የጥናት ርዕስ 4
“ይህ መንፈስ ራሱ . . . ይመሠክራል”
“የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።”—ሮም 8:16
መዝሙር 25 ልዩ ንብረት
ማስተዋወቂያa
1-2. በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ ምን አስደናቂ ነገር ተከናወነ?
ጊዜው 33 ዓ.ም. ሲሆን የጴንጤቆስጤ በዓል የሚከበርበት ቀን ነው። በዚህ ዕለት ማለትም እሁድ ጠዋት፣ በኢየሩሳሌም በሚገኝ አንድ ቤት ደርብ ላይ 120 የሚያህሉ ደቀ መዛሙርት ተሰባስበዋል። (ሥራ 1:13-15፤ 2:1) ከጥቂት ቀናት በፊት ኢየሱስ ለእነዚህ ደቀ መዛሙርት፣ ለየት ያለ ስጦታ ስለሚሰጣቸው በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ ነግሯቸው ነበር። (ሥራ 1:4, 5) ታዲያ በዚህ ዕለት ምን ተከናወነ?
2 “ድንገትም እንደ ኃይለኛ ነፋስ ያለ ድምፅ ከሰማይ መጣ።” ድምፁ ተቀምጠውበት የነበረውን ቤት ሞላው። ከዚያም “የእሳት ምላሶች የሚመስሉ” ነገሮች በደቀ መዛሙርቱ አናት ላይ ታዩ፤ በዚህ ጊዜ “ሁሉም በመንፈስ ቅዱስ ተሞሉ።” (ሥራ 2:2-4) ይሖዋ በእነዚያ ደቀ መዛሙርት ላይ ቅዱስ መንፈሱን ያፈሰሰው እንዲህ ባለ አስደናቂ መንገድ ነበር። (ሥራ 1:8) በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡትናb ከኢየሱስ ጋር በሰማይ የመግዛት ተስፋ የተሰጣቸው የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት እነዚህ ክርስቲያኖች ናቸው።
አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ የሚቀባው እንዴት ነው?
3. በጴንጤቆስጤ ዕለት ተሰባስበው የነበሩት ደቀ መዛሙርት በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀቡ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያስቻላቸው ምንድን ነው?
3 በዚያ ዕለት በደርብ ላይ ከተሰበሰቡት ደቀ መዛሙርት አንዱ ብትሆን የተከናወነውን ነገር ፈጽሞ እንደማትረሳው አያጠራጥርም። የእሳት ምላስ የሚመስል ነገር አናትህ ላይ ያረፈ ሲሆን በልሳን መናገር ጀመርክ! (ሥራ 2:5-12) በመንፈስ ቅዱስ እንደተቀባህ ምንም ዓይነት ጥርጣሬ አያድርብህም። ይሁንና ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ በመንፈስ ቅዱስ የሚቀቡት እንዲህ ባለ አስደናቂ መንገድ ነው? ደግሞስ ይህ የሚሆነው በሕይወታቸው ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው? አይደለም። ይህን እንዴት እናውቃለን?
4. በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በሙሉ ሰማያዊ ጥሪያቸውን ያገኙት በሕይወታቸው ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነበር? አብራራ።
4 እስቲ በመጀመሪያ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ስለሚቀባበት ጊዜ እንመልከት። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡት፣ 120 ገደማ የሚሆኑት እነዚህ ክርስቲያኖች ብቻ አልነበሩም። በዚያው ዕለት ወደ በኋላ ላይ 3,000 የሚያህሉ ሌሎች ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ ቃል የገባውን መንፈስ ቅዱስ ተቀብለዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች የተቀቡት ሲጠመቁ ነው። (ሥራ 2:37, 38, 41) ከዚያ በኋላ ባሉት ዓመታት ግን ሁሉም ክርስቲያኖች፣ በተጠመቁበት ወቅት በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል ማለት አይደለም። ሳምራውያን በመንፈስ የተቀቡት ከተጠመቁ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ነው። (ሥራ 8:14-17) ቆርኔሌዎስና ቤተሰቡ ደግሞ የተቀቡት ገና ሳይጠመቁ ነበር፤ በእርግጥ ይህ የተለመደ ሁኔታ አይደለም።—ሥራ 10:44-48
5. በ2 ቆሮንቶስ 1:21, 22 መሠረት አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባ ምን ያጋጥመዋል?
5 እስቲ አሁን ደግሞ አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባ ምን እንደሚያጋጥመው እንመልከት። በመንፈስ የተቀቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይሖዋ እነሱን መምረጡን መጀመሪያ ላይ መቀበል ይከብዳቸው ይሆናል። ‘አምላክ እኔን የመረጠኝ ለምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ይፈጠርባቸው ይሆናል። ሌሎች ግን እንዲህ ላይሰማቸው ይችላል። ግለሰቡ የሚኖረው ስሜት ምንም ይሁን ምን ሐዋርያው ጳውሎስ ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለሚያጋጥማቸው ነገር ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ካመናችሁ በኋላ በእሱ አማካኝነት፣ ቃል በተገባው መንፈስ ቅዱስ ታትማችኋል፤c ይህም . . . ለውርሻችን አስቀድሞ የተሰጠ ማረጋገጫ ነው።” (ኤፌ. 1:13, 14 ግርጌ) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም እነዚህ ክርስቲያኖች መመረጣቸውን ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ እንዲሆኑ ያደርጋል። ከዚህ አንጻር መንፈስ ቅዱስ፣ ወደፊት በምድር ላይ ሳይሆን በሰማይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ እንዲተማመኑ ለማድረግ ለእነዚህ ክርስቲያኖች የሚሰጣቸው “ማረጋገጫ [ዋስትና ወይም መያዣ]” ነው።—2 ቆሮንቶስ 1:21, 22ን አንብብ።
6. አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ሰማያዊ ሽልማቱን ለማግኘት ምን ማድረግ ይኖርበታል?
6 አንድ ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ስለተቀባ ብቻ ሰማያዊ ሽልማቱን በእርግጠኝነት ያገኛል ማለት ነው? አይደለም። ይህ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ለመሄድ እንደተመረጠ እርግጠኛ ነው። ያም ቢሆን የሚከተለውን ማሳሰቢያ ማስታወስ ይኖርበታል፦ “ወንድሞች፣ መጠራታችሁንና መመረጣችሁን አስተማማኝ ለማድረግ ከበፊቱ ይበልጥ ትጉ፤ እነዚህን ነገሮች የምታደርጉ ከሆነ ፈጽሞ አትወድቁም።” (2 ጴጥ. 1:10) ከዚህ ለማየት እንደሚቻለው አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ወደ ሰማይ ለመሄድ ቢመረጥም ወይም ቢጠራም፣ ሽልማቱን የሚያገኘው ታማኝ ሆኖ ከጸና ብቻ ነው።—ፊልጵ. 3:12-14፤ ዕብ. 3:1፤ ራእይ 2:10
አንድ ሰው በመንፈስ መቀባቱን የሚያውቀው እንዴት ነው?
7. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ጥሪ ማግኘታቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው?
7 አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ ማግኘቱን የሚያውቀው እንዴት ነው? ጳውሎስ ‘ቅዱሳን እንዲሆኑ ለተጠሩት’ በሮም ለሚገኙ ክርስቲያኖች የጻፈው ደብዳቤ ለዚህ ግልጽ መልስ ይሆናል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ዳግመኛ ለፍርሃት የሚዳርጋችሁን የባርነት መንፈስ አልተቀበላችሁም፤ ከዚህ ይልቅ አምላክ ልጆቹ አድርጎ እንዲወስዳችሁ የሚያስችል መንፈስ አግኝታችኋል፤ ይህም መንፈስ ‘አባ፣ አባት!’ ብለን እንድንጣራ ይገፋፋናል። የአምላክ ልጆች መሆናችንን ይህ መንፈስ ራሱ ከመንፈሳችን ጋር ሆኖ ይመሠክራል።” (ሮም 1:7፤ 8:15, 16) ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ጥሪ ማግኘታቸውን አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ግልጽ ያደርግላቸዋል።—1 ተሰ. 2:12
8. ቅቡዓን ክርስቲያኖች መቀባታቸውን በተመለከተ የሌላ አካል ማረጋገጫ እንደማያስፈልጋቸው 1 ዮሐንስ 2:20, 27 የሚያሳየው እንዴት ነው?
8 ይሖዋ፣ ሰማያዊ ጥሪ ያቀረበላቸው ክርስቲያኖች ስለዚህ ጉዳይ በልባቸው ውስጥ አንዳች ጥርጣሬ እንዳያድር ያደርጋል። (1 ዮሐንስ 2:20, 27ን አንብብ።) በእርግጥ እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ይሖዋ በጉባኤ አማካኝነት የሚሰጠውን ትምህርት ማግኘት አለባቸው። ይሁንና ለመቀባታቸው ማረጋገጫ የሚሰጣቸው ሌላ አካል አያስፈልጋቸውም። ይሖዋ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ኃይል ይኸውም ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም መቀባታቸውን በማያሻማ መንገድ አረጋግጦላቸዋል!
‘ዳግመኛ ተወልደዋል’
9. አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባ በኤፌሶን 1:18 ላይ እንደተገለጸው ምን ዓይነት ለውጥ ያጋጥመዋል?
9 በዛሬው ጊዜ ያሉ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች፣ አምላክ አንድን ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባው ግለሰቡ ምን እንደሚያጋጥመው መረዳት ይከብዳቸው ይሆናል። ይህም የሚያስገርም አይደለም፤ ምክንያቱም እነሱ ያለፉበት ነገር አይደለም። አምላክ ሰዎችን የፈጠረው በሰማይ ሳይሆን በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። (ዘፍ. 1:28፤ መዝ. 37:29) ሆኖም ይሖዋ ወደ ሰማይ ሄደው በዚያ እንዲኖሩ አንዳንዶችን መርጧል። በመሆኑም እነዚህን ሰዎች ሲቀባቸው፣ በሰማይ የመኖር ጉጉት እንዲያድርባቸው ሲል በተስፋቸውና በአመለካከታቸው ላይ ትልቅ ለውጥ እንዲፈጠር ያደርጋል።—ኤፌሶን 1:18ን አንብብ።
10. “ዳግመኛ መወለድ” ሲባል ምን ማለት ነው? (የግርጌ ማስታወሻውንም ተመልከት።)
10 ክርስቲያኖች በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ‘ዳግመኛ ይወለዳሉ’ ወይም ‘ከላይ ይወለዳሉ።’d “ዳግመኛ መወለድ” ወይም ‘ከመንፈስ መወለድ’ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ፣ በመንፈስ ቅዱስ ያልተቀባ ሰው ሙሉ በሙሉ እንዲረዳው ማድረግ የማይቻል ነገር መሆኑን ኢየሱስ ተናግሯል።—ዮሐ. 3:3-8 ግርጌ
11. አንድ ሰው ሲቀባ በአስተሳሰቡ ላይ የሚፈጠረውን ለውጥ አብራራ።
11 ወደ ሰማይ የሚሄዱ ክርስቲያኖች በመንፈስ ሲቀቡ በአስተሳሰባቸው ላይ ምን ለውጥ ያጋጥማቸዋል? እነዚህ ክርስቲያኖች በይሖዋ መንፈስ ከመቀባታቸው በፊት፣ በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ይሖዋ ክፋትን ሁሉ አስወግዶ ይህችን ምድር ገነት የሚያደርግበትን ጊዜ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ምናልባትም በሞት የተለያቸውን የቤተሰብ አባል ወይም ወዳጃቸውን በትንሣኤ ሲቀበሉ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸው ነበር። በመንፈስ ከተቀቡ በኋላ ግን አስተሳሰባቸው ይቀየራል። ለምን? በምድር ላይ የመኖር ተስፋ ስላላረካቸው አይደለም። አስተሳሰባቸው የተለወጠው ጭንቀት ወይም መከራ ስለበዛባቸው አይደለም። በምድር ላይ ለዘላለም መኖር አሰልቺ እንደሆነ ተሰምቷቸው በድንገት ሐሳባቸውን ስለቀየሩም አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት አስተሳሰባቸውንና ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ተስፋ ስለለወጠው ነው።
12. በ1 ጴጥሮስ 1:3, 4 መሠረት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ተስፋቸው ምን ይሰማቸዋል?
12 በመንፈስ ቅዱስ የተቀባ ክርስቲያን ይህን ውድ መብት ለማግኘት እንደማይበቃ ይሰማው ይሆናል። ይሁንና ይሖዋ እንደመረጠው ለቅጽበትም እንኳ አይጠራጠርም። ስለ ወደፊት ተስፋው ሲያስብ ልቡ በደስታና በአድናቆት ይሞላል።—1 ጴጥሮስ 1:3, 4ን አንብብ።
13. ቅቡዓን ክርስቲያኖች በምድር ላይ ስለሚመሩት ሕይወት ምን ይሰማቸዋል?
13 ይህ ሲባል ግን ቅቡዓኑ መሞት ይፈልጋሉ ማለት ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ሰጥቶናል። የቅቡዓንን ሥጋዊ አካል ከድንኳን ጋር በማነጻጸር እንዲህ ብሏል፦ “እንዲያውም በዚህ ድንኳን ውስጥ ያለነው እኛ ከባድ ሸክም ተጭኖን እንቃትታለን፤ ምክንያቱም ዘላለማዊው ሕይወት ሟች የሆነውን አካል እንዲተካ ይህን ድንኳን ማውለቅ ሳይሆን ሰማያዊውን መኖሪያ መልበስ እንፈልጋለን።” (2 ቆሮ. 5:4) እነዚህ ክርስቲያኖች ይሄኛው ሕይወት ስለሰለቻቸው ቶሎ እንዲያከትም ይፈልጋሉ ማለት አይደለም። እንዲያውም በሕይወታቸው የሚደሰቱ ከመሆኑም ሌላ እያንዳንዱን ቀን ከቤተሰባቸውና ከወዳጆቻቸው ጋር በይሖዋ አገልግሎት ማሳለፍ ይፈልጋሉ። ያም ሆኖ በየትኛውም እንቅስቃሴ ሲካፈሉ፣ ወደፊት የሚጠብቃቸው አስደናቂ ተስፋ ከአእምሯቸው አይጠፋም።—1 ቆሮ. 15:53፤ 2 ጴጥ. 1:4፤ 1 ዮሐ. 3:2, 3፤ ራእይ 20:6
ይሖዋ በመንፈስ ቀብቶሃል?
14. አንድ ሰው በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን የትኞቹ ነገሮች አያረጋግጡም?
14 ምናልባት አንተም ‘በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቼ ይሆን?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮብህ ይሆናል። ከሆነ ልታስብባቸው የሚገቡ አንዳንድ ጥያቄዎች ከዚህ ቀጥሎ ቀርበዋል፦ ‘የይሖዋን ፈቃድ የማድረግ ከፍተኛ ፍላጎት አለህ? በስብከቱ ሥራ የተለየ ቅንዓት እንዳለህ ይሰማሃል? “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” መቆፈር የሚያስደስትህ ትጉ የአምላክ ቃል ተማሪ ነህ? (1 ቆሮ. 2:10) ይሖዋ በስብከቱ ሥራ ግሩም ውጤት እንድታገኝ እንደረዳህ ይሰማሃል? ሌሎችን በመንፈሳዊ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለብህ ከልብህ ይሰማሃል? ይሖዋ በሕይወትህ ውስጥ በተለያዩ መንገዶች እንደረዳህ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ተመልክተሃል?’ ታዲያ ለእነዚህ ጥያቄዎች በልበ ሙሉነት “አዎ” የሚል መልስ የምትሰጥ ከሆነ ሰማያዊ ጥሪ አለህ ማለት ነው? አይደለም። ለምን? ምክንያቱም ቅቡዓን ሆኑም አልሆኑ ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች እንዲህ ያለ ስሜት ሊሰማቸው ይችላል። ደግሞም ተስፋቸው ምንም ይሁን ምን ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሁሉም አገልጋዮቹ እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማከናወን እንዲችሉ ሊረዳቸው ይችላል። እንዲያውም በመንፈስ ቅዱስ ስለ መቀባትህ ጥያቄ የሚፈጠርብህ ከሆነ ይህ በራሱ እንዲህ ዓይነት ጥሪ እንዳላገኘህ ያሳያል። ይሖዋ የጠራቸው ሰዎች ስለ መቀባታቸው ጥርጣሬ አይገባቸውም! ጥሪውን ማግኘታቸውን በእርግጠኝነት ያውቃሉ!
15. የአምላክን መንፈስ ያገኙ ሁሉ ወደ ሰማይ ለመሄድ ተመርጠዋል ማለት እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን?
15 መንፈስ ቅዱስ የተሰጣቸው በርካታ የእምነት ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተጠቅሰዋል፤ ያም ሆኖ እነዚህ ሰዎች በሰማይ የመኖር ተስፋ አልነበራቸውም። ዳዊት ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ያገኘ ሰው ነበር። (1 ሳሙ. 16:13) መንፈስ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ጥልቅ ነገሮች መረዳት እንዲችል እንዲሁም አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትን እንዲጽፍ ረድቶታል። (ማር. 12:36) ያም ቢሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንደተናገረው ዳዊት “ወደ ሰማያት አልወጣም።” (ሥራ 2:34) መጥምቁ ዮሐንስም ‘በመንፈስ ቅዱስ የተሞላ’ ሰው ነበር። (ሉቃስ 1:13-16) ኢየሱስ፣ ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ ሰው እንዳልተነሳ ተናግሯል፤ ይሁንና የሰማያዊው መንግሥት ወራሽ እንደማይሆን ገልጿል። (ማቴ. 11:10, 11) ይሖዋ ለእነዚህ ወንዶች ቅዱስ መንፈሱን በመስጠት አስደናቂ ነገሮችን ማከናወን እንዲችሉ ረድቷቸዋል፤ ሆኖም በሰማይ ሕይወት እንዲያገኙ በመንፈሱ አማካኝነት አልመረጣቸውም። ታዲያ እነዚህ ሰዎች በሰማይ የሚገዙትን የአምላክ አገልጋዮች ያህል ታማኝ አልነበሩም ማለት ነው? በፍጹም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ፣ ከሞት ተነስተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ሰጥቷቸዋል ማለት ነው።—ዮሐ. 5:28, 29፤ ሥራ 24:15
16. በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች የትኛውን ሽልማት ይጠባበቃሉ?
16 በዛሬው ጊዜ የሚገኙ አብዛኞቹ የአምላክ አገልጋዮች በሰማይ የመኖር ተስፋ የላቸውም። እንደ አብርሃም፣ ሣራ፣ ዳዊት፣ መጥምቁ ዮሐንስ እንዲሁም በጥንት ዘመን እንደኖሩ ሌሎች በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ሁሉ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮችም የአምላክ መንግሥት ተገዢዎች ሆነው በምድር ላይ ለመኖር በጉጉት ይጠባበቃሉ።—ዕብ. 11:10
17. በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን?
17 በዛሬው ጊዜ ከአምላክ ሕዝቦች መካከል የተወሰኑት፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች በመሆናቸው አንዳንድ ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም። (ራእይ 12:17) ለምሳሌ፣ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ለራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? በጉባኤህ ያለ አንድ ሰው በጌታ ራት ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ ቢጀምር ለግለሰቡ ምን አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? በመንፈስ እንደተቀቡ የሚናገሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድ ጉዳዩ ሊያሳስብህ ይገባል? የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን።
a በ33 ዓ.ም. ከዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት አንስቶ ይሖዋ ለአንዳንድ ክርስቲያኖች አስደናቂ የሆነ ተስፋ ይኸውም በሰማይ ከልጁ ጋር የመግዛት መብት ሰጥቷቸዋል። ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች ለዚህ አስደናቂ መብት መመረጣቸውን የሚያውቁት እንዴት ነው? አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት ጥሪ ሲቀበል ምን ለውጥ ያጋጥመዋል? ይህ ርዕስ በጥር 2016 መጠበቂያ ግንብ ላይ በወጣ ትምህርት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከላይ ለተጠቀሱት ትኩረት የሚስቡ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በመንፈስ ቅዱስ መቀባት። ይሖዋ በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የሚገዙ ሰዎችን ለመምረጥ ቅዱስ መንፈሱን ይጠቀማል። አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት ለእነዚህ ሰዎች ስለ ወደፊት ተስፋቸው “አስቀድሞ . . . ማረጋገጫ” ይሰጣቸዋል። (ኤፌ. 1:13, 14) እነዚህ ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማት ያላቸው መሆኑን መንፈስ ቅዱስ ‘እንደሚመሠክርላቸው’ ወይም ግልጽ እንደሚያደርግላቸው መናገር ይችላሉ።—ሮም 8:16
c ተጨማሪ ማብራሪያ፦ መታተም። ይህ የመጨረሻው ማኅተም አይደለም፤ አንድ ግለሰብ የመጨረሻው ማኅተም የሚደረግበት፣ በታማኝነት ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አሊያም ታላቁ መከራ ከመምጣቱ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ነው።—ኤፌ. 4:30፤ ራእይ 7:2-4፤ በሚያዝያ 2016 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።
d “ዳግመኛ መወለድ” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት የሚያዝያ 1, 2009 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 3-12ን ተመልከት።
መዝሙር 27 የአምላክ ልጆች መገለጥ
e የሥዕሉ መግለጫ፦ በእምነታችን ምክንያት የታሰርንም ሆነ እውነትን የመስበክና የማስተማር ነፃነት ያለን ክርስቲያኖች፣ ሁላችንም በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር በምድር ላይ ለመኖር ተስፋ እናደርጋለን።