የጥናት ርዕስ 8
ፈተናዎች እየደረሱባችሁም ደስታችሁን ጠብቃችሁ መኖር የምትችሉት እንዴት ነው?
“ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት።”—ያዕ. 1:2
መዝሙር 111 ለደስታችን ምክንያት የሆኑ ነገሮች
ማስተዋወቂያa
1-2. በማቴዎስ 5:11 መሠረት ፈተናዎችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል?
ኢየሱስ ተከታዮቹ እውነተኛ ደስታ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። ይሁንና የሚወዱት ሰዎች ፈተናዎች እንደሚደርሱባቸውም አስጠንቅቋል። (ማቴ. 10:22, 23፤ ሉቃስ 6:20-23) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችን ደስታ ያስገኝልናል። ሆኖም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስንሆን ከቤተሰብ ተቃውሞ ሊያጋጥመን፣ መንግሥታት ስደት ሊያደርሱብን አሊያም አብረውን የሚሠሩ ወይም የሚማሩ ሰዎች ትክክል ያልሆነ ነገር እንድናደርግ ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ፤ ታዲያ እነዚህ ፈተናዎች ሊደርሱብን እንደሚችሉ ስናውቅ ምን ይሰማናል? ስለ እነዚህ ፈተናዎች ስናስብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ብንጨነቅ የሚያስገርም አይደለም።
2 ማንም ሰው ቢሆን ስደት ደስታ ያስገኛል ብሎ ላያስብ ይችላል። የአምላክ ቃል ግን ስለ ስደት እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ፈተና ሲደርስብን በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ እንደ ደስታ እንድንቆጥረው ነግሮናል። (ያዕ. 1:2, 12) ኢየሱስም ቢሆን ስደት ሲደርስብን ልንደሰት እንደሚገባ ተናግሯል። (ማቴዎስ 5:11ን አንብብ።) ታዲያ ፈተናዎች እየደረሱብንም ደስታችንን ጠብቀን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? ያዕቆብ ለጥንቶቹ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ የሚገኙ አንዳንድ ሐሳቦችን በመመርመር ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። በቅድሚያ በወቅቱ የነበሩት ክርስቲያኖች የገጠሟቸውን አንዳንድ ፈተናዎች እንመልከት።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ምን ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል?
3. ያዕቆብ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ምን ተከሰተ?
3 የኢየሱስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ደቀ መዝሙር ከሆነ ብዙም ሳይቆይ በኢየሩሳሌም ባሉ ክርስቲያኖች ላይ ተቃውሞ ተነሳ። (ሥራ 1:14፤ 5:17, 18) ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ሲገደል ደግሞ ብዙ ክርስቲያኖች ከተማዋን ጥለው በመውጣት “በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ”፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ እስከ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ርቀው ሄደዋል። (ሥራ 7:58–8:1፤ 11:19) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምን ያህል ከባድ ሁኔታ እንደገጠማቸው መገመት እንችላለን። ያም ቢሆን ምሥራቹን በሄዱበት ሁሉ በቅንዓት ሰብከዋል፤ እንዲሁም በመላው የሮም ግዛት ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። (1 ጴጥ. 1:1) ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች ከዚህም የከፉ ፈተናዎች ይጠብቋቸው ነበር።
4. የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ምን ሌሎች ፈተናዎች ነበሩባቸው?
4 የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ልዩ ልዩ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ በ50 ዓ.ም. ገደማ የሮም ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ሮምን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። ስለዚህ ክርስቲያን የሆኑ አይሁዳውያን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሰደድ ተገደዱ። (ሥራ 18:1-3) በ61 ዓ.ም. ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ በአደባባይ እንደተነቀፉ፣ እንደታሰሩና እንደተዘረፉ ጽፎ ነበር። (ዕብ. 10:32-34) እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ደግሞ እነዚያ ክርስቲያኖች ከድህነት ወይም ከህመም ጋር መታገል ነበረባቸው።—ሮም 15:26፤ ፊልጵ. 2:25-27
5. የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?
5 ያዕቆብ ከ62 ዓ.ም. በፊት ደብዳቤውን ሲጽፍ ወንድሞቹና እህቶቹ ምን ዓይነት ፈተናዎችን እየተጋፈጡ እንዳለ በሚገባ ያውቅ ነበር። እነዚህ ክርስቲያኖች ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም በደስታ መጽናት እንዲችሉ የሚረዷቸውን ጠቃሚ ምክሮች እንዲጽፍ ይሖዋ ያዕቆብን በመንፈሱ መርቶታል። እስቲ የያዕቆብን ደብዳቤ በመመርመር የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት፦ ያዕቆብ የጻፈው ስለምን ዓይነት ደስታ ነው? አንድ ክርስቲያን ይህን ደስታውን እንዲያጣ ሊያደርጉት የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? እንዲሁም የሚያጋጥመን ፈተና ምንም ይሁን ምን ጥበብ፣ እምነትና ድፍረት ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር የሚረዱን እንዴት ነው?
አንድን ክርስቲያን ደስተኛ የሚያደርገው ምንድን ነው?
6. በሉቃስ 6:22, 23 መሠረት አንድ ክርስቲያን ፈተናዎች እየደረሱበትም ደስተኛ የሚሆነው ለምንድን ነው?
6 ሰዎች ደስተኛ የሚሆኑት ጥሩ ጤና፣ ብዙ ገንዘብ ወይም ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት ሲኖራቸው እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ያዕቆብ የጻፈው ግን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ ስለሆነው ደስታ ሲሆን ይህ ደስታ ግለሰቡ ባለበት ሁኔታ ላይ የተመካ አይደለም። (ገላ. 5:22) ለአንድ ክርስቲያን ደስታ ወይም ጥልቅ እርካታ የሚያስገኝለት ይሖዋን እያስደሰተና የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተለ እንዳለ ማወቁ ነው። (ሉቃስ 6:22, 23ን አንብብ፤ ቆላ. 1:10, 11) በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ያለው ደስታ ከፋኖስ ብርሃን ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የፋኖስ ብርሃን መከለያ ስላለው በቀላሉ አይጠፋም። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ጤንነቱ ቢቃወስ ወይም ገንዘብ ቢያጣም እንኳ ውስጣዊ ደስታው አይጠፋም። ከቤተሰቡ አባላት ወይም ከሌሎች የሚደርስበት ፌዝና ተቃውሞም ደስታውን አያጨልመውም። ተቃዋሚዎች ደስታውን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት ደስታውን አያደበዝዘውም፤ እንዲያውም ይበልጥ ደምቆ እንዲበራ ያደርገዋል። በእምነታችን ምክንያት የሚደርሱብን ፈተናዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን ያረጋግጣሉ። (ማቴ. 10:22፤ 24:9፤ ዮሐ. 15:20) ያዕቆብ “ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት” ብሎ የጻፈው በዚህ የተነሳ ነው።—ያዕ. 1:2
7-8. እምነታችን መፈተኑ ምን ውጤት ይኖረዋል?
7 ያዕቆብ፣ ክርስቲያኖች በጣም ከባድ የሆኑ ፈተናዎችን እንኳ ለመጋፈጥ ፈቃደኛ የሚሆኑበትን ሌላ ምክንያት ጠቅሷል። “ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት እንደሚያስገኝ ታውቃላችሁ” ብሏል። (ያዕ. 1:3) ፈተናዎች ብረት ቀጥቃጮች ብረትን ለማጠንከር ከሚጠቀሙበት ሂደት ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ብረት ቀጥቃጮች ብረቱን እሳት ውስጥ ከትተው ካጋሉት በኋላ አውጥተው ያቀዘቅዙታል፤ ይህ ሂደት ብረቱ እየጠነከረ እንዲሄድ ያደርጋል። በተመሳሳይም በፈተና ውስጥ ስናልፍ እምነታችን ይጠናከራል። ያዕቆብ “በሁሉም ረገድ . . . ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ያዕ. 1:4) የሚያጋጥሙን ፈተናዎች እምነታችንን እንደሚያጠነክሩት ስናይ በደስታ መጽናት ቀላል ይሆንልናል።
8 ያዕቆብ ደስታችንን ሊያሳጡን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችንም በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ምንድን ናቸው? እንዴት ልንቋቋማቸውስ እንችላለን?
ደስታችንን ሊያሳጡን የሚችሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም
9. ጥበብ ማግኘት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?
9 ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ምን ማድረግ እንዳለብን አለማወቅ። ፈተና ሲደርስብን ይሖዋን የሚያስደስት፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን የሚጠቅም እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚረዳ ውሳኔ ማድረግ እንፈልጋለን፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ ግን የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤር. 10:23) ምን ማድረግ እንዳለብንና ለተቃዋሚዎቻችን ምን መልስ እንደምንሰጥ ለማወቅ ጥበብ ያስፈልገናል። ምን ማድረግ እንዳለብን ካላወቅን ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ደስታችንን ሊያሳጣን ይችላል።
10. ያዕቆብ 1:5 ጥበብ ለማግኘት ምን እንድናደርግ ይመክረናል?
10 መፍትሔው፦ ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጠን መለመን። የሚደርስብንን ፈተና በደስታ ለመቋቋም በመጀመሪያ ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ይሖዋን በጸሎት መለመን ይኖርብናል። (ያዕቆብ 1:5ን አንብብ።) ይሖዋ ለጸሎታችን ወዲያውኑ ምላሽ እንዳልሰጠን ቢሰማን ምን ማድረግ ይኖርብናል? ያዕቆብ ‘አምላክን ያለማሰለስ መለመን’ እንዳለብን ተናግሯል። ይሖዋ፣ ጥበብ እንዲሰጠን በተደጋጋሚ ስንለምነው እንደጨቀጨቅነው አይሰማውም። እንዲህ በማድረጋችን አይነቅፈንም። የሰማዩ አባታችንን የገጠሙንን ፈተናዎች መቋቋም የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጠን ስንለምነው ‘በልግስና ይሰጠናል።’ (መዝ. 25:12, 13) ያሉብንን ፈተናዎች ያያል፣ ያዝንልናል እንዲሁም ሊረዳን ይፈልጋል። በእርግጥም ይህ ለደስታችን ምክንያት የሚሆን ነገር ነው! ይሁንና ይሖዋ ጥበብ የሚሰጠን እንዴት ነው?
11. ጥበብ ለማግኘት ሌላስ ምን ማድረግ አለብን?
11 ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ጥበብ ይሰጠናል። (ምሳሌ 2:6) ይህን ጥበብ ለማግኘት የአምላክን ቃልና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማጥናት አለብን። ሆኖም እውቀት ከማከማቸት የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። አምላክ የሚሰጠንን ምክር ተግባራዊ በማድረግ የአምላክ ጥበብ በሕይወታችን ውስጥ እንዲሠራ ማድረግ አለብን። ያዕቆብ “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:22) የአምላክን ምክር ተግባራዊ ስናደርግ ይበልጥ ሰላማዊ፣ ምክንያታዊና መሐሪ እንሆናለን። (ያዕ. 3:17) እነዚህ ባሕርያት ምንም ዓይነት ፈተና ቢደርስብን ደስታችንን ጠብቀን እንድንኖር ይረዱናል።
12. መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማወቃችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
12 የአምላክ ቃል እንደ መስታወት ነው፤ ልናስተካክለው የሚገባንን ነገር ለማስተዋልና ማስተካከያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። (ያዕ. 1:23-25) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን ቃል ስናጠና ቁጣችንን መቆጣጠር እንደሚያስፈልገን እንገነዘብ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የሚያስቆጡ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ገር መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይሖዋ ያስተምረናል። ገር መሆናችን የሚደርስብንን ጫና በተሻለ ሁኔታ ለመወጣት ያስችለናል። በትክክል ማሰብና የተሻለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። (ያዕ. 3:13) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማወቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!
13. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር ማድረግ እንደሌለብን የምንማረው ስህተት ከሠራን በኋላ ነው። ይህ ግን ከመከራ መማር ነው። ጥበብ ለማግኘት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከሌሎች ስኬትና ከሠሯቸው ስህተቶች መማር ነው። ያዕቆብ እንደ አብርሃም፣ ረዓብ፣ ኢዮብና ኤልያስ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ እንድንመረምር ያበረታታን ለዚህ ነው። (ያዕ. 2:21-26፤ 5:10, 11, 17, 18) እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ደስታቸውን ሊያሳጧቸው የሚችሉ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም ችለዋል። ጽናት በማሳየት ረገድ የተዉት ምሳሌ እኛም በይሖዋ እርዳታ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንደምንችል ይጠቁማል።
14-15. ያደረብንን ጥርጣሬ ማስወገድ ያለብን ለምንድን ነው?
14 ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ጥርጣሬ። አልፎ አልፎ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኝን ሐሳብ መረዳት የሚከብደን ጊዜ ይኖራል። ወይም ደግሞ ይሖዋ እኛ በጠበቅነው መንገድ ለጸሎታችን መልስ ላይሰጠን ይችላል። ይህ ጥርጣሬ እንዲፈጠርብን ያደርግ ይሆናል። የተፈጠረብንን ጥርጣሬ ችላ ብለን ከተውነው እምነታችንን ሊያዳክምብንና ከይሖዋ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ሊያበላሽብን ይችላል። (ያዕ. 1:7, 8) የወደፊቱ ተስፋችንም ብሩህ ሆኖ እንዳይታየን ሊያደርግ ይችላል።
15 ሐዋርያው ጳውሎስ ተስፋችንን ከመልሕቅ ጋር አመሳስሎታል። (ዕብ. 6:19) መልሕቅ፣ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ላይ ያለን መርከብ ባለበት እንዲቆምና ከዓለት ጋር እንዳይላተም ይረዳዋል። ሆኖም አንድ መልሕቅ እንዲህ ያለ ጥቅም ሊሰጥ የሚችለው ከመርከቡ ጋር የተያያዘበት ሰንሰለት እስካልተበጠሰ ብቻ ነው። ዝገት የመልሕቁን ሰንሰለት እንደሚበላው ሁሉ ጥርጣሬም እምነታችንን ይበላዋል። ጥርጣሬ ያደረበት አንድ ሰው ተቃውሞ ሲያጋጥመው ይሖዋ የገባውን ቃል እንደሚጠብቅ ያለው እምነት ሊጠፋ ይችላል። እምነታችን ከጠፋ ደግሞ ተስፋችን ይጨልማል። ያዕቆብ እንዳለው “የሚጠራጠር ሰው በነፋስ እንደሚገፋና እንደሚናወጥ የባሕር ማዕበል ነው።” (ያዕ. 1:6) እንዲህ ዓይነቱ ሰው ደግሞ ደስተኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው።
16. ጥርጣሬ ካደረብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
16 መፍትሔው፦ ጥርጣሬያችንን ማስወገድና እምነታችንን ማጠናከር። ቶሎ እርምጃ ውሰዱ። በነቢዩ ኤልያስ ዘመን የይሖዋ ሕዝቦች ወላዋይ ሆነው ነበር። በመሆኑም ኤልያስ እንዲህ አላቸው፦ “በሁለት ሐሳብ የምታነክሱት እስከ መቼ ነው? እውነተኛው አምላክ፣ ይሖዋ ከሆነ እሱን ተከተሉ፤ ባአል ከሆነ ደግሞ እሱን ተከተሉ!” (1 ነገ. 18:21) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ አምላክ እንደሆነ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የእሱ ቃል እንደሆነ እንዲሁም የይሖዋ ምሥክሮች የእሱ ሕዝቦች እንደሆኑ ለራሳችን ለማረጋገጥ ምርምር ማድረግ ያስፈልገናል። (1 ተሰ. 5:21) እንዲህ ማድረጋችን ጥርጣሬያችንን ያስወግደዋል እንዲሁም እምነታችንን ያጠናክርልናል። ጥርጣሬያችንን ለማስወገድ እገዛ ካስፈለገን ሽማግሌዎችን እንዲረዱን መጠየቅ እንችላለን። በይሖዋ አገልግሎት የምናገኘው ደስታ እንዳይጠፋ ከፈለግን ቶሎ እርምጃ መውሰድ አለብን!
17. ድፍረት ስናጣ ምን ይከሰታል?
17 ተፈታታኝ ሁኔታ፦ ተስፋ መቁረጥ። የአምላክ ቃል “በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል” ይላል። (ምሳሌ 24:10) ‘ተስፋ መቁረጥ’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘ድፍረት ማጣት’ ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ድፍረት ካጣን ደስታችን ወዲያውኑ ይጠፋል።
18. ጽናት ሲባል ምን ማለት ነው?
18 መፍትሔው፦ ለመጽናት የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጠን ይሖዋን መለመን። ፈተናዎችን በጽናት ለመቋቋም ድፍረት ያስፈልገናል። (ያዕ. 5:11) ያዕቆብ የተጠቀመበት “ጽናት” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ከቆሙበት ቦታ ንቅንቅ አለማለትን ያመለክታል። የጠላት ሠራዊትን ለመመከት ከቆመበት ንቅንቅ ሳይል የሚፋለምን አንድ ወታደር በዓይነ ሕሊናችን ልንሥል እንችላለን።
19. ሐዋርያው ጳውሎስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?
19 ሐዋርያው ጳውሎስ ድፍረትና ጽናት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ድካም የተሰማው ጊዜ ነበር። ሆኖም ይሖዋ የሚያስፈልገውን ኃይል እንደሚሰጠው ይተማመን ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ በሰጠው ኃይል መጽናት ችሏል። (2 ቆሮ. 12:8-10፤ ፊልጵ. 4:13) እኛም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን ከተቀበልን እንዲህ ዓይነቱን ጥንካሬና ድፍረት ማግኘት እንችላለን።—ያዕ. 4:10
ወደ አምላክ በመቅረብ ደስታችሁን ጠብቃችሁ ኑሩ
20-21. ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
20 የሚደርሱብን ፈተናዎች ይሖዋ እየቀጣን እንዳለ የሚያሳዩ ነገሮች እንዳልሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ያዕቆብ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም።” (ያዕ. 1:13) ይህን እውነታ አምነን ከተቀበልን አፍቃሪ ወደሆነው የሰማዩ አባታችን ይበልጥ እንቀርባለን።—ያዕ. 4:8
21 ይሖዋ “አይለዋወጥም።” (ያዕ. 1:17) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም እያንዳንዳችንን ይረዳናል። እንግዲያው ጥበብ፣ እምነትና ድፍረት እንዲሰጣችሁ ይሖዋን አጥብቃችሁ ለምኑት። ለጸሎታችሁ መልስ ይሰጣችኋል። ፈተናዎች ቢኖሩም ደስታችሁን ጠብቃችሁ እንድትጸኑ እንደሚረዳችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ!
መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት
a የያዕቆብ መጽሐፍ ፈተናዎችን ለመቋቋም የሚረዱ ብዙ ጠቃሚ ምክሮችን ይዟል። ይህ ርዕስ አንዳንዶቹን የያዕቆብ ምክሮች ያብራራል። እነዚህ ምክሮች በይሖዋ አገልግሎት የምናገኘውን ደስታ ሳናጣ አስቸጋሪ ሁኔታዎችን በጽናት መቋቋም እንድንችል ይረዱናል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ ፖሊሶች አንድን ወንድም ከቤቱ ይዘዉት እየሄዱ ነው። ሚስቱና ሴት ልጁ ፖሊሶቹ ይዘዉት ሲሄዱ ቆመው ይመለከቷቸዋል። ወንድም እስር ቤት ሳለ ወንድሞችና እህቶች ቤታቸው መጥተው ከእህትና ከልጇ ጋር የቤተሰብ አምልኮ እያደረጉ ነው። እህትና ልጇ ይሖዋ ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንዲሰጣቸው አዘውትረው ይጸልያሉ። ይሖዋም ውስጣዊ ሰላምና ድፍረት ሰጥቷቸዋል። በመሆኑም እምነታቸው ይበልጥ ተጠናክሯል፤ ይህም በደስታ እንዲጸኑ አስችሏቸዋል።