የክርስቲያናዊ ሕይወትና አገልግሎት ስብሰባ አስተዋጽኦ የማመሣከሪያ ጽሑፎች—ነሐሴ 2020
ከነሐሴ 3-9
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 13–14
“ጸንታችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ የሚፈጽመውን ማዳን እዩ”
(ዘፀአት 14:13, 14) በዚህ ጊዜ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አላቸው፦ “አትፍሩ። ጸንታችሁ ቁሙ፤ በዛሬው ዕለት ይሖዋ ለእናንተ ሲል የሚፈጽመውን የእሱን ማዳን እዩ። ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያን ዳግመኛ አታዩአቸውም፤ በጭራሽ አታዩአቸውም። 14 ይሖዋ ራሱ ስለ እናንተ ይዋጋል፤ ብቻ እናንተ ዝም በሉ።”
ሙሴ—የእምነት ሰው
አምላክ ለእስራኤላውያን ማምለጫ መንገድ ለመክፈት ሲል ቀይ ባሕርን ለሁለት ሊከፍል እንደሆነ ሙሴ ላያውቅ ይችላል። ይሁንና ሙሴ፣ አምላክ ሕዝቡን ለማዳን የሆነ ነገር እንደሚያደርግ እርግጠኛ ነበር። ወገኖቹ የሆኑት እስራኤላውያንም የእሱ ዓይነት እምነት እንዲኖራቸው ፈልጎ ነበር። ሙሴ ሕዝቡን “አትሸበሩ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር ዛሬ የሚያደርግላችሁን መታደግ ታያላችሁ” አላቸው። (ዘፀአት 14:13) ሙሴ የሕዝቡን እምነት ለማጠናከር ያደረገው ጥረት ተሳክቶለት ይሆን? እንዴታ! ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሙሴ ብቻ ሳይሆን ስለ ሁሉም እስራኤላውያን ሲናገር “በደረቅ ምድር እንደሚሄዱ ሆነው ቀይ ባሕርን በእምነት ተሻገሩ” ይላል። (ዕብራውያን 11:29) የሙሴ እምነት የጠቀመው ራሱን ብቻ ሳይሆን በይሖዋ ላይ እምነት ማድረግ የጥበብ እርምጃ መሆኑን የተገነዘቡትን ሁሉ ነው።
(ዘፀአት 14:21, 22) ሙሴም እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤ ይሖዋም ሌሊቱን ሙሉ ኃይለኛ የምሥራቅ ነፋስ በማምጣት ባሕሩ ወደ ኋላ እንዲመለስ አደረገ፤ የባሕሩንም ወለል ወደ ደረቅ መሬት ለወጠው፤ ውኃውም ተከፈለ። 22 በመሆኑም እስራኤላውያን ውኃው በቀኛቸውና በግራቸው እንደ ግድግዳ ቆሞ በባሕሩ መሃል በደረቅ መሬት ተሻገሩ።
ሁሉን ቻይ ሆኖም አሳቢ
13 ዘፀአት 14:19-22ን አንብብ። እስቲ ከእስራኤላውያን ጋር እንዳለህ አድርገህ አስብ፤ ከኋላህ የግብፃውያን ሠራዊት፣ ከፊትህ ደግሞ ቀይ ባሕር ስላለ ወዴት እንደምትሄድ ግራ ተጋብተሃል። በዚህ ጊዜ አምላክ እርምጃ ወሰደ። የደመናው ዓምድ ወደ ኋላ ሄዶ ከሕዝቡ በስተ ጀርባ ቆመ። የደመናው ዓምድ ግብፃውያንን ወደ እስራኤላውያን እንዳይደርሱ ያገዳቸው ከመሆኑም ሌላ አካባቢውን አጨለመባቸው። አንተ ያለህበት የእስራኤላውያን ሰፈር ግን በአስደናቂ ብርሃን ተሞልቷል! ከዚያም ሙሴ እጁን በባሕሩ ላይ ሲሰነዝር አየህ፤ በዚህ ጊዜ ከምሥራቅ የመጣ ኃይለኛ ነፋስ ውኃውን ለሁለት በመክፈል ባሕሩን ለመሻገር የሚያስችል ሰፊ መንገድ ከፈተ። አንተና ቤተሰብህ እንዲሁም የቤት እንስሶቻችሁ ከመላው ሕዝብ ጋር ሥርዓት ባለው መንገድ ቀይ ባሕርን መሻገር ጀመራችሁ። በድንገት ግን አንድ አስገራሚ ነገር አስተዋልክ። የባሕሩን ወለል ስትረግጠው ስምጥ ስምጥ የሚል ወይም የሚያንሸራትት ሳይሆን ደረቅ ነው፤ በመሆኑም እያዘገሙ የሚጓዙትን ጨምሮ ሁላችሁም ያለምንም ችግር ቀይ ባሕርን ተሻገራችሁ።
(ዘፀአት 14:26-28) ከዚያም ይሖዋ ሙሴን “ውኃው በግብፃውያን፣ በጦር ሠረገሎቻቸውና በፈረሰኞቻቸው ላይ ተመልሶ እንዲመጣባቸው እጅህን በባሕሩ ላይ ሰንዝር” አለው። 27 ሙሴም ወዲያውኑ እጁን በባሕሩ ላይ ሰነዘረ፤ ሊነጋጋ ሲልም ባሕሩ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ተመለሰ። ግብፃውያንም ውኃው እንዳይደርስባቸው ለመሸሽ ሲሞክሩ ይሖዋ ግብፃውያኑን ባሕሩ መሃል ጣላቸው። 28 ውኃውም ተመልሶ እስራኤላውያንን ተከትለው የገቡትን የጦር ሠረገሎችና ፈረሰኞች እንዲሁም የፈርዖንን ሠራዊት በሙሉ አለበሳቸው። ከእነሱም መካከል አንድም የተረፈ የለም።
ይሖዋን ፈጽሞ ልትረሳው አይገባም
ግብፃውያን ከጦር ሠረገሎቻቸው ጋር ሲታገሉ እስራኤላውያን በሙሉ በስተ ምሥራቅ ወዳለው የባሕሩ ዳርቻ ደረሱ። በዚህ ጊዜ ሙሴ በቀይ ባሕር ላይ እጁን ዘረጋ። ይሖዋም እንደ ግድግዳ ቀጥ ብሎ የቆመውን ውኃ ወደ ቦታው እንዲመለስ አደረገው። ባሕሩ በፈርዖንና በሠራዊቱ ላይ በመደርመስ አሰመጣቸው። ከእነዚህ የአምላክ ጠላቶች መካከል አንድም ሰው አልተረፈም። በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ከአሳዳጆቻቸው ነፃ ወጡ!—ዘፀ. 14:26-28፤ መዝ. 136:13-15
ይህን የሰሙ በአካባቢው የሚኖሩ ብሔራት በፍርሃት ራዱ፤ እነዚህ ብሔራት ከብዙ ዓመታት በኋላም እንኳ ፍርሃታቸው አልለቀቃቸውም ነበር። (ዘፀ. 15:14-16) እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በኢያሪኮ ትኖር የነበረችው ረዓብ ለሁለት እስራኤላውያን እንዲህ ብላቸዋለች፦ “እናንተንም መፍራት [አደረብን]፣ . . . ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እግዚአብሔር ቀይ ባሕርን በፊታችሁ እንዴት እንዳደረቀ . . . ሰምተናል።” (ኢያሱ 2:9, 10) እነዚህ አረማውያን እንኳ ይሖዋ ሕዝቡን ነፃ ያወጣቸው እንዴት እንደሆነ አልረሱም ነበር። በግልጽ ለመመልከት እንደምንችለው እስራኤላውያን ይሖዋን እንዲያስታውሱ የሚያደርጓቸው በርካታ ምክንያቶች ነበሯቸው።
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 13:17) ፈርዖን ሕዝቡን በለቀቀ ጊዜ አምላክ ምንም እንኳ አቋራጭ ቢሆንም ወደ ፍልስጤማውያን ምድር በሚወስደው መንገድ አልመራቸውም። ምክንያቱም “ሕዝቡ ጦርነት ቢያጋጥመው ሐሳቡን ለውጦ ወደ ግብፅ ሊመለስ ይችላል” በማለት አስቦ ነበር።
it-1 1117
አውራ ጎዳና፣ መንገድ
ከጥንት ዘመን አንስቶ በፓለስቲና ምድር ከተሞችንና መንግሥታትን የሚያገናኙ አውራ ጎዳናዎችና መንገዶች እንዲሁም ወሳኝ የንግድ መስመሮች ነበሩ። (ዘኁ 20:17-19፤ 21:21, 22፤ 22:5, 21-23፤ ኢያሱ 2:22፤ መሳ 21:19፤ 1ሳሙ 6:9, 12፤ 13:17, 18፤ የንጉሡ መንገድ የሚለውን ተመልከት።) ዋነኛ መንገድ ተደርጎ የሚቆጠረው ከግብፅ ተነስቶ የፓለስቲና ከተሞች ወደሆኑት ወደ ጋዛ እና አስቀሎና የሚሄደው ከዚያም በስተ ሰሜን ምሥራቅ ታጥፎ ወደ መጊዶ አቅጣጫ የሚወስደው መንገድ ነው። ይህ መንገድ ከገሊላ ባሕር በስተ ሰሜን ወደሚገኘው ወደ ሃጾር፣ ከዚያም ወደ ደማስቆ ይወስዳል። ከግብፅ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚወስደው አጭሩ መንገድ፣ ፍልስጤምን አቋርጦ የሚያልፈው ይህ መንገድ ነበር። ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያን በፍልስጤማውያን ጥቃት ተሰንዝሮባቸው እንዳይደናገጡ ሲል በደግነት ተነሳስቶ በሌላ መንገድ መርቷቸዋል።—ዘፀ 13:17
(ዘፀአት 14:2) “ወደ ኋላ ተመልሰው በሚግዶልና በባሕሩ መካከል ባለው በበዓልጸፎን ትይዩ በሚገኘው በፊሃሂሮት ፊት ለፊት እንዲሰፍሩ ለእስራኤላውያን ንገራቸው። በበዓልጸፎን ፊት ለፊት በባሕሩ አጠገብ ስፈሩ።
it-1 782 አን. 2-3
ዘፀአት
እስራኤላውያን ሲሻገሩ ቀይ ባሕር የተከፈለው የቱ ጋ ነው?
እስራኤላውያን በጉዟቸው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ማለትም “በምድረ በዳው ዳርቻ ላይ በሚገኘው በኤታም” በደረሱ ጊዜ አምላክ ሙሴን “ወደ ኋላ ተመልሰው . . . በፊሃሂሮት ፊት ለፊት . . . በባሕሩ አጠገብ” እንዲሰፍሩ አዘዘው። በዚህ መልኩ አቅጣጫቸውን መቀየራቸው ፈርዖን እስራኤላውያን “ግራ ተጋብተው በምድሪቱ ላይ እየተንከራተቱ ነው” ብሎ እንዲያምን ያደርገዋል። (ዘፀ 13:20፤ 14:1-3) እስራኤላውያን የተከተሉት የኤል ሃጅን መንገድ ነው ብለው የሚያምኑ ምሁራን “ወደ ኋላ ተመልሰው” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ግስ ለማጉላት የሚያገለግል ግስ እንደሆነ ይናገራሉ፤ በመሆኑም ቃሉ እንዲሁ “አቅጣጫ መቀየርን” ወይም “አጠፍ ማለትን” ሳይሆን ወደ ኋላ መመለስን ወይም ታጥፎ በሌላ አቅጣጫ መጓዝን ያመለክታል። እስራኤላውያን ከሱዊዝ የባሕር ወሽመጥ ጫፍ በስተ ሰሜን ሲደርሱ አቅጣጫቸውን ቀይረው በባሕር ወሽመጡ ምዕራባዊ ዳርቻ ከሚገኘው ጀቤል አተቃህ የተባለ የተራራ ሰንሰለት በስተ ምሥራቅ ሄደው ሊሆን እንደሚችል ምሁራኑ ይናገራሉ። እስራኤላውያን ብዙ ሕዝብ ስለነበሩ እዚህ ቦታ ላይ ሆነው ከሰሜን ጥቃት ቢሰነዘርባቸው ማምለጥ የሚችሉበት መንገድ አልነበረም፤ ባሕሩ መንገድ ስለሚዘጋባቸው አጣብቂኝ ውስጥ ይገባሉ።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. የነበረው የአይሁዳውያን ወግም ይህን ይደግፋል። (ፊሃሂሮት የሚለውን ተመልከት።) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይህ መደምደሚያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ጋር ይስማማል። እርግጥ በርካታ ምሁራን እስራኤላውያን ይህን መንገድ እንደተከተሉ አያምኑም። (ዘፀ 14:9-16) እስራኤላውያን የተሻገሩበት ቦታ ከባሕር ወሽመጡ ጫፍ (ወይም ከቀይ ባሕር ምዕራባዊ ዳርቻ) ርቆ የሚገኝ መሆን ይኖርበታል፤ ፈርዖንና ሠራዊቱ በባሕሩ ዳርቻ ዞረው እስራኤላውያንን ሊደርሱባቸው ያልቻሉት ለዚህ ነው።—ዘፀ 14:22, 23
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከነሐሴ 10-16
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 15–16
“ይሖዋን በመዝሙር አወድሱት”
(ዘፀአት 15:1, 2) በዚያን ጊዜ ሙሴና እስራኤላውያን የሚከተለውን መዝሙር ለይሖዋ ዘመሩ፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ እዘምራለሁ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው። 2 አዳኜ ስለሆነልኝ ያህ ብርታቴና ኃይሌ ነው። እሱ አምላኬ ነው፤ አወድሰዋለሁ፤ የአባቴ አምላክ ነው፤ እኔም ከፍ ከፍ አደርገዋለሁ።
እውነተኛውን አምላክ አሁኑኑ መፍራት ያለብን ለምንድን ነው?
11 ይሖዋ የግብፅን ወታደራዊ ኃይሎች በቀይ ባሕር ማጥፋቱ በአምላኪዎቹ ፊት ከፍ ከፍ እንዲል ከማድረጉም በላይ ስሙ በስፋት እንዲታወቅ አስችሏል። (ኢያሱ 2:9, 10፤ 4:23, 24) አዎን፣ ይህን አስደናቂ ተአምር በመፈጸሙ ምክንያት ስሙ አምላኪዎቻቸውን ለማዳን ሳይችሉ ከቀሩት ደካማ የግብፃውያን የሐሰት አማልክት በላይ እጅግ ከፍ ብሏል። ግብፃውያን በአማልክቶቻቸው፣ ሟች በሆነው ሰውና በወታደራዊ ኃይላቸው ላይ የነበራቸው ትምክህት መራራ ውድቀት አስከትሎባቸዋል። (መዝሙር 146:3) እስራኤላውያን ሕዝቦቹን በታላቅ ኃይል ነፃ ለሚያወጣ ሕያው አምላክ ያላቸውን ጤናማ ፍርሃት የሚያንጸባርቅ የውዳሴ መዝሙር እንዲዘምሩ መገፋፋታቸው አያስደንቅም!
(ዘፀአት 15:11) ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው? የምትፈራና የምትወደስ፣ ድንቅ ነገሮችን የምታደርግ አንተ ነህ።
(ዘፀአት 15:18) ይሖዋ ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይገዛል።
እውነተኛውን አምላክ አሁኑኑ መፍራት ያለብን ለምንድን ነው?
15 ከሙሴ ጋር በሰላም ተሻግረን ቢሆን ኖሮ “አቤቱ፣ በአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በምስጋና የተፈራህ፣ ድንቅንም የምታደርግ፣ በቅድስና የከበረ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?” ብለን ለመዘመር እንደምንገፋፋ አያጠራጥርም። (ዘጸአት 15:11) ከዚያ ዘመን ጀምሮ ባለፉት መቶ ዘመናት በሙሉ በዚህ መዝሙር የተገለጸው ስሜት ሲስተጋባ ኖሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በሆነው በራእይ መጽሐፍ ውስጥ ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ አንድ ታማኝ የቅቡዓን አገልጋዮች ቡድን ሲናገር “የእግዚአብሔርን ባሪያ የሙሴን ቅኔና የበጉን ቅኔ ይዘምራሉ” በማለት ይገልጻል። ይህ ታላቅ መዝሙር ምንድን ነው? “ሁሉን የምትገዛ ጌታ አምላክ ሆይ፣ ሥራህ ታላቅና ድንቅ ነው፤ የአሕዛብ ንጉሥ ሆይ፣ መንገድህ ጻድቅና እውነተኛ ነው፤ ጌታ ሆይ፣ የማይፈራህና ስምህን የማያከብር ማን ነው?”—ራእይ 15:2–4
16 ዛሬም ቢሆን የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች ብቻ ሳይሆን የጽድቅ ትእዛዛቱን ጭምር የሚያደንቁ ነፃ የወጡ አምላኪዎች አሉ። ከሁሉም ብሔራት የተውጣጡ ሰዎች የአምላክን የጽድቅ ሕግጋት ስለሚገነዘቡና በሥራም ላይ ስለሚያውሉ ከዚህ ከተበከለ ዓለም ተለይተው መንፈሳዊ ነፃነት አግኝተዋል። በየዓመቱ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከዚህ ብልሹ ዓለም ድነው ንጹሕና ሐቀኛ በሆነው የይሖዋ አምላኪዎች ድርጅት ውስጥ መኖር ጀምረዋል። በቅርቡም እሳታማ የሆነው የአምላክ ፍርድ በሐሰት ሃይማኖትና በቀሪው ክፉ ሥርዓት ላይ ከወረደ በኋላ ጽድቅ በሚሰፍንበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለዘላለም ይኖራሉ።
(ዘፀአት 15:20, 21) ከዚያም የአሮን እህት ነቢዪቱ ሚርያም አታሞ አነሳች፤ ሴቶቹም ሁሉ አታሞ እየመቱና እየጨፈሩ ተከተሏት። 21 ሚርያምም ከወንዶቹ ጋር እየተቀባበለች እንዲህ ስትል ዘመረች፦ “በክብር እጅግ ከፍ ከፍ ስላለ ለይሖዋ ዘምሩ። ፈረሱንና ፈረሰኛውን ባሕር ውስጥ ጣላቸው።”
it-2 454 አን. 1
ሙዚቃ
እስራኤላውያን አብዛኛውን ጊዜ በቡድን የሚዘምሩት እየተቀባበሉ የነበረ ይመስላል፤ አንዱ የመዘምራን ቡድን አንድ ስንኝ ሲዘምር ሁለተኛው ደግሞ ቀጣዩን ስንኝ ይዘምራል ወይም አንድ ዘማሪ ብቻውን ሲዘምር የመዘምራን ቡድኑ ተቀብሎት ይዘምራል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘እየተቀባበሉ’ እንደዘመሩ የሚናገረው ለዚህ ነው። (ዘፀ 15:21፤ 1ሳሙ 18:6, 7) እንደ መዝሙር 136 ያሉ አንዳንድ መዝሙሮች የተጻፉበት መንገድ ራሱ እንዲህ ያለ አዘማመር እንደሚከተሉ ያሳያል። በነህምያ ዘመን ስለነበሩት ምስጋና የሚያቀርቡ ሁለት ትላልቅ የዘማሪ ቡድኖች የተሰጠው መግለጫ እንዲሁም የኢየሩሳሌም ቅጥር በተመረቀበት ወቅት ያደረጉት ነገር ይህን የአዘማመር ዘይቤ እንደተከተሉ ይጠቁማል።—ነህ 12:31, 38, 40-42፤ መዝሙር የሚለውን ተመልከት።
it-2 698
ነቢዪት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢዪት ተብላ የተጠራችው የመጀመሪያዋ ሴት ሚርያም ነበረች። አምላክ በእሷ በኩል አንዳንድ መልእክቶችን ሳይናገር አልቀረም፤ ምናልባትም ይህን ያደረገው በመንፈስ መሪነት እንድትዘምር በማድረግ ሊሆን ይችላል። (ዘፀ 15:20, 21) በመሆኑም እሷና አሮን ሙሴን “ለመሆኑ ይሖዋ . . . በእኛስ በኩል አልተናገረም?” እንዳሉት ተገልጿል። (ዘኁ 12:2) እስራኤላውያን ከግብፅ ምድር በወጡበት ጊዜ “ሙሴን፣ አሮንንና ሚርያምን” እንደላከላቸው ይሖዋ ራሱ በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት ተናግሯል። (ሚክ 6:4) ሚርያም የአምላክን መልእክት ያስተላለፈች ቢሆንም ከአምላክ ጋር የነበራት ዝምድና ከወንድሟ ከሙሴ ያነሰ ነበር። ተገቢውን ቦታዋን ሳትጠብቅ በቀረችበት ወቅት አምላክ ከባድ ቅጣት ቀጥቷታል።—ዘኁ 12:1-15
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 16:13) በዚህም መሠረት ምሽት ላይ ድርጭቶች መጥተው ሰፈሩን አለበሱት፤ ጠዋት ላይም በሰፈሩ ውስጥ ሁሉ ጤዛ ወርዶ ነበር።
ይህን ያውቁ ኖሯል?
አምላክ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ በነበሩበት ጊዜ እነሱን ለመመገብ ድርጭቶችን የመረጠው ለምን ነበር?
እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ አምላክ እነሱን ሥጋ ለመመገብ በሁለት የተለያዩ አጋጣሚዎች በርካታ ድርጭቶችን ሰጥቷቸዋል።—ዘፀአት 16:13፤ ዘኍልቍ 11:31
ድርጭቶች 18 ሴንቲ ሜትር ገደማ ርዝመትና 100 ግራም ያህል ክብደት ያላቸው ትናንሽ ወፎች ናቸው። እነዚህ ወፎች የመራቢያ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉት በምዕራብ እስያና በአውሮፓ በሚገኙ በርካታ አካባቢዎች ነው። ድርጭቶች የክረምቱን ወቅት ለማሳለፍ ወደ ሰሜን አፍሪካና ወደ ዓረብ አገራት ይፈልሳሉ። የሚፈልሱበት ወቅት ሲደርስ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድርጭቶች የሜድትራንያንን ባሕር ምሥራቃዊ ዳርቻ አቋርጠው በሲና ባሕረ ገብ መሬት ላይ ይበራሉ።
ዘ ኒው ዌስትሚንስትር ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንደገለጸው ከሆነ ድርጭቶች “በፍጥነትና ቅልጥፍና ባለው መንገድ የሚበርሩ ከመሆኑም ሌላ ነፋሱ የሚነፍስበትን አቅጣጫ ተከትለው የሚጓዙ ወፎች ናቸው፤ ሆኖም ነፋሱ አቅጣጫ ከቀየረ ወይም ወፎቹ ለረጅም ሰዓት ከመብረራቸው የተነሳ ከዛሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ድርጭቶች መሬት ላይ ይወድቃሉ፤ መንቀሳቀስ አቅቷቸውም ባሉበት ይቆያሉ።” ጉዟቸውን ከመቀጠላቸው በፊት ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን መሬት ላይ መቆየት ይኖርባቸዋል፤ ይህ ደግሞ የአዳኞች ሲሳይ ያደርጋቸዋል። በ20ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ግብፅ ለምግብነት የሚሆኑ ሦስት ሚሊዮን ድርጭቶችን በየዓመቱ ለውጭ ገበያ ታቀርብ ነበር።
እስራኤላውያን ድርጭቶች የተመገቡባቸውን ሁለቱንም አጋጣሚዎች ከተመለከትን ጊዜው የጸደይ ወቅት እንደነበር እንረዳለን። ምንም እንኳ ድርጭቶች በዚህ ወቅት ላይ በሲና አካባቢ አዘውትረው የሚበርሩ ቢሆንም እነዚህ ወፎች እስራኤላውያን በሰፈሩባቸው አካባቢዎች እንዲወድቁ ለማድረግ ‘ነፋስ ያመጣው’ ይሖዋ ነው።—ዘኍልቍ 11:31
(ዘፀአት 16:32-34) ከዚያም ሙሴ እንዲህ አላቸው፦ “ይሖዋ እንዲህ ሲል አዟል፦ ‘ከግብፅ ምድር ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉት የሰጠኋችሁን ምግብ እንዲያዩ ከእሱ አንድ ኦሜር ሰፍራችሁ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ አስቀምጡ።’” 33 በመሆኑም ሙሴ አሮንን “ማሰሮ ወስደህ አንድ ኦሜር መና ጨምርበት፤ ለሚመጡት ትውልዶቻችሁ ሁሉ ተጠብቆ እንዲቆይ በይሖዋ ፊት አስቀምጠው” አለው። 34 አሮንም ይሖዋ ሙሴን ባዘዘው መሠረት ተጠብቆ እንዲቆይ መናውን በምሥክሩ ፊት አስቀመጠው።
የአንባቢያን ጥያቄዎች
ከግብፅ ከወጡ በኋላ ብዙም ሳይቆይ እስራኤላውያን ምግብን በተመለከተ ማጉረምረም ጀመሩ። በዚህም ምክንያት ይሖዋ መና ሰጣቸው። (ዘፀአት 12:17, 18፤ 16:1-5) በዚያን ወቅት ሙሴ አሮንን እንዲህ ሲል አዘዘው፦ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቆይም በእግዚአብሔር ፊት አስቀምጠው።” ዘገባው በመቀጠል “እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት [ጠቃሚ ሰነዶች በአስተማማኝ ሁኔታ የሚቀመጡበት መያዣ ነው] አስቀመጠው” በማለት ይገልጻል። (ዘፀአት 16:33, 34) በዚህ ጊዜ አሮን መና ሰብስቦ በማሰሮ ውስጥ እንዳስቀመጠ ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም መናው በምስክሩ ፊት እንዲቀመጥ ሙሴ ታቦቱን እስኪሠራና ጽላቶቹን በውስጡ እስኪያደርግ ድረስ መጠበቅ ሳያስፈልግ አይቀርም።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከነሐሴ 17-23
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 17–18
“ልካቸውን የሚያውቁ ወንዶች አሠልጥነው ኃላፊነት ይሰጣሉ”
(ዘፀአት 18:17, 18) በዚህ ጊዜ የሙሴ አማት እንዲህ አለው፦ “እያደረግክ ያለኸው ነገር መልካም አይደለም። 18 ይህ ሥራ ለአንተ ከባድ ሸክም ስለሚሆን አንተም ሆንክ ከአንተ ጋር ያለው ይህ ሕዝብ መድከማችሁ አይቀርም፤ ደግሞም ብቻህን ልትሸከመው አትችልም።
ሙሴ—አፍቃሪ ሰው
ሙሴ ወገኖቹ ለሆኑት እስራኤላውያንም ፍቅር እንደነበረው አሳይቷል። ሕዝቡ ይሖዋ እነሱን ለመምራት በሙሴ እንደሚጠቀም ስለተገነዘቡ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ይዘው ወደ እሱ ይመጡ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “እነርሱም በዙሪያው ከጧት እስከ ማታ ድረስ ቆሙ” ይላል። (ዘፀአት 18:13-16) የእስራኤላውያንን ችግር ቀኑን ሙሉ ሲያዳምጡ መዋል ለሙሴ ምን ያህል አድካሚ ሊሆን እንደሚችል አስብ! ሆኖም ሙሴ ሕዝቡን ይወድ ስለነበር እነሱን በመርዳቱ ደስተኛ ነበር።
(ዘፀአት 18:21, 22) ሆኖም ከመላው ሕዝብ መካከል አምላክን የሚፈሩትንና ብቃት ያላቸውን እንዲሁም አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት የማይፈልጉትንና እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች ምረጥ፤ እነዚህንም የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች አድርገህ በሕዝቡ ላይ ሹማቸው። 22 እነሱም የተለያዩ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ ሕዝቡን ይዳኙ፤ ከበድ ያሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሟቸው ወደ አንተ ያምጡ፤ ቀለል ያሉ ጉዳዮችን ግን ራሳቸው ይዳኙ። ሸክሙን እንዲጋሩህ በማድረግ በአንተ ላይ ያለውን ጫና አቅልል።
ደስተኛ ሕይወት ለመምራት መተማመን አስፈላጊ ነው
እነዚህ ሰዎች እምነት የሚጣልባቸው እንዲሆኑ የሚጠይቁ ኃላፊነቶችን ከመቀበላቸው በፊት አንዳንድ አምላካዊ ባሕርያትን ያሳዩ ሰዎች ናቸው። አምላክን የሚፈሩ ማለትም ለፈጣሪ ጤናማ የሆነ አክብሮታዊ ፍርሃት ያላቸውና እርሱን ላለማሳዘን የሚጠነቀቁ ሰዎች መሆናቸውን ቀደም ሲል ያረጋገጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች የአምላክን መሥፈርቶች ለመጠበቅ የተቻላቸውን ሁሉ እንዳደረጉ በግልጽ የሚታይ ነበር። የግፍን ረብ የጠሉ ሲሆን ይህም ሥልጣናቸውን አለአግባብ ከመጠቀም የሚያግዳቸው የሥነ ምግባር ጥንካሬ እንዳላቸው ያመለክታል። የግል ጥቅማቸውን ወይም የዘመዶቻቸውን አሊያም የወዳጆቻቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲሉ የተጣለባቸውን አደራ የማይበሉ ሰዎች ነበሩ።
(ዘፀአት 18:24, 25) ሙሴም ወዲያውኑ አማቱን በመስማት ያለውን ሁሉ አደረገ። 25 ሙሴም ከመላው እስራኤል ብቃት ያላቸውን ወንዶች መርጦ የሺህ አለቆች፣ የመቶ አለቆች፣ የሃምሳ አለቆችና የአሥር አለቆች አድርጎ በሕዝቡ ላይ ሾማቸው።
ጽኑ አቋም ቅኖችን ይመራቸዋል
ሙሴም እንዲሁ ልኩን የሚያውቅና ትሑት ሰው ነበር። አማቱ ዮቶር ሙሴ የሌሎችን ችግር ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት ራሱን እየጎዳ እንዳለ ሲገነዘብ አንዳንድ ኃላፊነቶችን ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች እንዲያካፍል መከረው። ሙሴም ያለበትን የአቅም ገደብ ተገንዝቦ የተሰጠውን ሐሳብ በእሺታ ተቀበለ። (ዘጸአት 18:17-26፤ ዘኁልቊ 12:3) ልኩን የሚያውቅ ሰው ለሌሎች ሥልጣን ለመስጠት ወደኋላ አይልም፤ ወይም ተገቢ የሆኑ የኃላፊነት ቦታዎችን ብቃት ላላቸው ሌሎች ወንዶች ቢሰጥ ሁሉ ነገር ከቁጥጥሩ ውጪ እንደሚሆን አድርጎ አያስብም። (ዘኁልቊ 11:16, 17, 26-29) ከዚህ ይልቅ ሌሎች በመንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ዝግጁ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 4:15) እኛስ እንዲህ መሆን አይገባንም?
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 17:11-13) ሙሴ እጆቹን ወደ ላይ አንስቶ በሚቆይበት ጊዜ ሁሉ እስራኤላውያን ያይሉ፣ እጆቹን በሚያወርድበት ጊዜ ግን አማሌቃውያን ያይሉ ነበር። 12 የሙሴ እጆች በዛሉ ጊዜ ድንጋይ ወስደው ከሥሩ አስቀመጡለት፤ እሱም በድንጋዩ ላይ ተቀመጠ። ከዚያም አሮንና ሁር አንዱ በአንደኛው በኩል፣ ሌላው ደግሞ በሌላኛው በኩል ሆነው እጆቹን ደገፉለት፤ በመሆኑም ፀሐይ እስከምትጠልቅበት ጊዜ ድረስ እጆቹ ባሉበት ጸኑ። 13 በዚህ መንገድ ኢያሱ አማሌቅንና ሕዝቦቹን በሰይፍ ድል አደረገ።
‘እጆቻችሁ አይዛሉ’
14 አሮን እና ሁር በውጊያው ወቅት ቃል በቃል የሙሴን እጅ ደግፈውለት ነበር። እኛም ሌሎችን መደገፍና መርዳት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለግ እንችላለን። ማንን መርዳት እንችላለን? የዕድሜ መግፋት፣ የጤና እክል፣ የቤተሰብ ተቃውሞ፣ ብቸኝነት ወይም የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት ከሚያስከትለው ተፈታታኝ ሁኔታ ጋር እየታገሉ ያሉ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን መርዳት እንችላለን። በተጨማሪም መጥፎ ነገር እንዲሠሩ ወይም በዚህ ሥርዓት በትምህርትም ይሁን በሙያቸው ጥሩ ደረጃ የሚባለው ቦታ ላይ እንዲደርሱ አሊያም ሀብት እንዲያሳድዱ ከፍተኛ ጫና የሚደርስባቸውን ወጣቶች ማበረታታት እንችላለን። (1 ተሰ. 3:1-3፤ 5:11, 14) ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር በመንግሥት አዳራሽ ውስጥም ሆነ በአገልግሎት ላይ ስትሆኑ አሊያም አብራችሁ ስትመገቡ ወይም በስልክ ስታወሩ ልባዊ አሳቢነት ልታሳዩ የምትችሉባቸውን መንገዶች ለማሰብ ሞክሩ።
(ዘፀአት 17:14) ይሖዋም ሙሴን እንዲህ አለው፦ “መታሰቢያ እንዲሆን ይህን በመጽሐፍ ጻፈው፤ ለኢያሱም ‘የአማሌቅን መታሰቢያ ከሰማይ በታች ሙሉ በሙሉ ጠራርጌ አጠፋለሁ’ በማለት ይህን ደግመህ ንገረው።”
it-1 406
የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑ መጻሕፍት ዝርዝር
መጽሐፍ ቅዱስን ስንመረምር እነዚህ የሙሴ መጻሕፍት መለኮታዊ ምንጭ እንዳላቸው፣ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፉ፣ የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል እንደሆኑና ከንጹሕ አምልኮ ጋር በተያያዘ አስተማማኝ መመሪያ እንደሚሰጡን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እናገኛለን። ሙሴ የእስራኤላውያን መሪ የሆነው በራሱ ተነሳሽነት አልነበረም፤ እንዲያውም መጀመሪያ ላይ ሙሴ ተልእኮውን ለመቀበል አመንትቶ ነበር። (ዘፀ 3:10, 11፤ 4:10-14) ሙሴን ያስነሳውና ተአምራት የመሥራት ችሎታ የሰጠው አምላክ ሲሆን የፈርዖን አስማተኛ ካህናት እንኳ ሙሴ ያደረገው ነገር መለኮታዊ ምንጭ እንዳለው አምነው ለመቀበል ተገደው ነበር። (ዘፀ 4:1-9፤ 8:16-19) ስለዚህ ሙሴ ሕዝባዊ ተናጋሪና ጸሐፊ የሆነው በራሱ ተነሳስቶ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ሙሴ ለሕዝቡ የተናገረውና ከዚያም የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍል የሆኑትን አንዳንድ መጻሕፍት የጻፈው በአምላክ ትእዛዝ እንዲሁም በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ነበር።—ዘፀ 17:14
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከነሐሴ 24-30
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 19–20
“አሥርቱ ትእዛዛት ለአንተ ምን ትርጉም አላቸው?”
(ዘፀአት 20:3-7) ከእኔ በቀር ሌሎች አማልክት አይኑሩህ። 4 “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። 5 አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤ 6 ሆኖም ለሚወዱኝና ትእዛዛቴን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ታማኝ ፍቅር የማሳይ አምላክ ነኝ። 7 “የአምላክህን የይሖዋን ስም በከንቱ አታንሳ፤ ምክንያቱም ይሖዋ ስሙን በከንቱ የሚያነሳውን ሳይቀጣ አይተወውም።
w89 11/15 5 አን. 6
አስርቱ ትእዛዛት ለአንተ ምን ትርጉም አላቸው?
የመጀመሪያዎቹ አራት ትእዛዛት ለይሖዋ ያለንን ግዴታ ያጎላሉ። (አንደኛ) ይሖዋ አሁንም ብቻውን መመለክ የሚፈልግ አምላክ ነው። (ማቴዎስ 4:10) (ሁለተኛ) አምላኪዎቹ በምስሎች መገልገል አይገባቸውም። (1 ዮሐንስ 5:21) (ሦስተኛ) የአምላክን ስም ትክክልና ክብር ባለው መንገድ መጠቀም ይኖርብናል እንጂ ማዋረድ ወይም ማቃለል አይገባንም። (ዮሐንስ 17:26፤ ሮሜ 10:13) (አራተኛ) ሕይወታችን ሁሉ በቅዱሳን ነገሮች ላይ ያተኮረ መሆን ይኖርበታል። ይህም ራስን ለማጽደቅ ከሚደረግ አካሄድና አኗኗር እንድናርፍ ወይም ሰንበት እንዲሆንልን ያስችለናል።—ዕብራውያን 4:9, 10
(ዘፀአት 20:8-11) “የሰንበትን ቀን ቅዱስ አድርገህ መጠበቅ እንዳለብህ አትርሳ። 9 ሥራህንና የምታከናውናቸውን ነገሮች በሙሉ በስድስት ቀን ሠርተህ አጠናቅ፤ 10 ሰባተኛው ቀን ግን ለአምላክህ ለይሖዋ ሰንበት ነው። በዚህ ቀን አንተም ሆንክ ወንድ ልጅህ ወይም ሴት ልጅህ፣ ወንድ ባሪያህም ሆነ ሴት ባሪያህ፣ የቤት እንስሳህም ሆነ በሰፈርህ ውስጥ ያለ የባዕድ አገር ሰው ምንም ሥራ አትሥሩ። 11 ምክንያቱም ይሖዋ ሰማያትን፣ ምድርን፣ ባሕርንና በውስጣቸው ያሉትን ነገሮች ሁሉ በስድስት ቀናት ውስጥ ሠርቶ ካጠናቀቀ በኋላ በሰባተኛው ቀን ማረፍ ጀምሯል። ይሖዋ የሰንበትን ቀን የባረከውና የቀደሰው ለዚህ ነው።
(ዘፀአት 20:12-17) “አምላክህ ይሖዋ በሚሰጥህ ምድር ላይ ዕድሜህ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር። 13 “አትግደል። 14 “አታመንዝር። 15 “አትስረቅ። 16 “በባልንጀራህ ላይ ምሥክር ሆነህ ስትቀርብ በሐሰት አትመሥክር። 17 “የባልንጀራህን ቤት አትመኝ። የባልንጀራህን ሚስት፣ ወንድ ባሪያውን፣ ሴት ባሪያውን፣ በሬውን ወይም አህያውን አሊያም የባልንጀራህ የሆነውን ማንኛውንም ነገር አትመኝ።”
w89 11/15 6 አን. 1-2
አስርቱ ትእዛዛት ለአንተ ምን ትርጉም አላቸው?
(አምስተኛ) ልጆች ለወላጆቻቸው መታዘዛቸው ዛሬም ለቤተሰብ አንድነትና ኅብረት እንደማዕዘን ድንጋይ ሆኖ ያገለግላል። የይሖዋንም በረከት ያስገኛል። ‘ይህ የተስፋ ቃል ያለው የመጀመሪያ ትእዛዝ’ በጣም ታላቅ ተስፋ ይዞልናል። ይህን ትእዛዝ መጠበቅ “መልካም እንዲሆንልህ” ከማስቻሉም በላይ “በምድር ላይ ዕድሜህን” ያረዝመዋል። (ኤፌሶን 6:1-3) በተለይ አሁን በዚህ ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ ላይ የምንኖር ስለሆነ እንዲህ ያለው አምላካዊ ታዛዥነት ለወጣቶች ያለመሞትን ተስፋ ይሰጣቸዋል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1፤ ዮሐንስ 11:26
ለጎረቤቶቻችን ያለን ፍቅር እንደ ግድያ፣ (ስድስተኛው) ምንዝር፣ (ሰባተኛው) ስርቆት (ስምንተኛው) እና በሐሰት መስካሪነት (ዘጠነኛው) ያሉ ጎጂ ድርጊት እንዳንፈጽምባቸው ያግደናል። (1 ዮሐንስ 3:10-12፤ ዕብራውያን 13:4፤ ኤፌሶን 4:28፤ ማቴዎስ 5:37፤ ምሳሌ 6:16-19) ይሁን እንጂ ልባችንን የሚገፋፋው ዓላማስ ምን መሆን አለበት? የሌላውን ንብረት መጎምጀትን የሚከለክለው (አሥረኛው) ትእዛዝ ሁልጊዜ ውስጣዊ ዓላማችን በይሖዋ ፊት የቀና እንዲሆን እንደሚፈልግብን ያስገነዝበናል።—ምሳሌ 21:2
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 19:5, 6) አሁንም ቃሌን በጥብቅ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ መላው ምድር የእኔ ስለሆነ እናንተ ከሌሎች ሕዝቦች ሁሉ የተመረጣችሁ ልዩ ንብረቶቼ ትሆናላችሁ። 6 እናንተ ለእኔ የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር ትሆናላችሁ።’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይህ ነው።”
it-2 687 አን. 1-2
ካህን
የክርስቲያኖች ክህነት። ይሖዋ እስራኤላውያን ቃል ኪዳኑን ከጠበቁ ለእሱ “የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር” እንደሚሆኑ ቃል ገብቶላቸው ነበር። (ዘፀ 19:6) ሆኖም የአሮንና የዘሮቹ ክህነት የሚቀጥለው ይህ ዝግጅት ጥላ የሆነለት ታላቅ ክህነት እስኪመጣ ድረስ ብቻ ነበር። (ዕብ 8:4, 5) ይህ ክህነት የሕጉ ቃል ኪዳን እስኪያበቃና አዲሱ ቃል ኪዳን እስኪመረቅ ድረስ ይጸናል። (ዕብ 7:11-14፤ 8:6, 7, 13) አምላክ ቃል በገባው መንግሥት ውስጥ ካህናት ሆነው ለማገልገል በመጀመሪያ ግብዣ የቀረበላቸው እስራኤላውያን ብቻ ነበሩ፤ ከጊዜ በኋላ ግብዣው ለአሕዛብም ቀረበ።—ሥራ 10:34, 35፤ 15:14፤ ሮም 10:21
ክርስቶስን የተቀበሉት ጥቂት አይሁዳውያን ብቻ ነበሩ፤ በመሆኑም ብሔሩ የእውነተኛው የካህናት መንግሥትና ቅዱስ ብሔር አባላት የሚሆኑ ሰዎችን ማስገኘት አልቻለም። (ሮም 11:7, 20) እስራኤላውያን ታማኝነታቸውን ስላጓደሉ አምላክ በነቢዩ ሆሴዕ አማካኝነት ከበርካታ መቶ ዘመናት በፊት እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸው ነበር፦ “እናንተ እውቀትን ስለናቃችሁ እኔም ካህናት ሆናችሁ እንዳታገለግሉኝ እንቃችኋለሁ፤ የአምላካችሁን ሕግ ስለረሳችሁ እኔም ልጆቻችሁን እረሳለሁ።” (ሆሴዕ 4:6) በተመሳሳይም ኢየሱስ ለአይሁድ መሪዎች “የአምላክ መንግሥት ከእናንተ ተወስዶ ፍሬውን ለሚያፈራ ሕዝብ ይሰጣል” ብሏቸው ነበር። (ማቴ 21:43) ያም ቢሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት በሙሴ ሕግ ሥር እንደሆነ እንዲሁም የአሮንና የዘሮቹ ክህነት እንዳላበቃ ተገንዝቦ ነበር፤ በመሆኑም ከሥጋ ደዌ የፈወሳቸውን ሰዎች ራሳቸውን ለካህን እንዲያሳዩና የሚጠበቅባቸውን መባ እንዲያቀርቡ ነግሯቸዋል።—ማቴ 8:4፤ ማር 1:44፤ ሉቃስ 17:14
(ዘፀአት 20:4, 5) “በላይ በሰማያት ወይም በታች በምድር አሊያም ከምድር በታች በውኃ ውስጥ ባለ በማንኛውም ነገር አምሳል የተቀረጸን ቅርጽ ወይም የተሠራን ምስል ለራስህ አታድርግ። 5 አትስገድላቸው፤ ተታለህም እነሱን አታገልግል፤ ምክንያቱም እኔ አምላክህ ይሖዋ እኔ ብቻ እንድመለክ የምፈልግና በሚጠሉኝ ሁሉ ላይ በአባቶች ስህተት የተነሳ በልጆቻቸው እንዲሁም በሦስተኛና በአራተኛ ትውልዶቻቸው ላይ ቅጣት የማመጣ አምላክ ነኝ፤
የዘፀአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
20:5—ይሖዋ ‘በአባቶች ኀጢአት የተነሣ’ ቀጣዮቹን ትውልዶች ‘የሚቀጣው’ እንዴት ነው? ኃላፊነት መቀበል የሚችልበት ዕድሜ ላይ የደረሰ ማንኛውም ግለሰብ ፍርድ የሚሰጠው ራሱ በፈጸመው ነገር ወይም በዝንባሌው መሠረት ነው። ሆኖም እስራኤላውያን ወደ ጣዖት አምልኮ ዘወር ባሉ ጊዜ ይህ አድራጎታቸው ያስከተለውን መዘዝ ቀጣዮቹ ትውልዶችም ቀምሰዋል። ብሔሩ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቸልተኛ በመሆኑ ታማኞቹ እስራኤላውያንም ጭምር ጽኑ አቋማቸውን ጠብቀው መኖር አስቸጋሪ ሆኖባቸዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ
ከነሐሴ 31–መስከረም 6
ከአምላክ ቃል የሚገኝ ውድ ሀብት | ዘፀአት 21–22
“ይሖዋ ለሕይወት ያለውን አመለካከት አንጸባርቁ”
(ዘፀአት 21:20) “አንድ ሰው ወንድ ባሪያውን ወይም ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታና እጁ ላይ ቢሞትበት ወይም ብትሞትበት ይህ ሰው የበቀል ቅጣት መቀጣት አለበት።
it-1 271
መምታት
ባሪያዎች ያሉት አንድ ዕብራዊ ወንድ ወይም ሴት ባሪያው ካመፁበት ወይም ካልታዘዙት በበትር እንዲመታቸው ይፈቀድለት ነበር። ሆኖም ባሪያው እጁ ላይ ከሞተበት የባሪያው ባለቤት ይቀጣል። ባሪያው የሞተው ከአንድ ወይም ከሁለት ቀን በኋላ ከሆነ ግን ይህ የባሪያው ባለቤት ነፍስ ለማጥፋት አስቦ እንዳልነበር የሚያሳይ ማስረጃ እንደሆነ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ጌታው ባሪያውን ‘በገንዘብ ስለገዛው’ እሱን የመቅጣት መብት አለው። አንድ ሰው የራሱን ውድ ንብረት ሙሉ በሙሉ በማጥፋት ለኪሳራ መዳረግ እንደማይፈልግ የታወቀ ነው። በተጨማሪም ባሪያው የሞተው ከአንድ ወይም ከዚያ ከሚበልጥ ቀን በኋላ ከሆነ የሞተው በመመታቱ ምክንያት ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። በመሆኑም ባሪያው ለአንድ ወይም ለሁለት ቀን በሕይወት ከቆየ ጌታው አይቀጣም።—ዘፀ 21:20, 21
(ዘፀአት 21:22, 23) “ሰዎች እርስ በርስ ሲታገሉ በአንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርሱባትና ያለጊዜዋ ብትወልድ ሆኖም ለሞት የተዳረገ ባይኖር ጉዳት ያደረሰው ሰው የሴትየዋ ባል የጠየቀውን ካሳ መክፈል አለበት፤ ፈራጆቹ የወሰኑበትን ካሳ መክፈል ይኖርበታል። 23 ሆኖም ለሞት የተዳረገ ካለ ሕይወት ስለ ሕይወት፣
ለሕይወት የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለህ?
16 የሁሉም ሰው ሕይወት በይሖዋ ፊት ውድ ነው። በእናቱ ማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃን ሕይወትም እንኳ በይሖዋ ዓይን ትልቅ ቦታ አለው። በሙሴ ሕግ መሠረት፣ አንድ ሰው ሳያስበው በእርጉዝ ሴት ላይ ጉዳት ቢያደርስና ሴትየዋ ወይም ልጇ ቢሞቱ ጉዳት ያደረሰውን ግለሰብ ይሖዋ በነፍስ ግድያ ይጠይቀው ነበር። ግለሰቡ ነፍስ ያጠፋው ሳያስበው ቢሆንም የሰው ሕይወት ስለጠፋ ካሳ መከፈል ነበረበት። (ዘፀአት 21:22, 23ን አንብብ።) አምላክ በማህፀን ውስጥ ያለ ሕፃንን ሕይወትም እንኳ እንደ ማንኛውም ሰው ሕይወት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። ከዚህ አንጻር አምላክ ስለ ውርጃ ምን አመለካከት ያለው ይመስልሃል? በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕፃናት በእናታቸው ማህፀን ውስጥ እንደሚገደሉ ሲመለከት አምላክ ምን የሚሰማው ይመስልሃል?
(ዘፀአት 21:28, 29) “አንድ በሬ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢወጋና የተወጋው ሰው ቢሞት በሬው በድንጋይ ተወግሮ ይገደል፤ ሥጋውም መበላት የለበትም። የበሬው ባለቤት ግን ከቅጣት ነፃ ነው። 29 በሬው የመዋጋት አመል እንዳለው የሚታወቅ ከሆነና ለባለቤቱም ስለ በሬው ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት ከነበረ በሬውን ሳይጠብቀው ቀርቶ አንድን ወንድ ወይም አንዲትን ሴት ቢገድል፣ በሬው በድንጋይ ይወገር፤ ባለቤቱም ይገደል።
ይሖዋ ‘ደኅንነትህ’ እንዲጠበቅ ይፈልጋል
በቤት እንስሳት አማካኝነት የሚደርስ ጉዳትን በተመለከተም ሕጉ ተፈጻሚነት ነበረው። አንድ በሬ አንድን ሰው በቀንዱ ወግቶ ቢገድል ባለቤቱ የሌሎች ሰዎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲል በሬውን ማስወገድ ነበረበት። ባለቤቱ የበሬውን ሥጋ ሊበላው ወይም ለሌሎች ሊሸጠው ስለማይችል በሬውን መግደሉ ትልቅ ኪሳራ ይሆንበት ነበር። ይሁንና አንድ በሬ በሰው ላይ ጉዳት እንዳደረሰ እያወቀ ባለቤቱ ሳያስረው ቢቀርስ? ይህ በሬ በሌላ ጊዜ አንድ ሰው ቢገድል፣ በሬውም ሆነ ባለቤቱ ይገደሉ ነበር። ይህ ሕግ ማንኛውም ሰው ከእንስሶቹ ጋር በተያያዘ ግድ የለሽ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ ይሆን ነበር።—ዘፀ. 21:28, 29
መንፈሳዊ ዕንቁዎችን በምርምር ማግኘት
(ዘፀአት 21:5, 6) ሆኖም ባሪያው ‘ጌታዬን፣ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ፤ ነፃ መውጣት አልፈልግም’ በማለት በአቋሙ ከጸና 6 ጌታው በእውነተኛው አምላክ ፊት ያቅርበው። ከዚያም ጌታው ወደ በሩ ወይም ወደ መቃኑ አምጥቶ ጆሮውን በወስፌ ይበሳዋል፤ እሱም ዕድሜውን ሙሉ ባሪያው ይሆናል።
ራስህን ለይሖዋ መወሰን ያለብህ ለምንድን ነው?
4 ክርስቲያን በመሆን ራስን ለአምላክ መወሰን በቁም ነገር ሊታይ የሚገባው ጉዳይ ነው። ይህ እርምጃ እንዲሁ ቃል መግባት ማለት ብቻ አይደለም። ይሁንና ራሳችንን መወሰናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል? ይህን ለመረዳት ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ቃል መግባታቸው ጥቅም የሚያስገኝላቸው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። ለዚህ አንዱ ምሳሌ በሰዎች መካከል የሚመሠረተው ጓደኝነት ነው። ጓደኛ ማፍራት የሚያስገኘውን ጥቅም ማግኘት የምትፈልግ ከሆነ ጓደኝነት የሚያስከትለውን ኃላፊነት መቀበል አለብህ። ይህም ሲባል ለጓደኛህ ቃል መግባትን ይጨምራል፤ ይህ ደግሞ ስለ ጓደኛህ ደኅንነት የማሰብ ግዴታ እንዳለብህ እንዲሰማህ ያደርጋል ማለት ነው። ወዳጅነትን በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት ታሪኮች ሁሉ ጎላ ብሎ የሚታየው ዳዊትና ዮናታን የነበራቸው ጓደኝነት ነው። እንዲያውም ጓደኝነታቸውን በተመለከተ ቃል ኪዳን ተገባብተው ነበር። (1 ሳሙኤል 17:57 እና 18:1, 3ን አንብብ።) በአሁኑ ጊዜ እንዲህ ያለ ቃል ኪዳን የሚገባቡት ከስንት አንድ ቢሆኑም ጓደኛሞች ቃላቸውን ሲፈጽሙ ወይም አንዳቸው ለሌላው ደኅንነት የማሰብ ግዴታ እንዳለባቸው ሲሰማቸው ጓደኝነታቸው ይጠናከራል።—ምሳሌ 17:17 NW፤ 18:24
5 ሰዎች እርስ በርስ ቃል መገባባታቸው ጥቅም እንደሚያስገኝላቸው የሚጠቁመውን ሌላውን ምሳሌ ደግሞ አምላክ ለእስራኤላውያን ከሰጣቸው ሕግ ውስጥ ማግኘት እንችላለን። አንድ አገልጋይ ጥሩ ለሆነው ጌታው ለዘለቄታው ባሪያ በመሆን ደኅንነት ማግኘት ከፈለገ ዘላቂና ጽኑ የሆነ ስምምነት ማድረግ ይችል ነበር። ሕጉ እንደሚከተለው ይላል፦ “አገልጋዩ፤ ‘ጌታዬን፤ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ ነጻ ሆኜ አልሄድም’ ቢል፣ ጌታው ወደ ዳኞች ይውሰደው፤ ወደ በር ወይም ወደ በሩ መቃን ወስዶ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም ዕድሜ ዘመኑን የእርሱ አገልጋይ ይሆናል።”—ዘፀ. 21:5, 6
(ዘፀአት 21:14) አንድ ሰው በባልንጀራው ላይ እጅግ ቢቆጣና ሆን ብሎ ቢገድለው ይህን ሰው ከመሠዊያዬ አጠገብም እንኳ ቢሆን ወስደህ ግደለው።
it-1 1143
ቀንድ
በዘፀአት 21:14 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ካህንም እንኳ ቢሆን ነፍስ ካጠፋ መገደል እንዳለበት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል፤ ወይም ደግሞ ሆን ብሎ ሕይወት ያጠፋ ሰው የመሠዊያውን ቀንዶች ቢይዝ እንኳ ከቅጣት እንደማያመልጥ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።—ከ1ነገ 2:28-34 ጋር አወዳድር።
የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ