የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ሐምሌ 2016
ሐምሌ 4-10
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 60-68
“ጸሎት ሰሚ የሆነውን ይሖዋን አወድሱ”
ቃልህን መጠበቅ የሚኖርብህ ለምንድን ነው?
እስከ አሁን ከገባነው ቃል ሁሉ ትልቁን ቦታ የሚይዘው ራሳችንን ለአምላክ ስንወስን የገባነው ቃል እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ይህን እርምጃ በመውሰዳችን ይሖዋን ለዘላለም ማገልገል የምንፈልግ መሆናችንን አሳይተናል። የአምላክ ትእዛዛት ከባዶች ባይሆኑም እንኳ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት እየኖርን ፈቃዱን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል። (2 ጢሞቴዎስ 3:12፤ 1 ዮሐንስ 5:3) ይሁን እንጂ አንድ ጊዜ ‘ዕርፉን ከጨበጥንና’ ራሳችንን ወስነን የይሖዋ አገልጋዮችና የልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከሆንን በኋላ ትተናቸው ወደመጣናቸው ወደዚህ ዓለም ነገሮች ፈጽሞ መመለስ አይኖርብንም።—ሉቃስ 9:62
ወደ ይሖዋ ስንጸልይ ያለብንን ድክመት ተዋግተን ለማሸነፍ፣ አንድን ክርስቲያናዊ ባሕርይ ለማዳበር ወይም በአንዱ የቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴ መስክ እድገት ለማድረግ ቃል እንገባ ይሆናል። ታዲያ ይህን የገባነውን ቃል ወደ ፍጻሜው ለማድረስ ምን ይረዳናል?—ከመክብብ 5:2-5 ጋር አወዳድር።
የምንገባው ቃል እውነተኛ ከሆነ የሚመነጨው ከልብና ከአእምሮአችን ነው። ስለዚህ ፍርሃታችንን፣ ምኞታችንንና ድክመታችንን በሐቀኝነት በመግለጽና ልባችንን በጸሎት ለእርሱ በማፍሰስ፣ ለይሖዋ የምንገባውን ቃል ሁሉ የምንፈጽም ለመሆናችን ማረጋገጫ እንስጥ። ስለ ገባነው ቃል መጸለያችን ቃላችንን ለመጠበቅ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠነክረዋል። ለአምላክ የገባነውን ቃል መክፈል እንዳለብን ዕዳ ልንቆጥረው እንችላለን። አንድ ዕዳ በጣም ብዙ ከሆነ ከስር ከስር መከፈል ይኖርበታል። በተመሳሳይም ለይሖዋ የገባነውን ቃል ሁሉ ለመፈጸም ጊዜ ይወስዳል። ይሁን እንጂ የተናገርነውን የምንፈጽም ሰዎች መሆናችንን እናሳይ፤ እርሱም በምላሹ ይባርከናል።
ስለ ገባነው ቃል አዘውትረን ምናልባትም በየቀኑ በመጸለይ የገባነውን ቃል በቁምነገር እንደምንመለከተው ልናሳይ እንችላለን። እንዲህ ማድረጋችን የሰማዩ አባታችን ከልባችን ቃል መግባታችንን እንዲያይ ያደርገዋል። በተጨማሪም ጸሎት የገባነው ቃል ዘወትር ትዝ እንዲለን ያደርጋል። በዚህ ረገድ ዳዊት ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። “አምላክ ሆይ፣ ልመናዬን ስማ፣ ጸሎቴንም አድምጥ። . . . እንዲሁ ለስምህ ለዘላለም እዘምራለሁ ስእለቴን ሁልጊዜ እፈጽም ዘንድ” በማለት በመዝሙር ይሖዋን ተማጽኗል።—መዝሙር 61:1, 8
(መዝሙር 62:8) ሰዎች ሆይ፣ ሁልጊዜ በእሱ ታመኑ። ልባችሁን በፊቱ አፍስሱ። አምላክ መጠጊያችን ነው። (ሴላ)
ምንጊዜም በይሖዋ ታመኑ!
በአምላክ መታመን ከእሱ ጋር ላለን ግንኙነት ወሳኝ ነው
6 አንድ አስጨናቂ ችግር ሲያጋጥምህ ጉዳዩን ለይሖዋ በጸሎት ከነገርከው በኋላ የምትችለውን እንዳደረግህና የቀረውን እሱ እንደሚፈታው በመተማመን ውስጣዊ ሰላም ማግኘት ትችላለህ? እንዴታ! (መዝሙር 62:8ን እና 1 ጴጥሮስ 5:7ን አንብብ።) በይሖዋ መታመንን መማር ከእሱ ጋር ያለህን ዝምድና ለማጠናከር አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ ነው። ይሁንና የሚያስፈልግህን ነገር ይሖዋ እንደሚሰጥህ መተማመን ከባድ ሊሆን ይችላል። ለምን? ይሖዋ ለጸሎታችን ወዲያውኑ ምላሽ የማይሰጥባቸው ጊዜያት ስላሉ ነው።—መዝ. 13:1, 2፤ 74:10፤ 89:46፤ 90:13፤ ዕን. 1:2
7 ይሖዋ አንዳንድ ጊዜ ለምንጠይቀው ነገር አፋጣኝ ምላሽ የማይሰጠን ለምንድን ነው? ይሖዋ ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና በአባትና በልጅ መካከል ካለው ግንኙነት ጋር እንዳመሳሰለው አስታውስ። (መዝ. 103:13) አንድ ልጅ፣ የሚጠይቀውን ነገር ሁሉ ወላጆቹ እንዲያደርጉለት ወይም ፍላጎቱን በሙሉ ወዲያውኑ እንዲያሟሉለት መጠበቁ ተገቢ አይሆንም። ልጁ አንዳንድ ነገሮችን የሚጠይቀው በስሜታዊነት በመሆኑ ብዙም ሳይቆይ ይረሳዋል። የሚጠይቃቸውን ሌሎች ነገሮች ለማድረግ ደግሞ ተገቢው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ያስፈልግ ይሆናል። አንዳንድ ጊዜ ልጁ የሚፈልገው ነገር እሱንም ሆነ ከእሱ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሌሎች ሰዎች የሚጎዳ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ወላጆች ልጁ የጠየቀውን ነገር ሁሉ ካደረጉለት ግንኙነታቸው የጌታና የባሪያ ዓይነት ይሆንና ልጁ አዛዥ ሆኖ ቁጭ ይላል። በተመሳሳይም ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት የተወሰነ ጊዜ እንዲያልፍ የሚያደርገው ለእኛ ጥቅም ሲል ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ጥበበኛ ፈጣሪያችን፣ አፍቃሪ ጌታችንና ሰማያዊ አባታችን እንደ መሆኑ መጠን ይህን የማድረግ መብት አለው። የጠየቅነውን ሁሉ ወዲያውኑ የሚያደርግልን ከሆነ በመካከላችን ያለው ግንኙነት ትክክለኛውን አካሄድ የጠበቀ አይሆንም።—ከኢሳይያስ 29:16 እና 45:9 ጋር አወዳድር።
8 ሌላው ምክንያት ደግሞ ይሖዋ አቅማችን ምን ያህል እንደሆነ በደንብ የሚያውቅ መሆኑ ነው። (መዝ. 103:14) ስለዚህ የሚያጋጥመንን ፈተና በራሳችን ኃይል እንድንወጣው አይጠብቅብንም፤ ከዚህ ይልቅ ልክ እንደ አባት እርዳታ ይሰጠናል። እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ፈተናውን መቋቋም የማንችልበት ደረጃ ላይ እንደደረስን ይሰማን ይሆናል። ያም ቢሆን ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ከሚችሉት በላይ እንዲፈተኑ ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። እንዲያውም “መውጫ መንገዱን” ያዘጋጅልናል። (1 ቆሮንቶስ 10:13ን አንብብ።) እንግዲያው ይሖዋ መሸከም የምንችለው ምን ያህል እንደሆነ በትክክል እንደሚያውቅ ለመተማመን የሚያበቃ ምክንያት አለን።
9 እርዳታ ለማግኘት ከጸለይን በኋላ ወዲያውኑ ምላሽ እንዳላገኘን ከተሰማን፣ እኛን ለመርዳት መቼ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት የሚያውቀውን አምላካችንን በትዕግሥት እንጠብቅ። ይሖዋ እኛን ለመርዳት በጣም ስለሚጓጓ እሱም ቢሆን መታገሥ እንደሚያስፈልገው እናስታውስ። “ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።”—ኢሳ. 30:18
(መዝሙር 65:1, 2) አምላክ ሆይ፣ በጽዮን ውዳሴ ይቀርብልሃል፤ የተሳልነውን ለአንተ እንሰጣለን። 2 ጸሎት ሰሚ የሆንከው አምላክ ሆይ፣ ሁሉም ዓይነት ሰው ወደ አንተ ይመጣል።
ከይሖዋ ጋር ያለህ ወዳጅነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?
13 እስቲ ይህን አስብ፦ ይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ የሚያቀርቡለትን ጸሎት ሲመልስ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ተመልክቷል። እሱም በምድር ላይ አገልግሎቱን ሲያከናውን በሰማይ ላለው አባቱ ስሜቱን አውጥቶ ለመግለጽ በጸሎት ተጠቅሟል። እንዲያውም በአንድ ወቅት ሌሊቱን ሙሉ ሲጸልይ አድሯል፤ ታዲያ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንደሚሰማው እርግጠኛ ባይሆን ኖሮ እንዲህ ያደርግ ነበር? (ሉቃስ 6:12፤ 22:40-46) ጸሎት አእምሮን ከማረጋጋት ያለፈ ጥቅም እንደሌለው ቢሰማው ኖሮ ደቀ መዛሙርቱን እንዲጸልዩ ያስተምራቸው ነበር? ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ጸሎት፣ ከይሖዋ ጋር የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ የሚያስችል መንገድ እንደሆነ ኢየሱስ ያውቅ ነበር። በአንድ ወቅት ኢየሱስ “አባት ሆይ፣ ስለሰማኸኝ አመሰግንሃለሁ። እውነት ነው፣ ሁልጊዜ እንደምትሰማኝ አውቃለሁ” በማለት ጸልዮአል። እኛም ይሖዋ “ጸሎት ሰሚ” አምላክ እንደሆነ መተማመን እንችላለን።—ዮሐ. 11:41, 42፤ መዝ. 65:2
14 ስትጸልይ የምትፈልገውን ነገር ለይተህ የምትጠቅስ ከሆነ ይሖዋ የሚሰጥህ ምላሽ በግልጽ የሚታይ ባይሆንም እንኳ አንተ ለጸሎትህ መልስ እንዳገኘህ በቀላሉ ታስተውላለህ። ጸሎትህ ምላሽ ማግኘቱ ደግሞ ይሖዋ ይበልጥ እውን እንዲሆንልህ ያደርጋል። በተጨማሪም የሚያሳስቡህን ነገሮች ለይሖዋ ግልጥልጥ አድርገህ በነገርከው መጠን እሱ ወደ አንተ ይበልጥ እየቀረበ ይሄዳል።
እናንት ወጣቶች ይሖዋን ለማገልገል ያላችሁ ፍላጎት እያደገ ይሂድ
ጸሎት ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እንዲጠነክር የሚረዳችሁ እንዴት ነው?
10 ይሖዋን በሙሉ ልባችሁ ለማገልገል ያላችሁን ፍላጎት ማሳደግ የምትችሉበት ሁለተኛው መንገድ ጸሎት ነው። መዝሙር 65:2 “ጸሎትን የምትሰማ ሆይ፤ የሰው ልጆች ሁሉ ወደ አንተ ይመጣሉ” ይላል። (መዝ. 65:2) እስራኤላውያን የአምላክ የቃል ኪዳን ሕዝቦች በነበሩበት ጊዜም እንኳ ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚመጡ የባዕድ አገር ሰዎች ወደ እሱ መጸለይ ይችሉ ነበር። (1 ነገ. 8:41, 42) አምላክ ፈጽሞ አያዳላም። የአምላክን ትእዛዛት የሚጠብቁ ሰዎች፣ የሚያቀርቡትን ጸሎት ይሖዋ እንደሚሰማላቸው እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። (ምሳሌ 15:8) መጽሐፍ ቅዱስ “የሰው ልጆች ሁሉ” ሲል እናንተን ወጣቶችንም እንደሚጨምር ጥርጥር የለውም።
it-2-E 668 አን. 2
ጸሎት
አምላክ የሚሰማቸው ጸሎቶች። ‘ሁሉም ዓይነት ሰው ጸሎት ሰሚ ወደሆነው’ ወደ ይሖዋ አምላክ ሊመጣ ይችላል። (መዝ. 65:2፤ ሥራ 15:17) እስራኤላውያን የአምላክ ‘የግል ንብረት’ ይኸውም የቃል ኪዳን ሕዝቦቹ በነበሩበት ጊዜም እንኳ የባዕድ አገር ሰዎች ወደ ይሖዋ መጸለይ ይችሉ ነበር፤ እነዚህ የባዕድ አገር ሰዎች ይህን ያደርጉ የነበረው እስራኤላውያን አምላክ የሚጠቀምባቸው ሕዝብ እንደሆኑ፣ በኢየሩሳሌም የሚገኘው ቤተ መቅደስ ደግሞ አምላክ የመረጠው የአምልኮ ስፍራ እንደሆነ በመገንዘብ ነበር። (ዘዳ. 9:29፤ 2 ዜና 6:32, 33፤ ከኢሳ. 19:22 ጋር አወዳድር።) ከጊዜ በኋላ ግን በክርስቶስ ሞት አማካኝነት በአይሁዳውያንና በአሕዛብ መካከል የነበረው ልዩነት ለዘለቄታው ተወገደ። (ኤፌ. 2:11-16) ጴጥሮስ፣ ጣሊያናዊ ወደሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት በሄደበት ወቅት “አምላክ እንደማያዳላ . . . ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት” እንዳለው ተረዳ። (ሥራ 10:34, 35) ዋናው ነገር የግለሰቡ ልብ እንዲሁም ከልቡ ተነሳስቶ የሚያደርገው ነገር ነው። (መዝ. 119:145፤ ሰቆ. 3:41) የአምላክን ትእዛዛት የሚፈጽሙና “በፊቱ ደስ የሚያሰኙትን ነገሮች” የሚያደርጉ ሰዎች፣ ጸሎታቸው ወደ አምላክ “ጆሮ” እንደሚደርስ እርግጠኞች መሆን ይችላሉ።—1 ዮሐ. 3:22፤ መዝ. 10:17፤ ምሳሌ 15:8፤ 1 ጴጥ. 3:12
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
63:3፦ የአምላክ ፍቅራዊ ደግነት ወይም ‘ምሕረት ከሕይወት ይበልጣል።’ ምክንያቱም ፍቅራዊ ደግነቱን ካላገኘን ሕይወታችን ትርጉም ያጣና ዓላማ ቢስ ይሆናል። ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት የጥበብ መንገድ ነው።
(መዝሙር 68:18) ወደ ላይ ወጣህ፤ ምርኮኞችን ወሰድክ፤ አምላካችን ያህ ሆይ፣ በመካከላቸው ትኖር ዘንድ ሰዎችን፣ አዎ እልኸኛ የሆኑትን ጭምር እንደ ስጦታ አድርገህ ወሰድክ።
የመዝሙር ሁለተኛ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
68:18 NW—‘ስጦታ ሆነው የተሰጡት ወንዶች’ እነማን ነበሩ? እነዚህ ወንዶች እስራኤላውያን ተስፋይቱን ምድር በወረሩበት ወቅት ከማረኳቸው ሰዎች መካከል ነበሩ። በኋላ ላይም እነዚህ ሰዎች ሌዋውያንን በሥራ እንዲያግዙ ተመድበዋል።—ዕዝራ 8:20
ሐምሌ 11-17
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 69-73
“የይሖዋ ሕዝቦች ለእውነተኛው አምልኮ ይቀናሉ”
ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ
2 በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ እውነተኛ ክርስቲያኖች፣ የመንግሥቱን ምሥራች ከመስበክና ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ከማድረግ የበለጠ አጣዳፊ ሥራ የለም። (ማቴ. 24:14፤ 28:19, 20) ደቀ መዝሙሩ ማርቆስ፣ ኢየሱስ የተናገረውን በመጥቀስ ይህ ሥራ “አስቀድሞ” ይኸውም መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት መሠራት እንዳለበት ጽፏል። (ማር. 13:10) ይህ መሆኑም ተገቢ ነው። ኢየሱስ “አዝመራው ብዙ ነው፤ ሠራተኞቹ ግን ጥቂት ናቸው” ብሏል። አዝመራ ወቅቱ ከማለፉ በፊት መሰብሰብ አለበት።—ማቴ. 9:37
3 የስብከቱ ሥራ ትልቅ ቦታ የምንሰጠው ነገር ስለሆነ አቅማችን በፈቀደ መጠን ጊዜያችንን፣ ኃይላችንንና ትኩረታችንን በዚህ ሥራ ላይ ማዋል ይኖርብናል። በርካታ ወንድሞችና እህቶች እንዲህ እያደረጉ በመሆኑ ሊመሰገኑ ይገባል። አንዳንዶች አቅኚዎች ወይም ሚስዮናውያን አሊያም ቤቴላውያን ሆነው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ አኗኗራቸውን ቀለል አድርገዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው በሥራ የተጠመደ ነው። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ሲሉ ብዙ መሥዋዕቶችን ከፍለው ይሆናል፤ እንዲሁም በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ያም ሆኖ ይሖዋ በእጅጉ ባርኳቸዋል። እኛም በዚህ እንደሰታለን። (ሉቃስ 18:28-30ን አንብብ።) ሌሎች ደግሞ የሙሉ ጊዜ አዋጅ ነጋሪዎች መሆን ባይችሉም በዚህ ሕይወት አድን ሥራ የቻሉትን ያህል ጊዜ ለማሳለፍ ይጥራሉ፤ ይህ ሥራ ልጆቻችን እንዲድኑ መርዳትንም ይጨምራል።—ዘዳ. 6:6, 7
4 ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ብዙውን ጊዜ ሰዎች የጥድፊያ ስሜት የሚታይባቸው አንድ ነገር የጊዜ ገደብ ወይም የሚያበቃበት ጊዜ ሲኖረው ነው። የምንኖረው በመጨረሻው ጊዜ ውስጥ ሲሆን ይህን የሚያረጋግጡ በርካታ ቅዱስ ጽሑፋዊና ታሪካዊ ማስረጃዎች አሉ። (ማቴ. 24:3, 33፤ 2 ጢሞ. 3:1-5) ያም ቢሆን መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ የሚያውቅ ማንም ሰው የለም። ኢየሱስ “የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት” ምን እንደሆነ በገለጸበት ወቅት “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 24:36) በመሆኑም አንዳንዶች በተለይ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በጥድፊያ ስሜት ሲያገለግሉ የቆዩ ከሆኑ ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ ይህን ስሜት ይዘው መቀጠል አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል። (ምሳሌ 13:12) አንተስ አንዳንድ ጊዜ እንዲህ ይሰማሃል? ይሖዋ አምላክና ኢየሱስ ክርስቶስ በዛሬው ጊዜ እንድናከናውነው ለሚፈልጉት ሥራ የጥድፊያ ስሜት እንዲኖረንና ይህን ስሜት ይዘን እንድንቀጥል ምን ሊረዳን ይችላል?
ምሳሌያችን የሆነውን ኢየሱስን ተመልከቱ
5 ለአምላክ በሚያቀርቡት አገልግሎት የጥድፊያ ስሜት ካሳዩት ሰዎች ሁሉ የላቀ ምሳሌ የሚሆነን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ይህን እንዲያደርግ ካነሳሱት ምክንያቶች አንዱ በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሊያከናውነው የሚገባ በጣም ብዙ ሥራ የነበረው መሆኑ ነው። ከእውነተኛው አምልኮ ጋር በተያያዘ ባከናወነው ነገር ኢየሱስን ማንም ሊወዳደረው አይችልም። የአባቱን ስምና ዓላማ አሳውቋል፣ የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል፣ የሃይማኖት መሪዎችን ግብዝነትና የሐሰት ትምህርቶችን አጋልጧል እንዲሁም የይሖዋን ሉዓላዊነት በመደገፍ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ጸንቷል። ኢየሱስ በሄደበት ቦታ ሁሉ ራሱን ሳይቆጥብ ሰዎችን አስተምሯል፣ ረድቷል እንዲሁም ከበሽታቸው ፈውሷል። (ማቴ. 9:35) ማንም ሰው ቢሆን በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ያከናወነውን ያህል አከናውኖ አያውቅም። ኢየሱስ በዚህ ሥራ ላይ አቅሙ የሚፈቅደውን ሁሉ አድርጓል።—ዮሐ. 18:37
6 ኢየሱስ፣ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በአገልግሎቱ በትጋት እንዲካፈል ያነሳሳው ምንድን ነው? በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ሥራውን ለማከናወን ምን ያህል ጊዜ እንዳለው ከዳንኤል ትንቢት መረዳት ይችል ነበር። (ዳን. 9:27) በትንቢቱ መሠረት ‘በሱባዔው እኩሌታ’ ላይ ወይም ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ምድራዊ አገልግሎቱ ያበቃል። ኢየሱስ በ33 ዓ.ም. በጸደይ ወቅት በክብር ወደ ኢየሩሳሌም ከገባ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ “የሰው ልጅ ክብር የሚያገኝበት ሰዓት ደርሷል” በማለት ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 12:23) ኢየሱስ የሚሞትበት ጊዜ እንደተቃረበ ቢያውቅም ይህ ሕይወቱን እንዲቆጣጠረው አልፈቀደም፤ ተግቶ እንዲሠራ ያነሳሳው ዋነኛ ምክንያት ይህ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ማንኛውንም አጋጣሚ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸምና ለሰዎች ፍቅር ለማሳየት ተጠቅሞበታል። ይህ ፍቅር ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ እንዲሁም እነሱን አሠልጥኖ በስብከቱ ሥራ ላይ እንዲካፈሉ ለመላክ አነሳስቶታል። ይህን ያደረገው እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ እንዲያውም ከእሱ የበለጠ ሥራ እንዲያከናውኑ ስለሚፈልግ ነው።—ዮሐንስ 14:12ን አንብብ።
7 በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸመ አንድ ክንውን ምን ያህል ቅንዓት እንደነበረው በግልጽ ያሳያል። ሁኔታው የተፈጸመው አገልግሎቱን በጀመረበት አካባቢ ይኸውም በ30 ዓ.ም. በዋለው የፋሲካ በዓል ወቅት ነበር። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲመጡ በቤተ መቅደሱ ውስጥ “ከብቶችን፣ በጎችንና ርግቦችን የሚሸጡ ሰዎችን እንዲሁም በዚያ የተቀመጡ ገንዘብ መንዛሪዎችን” ተመለከቱ። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ ምን አደረገ? ደቀ መዛሙርቱስ የወሰደውን እርምጃ ሲመለከቱ ምን ተሰማቸው?—ዮሐንስ 2:13-17ን አንብብ።
8 ኢየሱስ በዚህ ወቅት ያደረገውና የተናገረው ነገር ደቀ መዛሙርቱ፣ በዳዊት መዝሙሮች ውስጥ የሚገኘውን “የቤትህ ቅናት በላችኝ” የሚለውን ትንቢት እንዲያስታውሱ አደረጋቸው። (መዝ. 69:9) ደቀ መዛሙርቱ ይህን ትንቢት ያስታወሱት ለምን ነበር? ምክንያቱም ኢየሱስ ያከናወነው ነገር ለአደጋ የሚያጋልጠው በመሆኑ ነው። በቤተ መቅደሱ በሚካሄደው ስግብግብነት የሚንጸባረቅበት ንግድ ላይ የቤተ መቅደሱ ባለሥልጣናት ይኸውም የካህናቱ፣ የጸሐፍቱና የሌሎች ሰዎች እጅ ነበረበት። በመሆኑም ኢየሱስ፣ ምግባረ ብልሹነት የሚንጸባረቅበትን ይህን ሥራቸውን በማጋለጡና በማስተጓጎሉ በወቅቱ ከነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች ጋር ጠላትነት ፈጥሯል። በእርግጥም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ‘ለአምላክ ቤት’ ወይም ለእውነተኛው አምልኮ ‘ቅንዓት’ እንዳለው የሚናገረውን ጥቅስ ማስታወሳቸው ትክክል ነበር። ይሁንና ቅንዓት ምንድን ነው? ከጥድፊያ ስሜት ይለያል?
የጥድፊያ ስሜት ከቅንዓት የሚለየው እንዴት ነው?
9 አንድ መዝገበ ቃላት “ቅንዓት” የሚለውን ቃል “አንድ ግብ ላይ ለመድረስ ጉጉትና ጽኑ ፍላጎት ማሳደር” በማለት ፈትቶታል፤ እንዲሁም ኃይለኛ ስሜትና ግለት ከሚሉት ቃላት ጋር ተቀራራቢ ትርጉም እንዳለው ይገልጻል። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲያከናውን እንዲህ ዓይነት ስሜት እንደነበረው ጥርጥር የለውም። የ1980 ትርጉም ከላይ ያለውን ጥቅስ “ለቤትህ ያለኝ መንፈሳዊ ቅንኣት በውስጤ እንደ እሳት ይነድዳል” በማለት አስቀምጦታል። “ቅንዓት” የሚለው ቃል በአንዳንድ የምሥራቃውያን አገሮች ቋንቋ የሚገለጸው በሁለት ቃላት ነው፤ የእነዚህ ቃላት ቀጥተኛ ትርጉም “የጋለ ልብ” የሚል ሐሳብ የሚያስተላልፍ ሲሆን ይህም ልብ በእሳት እየነደደ እንዳለ አድርጎ የሚገልጽ ምሳሌያዊ አባባል ነው። በእርግጥም ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያደረገውን ነገር ሲመለከቱ ዳዊት የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳቸው አያስገርምም። ይሁንና ኢየሱስ ልቡ በእሳት እየነደደ ያለ ያህል እንዲህ ያለ እርምጃ እንዲወስድ ያነሳሳው ወይም የገፋፋው ምንድን ነው?
10 በዳዊት መዝሙር ላይ የሚገኘው ‘ቅንዓት’ የሚለው ቃል ከአንድ የዕብራይስጥ ቃል የተገኘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች የሚገኘው ይህ ቃል ጠለቅ ያለ ትርጉም አለው። (ዘፀአት 20:5ን፤ ዘፀአት 34:14ን እና ኢያሱ 24:19ን አንብብ።) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ይህን ቃል አስመልክቶ እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ቃል ብዙውን ጊዜ የሚሠራበት ከጋብቻ ጋር በተያያዘ ነው። . . . አንድ ባል ወይም አንዲት ሚስት የትዳር ጓደኛቸው የእነሱ ብቻ እንዲሆን የመጠበቅ መብት እንዳላቸው ሁሉ አምላክም የእሱ የሆኑት እሱን ብቻ እንዲያመልኩት የመጠየቅ መብት አለው፤ ይህን መብቱን ሌላ እንዲጋራው አይፈቅድም።” በመሆኑም ቅንዓት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት፣ ለአንድ ነገር ኃይለኛ ስሜትና ግለት ከማሳየት የበለጠ ነገርን ለማመልከት ነው፤ ለምሳሌ በርካታ የስፖርት ደጋፊዎች ለሚወዱት ስፖርት ከሚኖራቸው ስሜት የተለየ ነው። ከላይ ባለው ጥቅስ ላይ ዳዊት ቅንዓትን የገለጸው በአዎንታዊ ጎኑ ነው፤ ይኸውም ተቀናቃኝን ወይም ነቀፌታን በዝምታ አለማየትን፣ ጥሩ ስም እንዳይጎድፍ ለመከላከል አሊያም የጎደፈውን ስም ለማስተካከል የሚያነሳሳ ኃይለኛ ስሜትን ለማመልከት ነው።
11 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት፣ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያደረገውን ነገር ዳዊት ከተናገረው ሐሳብ ጋር ማያያዛቸው ትክክል ነበር። ኢየሱስ በትጋት ይሠራ የነበረው ሥራውን ለማከናወን ያለው ጊዜ የተወሰነ በመሆኑ ብቻ ሳይሆን ለአባቱ ስምና ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ስለነበረው ጭምር ነው። በአምላክ ስም ላይ የተከመረውን ነቀፋና ስድብ ሲመለከት በቅንዓት ተነሳስቶ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ኢየሱስ፣ ተራው ሕዝብ በሃይማኖት መሪዎች ሲጨቆንና ሲበዘበዝ በተመለከተበት ወቅት ቅንዓት ስላደረበት ሰዎቹ እረፍት እንዲያገኙ የሚያስችል እርምጃ ወስዷል፤ እንዲሁም ጨቋኝ የሆኑትን የሃይማኖት መሪዎች ጠንከር ባሉ ቃላት አውግዟቸዋል።—ማቴ. 9:36፤ 23:2, 4, 27, 28, 33
ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት ይኑራችሁ
12 በዛሬው ጊዜም አምላክን እናመልካለን የሚሉ ሰዎች አመለካከትና ድርጊት በኢየሱስ ዘመን ከነበረው ጋር ይመሳሰላል፤ እንዲያውም ይብሳል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ለተከታዮቹ ባስተማረው ጸሎት መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ስለ አምላክ ስም እንደነበር አስታውስ፤ “ስምህ ይቀደስ” ብለው እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:9) በዛሬው ጊዜ የሃይማኖት መሪዎች በተለይም የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት ሰዎች የአምላክን ስም እንዲያውቁና ስሙን እንዲቀድሱት ወይም እንዲያከብሩት ሲያስተምሩ አይተን እናውቃለን? ከዚህ በተቃራኒ እንደ ሥላሴ፣ ገሃነመ እሳትና የሰው ነፍስ አትሞትም እንደሚሉ ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን በማስተማር አምላክን ሚስጥራዊ፣ ለመረዳት የሚከብድ፣ ጨካኝ አልፎ ተርፎም በሰዎች ሥቃይ የሚደሰት እንደሆነ አድርገው ያቀርቡታል። በተጨማሪም አሳፋሪ የሆነው ምግባራቸውና ግብዝነታቸው በአምላክ ላይ ስድብ እንዲከመር አድርጓል። (ሮም 2:21-24ን አንብብ።) ከዚህም በላይ የአምላክ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም፤ ሌላው ቀርቶ ከመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቻቸው ውስጥ እንኳ አውጥተውታል። ይህ ድርጊታቸው ሰዎች ወደ አምላክ እንዳይቀርቡና ከእሱ ጋር የግል ዝምድና እንዳይመሠርቱ እንቅፋት ሆኗል።—ያዕ. 4:7, 8
13 ኢየሱስ፣ ተከታዮቹን “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ብለው ስለ አምላክ መንግሥት መምጣት እንዲጸልዩም አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:10) የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖታዊ መሪዎች ይህን ጸሎት አዘውትረው የሚደግሙት ቢሆንም ሰዎች ፖለቲካዊና ሌሎች ሰብዓዊ ተቋማትን እንዲደግፉ ያበረታታሉ። በተጨማሪም ስለ አምላክ መንግሥት የሚሰብኩና ምሥክርነት ለመስጠት የሚጥሩ ሰዎችን ያንቋሽሻሉ። በዚህም ምክንያት ክርስቲያኖች እንደሆኑ ከሚናገሩት ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአምላክ መንግሥት ማመን ይቅርና ስለዚህ መንግሥት ሲናገሩ እንኳ አይሰሙም።
14 ኢየሱስ ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ዮሐ. 17:17) ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት ደግሞ ለሕዝቡ መንፈሳዊ ምግብ የሚያዘጋጅ “ታማኝና ልባም ባሪያ” እንደሚሾም ጠቁሟል። (ማቴ. 24:45) የሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት የአምላክ ቃል መጋቢዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፤ ሆኖም ጌታ በአደራ የሰጣቸውን ሥራ በታማኝነት ተወጥተዋል? በጭራሽ! በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሐሳብ ተረት ወይም አፈ ታሪክ እንደሆነ የመናገር አዝማሚያ ይታይባቸዋል። ቀሳውስቱ ለመንጎቻቸው መንፈሳዊ ምግብ በማቅረብ መጽናኛና እውቀት እንዲያገኙ ከማድረግ ይልቅ ሰብዓዊ ፍልስፍናን በማስተማር የአማኞቻቸውን ጆሮ ይኮረኩራሉ። ከዚህም በተጨማሪ ሰዎች የሚፈልጉትን ዓይነት የሥነ ምግባር መመሪያዎች ለማስተማር ሲሉ የአምላክን መሥፈርቶች አለሳልሰው ያቀርባሉ።—2 ጢሞ. 4:3, 4
15 ይህ ሁሉ የሚደረገው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው አምላክ ስም በመሆኑ በርካታ ቅን ሰዎች ግራ ተጋብተዋል ወይም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጨርሶ እምነት አጥተዋል። እንዲሁም በሰይጣንና ክፉ በሆነው ሥርዓቱ ወጥመድ ውስጥ ወድቀዋል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎችን ነጋ ጠባ ስትሰማና ስትመለከት ምን ይሰማሃል? የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን በአምላክ ስም ላይ የሚከመረውን ስድብና ነቀፋ ስትሰማ ይህን ለማስተካከል ልብህ አይገፋፋህም? ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ሲታለሉና መጠቀሚያ ሲደረጉ ስትመለከት እነዚህን የተጨቆኑ ሰዎች ለማጽናናት አትነሳሳም? ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩት ሰዎች “እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው” ሲመለከት በጣም ያዘነ ከመሆኑም በላይ ‘ብዙ ነገር አስተምሯቸዋል።’ (ማቴ. 9:36፤ ማር. 6:34) እኛም እንደ ኢየሱስ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዲኖረን የሚገፋፉን ብዙ ምክንያቶች አሉን።
16 በአገልግሎታችን ቀናተኞች ስንሆን ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ጢሞቴዎስ 2:3, 4 ላይ የተናገረው ሐሳብ ጥልቅ ትርጉም ይኖረዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) አገልግሎታችንን በትጋት የምናከናውነው በመጨረሻው ጊዜ ውስጥ እንዳለን ስለምናውቅ ብቻ ሳይሆን እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ ፈቃድ መሆኑን ስለምንገነዘብም ነው። አምላክ፣ ሰዎች እውነትን አግኝተው እሱን እንዲያመልኩትና እንዲያገለግሉት በዚህም በረከት እንዲያጭዱ ይፈልጋል። አገልግሎታችንን በትጋት እንድናከናውን በዋነኝነት የሚያነሳሳን የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን ማወቃችን ሳይሆን የአምላክን ስም ለማክበርና ሰዎች ፈቃዱን እንዲያውቁ ለመርዳት ያለን ፍላጎት ነው። እንዲሁም ለእውነተኛው አምልኮ ያለን ቅንዓት ነው።—1 ጢሞ. 4:16
17 ይሖዋ ሕዝቦች በመሆናችን አምላክ ለሰው ልጆችና ለምድር ያለውን ዓላማ በተመለከተ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ተባርከናል። በተጨማሪም ሰዎች ደስታና ለወደፊቱ ጊዜ የተረጋገጠ ተስፋ እንዲኖራቸው መርዳት እንችላለን። የሰይጣን ሥርዓት ሲጠፋ ጥበቃ ማግኘት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ልናስተምራቸው እንችላለን። (2 ተሰ. 1:7-9) የይሖዋ ቀን የዘገየ በመምሰሉ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ለእውነተኛው አምልኮ ቅንዓት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት ጊዜ በመኖሩ መደሰት ይኖርብናል። (ሚክ. 7:7፤ ዕን. 2:3) እንዲህ ያለ ቅንዓት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ በሚቀጥለው የጥናት ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
(መዝሙር 71:17, 18) አምላክ ሆይ፣ ከልጅነቴ ጀምሮ አስተምረኸኛል፤ እኔም እስካሁን ድረስ ድንቅ ሥራዎችህን አስታውቃለሁ። 18 አምላክ ሆይ፣ ሳረጅና ስሸብትም እንኳ አትጣለኝ። ለቀጣዩ ትውልድ ስለ ብርታትህ፣ ገና ለሚመጡትም ሁሉ ስለ ኃያልነትህ ልናገር።
የጭንቀት ጊዜ ከመምጣቱ በፊት ይሖዋን ማገልገል
4 የብዙ ዓመት ተሞክሮ ያለህ ሰው ከሆንክ ‘አሁን ያለኝን ጉልበትና ጥንካሬ እንዴት ብጠቀምበት ይሻላል?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ በጣም አስፈላጊ ነው። ተሞክሮ ያካበትክ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ሌሎች የሌሏቸው አጋጣሚዎች አሉህ። ከይሖዋ የተማርከውን ነገር ለወጣቶች ማካፈል ትችላለህ። አምላክን ስታገለግል ያገኘሃቸውን ተሞክሮዎች በመናገር ሌሎችን ማበረታታት ትችላለህ። ንጉሥ ዳዊት፣ አምላክ እንዲህ ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንዲሰጠው ጸልዮአል። “አምላክ ሆይ፤ አንተ ከልጅነቴ ጀምረህ አስተማርኸኝ፤ . . . አምላክ ሆይ፤ ሳረጅና ስሸብትም አትተወኝ፤ ክንድህን ለመጭው ትውልድ፣ ኀይልህን ኋላ ለሚነሣ ሕዝብ ሁሉ፣ እስከምገልጽ ድረስ” ሲል ጽፏል።—መዝ. 71:17, 18
5 በረጅም ዓመታት ውስጥ ያካበትከውን ጥበብ ለሌሎች ማካፈል የምትችለው እንዴት ነው? አምላክን የሚያገለግሉ ወጣቶችን ቤትህ በመጋበዝ የሚያንጽ ጊዜ ማሳለፍ ትችል ይሆን? ከእነሱ ጋር አገልግሎት በመውጣት ይሖዋን ማገልገል ምን ያህል እንደሚያስደስትህ እንዲያዩ ማድረግ ትችላለህ? ከበርካታ ዘመናት በፊት የኖረው ኤሊሁ “ዕድሜ ይናገራል፤ ረጅም ዘመን ጥበብን ያስተምራል” ብሏል። (ኢዮብ 32:7) ሐዋርያው ጳውሎስ ተሞክሮ ያካበቱ ክርስቲያን ሴቶች በቃልም ሆነ በተግባር ሌሎችን እንዲያበረታቱ አሳስቧቸዋል። “አረጋውያን ሴቶች . . . ጥሩ የሆነውን ነገር የሚያስተምሩ ይሁኑ” በማለት ጽፏል።—ቲቶ 2:3
ሌሎችን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?
6 ተሞክሮ ያካበትክ ክርስቲያን ከሆንክ ሌሎችን ለመርዳት ልታደርገው የምትችለው ብዙ ነገር አለ። በዕድሜ ከበሰልክ በኋላ የተማርካቸውን ነገሮች እስቲ ቆም ብለህ አስብ፤ ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከዛሬ 30 ወይም 40 ዓመት በፊት የማታውቃቸው ነገሮች ሊሆኑ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚቻል ታውቃለህ። የሌሎችን ልብ በሚነካ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዴት ማስተማር እንደሚቻል ተምረሃል። ሽማግሌ ከሆንክ ደግሞ የተሳሳተ እርምጃ የወሰዱ ወንድሞችን እንዴት መርዳት እንዳለብህ ታውቃለህ። (ገላ. 6:1) የጉባኤ ሥራዎችን፣ በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ያሉትን የተለያዩ የሥራ ምድቦች ወይም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታን እንዴት በበላይነት መከታተል እንደሚቻል የቀሰምከው ልምድ ይኖር ይሆናል። ዶክተሮች ያለ ደም ሕክምና መስጠት የሚችሉባቸውን መንገዶች እንዲጠቀሙ እንዴት ማግባባት እንደሚቻል ታውቅ ይሆናል። እውነትን ያወቅከው በቅርቡ ቢሆንም እንኳ ጠቃሚ የሕይወት ተሞክሮ አለህ። ለምሳሌ ያህል፣ ልጆች ያሳደግክ ከሆንክ ከፍተኛ እውቀትና ችሎታ አካብተሃል ማለት ነው። በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች፣ ወንድሞችንና እህቶችን በማስተማር፣ በመምራትና በማበረታታት የይሖዋን ሕዝቦች መጥቀም የሚችሉበት ከፍተኛ አቅም አላቸው።—ኢዮብ 12:12ን አንብብ።
7 ያለህን ችሎታ በተሟላ መንገድ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው? የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዴት ማስጀመርና መምራት እንደሚቻል ለወጣቶች ማሳየት ትችላለህ። እህት ከሆንሽ፣ ወጣት እናቶች ትናንሽ ልጆቻቸውን እየተንከባከቡ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎቻቸውን እንዴት ማከናወን እንደሚችሉ ምክር መለገስ ትችያለሽ? ወንድም ከሆንክ ደግሞ ወጣት ወንድሞች ንግግራቸውን በግለት እንዲያቀርቡና ይበልጥ ውጤታማ የምሥራቹ ሰባኪዎች እንዲሆኑ ማሠልጠን ትችላለህ? ደግሞስ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችንና እህቶችን ስትጠይቅ በመንፈሳዊ የምታበረታታቸው እንዴት እንደሆነ ልታሳያቸው ትችላለህ? የቀድሞውን ያህል አካላዊ ብርታት ባይኖርህም እንኳ ወጣቶችን ማሠልጠን የምትችልበት ግሩም አጋጣሚ አለህ። የአምላክ ቃል “የጎልማሶች ክብር ብርታታቸው፣ የሽማግሌዎችም ሞገስ ሽበታቸው ነው” ይላል።—ምሳሌ 20:29
ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ማገልገል
8 ሐዋርያው ጳውሎስ በኋለኛው የሕይወት ዘመኑ ባለው አቅም ሁሉ አምላክን አገልግሏል። በ61 ዓ.ም. ገደማ ሮም ውስጥ ከእስር በተፈታበት ጊዜ በሚስዮናዊነት አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት ብዙ ደክሟል፤ በመሆኑም ሮም ውስጥ ተደላድሎ ተቀምጦ መስበክ ይችል ነበር። (2 ቆሮ. 11:23-27) በዚያ ትልቅ ከተማ የሚኖሩት ወንድሞች ጳውሎስ እዚያው ተቀምጦ ቢረዳቸው እንደሚደሰቱ ምንም ጥርጥር የለውም። ጳውሎስ ግን ከፍተኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሌሎች አገሮች እንዳሉ ተገንዝቦ ነበር። ከጢሞቴዎስና ከቲቶ ጋር ሆኖ ሚስዮናዊ አገልግሎቱን በመቀጠል ወደ ኤፌሶን ከዚያም ወደ ቀርጤስ ተጓዘ፤ ወደ መቄዶንያም ሳይሄድ አልቀረም። (1 ጢሞ. 1:3፤ ቲቶ 1:5) ወደ ስፔን ስለመሄዱ የምናውቀው ነገር ባይኖርም ወደዚያ የመሄድ ዕቅድ እንደነበረው ተናግሯል።—ሮም 15:24, 28
9 ሐዋርያው ጴጥሮስ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ በተዛወረበት ወቅት ዕድሜው ከ50 ዓመት በላይ ሳይሆን አይቀርም። ይህን ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በዕድሜ የኢየሱስ እኩያ ከሆነ ወይም ኢየሱስን ትንሽ ይበልጠው ከነበረ በ49 ዓ.ም. ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ኢየሩሳሌም ውስጥ በተገናኘበት ጊዜ 50 ዓመት ገደማ ሊሆነው ይችላል። (ሥራ 15:7) ይህ ስብሰባ ከተካሄደ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ በባቢሎን ለመኖር ወደዚያ ሄዷል፤ እንዲህ ያደረገው በዚያ አካባቢ ለሚኖሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አይሁዳውያን ለመስበክ እንደሆነ ግልጽ ነው። (ገላ. 2:9) በ62 ዓ.ም. ገደማ በመንፈስ መሪነት የመጀመሪያውን ደብዳቤ የጻፈው በባቢሎን በነበረበት ጊዜ ነው። (1 ጴጥ. 5:13) ውጭ አገር መኖር ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል፤ ይሁንና ጴጥሮስ በዕድሜ የገፋ መሆኑ ይሖዋን በተሟላ መንገድ ማገልገል የሚያስገኘውን ደስታ እንዲያሳጣው አልፈቀደም።
10 በዛሬው ጊዜ በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኙና ከዚያ በላይ የሆናቸው ብዙ ክርስቲያኖች ያሉበት ሁኔታ እንደተለወጠና ከቀድሞው ለየት ባለ መንገድ ይሖዋን ማገልገል እንደሚችሉ ተገንዝበዋል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታ ተዛውረዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ሮበርት እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኔና ባለቤቴ በ50ዎቹ ዕድሜ አጋማሽ ላይ በነበርንበት ጊዜ ልንጠቀምባቸው የምንችል በርካታ አጋጣሚዎች እንዳሉን ተገነዘብን። ያለን አንድ ልጅ ራሱን ችሎ መኖር ጀምሯል፤ የእኛን እርዳታ የሚሹ በዕድሜ የገፉ ወላጆች የሉንም፤ በዚህ ላይ ደግሞ አነስተኛ ውርስ አግኝተን ነበር። መኖሪያ ቤታችንን ብንሸጥ የቤቱን ዕዳ መክፈልና የጡረታ አበል መቀበል እስክጀምር ድረስ በዚህ ገንዘብ መተዳደር እንደምንችል ተገነዘብኩ። በቦሊቪያ መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት የሚፈልጉ ብዙ ሰዎች እንዳሉና ኑሮ ርካሽ እንደሆነ ሰማን። በመሆኑም ወደዚያ ለመዛወር ወሰንን። አዲሱን መኖሪያችንን መልመድ ቀላል ሆኖ አላገኘነውም። ሁሉም ነገር በሰሜን አሜሪካ ከለመድነው በጣም የተለየ ሆኖብን ነበር። ሆኖም ያደረግነው ጥረት በሚገባ ክሶናል።”
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
ድህነትን ማጥፋት የሚችለው ማን ነው?
አምላክ ልጁን ኢየሱስን በመላው የሰው ዘር ላይ እንዲገዛ ሾሞታል። (መዝሙር 2:4-8) ኢየሱስ ድሆችን ከችግራቸው የሚገላግላቸው ከመሆኑም ሌላ ጭቆናንና ዓመፅን ያጠፋል።—መዝሙር 72:8, 12-14ን አንብብ።
እርዳታ ለማግኘት የሚጮኹትን የሚታደገው ማነው?
ሁሉም ነገር የተትረፈረፈበት አዲስ ዓለም ከፊታችን ይጠብቀናል
19 የታላቁ ሰለሞን አገዛዝ በሚያመጣው የአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ የሚኖሩ ጻድቅ ሰዎች የሚያገኙትን የወደፊት ሕይወት እንደገና በአእምሮህ ለመሳል ሞክር። ‘በምድሪቱ ላይ እህል እንደሚትረፈረፍና በተራሮችም ዐናት ላይ እንደሚወዛወዝ’ ተስፋ ተሰጥቶናል። (መዝ. 72:16) እህል በተራራ ዐናት ላይ መብቀሉ የተለመደ ነገር ስላልሆነ ይህ አባባል ምድር ምን ያህል የተትረፈረፈ ምርት እንደምትሰጥ ያጎላል። ምድር በምትሰጠው ምርት የተነሳ በሰለሞን የግዛት ዘመን የተትረፈረፈ ምርት ይገኝባት እንደነበረው “እንደ ሊባኖስ” ትሆናለች። እስቲ አስበው! በዚያ ጊዜ የምግብ እጥረት አይኖርም፣ ማንም ሰው በተመጣጠነ ምግብ እጦት አይሠቃይም እንዲሁም ማንም ሰው አይራብም! ለሁሉም ሰው “ታላቅ የምግብ ግብዣ” ይደረጋል።—ኢሳ. 25:6-8፤ 35:1, 2
20 ለዚህ ሁሉ በረከት መመስገን ያለበት ማነው? በዋነኝነት ሊመሰገን የሚገባው ዘላለማዊ ንጉሥና የአጽናፈ ዓለም ገዥ የሆነው ይሖዋ አምላክ ነው። ሁላችንም በምሳሌያዊ ሁኔታ ድምፃችንን አስተባብረን በዚህ ማራኪና አስደሳች መዝሙር መደምደሚያ ላይ የሚገኘውን የሚከተለውን ሐሳብ እንዘምራለን፦ “[ንጉሥ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ስም] ለዘላለም ጸንቶ ይኑር፤ ዝናው ፀሓይ የምትኖረውን ዘመን ያህል ይዝለቅ፤ ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ይባረኩ፤ ሕዝቡ ሁሉ ቡሩክ ነህ ይበለው። ብቻውን ድንቅ ነገር የሚያደርግ፣ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ይባረክ። ክቡር ስሙ ለዘላለም ይባረክ፤ ምድርም ሁሉ በክብሩ ይሞላ። አሜን፤ አሜን።”—መዝ. 72:17-19
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
የመሲሑን መምጣት ይጠባበቁ ነበር
17 መሲሑ ያለ ምክንያት ይጠላል። (መዝ. 69:4) ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ እንደተናገረ ጽፏል፦ “ሌላ ማንም ያላደረገውን ነገር [በሕዝቡ መካከል] ባላደርግ ኖሮ ኃጢአት ባልሆነባቸው ነበር፤ አሁን ግን አይተዋል፤ እንዲሁም እኔንም ሆነ አባቴን ጠልተዋል። ይሁን እንጂ ይህ የሆነው ‘ያለ ምክንያት ጠሉኝ’ ተብሎ በሕጋቸው የተጻፈው ቃል እንዲፈጸም ነው።” (ዮሐ. 15:24, 25) ብዙውን ጊዜ ‘ሕግ’ የሚለው ቃል ቅዱሳን መጻሕፍትን በሙሉ ያመለክታል። (ዮሐ. 10:34፤ 12:34) የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ በተለይ በአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ይጠላ እንደነበር ያሳያሉ። ከዚህም በተጨማሪ ክርስቶስ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ዓለም እናንተን የሚጠላበት ምንም ምክንያት የለውም፤ እኔ ግን ሥራው ክፉ እንደሆነ ስለምመሠክርበት ይጠላኛል።”—ዮሐ. 7:7
መሲሑን አገኙት!
15 ለመሲሑ ሆምጣጤና ሐሞት ይሰጡታል። መዝሙራዊው “ምግቤን ከሐሞት ቀላቀሉ፤ ለጥማቴም ሆምጣጤ ሰጡኝ” ብሏል። (መዝ. 69:21) ማቴዎስ እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ሐሞት የተቀላቀለበት ወይን ጠጅ እንዲጠጣ [ለኢየሱስ] ሰጡት፤ እሱ ግን ከቀመሰው በኋላ ሊጠጣው አልፈለገም።” በኋላም “ከመካከላቸው አንዱ ሮጦ በመሄድ ሰፍነግ ወስዶ የኮመጠጠ ወይን ጠጅ ውስጥ ከነከረ በኋላ በመቃ ላይ አድርጎ እንዲጠጣ ሰጠው።”—ማቴ. 27:34, 48
(መዝሙር 73:24) በምክርህ ትመራኛለህ፤ በኋላም ክብር ታጎናጽፈኛለህ።
የአምላክን ክብር እንዳታገኙ ምንም ነገር እንቅፋት አይሁንባችሁ
3 መዝሙራዊው፣ ይሖዋ ቀኝ እጁን ይዞ እንደሚመራውና ወደ ክብር እንደሚያስገባው ያለውን እምነት ገልጿል። (መዝሙር 73:23, 24ን አንብብ።) ይሖዋ ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው? ይሖዋ ትሑት አገልጋዮቹን ወደ ክብር የሚያስገባቸው በተለያዩ መንገዶች ነው። ፈቃዱን እንዲገነዘቡ በማድረግ ይባርካቸዋል። (1 ቆሮ. 2:7) እንዲሁም ቃሉን የሚሰሙና እሱን የሚታዘዙ ሰዎችን ከእሱ ጋር የቅርብ ዝምድና እንዲመሠርቱ በመፍቀድ ያከብራቸዋል።—ያዕ. 4:8
4 ከዚህም ሌላ ይሖዋ፣ እጅግ ውድ ሀብት የሆነውን ክርስቲያናዊ አገልግሎት ለአገልጋዮቹ በአደራ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 4:1, 7) ይህ አገልግሎት ደግሞ ክብር እንዲያገኙ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ፣ በዚህ የአገልግሎት መብት ተጠቅመው እሱን ለሚያወድሱና ሌሎችን ለሚረዱ ሁሉ “የሚያከብሩኝን አከብራለሁ” የሚል ቃል ገብቷል። (1 ሳሙ. 2:30) እንዲህ ያሉ ሰዎች በይሖዋም ሆነ በሌሎች የአምላክ አገልጋዮች ዘንድ ጥሩ ስም ስለሚያተርፉ ክብር ያገኛሉ።—ምሳሌ 11:16፤ 22:1
ሐምሌ 18-24
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 74-78
‘ይሖዋ ያከናወናቸውን ሥራዎች አስታውሱ’
በይሖዋ ጽኑ ፍቅር ላይ አሰላስሉ
3 ቀደም ብለው የተጠቀሱት ግለሰቦች በፈተና ወቅት አምላክ ከእነሱ ጋር እንደነበረ እርግጠኞች ናቸው። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ ከጎናችን እንደሆነ መተማመን እንችላለን። (መዝ. 118:6, 7) የአምላክ ፍቅር (1) ከፍጥረት ሥራዎቹ፣ (2) በመንፈስ መሪነት ከተጻፈው ቃሉ፣ (3) ከጸሎት እና (4) ከቤዛው ጋር በተያያዘ እንዴት እንደተገለጸ በዚህ የጥናት ርዕስ ላይ ይብራራል። ይሖዋ ባከናወናቸው መልካም ሥራዎች ላይ ማሰላሰላችን እሱ ለሚያሳየን ጽኑ ፍቅር ያለንን አድናቆት እንደሚጨምረው ግልጽ ነው።—መዝሙር 77:11, 12ን አንብብ።
በይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ላይ አሰላስሉ
4 ይሖዋ የፈጠራቸውን ነገሮች በማየት ለእኛ ጽኑ ፍቅር እንዳለው ማወቅ እንችላለን? አዎ እንችላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለመፍጠር መነሳሳቱ በራሱ ፍቅሩን ይገልጻል። (ሮም 1:20) ምድርን ሲፈጥር ሕይወት ያለምንም ስጋት እንዲቀጥል የሚያስችል ሥነ ምህዳር እንዲኖራት አድርጓል። ያም ቢሆን በሕይወት ከመኖር ባለፈ እንድናገኝ የሚፈልገው ነገር አለ። ለምሳሌ በሕይወት ለመቀጠል መብላት ይኖርብናል። ይሖዋ ምድርን ሲፈጥር ለጤና ተስማሚ የሆነ ምግብ ለማዘጋጀት የሚያስችሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ዕፀዋትን እንድታፈራ አድርጓታል። ሌላው ቀርቶ ምግብ መመገብ በራሱ አስደሳችና አርኪ እንዲሆንልን አድርጓል! (መክ. 9:7) ካትሪን የተባለች እህት፣ በተለይ መንፈስን በሚያድሰው የካናዳ የጸደይ ወቅት የፍጥረት ሥራዎችን መመልከት በጣም ያስደስታታል። ሕይወት ያላቸው ነገሮች የሚያደርጉት ለውጥ ምን ያህል እንደሚያስደንቃት ተናግራለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “አበቦች ጊዜያቸውን ጠብቀው ማበባቸው፣ ወፎች ከፈለሱበት መመለስ መቻላቸው እንዲሁም ትንሿ ሃሚንግበርድ እንኳ ኩሽናዬ መስኮት ላይ ወዳስቀመጥኩላት ጎጆዋ ተመልሳ መምጣቷ ያስገርማል። ይሖዋ እነዚህን ሁሉ አስደሳች ነገሮች የሰጠን ቢወደን ነው።” አፍቃሪው ሰማያዊ አባታችን በፍጥረት ሥራዎቹ ይደሰታል፤ እኛም በእነዚህ ነገሮች እንድንደሰት ይፈልጋል።—ሥራ 14:16, 17
ለአምላክ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
ስለ አምላክ እውቀት ማካበት ብቻውን ለእርሱ ፍቅር እንዲያድርብን አያደርገንም። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የአምላክ አገልጋዮች በተሞክሮ እንዳዩት አንድ ሰው ስለ አምላክ ባሕርያት ይበልጥ ባወቀ መጠን ለእርሱ ያለው እውነተኛ ፍቅር ይጨምራል። አምላክ የሚወደውን፣ የሚጠላውንና ከሰዎች የሚፈልገውን ነገር ሲገነዘብ ፍቅሩም ይበልጥ እየጠነከረ ይሄዳል።
ይሖዋ በፍቅር ተነሳስቶ ቃሉን መጽሐፍ ቅዱስን የሰጠን ሲሆን በቃሉ አማካኝነት ራሱን ገልጦልናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር ስለወሰዳቸው እርምጃዎች ለማወቅ ያስችለናል። ከምንወደው ሰው የተላከ ደብዳቤ በጣም እንደሚያስደስተን ሁሉ ስለ ይሖዋ ባሕርያት አዳዲስ ነገሮችን ከመጽሐፍ ቅዱስ በተማርን መጠን እንደሰታለን።
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎታችን ከሚያጋጥመን ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው አንድ ሰው ስለ አምላክ ማወቁ ብቻ ለእርሱ ፍቅር እንዲያድርበት ላያደርገው ይችላል። ኢየሱስ በዘመኑ ለነበሩ አንዳንድ አድናቆት የጎደላቸው አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸዋል:- “በእነርሱ የዘላለም ሕይወትን የምታገኙ እየመሰላችሁ፣ መጻሕፍትን ትመረምራላችሁ፤ . . . ነገር ግን እናንተን ዐውቃችኋለሁ፤ የእግዚአብሔርም ፍቅር በልባችሁ እንደሌለ ዐውቃለሁ።” (ዮሐንስ 5:39, 42) አንዳንዶች ስለ ይሖዋ ፍቅራዊ ዝግጅቶች ለዓመታት ቢማሩም ለእርሱ ፍቅር ሳያዳብሩ ይቀራሉ። ምክንያቱ ምንድን ነው? የተማሩትን ነገር ቆም ብለው ስለማያገናዝቡት ነው። በአንጻሩ ደግሞ ከእኛ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠኑ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለአምላክ ያላቸው ፍቅር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ ሲሄድ ተመልክተዋል። ይህ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ልክ እንደ እኛ እነርሱም የአሳፍን አርዓያ በመከተላቸው ነው። እንዴት?
በአድናቆት ስሜት አሰላስሉ
አሳፍ ለይሖዋ ፍቅር ለማዳበር ልባዊ ፍላጎት ነበረው። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ከልቤም ጋር ተጫወትሁ፤ . . . የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፤ የጥንት ታምራትህን በእርግጥ አስታውሳለሁ፤ ሥራህን ሁሉ አሰላስላለሁ፤ ድንቅ ሥራህን ሁሉ አውጠነጥናለሁ።” (መዝሙር 77:6, 11, 12) የአንድ ሰው ልብ ለአምላክ ባለው ፍቅር የሚሞላው መዝሙራዊው እንዳደረገው በይሖዋ ሥራዎች ላይ ሲያሰላስል ነው።
ከዚህም በላይ ይሖዋን ስናገለግል ያገኘናቸውን ተሞክሮዎች ማስታወስም ከእርሱ ጋር ያለንን ዝምድና ለማጠናከር ያስችለናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ከአምላክ ጋር “አብረን የምንሠራ” እንደሆንን ተናግሯል፤ በሥራ ባልደረቦች መካከል ለየት ያለ ወዳጅነት ይፈጠራል። (1ቆሮንቶስ 3:9) ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ የምንናገራቸውን ቃላትና የምናደርጋቸውን ነገሮች ይሖዋ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል፣ ልቡንም ደስ ያሰኙታል። (ምሳሌ 27:11) አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሞን ይሖዋ እንዲረዳን ስንጠይቀውና መመሪያ ሲሰጠን ከእኛ ጋር እንደሆነ ስለሚሰማን ለእርሱ ያለን ፍቅር ጥልቅ እየሆነ ይሄዳል።
ጓደኛሞች አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ ወዳጅነታቸው ይበልጥ ይጠነክራል። በተመሳሳይም ራሳችንን ለእርሱ የወሰንበትን ምክንያት ለይሖዋ ስንነግረው ለእርሱ ያለን ፍቅር እየጠነከረ ይሄዳል። እንዲሁም “አንተም ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህና በፍጹም ኀይልህ ውደድ” በሚሉት የኢየሱስ ቃላት ላይ ማሰላሰል እንችላለን። (ማርቆስ 12:30) ይሖዋን በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን፣ በፍጹም ሐሳባችንና በፍጹም ኃይላችን መውደዳችንን ለመቀጠል ምን ማድረግ እንችላለን?
ይሖዋን በፍጹም ልባችን መውደድ
መጽሐፍ ቅዱስ ውስጣዊ ማንነታችንን ለመግለጽ በምሳሌያዊው ልብ የሚጠቀም ሲሆን ይህም ፍላጎታችንን፣ ዝንባሌያችንንና ስሜታችንን ያመለክታል። ስለዚህ ይሖዋን በፍጹም ልባችን እንወደዋለን ሲባል ከምንም ነገር በላይ እርሱን ለማስደሰት እንፈልጋለን ማለት ነው። (መዝሙር 86:11) በእርሱ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸውን ባሕርያት በማንጸባረቅ እንደዚህ ዓይነት ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። ‘ክፉ የሆነውን ሁሉ በመጸየፍና በጎ ከሆነው ነገር ጋር በመቆራኘት’ አምላክን ለመምሰል እንጥራለን።—ሮሜ 12:9
ለአምላክ ያለን ፍቅር ለማንኛውም ነገር ያለንን ስሜት ይነካል። ለምሳሌ፣ ሥራችንን በጣም እንወደውና እንረካበት ይሆናል፤ ሆኖም ልባችን ሙሉ በሙሉ ያረፈው በሥራችን ላይ መሆን ይኖርበታል? በፍጹም። ይሖዋን በፍጹም ልባችን ስለምንወደው የመጀመሪያውን ቦታ የምንሰጠው እርሱን ለማገልገል ነው። በተመሳሳይም ወላጆቻችንን፣ የትዳር ጓደኛችንን እንዲሁም አሠሪያችንን ማስደሰት እንፈልጋለን፤ ሆኖም በዋነኝነት ይሖዋን ለማስደሰት የምንጥር ከሆነ ከልባችን እንደምንወደው እናሳያለን። ደግሞም በልባችን ውስጥ ዋነኛውን ቦታ መያዝ የሚገባው እርሱ ነው።—ማቴዎስ 6:24፤ 10:37
ይሖዋን በፍጹም ነፍሳችን መውደድ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ነፍስ” የሚለው ቃል ሁለንተናችንን እንዲሁም ሕይወታችንን ያመለክታል። በመሆኑም ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን መውደድ ሲባል ሕይወታችንን እርሱን ለማወደስና ለእርሱ ያለንን ፍቅር ለመግለጽ እንጠቀምበታለን ማለት ነው።
“እነሆ፣ አምላካችን ይህ ነው”
6 ብዙውን ጊዜ በበጋ ወራት ወደ ውጭ ስትወጣ የፀሐይዋ ሙቀት እንደሚሰማህ የታወቀ ነው። በተዘዋዋሪ መንገድ እየተሰማህ ያለው ይሖዋ ለመፍጠር የተጠቀመበት ኃይል ነው። ፀሐይ ምን ያህል ኃይል አላት? መካከለኛው የፀሐይ ክፍል 15 ሚልዮን ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ የሚያክል ሙቀት አለው። ከፀሐይ መካከለኛ ክፍል ላይ ከምስር የሚያንስ ቅራፊ ወስደን ወደ ምድራችን ማምጣት ብንችል ወደዚች ቅንጣት 140 ኪሎ ሜትር ከሚያህል ርቀት በላይ መቅረብ አይቻልም! ፀሐይ በየሴኮንዱ ከብዙ መቶ ሚልዮን የኑክሌር ቦምብ ፍንዳታ ጋር የሚመጣጠን ኃይል ታመነጫለች። ያም ሆኖ ምድራችን ከፍተኛ ኃይል ከምታመነጨው ከዚህች የኑክሌር ምድጃ በትክክለኛው ርቀት ላይ ትገኛለች። ፀሐይ ወደ ምድር በጣም ብትቀርብ ኖሮ በምድር ላይ ያለው ውኃ ተንኖ ያልቅ ነበር፤ በአንጻሩ ደግሞ በጣም ብትርቅ ውኃው ወደ በረዶነት ይቀየር ነበር። ሁለቱም ክስተቶች ምድርን ሕይወት አልባ ያደርጓታል።
7 ሰዎች ሕልውናቸው በፀሐይ ላይ የተመካ ቢሆንም ፀሐይ ስለምትሰጠው ጥቅም የሚያስቡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። በመሆኑም ከፀሐይ ሊያገኙ የሚችሉትን ትምህርት ሳያገኙ ይቀራሉ። መዝሙር 74:16 “አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ” በማለት ስለ ይሖዋ ይናገራል። አዎን፣ ፀሐይ “ሰማይንና ምድርን” የፈጠረውን የይሖዋን ክብር ትናገራለች። (መዝሙር 146:6) ሆኖም ይሖዋ እጅግ ከፍተኛ ኃይል እንዳለው ትምህርት ሊሰጡን ከሚችሉት በርካታ ፍጥረታት መካከል ፀሐይ አንዷ ብቻ ናት። ይሖዋ ለመፍጠር ስለሚጠቀምበት ኃይል ይበልጥ እያወቅን በሄድን መጠን ለእርሱ ያለን አክብሮትም የዚያኑ ያህል እያደገ ይሄዳል።
(መዝሙር 75:4-7) ጉራቸውን ለሚነዙት “ጉራ አትንዙ” እላለሁ፤ ክፉዎቹንም እንዲህ እላለሁ፦ “ኃይላችሁን ከፍ ከፍ አታድርጉ። 5 ኃይላችሁን ወደ ላይ ከፍ አታድርጉ፤ ወይም በትዕቢት አትናገሩ። 6 ክብር ከምሥራቅም ሆነ ከምዕራብ ወይም ከደቡብ አይመጣምና። 7 አምላክ ፈራጅ ነውና። አንዱን ያዋርዳል፤ ሌላውን ደግሞ ከፍ ከፍ ያደርጋል።
የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
75:4, 5, 10—“ቀንድ” የሚለው አባባል ምን ያመለክታል? እንስሳት ቀንዳቸውን እንደ ኃይለኛ መሣሪያ ይጠቀሙበታል። በመሆኑም “ቀንድ” የሚለው ቃል ምሳሌያዊ በሆነ መንገድ ኃይልን ወይም ጥንካሬን ለማመልከት ተሠርቶበታል። ይሖዋ የሕዝቡን ቀንድ ከፍ ከፍ በማድረግ እንዲደሰቱ ሲያደርግ ‘የክፉዎችን ቀንድ ግን ይሰብራል።’ የኩራትና የትዕቢት መንፈስ እንዳይጠናወተን “ቀንድህን ከፍ አታድርግ” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። ከፍ ከፍ ያደረገን ይሖዋ በመሆኑ በጉባኤ ውስጥ የሚሰጡንን ኃላፊነቶች ከእርሱ እንደተቀበልናቸው አድርገን መመልከት ይኖርብናል።—መዝሙር 75:7
it-1-E 1160 አን. 7
ትሕትና
ሹመት የሚገኘው ከአምላክ በመሆኑ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች አመራር ለሚሰጡት መገዛት ያለባቸው ሲሆን ኃላፊነት ወይም መብት ለማግኘት ይሖዋን መጠበቅ ይኖርባቸዋል። (መዝ 75:6, 7) ሌዋውያን የነበሩት የቆሬ ልጆች እንዲህ ብለዋል፦ “በሌላ ቦታ አንድ ሺህ ቀን ከመኖር በቅጥር ግቢዎችህ አንዲት ቀን መዋል ይሻላልና! በክፉዎች ድንኳን ከመኖር፣ በአምላኬ ቤት ደጃፍ ላይ መቆም እመርጣለሁ።” (መዝ 84:10) እንዲህ ያለውን ከልብ የመነጨ ትሕትና ለማዳበር ጊዜ ይጠይቃል። መጽሐፍ ቅዱስ፣ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚሾም ሰው ሊያሟላቸው የሚገቡ ብቃቶችን ሲዘረዝር “በትዕቢት ተነፍቶ ዲያብሎስ የተፈረደበት ዓይነት ፍርድ እንዳይፈረድበት አዲስ ክርስቲያን አይሁን” ይላል።—1 ጢሞ 3:6
(መዝሙር 78:11-17) በተጨማሪም ያደረጋቸውን ነገሮች፣ ያሳያቸውን ድንቅ ሥራዎች ረሱ። 12 በአባቶቻቸው ፊት በግብፅ አገር፣ በጾዓን ምድር አስደናቂ ነገሮች አከናውኖ ነበር። 13 በዚያ አቋርጠው እንዲሄዱ ባሕሩን ከፈለው፤ ውኃዎቹንም እንደ ግድብ አቆመ። 14 ቀን በደመና፣ ሌሊቱን ሙሉ ደግሞ በእሳት ብርሃን መራቸው። 15 በምድረ በዳ ዓለቶችን ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ ውኃ የሚጠጡ ያህል እስኪረኩ ድረስ አጠጣቸው። 16 ከቋጥኝ ውስጥ ወራጅ ውኃ አወጣ፤ ውኃዎችም እንደ ወንዝ እንዲፈስሱ አደረገ። 17 እነሱ ግን በበረሃ፣ በልዑሉ አምላክ ላይ በማመፅ በእሱ ላይ ኃጢአት መሥራታቸውን ቀጠሉ፤
ትኩረታችሁ ያረፈው ሽልማቱ ላይ ነው?
ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን አመለካከት ማወቃችን ተስፋ ለማድረግ ምክንያት ይሆነናል፤ ተስፋ የእምነትን ያህል አስፈላጊ የሆነ ባሕርይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 13:13) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ተስፋ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “መልካም ነገርን [በጉጉት] መጠባበቅ” የሚል ሐሳብ ያስተላልፋል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያለውን ተስፋ በአእምሮው በመያዝ እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “የተሰጠው ተስፋ እስኪፈጸም ድረስ እያንዳንዳችሁ እንዲህ ያለውን ትጋት እስከ መጨረሻ እንድታሳዩ እንመኛለን። በእምነትና በትዕግሥት የተስፋውን ቃል የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንድትሆኑ አንፈልግም።” (ዕብራውያን 6:11, 12) ይሖዋን በታማኝነት ማገልገላችንን ከቀጠልን ተስፋችን እንደሚፈጸምልን እርግጠኞች መሆን እንደምንችል ልብ በል። በዓለም ላይ ካሉ ከአብዛኞቹ ተስፋዎች በተቃራኒ ይህ ተስፋ “ለዕፍረት አይዳርገንም።” (ሮሜ 5:5) ታዲያ ተስፋችን ብሩሕ ሆኖ እንዲታየንና ከአእምሯችን እንዳይጠፋ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
የመንፈሳዊ እይታችንን ጥራት ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?
ሥጋዊ ዓይናችን በአንድ ጊዜ በሁለት ነገሮች ላይ ማተኮር አይችልም። መንፈሳዊ እይታችንን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ትኩረታችን ያረፈው በዚህ ሥርዓት ውስጥ ባሉ ነገሮች ላይ ከሆነ አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ላይ እንዳናተኩር ሊያደርገን እንደሚችል ግልጽ ነው። ውሎ አድሮ፣ እይታችን በመደብዘዙ ተስፋው ማራኪ መሆኑ እየቀረ ይሄድና ከአእምሯችን ይጠፋል። ይህ እንዴት አሳዛኝ ይሆናል! (ሉቃስ 21:34) እንግዲያው በአምላክ መንግሥትና በዘላለም ሕይወት ሽልማታችን ላይ ያተኮረ “ጤናማ” ዓይን እንዲኖረን ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ማቴዎስ 6:22
ጤናማ ዓይን እንዲኖረን ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። በየዕለቱ የሚያጋጥሙን ችግሮች ትኩረታችንን ሊሰርቁት እንዲሁም ሐሳባችንን የሚከፋፍሉ ሁኔታዎችና ፈተናዎች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። እነዚህ ሁኔታዎች እያሉም፣ ሌሎች አስፈላጊ ጉዳዮችን ቸል ሳንል ትኩረታችንን በመንግሥቱና አምላክ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ላይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ሦስት መንገዶችን እንመልከት።
የአምላክን ቃል በየዕለቱ አጥና። አዘውትረን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማጥናት አእምሯችን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ይረዳናል። እውነት ነው፣ የአምላክን ቃል ለዓመታት ስናጠና ቆይተን ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም በሕይወት ለመቆየት አዘውትረን ሥጋዊ ምግብ መመገብ እንደሚያስፈልገን ሁሉ የአምላክንም ቃል ማጥናታችንን ልንቀጥል ይገባል። ባለፉት ዓመታት ስንበላ ስለኖርን አሁን ምግብ አናቆምም። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን የቱንም ያህል ብናውቀው ተስፋችን ብሩሕ እንዲሆንና እምነታችንና ፍቅራችን እንዲጠነክር አዘውትረን ልናነበው ይገባል።—መዝሙር 1:1-3
በአምላክ ቃል ላይ በአድናቆት አሰላስል። ማሰላሰል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሁለት ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል። በመጀመሪያ፣ ማሰላሰል ያነበብነውን ነገር በሚገባ ለመረዳት የሚያስችለን ሲሆን ስለ ጉዳዩም ጥልቅ አድናቆት እንዲያድርብን ያደርገናል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ማሰላሰል ይሖዋንና ድንቅ ሥራዎቹን እንዲሁም በፊታችን ያስቀመጠልንን ተስፋ እንዳንረሳ ይረዳናል። ሁኔታውን በምሳሌ ለማስረዳት:- ከሙሴ ጋር ከግብጽ የወጡት እስራኤላውያን የይሖዋን ታላቅ ኃይል ተመልክተው ነበር። ከዚህም በላይ ወደ ተስፋይቱ ምድር በመራቸው ወቅት ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ጥበቃ ሲያደርግላቸው አይተዋል። ያም ሆኖ እስራኤላውያን ማጉረምረም የጀመሩት ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመጓዝ ምድረ በዳውን ማቋረጥ እንደጀመሩ ነበር፤ ይህም እምነት እንዳልነበራቸው የሚያሳይ ነው። (መዝሙር 78:11-17) ችግራቸው ምን ነበር?
ሕዝቡ በይሖዋና ከፊታቸው በዘረጋላቸው ግሩም ተስፋዎች ላይ ከማተኮር ይልቅ ጊዜያዊ ለሆነው ምቾታቸውና ሥጋዊ ፍላጎታቸው ቅድሚያ ሰጡ። ድንቅ ተዓምራትን ሲፈጽም በገዛ ዓይናቸው የተመለከቱ ቢሆንም በርካታ እስራኤላውያን እምነት በማጣት አጉረምራሚዎች ሆኑ። መዝሙር 106:13 ይሖዋ “ያደረገውን ወዲያውኑ ረሱ” ይላል። ያ ትውልድ እንደዚህ ያለ በይቅርታ ሊታለፍ የማይችል ቸልተኝነት በማሳየቱ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሳይገባ ቀረ።
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን ወይም መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ ጽሑፎችን ስታነብብ ጊዜ ወስደህ ባነበብከው ነገር ላይ አሰላስል። እንደዚህ ማድረግህ መንፈሳዊ ጤንነትህን ለመጠበቅና እድገት ለማድረግ ይረዳሃል። ለምሳሌ፣ በከፊል ከላይ የተጠቀሰውን መዝሙር 106ን በምታነብበት ጊዜ በይሖዋ ባሕርያት ላይ አሰላስል። ከእስራኤላውያን ጋር በነበረው ግንኙነት ምን ያህል ታጋሽና መሐሪ እንደነበረ ለማስተዋል ሞክር። ወደ ተስፋይቱ ምድር እንዲገቡ ለመርዳት ያላደረገው ነገር እንደሌለ ልብ በል። በተደጋጋሚ ጊዜ ያምፁበት እንደነበር አስብ። ጨርሶ ምስጋና ቢስ የሆኑት እነዚህ ሰዎች ምሕረቱንና ትዕግሥቱን ሲፈታተኑት ይሖዋ ምን ያህል እንዳዘነ በዓይነ ሕሊናህ ተመልከት። ከዚህም በላይ ፊንሐስ ለጽድቅ ሲል የወሰደውን ጠንካራና ድፍረት የተሞላበት እርምጃ በሚያብራሩት በቁጥር 30 እና 31 ላይ በማሰላሰል ይሖዋ ታማኞቹን እንደማይረሳና አትረፍርፎ እንደሚባርካቸው ማረጋገጫ ማግኘት እንችላለን።
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ አድርግ። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ስናደርግ የይሖዋ ምክሮች ጠቃሚ እንደሆኑ ከራሳችን ተሞክሮ መመልከት እንችላለን። ምሳሌ 3:5, 6 እንዲህ ይላል:- “በፍጹም ልብህ በእግዚአብሔር ታመን፤ በራስህ ማስተዋል አትደገፍ፤ በመንገድህ ሁሉ እርሱን ዕወቅ፤ እርሱም ጐዳናህን ቀና ያደርገዋል።” ሥነ ምግባር የጎደለው አካሄድ የተከተሉ በርካታ ሰዎች ድርጊታቸው ያስከተለባቸውን አእምሯዊ፣ ስሜታዊና አካላዊ ችግር አስብ። እነዚህ ሰዎች ለጊዜያዊ ተድላ በመሸነፋቸው ለዓመታት ይባስ ብሎም ዕድሜያቸውን ሙሉ ለመከራ ተዳርገዋል። ከዚህ በተቃራኒ ‘በቀጠነው መንገድ’ የሚሄዱ ሰዎች በአሁኑ ጊዜ የአዲሱን ሥርዓት ቅምሻ የሚያገኙ ሲሆን ይህም በሕይወት መንገድ ላይ መጓዛቸውን እንዲቀጥሉ ብርታት ይሰጣቸዋል።—ማቴዎስ 7:13, 14፤ መዝሙር 34:8
የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በተግባር ማዋል ፈታኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ እርምጃ በመውሰድ አፋጣኝ መፍትሔ ማግኘት እንደምንችል ይሰማን ይሆናል። ለአብነት ያህል፣ በገንዘብ ረገድ ችግር ሲያጋጥመን መንፈሳዊ ነገሮችን በሁለተኛ ደረጃ ለማስቀመጥ እንፈተን ይሆናል። ይሁን እንጂ በእምነት የሚመላለሱና ትኩረታቸውን በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ የሚያደርጉ ሁሉ “ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ሰዎች መልካም እንደሚሆንላቸው” እርግጠኛ መሆን ይችላሉ። (መክብብ 8:12) አንድ ክርስቲያን አልፎ አልፎ ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ያስፈልገው ይሆናል፤ ሆኖም ለመንፈሳዊ ነገሮች ቦታ ባለመስጠት አቃልሎ እንደተመለከታቸው እንደ ዔሳው መሆን የለበትም።—ዘፍጥረት 25:34፤ ዕብራውያን 12:16
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
የመሲሑን መምጣት ይጠባበቁ ነበር
መሲሑ ስለሚያከናውናቸው ሌሎች ተግባራት አስቀድሞ ተነግሯል
14 መሲሑ በምሳሌ እንደሚናገር ተተንብዮ ነበር። መዝሙራዊው አሳፍ “አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ” ሲል ዘምሯል። (መዝ. 78:2) ይህ ትንቢት በኢየሱስ ላይ እንደተፈጸመ እንዴት እናውቃለን? ማቴዎስ ይህን ያረጋግጥልናል። ማቴዎስ፣ ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት እያደገች ከሄደች የሰናፍጭ ዘር እና ከእርሾ ጋር በማመሳሰል የተናገረውን ምሳሌ ከገለጸ በኋላ እንዲህ ብሏል፦ “[ኢየሱስ] ያለ ምሳሌ አይነግራቸውም ነበር፤ ይህም የሆነው ‘አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተሰወሩትን ነገሮች አሳውቃለሁ’ ተብሎ በነቢዩ የተነገረው ይፈጸም ዘንድ ነው።” (ማቴ. 13:31-35) ኢየሱስ ከተጠቀመባቸው ውጤታማ የማስተማሪያ ዘዴዎች መካከል ምሳሌዎች ይገኙበታል።
(መዝሙር 78:40, 41) በምድረ በዳ ስንት ጊዜ በእሱ ላይ ዓመፁ! በበረሃ ሳሉም ብዙ ጊዜ ስሜቱን ጎዱት! 41 ደግመው ደጋግመው አምላክን ተፈታተኑት፤ የእስራኤልንም ቅዱስ እጅግ አሳዘኑት።
መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል
መጽሐፍ ቅዱስን ሳጠና ስለ አምላክ የነበረኝ አመለካከት ሙሉ በሙሉ ተቀየረ። ክፋትንና መከራን ያመጣው አምላክ እንዳልሆነና ሰዎች መጥፎ ነገር ሲፈጽሙ እሱም እንደሚያዝን ተማርኩ። (ዘፍጥረት 6:6፤ መዝሙር 78:40, 41) ይሖዋን የሚያሳዝን ምንም ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። የእሱን ልብ የማስደሰት ፍላጎት አደረብኝ። (ምሳሌ 27:11) ከመጠን በላይ መጠጣትና ትንባሆ መጠቀም አቆምኩ፤ እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች መፈጸሜን ተውኩ። ከዚያም መጋቢት 1994 ተጠምቄ የይሖዋ ምሥክር ሆንኩ።
ወደ አምላክ ቅረብ
ይሖዋ ስሜት አለው?
የዚህ ጥያቄ መልስ ‘አዎን’ የሚል ከሆነ እንዲህ የሚል ሌላ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፦ የምናሳየው ምግባር በአምላክ ስሜት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል? ማለትም አምላክ በምናደርጋቸው ነገሮች ሊደሰት ወይም ሊያዝን ይችላል? አንዳንድ የጥንት ፈላስፎች አምላክ ሊደሰት ወይም ሊያዝን እንደማይችል ይናገሩ ነበር። እነዚህ ሰዎች ማንም ሰው በአምላክ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለማይችል አምላክ ስሜት የለውም የሚል የመከራከሪያ ነጥብ ያነሳሉ። ከዚህ በተቃራኒ መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ጥልቅ ስሜት ያለውና የምናደርገው ነገር በእጅጉ የሚያሳስበው አምላክ እንደሆነ ይገልጻል። እስቲ በዚህ ረገድ በመዝሙር 78:40, 41 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመልከት።
መዝሙር 78 አምላክ ከጥንቶቹ እስራኤላውያን ጋር ስለነበረው ግንኙነት ይነግረናል። ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ የባርነት ሕይወት ከታደጋቸው በኋላ በብሔር ደረጃ ከእሱ ጋር የተለየ ዝምድና እንዲመሠርቱ ግብዣ አቅርቦላቸው ነበር። ሕጎቹን ጠብቀው የሚኖሩ ከሆነ ‘የተወደደ ርስቱ’ እንደሚሆኑና ዓላማውን ዳር ለማድረስ ፈጽሞ በተለየ መንገድ እንደሚጠቀምባቸው ቃል ገብቶ ነበር። ሕዝቡም በዚህ ተስማምቶ በሕጉ ቃል ኪዳን ውስጥ ታቀፈ። ታዲያ ሕዝቡ ከገባው ቃል ጋር ተስማምቶ ኖረ?—ዘፀአት 19:3-8
መዝሙራዊው “በምድረ በዳ ስንት ጊዜ ዐመፁበት!” በማለት ተናግሯል። (ቁጥር 40) በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ደግሞ “ደግመው ደጋግመው እግዚአብሔርን ተፈታተኑት” የሚል ሐሳብ ይገኛል። (ቁጥር 41) ጸሐፊው እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ ያምፁ እንደነበር መግለጹን ልብ በል። እንዲህ ያለው መጥፎ ዝንባሌ የጀመረው ከግብፅ ከወጡ ብዙም ሳይቆዩ ገና በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ ነው። ሕዝቡ፣ አምላክ እነሱን ለመንከባከብ ያለውን አቅምና ፍላጎት በመጠራጠር በእሱ ላይ ማመፅ ጀመረ። (ዘኍልቍ 14:1-4) ለመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የተዘጋጀ አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “ዐመፁበት” የሚለው ቃል “‘በአምላክ ላይ ልባቸውን አደነደኑ’ ወይም ‘አምላክን “እንቢ” አሉ’ ተብሎ ሊተረጎም” እንደሚችል ገልጿል። እንደዚያም ሆኖ ይሖዋ ንስሐ ሲገቡ በምሕረት ተነሳስቶ ይቅር ይላቸው ነበር። ይሁንና ወደ ቀድሞ ሕይወታቸው በመመለስ እንደገና ዓመፁ፤ እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ በተደጋጋሚ ጊዜ ይከሰት ነበር።—መዝሙር 78:10-19, 38
ይሖዋ ወጥ አቋም የሌለው ይህ ሕዝብ በሚያምፅበት ጊዜ ምን ተሰምቶት ነበር? ቁጥር 40 “አሳዘኑት” ይላል። ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ “ለመሪር ሐዘን ዳረጉት” በማለት ይገልጻል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ የማመሳከሪያ ጽሑፍ ይህን ጉዳይ ሲያብራራ “ይህ ሐረግ የማይታዘዝና ዓመፀኛ የሆነ አንድ ልጅ የሚያደርገው ነገር ሥቃይ እንደሚያስከትል ሁሉ የዕብራውያኑ ድርጊትም ለሥቃይ ምክንያት እንደሆነ የሚገልጽ ትርጉም አለው” ብሏል። በጥባጭ የሆነ ልጅ ወላጆቹን እንደሚያበሳጭ ሁሉ ዓመፀኛ የሆኑት እነዚህ እስራኤላውያንም ‘የእስራኤልን ቅዱስ አስቈጥተውታል።’—ቁጥር 41
ከዚህ ጥቅስ ምን እንማራለን? ይሖዋ እሱን ከሚያመልኩት ሰዎች ጋር ጥብቅ ዝምድና እንዳለውና በቀላሉ በእነሱ ተስፋ እንደማይቆርጥ ማወቅ የሚያጽናና ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ይሖዋ ስሜት እንዳለውና የምናሳየው ምግባር በስሜቱ ላይ ለውጥ ሊያመጣ እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። ታዲያ አንተ ይህን ማወቅህ ምን ስሜት ሊያሳድርብህ ይገባል? ይህ ሁኔታ ትክክል የሆነውን ነገር እንድታደርግ አነሳስቶሃል?
የኃጢአት ጎዳና በመከተል የይሖዋን ልብ ከማሳዘን ይልቅ የጽድቅን መንገድ በመከተል ልቡን ደስ ለማሰኘት መምረጥ እንችላለን። ደግሞም አምላክ እሱን ከሚያመልኩት ሰዎች የሚፈልገው ይህንኑ ነው፤ አዎን፣ አምላክ “ልጄ ሆይ፤ ጠቢብ ሁን፤ ልቤን ደስ አሰኘው” የሚል ግብዣ አቅርቧል። (ምሳሌ 27:11) ለይሖዋ የእሱን ልብ ደስ በሚያሰኝ መንገድ ከመኖር የበለጠ ልንሰጠው የምንችለው ውድ ነገር የለም።
ሐምሌ 25-31
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | መዝሙር 79-86
“በሕይወታችሁ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምትሰጡት ለማን ነው?”
ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ
7 መዝሙራዊውን በዋነኝነት ያሳሰበው ምን ነበር? ይህ መዝሙራዊ የራሱም ሆነ የቤተሰቡ ደኅንነት በጣም አሳስቦት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሆኖም ጸሎቱ በዋነኝነት ያተኮረው በይሖዋ ስም ላይ በሚመጣው ነቀፌታ እንዲሁም የእሱን ስም የተሸከመው ብሔር በተሰነዘረበት ዛቻ ላይ ነበር። እኛም በዚህ አሮጌ ዓለም የመጨረሻ ቀን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጽናት በምንቋቋምበት ጊዜ እንዲህ ዓይነት ሚዛናዊ አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናድርግ።—ማቴዎስ 6:9, 10ን አንብብ።
8 መዝሙራዊው፣ “የእስራኤል ስም ከእንግዲህ እንዳይታወስ፣ ኑና ሕዝብ እንዳይሆኑ እንደምስሳቸው” በማለት ጠላቶቻቸው እንደተናገሩ ገልጿል። (መዝ. 83:4) እነዚያ ብሔራት፣ አምላክ ለመረጣቸው ሕዝቦች እንዴት ያለ ጥላቻ ነበራቸው! ይሁንና በእስራኤል ላይ እንዲያሤሩ ያነሳሳቸው ምክንያት ይህ ብቻ አልነበረም። የእስራኤላውያንን ምድር ለመውረስ የተመኙ ከመሆኑም በላይ “የእግዚአብሔርን የግጦሽ ቦታ፣ [“ማደሪያ፣” NW] ወስደን የግላችን እናድርግ” በማለት ፎክረው ነበር። (መዝ. 83:12) በዘመናችንስ ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ ተከስቷል? አዎን!
(መዝሙር 83:16) ይሖዋ ሆይ፣ ስምህን ይሹ ዘንድ፣ ፊታቸውን በኀፍረት ሸፍን።
ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ
የይሖዋ ሉዓላዊነት እንዲረጋገጥ እንጸልይ
16 በዚህ ‘የመጨረሻ ዘመን’ ይሖዋ ሕዝቦቹን ለማጥፋት የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ እንዲከሽፉ አድርጓል። (2 ጢሞ. 3:1) በዚህም የተነሳ ተቃዋሚዎች አፍረዋል። መዝሙራዊው በመዝሙር 83:16 ላይ “እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ ስምህን ይሹ ዘንድ፣ ፊታቸውን በዕፍረት ሙላው” ሲል ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ መናገሩ ነበር። ተቃዋሚዎች በተለያዩ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮችን ዝም ለማሰኘት ያደረጉት ጥረት ከንቱ ሆኗል። በእነዚህ አገሮች ውስጥ የሚኖሩ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች ከአቋማቸው ፍንክች አለማለታቸውና በጽናት መቀጠላቸው ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ምሥክርነት ከመስጠቱም በላይ ብዙዎች የይሖዋን ‘ስም እንዲሹ’ አድርጓቸዋል። በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከፍተኛ ስደት ይደርስ በነበረባቸው ብዙ አገሮች ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በአሥር ሺዎች እንዲያውም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይሖዋን በደስታ እያወደሱት ነው። ይህ ለይሖዋ እንዴት ያለ ታላቅ ድል ነው! ጠላቶቹንስ ምንኛ የሚያሳፍር ነው!—ኤርምያስ 1:19ን አንብብ።
(መዝሙር 83:17, 18) ለዘላለም ይፈሩ፣ ይሸበሩም፤ ውርደት ይከናነቡ፤ ደግሞም ይጥፉ፤ 18 ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ አዎ፣ አንተ ብቻ በመላው ምድር ላይ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ይወቁ።
በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ለማን ነው?
የይሖዋን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከትኸው የት ነው? ምናልባትም በዘፀአት 6:3 ላይ ሊሆን ይችላል። ጥቅሱ በ1879 ትርጉም እንዲህ ይላል፦ “ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ ይሖዋ አልታወቅሁላቸውም።” ከዚያ ጊዜ ወዲህ አንተም ሰዎች አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ ለመርዳት በዚህ ጥቅስ ተጠቅመህ ሊሆን እንደሚችል ጥርጥር የለውም።—ሮም 10:12, 13
2 ሰዎች የይሖዋን ስም ማወቃቸው አስፈላጊ ቢሆንም ይህ ብቻ ግን በቂ አይደለም። መዝሙራዊው፣ ይሖዋ “በምድር ሁሉ ላይ ልዑል” ወይም ከሁሉ በላይ እንደሆነ በመግለጽ ለመዳን ወሳኝ ስለሆነ አንድ እውነታ ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝ. 83:18) አዎን፣ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የሚይዘው ይሖዋ ነው። ይሖዋ የሁሉ ነገር ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ሁሉም ፍጡሮቹ ለእሱ ሙሉ በሙሉ እንዲገዙለት የመጠበቅ መብት አለው። (ራእይ 4:11) እንግዲያው ‘በሕይወቴ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምሰጠው ለማን ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። እያንዳንዳችን ለዚህ ጥያቄ የምንሰጠውን መልስ በጥንቃቄ መመርመራችን በጣም አስፈላጊ ነው።
ይሖዋ ከልብ ለቀረበ ጸሎት የሰጠው መልስ
17 እርግጥ ነው፣ አሁንም ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክሮችን ማሳደዳቸው እንዳላቆሙ እናውቃለን። እኛም ለተቃዋሚዎቻችንም ጭምር ምሥራቹን መስበካችንን አናቋርጥም። (ማቴ. 24:14, 21) ሆኖም እነዚህ ተቃዋሚዎች ንስሐ ገብተው መዳን እንዲያገኙ የተከፈተላቸው አጋጣሚ በቅርቡ ያበቃል። ከሰው ልጆች መዳን ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር የይሖዋ ስም መቀደስ ነው። (ሕዝቅኤል 38:23ን [NW] አንብብ።) አስቀድሞ በተነገረው መሠረት ብሔራት በሙሉ የአምላክን ሕዝቦች ለማጥፋት ሲሰባሰቡ መዝሙራዊው “ለዘላለም ይፈሩ፤ ይታወኩም፤ በውርደትም ይጥፉ” በማለት ያቀረበውን ጸሎት እናስታውሳለን።—መዝ. 83:17
18 የይሖዋን ሉዓላዊነት ለመቃወም ቆርጠው የተነሱ ሁሉ ኃፍረት ተከናንበው ይጠፋሉ። የአምላክ ቃል፣ ‘ለወንጌል ባለመታዘዛቸው’ የተነሳ በአርማጌዶን እርምጃ የሚወሰድባቸው ሰዎች ‘ለዘላለም እንደሚጠፉ’ ይናገራል። (2 ተሰ. 1:7-9) እነዚህ ሰዎች መጥፋታቸው እንዲሁም ይሖዋን በእውነት የሚያመልኩ ሰዎች ከጥፋቱ መዳናቸው ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ ይሆናል። ይህ ታላቅ ድል በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ሲታወስ ይኖራል። “ጻድቃንና ኀጥአን ከሙታን [ሲነሡ]” ስለ ይሖዋ ታላቅ ሥራ ይማራሉ። (ሥራ 24:15) እነዚህ ሰዎች፣ ለይሖዋ ሉዓላዊነት መገዛት የጥበብ አካሄድ መሆኑን የሚያሳይ አሳማኝ ማስረጃ በአዲሱ ዓለም ውስጥ ይመለከታሉ። ገሮችም ይሖዋ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ መሆኑን አምነው ለመቀበል ጊዜ አይፈጅባቸውም።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(መዝሙር 79:9) አዳኛችን የሆንክ አምላክ ሆይ፣ ለታላቁ ስምህ ስትል እርዳን፤ ለስምህም ስትል ታደገን፤ ኃጢአታችንንም ይቅር በለን።
የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
79:9፦ ይሖዋ፣ በተለይም ከስሙ መቀደስ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ጠቅሰን ስንጸልይ ጸሎታችንን ይሰማል።
(መዝሙር 86:5) ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ፤ አንተን ለሚጠሩ ሁሉ የምታሳየው ታማኝ ፍቅር ወሰን የለውም።
የመዝሙር ሦስተኛና አራተኛ መጻሕፍት ጎላ ያሉ ነጥቦች
86:5፦ ይሖዋ “ይቅር ባይ” በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል! ለአንድ ንስሐ የገባ ኃጢአተኛ ምሕረት ለማሳየት የሚያበቃ ምክንያት በሚኖርበት ጊዜ ሁሉ ይሖዋ ይቅር ለማለት ዝግጁ ነው።