በወጣህ ቁጥር የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ወዲያውኑ አትመዘግብም? አንዳንዶች የቀን መቁጠሪያ ወይም ማስታወሻ ደብተር ይጠቀማሉ። ሌሎች ደግሞ ባዶ የመስክ አገልግሎት ሪፖርት ቅጽ ይይዛሉ። በወሩ መጨረሻ ላይ የአገልግሎት ሪፖርትህን ለመጽሐፍ ጥናትህ የበላይ ተመልካች ሳትዘገይ ስጠው። ወይም ደግሞ በመንግሥት አዳራሹ ለዚሁ ዓላማ ተብሎ በተዘጋጀው ሣጥን ውስጥ ልትከተው ትችላለህ። ሪፖርትህን ለመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካችህ መስጠት ከረሳህ እሱ መጥቶ እስኪጠይቅህ ከመጠበቅ ይልቅ ራስህ ሄደህ ለመስጠት ጥረት አድርግ። የአገልግሎት እንቅስቃሴህን ሳትዘገይ መስጠትህ ለይሖዋ ዝግጅት አክብሮት፣ ሪፖርቱን አሰባስበው ለሚያጠናቅሩት ወንድሞችም ፍቅራዊ አሳቢነት እንዳለህ ያሳያል።—ሉቃስ 16:10
4 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ኃላፊነት፦ የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ንቁና አሳቢ እንደሆነ እረኛ የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑን የአገልግሎት እንቅስቃሴ ትኩረት ሰጥቶ ወሩን በሙሉ ይከታተላል። (ምሳሌ 27:23) እያንዳንዱ አስፋፊ በመስክ አገልግሎት በቋሚነትና በደስታ ጥሩ ተሳትፎ ያደርግ እንደሆነ ይከታተላል። ወሩን ሙሉ በአገልግሎት ያልተሳተፉ ካሉም ሳይዘገይ እርዳታ ያደርግላቸዋል። አብዛኛውን ጊዜ የሚያስፈልጋቸው ጥቂት የማበረታቻ ቃላትና ጠቃሚ የሆነ ምክር ማካፈል ወይም አብረውት በመስክ አገልግሎት እንዲሠሩ መጋበዝ ብቻ ሊሆን ይችላል።
5 የጉባኤው ጸሐፊ የጉባኤውን የተሟላ ሪፖርት ወሩ በገባ እስከ ስድስተኛው ቀን ለቅርንጫፍ ቢሮው መላክ እንዲችል የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች ሁሉም የቡድኑ አባላት የወሩን የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት ማድረጋቸውን ያረጋግጣል። የወሩ መጨረሻ ሲደርስ የአገልግሎት ሪፖርታቸውን የሚሰጡበት ቀን መቅረቡን ለመጽሐፍ ጥናት ቡድኑ ማስታወስና የመጽሐፍ ጥናቱ በሚካሄድበት ቤት ባዶ የአገልግሎት ሪፖርት ቅጾች ማስቀመጡ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። የአገልግሎት እንቅስቃሴያቸውን ሪፖርት ማድረግ የሚዘነጉ ካሉም ተገቢውን ማሳሰቢያና ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይችላል።
6 የመስክ አገልግሎት ሪፖርታችንን በጊዜው መስጠታችን በአገልግሎት የተደረገውን እንቅስቃሴ በትክክል የሚያሳይ ሪፖርት ለማዘጋጀት ያስችላል። በየወሩ የአገልግሎት ሪፖርትህን ሳትዘገይ በመስጠት የበኩልህን አስተዋጽኦ ታደርጋለህ?