የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች ለሌሎች በግል ትኩረት ይሰጣሉ
1 የጉባኤ የመጽሐፍ ጥናት “እያንዳንዱ ግለሰብ ለሚያደርገው መንፈሳዊ እድገት በግሉ የበለጠ ትኩረት እንዲሰጠው” ለማስቻል ተብሎ የተደረገ ዝግጅት ሲሆን “የይሖዋ ፍቅራዊ ደግነትና ለሕዝቡ ያለው አሳቢነት በዚህ ይንጸባረቃል።” (አገልግሎታችን ገጽ 75፤ ኢሳ. 40:11) እንዲህ ዓይነቱን አሳቢነት በማሳየት ረገድ የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
2 በመጽሐፍ ጥናቱ ላይ:- በአንድ የመጽሐፍ ጥናት ቡድን ውስጥ የሚመደቡት አስፋፊዎች ቁጥር አነስተኛ ስለሚሆን የመጽሐፍ ጥናት መሪው ከቡድኑ አባላት ጋር በሚገባ እንዲተዋወቅ ያስችለዋል። (ምሳሌ 27:23) አብዛኛውን ጊዜ ከጥናቱ በፊትና በኋላ ከወንድሞች ጋር ለመቀራረብ የሚያስችሉ አጋጣሚዎች ይኖራሉ። ይህም በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከሞላ ጎደል ከእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ጋር በግል ለመጨዋወት ያስችለዋል። ይህም የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑ አባላት ችግሮች ሲያጋጥሟቸው ወይም ማበረታቻ ሲያስፈልጋቸው ምንም ፍርሃት ሳይሰማቸው ቀርበው እንዲያነጋግሩት ይረዳቸዋል።—ኢሳ. 32:2
3 የመጽሐፍ ጥናት ቡድኑ የበላይ ተመልካች ሁሉም የቡድኑ አባላት በጥናቱ ወቅት እንዲሳተፉ ለማበረታታት ይጥራል። ይህን ማድረግ የሚችልበት አንዱ መንገድ ጥናቱን በደግነትና ረጋ ባለ መንፈስ በመምራት ነው። (1 ተሰ. 2:7, 8) ትንንሽ ልጆችን ጨምሮ ሁሉንም በውይይቱ ውስጥ ለማሳተፍ ጥረት ያደርጋል። አንዳንዶች ሐሳብ ለመስጠት የሚፈሩ ከሆነ አንድ ጥቅስ እንዲያነቡ ወይም በአንድ አንቀጽ ላይ ሐሳብ እንዲሰጡ አስቀድሞ ዝግጅት ሊያደርግ ይችላል። ወይም ደግሞ በራሳቸው አባባል እንዴት ሐሳብ መስጠት እንደሚችሉ ሊያሳያቸው ይችላል።
4 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቹ ረዳት የጉባኤ አገልጋይ ከሆነ በሁለት ወር አንድ ጊዜ ጥናቱን እንዲመራ ዝግጅት ያደርግለታል። ይህም የበላይ ተመልካቹ ረዳቱን ለመመልከትና ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ለማካፈል ያስችለዋል። ይህ ወንድሞች የማስተማር ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ለመርዳት የሚያስችል እንዴት ያለ ግሩም ዝግጅት ነው!—ቲቶ 1:9
5 በመስክ አገልግሎት:- የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካች ካሉት ዋና ዋና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ በወንጌላዊነቱ ሥራ ግንባር ቀደም ሆኖ ማገልገል ነው። (ዘኍ. 27:16, 17) የቡድን ምሥክርነት ለመስጠት የሚያስችሉ ተግባራዊ ዝግጅቶችን የሚያደርግ ከመሆኑም በላይ በቡድኑ ውስጥ ያሉት ሁሉ ከአገልግሎታቸው ደስታ እንዲያገኙ ለመርዳት ይጥራል። (ኤፌ. 4:11, 12) ይህን ጥረቱን ዳር ለማድረስ ከእያንዳንዱ የቡድኑ አባል ጋር ለማገልገል ግብ ያወጣል። እንዲሁም በአንዳንድ የአገልግሎታቸው ዘርፎች መሻሻል ለማድረግ የሚፈልጉ የቡድኑ አባላት ይበልጥ ልምድ ካካበቱ አስፋፊዎች እርዳታ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ከአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ጋር በመተባበር ይሠራል።
6 እንደ አፍቃሪ እረኛ:- የመጽሐፍ ጥናቱ የበላይ ተመልካች ባለባቸው የአቅም ገደብ የተነሳ በስብከቱ ሥራ አነስተኛ ተሳትፎ ለሚያደርጉ አስፋፊዎች በግል አሳቢነት ያሳያል። በእድሜ መግፋት ወይም የአልጋ ቁራኛ በመሆናቸው የተነሳ የአቅም ገደብ ያለባቸው እንዲሁም ባጋጠማቸው ከባድ ሕመም ወይም አደጋ ምክንያት ለጊዜውም ቢሆን እንደ ልብ መንቀሳቀስ የተሳናቸው አስፋፊዎች በወር ውስጥ አንድ ሰዓት ማገልገል ባይችሉ እንኳ እስከ 15 ደቂቃ የሚደርስ የመስክ አገልግሎት ሪፖርት መመለስ እንዲችሉ የተደረገውን ዝግጅት ሊያስታውሳቸው ይችላል። (በዚህ ዝግጅት መጠቀም የሚችሉት እነማን እንደሆኑ የሚወስነው የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ይሆናል።) እንዲሁም በቡድኑ ውስጥ ላሉት አገልግሎት ያቆሙ አስፋፊዎች ትኩረት በመስጠት ከጉባኤው ጋር ተባብረው እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት ጥረት ያደርጋል።—ሉቃስ 15:4-7
7 የመጽሐፍ ጥናት የበላይ ተመልካቾች ለሚያሳዩን ፍቅራዊ አሳቢነት ምንኛ አመስጋኞች ነን! በግለሰብ ደረጃ የሚያሳዩን አሳቢነት ‘በማመን ወደሚገኘው አንድነትና . . . በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እንድንደርስ’ ይረዳናል።—ኤፌ. 4:13 አ.መ.ት