የጥናት ርዕስ 34
ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ተማሩ
“ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው . . . ይረዱታል።”—ዳን. 12:10
መዝሙር 98 ቅዱሳን መጻሕፍት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ናቸው
ማስተዋወቂያa
1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናት አስደሳች እንዲሆንልን ምን ይረዳናል?
ቤን የተባለ ወጣት ወንድም “የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናት እወዳለሁ” ብሏል። አንተስ በእሱ ሐሳብ ትስማማለህ? ወይስ ትንቢቶችን መረዳት ከባድ እንደሆነ ይሰማሃል? ምናልባትም ትንቢቶችን ማጥናት አሰልቺ እንደሚሆን ይሰማህ ይሆናል። ሆኖም ይሖዋ ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲካተቱ ያደረገው ለምን እንደሆነ በደንብ ሲገባህ አመለካከትህን ትቀይር ይሆናል።
2. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?
2 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መመርመር ያለብን ለምን እንደሆነ ብቻ ሳይሆን ትንቢቶችን ማጥናት የምንችለው እንዴት እንደሆነም እንመለከታለን። ከዚያም በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ትንቢቶችን በመመርመር ትንቢቶቹን መረዳታችን በዛሬው ጊዜ የሚጠቅመን እንዴት እንደሆነ እናያለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናት ያለብን ለምንድን ነው?
3. የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
3 የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጨርሶ የማታውቀውን ቦታ ለመጎብኘት አስበሃል እንበል። ሆኖም አብሮህ የሚጓዘው ጓደኛህ አካባቢውን በደንብ ያውቀዋል። የት እንዳላችሁ እንዲሁም እያንዳንዱ መንገድ ወዴት እንደሚያመራ ጠንቅቆ ያውቃል። ጓደኛህ አብሮህ ለመምጣት በመስማማቱ በጣም እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም ይሖዋ በጊዜ ሰሌዳ ላይ የቱ ጋ እንዳለን እንዲሁም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ያውቃል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን ይሖዋ እንዲረዳን በትሕትና ልንጠይቀው ይገባል።—ዳን. 2:28፤ 2 ጴጥ. 1:19, 20
4. ይሖዋ ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያደረገው ለምንድን ነው? (ኤርምያስ 29:11) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
4 እንደ ማንኛውም ጥሩ ወላጅ፣ ይሖዋ ልጆቹ ወደፊት ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኤርምያስ 29:11ን አንብብ።) ሆኖም ከሰብዓዊ ወላጆች በተለየ መልኩ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ትንቢት መናገር ይችላል። ወሳኝ የሆኑ ክንውኖች ከመከሰታቸው በፊት እንድናውቅ ሲል ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል። (ኢሳ. 46:10) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች የሰማዩ አባታችን በፍቅር ተነሳስቶ የሰጠን ውድ ስጦታዎች ናቸው። ይሁንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በእርግጥ እንደሚፈጸሙ መተማመን የምትችለው እንዴት ነው?
5. ወጣቶች ከማክስ ተሞክሮ ምን ትምህርት ያገኛሉ?
5 ልጆቻችን በትምህርት ቤት ለመጽሐፍ ቅዱስ ምንም አክብሮት ከሌላቸው ልጆች ጋር አብረው ይውላሉ። እነዚህ ልጆች የሚናገሩትና የሚያደርጉት ነገር በወጣት የይሖዋ ምሥክሮች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ ሊፈጥር ይችላል። ማክስ የተባለ ወንድም ያጋጠመውን እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ ወላጆቼ እውነተኛውን ሃይማኖት ያስተማሩኝ መሆኑን እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን መጠራጠር ጀመርኩ።” ታዲያ ወላጆቹ ምን አደረጉ? ማክስ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታው እንዳስጨነቃቸው ምንም ጥያቄ የለውም፤ ሆኖም በተረጋጋ መንፈስ አነጋገሩኝ።” የማክስ ወላጆች ጥያቄዎቹን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ መለሱለት። ማክስም እርምጃ ወስዷል። እንዲህ ብሏል፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በራሴ ማጥናት ጀመርኩ፤ እንዲሁም የተማርኳቸውን ነገሮች ከሌሎች የይሖዋ ምሥክር ወጣቶች ጋር እነጋገር ነበር።” ይህስ ምን ውጤት አስገኘ? ማክስ “ከዚያ በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንደተጻፈ እርግጠኛ ሆንኩ” ብሏል።
6. ጥርጣሬ ካደረብህ ምን ልታደርግ ይገባል? ለምንስ?
6 አንተም እንደ ማክስ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን መጠራጠር ብትጀምር የጥፋተኝነት ስሜት ሊሰማህ አይገባም። ሆኖም እርምጃ መውሰድ አለብህ። ጥርጣሬ እንደ ዝገት ነው። ዝም ተብሎ ከተተወ፣ ውድ ዋጋ ያለውን ነገር ቀስ በቀስ ሊያበላሽ ይችላል። አንተም ከእምነትህ ላይ ማንኛውንም “ዝገት” ለማስወገድ ከፈለግክ ራስህን እንዲህ ብለህ ልትጠይቅ ይገባል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሚናገረው ነገር እውነት እንደሆነ አምናለሁ?” እርግጠኛ ካልሆንክ ፍጻሜያቸውን ያገኙ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መመርመር ይኖርብሃል። ሆኖም ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናት የምንችለው እንዴት ነው?
7. ትንቢቶችን ማጥናት ከምንችልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ዳንኤል ምን ምሳሌ ትቷል? (ዳንኤል 12:10) (ሥዕሉንም ተመልከት።)
7 ትንቢቶችን ማጥናት ከምንችልበት መንገድ ጋር በተያያዘ ዳንኤል ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ትንቢቶችን ያጠናው በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ ተነሳስቶ ማለትም እውነትን ለማወቅ ነበር። በተጨማሪም ዳንኤል ትሑት ነበር፤ ይሖዋ እሱን ለሚያውቁና ንጹሕ በሆኑት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቹ ለሚመሩ ሰዎች ማስተዋልን እንደሚሰጣቸው ተገንዝቧል። (ዳን. 2:27, 28፤ ዳንኤል 12:10ን አንብብ።) ዳንኤል የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ ትሑት መሆኑን አሳይቷል። (ዳን. 2:18) ከዚህም ሌላ ዳንኤል ትንቢቶችን ያጠናው በጥልቀት ነው። በወቅቱ የነበሩትን በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ቅዱሳን መጻሕፍት በጥንቃቄ መርምሯል። (ኤር. 25:11, 12፤ ዳን. 9:2) ታዲያ የዳንኤልን ምሳሌ መከተል የምትችለው እንዴት ነው?
8. አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች እንደሚፈጸሙ ማመን የማይፈልጉት ለምንድን ነው? እኛ ግን ምን ልናደርግ ይገባል?
8 የልብ ዝንባሌህን መርምር። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለማጥናት የሚያነሳሳህ እውነትን ለማወቅ ያለህ ጠንካራ ፍላጎት ነው? ከሆነ ይሖዋ ይረዳሃል። (ዮሐ. 4:23, 24፤ 14:16, 17) ይሁንና አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለማጥናት የሚያነሳሳቸው ሌላ ምክንያት ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ በአምላክ መንፈስ መሪነት እንዳልተጻፈ የሚያሳይ ማስረጃ ለማግኘት ሲሉ ትንቢቶችን ይመረምሩ ይሆናል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ካልሆነ ትክክልና ስህተት ስለሆነው ነገር የራሳቸውን መሥፈርት ማውጣትና በዚያ መመራት እንደሚችሉ ይሰማቸዋል። እኛ ግን በትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ተነሳስተን ትንቢቶችን መመርመር ይኖርብናል። ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለመረዳት አንድ ወሳኝ ባሕርይ ያስፈልጋል።
9. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለመረዳት የትኛው ባሕርይ ያስፈልጋል? አብራራ።
9 ትሑት ሁን። ይሖዋ ትሑታንን እንደሚረዳ ቃል ገብቷል። (ያዕ. 4:6) በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ለመረዳት እሱ እንዲረዳን መጸለይ ይኖርብናል። በተጨማሪም ይሖዋ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ የሚጠቀምበት መስመር የሆነው የታማኝና ልባም ባሪያ እርዳታ እንደሚያስፈልገን አምነን መቀበል ይኖርብናል። (ሉቃስ 12:42) ይሖዋ የሥርዓት አምላክ ነው። በመሆኑም በቃሉ ውስጥ የሚገኙ እውነቶችን ለመረዳት እንዲያግዘን አንድ መስመር ብቻ ይጠቀማል ብሎ ማሰቡ ምክንያታዊ ነው።—1 ቆሮ. 14:33፤ ኤፌ. 4:4-6
10. ከኤስተር ተሞክሮ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
10 በጥልቀት አጥና። በመጀመሪያ ትኩረትህን የሚስብ አንድ ትንቢት ምረጥና ምርምር አድርግበት። ኤስተር የተባለች እህት ያደረገችው ይህንኑ ነው። ስለ መሲሑ መምጣት የሚናገሩ ትንቢቶችን መመርመር ፈልጋ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “15 ዓመት ሲሆነኝ እነዚህ ትንቢቶች ኢየሱስ ከመወለዱ በፊት የተነገሩ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ማስረጃ መፈለግ ጀመርኩ።” ኤስተር ስለ ሙት ባሕር ጥቅልሎች ያነበበችው ነገር አሳመናት። እንዲህ ብላለች፦ “አንዳንዶቹ የተጻፉት ከክርስቶስ ዘመን በፊት ነው፤ በመሆኑም ትንቢቶቹ ከአምላክ የመነጩ መሆን አለባቸው።” አክላም “እርግጥ ትንቢቶቹን ለመረዳት በተደጋጋሚ ማንበብ ነበረብኝ” በማለት ሳትሸሽግ ተናግራለች። ያም ቢሆን ጥረት በማድረጓ ደስተኛ ነች። የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን በጥልቀት ከመረመረች በኋላ “መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን ለራሴ አረጋገጥኩ” ብላለች።
11. መጽሐፍ ቅዱስ እውነት መሆኑን ለራሳችን ማረጋገጣችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?
11 በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ አንዳንድ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት እንዴት እንደሆነ ስንመለከት በይሖዋና በሚሰጠን አመራር ላይ የማይናወጥ እምነት እናዳብራለን። በተጨማሪም በአሁኑ ጊዜ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን ይረዱናል። በዛሬው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እያገኙ ያሉ ሁለት የዳንኤል ትንቢቶችን እስቲ በአጭሩ እንመልከት። ትንቢቶቹን መመርመራችን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ሊረዳን ይችላል።
ከብረትና ከሸክላ ስለተሠሩት እግሮች ከሚናገረው ትንቢት ምን ትምህርት እናገኛለን?
12. ‘ከብረትና ከሸክላ ጭቃ’ የተሠሩት እግሮች ምን ያመለክታሉ? (ዳንኤል 2:41-43)
12 ዳንኤል 2:41-43ን አንብብ። ዳንኤል ለንጉሥ ናቡከደነጾር በተረጎመለት ሕልም ላይ ንጉሡ የተመለከተው ምስል እግሮች የተሠሩት ‘ከብረትና ከሸክላ ጭቃ’ ነበር። ይህን ትንቢት በዳንኤልና በራእይ መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር ስናወዳድር እግሮቹ የሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ የዓለም ኃያል መንግሥት የሆነውን የአንግሎ አሜሪካ ጥምረት ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን። ዳንኤል ይህን የዓለም ኃያል መንግሥት አስመልክቶ ሲናገር “በከፊል ብርቱ፣ በከፊል ደግሞ ደካማ ይሆናል” ብሏል። ይህ መንግሥት በከፊል ደካማ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በሸክላ ጭቃ የተወከለው ተራው ሕዝብ ይህ መንግሥት እንደ ብረት ባለ ጥንካሬ እርምጃ እንዳይወስድ አቅሙን ያዳክመዋል።b
13. ይህን ትንቢት ስንረዳ የትኞቹን ወሳኝ እውነቶች እንማራለን?
13 ዳንኤል ስለ ምስሉ በተለይም ስለ እግሮቹ ከሰጠው መግለጫ በርካታ ወሳኝ እውነቶችን እንማራለን። አንደኛ፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት በአንዳንድ መንገዶች ጥንካሬውን አሳይቷል። ለምሳሌ አንደኛውንና ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት ካሸነፉት አገሮች መካከል አሜሪካና ብሪታንያ ይገኙበታል። ሆኖም ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት በዜጎቹ መካከል ባሉ ግጭቶች የተነሳ ተዳክሟል፤ እንዲሁም መዳከሙን ይቀጥላል። ሁለተኛ፣ የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ ከማጥፋቱ በፊት የሚኖረው የመጨረሻ የዓለም ኃያል መንግሥት ይህ ጥምር መንግሥት ነው። አንዳንድ ብሔራት አልፎ አልፎ የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ቢገዳደሩትም እንኳ እሱን ተክተው የዓለም ኃያል መንግሥት አይሆኑም። እንዲህ የምንለው፣ የአምላክን መንግሥት የሚያመለክተው ድንጋይ የምስሉን እግሮች ማለትም የአንግሎ አሜሪካን ጥምር መንግሥት እንደሚያደቅ ትንቢቱ ስለሚገልጽ ነው።—ዳን. 2:34, 35, 44, 45
14. ከብረትና ከሸክላ ስለተሠሩት እግሮች የሚገልጸውን ትንቢት መረዳታችን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳን እንዴት ነው?
14 ከብረትና ከሸክላ ስለተሠሩት እግሮች የሚናገረው የዳንኤል ትንቢት እንደተፈጸመ ታምናለህ? ከሆነ እምነትህ በአኗኗርህ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ አይቀርም። በቅርቡ በሚጠፋ ዓለም ውስጥ ቁሳዊ ሀብት ለማካበት ጥረት አታደርግም። (ሉቃስ 12:16-21፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) ይህን ትንቢት መረዳትህ የስብከቱና ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ያለውን አስፈላጊነት ለመገንዘብም ይረዳሃል። (ማቴ. 6:33፤ 28:18-20) ይህን ትንቢት ካጠናህ በኋላ ራስህን እንዲህ ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማደርጋቸው ውሳኔዎች የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ እንደሚያጠፋ እርግጠኛ እንደሆንኩ ያሳያሉ?’
ስለ ‘ሰሜኑ ንጉሥና’ ስለ “ደቡቡ ንጉሥ” ከሚናገረው ትንቢት ምን እንማራለን?
15. በዛሬው ጊዜ ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” እነማን ናቸው? (ዳንኤል 11:40)
15 ዳንኤል 11:40ን አንብብ። ዳንኤል ምዕራፍ 11 ዓለምን ለመቆጣጠር ስለሚታገሉ ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት ወይም የፖለቲካ ኃይሎች ይናገራል። ይህን ትንቢት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር በማወዳደር ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ ሩሲያንና አጋሮቿን፣ “የደቡቡ ንጉሥ” ደግሞ የአንግሎ አሜሪካን የዓለም ኃያል መንግሥት ያመለክታል የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ እንችላለን።c
16. ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ ክርስቲያኖች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል?
16 ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች በዚህ ንጉሥ ስደት እየደረሰባቸው ነው። አንዳንድ የይሖዋ ምሥክሮች በእምነታቸው ምክንያት ተደብድበዋል እንዲሁም ወህኒ ወርደዋል። ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ የሚያደርገው ነገር ወንድሞቻችንን ከማሸበር ይልቅ እምነታቸውን ያሳድግላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ወንድሞቻችን በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚደርሰው ስደት ዳንኤል የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ ይገነዘባሉ።d (ዳን. 11:41) እኛም ይህን ማወቃችን ብሩህ ተስፋ እንዲኖረንና ንጹሕ አቋማችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል።
17. ‘በደቡቡ ንጉሥ’ አገዛዝ ሥር የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል?
17 ቀደም ሲል ‘የደቡቡ ንጉሥም’ በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝሯል። ለምሳሌ በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በርካታ ወንድሞቻችን በክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋማቸው ምክንያት ታስረዋል፤ እንዲሁም አንዳንድ የይሖዋ ምሥክር ልጆች በዚሁ ምክንያት ከትምህርት ቤት ተባረዋል። ካለፉት አሥርተ ዓመታት ወዲህ ግን በዚህ ንጉሥ አገዛዝ ሥር ያሉ የይሖዋ አገልጋዮች ለአምላክ መንግሥት ያላቸው ታማኝነት ስውር በሆኑ መንገዶች እየተፈተነ ነው። ለምሳሌ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት አንድ ክርስቲያን አንድን የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የምርጫ ተወዳዳሪ ለመደገፍ ሊፈተን ይችላል። እርግጥ ነው፣ በምርጫው ላይ ድምፅ አይሰጥ ይሆናል፤ ሆኖም በአእምሮውና በልቡ ወገን ሊይዝ ይችላል። በድርጊታችን ብቻ ሳይሆን በአስተሳሰባችንና በስሜታችንም ጭምር በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ መሆናችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!—ዮሐ. 15:18, 19፤ 18:36
18. ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ እና ‘በደቡቡ ንጉሥ’ መካከል ያለውን ግጭት ስንመለከት ምን ሊሰማን ይገባል? (ሥዕሉንም ተመልከት።)
18 በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ እምነት የሌላቸው ሰዎች ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ እና ‘በደቡቡ ንጉሥ’ መካከል ያለውን ‘ግፊያ’ ሲመለከቱ በጣም ሊጨነቁ ይችላሉ። (ዳን. 11:40) ሁለቱም ነገሥታት በምድር ላይ ያለውን ሕይወት በሙሉ ማጥፋት የሚችል የኑክሌር ክምችት አላቸው። ሆኖም ይሖዋ ይህ እንዲሆን እንደማይፈቅድ እናውቃለን። (ኢሳ. 45:18) በመሆኑም ‘በሰሜኑ ንጉሥ’ እና ‘በደቡቡ ንጉሥ’ መካከል ያለው ጠብ አያሳስበንም፤ እንዲያውም እምነታችንን ያጠናክረዋል። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ እንደቀረበ ያረጋግጥልናል።
ለትንቢቶች ትኩረት መስጠታችሁን ቀጥሉ
19. ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ጋር በተያያዘ ምን ልንገነዘብ ይገባል?
19 አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙት እንዴት እንደሆነ አናውቅም። ነቢዩ ዳንኤል እንኳ ከጻፋቸው ነገሮች መካከል ሙሉ በሙሉ ያልተረዳቸው ነበሩ። (ዳን. 12:8, 9) ያም ቢሆን አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የሚፈጸመው እንዴት እንደሆነ አልተረዳንም ማለት ትንቢቱ አይፈጸምም ማለት አይደለም። ይሖዋ ቀደም ሲል እንዳደረገው ማወቅ ያለብንን ነገር በትክክለኛው ጊዜ ላይ እንደሚገልጥልን ልንተማመን እንችላለን።—አሞጽ 3:7
20. በቅርቡ የትኞቹ አስደናቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እንመለከታለን? ምን ማድረጋችንን መቀጠልስ ይኖርብናል?
20 “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” የሚል አዋጅ ይታወጃል። (1 ተሰ. 5:3) ከዚያም የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች በሐሰት ሃይማኖቶች ላይ ይነሱና ሙሉ በሙሉ ያጠፏቸዋል። (ራእይ 17:16, 17) ቀጥሎም በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ። (ሕዝ. 38:18, 19) ከዚያም የአርማጌዶን ጦርነት ይነሳል። (ራእይ 16:14, 16) እነዚህ ክንውኖች በቅርቡ እንደሚፈጸሙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እስከዚያው ግን ለመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ትኩረት በመስጠትና ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ በመርዳት በሰማይ ለሚኖረው አፍቃሪ አባታችን ያለንን አድናቆት ማሳየታችንን እንቀጥል።
መዝሙር 95 ብርሃኑ እየደመቀ ነው
a በዓለም ላይ ያለው ሁኔታ እየተባባሰ ቢሄድም እንኳ የወደፊቱ ሕይወታችን አስደሳች እንደሚሆን መተማመን እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ማጥናታችን ስለዚህ ጉዳይ እርግጠኞች እንድንሆን ይረዳናል። ይህ ርዕስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን መመርመር ያለብን ለምን እንደሆነ በዝርዝር ያብራራል። በተጨማሪም ዳንኤል የጻፋቸውን ሁለት ትንቢቶች በአጭሩ እንመለከታለን፤ እንዲሁም እነዚህን ትንቢቶች መመርመራችን በግለሰብ ደረጃ ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት እንደሆነ እናያለን።