የጥናት ርዕስ 25
“እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ”
“እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ ደግሞም እንከባከባቸዋለሁ።”—ሕዝ. 34:11
መዝሙር 105 “አምላክ ፍቅር ነው”
ማስተዋወቂያa
1. ይሖዋ ከምታጠባ እናት ጋር ራሱን ያመሳሰለው ለምንድን ነው?
“እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች?” ይሖዋ ይህን ጥያቄ ያቀረበው በነቢዩ ኢሳይያስ ዘመን ነበር። አምላክ ሕዝቡን “እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም” ብሏቸዋል። (ኢሳ. 49:15) አምላክ ራሱን ከእናት ጋር አነጻጽሮ የሚናገረው ብዙ ጊዜ አይደለም። በዚህ ወቅት ግን እንዲህ አድርጓል። ይሖዋ፣ ለአገልጋዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅር ለመግለጽ በእናትና በልጇ መካከል ያለውን ዝምድና ተጠቅሟል። አብዛኞቹ እናቶች ሃስሚን የተባለች እህት በተናገረችው ሐሳብ ይስማማሉ፤ እንዲህ ብላለች፦ “ልጃችሁን ስታጠቡ ከልጃችሁ ጋር ዕድሜ ልክ የሚዘልቅ በጣም ልዩ የሆነ ትስስር ትፈጥራላችሁ።”
2. ይሖዋ ከልጆቹ መካከል አንዱ ከእሱ ሲርቅ ምን ይሰማዋል?
2 ይሖዋ ከልጆቹ መካከል አንዱም እንኳ ቢሆን በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘቱንና በስብከቱ ሥራ መሳተፉን ሲያቆም ያስተውላል። ከዚህ አንጻር፣ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ አገልጋዮቹ በመንፈሳዊ ሲቀዘቅዙb ምን ያህል ስሜቱ እንደሚጎዳ ማሰብ አይከብድም።
3. የይሖዋ ፍላጎት ምንድን ነው?
3 በመንፈሳዊ ከቀዘቀዙ ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መካከል ብዙዎቹ ወደ ጉባኤው ይመለሳሉ፤ በመመለሳቸውም በጣም ደስ ይለናል! ይሖዋ እነዚህ አስፋፊዎች እንዲመለሱ ይፈልጋል፤ የእኛም ፍላጎት ይኸው ነው። (1 ጴጥ. 2:25) ታዲያ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው? የዚህን ጥያቄ መልስ ከመመርመራችን በፊት፣ አንዳንዶች ስብሰባ ላይ መገኘትና በአገልግሎት መካፈል የሚያቆሙት ለምን እንደሆነ መመልከታችን ጠቃሚ ነው።
አንዳንዶች ይሖዋን ማገልገል የሚያቆሙት ለምንድን ነው?
4. አንዳንዶች ሰብዓዊ ሥራቸው ምን ተጽዕኖ አሳድሮባቸዋል?
4 አንዳንዶች በሰብዓዊ ሥራቸው ከሚገባው በላይ ተጠምደዋል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የሚኖር ሃንግc የተባለ ወንድም “በሥራዬ ከልክ በላይ ተጠላልፌ ነበር” በማለት ተናግሯል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “‘በቁሳዊ ነገሮች በደንብ ከተደላደልኩ ይሖዋን በተሻለ መንገድ ማገልገል እችላለሁ’ የሚል የተሳሳተ አመለካከት ነበረኝ። በመሆኑም ተጨማሪ ሰዓት መሥራት ጀመርኩ። በተደጋጋሚ ከስብሰባዎች እቀር ጀመር፤ ውሎ አድሮም ከናካቴው ስብሰባ መሄዴን ተውኩ። የሰይጣን ዓላማ በዚህ ዓለም ላይ ያሉ ነገሮችን ተጠቅሞ ሰዎችን ቀስ በቀስ ከአምላክ ማራቅ ነው።”
5. አንዲት እህት ችግሮች ሲደራረቡባት ምን አድርጋለች?
5 አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ደግሞ ተደራራቢ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል። በብሪታንያ የምትኖረውን አን የተባለች እህት እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ አን የአምስት ልጆች እናት ናት። እንዲህ ብላለች፦ “አንደኛው ልጄ ሲወለድ ጀምሮ የአካል ጉዳተኛ ነው። ከጊዜ በኋላ ደግሞ አንዷ ልጄ ተወገደች፤ ሌላኛው ልጄ ደግሞ የአእምሮ ሕመምተኛ ሆነ። መንፈሴ ከመደቆሱ የተነሳ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና መስበክ አቆምኩ። ውሎ አድሮም ቀዘቀዝኩ።” ለአንና ለቤተሰቧ እንዲሁም ተመሳሳይ ችግሮች ለገጠሟቸው ሌሎች ክርስቲያኖች ከልብ እናዝናለን!
6. አንድ ሰው በቆላስይስ 3:13 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ አለማድረጉ ከይሖዋ ሕዝቦች ሊያርቀው የሚችለው እንዴት ነው?
6 ቆላስይስ 3:13ን አንብብ። አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የእምነት ባልንጀራቸው በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ተጎድተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በወንድማችን ወይም በእህታችን ‘ቅር እንድንሰኝ’ የሚያደርገን ነገር ሊያጋጥመን እንደሚችል ጠቁሟል። ሌላው ቀርቶ ፍትሕ የጎደለው ነገር ይፈጸምብን ይሆናል። ካልተጠነቀቅን እንዲህ ያለው ነገር በምሬት እንድንዋጥ ሊያደርገን ይችላል። ምሬት ደግሞ አንድን ሰው ቀስ በቀስ ከይሖዋ ሕዝቦች ሊያርቀው ይችላል። በደቡብ አሜሪካ የሚኖረው ፓብሎ የደረሰበትን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይህ ወንድም በሐሰት ስለተከሰሰ በጉባኤ ውስጥ የነበረውን የአገልግሎት መብት አጣ። ታዲያ ፓብሎ ምን አደረገ? “በጣም ስለተበሳጨሁ ቀስ በቀስ ከጉባኤው እየራቅሁ ሄድኩ” ብሏል።
7. የጥፋተኝነት ስሜት በአንድ ሰው ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
7 በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ቀደም ሲል የአምላክን ሕግ በመጣሱ ምክንያት ለረጅም ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ይሆናል፤ ግለሰቡ አምላክ ሊወደው እንደማይችል ይሰማው ይሆናል። ይህ ሰው ንስሐ ገብቶ ምሕረት ቢደረግለትም እንኳ ከአምላክ ሕዝቦች እንደ አንዱ ሊቆጠር እንደማይገባው ሊሰማው ይችላል። ፍራንሲስኮ የተባለ ወንድም እንደዚህ ተሰምቶት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “የፆታ ብልግና በመፈጸሜ ወቀሳ ተሰጥቶኝ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ በስብሰባዎች ላይ መገኘቴን ቀጥዬ ነበር፤ ሆኖም ከይሖዋ ሕዝቦች እንደ አንዱ መቆጠር እንደማይገባኝ ስላሰብኩ ተስፋ ቆረጥኩ። ሕሊናዬ በጣም ረበሸኝ፤ ይሖዋ ይቅር እንዳለኝ አልተሰማኝም ነበር። ከጊዜ በኋላም በአገልግሎት መካፈሌንም ሆነ ጉባኤ መሄዴን ከነጭራሹ አቆምኩ።” እስካሁን የተመለከትናቸው ሁኔታዎች ስላጋጠሟቸው ወንድሞችና እህቶች ምን ይሰማሃል? ስሜታቸውን ትረዳላቸዋለህ? ይበልጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላም ጥያቄ አለ፦ ይሖዋ ስለ እነዚህ ሰዎች ምን ይሰማዋል?
ይሖዋ በጎቹን ይወዳል
8. ይሖዋ በአንድ ወቅት ያገለግሉት የነበሩ ሰዎችን ይረሳቸዋል? አብራራ።
8 ይሖዋ በአንድ ወቅት ያገለግሉት የነበሩ አሁን ግን ከሕዝቦቹ ጋር እሱን ማገልገላቸውን ያቆሙ አገልጋዮቹን አይረሳቸውም፤ በእሱ አገልግሎት ያከናወኑትን ሥራም ቢሆን አይዘነጋም። (ዕብ. 6:10) ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚንከባከብ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ አስፍሮልናል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መንጋውን እንደ እረኛ ይንከባከባል። ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል።” (ኢሳ. 40:11) ታዲያ ታላቁ እረኛ ከበጎቹ አንዱ ከመንጋው ሲርቅ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበው የሚከተለው ጥያቄ የይሖዋን ስሜት የሚገልጽ ነው፦ “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው 100 በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ 99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም? እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋችውን በግ ካገኛት፣ ካልጠፉት ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል።”—ማቴ. 18:12, 13
9. በጥንት ዘመን የነበሩ ጥሩ እረኞች በጎቻቸውን የሚይዙት እንዴት ነበር? (ሽፋኑን ተመልከት።)
9 ይሖዋ በእረኛ መመሰሉ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በጥንት ዘመን የነበረ አንድ ጥሩ እረኛ ለበጎቹ በጥልቅ ያስብ ነበር። ለምሳሌ ዳዊት፣ መንጋውን ከአደጋ ለመጠበቅ ሲል ከአንበሳና ከድብ ጋር ታግሏል። (1 ሳሙ. 17:34, 35) አንድ ጥሩ እረኛ ከበጎቹ መካከል አንዱ እንኳ ቢጠፋ ማስተዋሉ አይቀርም። (ዮሐ. 10:3, 14) እንዲህ ያለው እረኛ 99ኙን በጎች በረት ውስጥ ወይም ለሌሎች እረኞች ትቶ፣ የጠፋውን በግ ፍለጋ ይሄዳል። ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተጠቀመው አንድ አስፈላጊ እውነት እንድንገነዘብ ለማድረግ ነው፤ ኢየሱስ ይህን እውነት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም።”—ማቴ. 18:14
ይሖዋ የጠፉ በጎቹን ይፈልጋል
10. በሕዝቅኤል 34:11-16 መሠረት ይሖዋ ለጠፉ በጎቹ ምን እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል?
10 ይሖዋ ‘ትናንሾች’ የተባሉትን ከመንጋው የባዘኑ አገልጋዮቹን ጨምሮ እያንዳንዳችንን ይወደናል። አምላክ፣ የጠፉ በጎቹን እንደሚፈልግና መንፈሳዊ ጤንነታቸውን መልሰው እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው በነቢዩ ሕዝቅኤል አማካኝነት ቃል ገብቷል። በተጨማሪም እነሱን ለመታደግ የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በዝርዝር ጠቅሷል፤ አንድ እስራኤላዊ እረኛ በጉ ሲጠፋበት እነዚህን እርምጃዎች ይወስድ ነበር። (ሕዝቅኤል 34:11-16ን አንብብ።) በመጀመሪያ እረኛው በጉን ፍለጋ ይሄዳል፤ ይህም ብዙ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅበት ይችላል። የባዘነውን በግ ካገኘው በኋላ ደግሞ ወደ መንጋው መልሶ ያመጣዋል። በጉ ተጎድቶ ወይም ተርቦ ከነበረም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይንከባከበዋል፤ የተጎዳ አካሉን በጨርቅ ያስርለታል፣ ይሸከመዋል እንዲሁም ይመግበዋል። ‘የአምላክ መንጋ’ እረኛ ሆነው የሚያገለግሉት ሽማግሌዎችም ከጉባኤ የራቀን ማንኛውንም ሰው ሲረዱ እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ሽማግሌዎች እነዚህን ግለሰቦች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ወደ መንጋው እንዲመለሱ ይረዷቸዋል እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ እርዳታ በመስጠት ፍቅር ያሳዩአቸዋል።d
11. አንድ ጥሩ እረኛ ምን ይገነዘባል?
11 ጥሩ እረኛ፣ አንድ በግ ከመንጋው ተለይቶ ሊጠፋ እንደሚችል ይገነዘባል። ከመንጋው መካከል አንዱ በግ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥመው እረኛው ርኅራኄ በጎደለው መንገድ አይዘውም። ይሖዋ ለተወሰነ ጊዜ ከእሱ ርቀው የነበሩ አንዳንድ አገልጋዮቹን ከረዳበት መንገድ ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት።
12. ይሖዋ ዮናስን የያዘው እንዴት ነበር?
12 ነቢዩ ዮናስ የተሰጠውን ኃላፊነት መቀበል ስላልፈለገ ሸሽቶ ነበር። ያም ቢሆን ይሖዋ በዮናስ ቶሎ ተስፋ አልቆረጠም። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ ጥሩ እረኛ ዮናስን የታደገው ሲሆን ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ እንዲያገኝ ረድቶታል። (ዮናስ 2:7፤ 3:1, 2) በኋላ ላይም አምላክ የቅል ተክልን በመጠቀም፣ የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት ምን ያህል ዋጋ እንዳለው ዮናስን አስተምሮታል። (ዮናስ 4:10, 11) ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ምንድን ነው? ሽማግሌዎች በቀዘቀዙ አስፋፊዎች ቶሎ ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ በጉ ከመንጋው እንዲባዝን ያደረገው ምን እንደሆነ ለመረዳት ይጥራሉ። በጉ ወደ ይሖዋ ሲመለስ ደግሞ ሽማግሌዎቹ እሱን በፍቅር መንከባከባቸውን ይቀጥላሉ።
13. ይሖዋ የመዝሙር 73ን ጸሐፊ ከያዘበት መንገድ ምን እንማራለን?
13 የመዝሙር 73 ጸሐፊ ክፉዎች በምቾት እንደሚኖሩ ስለተሰማው ተስፋ ቆርጦ ነበር። የአምላክን ፈቃድ መፈጸም የሚክስ ነገር ስለ መሆኑ ጥያቄ ተፈጥሮበት ነበር። (መዝ. 73:12, 13, 16) ታዲያ ይሖዋ ስለዚህ መዝሙራዊ ምን ተሰማው? ይህን ሰው አላወገዘውም። እንዲያውም አምላክ፣ ይህ መዝሙራዊ የተናገረው ሐሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። ውሎ አድሮም መዝሙራዊው፣ በሕይወት ውስጥ ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ከመመሥረት የሚበልጥ ምንም ነገር እንደሌለ ተገንዝቧል። (መዝ. 73:23, 24, 26, 28) ይህ ዘገባ ምን ያስተምረናል? አንዳንዶች ይሖዋን ማገልገል ጠቃሚ ስለ መሆኑ ጥርጣሬ ቢያድርባቸው ሽማግሌዎች በእነሱ ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለባቸውም። ሽማግሌዎች እነዚህን ግለሰቦች ከመንቀፍ ይልቅ ይህን አካሄድ ለመከተል ምክንያት የሆናቸውን ነገር ለመረዳት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ሽማግሌዎች ግለሰቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ መስጠት የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው።
14. ኤልያስ እርዳታ ያስፈለገው ለምን ነበር? ይሖዋስ የረዳው እንዴት ነው?
14 ነቢዩ ኤልያስ ከንግሥት ኤልዛቤል ሸሽቶ ነበር። (1 ነገ. 19:1-3) ኤልያስ ከእሱ በቀር ይሖዋን የሚያገለግል ነቢይ እንደሌለና ያከናወነው ሥራ ከንቱ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር። ኤልያስ በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሞትን ተመኝቶ ነበር። (1 ነገ. 19:4, 10) ይሖዋ ግን ኤልያስን ከመውቀስ ይልቅ ብቻውን እንዳልሆነ፣ በአምላክ ኃይል መተማመን እንደሚችል እንዲሁም ገና ብዙ የሚያከናውነው ሥራ እንዳለ አረጋግጦለታል። ኤልያስ የሚያሳስበውን ነገር ሲናገር ይሖዋ በደግነት ያዳመጠው ሲሆን ሌሎች ኃላፊነቶችም ሰጥቶታል። (1 ነገ. 19:11-16, 18) ከዚህ ዘገባ ምን እንማራለን? ሁላችንም በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች በደግነት ልንይዝ ይገባል። አንድ ሰው ምሬቱን ቢገልጽ ወይም የይሖዋ ምሕረት የማይገባው ሰው እንደሆነ ቢሰማውም እንኳ ግለሰቡ የልቡን አውጥቶ ሲናገር ሽማግሌዎች ያዳምጡታል። ከዚያም በይሖዋ ፊት የላቀ ዋጋ እንዳለው በመግለጽ የጠፋውን በግ ያጽናኑታል።
ለጠፉ የአምላክ በጎች ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
15. በዮሐንስ 6:39 ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ ለአባቱ በጎች ምን አመለካከት ነበረው?
15 ይሖዋ ለጠፉት በጎቹ ምን አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል? ኢየሱስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ ሁሉም የይሖዋ በጎች በእሱ ፊት ውድ እንደሆኑ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ‘ከእስራኤል ቤት የጠፉት በጎች’ ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። (ማቴ. 15:24፤ ሉቃስ 19:9, 10) ከዚህም ሌላ፣ ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ ከይሖዋ በጎች መካከል አንዱም እንኳ እንዳይጠፋበት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል።—ዮሐንስ 6:39ን አንብብ።
16-17. ሽማግሌዎች የባዘኑ ክርስቲያኖችን ስለ መርዳት ምን ሊሰማቸው ይገባል? (“የጠፉ በጎች ምን ሊሰማቸው ይችላል?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)
16 ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ የሚገኙ ሽማግሌዎችን የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ አሳስቧቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።” (ሥራ 20:17, 35) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በስፔን የሚኖር ሳልቫዶር የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ የጠፉ በጎቹን ምን ያህል እንደሚወዳቸው ሳስብ እነሱን ለመርዳት የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ እነሳሳለሁ። መንፈሳዊ እረኛ እንደመሆኔ መጠን ይሖዋ እነሱን እንድንከባከብ እንደሚጠብቅብኝ እገነዘባለሁ።”
17 በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱት ከጉባኤ ርቀው የነበሩ ሰዎች በሙሉ የተሰጣቸውን እርዳታ ተቀብለው ወደ ይሖዋ ተመልሰዋል። ወደ ይሖዋ መመለስ የሚፈልጉ ሌሎች ብዙ ሰዎችም አሉ። እነዚህን ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ እንዴት ልንረዳቸው እንደምንችል በሚቀጥለው ርዕስ ላይ በዝርዝር እንመለከታለን።
መዝሙር 139 በአዲሱ ዓለም ስትኖር ይታይህ
a ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት በታማኝነት ያገለገሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከጉባኤው የሚርቁት ለምንድን ነው? አምላክ ስለ እነዚህ አገልጋዮቹ ምን ይሰማዋል? ይህ ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። በተጨማሪም በጥንት ዘመን ይሖዋ ከእሱ የራቁ አንዳንድ አገልጋዮቹን ከረዳበት መንገድ ምን እንደምንማር ያብራራል።
b ተጨማሪ ማብራሪያ፦ የቀዘቀዘ አስፋፊ የሚባለው በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ያደረገውን ተሳትፎ ለስድስት ወር ወይም ከዚያ ለሚበልጥ ጊዜ ሪፖርት ያላደረገ ክርስቲያን ነው። በእርግጥ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች አሁንም ቢሆን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ናቸው፤ ደግሞም እንወዳቸዋለን።
c አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
d የሚቀጥለው ርዕስ ሽማግሌዎች እነዚህን እርምጃዎች ስለሚወስዱበት መንገድ በዝርዝር ያብራራል።
e የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ እስራኤላዊ እረኛ የጠፋው በጉ ያለበት ሁኔታ ስለሚያሳስበው በጉን ፍለጋ ይሄዳል፤ እንዲሁም ወደ መንጋው መልሶ ያመጣዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ መንፈሳዊ እረኞችም እንዲሁ ያደርጋሉ።
f የሥዕሉ መግለጫ፦ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በአደባባይ ምሥክርነት በደስታ ሲካፈሉ አንዲት የቀዘቀዘች እህት አውቶቡስ ውስጥ ሆና እየተመለከተቻቸው ነው።