የጥናት ርዕስ 16
ለይሖዋ ምርጥህን በመስጠት ተደሰት
“እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር።”—ገላ. 6:4
መዝሙር 37 ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል
ማስተዋወቂያa
1. ጥልቅ ደስታ የሚያስገኝልን ምንድን ነው?
ይሖዋ ደስተኛ እንድንሆን ይፈልጋል። ይህን እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ደስታ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬ አንድ ገጽታ ነው። (ገላ. 5:22) ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ስለሚያስገኝ በአገልግሎታችን ሙሉ በሙሉ ስንጠመድ እንዲሁም ወንድሞቻችንን በተለያዩ መንገዶች ስንረዳ ጥልቅ ደስታ እናገኛለን።—ሥራ 20:35
2-3. (ሀ) በገላትያ 6:4 መሠረት በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛ ሆነን ለመኖር የሚረዱን ሁለት ነገሮች የትኞቹ ናቸው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
2 በገላትያ 6:4 ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ደስታችንን ጠብቀን ለመኖር የሚረዱንን ሁለት ነገሮች ጠቅሷል። (ጥቅሱን አንብብ።) አንደኛ፣ ለይሖዋ ምርጣችንን መስጠት ይኖርብናል። ለይሖዋ ምርጣችንን እየሰጠነው እስከሆነ ድረስ ልንደሰት ይገባል። (ማቴ. 22:36-38) ሁለተኛ፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር መቆጠብ ይኖርብናል። ከጤንነታችን፣ ካገኘነው ሥልጠና ወይም ከተፈጥሯዊ ችሎታችን አንጻር ማከናወን የምንችለው ነገር ምንም ይሁን ምን ይሖዋን ማመስገን አለብን። ምክንያቱም ማንኛውንም ነገር ያገኘነው ከይሖዋ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ በአንዳንድ የአገልግሎት ዘርፎች ረገድ ሌሎች ከእኛ የበለጠ ውጤታማ ከሆኑ ችሎታቸውን ወደ ራሳቸው ትኩረት ለመሳብ ወይም የራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ ሳይሆን ይሖዋን ለማወደስ ስለተጠቀሙበት ልንደሰት ይገባል። ከእነሱ ጋር ከመፎካከር ይልቅ ከእነሱ ለመማር ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።
3 በአገልግሎታችን ማከናወን የምንችለው ነገር እንደተገደበ ሲሰማን ምን ማድረግ እንደምንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም ያሉንን ስጦታዎች ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም ከሌሎች ምሳሌ ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እንመለከታለን።
አገልግሎታችን እንደተገደበ ሲሰማን
4. የትኛው ሁኔታ ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል? አንድ ምሳሌ ጥቀስ።
4 አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል ምክንያት አገልግሎታቸው ሲገደብ ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። ካሮል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟታል። ቀደም ሲል የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ቦታ ታገለግል ነበር። በዚያ ወቅት 35 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርታለች። ብዙዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁም ረድታለች። ካሮል በአገልግሎቷ ውጤታማ ነበረች። በኋላ ግን ባደረባት የጤና እክል ምክንያት ከቤት መውጣት አስቸጋሪ ሆነባት። ካሮል እንዲህ ብላለች፦ “በአገልግሎቴ የሌሎችን ያህል ማከናወን ያልቻልኩት በመታመሜ ምክንያት እንደሆነ አውቃለሁ። ሆኖም የእነሱን ያህል ታማኝ እንዳልሆንኩ ይሰማኛል። ፍላጎቴና አቅሜ አልተመጣጠነም፤ ይህ ደግሞ ተስፋ ያስቆርጠኛል።” ካሮል አቅሟ በፈቀደ መጠን ይሖዋን ማገልገል ትፈልጋለች። ደግሞም ይህ በጣም የሚያስመሰግን ነው! ሩኅሩኅ የሆነው አምላካችን ካሮል ምርጧን በመስጠቷ እንደሚደሰት ምንም ጥርጥር የለውም።
5. (ሀ) ያለብን የአቅም ገደብ ተስፋ የሚያስቆርጠን ከሆነ ምን ማስታወስ ይኖርብናል? (ለ) በሥዕሉ ላይ ያለው ወንድም ዕድሜውን በሙሉ ለይሖዋ ምርጡን የሰጠው እንዴት ነው?
5 ያለብህ የአቅም ገደብ አንዳንድ ጊዜ ተስፋ የሚያስቆርጥህ ከሆነ ‘ይሖዋ ከእኔ የሚፈልገው ምንድን ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። ይሖዋ የሚፈልገው ካለህበት ሁኔታ አንጻር ምርጥህን እንድትሰጠው ብቻ ነው። እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ በ80ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ እህት በ40ዎቹ ዕድሜ ሳሉ እንደነበረው ማገልገል ባለመቻላቸው ተስፋ ይቆርጡ ይሆናል። ለይሖዋ ምርጣቸውን እየሰጡት ቢሆንም እንደማይደሰትባቸው ይሰማቸዋል። ግን እውነታው እንደዚያ ነው? እስቲ አስበው። እኚህ እህት በ40ዎቹ ዕድሜ እያሉ ለይሖዋ ምርጣቸውን ይሰጡት ነበር፤ አሁንም በ80ዎቹ ዕድሜ ሆነው ምርጣቸውን እየሰጡት ነው። ስለዚህ ለይሖዋ ምርጣቸውን መስጠት አላቋረጡም ማለት ነው። የምናቀርበው አገልግሎት ይሖዋን ለማስደሰት በቂ እንዳልሆነ ከተሰማን፣ እሱን የሚያስደስተውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የሚያወጣው ይሖዋ ራሱ እንደሆነ ማስታወስ አለብን። ምርጣችንን ከሰጠነው ይሖዋ “ጎበዝ!” ይለናል።—ከማቴዎስ 25:20-23 ጋር አወዳድር።
6. ከማሪያ ተሞክሮ ምን እንማራለን?
6 ማድረግ በማንችለው ሳይሆን ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ካተኮርን ደስታችንን መጠበቅ ቀላል ይሆንልናል። ማሪያ የተባለችን እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ማሪያ አገልግሎቷን የሚገድብ የጤና እክል አለባት። መጀመሪያ ላይ ማሪያ ቅስሟ የተሰበረ ከመሆኑም ሌላ ዋጋ ቢስ እንደሆነች ተሰምቷት ነበር። በኋላ ግን፣ በጉባኤዋ ውስጥ ያለችን አንዲት የአልጋ ቁራኛ እህት አሰበች፤ እሷን ለመርዳትም ወሰነች። ማሪያ እንዲህ ብላለች፦ “ከእሷ ጋር በስልክና በደብዳቤ አማካኝነት ለመስበክ ዝግጅት አደረግኩ። ከእሷ ጋር ባገለገልኩ ቁጥር ወደ ቤት የምመለሰው እህቴን መርዳት በመቻሌ ተደስቼና ረክቼ ነው።” እኛም ማድረግ በማንችለው ነገር ላይ ሳይሆን ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ካተኮርን ደስታችንን ማሳደግ እንችላለን። ይሁንና በይሖዋ አገልግሎት ተጨማሪ ነገር ማድረግ የምንችል ቢሆንስ? ወይም ደግሞ በአንዳንድ የአገልግሎት መስኮች ረገድ የተዋጣልን ብንሆንስ?
ስጦታ ካለህ ‘ተጠቀምበት!’
7. ሐዋርያው ጴጥሮስ ለክርስቲያኖች ምን ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸዋል?
7 ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ወንድሞቹ ያላቸውን ስጦታና ችሎታ ተጠቅመው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዲያንጹ አበረታቷቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።” (1 ጴጥ. 4:10) ሌሎች በእኛ ምክንያት ይቀናሉ ወይም ተስፋ ይቆርጣሉ ብለን በመስጋት ስጦታችንን በተሟላ ሁኔታ ከመጠቀም ወደኋላ ማለት የለብንም። እንዲህ ካደረግን ለይሖዋ ምርጣችንን አልሰጠነውም ማለት ነው።
8. በ1 ቆሮንቶስ 4:6, 7 መሠረት በስጦታዎቻችን መኩራራት የሌለብን ለምንድን ነው?
8 ስጦታዎቻችንን በተሟላ ሁኔታ ልንጠቀምባቸው ይገባል፤ ሆኖም በስጦታዎቻችን መኩራራት የለብንም። (1 ቆሮንቶስ 4:6, 7ን አንብብ።) ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማስጀመር ረገድ ብዙ ጊዜ ይሳካልህ ይሆናል። በዚህ ስጦታ ከመጠቀም ወደኋላ ማለት የለብህም! ይሁንና በስጦታችን በመጠቀምና ስለ ስጦታችን ጉራ በመንዛት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። በቅርቡ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ችለሃል እንበል። ይህን ግሩም ተሞክሮ ለአገልግሎት ጓደኞችህ ለመናገር ጓጉተሃል። ይሁንና ከእነሱ ጋር ስትገናኝ አንዲት እህት መጽሔት ያበረከተችው እንዴት እንደሆነ ተሞክሮ እየተናገረች ነው። እሷ መጽሔት ማበርከት ነው የቻለችው፤ አንተ ግን ጥናት አስጀምረሃል። ታዲያ ምን ታደርጋለህ? ወንድሞች ተሞክሮህን ቢሰሙ እንደሚበረታቱ ታውቃለህ። ሆኖም እህት መጽሔት በማበርከቷ ያገኘችው ደስታ እንዳይቀንስ ተሞክሮህን ሌላ ጊዜ ለመናገር ልትወስን ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ ደግነት ይሆናል። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመርህን ማቆም የለብህም። ስጦታ አለህ፤ ተጠቀምበት!
9. ስጦታዎቻችንን እንዴት ልንጠቀምባቸው ይገባል?
9 በተፈጥሮ ያገኘናቸው ተሰጥኦዎች በሙሉ የአምላክ ስጦታዎች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርብናል። እነዚህን ስጦታዎች ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ጉባኤውን ለማነጽ ልንጠቀምባቸው ይገባል። (ፊልጵ. 2:3) ጉልበታችንን እና ችሎታችንን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ስንጠቀምበት እጅግ የምንደሰትበት ነገር እናገኛለን፤ የምንደሰተው ከሌሎች በልጠን ስለተገኘን ሳይሆን ስጦታችንን ተጠቅመን ለይሖዋ ውዳሴ ስላመጣን ነው።
10. ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደራችን ምክንያታዊ ያልሆነው ለምንድን ነው?
10 ካልተጠነቀቅን የእኛን ጠንካራ ጎን ከሌላ ሰው ደካማ ጎን ጋር ልናወዳድር እንችላለን። ለምሳሌ አንድ ወንድም ግሩም የሕዝብ ንግግር ይሰጥ ይሆናል። ይህ ጠንካራ ጎኑ ነው። ሆኖም ንግግር መስጠት የሚከብደውን ሌላ ወንድም ዝቅ አድርጎ ይመለከት ይሆናል። ይሁንና ያ ወንድም በእንግዳ ተቀባይነት፣ ልጆቹን በማሠልጠን ወይም በቅንዓት በማገልገል ረገድ የላቀ ችሎታ ይኖረው ይሆናል። ስጦታቸውን ይሖዋን ለማገልገልና ሌሎችን ለመርዳት የሚጠቀሙ ግሩም ችሎታ ያላቸው እጅግ ብዙ ወንድሞችና እህቶች ያሉን በመሆኑ በጣም አመስጋኞች ነን!
ከሌሎች ምሳሌ ተማር
11. የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
11 ራሳችንን ከሌሎች ጋር ማወዳደር ባይኖርብንም ከታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ምሳሌ ብዙ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ከሁሉ የተሻለው ምሳሌያችን ኢየሱስ ነው። እኛ እንደ እሱ ፍጹማን ባንሆንም ግሩም ከሆኑት ባሕርያቱ እና ካከናወናቸው ነገሮች ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (1 ጴጥ. 2:21) የእሱን ምሳሌ በጥብቅ ለመከተል አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ካደረግን ይሖዋን በተሻለ መንገድ ማገልገል እንችላለን፤ በአገልግሎታችንም ይበልጥ ውጤታማ እንሆናለን።
12-13. ከንጉሥ ዳዊት ምን እንማራለን?
12 ፍጹማን ባይሆኑም እንኳ ልንመስላቸው የሚገቡ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶችን ምሳሌ በአምላክ ቃል ውስጥ እናገኛለን። (ዕብ. 6:12) ንጉሥ ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይሖዋ ዳዊትን “እንደ ልቤ የሆነ” በማለት ጠርቶታል፤ ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ይህን ሐሳብ “በጣም የሚያስደስተኝ ሰው” በማለት ተርጉሞታል። (ሥራ 13:22) እርግጥ ዳዊት ፍጹም አልነበረም። እንዲያውም ከባባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል። ያም ቢሆን ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። ለምን? ምክንያቱም እርማት ሲሰጠው ሰበብ አስባብ አልደረደረም። ከዚህ ይልቅ የተሰጠውን ጠንከር ያለ ተግሣጽ ተቀብሏል፤ በፈጸመው ኃጢአትም ከልቡ ተጸጽቷል። በመሆኑም ይሖዋ ይቅር ብሎታል።—መዝ. 51:3, 4, 10-12
13 ከዳዊት ምሳሌ ትምህርት ለመውሰድ ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክር ሲሰጠኝ ምን ዓይነት ምላሽ እሰጣለሁ? ስህተቴን ቶሎ አምኜ እቀበላለሁ? ወይስ ሰበብ አስባብ እደረድራለሁ? ጥፋቴን በሌሎች ላይ አላክካለሁ? ስህተቴን ላለመድገም ከፍተኛ ጥረት አደርጋለሁ?’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ሌሎች ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስታነብም ተመሳሳይ ጥያቄዎችን መጠየቅ ትችላለህ። እነዚህ ሰዎች ከአንተ ጋር የሚመሳሰል ፈተና አጋጥሟቸዋል? የትኞቹን ግሩም ባሕርያት አንጸባርቀዋል? እያንዳንዱን ምሳሌ ስትመረምር ‘ይህን ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ መምሰል የምችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ።
14. የእምነት ባልንጀሮቻችንን ምሳሌ ማጤናችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?
14 በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ወጣቶችና አረጋውያንም መማር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመውን ፈተና በታማኝነት እየተቋቋመ ያለ ሰው በጉባኤህ ውስጥ አለ? ፈተናው የእኩዮች ተጽዕኖ፣ የቤተሰብ ተቃውሞ ወይም የጤና እክል ሊሆን ይችላል። ይህ ግለሰብ አንተም ማዳበር የምትፈልጋቸው ግሩም ባሕርያት አሉት? የእሱን ምሳሌ በማጤን ያጋጠመህን ፈተና በጽናት ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ ትምህርት ታገኝ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ግሩም የእምነት ምሳሌዎች በዙሪያችን በመኖራቸው በጣም አመስጋኞች ነን። እጅግ የምንደሰትበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው!—ዕብ. 13:7፤ ያዕ. 1:2, 3
በይሖዋ አገልግሎት ተደሰት
15. ሐዋርያው ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት መደሰታችንን እንድንቀጥል የሚረዳ ምን ምክር ሰጥቷል?
15 በጉባኤያችን ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን እያንዳንዳችን ምርጣችንን መስጠት ይኖርብናል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ክርስቲያኖች የተለያየ ስጦታና የተለያየ የአገልግሎት ምድብ ነበራቸው። (1 ቆሮ. 12:4, 7-11) ሆኖም ይህ ለፉክክርና ለክፍፍል ምክንያት አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ፣ እያንዳንዳቸው ‘የክርስቶስን አካል ለመገንባት’ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል” በማለት ጽፎላቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3, 11, 12, 16) ይህን ምክር በሥራ ላይ ያዋሉት ክርስቲያኖች ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን አድርገዋል፤ በዛሬው ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ሰፍኖ እናያለን።
16. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል? (ዕብራውያን 6:10)
16 ራስህን ከሌሎች ጋር ላለማወዳደር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከዚህ ይልቅ ከኢየሱስ ተማር፤ እንዲሁም ባሕርያቱን ለመኮረጅ ጥረት አድርግ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱም ሆነ በዘመናችን ካሉ የእምነት ምሳሌዎች ተማር። ለይሖዋ ምርጥህን ስትሰጠው እሱ ‘ሥራህን በመርሳት ፍትሕ እንደማያዛባ’ እርግጠኛ ሁን። (ዕብራውያን 6:10ን አንብብ።) ይሖዋ እሱን ለማስደሰት በሙሉ ነፍስህ የምታደርገውን ጥረት እንደሚያደንቅ በማስታወስ በእሱ አገልግሎት መደሰትህን ቀጥል።
መዝሙር 65 ወደፊት ግፋ!
a ሁላችንም የሌሎችን ምሳሌ በመመልከት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ሆኖም ራሳችንን ከሌሎች ጋር እንዳናወዳድር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ይህ ርዕስ፣ ራሳችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ከመኩራት ወይም ተስፋ ከመቁረጥ መቆጠብ እንዲሁም ደስታችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ያብራራል።
b የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም ወጣት እያለ በቤቴል ያገለግል ነበር። ትዳር ከመሠረተ በኋላ ደግሞ ከባለቤቱ ጋር በአቅኚነት ማገልገል ጀመረ። ልጆች ከወለደ በኋላ እነሱን ለአገልግሎት አሠልጥኗቸዋል። ወንድም አሁን ዕድሜው ቢገፋም በደብዳቤ በመመሥከር ምርጡን መስጠቱን ቀጥሏል።